No summary available.
ጥር 15 ቀን 2006 ዓ.ም.
ዳኞች፡- አልማው ወል ዓላ መሐመድ ረታ ቶሎሳ አዳነ ንጉሴ ሙስጠፋ አህመድ አመልካች- የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር መንገድና ትራንስፖርት ቢሮ ነገረ-ፈጅ ፅጌ መለሰ ቀረቡ ተጠሪ:- ካኪ ኃላፊነቱ የተወሰነ የግል ማህበር ጠበቃ ሀጎስ አብርሃ ቀረቡ መዝገቡን መርምረን የሚከተለውን ፍርድ ሰጥተናል ።
ጉዳዩ የቀረበው አመልካች የፍድራል ከፍተኛ ፍርድ ቤት በመዝገብ ግንቦት 12 ቀን 2005 ዓ.ም የሰጠው ውሣኔ በከፊል መሰረታዊ የሕግ ስህተት ያለበት ስለሆነ በሰበር ታይቶ ይታረምልኝ በማለት ያቀረበዉን የሰበር አቤቱታ አጣርቶ ለመወሰን ነው። ጉዳዩ ወጭና ኪሣራን በተመለከተ የተሰጠውን ውሣኔ የሚመለከት ነው። ጉዳዩ በመጀመሪያ የቀረበው ለፍድራል የመጀመሪያ ደረጃ ፍርድ ቤት ነው። በሥር ፍርድ ተጠሪ ከሳሽ አመልካችተከሳሽ በመሆን ተከራክረዋል።
ተጠሪ በመኪና አስመጭነት የሚሰራ ነጋድ መሆኑን ገልፆ፣ ከውጭ ያስመጣኋቸው አሥር ትራክተሮች የሚገዛኝ በማጣቴ በንብረትነት በማስመዝገብ በግል ልገለገልባቸው ስለፈለግሁ የባለሀብትነት ስም ለማዛወር 422,604.22 /አራት መቶ ሃያ ሁለት ሺ ስድስት መቶ አራት ብር ከሃያ ሁለት ሣንቲም/ ለተከሳሽ (አመልካች) በ3-10-2003 ዓ.ም ከፍያለሁ። ከሳሽ ይህንን ገንዘብ ከከፈልኩ በኋላ ትራክተሮቹን ጌትስ ኢንተርናሽናል ኃላፊነቱ የተወሰነ የግል ማህበር ገዝቶኛል። ተከሳሽ የከፈልኩትን ገንዘብ እንዲመልስ ብጠይቀው ፈቃደኛ ስላልሆነ ገንዘቡን ከነወለዱ እንደዚሁም ወጭና ኪሣራ እንዲከፍል ይወሰንልኝ በማለት ክስ አቅርቧል። አመልካች ገንዘቡን ከመመለሳችን በፊት የኢኮኖሚና ገንዘብ ሚኒስትር አስተያየት መጠየቅ ያለብን በመሆኑ ጠይቀናል ገንዘቡንም ለመመለስ በሂደት ላይ ስንሆን፣ ወጭና ኪሣራ ግን ልንከፍል አይገባም በማለት ተከራክሯል። የሥር ፍርድ ቤት ተከሳሽ ከሳሽ በክሱ የጠየቀውን ገንዘብ እንዲከፍል በማለት ውሣኔ ሰጥቷል። ወጭና ኪሣራን በተመለከተ ተከሳሽ ከሳሽን ለክርክርና ለወጭ ያልጋበዘ በመሆኑ፣ ወለድ ወጭና ኪሣራ ለከሳሽ ላከፍል አይገባም በማለት ውሣኔ ሰጥቷል።
ተጠሪ ወለድ ወጭና ኪሣራ የሥር ፍርድ ቤት አይገባህም ማለቱን በመቃወም ይግባኝ ለፍድራል ከፍተኛ ፍርድ ቤት አቅርቧል። ይግባኝ ሰሚው ፍርድ ቤት የግራ ቀኙን ክርክር ከሰማ በኋላ አመልካች ተጠሪን ስምንት ወራት ያህል ገንዘቡን አልመለሰለትም። ስለዚህ አመልካች ወለድ፣ ለዳኝነት የተከፈለ ገንዘብና የጠበቃ አበል የመክፈል ግድታ አለበት። አመልካች ተጠሪ የጠየቀውን ወለድ ፣ የዳኝነት ገንዘብ ፣ ይክፈል ። የጠበቃ አበል ተጠሪ ከጠየቀው ብር 44,000 ግማሹን ብር 22,000 /ሃያ ሁለት ሺ ብር/ ይክፈል በማለት ውሣኔ ሰጥቷል።
ለዚህ የሰበር ክርክር መነሻ የሆነው የሰበር አቤቱታ የቀረበው፣ የፍድራል ከፍተኛ ፍርድ ቤት የሰጠውን የወጭና ኪሣራ ውሣኔ በመቃወም ነው። አመልካች ተጠሪ ራሱ አገልግሎት ለማግኘት ገንዘቡን በፈቃዱ ከፍሎ አገልግሎት ለመስጠት በሂደት ላይ እያለን፣አገልግሎቱ እንዲቋረጥ ጥያቄ አቀረበ። ከዚያም የመንግሥት የፋይናንስ አሰራር በመጠበቅ ልንመልስለት በሂደት ላይ በነበርንበት ወቅት፣ ወለድ፣ወጭና ኪሣራ እንድንከፍለው ያቀረበው ክስ የሕግ መሰረት የለውም በማለት ተከራክሯል።
ተጠሪ አመልካች ገንዘቡን በወቅቱ ያልመለሰ በመሆኑ ይግባኝ ሰሚው ፍርድ ቤት የሰጠው ውሣኔ ተገቢ ነው በማለት ተከራክሯል።
ከሥር የክርክሩ አመጣጥና በሰበር የቀረበው ክርክር ከላይ የተገለፀው ሲሆን እኛም ጉዳዩን መርምረናል። ጉዳዩን እንደመረመርነው አመልካች ከዋናው ገንዘብ በተጨማሪ ወለድ እንዲከፍል መወሰኑ ተገቢ ነው ወይስ አይደለም? የሚለውን ጭብጥ በመያዝ ጉዳዩን መርምረናል።
ጉዳዩን እንደመረመርነው፣ ተጠሪ ገንዘቡን ለአመልካች የከፈለው ገዥ ያጡ መኪናዎች በስሙ ለማዛዋር በማሰብ እንደሆነ ከክስ ማመልከቻው ተገልጿል። ተጠሪ ገንዘቡን ከከፈለ በኋላ መኪናዎቹ (ትራክተሮች) በመሸጣቸው፣ የመኪናዎቹ ስመሀብት በስሙ ለማዛወር ጠይቆት የነበረው አገልግሎት እንዲቋረጥና አገልግሎቱን ለማግኘት ለአመልካች የከፈለው ገንዘብ እንዲ መለስለት እንደጠየቀ፣ ግራቀኙ በበታች ፍርድ ቤቶች እና በሰበር ካቀረቡት ክርክር ተረድተናል። ይህም የተጠሪ ጥያቄ ልከፍል የማይገባኝን ገንዘብ የከፈልኩ ስለሆነ ላመለስልኝ ይገባል የሚል እንደሆነና በፍትሐብሕር ሕግ ቁጥር 2164 ንዑስ አንቀፅ 1 መሰረት በማድረግ የቀረበ ጥያቄ ነው። አመልካች ተጠሪን ገንዘቡን የተቀበለው ተጠሪ የጠየቀውን አገልግሎት ለመሥጠት የግድ መከፈል የነበረበት ክፍያ በመሆኑ ምክንያት ነው። አመልካች ተጠሪን ገንዘቡን የተቀበለው እምነትን የሚያጓድል ተግባራትን በመፈፀም አይደለም።
የማይገባውን ክፍያ የከፈለ ሰው ገንዘቡን ከከፈለበት ቀን አንሥቶ ሕጋዊ ወለድ እንዲከፈለው ለመጠየቅ የሚችለው፣ ገንዘቡን የተቀበለው ሰው እምነትን በሚያጓድል ሁኔታ ክፍያውን ተቀብሎት በሆነ ጊዜ እንደሆነ በፍትሐብሕር ሕግ ቁጥር 2164 ንዑስ አንቀፅ 2 ተደንግጓል። ከዚህ አንፃር ሲታይ ይግባኝ ሰሚው ፍርድ ቤት በፍትሐ ብሕር ሕግ ቁጥር 2164 ንዑስ አንቀፅ 1 እና ንዑስ አንቀፅ 2 ድንጋጌዎች ይዘት መሰረታዊ ዓላማና ተግባርና ተፈፃሚነት በአግባቡ ሣያገናዝብ፣ አመልካች ብር 38,034 (ሰላሣ ስምንት ሺ ሰላሣ አራት ብር) ወለድ ለተጠሪ መክፈል አለበት በማለት የሰጠው ውሣኔ የሕግ መሰረት የልለውና መሰረታዊ የሕግ ስህተት የተፈፀመበት ሆኖ አግኝተነዋል።
ውሣኔ
የፍድራል ከፍተኛ ፍርድ ቤት የሰጠው ውሣኔ ተሻሽሐል።
የፍድራል ከፍተኛ ፍርድ ቤት አመልካች ለተጠሪ ወለድ ብር 38,034/ሰላሣ ስምንት ሺ ሰላሣ አራት ብር/ እንዲከፍል የሰጠው የውሣኔ ክፍል ተሽሯል።
አመልካች ተጠሪ ለዳኝነት የከፈለውን ብር 7,076 /ሰባት ሺ ሰባ ስድስት ብር/ ለቴምብር ቀረጥ የከፈለውን ብር 275 /ሁለት መቶ ሰባ አምስት ብር/ እና የጠበቃ አበል 22,000/ሃያ ሁለት ሺ ብር/ እንዲከፍል በማለት የሰጠው የውሣኔ ክፍል ፀንቷል።
በዚህ ፍርድ ቤት ያወጡትን ወጭ ለየራሳቸው ይቻሉ። መዝገብ ወደ መዝገብ ቤት ይመለስ።
No topics extracted.