No summary available.
ጥር 27 ቀን 2ዐዐ6 ዓ.ም.
ዳኞች፡- አልማው ወል ዓላ መሐመድ ረታ ቶሎሣ አዳነ ንጉሴ ሙስጠፋ አህመድ አመልካች፡- የአቶ ፍፁም አስታጥቄ ወኪል አቶ ታምራት አስታጥቄ ቀረቡ ተጠሪ፡- የተቀናጀ የቤተሰብ አገልግሎት ድርጅት የቀረበ የለም።
**
መዝገቡ ተመርምሮ ተከታዩ ፍርድ ተሰጥቷል።
**
ጉዳዩ የአሰሪና ሰራተኛ ክርክርን የሚመለከት ሲሆን ክርክሩም የተጀመረው የአሁኑ አመልካች በፍድራሉ መጀመሪያ ደረጃ ፍ/ቤት ስራ ክርክር ችሎት በአሁኑ ተጠሪ ላይ በመሰረተው ክስ መነሻነት ነው። በአመልካች የቀረበው የክሱ ፍሬ ነገርም ባጭሩ፡- ከሣሽ በተከሳሽ ድርጅት ውስጥ በኘሮጄክት አስተባባሪነት የስራ መደብ ላይ በ1/3/2001 ዓ.ም ተቀጥረው እያገለገሉ ሳሉ ተከሳሹ ድርጅት ያለአግባብ የስራ ውላቸውን ያቋረጡ መሆኑን ጠቅሰው ስንብቱ ህገ-ወጥ ነው ተብሎ የተለያዩ ክፍያዎች እንዲፈፀምላቸው እንዲወሰንላቸው ዳኝነት የጠየቁ መሆኑን የሚያሳይ ሲሆን ተከሳሹም በበኩሉ ቀርቦ ለክሱ በሰጠው መከላከያ መልስ የስራ ውሉ በተከሳሽ አነሳሽነት ላቋረጥ የቻለው በተከሳሽ ድርጅት ውስጥ ሆነው ድጋፍ የሚደረግላቸውንና በወሲብ ጥቃት ምክንያት ለስነ-ልቦና ቀውስ የተጋለጡ ህፃናትን ከሳሽ ያለተከሳሽ ድርጅት እውቅናና ፈቃድ በእንግዶች እንዲጐበኙ፣ እንዲጨፍሩ እና ፎቶግራፍ በእንግዶች እንዲነሱ በማድረጉና ይህ ድርጊትም ከከሳሹ የስራ ሙያ ውጭ ከመሆኑም በላይ የድርጅቱን የስራ ደንብም የጣሰ በመሆኑ ስንብቱ ህጉን ተከትሎ የተፈፀመ በመሆኑ ለከሳሹ የሚፈፀም ክፍያ የለም ሲሉ በመከራከር መልሱን ሰጥቷል።
ጉዳዩን የተመለከተው የፍድራሉ መጀመሪያ ደረጃ ፍ/ቤት በበኩሉ የግራ ቀኙን ክርክርና ምስክሮች ቃል ሰምቶ ጉዳዩንም ከቀረበው ማስረጃ እና ህጉ ጋር አገናዝቦ ተመልክቶ መመርመሩን ከገለፀ በኋላ ምንም እንኳ ጉብኝቱን ያለተከሳሹ እውቅና የፈቀዱ ስለመሆኑ እና እንዲሁም እነኝህ የወሲባዊ ጥቃት ሰለባ የሆኑት ህፃናትን ያለጥንቃቄ እንዲጐበኙ ማድረግ፣ ከእንግዶቹ ጋር እንዲጨፍሩ ማድረግ እና ፎቶ ግራፍ እንዲነሱ ማድረግ በህፃናቱ ስነ-ልቦና ጤንነት ጋር በተያያዘ ችግር የሚፈጥርባቸው ስለመሆኑ በባለሙያ ምስክርነት ቃል ጭምር የተረጋገጠ ቢሆንም ሆኖም ግን ከሳሹ ጉብኝቱን የፈቀዱት ህፃናቱ ከእንግዶቹ ጋር እንዲጨፍሩና ፎቶግራፍ እንዲነሱ ጭምር ስለመሆኑ ባለመረጋገጡ እና እንዲህ ከሆነ ደግሞ ከሳሽ ድርጊቱን በህፃናቱ ህይወት ላይ ጉዳት እንዲከተል ሆነ ብሎ የፈፀመው ነው ለማለት ስለማይቻል እና በአጠቃላይ የከሳሽ ስራ ውል የተቋረጠው በህጉ መሰረት ባለመሆኑ ስንብቱ ህገ-ወጥ ነው በማለት ከወሰነ በኋላ የካሳ ክፍያ ብር 33030 /ሰላሳ ሦስት ሺህ ሰላሳ ብር/፣ የማስጠንቀቂያ ጊዜ ክፍያ ብር 11010/አሥራ አንድ ሺህ አሥር ብር/ እና ከወጪና ኪሳራ ብር 400/አራት መቶ ብር/ ጋር ተከሳሹ ለከሳሽ ይክፈል በማለት ወስኗል።
በአሁኑ ተጠሪ አመልካችነት ጉዳዩን በይግባኝ የተመለከተው የፍድራሉ ከፍተኛ ፍ/ቤት ይግባኝ ሰሚ ችሎት በበኩሉ የግራ ቀኙን ክርክር ሰምቶ ጉዳዩን ከመረመረ በኋላ አመልካች ከድርጅቱ እውቅና ውጭ የወሲብ ተጠቂ የሆኑት ህፃናት በእንግዶች እንዲጐበኙ ማድረጉ መረጋገጡን በመግለፅና ይህ በአመልካች የተፈፀመው ድርጊትም በድርጅቱ የተቀመጠውን የአሰራር ደንብ መጣስ ብቻ ሳይሆን ሙያው የሚጠይቀውን ልዩ ጥንቃቄንም አለማድረጉን የሚያስረዳ በመሆኑ እና ጥፋቱም በአዋጅ ቁጥር 377/96 አንቀጽ 27(1)(ሰ) ስር የሚያስጠይቅ ሆኖ ሳለ የስር ፍ/ቤት ይሄንኑ ባለመገንዘብ ስንብቱ ህገ-ወጥ ነው በማለት መወሰኑ አለአግባብ ነው ሲል የስር ፍ/ቤቱን ውሳኔ በፍ/ብ/ስ/ስ/ህ/ቁጥር 348/1/ መሰረት በመሻር ወስኗል።
አሁን የቀረበው የሰበር አቤቱታም ይሄንኑ በይግባኝ ሰሚ ፍ/ቤት ስንብቱ ህጋዊ ነው በማለት ውሳኔ መስጠቱ መሰረታዊ የህግ ስህተት የተፈፀመበት በመሆኑ ውሳኔው ተሽሮ የስር ፍ/ቤቱ ውሳኔ ይፅናልኝ የሚል ይዘት ያለው አቤቱታውም በሰበር አጣሪ ችሎት ተመርምሮ ለሰበር ሰሚ ችሎት ያስቀርባል በመባሉ ተጠሪም ቀርቦ ግራ ቀኙ በፅሑፍ እንዲከራከሩ ተደርጓል።
የጉዳዩ አመጣጥና ይዘት ባጭር ባጭሩ ከላይ የተመለከተው ሲሆን እኛም በበኩላችን የግራ ቀኙን የሰበር ፅሑፍ ክርክር ለሰበር አቤቱታ መነሻ ከሆነው ውሳኔ እና አግባብነት ካላቸው ድንጋጌዎች ጋር በማገናዘብ የሰበር አቤቱታ በቀረበበት ውሳኔ ላይ የተፈፀመ መሰረታዊ የህግ ስህተት መኖር አለመኖሩን በጭብጥነት ይዘን ጉዳዩን በሚከተለው መልኩ መርምረናል።
እንደመረመርነውም የተጠሪ ድርጅት ከተቋቋመበት ዋና ዋና አላማዎች መካከል አንዱ እነዚሁኑ የወሲብ ጥቃት የደረሰባቸውን ህፃናት መንከባከብ እና በጥቃቱ ምክንያት ከደረሰባቸው የስነ-ልቦና ቀውስ እንዲድኑ እርዳታ ማድረግ መሆኑን፣ አመልካችም ይሄንኑ አላማ ለማስፈፀም ተቀጥሮ እነዚሁ ህፃናት ተጠልለው የሚገኙበት ማዕከል ኘሮጀክት አስተባባሪ መሆኑን፣ በዚህም መሰረት የህፃናቱን ጤንነት ለመጠበቅ፣ ለመንከባከብ ከስነ-ልቦና ቀውሱ እንዲያገግሙ የበኩሉን ሚና መወጣት ሚስጥራቸውን መጠበቅ እና እንዲጠበቅ ወይም እንዳይጋለጥ ለማድረግ በስራ ውሉ እና በድርጅቱ አሰራር ስርዓት መሰረት ከፍተኛ ግድታ የተጣለበት መሆኑን፣ ሆኖም ግን አመልካች ከተጠሪ ድርጅት እውቅናና ፈቃድ ውጭ ህፃናቱ ያለጥንቃቄ በእንግዶች እንዲጐበኙ፣ እንዲጨፍሩ እና በእንግዶቹ ፎቶግራፍ እንዲነሱ ማድረጉን በሰውና ሰነድ ማስረጃ መረጋገጡን፣ ይህ ድርጊትም የህፃናቱ ሚስጥር እንዲጋለጥ የሚያደርግ መሆኑንና ሚስጥራቸው በተጋለጠ ቁጥር ደግሞ በወሲብ ጥቃቱ ምክንያት የደረሰባቸውን የስነ-ልቦና ቀውስ በማባባስ ከፍተኛ የጤንነት ችግር ውስጥ እንዲገቡና የወደፊት ማህበራዊ ህይወታቸውም እንዲጐዳ የሚያደርግ ስለመሆኑ በተጠሪ ድርጅት በኩል ተቆጥረው በስር ፍ/ቤት ቀርበው በተሰሙት የባለሙያዎች ምስክርነት ቃል መረጋገጡን ከክርክሩ ሂደት ለመገንዘብ ተችሐል።
በልላ በኩል አንድ ሰራተኛ ደግሞ በስራ ውሉ እና በስራ ደንቡ መሰረት በአሰሪ የተሰጠውን ትዕዛዝ የመፈፀም ግድታ እንዳለበት በአሰሪና ሰራተኛ አዋጅ አንቀጽ 13(2) ስር ተመልክቶ ይገኛል። እንዲሁም የዚሁኑ አዋጅ ድንጋጌዎችን፣ የህብረት ስምምነትን፣ የስራ ደንብ እና በህግ መሰረት የሚተላለፉ መመሪያዎችንና ትዕዛዞችን የማክበር ግድታም እንዳለበት በንዑስ አንቀጽ 7 ስር ተደንግጓል። በተያዘው ጉዳይም አመልካች እነዚህ የወሲብ ተጠቂ የሆኑትን ህፃናት ጤንነት የመጠበቅ፣ የመንከባከብ፣ ከደረሰባቸው የስነ-ልቦና ቀውስ እንዲድኑ የበኩሉን እገዛ ማድረግ፣ ሚስጥራቸውንም የመጠበቅ እና እንዳይጋለጥ የማድረግ ግድታ የተጣለበት ሆኖ ሳለ ያለድርጅቱ ፈቃድና እውቅና ውጭ ህፃናቱ ጥንቃቄ በጐደለ ሁኔታ በውጭ እንግዶች እንዲጐበኙ እና ፎቶግራፍም በእንግዶች እንዲነሱ በመፍቀድ ሚስጥራቸው እንዲጋለጥ ማድረጉ በአዋጁ አንቀጽ 13(2) እና 13(7) መሰረት በስራ ውሉ እና በድርጅቱ የአሰራር ስርዓት መሰረት እንዲፈፀም የተጣለበትን ግድታ አለመወጣቱንና መጣሱን የሚያሳይ ነው። ይህ ድርጊትም በመካከላቸው የተደረገውን የስራ ውሉን መሰረታዊ ስምምነት የሚጥስ በመሆኑ ተጠሪም ይህንኑ መነሻ በማድረግ የስራ ውሉን ማቋረጡ የአዋጁን አንቀጽ 13(2) እና 13(7) ድንጋጌዎች ይዘት፣ አላማ እና መንፈስ ያገናዘበ ነው ከሚባል በቀር የሚነቀፍ ሆኖ አላገኘንም። የፍድራሉ ከፍተኛ ፍ/ቤት ይግባኝ ሰሚ ችሎትም ለጉዳዩ በቀጥታ አግባብነት የልለውን የአዋጁን አንቀጽ 27(1)(ሰ) ድንጋጌን ጠቅሶ ስንብቱ ህጋዊ ነው በማለት የሰጠው የውሳኔ ክፍል ላስተካከልና ላታረም የሚገባ ቢሆንም ሆኖም ግን በውጤት ደረጃ ስንብቱ ህጋዊ ነው በማለት የበታች ፍ/ቤቱን ውሳኔ ሽሮ በሰጠው ውሳኔ ላይ የተፈፀመ መሰረታዊ የሆነ የህግ ስህተት ስላላገኘን ተከታዩን ውሳኔ ሰጥተናል።
የፍድራል መጀመሪያ ደረጃ ፍ/ቤት በኮ/መ/ በ11/3/2ዐዐ5 ዓ.ም. የሰጠው ፍርድ በፍ/ብ/ስ/ስ/ህ/ቁ 348/1/ መሰረት ተሽሯል።
የፍድራሉ ከፍተኛ ፍርድ ቤት በኮ/መ/ በ2ዐ/ዐ7/2ዐዐ5 ዓ.ም. የሰጠው ፍርድ በፍ/ብ/ስ/ስ/ህ/ቁ 348/1/ መሰረት በተለወጠ ምክንያት በውጤት ደረጃ ፀንቷል።
የሰበር ወጪና ኪሳራን ግራ ቀኙ የየራሳቸውን ይቻሉ ብለናል።
No topics extracted.