No summary available.
ሚያዝያ 9 ቀን 2006 ዓ.ም ዳኞች፡- አልማው ወል ዓላ መሐመድ ረታ ቶሎሣ አዳነ ንጉሴ ሙስጠፋ አህመድ አመልካች፡- ሸዋ ንግድና ኢንዱስትሪ ኃ/የተ/የግ/ማህበር፡- የቀረበ የለም ተጠሪ፡- አቶ አሸብር አበበ፡- ቀረቡ **
መዝገቡ ተመርምሮ ተከታዩ ፍርድ ተሰጥቷል።
**
ጉዳዩ የአሰሪና ሰራተኛ ክርክርን የሚመለከት ሆኖ ክርክሩም የተጀመረው የአሁኑ ተጠሪ ለፍድራሉ መጀመርያ ደረጃ ፍ/ቤት ባቀረቡት ክስ፡-አመልካች ለ1ወር ከህግ ውጭ ከስራ አግዶኝ ካቆየኝ በኃላ ወደ ስራ እንዲመልሰኝ በተደጋጋሚ ብጠይቀውም ለመመለስ ፍቃደኛ ባለመሆን የስራ ውልን ከህግ ውጭ ስላቋረጠ በአሰሪና ሰራተኛ አዋጅ መሰረት ካሳና የተለያዩ ክፍያዎች ይፈፅምላቸው ዘንድ ዳኝነት የተጠየቀበት ሲሆን ተጠሪም ቀርቦ ለክሱ በሰጠው መልስ ተጠሪ የአመልካች ድርጅትን ስም፤የስራ አስኪያጁን ፊርማና የድርጅቱን ማህተም አስመስለው ሀሰተኛ የምስክር ወረቀት አዘጋጅተው በመገልገል የማታለል ወይም የማጭበርበር ድርጊት ፈፅመዋል በሚል በመጠርጠሩ ጉዳዩ እስኪጣራ ድረስ ለ1ወር ከስራ ታግደው የነበረ ቢሆንም ምርመራው ባለመጠናቀቁ ፖላስ ጉዳዩን አጣርቶ የመጨረሻ ውሳኔ እስኪሰጥ ድረስ ተጠሪ ለጊዜው መደበኛ ስራውን እንዲቀጥል ቢነገረውም ፍቃደኛ ባለመሆኑና በዚህም መሰረት በስራ ገበታው ላይ በመደዳው ከ5 የስራ ቀናት በላይ ባለመገኘቱና በፈፀሙት የማጭበርበር ድርጊት የስራ ውላቸው በአዋጅ ቁ.377/96 አንቀፅ 27(1)(ለ)(ሐ) መሰረት በህጉ አግባብ መቋረጡን በመግለፅ ተከራክሯል።
ጉዳዩን በመጀመርያ ደረጃ የተመለከተው የፍደራሉ መጀመርያ ደረጃ ፍ/ቤት በበኩሉ የግራ ቀኙን ክርክርና የአመልካችን ምስክሮች ከሰማ በኃላ ጉዳዩን መርምሮ ተጠሪ ክርክሩ ከተጀመረ በኃላ በፈፀሙት የማጭበርበር ድርጊት በወንጀል ችሎቱ ጉዳዩ ታይቶ ጥፋተኛ ተብለው የተቀጡ መሆኑን አመልካች ገልፀው መዝገቡ ቀርቦ እንዲታይላቸው ያመለከቱትን በተመለከተ ቀደም ሲል ጉዳዩን ሲመለከቱት በነበሩት ዳኛ በጭብጥነት የተያዘው ተጠሪ ከስራ ታግደው ከቆዩ በኃላ ወደ ስራ ለመመለስ ፍቃደኛ ነበሩ ወይስ አልነበሩም? የሚለው ነጥብ ብቻ በመሆኑና ክርክሩም የቀጠለው በዚሁ ነጥብ ላይ በመሆኑ በወንጀል ጥፋተኛ የመሆናቸው ጉዳይ የወንጀሉን መዝገብ በማስቀረብ ላመረመር አይችልም በማለት ካለፈ በኃላ ተጠሪ ወደ ስራ ለመመለስ እምቢተኛ ሆነው ከ 5 የስራቀናት በላይ ስለመቅረታቸው የአመልካች ማስረጃ ስላላስረዳ የተጠሪ ስራ ውል የተቋረጠው በህገ ወጥ መንገድ ስለሆነ አመልካች የ6ወር ደመወዝ የካሳ ክፍያ የ2ወር ደመወዝ የማስጠንቀቂያ ጊዜ ክፍያ፣ የስራ ስንብትና የዓመት ረፍት ጊዜ ወደ ገንዘብ ተለውጦ በድምሩ ብር 13,296.33 የገቢ ግብር ቀንሶ ለተጠሪ ይክፈል ሲል ወስኗል። ይህ ውሳኔም በፍድራሉ ከፍተኛ/ፍ/ቤት በይግባኝ ታይቶ በፍ/ብ/ስ/ስ/ህ/ቁ.337 መሰረት ፀንቷል።
አሁን የቀረበው የሰበር አቤቱታም ይሄንኑ ውሳኔ በመቃወም ሲሆን መሰረታዊ የቅሬታ ነጥቦችም የተጠሪ ስራ ውል የተቋረጠው በፈፀሙት የማጭበርበር ወንጀል ድርጊት ጭምር መሆኑን አመልካች ከመጀመሪያ ጊዜ ጀምሮ ማለትም የፅሑፍ መልስ ሲሰጥ ጀምሮ ክርክሩ ቀርቦ እያለ የስር ፍ/ቤቱ ግን ይሄንን በጭብጥነት ሳይዝ ማለፉ ስለጭብጥ አያያዝና አመሰራረት አስመልክቶ በፍ/ብ/ስ/ስ/ህ/ቁ.247 እና 248 የተደነገገውን የሚጥስ ነው።ተጠሪ የአመልካችን ድርጅት ማህተምና የስራአስኪያጁን ቲተር የሚመስል ሀሰተኛ ማህተም በራሳቸው ወይም በልላ ሰው አማካኝነት የተዘጋጀውን በመገልገል በፈፀመው ወንጀል ድርጊት ተከሶ እና ጉዳዩም ተጣርቶ የጥፋተኝነት ውሳኔ ተሰጥቶባቸዋል። በስራ ክርክር ችሎት በክርክር ላይ እያለን የተጠሪ ስራ ውል ከተቋረጠበት ጉዳይ ጋር በተያያዘ ተጠሪ በወንጀል ጥፋተኛ የተደረገበት ውሳኔ ቀርቦ ታይቶ እና ጉዳዩ ከዚህ አንፃር በጭብጥነት ተይዞና ተመርምሮ በስር ፍ/ቤቶች ውሳኔ መሰጠት ሲገባዉ ታልፎ ስንብቱ ህገ-ወጥ ነው በማለት የሰጡት ውሳኔ ከፍ/ብ/ሥ/ሥ/ህ/ቁ.247 እና 248 ድንጋጌዎች አኳያ መሰረታዊ የህግ ስህተት ስላለበት ውሳኔዎቹ ተሽረው የተጠሪ ስራ ውል የተቋረጠው በህግ አግባብ ስለሆነ የካሳ ክፍያና ልሎች ልዩ ልዩ ክፍያዎችን ላከፈላቸው አይገባም በማለት ይወስንልን የሚል ነው።
የሰበር አጣሪ ችሎቱም ተጠሪ በወንጀል ጥፋተኛ ተብለው የተቀጡበትን የወንጀል መዝገብ በትዕዛዝ አስቀርቦ እና አቤቱታውንም ከወንጀል ጥፋተኝነት ውሳኔ ጋር በማገናዘብ መርምሮ የግራ ቀኙን የክርክር ሂደት አመልካች ስለስንብቱ ጉዳይ ተጠሪ በፈፀመው ድርጊት በወንጀል ተከሶ ክርክሩ ተጠናቆ የጥፋተኝነት ውሳኔ ተሰጥቷል፣ ይህ የወንጀል ችሎትጥፋተኝነት ውሳኔ ለጉዳዩ አግባብነት ያለው ስለሆነ ይታይልን በሚል አመልካች ላቀረበው ክርክር የስር ፍ/ቤት ከጭብጥ ውጭ ነው በሚል መታለፉ ስነ-ስርዓታዊ ነው?ወይስ አይደለም?የሚለውን ማየት እንዲቻል ጉዳዩ ለዚህ ሰበር ችሎት እንዲቀርብ የተደረገ ሲሆን ተጠሪም ቀርቦ ግራ ቀኙ በፅሑፍ እንዲከራከሩ ተደርጓል።
የጉዳዩ አመጣጥና ይዘት ከላይ የተመለከተውን የሚመስል ሲሆን እኛም በበኩላችን የግራ ቀኙን የሰበር ፅሑፍ ክርክር ለሰበር አቤቱታ መነሻ ከሆነው ውሳኔና አግባብነት ካላቸው ድንጋጌዎች ጋር በማገናዘብ ጉዳዩ ለዚህ ሰበር ሰሚ ችሎት ሲቀርብ ተይዞ ከነበረው ጭብጥ አንፃር ጉዳዩን በሚከተለው መልኩ መርምረናል።
መዝገቡን እንደመረመርነውም አመልካች ተጠሪን ከስር ለማሰናበት በምክንያትነት የጠቀሰው የአንድ ወር እግዱ ጊዜ ካበቃ በኃላ ተጠሪ ወደ ስራቸው ለመመለስ ፍቃደኛ ባለመሆን በተከታታይ ከ5 የስራ ቀናት በላይ በስራ ገበታቸው ላይ ባለመገኘታቸውና እንዲሁም የድርጅቱን ማህተም እና የስራአስኪያጁን ቲተር አስመስሎ ሐሰተኛ የስራ ልምድ ሰርተው ወይም አሰርተው በመጠቀም በፈፀሙት የወንጀል ድርጊት ምክንያት ነው በሚል መሆኑንና እነዚህን ምክንያቶችም ለክሱ መልሱን ሲሰጥ ጀምሮ ስንብቱ ህጋዊ መሆኑን ለማሳየት በመከላከያነት አንስቶ መከራከሩን የስር ፍ/ቤቱ ውሳኔ ግልባጭ ያሳያል። ይህ ብቻ ሳይሆን ተጠሪ ለስራ ስንብቱ ምክንያት ከሆነው ጋር በተያያዘ በፈፀሙት የወንጀል ድርጊት ተከሰው በወንጀል ችሎት ጥፋተኛ ስለተባሉ እና ይህ የወንጀል ችሎት ጥፋተኝነት ውሳኔም ለጉዳዩ አግባብነት ስላለው ቀርቦ ይታይልን በማለት አመልካች ፍ/ቤቱን በክርክሩ ሂደት መጠየቁንም ተገንዝበናል። ሆኖም ግን ፍ/ቤቱ በጭብጥነት የተያዘው ጉዳይ ተጠሪ ወደ ስራ ለመመለስ ፍቃደኛ ነበሩ?ወይስ አይደለም?የሚል እንጂ የተጠሪ በወንጀል ጥፋተኛ መሆን ጉዳይ አይደለም በማለት የአመልካችን ጥያቄ ሳይቀበለው አልፏል።ይሁን እንጂ ይህ በወንጀል ችሎቱ በተጠሪ ላይ የተሰጠው የጥፋተኝነትውሳኔ አመልካች ስር ፍ/ቤት ካቀረበው መከራከሪያ ነጥብ አኳያ ለጉዳዩ አግባብነት ያለው ሆኖ ሳለ ፍ/ቤቱ አስቀርቦ ሳይመለከት እና ጉዳዩንም ከወንጀሉ ጥፋተኝነት ውሳኔ ጋር አገናዝቦ ከመረመረ በኃላ በጉዳዩ ላይ ውሳኔ መስጠት ነበረበት።
በመሰረቱ ተጠሪ የአመልካችን ማህተም እና እንዲሁም የድርጅቱን ስራ አስኪያጅ ቲተር አስመስሎ ሐሰተኛ የስራ ልምድ አሰርተው እና ይሄንኑ ሐሰተኛ ሰነድም ልላ ቦታ ለስራ መወዳደሪያነት አለአግባብ በመጠቀም በፈጸሙት ወንጀል ድርጊት ተከሰው በኢ.ፍ.ዲ.ሬ የወንጀል ህግ አንቀጽ 378 ድንጋጌን በመተላለፍ በሐሰተኛ ሰነድ መገልገል ወንጀል ጥፋተኛ ተብለው መቀጣቱ የተረጋገጠ ጉዳይ ነው። በሰበር አጣሪ ችሎቱ ትዕዛዝ ቀርቦ ከዚህ መዝገብ ጋር እንዲያያዝ የተደረገው የወንጀል መዝገብም ይሄንኑን ያስገነዝባል።
ይህ የተጠሪ ጥፋትም በአዋጅ ቁ.377/96 አንቀጽ 27(1)(ሐ) ስር እንደተመለከተው በስራ ላይ የማታለል ወይም የማጭበርበር ድርጊት መፈፀም የሚለውን የሚያሟላከመሆኑም በላይ በአዋጁ አንቀጽ 27(1)(መ) ስር እንደተመለከተውም ተጠሪ የማይገባ ብልፅግና በመሻት የአመልካች ንብረት በሆነው ማህተም በድርጅቱ ስራአስኪያጅ ቲተር እና በድርጅቱ ስም አላአግባብ መጠቀም ድርጊት እና ጥፋትመፈፀሙን የሚያሳይ ሲሆን አመልካቹ ከዚህ ምክንያት ጋር በተያያዘ በተጠሪ ላይ የወሰደው የስንብት እርምጃም ከእነዚህ የአዋጁ ድንጋጌዎች አኳያ ህጋዊ ላሆን የማይችልበት ምክንያት የለም። በመሆኑም የስር ፍ/ቤቶች የተጠሪ ስራ ውል የተቋረጠው ከህግ አግባብነት ውጭ ነው ሲሉ የሰጡት ውሳኔ ከዚህ በላይ በተገለፁት ምክንያቶች መሰረታዊ የህግ ስህተት ያለበት ስለሆነ ተከታዩን ውሳኔ ሰጥተናል።
የፍድራል መጀመሪያ ደረጃ ፍ/ቤት በኮ/መ/ቁ.72453 በ29/8/05ዓ.ምየሰጠው ፍርድ እና የፍድራሉ ከ/ፍ/ቤትበኮ/መ/ቁ.135773 በ23/11/05ዓ.ም. ይህንኑን በማፅናት የሰጠው ትዕዛዝ በፍ/ብ/ስ/ስ/ህ/ቁ.348(1)መሰረት ተሻሽሐል።
የተጠሪ ስራ ውል የተቋረጠው በህጉ አግባብ ነው ብለናል።
አመልካች ለተጠሪ የ6ወር የካሳ ክፍያ፤የስንብት እና የማስጠንቀቂያ ጊዜ ክፍያ ላከፈል አይገባም ብለናል።
ነገር ግን የስር ፍ/ቤቶች የዓመት ረፍት ፍቃድንና ምስክር ወረቀትን አስመልክቶ የሰጡት የውሳኔ ክፍል ብቻ በፍ/ብ/ሥ/ሥ/ህ/ቁ.348(1) መሰረት ፀንቷል።
ግራ ቀኙ የሰበር ወጪና ኪሳራ የየራሳቸውን ይቻሉ ብለናል።
ከስር ፍ/ቤት የቀረበው የወንጀል መዝገብ ይመለስ።
በዚህ መዝገብ ላይ የተሰጠው የአፈፃፀም እግድም ተነስቷል።ይፃፍ
የዚህ ውሳኔ ግልባጭ ለስር ፍ/ቤት ይድረስ።
መዝገቡ ተዘግቷል ወደ መዝገብ ቤት ይመለስ።
No topics extracted.