No summary available.
ሰኔ 03 ቀን 2006 ዓ.ም.
ዳኞች፡- አልማው ወል ዓላ መሐመድ ረታ ቶሎሳ አዳነ ንጉሤ ሙስጠፋ አህመድ አመልካች፡- አቶ አየለ ሚናሞ - ቀረቡ።
ተጠሪ፡- አቶ አሰፋ ባዩ -ተወካይ አቶ ዘርይሁን ሞገስ - ቀረቡ።
መዝገቡን መርምረን የሚከተለውን ፍርድ ሰጥተናል።
የአሁኑ ተጠሪ ተወካይ በጠበቃቸው አማካኝነት ግንቦት 7 ቀን 2004 ዓ/ም በተጻፈ አቤቱታ የአሁን አመልካች ተጠሪው በልለበት የንብረት ግምት ክስ አቅርበው በመ/ቁ/06973 በቀን 15/01/2004 ዓ.ም በዋለው ችሎት ብር 95,067. ተጠሪው እንዲከፍላቸው በማስወሰን የተጠሪን ይዞታ በስማቸው ማዛወራቸውን ሚያዚያ 22 ቀን 2004 ዓ/ም ተጠሪ ባቀረቡት ክርክር መነሻ አመልካቹ ውሳኔውን በማስረጃነት አያይዘው በማቅረባቸው የተረዱ ስለሆነ እና ውሳኔውም መብታቸውን የሚያሳጣ በመሆኑ በፍ/ብ/ሥ/ሥ/ህ/ቁ/ 78(2) መሰረት ውሳኔው ተነስቶ ተወካዩ ወደ ጉዳዩ ገብቼ እንድከራከር ይታዘዝልኝ ብለዋል።
ለአመልካችም የተጠሪው ተወካይ አቤቱታ እንዲደርሳቸው በተደረገው መሰረት ቀርበው በ06/10/2004 ዓ/ም በዋለው ችሎት ባቀረቡት መቃወሚያ፡-ተጠሪው ለተወካዩ የሰጡት ውክልና በፍ/ሕ/ቁ/2205 መሰረት ንብረት እንዲያስተዳድሩ የተሰጠ እንጂ ተጠሪውን ወክለው በፍርድ ቤት ቆመው ለመከራከር የሚያስችላቸው ባለመሆኑ ውክልናው ተቀባይነት የለውም ሲሉ በመከራከራቸው ተወካዩም ለመቃወሚያው በሰጡት መልስ፡- ቀደም ሲል እስከ ክልሉ ጠቅላይ ፍርድ ቤት ድረስ በዚሁ የውክልና ማስረጃ ከአመልካች ጋር ስንከራከር ስለነበረ መቃወሚያው ውድቅ ተደርጎ ወደ ጉዳዩ ገብቼ እንድከራከር ይታዘዝልኝ ብለዋል።
የወንዶ ገነት ወረዳ ፍርድ ቤትም፡-በ01/12/2004 ዓ.ም በዋለው ችሎት በሰጠው ብይን፡አመልካች ቀደም ሲል ክሱን ሲያቀርቡ የተጠሪው አድራሻ አዲስ አበባ ከተማ ወረዳ 15 ቀበል 28 የቤት ቁጥሩ 171 በሚል በገለጹት መሰረት መጥሪያውን በአድራሻቸው ማድረስ ሲገባቸው ሳያደርሱ መጥሪያው ወደ ልላ አድራሻ እንዲላክ በማድረግ ውሳኔ እንዲሰጥ ያደረጉ ስለሆነ ውሳኔው በፍ/ብ/ሥ/ሥ/ህ/ቁ. 78(2) መሰረት ተነስቶ የተጠሪው ተወካይ ወደ ጉዳዩ ገብተው ላከራከሩ ይገባል ሲል በይኗል።
ከዚህ ብይን በኋላ የአሁኑ አመልካች ባቀረቡት አቤቱታ፡- በዋናው ጉዳይ ላይ ተጠሪው በልሉበት ክርክር ተካሂዶ ፍርድ ከተሰጠ በኋላ የአፈጻጸም ክስ አቅርቤ ተጠሪው በልሉበት ፍርዱ እንዲፈጸም ትዕዛዝ ተሰጥቶ ቤቱን እና ቦታውን ተረክቤ ወደ ስሜ ተዛውሮ የይዞታ ማረጋገጫ የምስክር ወረቀት ተሰጥቶኝ ጉዳዩ ተጠናቆ ሳለ በፍርድ በተጠናቀቀ ጉዳይ ክርክሩ ላቀጥል አይገባም፣ለተጠሪው ተወካይ ተጠሪው ውክልና የሰጡት በ1996 ዓ.ም ሲሆን ክሱ በቀረበ ጊዜም ተጠሪው ቀርበው እንዲከራከሩ በጋዜጣ ጥሪ ተደርጎ መቅረብ ስላልቻሉ በሕይወት መኖራቸውን ስለምጠራጠር በፍ/ብ/ሥ/ሥ/ህ/ቁ.65(1) መሰረት ራሳቸው እንዲቀርቡ ይታዘዝልኝ ሲሉ በመከራከራቸው የተጠሪው ተወካይም በጉዳዩ ለመከራከር የሚያስችለኝ ሙሉ ውክልና እያለኝ ዋናውን ባለጉዳይ ማቅረብ አስፈላጊ ስላልሆነ አመልካች ያቀረበው መቃወሚያ ተቀባይነት የለውም ሲሉ መልስ በመስጠታቸው ፍርድ ቤቱም 01/04/2005 ዓ/ም በዋለው ችሎት በሰጠው ብይን፡- ከመዝገቡ ማጣራት እንደተቻለው ተጠሪው ቀደም ሲል የተሰጠው ውሳኔ ተነስቶ እንደገና እንዲከራከሩ በፍ/ብ/ሥ/ሥ/ህ/ቁ. 78(2) መሰረት የተፈቀደላቸው ሆኖ ሳለ የፍርድ ባለመብቱ (የአሁን አመልካች) እንደገና መቃወሚያ ማቅረባቸው ተገቢ ባለመሆኑ ተጠሪው በፍ/ሥ/ሥ/ህ/ቁ/78(2) በተፈቀደላቸው መሰረት በተወካያቸው በዋናው ጉዳይ መከራከር ይችላሉ ሲል አመልካች ያቀረቡትን ክርክር ውድቅ አደርጓል።
አመልካችም በዚሁ ብይን ቅር በመሰኘት ይግባኙን ለሲዳማ ዞን ከፍተኛ ፍርድ ቤት ያቀረቡ ሲሆን ፍርድ ቤቱም የግራ ቀኙን ወገን ካከራከረ በኋላ የወረዳውን ፍርድ ቤት ብይን ያጸናው ሲሆን ጉዳዩ በሰበር የቀረበለት የደቡብ/ብ/ብ/ሕ/ክ/መ/ጠ/ፍርድ ቤትም የግራ ቀኙን ክርክር ከሰማ በኋላ በሥር ፍርድ ቤቶች ብይን ላይ የተፈጸመ የህግ ስህተት የለም ሲል አጽንቷል።
አመልካች ለዚህ ችሎት ባቀረቡት የሰበር አቤቱታም በዋናነት የጠቀሱት የቅሬታ ነጥብ ሲጠቃለል፡- የተጠሪው ተወካይ ጠበቃ በንብረት ግምት ላይ ተጠሪው በልለበት የተሰጠው ውሳኔ እንዲነሳላቸው በፍ/ብ/ሥ/ሥ/ህ/ቁ/ 78(1) መሰረት አቤቱታ አቅርበው መዝገቡ ከአመልካች በኩል የሚቀርበውን መልስ ለመቀበል እና የቃል ክርክር ለማድረግ በተቀጠረበት ቀን የተጠሪ ተወካይ በመቅረባቸው የውክልናው ማስረጃ በወካዩና በተወካዩ መካከል የዝምድና ትስስር ሳይኖር የተሰጠ መሆኑን፤እንዲሁም የውክልና ማስረጃው በፍ/ሕ/ቁ/2205(2) መሰረት ተወካዩ በፍርድ ቤት ቀርቦ ለመከራከር በሚያስችል መልኩ የተሰጠ ባለመሆኑ ተወካዩ ተጠሪውን ወክለው ለመከራከር የሚያስችል ውክልና ማስረጃ የላቸውም በሚል ክርክር ከማቅረብም ልላ ዋናው ባለጉዳይ በህይወት መኖር አለመኖራቸውን ስለምጠራጠር በፍ/ብ/ሥ/ሥ/ህ/ቁ. 50(1) መሰረት ቀርበው እንዲከራከሩ እንዲታዘዝ በሚል ላቀረብኩት ክርክር የወረዳው ፍርድ ቤት የውክልና ማስረጃው ተወካዩ ክርክር ለማድረግ የሚያስችላቸው መሆን ስላለመሆኑ በዝምታ በማለፍ ቀደም ሲል የተሰጠውን ውሳኔ በፍ/ብ/ሥ/ሥ/ህ/ቁ.58(2) መሰረት በማንሳት ክርክሩ እንዲቀጥል መበየኑና በይግባኝ እና በሰበር በየደረጃው ያሉ የክልሉ የበላይ ፍርድ ቤቶችም ማጽናታቸው ተቀባይነት የለውም የሚል ነው።
የተጠሪው ተወካይ በሰጡት መልስ፡- በውክልናው ማስረጃው ለክርክሩ መነሻ የሆነውን የተጠሪን ንብረት በተመለከተ ክስ እንዳቀርብ፣መልስ እንድሰጥ እና ክርክር ለማድረግ በግልጽ ሥልጣን የተሰጠኝ በመሆኑ፤ እንዲሁም በዚሁ የውክልና ማስረጃም ተጠሪውን በመወከል ያሰጠሁትን ውሳኔ መሰረት በማድረግ አመልካች ያቀረቡት ክስ በመሆኑ ቀደም ሲል በተደረጉት ክርክሮች አንድም ቀን የውክልና ማስረጃውን በመቃወም ያቀረቡት ክርክር ሳይኖር አሁን ግን ማስረጃው ተቀባይነት የለውም ሲሉ ያቀረቡት ክርክር ተገቢ ባለመሆኑ የሰበር አቤቱታቸው ውድቅ ላደረግባቸው ይገባል ብለዋል።
አመልካችም ለተጠሪው የመልስ መልስ ከማቅረባቸውም ልላ ይህ ችሎት የግራ ቀኙን ወገኖች የቃል ክርክር ሰምቷል።
የጉዳዩ አመጣጥ ከዚህ በላይ የተመለከተው ሲሆን እኛም፡- አመልካች የተጠሪው ተወካይ የያዙት የውክልና ማስረጃ ክርክሩን ለማድረግ የሚያስችላቸው አይደለም ሲሉ ያቀረቡትን ክርክር የስር ፍርድ ቤቶች በማለፍ ቀደም ሲል የተሰጠውን ውሳኔ በማንሳት ተወካዩ ክርክሩን እንዲቀጥሉ ብይን የሰጡት በአግባቡ ነው? ወይስ አይደለም? የሚለውን ጭብጥ ይዘን ክርክሩን እንደሚከተለው መርምረናል።
ባለጉዳዩ ራሱ ቀርቦ እንዲከራከር ፍርድ ቤቱ ካላዘዘ ወይም ራሱ እንዲቀርብ የሚያስገድድ ህግ ከልለ ራሱ ለመቅረብ የማይችል ወይም የማይፈቅድ ሰው ሲሆን ነገሩን ለማስረዳት፣ለመከራከር፣ለሚጠየቀው ሁሉ በቂ መልስ ለመስጠት የሚችል ሰው በዋናው ባለጉዳይ ተተክቶ በነገረ ፈጅነት፣በወኪልነት እና በጠበቃነት እንዲከራከር ለማድረግ እንደሚችል በፍ/ብ/ሥ/ሥ/ህ/ቁ. 57 ከተደነገገው መገንዘብ የሚቻል ነው። በዚህ በተያዘው ጉዳይ ተጠሪው ለተወካዩ በሰጡት ውክልና ሥልጣን መሰረት ተወካዩ ክርክር ሲያደርጉ የቆዩ ቢሆንም በዚህ ችሎት የቃል ክርክር በተደረገበት ወቅት በወካዩና በተወካዩ መካከል ዝምድና መኖሩን ወይም አለመኖሩ ተወካዩ እንዲገልጹ ተጠይቀው ወካዩ የአክስታቸው ልጅ እንደሆኑ የገለጹ በመሆኑ የአክስታቸውን ልጅ በመወከል ክርክር ለማቅረብም የፍ/ብ/ሥ/ሥ/ህ/ቁ58(ሀ) መብት የሚሰጣቸው ሆኖ አልተገኘም። በመሆኑም በተጠሪውና በተወካዩ መካከል ያለው የዝምድና ደረጃ በፍ/ብ/ሥ/ሥ/ህ/ቁ. 58(ሀ) የዋናው ባለጉዳይ ተወካይ ሆኖ ለመከራከር ከተቀመጠው የዝምድና ደረጃ ውጪ ሆኖ በመገኘቱ የውክልናው ማስረጃው በዚህ ድንጋጌ መሰረት የተገኘ ነው ለማለት የሚቻል አይሆንም። እንዲሁም ተወካዩ የውክልና ማስረጃ በፍ/ሕ/ቁ205 መሰረት የተሰጠ ስለመሆኑ ጠቅሰው የሚከራከሩ ቢሆንም በዚሁ ድንጋጌ መሰረት የተሰጣቸውን ተግባራት ለማከናወን ውክልናው በፍ/ብ/ሥ/ሥ/ህ/ቁ58(ሀ) የተዘረዘረውን የዝምድና ደረጃ ተከትሎ የተሰጠ ለመሆኑ ስላላረጋገጡ ወይም በፍ/ብ/ሥ/ሥ/ህግ ቁጥር 63 መሰረት መስፈርቱን አሟልተው በጠበቃነት የሚከራከሩ ስለመሆኑ በግልጽ ሳያመለክቱ በውክልና ማስረጃው ላይ የፍ/ህ/ቁ205 በመጠቀሱ ብቻ ማስረጃው ተጠሪውን ተክቶ ለመከራከር ብቁ የሚያደርጋቸው አይሆንም። በልላ በኩል ተወካዩ ቀደም ሲል በይዞታ መብት ላይ ክርክር ሲደረግ ዋናው ባለጉዳይ በመወከል እስከ ክልሉ ሰበር ሰሚ ችሎት ስከራከር እንደነበር አመልካች እያወቁ በዝምታ ቆይተው አሁን ውክልናውን ላቃወሙ አይገባም ያሉትም ቢሆን አመልካች ውክልናው ህጋዊ አለመሆኑን በመረዳት በንብረት ግምት ላይ የተሰጠው ውሳኔ እንዲነሳላቸው ተጠሪው በተወካያቸው አማካኝነት ክርክር በማቅረባቸው ያነሱት የክርክር ጭብጥ መሆኑ መቃወሚያውን ከማቅረብ የሚያግዳቸው ነገር የለም። በመሆኑም የሥር ፍርድ ቤቶች አመልካች ተጠሪው ለተወካዩ የሰጡትን ውክልና ማስረጃ በመቃወም ያቀረቡትን ክርክር ተቀብለው ዋናው ባለጉዳይ ወይም ትክክለኛ ተወካይ ቀርቦ ክርክሩን እንዲቀጥል ማድረግ ሲገባቸው የውክልና ማስረጃው ሕጋዊ መሆን አለመሆኑን ሳይመረምሩ በማለፍ ክርክሩ እንዲቀጥል ብይን የሰጡት መሰረታዊ የሆነ የህግ ስህተት የተፈጸመበት ሆኖ በማግኘታችን ተከታዩን ውሳኔ ሰጥተናል።
የወንዶ ገነት ወረዳ ፍርድ ቤት በመ/ቁ/6973 በቀን 01/04/2005 ዓ/ም በዋለው ችሎት የሰጠውን ብይን፣የሲዳማ ዞን ከፍተኛ ፍርድ ቤት በመ/ቁ/27806 በቀን 05/06/2005 ዓ.ም በዋለው ችሎት የሰጠውን ውሳኔ፣እና የደቡብ ብሕሮች፣ብሕረሰቦችና ሕዝቦች ክልላዊ መንግስት ጠ/ፍርድ ቤት ሰበር ሰሚ ችሎት በመ/ቁ. 59120 በቀን 27/09/2005 ዓ.ም በዋለው ችሎት የሰጠውን ውሳኔ በፍ/ብ/ሥ/ሥ/ህ/ቁ.348(1) መሰረት ሽረናል።
ተጠሪው ለተወካያቸው የሰጡት ውክልና ተወካዩ ተጠሪውን ተክተው ለመከራከር የሚያስችላቸው አይደለም ብለናል። ይህ ውሳኔ ዋናው ባለጉዳይ ወይም ህጋዊ ወኪላቸው ወይም ጠበቃቸው ላያቀርቡ የሚችሉትን ክርክር የሚያስቀር አይሆንም ብለናል።
የዚህን ፍርድ ቤት ወጪና ኪሳራ የግራ ቀኙ ወገኖች የየራሳቸውን ይቻሉ።
No topics extracted.