No summary available.
የካቲት 12 ቀን 2006 ዓ.ም.
ዳኞች፡- አልማው ወል ዓላ መሐመድ ረታ ቶሎሳ አዳነ ንጉሴ ሙስጠፋ አህመድ አመልካች፡- አቶ ዳዊት አበበ - ቀረቡ ተጠሪዎች፡-
ጉዳዩ የቀረበው አመልካች የበታች ፍርድ ቤቶች፣ አመልካች በመጀመሪያ ክርክሩን ለሽማግል ዳኞች ያላቀረበ በመሆኑ፣ አከራክሮ ለመወሰን ሥልጣን የለንም በማለት የሰጡት ብይን መሰረታዊ የሆነ የህግ ስህተት አለበት በማለት ያቀረበውን አቤቱታ አጣርቶ ለመወሰን ነው። አመልካች የአንደኛው ተጠሪ አባል የነበረ መሆኑን ገልፆ ሁለተኛው ተጠሪ የማህበሩ ላቀመንበር ሆኖ ወርሃዊ መዋጮ መክፈል አቋርጠሀል በማለት አላግባብ ከአባልነት ያሰናበተኝ ስለሆነ የማህበር አባልነት መብቴ እንዳይሰረዝ ውሳኔ ይሰጥልኝ በማለት በስር ፍርድ ቤት ክስ አቅርቧል። ተጠሪዎች ተከሳሽ ሆነው የአመልካች ክስ በግልግል መታየት ያለበትና ለፍ/ቤት መቅረቡ ተገቢ አለመሆኑን በመግለጽ ተከራክረዋል።
የሥር ፍርድ ቤት አመልካች ጉዳዩን ለሽማግል ዳኞች ከሚያቀርብ ወይም ለሽማግል ዳኞች ቀርቦም ከሆነ ውጤቱን ጠብቆ በሕጉ መሰረት ይግባኝ ሥልጣን ላለው ፍርድ ቤት ከሚያቀርብ በስተቀር በቀጥታ ለፍርድ ቤት የማቅረብ መብት የለውም። ፍርድ ቤቱም ጉዳዩን በመጀመሪያ አይቶ ለመወሰን የሚያስችለው የዳኝነት ስልጣን የለውም በማለት ብይን ሰጥቷል። አመልካች የፍድራል የመጀመሪያ ደረጃ ፍርድ ቤት በሰጠው ብይን ቅር በመሰኘት ይግባኝ ለፍድራል ከፍተኛ ፍርድ ቤት አቅርቧል ይግባኝ ሰሚው ፍርድ ቤት የአመልካችን ይግባኝ በፍ/ስ/ስ/ሕግ ቁጥር 337 መሰረት ሰርዞታል።
አመልካች ሐምል 5 ቀን 2005 ዓ/ም በተፃፈ የሰበር አቤቱታ አመልካች የክስ ምክንያት ያላግባብ ከማህበር አባልነቴ ተሰናበትኩ የሚል በመሆኑ በፍርድ ቤት የሚታይ እንጂ በሽማግል ዳኞች የሚታይ አይደለም። ክስ ከማቅረቤ በፊት በንፋስ ስልክ ላፍቶ ክፍለ ከተማ ማህበራት ማደራጃ ጽ/ቤት አመልክቼ አመልካች አንድ፣ ተጠሪዎች አንድ የሽማግል ዳኛ ከመረጥን በኋላ ተጠሪዎች ሰብሳቢ ዳኛ መርጠዋል። ሰብሳቢው ዳኛም አድሐዊነት የሚታይበት በመሆኑ እንዲቀየር በማህበራት ማደራጃ ጽ/ቤት አመልክቼ ዳኛ መቀየር የማይችሉ መሆኑን ማህበራት ማደራጃ ስለገለፀልኝ ክስ ለፍርድ ቤት አቅርቤያለሁ። የፍድራል ጠቅላይ ፍርድ ቤት የሰበር ችሎት በመዝገብ መጋቢት 10 ቀን 2004 በሰጠው ውሳኔ የሥር ፍርድ ቤት ጉዳዩን አይቶ እንዲወስን የሰጠውን ውሳኔ ወደጎን በመተው የበታች ፍርድ ቤቶች ጉዳዩን የማየት ስልጣን የለኝም በማለት የሰጡት ብይን መሰረታዊ የህግ ስህተት ያለበት ስለሆነ በሰበር ታይቶ እንዲታረምልኝ በማለት አመልክቷል።
ተጠሪዎች የስር ፍርድ ቤት ይህ ሰበር ችሎት በፍ/ብ/ስ/ስ/ሕግ ቁጥር 73 የተዘጋውን መዝገብ በማንቀሳቀስ የግራ ቀኛችንን ክርክር በመመርመር ውሳኔ እንዲሰጥበት በወሰነው መሰረት ተጠሪዎች ጉዳዩ በመጀመሪያ መታየት ያለበት በሽማግል ዳኞች ነው በማለት አዋጅ ቁጥር 147/91 ድንጋጌዎች በመጥቀስ ያቀረብነውን መቃወሚያ በመቀበል የሰጠው ውሳኔ መሰረታዊ የህግ ስህተት የለበትም መስከረም 21 ቀን 2006 ዓ/ም በተፃፈ መልስ ተከራክረዋል።አመልካች ጥቅምት 19 ቀን 2006 ዓ/ም የተፃፈ የመልስ መልስ አቅርቧል።
ከስር የክርክሩ አመጣጥና በሰበር የቀረበው ክርክር ከላይ የተገለፀው ሲሆን እኛም የበታች ፍርድ ቤቶች ጉዳዩ መጀመሪያ መቅረብ ያለበት ለሽማግል ዳኞች ነው በማለት የሰጡት ውሳኔ በአግባቡ ነው ወይስ አይደለም? የሚለውን ጭብጥ በመያዝ ጉዳዩን መርምረናል።
ጉዳዩን እንደመረመርነው አመልካች የአንደኛው ተጠሪ አባል እንደነበርና ሁለተኛ ተጠሪ የማህበሩ ላቀመንበር ሆኖ ሲሰራ ወርሃዊ ክፍያ አልከፈልክም በማለት ከአባልነት እንዲሰናበት አላግባብ በልላ ሰው እንዲተካ ያደረገ በመሆኑ የማህበሩ አባል ሆኜ እንድቀጥል ይደረግልኝ የሚል የዳኝነት ጥያቄ ያቀረበ መሆኑን ከስር ፍርድ ቤት ውሳኔና በሰበር ከቀረበው ክርክር ተገንዝበናል። ይህም የሚያሳየው ክርክሩ የተነሳው በህብረት ሥራ ማህበሩና አላግባብ የማህበር አባልነት መብቴ ተቋርጧል በሚለው የቀድሞው የማህበሩ አባል በሆነው አሁን ግን አባልነቱ በአንደኛ ተጠሪ በመሰረዙ በአባልነት መጠቀስ ያለበት ወይም የልለበት ስለመሆኑ ከፍሬ ጉዳይና ከህግ አንፃር ተመዝኖ ውሳኔ ላሰጥበት ከሚገባው በአመልካች መካከል መሆኑን ነው። በአንድ ማህበር አቋም ስለ ስራው አካሄድ ወይም ስለስራው አፈፃፀም በአባላት ወይም በቀድሞ አባላት ወይም በቀድሞ አባላት ወኪሎች ወይም በሞት በተለዩ አባላት ስም ክርክር የሚያቀርቡ ሰዎች በማህበሩና በማህበሩ አመራር መካከል የሚነሳ ክርክር በመጀመሪያ ለሽማግል ዳኞች ቀርቦ መታየት እንዳለበት በአዋጅ ቁጥር 147/96 አንቀጽ 49 ንዑስ አንቀጽ 1 እና ንዑስ አንቀጽ 2 ተደንግጓል። አመልካች አንደኛ ተጠሪ አላግባብ ከአባልነት ሰርዞኛል ከማለቱም በተጨማሪ የማህበሩ አመራር የሆነውን ሁለተኛ ተጠሪም ላይ ክስ አቅርቧል።
ማንኛውም ሰው በፍርድ ላያልቁ የሚችሉ ጉዳዮችን ለፍርድ ቤት ወይም በህግ የዳኝነት ሥልጣን ለተሰጠው አካል የማቅረብና ፍትህ የማግኘት መብት ያለው መሆኑ በሕገመንግስቱ አንቀጽ 37 ተደንግጓል። የሕገ መንግስቱ አንቀጽ 79 ንዑስ አንቀጽ 1 ድንጋጌ ተግባራዊ ተፈፃሚነትም የሕገ መንግስቱን አንቀጽ 37 ድንጋጌዎች ውጤታማነት በሚያጎለብትና በሚያጠናክር መንገድ መሆን ይኖርበታል። ከዚህ አንፃር ሲታይ በህብረት ሥራ ማህበራትና በአባሎቻቸው ወይም በቀድሞ አባላቸው ወይም በህብረት ስራ ማህበር አባላት ወይም የቀድሞ አባላትና በማህበሩ አመራር መካከል የሚነሳ ክርክር በመጀመሪያ አይቶ ውሳኔ ለመስጠት በሕግ የዳኝነት ሥልጣን የተሰጠው የሽምግልና ጉባኤ ነው።
ከዚህ አንፃር ጉዳዩ በአዋጅ ቁጥር 147/91 አንቀጽ 49 ሥልጣን ለተሰጠው ለሽምግልና የዳኝነት አካል ሳይቀርብ ፍርድ ቤቶች ተቀብለው ዳኝነት ለማየትና ለመወሰን የማይችሉ መሆኑን የሕገ-መንግስቱ አንቀጽ 37፣ አንቀጽ 79(1) እና የአዋጅ ቁጥር 147/91 አንቀጽ 49 ድንጋጌዎች በማየት መረዳት ይቻላል። ከዚህ አንፃር አመልካች ጉዳዩ በቀጥታ በፍርድ ቤት ላታይ ይገባዋል በማለት ያቀረበው ክርክር የሕግ መሰረት የልለው በመሆኑ አልተቀበልነውም።
ልላው አመልካች ያቀረበው መከራከሪያ ይህ ሰበር ችሎት በሰበር መዝገብ መጋቢት 10 ቀን 2004 ዓ/ም የሰጠውን ውሳኔ ነው። ይህ ሰበር ችሎት በሰበር መዝገብ ያየው መሰረታዊ ጭብጥ ተካሳሾች የቃል ክርክር በሚያሰሙበት ቀን ከሳሽ የነበረው (አመልካች) ባለመቅረቡና ተከሳሾች (ተጠሪዎች) በመካዳቸው መዝገቡ ከተዘጋ በኋላ አመልካች በፍ/ስ/ስ/ሕግ ቁጥር 74(2) መሰረት እንዲከፈት ሲጠይቅ በቀነ ቀጠሮው ያልቀረብከው በቂ በሆነ ምክንያት አይደለም በማለት የፍድራል መጀመሪያ ደረጃ ፍርድ ቤትና የፍድራል ከፍተኛ ፍርድ ቤት ብይን በመስጣቸው ይህ ሰበር ችሎት ከሳሽ (አመልካች) በቀነ ቀጠሮው ያልቀረበው በበቂ ምክንያት በመሆኑ መዝገቡ ተከፍቶ የሥር ፍርድ ቤት የግራ ቀኙን ክርክር ሰምቶ እንዲወሰን ጉዳዩን በፍ/ብ/ስ/ስ/ሕግ ቁጥር 341(1) መሰረት የመለሰበት ነው። ጉዳዩ በፍ/ብ/ስ/ስ/ስ/ሕግ ቁጥር 341(1) የተመለሰ በመሆኑ የሥር ፍርድ ቤት ተከሳሾች (አመልካቾች) ያቀረቡትን የመጀመሪያ የክስ መቃወሚያ በመመርመር የሰጠው ብይን የፍ/ብ/ሥ/ሥ/ሕግ ቁጥር 244(1) ድንጋጌዎች መሰረት ያደረገ ነው። የሥር ፍርድ ቤት ብይኑን የሰጠውም ይህ ሰበር ችሎት በሰበር መዝገብ የሰጠውን ውሳኔ ይዘትና ሕጋዊ ውጤት መሰረት በማድረግ በመሆኑ አመልካች ያቀረበው የሰበር አቤቱታና መከራከሪያ የሕግ ድጋፍ የለውም።
አመልካች የሽማግል ዳኞች በንፋስ ስልክ ላፍቶ ክፍለ ከተማ ማህበራት ማደራጃ ጽ/ቤት በኩል ተሰይሞ የነበረ መሆኑንና ሰብሳቢው ዳኛ አድሐዊ በመሆኑ ለፍርድ ቤት ክስ አቀረብኩ የሚለው መከራከሪያ ህግን መሰረት ያደረገ አይደለም። የሽማግል ዳኞች ከተሰየሙ በኋላ አንድ ዳኛ እንዲለወጥ ማድረግ አስፈላጊ በሆነ ጊዜ ከተከራከሪዎች አንደኛው ዳኛው እንዲለወጥ የሚጠይቅበትን ምክንያት በመዘርዘር በመጀመሪያ የሽማግል ዳኞቹ ፣የሽማግል ዳኞቹ እንቢተኛ ከሆኑ ለፍርድ ቤት ጥያቄውን ማቅረብ እንደሚችል ከፍትሐብሕር ሕግ ቁጥር 3340 እስከ ፍትሐብሕር ሕግ ቁጥር 3342 ተደንግጓል። ከዚህ አንፃር አመልካች ህጉን በመከተል ጥያቄያቸውን ሳያቀርቡ ክሱን በቀጥታ ለፍርድ ቤት ማቅረባቸው የህግ መሰረት የልለው በመሆኑ የአመልካችን መከራከሪያ አልተቀበለውም።
ከላይ በዝርዝር በገለጽናቸው ምክንያቶች የበታች ፍርድ ቤቶች የሰጡት ብይን መሰረታዊ የሕግ ስህተት የለበትም በማለት ወስነናል።
የፍድራል የመጀመሪያ ደረጃ ፍ/ቤትና የፍድራል የከፍተኛ ፍርድ ቤት የሰጠው ብይን መሰረታዊ የሕግ ስህተት የለበትም።
አመልካችና ተጠሪ የሚከራከሩበትን ጉዳይ ፍርድ ቤት በመጀመሪያ አይቶ ውሳኔ የመስጠት ሥልጣን የለውም በማለት ወስነናል።
አመልካችና ተጠሪ የሚከራከሩበት ጉዳይ በአዋጅ ቁጥር 147/91 አንቀጽ 49 መሰረት በተቋቋመ የሽማግል ዳኞች ቀርቦ ውሳኔ ማግኘት አለበት በማለት ወስነናል።
ይህ ውሳኔ አመልካች የሽማግል ዳኞች እንዲቋቋምለት ጥያቄውን ለሚመለከተው የአስተዳደር ክፍል ወይም ሥልጣን ላለው ፍርድ ቤት ከማቅረብ የሚገድበው አይደለም በማለት ወስነናል።
በዚህ ፍርድ ቤት ያወጡትን ወጭና ኪሳራ ግራ ቀኙ ለየራሳቸው ይቻሉ።
መዝገቡ ወደ መዝገብ ቤት ይመለስ።
No topics extracted.