No summary available.
ጥር 29 ቀን 2006 ዓ.ም.
ዳኞች- አልማው ወል ዓላ መሐመድ ረታ ቶለሳ አዳነ ንጉሴ ሙስጠፋ አህመድ አመልካች፡- ቻይና ሀይ ዌይ ግሩፕ ላሚትድ- የቀረበ የለም ተጠሪ፡- አቶ ውብሸት እንግዳው - የቀረበ የለም መዝገቡ ተመርምሮ የሚከተለው ፍርድ ተሰጥቶአል።
ጉዳዩ የአሰሪና ሰራተኛ ክርክርን የሚመለከት ሲሆን የተጀመረውም ከሳሽ የነበሩት የአሁኑ ተጠሪ ተከሳሽ በነበረው የአሁኑ አመልካች ላይ በፍ/የመ/ደ/ፍ/ቤት ባቀረቡት ክስ ነው።የክሱም ይዘት ባጭሩ ከሳሽ በተከሳሽ ድርጅት ውስጥ ከ30/08/2002 ዓ.ም.ጀምሮ እስከ 15/02/2005 ዓ.ም.
ድረስ በወር የተጣራ ደመወዝ ብር 25,000 እያገኙ ሲሰሩ ቆይተው የስራ ውላቸው ሲቋረጥ ደመወዝ እና የስራ ስንብት ክፍያ የተፈጸመላቸው ቢሆንም የዓመት ዕረፍት፣የሳምንት ዕረፍት እና የሕዝብ በዓላት ክፍያ ያልተፈጸመላቸው በመሆኑ ይኸው ክፍያ ታስቦ እንዲከፈላቸው ይወሰን ዘንድ ዳኝነት የተጠየቀበት ሲሆን ተከሳሽ ድርጅት በበኩሉ ባቀረበው የመቃወሚያና የፍሬነገር መልስ ክሱ በይርጋ የታገደ መሆኑን፣ከሳሽ የስራ ውላቸውን በፈቃዳቸው ባቋረጡበት ጊዜ የሚገባቸውን ክፍያ በሙሉ ተሳስበው የተቀበሉ መሆኑን፣አሁን ጥያቄ ያቀረበባቸውን ክፍያዎች በወቅቱ መጠየቅ የሚችሉ ሆኖ እያለ ክፍያዎችን በመከፋፈል አሁን ያቀረቡት ጥያቄ በፍ/ብ/ሥ/ሥ/ሕ/ቁ.216 መሰረት ተቀባይነት የልለው መሆኑን፣የዓመት ዕረፍታቸውን የተጠቀሙ መሆኑን፣የሳምንት ዕረፍት እና የሕዝብ በዓላት ክፍያ የየትኛው ዓመት እንደሆነና እና በማን ትዕዛዝ እንደሰሩ በክሳቸው ለይተው ያልገለጹ መሆኑን፣በሳምንት ዕረፍት እና በሕዝብ በዓላት ጊዜ ስራ የሚሰራ ከሆነ ክፍያ የሚፈጸመው ከየወሩ ደመወዝ ጋር ተጨምሮ በዚያው በተሰራበት ወር በመሆኑ ያልተከፈላቸው ክፍያ የልለ መሆኑን፣ከሳሽ ቀደም ሲል ከተፈጸመላቸው ውጪ ከአሰሪው የሚጠይቁት ልላ ክፍያ አለመኖሩን በማረጋገጥ ስምምነት ከፈረሙ በኋላ አሁን ያቀረቡት የተጨማሪ ክፍያ ጥያቄ ተቀባይነት ላኖረው የማይገባ መሆኑን በዝርዝር በመግለጽ ክሱ ውድቅ እንዲደረግ ተከራክሯል።
ፍ/ቤቱም የዳኝነት ጥያቄ ከቀረበበት ክፍያ ውስጥ በይርጋ ቀሪ የሚደረገውን መጠን በመለየት፣በቀሪው መጠን ላይ በተከሳሽ የቀረበውን የይርጋ መቃወሚያ ባለመቀበል እና ሰራተኛው መብቱን ለመተው የሚያደርገው ስምምነት በአዋጅ ቁጥር 377/1996 በአንቀጽ 25(1) መሰረት ሕጋዊ ውጤት የልለው መሆኑን ገልጾ በዚህ ረገድ ከተከሳሽ የቀረበውን መቃወሚያ ውድቅ በማድረግ የግራ ቀኙን ምስክሮች ከሰማ በኋላ ስራው የመንገድ ስራ በመሆኑ ቻይናውያን የፕሮጀክቱ ኃላፊዎች በሚሰጡት የቃል ትዕዛዝ መሰረት ስራው ከሳምንት እስከ ሳምንት ይሰራ የነበረ መሆኑ እና የዓመት ዕረፍትም የሚጠየቀው በጽሁፍ መሆኑ በከሳሽ ምስክሮች መረጋገጡን እና በአንፃሩ ከሳሽ በትርፍ ሰዓት እና በበዓላት ቀናት ስላለመስራታቸው ወይም ለስራው ክፍያ የተፈጸመላቸው ስለመሆኑ እንዲሁም ከሳሽ የዓመት ዕረፍት የወሰዱ ስለመሆኑ የተከሳሽ ምስክሮች ማስረዳት እንዳልቻሉ ገልጾ የ13 ቀናት የሳምንት ዕረፍት እና የትርፍ ሰዓት ክፍያ ብር 21,663 እና የ29 ቀናት የዓመት ዕረፍት ክፍያ ብር 24,167 በድምሩ ብር 45,830 ከ10% የጠበቃ አበል ጋር ተከሳሽ ድርጅት ለከሳሽ እንዲከፍል ውሳኔ የሰጠ ሲሆን አመልካች አቤቱታውን ለዚህ ችሎት ያቀረበው ይ/ሰሚው ፍ/ቤት ይግባኙን ሳይቀበለው በመቅረቱ ነው።
የሰበር አቤቱታው ተመርምሮ በዚህ ጉዳይ ተጠሪው ከአመልካች የሚጠይቀው ቀሪ ክፍያ አለመኖሩን ተስማምቶ የፈረመ መሆኑ ተረጋግጦ እያለ በዚህ ረገድ የአመልካች መቃወሚያ ውድቅ ተደርጎ ለተጠሪው ተጨማሪ ክፍያ እንዲከፈለው የመወሰኑን አግባብነት ተጠሪው ባሉበት ለማጣራት ይቻል ዘንድ ጉዳዩ ለሰበር ክርክር እንዲቀርብ በመደረጉ ግራ ቀኙ የጽሁፍ ክርክር ተለዋውጠዋል።የጉዳዩ አመጣጥና የክርክሩ ይዘት ከላይ የተመለከተው ሲሆን እኛም አቤቱታ የቀረበበት ውሳኔ መሰረታዊ የህግ ስህተት የተፈጸመበት መሆን አለመሆኑን መርምረናል።
በዚህም መሰረት አመልካቹ የፈረሙት ስምምነት ስራቸውን በለቀቁበት ጊዜ ቀሪ የደመወዝ ክፍያ፣ የስራ ስንብት እና የካሳ ክፍያ በድምሩ ብር 60,000 የተከፈላቸው መሆኑ እና ከዚህ በኋላ በአሰሪው ላይ የሚያቀርቡት ልላ የይገባኛል ጥያቄ አለመኖሩ የተገለጸበት ነው።የፍ/የመ/ደ/ፍ/ቤት አመልካች በዚህ ረገድ ያቀረበውን መቃወሚያ ሳይቀበል የቀረው ተዋዋይ ወገኖች የስራ ውላቸውን በስምምነት ማቋረጥ እንደሚችሉ እና ሆኖም ግን ሰራተኛው በሕግ የተሰጠውን መብቱን ለመተው የሚያደርገው ስምምነት የህግ ውጤት እንደማይኖረው በአዋጅ ቁጥር 377/1996 በአንቀጽ 25(1) ስር የተመለከተውን ድንጋጌ በመጥቀስ ነው።የትርፍ ሰዓት፣የበዓላት ቀናት እና የዓመት ዕረፍት ክፍያ ደግሞ ለሰራተኛው በሕግ የተጠበቁ መብቶች ስለመሆናቸው በአዋጅ ቁጥር 377/1996 በአንቀጽ 68(1)፣75(1) እና 77(5) ድንጋጌዎች ላይ ተመልክቶአል።በመሰረቱ ተጠሪው የፈረሙት ስምምነት ቀሪ የደመወዝ ክፍያ፣ የስራ ስንብት እና የካሳ ክፍያ በድምሩ ብር 60,000 የተከፈላቸው መሆኑን የሚገልጽ ከመሆኑ ውጪ የትርፍ ሰዓት፣የሕዝብ በዓላት እና የዓመት ዕረፍት ክፍያዎችን ጨምሮ ከአሰሪው የሚገባቸውን ክፍያዎች በሙሉ የተቀበሉ ስለመሆኑ ወይም እነዚህን ክፍያዎች ለመጠየቅ የሚያስችልየስራ ሁኔታ ያልነበረ ስለመሆኑ የተገለፀበት አይደለም።በመሆኑም በዚህ ረገድ ከአመልካች የቀረበው መቃወሚያ ውድቅ መደረጉ ላነቀፍ የሚችልበት ሕጋዊ ምክንያት አልተገኘም።
በልላ በኩል ግን ለተጠሪው የተወሰነው የዓመት ዕረፍት ክፍያ መጠን የግራ ቀኙን ክርክር እና የአዋጅ ቁጥር 377/1996 በአንቀጽ 77(1) የተመለከተውን ድንጋጌ መሰረት ያደረገ መሆን አለመሆኑ መመርመር የሚገባው ሆኖ ተገኝቷል።በዚህም መሰረት ተጠሪ በስራው ላይ የቆዩት ከ30/08/2002 ዓ.ም.ጀምሮ እስከ 15/02/2005 ዓ.ም. ድረስ መሆኑን በክስ ማመልከቻቸው ላይ የገለጹ ሲሆን ይህ ጊዜም 2 ዓመት ከ 6 ወር ከ15 ቀን ነው።በመሰረቱ ከሰራተኛ የሚሰጠው የዓመት ዕረፍት ለመጀመሪያው የአንድ ዓመት አገልግሎት 14 ቀን መሆኑ እና ከአንድ ዓመት በላይ ለሆነ አገልግሎት በ14 ቀን ላይ ለእያንዳንዱ ተጨማሪ የአገልግሎት ዓመት 1 የስራ ቀን እየታከለ ስለመሆኑ በአዋጁ አንቀጽ 77(1) (ሀ) እና(ለ) ስር ተመልክቷል።አመልካች በዚህ ረገድ በግልጽ ላቀረበው ክርክር ተጠሪ በሰበር መልሳቸው ላይ በዝምታ ከማለፍ በስተቀር የሰጡት ማስተባበያ የለም።በመሆኑም ለተጠሪ ላከፈል የሚገባው የዓመት ዕረፍት ክፍያ የ15 ቀን ተኩል ሆኖ እያለ በ29 ቀን ታስቦ እንዲከፈል መደረጉ ከግራ ቀኙ ክርክር እና በሕጉ ከተመለከተው ውጪ ሆኖ በመገኘቱ በዚህ መጠን ማስተካከያ ላደረግበት የሚገባ ሆኖ ተገኝቷል።
ሲጠቃለል አቤቱታ የቀረበበት የስር ፍ/ቤቶች ውሳኔ በከፊል መሰረታዊ የህግ ስህተት የተፈጸመበት ሆኖ በመገኘቱ የሚከተለው ውሳኔ ተሰጥቶአል።
የፍ/የመ/ደ/ፍ/ቤት በመ.ቁ. 82043 በ11/10/2003 ዓ.ም. የሰጠው እና በፍ/ከ/ፍ/ቤት በመ.ቁ.135827 በ18/11/2005ዓ.ም. በትዕዛዝ የፀናው ውሳኔ በፍ/ብ/ሥ/ሥ//ሕ/ቁ.348(1) መሰረት ተሻሽሐል።
ከላይ በተ.ቁ. 1 ከተጠቀሰው ውሳኔ ውስጥ ሰራተኛው መብቱን ለመተው የሚያደርገው ስምምነት በአዋጅ ቁጥር 377/1996 በአንቀጽ 25(1) መሰረት ሕጋዊ ውጤት የልለው መሆኑን በመግለጽና በዚህ ረገድ ከአመልካች የቀረበውን መቃወሚያ ውድቅ በማድረግ የሳምንት ዕረፍት፣የሕዝብ በዓላት እና የዓመት ዕረፍት ክፍያ ለተጠሪ እንዲከፈል የተሰጠው የውሳኔ ክፍል በፍ/ስ/ሥሥ/ሕ.ቁ.348(1) መሰረት ፀንቷል።
ከላይ በተ.ቁ. 1 ከተጠቀሰው ውሳኔ ውስጥ ለተጠሪው የሚከፈለው የዓመት ዕረፍት ክፍያ መጠን የ29 ቀን ነው በሚል የተሰጠው የውሳኔ ክፍል በፍ/ብ/ሥ/ሥ/ሕ.ቁ.348(1) መሰረት ተሽሯል።
ለተጠሪው ላከፈል የሚገባው የዓመት ዕረፍት ክፍያ የ15 ቀን ተኩል ነው በማለት ወስነናል።
ለተጠሪው ላከፈል የሚገባው የሳምንት ዕረፍት፣የትርፍ ሰዓት እና የዓመት ዕረፍት ክፍያ በድምሩ ብር 34,579.68(ሰላሳ አራት ሺህ አምስት መቶ ሰባ ዘጠኝ ከስድሳ ስምንት ሳንቲም) ከ10% የጠበቃ አበል ጋር ነው በማለት ወስነናል።
በፍ/የመ/ደ/ፍ/ቤት በመ.ቁ.84794 የተጀመረው አፈጻጸም ታግዶ እንዲቆይ በዚህ መዝገብ በ29/11/2005 ዓ.ም. ተሰጥቶ የነበረው የአፈጻጸም ዕግድ ተነስቷል።
የውሳኔው ግልባጭ ለስር ፍ/ቤቶች ይላክ።
የሰበር ክርክሩ ያስከተለውን ወጪና ኪሳራ ግራ ቀኙ የየራሳቸውን ይቻሉ።
ውሳኔ ያገኘ ስለሆነ መዝገቡ ተዘግቷል።
No topics extracted.