No summary available.
መጋቢት 22 ቀን 2006 ዓ.ም.
ዳኞች፡- አልማው ወል ዓላ መሐመድ ረታ ቶሎሳ አዳነ ንጉሴ ሙስጠፋ አህመድ አመልካች፡- ቱልን ዩኒቨርሲቲ አሲስታንስ ፕሮግራም ኢትዮጵያ - ጠበቃ ሰማው ንጋቱቀረቡ።
ተጠሪ፡- ዶ/ር ዮዲት አብርሃም -ቀረቡ።
መዝገቡ ተመርምሮ የሚከተለው ፍርድ ተሰጥቷል።
ጉዳዩ ከአሰሪና ሰራተኛ ጉዳይ ጋር የተያያዘ የይርጋ ክርክርን የሚመለከት ሲሆን የተጀመረውም ከሳሽ የነበሩት የአሁኗ ተጠሪ በፍ/የመ/ደ/ፍ/ቤት ተከሳሽ በነበረው የአሁኑ አመልካች ላይ በ06/08/2004 ዓ.ም ባቀረቡት ክስ ነው። የክሱም ይዘት ባጭሩ ከሳሽ ከ20/01/2001 ዓ.ም ጀምሮ በሰው ኃይል ከፍተኛ አማካሪነት የስራ መደብ በተከሳሽ ድርጅት ሲያገለግሉ ቆይተው የስራ ውላቸውን በራሳቸው ፈቃድ ከ13/02/2004 ዓ.ም ጀምረው ማቋረጣቸውን እና ተከሳሽ ድርጅት የተለያዩ ክፍያዎችን ላከፍላቸው ፈቃደኛ ሳይሆን መቅረቱን የሚገልጽ ሆኖ ያልተከፈላቸው የአራት ወር ደመወዝ፣የዓመት ዕረፍት ክፍያ፣የተጠራቀመ ፕሮፊደንት ፈንድ እና ክፍያ የዘገየበት ታስቦ እንዲከፈላቸው ይወሰን ዘንድ ዳኝነት የተጠየቀበት ነው።ተከሳሽ ድርጅት በ17/09/2004 ዓ.ም በሰጠው መልስ የይርጋ መቃወሚያ እና የፍሬ ጉዳይ መልስ ያቀረበ ሲሆን የይርጋ መቃወሚያው ይዘትም ከከሳሽ ጋር የነበረው በየጊዜው የሚታደስ የስራ ውል ለመጨረሻ ጊዜ ለሶስት ወር የተራዘመው በ22/07/2003 ዓ.ም በመሆኑ የከሳሽ የስራ ውል የተቋረጠው ከሳሽ እንደሚሉት ከ13/02/2004 ዓ.ምሳይሆን ከ23/10/2003 ዓ.ምጀምሮ መሆኑን እና ከዚህ ጊዜ ጀምሮ ክሱ እስከቀረበበት 06/08/2004 ዓ.ም ድረስ ያለው ጊዜ ሲቆጠር ደግሞ ከዘጠኝ ወር በላይ በመሆኑ ክሱ በይርጋ ላዘጋ ይገባል የሚል ነው።
ፍ/ቤቱም ክሱን ከሰማ እና የመቃወሚያ ክርክሩን ከመረመረ በኃላ በግራ ቀኙ መካከል በ21/01/2001 ዓ.ምበተደረገው የመጀመሪያ ውል ላይ የስምምነቱ ጊዜ የሚራዘመው ሁለቱም ወገኖች በጊዜው ርዝማኔ ላይ በጽሁፍ በሚያደርጉት ስምምነት እንደሆነ መገለጹን፣ተከሳሽ በ22/07/2003 ዓ.ም ፃፍኩ የሚለው የማራዘሚያ ደብዳቤ ከሳሽ ያልተስማሙበት እና ማብራሪያም የጠየቁበት መሆኑን፣በዚህም ምክንያት በግራ ቀኙ መካከል የውል ማራዘሚያ ስምምነት አለ ላባል የማይችል መሆኑን እና ከሳሽ ስራቸውን መቀጠል በመፈለጋቸው ከ23/10/2003 ዓ.ምበኃላም ስራ ላይ መቆየታቸውን ተከሳሽ ድርጅት ክሱ በተሰማበት ወቅት ያመነ መሆኑን ገልጾ የከሳሽ የስራ ውል የተቋረጠው ከሳሽ እንደሚለው በ23/10/2003 ዓ.ምጀምሮ ሳይሆን ከ13/02/2004 ዓ.ም ጀምሮ መሆኑን፣የስራ ውሉ የተቋረጠው ከ23/10/2003 ዓ.ምጀምሮ ነው በማለት ተከሳሽ ያቀረበው ክርክር ተቀባይነት ያጣ ቢሆንም ከሳሽ የስራ ውላቸውን ካቋረጡበት ከ13/02/2004 ዓ.ምጀምሮ ፍ/ቤት ቀርበው ፋይል እስካስከፈቱበት 17/08/2004 ዓ.ም ድረስ ያለው ጊዜ ሲሰላ ስድስት ወር ከአራት ቀን በመሆኑ እና በዚህም ሁኔታ ክሱ የቀረበው ይርጋው ከሞላ ከአራት ቀናት በኃላ በመሆኑ ክሱ በይርጋ ቀሪ ነው በማለት መዝገቡን በብይን ዘግቶታል።
በዚህ ብይን ቅር በመሰኘት የስር ከሳሽ ባቀረቡት ይግባኝ ሳቢያ የፍ/ከ/ፍ/ቤት የግራ ቀኙን ክርክር ከሰማ በኃላ በፍ/ሥ/ሥ/ሕ/ቁ. 213(1) ድንጋጌ መሰረት አንድ ክስ እንደቀረበ የሚቆጠረው ክስ የቀረበበት ጽሁፍ በፍ/ቤት በቀረበ ጊዜ በመሆኑ እና የክስ ማመልከቻው ለሬጅስትራር ጽ/ቤት ቀርቦ ምልክት የተደረገበት በ12/08/2004 ዓ.ምሆኖ እያለ የስር ፍ/ቤት ፋይሉ የተከፈተበትን 16/08/2004 ዓ.ምክስ የቀረበበት ቀን አድርጎ መውሰዱ ተገቢ እንዳልሆነ ገልጾ የስራ ውሉ ከተቋረጠበት ከ13/02/2004 ዓ.ምጀምሮ ክስ እስከቀረበበት 12/08/2004 ዓ.ም ድረስ ያለው ጊዜ ስድስት ወር ያልሞላው በመሆኑ ክሱ በይርጋ አይታገድም ሲል ብይኑን ሽሮ የስር ፍ/ቤት የፍሬ ጉዳይ ክርክሩን ሰምቶ ውሳኔ ይሰጥበት ዘንድ ጉዳዩን በፍ/ሥ/ሥ/ሕ/ቁ. 341(1) መሰረት በመመለስ ውሳኔ የሰጠ ሲሆን ተከሳሽ ድርጅት አቅርቦት የነበረውን መስቀለኛ ይግባኝ ደግሞ በተመሳሳይ ቀን በፍ/ሥ/ሥ/ሕ/ቁ. 337 መሰረት ዘግቶ አሰናብቷል።
አመልካች አቤቱታውን ለዚህ ችሎት ያቀረበው ይ/ሰሚው ፍ/ቤት የሰጠው ውሳኔ እና መስቀለኛ ይግባኙን በትዕዛዝ በመዝጋት የሰጠው ትዕዛዝ መሰረታዊ የሕግ ስህተት የተፈጸመበት በመሆኑ ላታረም ይገባል በማለት ሲሆን የሰበር አቤቱታው ተመርምሮ ይ/ሰሚው ፍ/ቤት አመልካች ባቀረበው መስቀልኛ ይግባኝ ላይ የግራ ቀኙን ክርክር ሳይሰማ በፍ/ሥ/ሥ/ሕ/.ቁ. 337 መሰረት የመዝጋቱን አግባብነት ከፍ/ሥ/ሥ/ሕ/ቁ. 340 ድንጋጌ አንጻር ተጠሪዋ ባሉበት ለማጣራት ይቻል ዘንድ ጉዳዩ ለሰበር ክርክር እንዲቀርብ በመደረጉ ግራ ቀኙ የጽሁፍ ክርክር ተለዋውጠዋል።የጉዳዩ አመጣጥ እና የክርክሩ ይዘት ከላይ የተመለከተው ሲሆን እኛም አቤቱታ የቀረበበት ውሳኔ መሰረታዊ የሕግ ስህተት የተፈጸመበት መሆን አለመሆኑን ለክርክሩ ከተያዘው ጭብጥ አንጻር መርምረናል።
No topics extracted.
በዚህም መሰረት በአንድ የይግባኝ ክርክር መልስ ሰጪ የሆነው ወገን በቀጥታ ይግባኝ ያላቀረበ ቢሆንም እንኳ ተገቢውን ዳኝነት ከፍሎ ይግባኝ ባዩ ባቀረበው የይግባኝ ክርክር በመልስ ሰጪነት ከሚያቀርበው ክርክር ጋር በፍርዱ ቅር የተሰኘበትን ጉዳይ በማቅረብ በይግባኝ ባይነትም ለመከራከር እንደሚችል እና በዚህ ሁኔታ የቀረበውን ይግባኝ መልስ ሰጪው ለይግባኝ ባይ ያደረሰ ስለመሆኑ መተማመኛ ካላቀረበ ማመልከቻው በመልስ ሰጪው ኪሳራ ተገልብጦ ለይግባኝ ባዩ እንዲደርስ ፍ/ቤቱ ትዕዛዝ ላሰጥ እንደሚችል በፍ/ብ/ሥ/ሥ/ሕ/ቁ. 340(1) እና (2) ተመልክቷል።በመሰረቱ አንድ ይግባኝ በሚቀርብበት ጊዜ ይግባኙ የተመሰረተው በስር ፍ/ቤት የመዝገብ ግልባጭ ላይ ብቻ ከሆነ ፍ/ቤቱ ይግባኝ ባዩን ከሰማ በኃላ መልስ ሰጪን መጥራት ሳያስፈልግ ይግባኙን ዘግቶ ማሰናበት የሚችል ስለመሆኑ እና መ/ሰጪው ወገን የሚጠራው ይግባኙ ባልተሰረዘ ጊዜ ብቻ ስለመሆኑ በፍ/ብ/ሥ/ሥ/ሕ/ቁ. 337 እና 338 ድንጋጌዎች ላይ በግልጽ ተመልክቷል።
መስቀለኛ ይግባኝ ስለሚስተናገድበት ስርዓት በሕጉ በተለየ ሁኔታ በግልጽ የተመለከተ ነገር እስከልለ ድረስ በፍ/ብ/ሥ/ሥ/ሕ/ቁ. 337 እና 338 ድንጋጌዎች የተመለከተው የክርክር አመራር ስርዓት ለመስቀለኛ ይግባኝም በተመሳሳይ ሁኔታ ተፈጻሚነት የሚኖረው በመሆኑ በፍ/ብ/ሥ/ሥ/ሕ/ቁ.340(2) በተመለከተው መሰረት መልስ ሰጪው ወገን የሚያቀርበው የይግባኝ ማመልከቻ ግልባጭ በፍ/ብ/ሥ/ሥ/ሕ.ቁ.338 መሰረት ለይግባኝ ባዩ እንዲደርስ ላደረግ የሚችለው ይግባኙ በፍ/ብ/ሥ/ሥ/ሕ/.ቁ.337 መሰረት ያልተሰረዘ በሆነ ጊዜ ብቻ ነው።በመሆኑም መልስ ሰጪው ወገን ያቀረበው የይግባኝ አቤቱታ ከተሰማ በኃላ የልላኛውን ወገን ክርክር መስማት ሳያስፈልግ ይግባኙ በፍ/ብ/ሥ/ሥ/ሕ/ቁ.337 መሰረት እንዲሰረዝ በማድረግ የሚሰጥ ትዕዛዝ በፍ/ብ/ሥ/ሥ/ሕ/ቁ. 340(2) የተመለከተውን የክርክር አመራር ስርዓት የሚቃረን ነው ለማለት የሚቻል ሆኖ አልተገኘም።
ሲጠቃለል በፍ/የመ/ደ/ፍ/ቤት የተሰጠው ብይን ከአመልካች ክርክር አንጻር ጉድለት የልለበት መሆኑን በማረጋገጥ የአሁኑ አመልካች በመልስ ሰጪነት አቅርቦት በነበረው ይግባኝ ላይ የልላኛውን ወገን ክርክር መስማት ሳያስፈልግ መስቀልኛ ይግባኙን በፍ.ሥ.ሥ.ሕ.ቁ. 337 መሰረት ዘግቶ በማሰናበት ይ/ሰሚው ፍ/ቤት የሰጠው ትዕዛዝ መሰረታዊ የሕግ ስህተት የተፈጸመበት ነው ለማለት የሚቻል ሆኖ ስላልተገኘ የሚከተለው ውሳኔ ተሰጥቷል።
337 መሰረት ዘግቶ በማሰናበት የፍ/ከ/ፍ/ቤት በመ.ቁ. 132623 በ06/10/2005 ዓ.ም የሰጠው ትዕዛዝ በፍ.ሥ.ሥ.ሕ.ቁ. 348(1) መሰረት ፀንቷል።
በፍ/የመ/ደ/ፍ/ቤት በመ. የተያዘው ክርክር ለጊዜው ታግዶ እንዲቆይ በዚህ መዘገብ በ04/03/2006 ዓ.ም ተሰጥቶ የነበረው ትዕዛዝ ተነስቷል።
የውሳኔው ግልባጭ ለስር ፍ/ቤቶች ይላክ።
የሰበር ክርክሩ ያስከተለውን ወጪና ኪሳራ ግራ ቀኙ የየራሳቸውን ይቻሉ።
ውሳኔ ያገኘ ስለሆነ መዝገቡ ተዘግቷል።