No summary available.
መስከረም 23 ቀን 2005 ዓ/ም ዳኞች፡- ተገኔ ጌታነህ ተሻገር ገ/ሥላሴ አልማው ወል ዓላ መሐመድ አዳነ ንጉሴ አመልካች፡- የኢትዮጵያ የሕግ ባለሙያ ሴቶች ማህበር - ዜናዬ ታደሰ አሰለፈች መርሻ ጠበቆች ቀረቡ ተጠሪ፡- የበጎ አድራጎት ድርጅትና ማህበራት ኤጀንሲ -ነገረፈጅ ሙዑዝ ገ/ልዑል ቀረቡ **
መዝገቡ ተመርምሮ ተከታዩ ፍርድ ተሰጥቷል።
**
ጉዳዩ በተጠሪ የታገደ ገንዘብ ይለቀቅልኝ ጥያቄ የሚመለከት ሲሆን ክርክሩ በይግባኝ ደረጃ የታየው በተጠሪ ቦርድ ነው።
በዚህ ቦርድ አቤቱታ አቅራቢ የነበረው የአሁኑ አመልካች ሲሆን የአቤቱታው ዋና ሐሳብም አመልካች ማህበር ከውጭ ካገኘው እስከ 12,000,000.00 (አስራ ሁለት ሚላዮን) ብር በጀት በመጠቀም በአዋጁና አዋጁን ለማስፈፀም በወጣው ደንብ መሰረት እስከ መጨረሻው ለመስራት ዝግጅት ሲያደርግ መቆየቱን፣ ኤጀንሲው ታህሳስ 14 ቀን 2002 ዓ/ም በጻፈው ደብዳቤ በበጎ አድራጎት ማህበሩ የባንክ አካውንት ውስጥ ከነበረው ከ10,000,000.00 (አስር ሚላዮን) ብር በላይ እንዳገደበት እና 1,596,229.00 እንደለቀቀለት፣ የአዋጅ ቁጥር 621/2001 ተፈጻሚነት ከየካቲት 06 ቀን 2002 ዓ/ም በኋላ እንደሚሆን በኤጀንሲው ተገልፆ እያለ የዝግጅት ስራ እስከዚያው ድረስ ለመጨረስ አመልካች እየተንቀሳቀሰ በነበረበት ወቅት በደንብ ቁጥር 168/2001 አንቀፅ 10 የአዋጁ አፈፃፀም መሸጋገሪያ ጊዜ ተሰጥቶ ባለበት ሁኔታ፣ አዋጁ ነባር ድርጅቶችን ቀድሞ የነበራቸውን ሀብትና ንብረት ይዘው እንዲሸጋገሩ የሚከለክሉ ድንጋጌዎች ሳይኖሩበት፣ ማህበሩ ከኪራይ ነጻ ሆኖ ለተገልጋዮች ነጻ አገልግሎቱን ለመስጠት የሚያስችለውን ቤት ለመግዛት ብር 8,600,000.00 (ስምንት ሚላዮን ስድስት መቶ ሺህ ብር) እንደሚያስፈልገው ለኤጀንሲው አቅርቦ እያለና ቀድሞ ይህን እንዳያስፈጽም በፍትህ ሚኒስቴር የማህበራት ምዝገባና ጽ/ቤት የፈቃድ እድሳት ቆሞ በመቆየቱ አመልካች ማስፈጸም ያለመቻሉን፣ በመሸጋገሪያ ጊዚ ለመጠቀም አመልካች ያቀዳቸውን ተግባራት ለማከናወን የባንክ አካውንቱ በኤጀንሲው በመታገዱ ምክንያት ማህበሩ በአስቸጋሪ ሁኔታ ውስጥ መውደቁን በመዘርዘር ቦርዱ አመልካች በመሸገገሪያ ጊዜ ለማስፈጸም ያቀዳቸውን እቅዶችን ለማሳካት፣ የድርጅት ሰራተኞችን ደመወዝ በግማሽ እንዲቀንስ አድርጎ ባለበት ሁኔታና ለጋሾች ገንዘቡን አመልካች ድርጅት ባለመጠቀሙ መልሰው እንዲወስዱት ከማድረግ በሴቶች መብት ላይ የሚሰራው አመልካች ድርጅት እንዲጠቀምበት ይወስንለት ዘንድ ዳኝነት ጠይቋል። የአሁኑ ተጠሪ በበኩሉ አመልካች በአዋጁ መሰረት የኢትዮጵያ በጎ አድራጎት ድርጅት ሆኖ መመዝገቡንና የኢትዮጵያ በጎ አድራጎት ድርጅት ደግሞ ከ10 ከመቶ በላይ ከውጭ ገቢ ምንጭ መጠቀም እንደማይችል አዋጁ የሚከለከል መሆኑንና ማኅበሩ ከውጭ የሰበሰበው በርካታ ገንዘብ የነበረው ከመሆኑም በላይ አዋጁ ከጸናበት ከየካቲት 06 ቀን 2001 በኋላም በርካታ ገንዘብ ከውጭ የገቢ ምንጮች የሰበሰበ መሆኑን፣ አዋጁ ከጸናበት ከየካቲት 06 ቀን 2001 ዓ/ም በኋላ በቀድሞ ሕጎች የተገኙ መብትና ግድታዎች ተፈጻሚ የሚሆኑት አዋጁን የማይቃረኑ ከሆኑ ብቻ ስለመሆኑ በአዋጁ አንቀፅ 111(1) መደንገጉንና ድርጅቱ ኢትዮጵያዊ በጎ አድራጎት ድርጅት ሆኖ የተመዘገበ በመሆኑ ገንዘቡን ለተሰማራበት ዓላማ መጠቀም የማይችል መሆኑን፣ በጎ አድራጎት ድርጅቱ ከአገር ውስጥ 90% የሚያመነጭ የኢትዮጵያ በጎ አድራጎት ድርጅት ሆኖ መመዝገቡን ከመመዝገቡ በፊት ከውጭ ምንጭ የሰበሰበው ገንዘብ መጠቀም ስለማይችል በኤጀንሲው መታገዱን፣ በአዋጁ መሰረት ገንዘቡን ለልላ ድርጅት ማስተላለፍ ቢቻልም ኤጀንሲው የወሰደው አቋም ግን በየአመቱ 90% ከአገር ውስጥ አመንጭቶ ለኤጀንሲው ሲያቀርብ ቀሪው 10% ደግሞ ከታገደው ገንዘብ ውስጥ እየተለቀቀለት መንቀሳቀስ እንዲችል የሚያደርግ መሆኑን ዘርዝሮ አቤቱታው ውድቅ ላሆን ይገባል ሲል ተከራክሯል። ቦርዱም የግራ ቀኙን ክርክር መርምሮ የአመልካችን ክርክር ውድቅ በማድረግ የተጠሪ እርምጃ ሕጋዊ ነው በማለት ወስኗል። የአሁኑ አመልካች በአዋጅ ቁጥር 621/2001 አንቀፅ 104 በተዘረጋው የይግባኝ ስርዓት መሰረት ይግባኙን ለፍድራሉ ከፍተኛ ፍርድ ቤት አቅርቦ ግራ ቀኙ ከተከራከሩ በኋላ የቦርዱ ውሳኔ ሙሉ በሙሉ ፀንቷል። የአሁኑ የሰበር አቤቱታ የቀረበውም ይህንኑ ውሳኔ በመቃወም ለማስለወጥ ነው። የአመልካች የሰበር አቤቱታ መሰረታዊ ይዘትም ተጠሪ አከራካሪውን ገንዘብ ለማገድ ሕጉ ስልጣን የማይሰጠው መሆኑና እገዳውም የተደረገው አመልካች ድርጅት ሕጉ ተግባራዊ ከመሆኑ በፊት በልዩ ልዩ ሁኔታና ሕጋዊ መንገዶች ከውጭ ምንጭ የተገኘ ገንዘብ መሆኑና ለቤት መግዣ እቅድ ይዞ ፈቃዱ ባለመታደሱ ምክንያት እቅዱን ተግባራዊ ለማድረግ ያልቻለ መሆኑን፣ የአመልካች የመከራከር መብት በቦርዱ በአግባቡ ያልተጠበቀለት መሆኑን ዘርዝሮ በጠቅላላው ገንዘቡ የሚታገድበት ሕጋዊ አግባብ ያለመኖሩንና የተጠሪ እርምጃም ሕገ መንግስቱንና አለም አቀፍ ሰብአዊ መብት ስምምነትን የሚጻረር ስለመሆኑ ጠቅሶ ገንዘቡ የሚታገድበት ሕጋዊ አግባብ የለም ብሎ መከራከሩን የሚያሳይ ነው። አቤቱታው ተመርምሮም በጉዳዩ ላይ የተሰጠው ውሳኔ ከአዋጅ ቁጥር 621/2001 አንቀፅ 111(1)፣ አዋጁን ለማስፈፀም በሚኒስትሮች ምክር ቤት ከወጣው ደንብ ቁጥር 168/2001 አንቀፅ 10(2) እና የፍትህ ሚኒስትር መጋቢት 16 ቀን 2001 ለተለያዩ የፍድራልና የክልል አካላት በአዋጁ መሰረት የምዝገባና የድጋሚ ምዝገባ ሥርዓት እስከሚጀምር ድረስ ነባር የበጎ አድራጎት ድርጅቶችና ማህበራት ቀደም ሲል ሲሰሩ በነበረበት ሁኔታ ስራቸውን መቀጠል እንደሚችሉ በመግለጽ ከፃፈው ደብዳቤ አንፃር ለመመርመር ሲባል ሲሆን ለተጠሪ ጥሪ ተደርጎለት ቀርቦም ግራ ቀኙ በጽሑፍ እንዲከራከሩ ተደርጓል።
የጉዳዩ አመጣጥ አጠር አጠር ባለመልኩ ከላይ የተገለፀው ሲሆን ይህ ችሎትም የግራ ቀኙን ክርክር ለሰበር አቤቱታው መነሻ ከሆነው ውሳኔ እና አግባብነት ካላቸው ድንጋጌዎች ጋር በማገናዘብ ጉዳዩን ለሰበር ችሎቱ ሲቀርብ ከተያዘው ጭብጥ አንጻር በሚከተለው መልኩ መርምሮታል።
ከክርክሩ ሂደት መገንዘብ የተቻለው አመልካች ለቦርዱ አቤቱታውን ላያቀርብ የቻለው አዋጅ ቁጥር 621/2001 ከመፅናቱ በፊትም ሆነ የምስክር ወረቀት እስከተሰጠበት እስከ ታህሳስ 07 ቀን 2002 ዓ/ም ድረስ ከውጭ የተሰበሰበውን ገንዘብ ያላግባብ አግዶብኛል፣ ይህንን ለማድረግም አዋጁም ሆነ ደንቡ አይፈቅዱለትም፤ ስልጣን አይሰጡትም በሚል ምክንያት መሆኑን ነው። በዚህ የሰበር ሰሚ ችሎት ባቀረበው የሰበር ቅሬታም ተጠሪ በሕጉ ስልጣን ያልተሰጠው ከመሆኑም በላይ የአዋጁንና የደንቡን ዝርዝር ድንጋጌዎች እንዲሁም ከፍትህ ሚኒስቴር መጋቢት 16 ቀን 2001 ዓ/ም የተፃፈው ደብዳቤ ይዘት ባላገናዘበ መልኩ እገዳውን ማከናወኑንና በቦርዱ በነበረው ክርክርም የመከራከር መብቱ በስነ ስርአት ሕጉ መሰረት ሳይጠበቅለት የቀረ ስለመሆኑ ዘርዝሮ መከራከሩን ተመልክተናል።
በመሰረቱ አዋጅ ቁጥር 621/2001 ከውጪ የሚሰበሰበው ገንዘብን መሰረት በማድረግ የበጎ አድራጎት ድርጅቶችንና ማህበራት ትርጉም፣ አይነታቸውንና ዓላማቸውን ለይቶ ገደብ ያደረገ ስለመሆኑ የሚያመላክቱ ድንጋጌዎችን ይዞ ይገኛል። ይህንኑ መለኪያ መሰረት አድርጎም አዋጁ ሶስት አይነት የበጎ አድራጎት ድርጅቶችና ማህበራት በአገሪቱ የህግ ማዕቀፍ የሚታወቁ መሆኑን የሚያሳዩ ድንጋጌዎችን አስቀምጧል። የአዋጁ አንቀፅ 2 ንዑስ ቁጥር (2)፣ ንዑስ ቁጥር (3) እና ንዑስ ቁጥር (4) ድንጋጌዎች እንደየቅደምተከተላቸው ሲታዩም የኢትዮጵያ በጎ አድራጎት ድርጅት፣ የኢትዮጵያ ነዋሪዎች የበጎ አድራጎት ድርጅት እና የውጭ የበጎ አድራጎት ድርጀት በሕጉ የሚታወቁ የበጎ አድራጎት ድርጅቶችና የማህበራት አይነቶች መሆናቸውን በመጥቀስ ትርጓሜአቸውን አስቀምጠው እናገኛለን። የእነዚህ ድንጋጌዎች ይዘትና መንፈስ ሲታይ የበጎ አድራጎት ድርጅቶና የማህበራት አይነት የሚወሰነው በመሰረታዊነት የገቢ ምንጭን በመመርኮዝ ስለመሆኑ ያስረዳል። በመሆኑም በእነዚህ ድንጋጌዎች መሰረት አንድ የበጎ አድራጎት ድርጅት ወይም ማህበር ኢትዮጵያዊ ነው ተብሎ ላመደብ የሚገባው በኢትዮጵያ ሕግ መሰረት መመስረቱ ብቻ ሳይሆን ከውጪ ምንጮች የሚገኘው የገቢ መጠን ከጠቅላላ ገቢው አስር ከመቶ (10%) የማይበልጥ ሲሆን ስለመሆኑ መገንዘብ ይቻላል። ድርጅቱ ወይም ማህበሩ ከጠቅላላ ገቢው ከአስር ከመቶ በላይ የሆነውን ገቢ ከውጭ ምንጮች ስለማግኘቱ ከተረጋገጠ የኢትዮጵያ ነዋሪ ተብሎ እንደማይመደብ በአዋጁ አንቀፅ 2(2) እና 2(3) የተቀመጡት የትርጓሜ ድንጋጌዎች ይዘትና መንፈስ ያሳያል። ሕጉ በዚህ ረገድ ያስቀመጠው የትርጉም መሰረት ድርጅቱ ወይም ማህበሩ የሚሰማራበትን ዓላማ ለመለየትም መለኪያ ስለመሆኑ የአዋጁ አንቀጽ 14 ድንጋጌ ከላይ ከተጠቀሱት የአዋጁ ድንጋጌዎች ጋር ተጣምሮ ሲነበብ የሚያስገነዝበን ጉዳይ ነው።
የአዋጁ አንቀፅ 14(2) የበጎ አድራጎት ዓላማዎችን የዘረዘረ ሲሆን በአንቀፁ ንኡስ አንቀጽ 5 ድንጋጌ ስር ደግሞ ለኢትዮጵያ የበጎ አድራጎት ድርጅቶችና ማህበራት ተለይተው የተሰጡትን ዓላማዎችን በግልፅ አስቀምጧል። በዚህ ንኡስ ድንጋጌ መሰረት ለኢትዮጵያ የበጎ አድራጎት ድርጅቶችና ማህበራት ብቻ ተለየተው የተሰጡት ዓላማዎች የሰብአዊና ዲሞክራሲያዊ መብቶች ተግባራዊነትን ማበረታታት፣ የብሕሮች፣ ብሕረሰቦችና ሕዝቦች፣ የጾታ እና የሐይማኖት እኩልነት መረጋገጥን ማበረታታት፣ የሕጻናትና የአካል ጉዳተኞች መብቶች መከበርን ማበረታታት፣ የግጭት አፈታትን ወይም እርቅን ማስፋፋት እና የፍትህና የሕግ ማስፈጸም አገልግሎቶችን ቀልጣፋነት ማጠናከር ስለመሆናቸው በግልጽ ተለይቶ ተደንግጓል። አዋጁ የበጎ አድራጎት ድርጅቶችና ማህበራት አይነትና ዓላማቸውን ለይቶ ከማስቀመጡም በላይ አዋጁን ለማስፈፀም የሚያስፈልጉ ደንቦችን የሚኒስትሮች ምክር ቤት ላያወጣ እንደሚችል፣ ተፈጻሚነት ስለማይኖራቸው ሕጎች፣ የመሻሻገሪያ ድንጋጌዎች እንዲሁም አዋጁ የሚፀናበትን ጊዜ እንደየቅደምተከተላቸው በአንቀፅ 109፣ 110፣ 111 እና በአንቀፅ 112 ስር አስቀምጧል። በዚህ አግባብም የሚኒስትሮች ምክር ቤት ደንብ ቁጥር 168/2001 አውጥቶ ከጥቅምት 30 ቀን 2002 ዓ/ም ጀምሮ ተፈፃሚ እንዲሆን ያደረገ ሲሆን አዋጅ ቁጥር 621/2001 ደግሞ ከየካቲት 06 ቀን 2001 ዓ/ም ጀምሮ የጸና ስለመሆኑ የአዋጁ አንቀጽ 112 በግልጽ ያሳያል። የአዋጁ ቁጥር 621/2001 አንቀጽ 111 ንዑስ ቁጥር (1) ድንጋጌ አዋጁ ከመውጣቱ በፊት ቀድሞ በነበረው ሕግ የተገኘ መብትና ግድታ አዋጁን እስካልተቃረነ ድረስ ብቻ እንደሚቀጥል ሲደነግግ ንዑስ ቁጥር (2) ድንጋጌ ደግሞ ቀደም ሲል የተመዘገቡ ማንኛውም የበጎ አድራጎት ድርጅቶች እና ማህበራት አዋጁ ከጸናበት ቀን ጀምሮ በአንድ አመት ጊዜ ውስጥ እንደገና መመዝገብ አለባቸው በማለት አስገዳጅነት ባለው መልኩ ደንግጓል።
ወደተያዘው ጉዳይ ስንመለስም አመልካች ድርጅት የኢትዮጵያ በጎ አድራጎት ድርጅት ሆኖ ታህሳስ 07 ቀን 2002 ዓ/ም መመዝገቡንና አዋጅ ቁጥር 621/2001 ከፀናበት ከየካቲት 06 ቀን 2001 በፊትና በኋላ በርካታ ገንዘብ ከውጭ የገቢ ምንጮች የሰበሰበ መሆኑን ፍሬ ነገርን የማጣራትና ማስረጃን የመመዘን ስልጣን ያላቸው፤ አቤቱታውን በመጀመሪያ ደረጃ የተመለከተው የተጠሪ መስሪያ ቤት ቦርድና ጉዳዩን በይግባኝ እንዲመለከት በአዋጁ አንቀፅ 104(3) መሰረት ስልጣን የተሰጠው የፍድራል ከፍተኛ ፍርድ ቤት ያረጋገጧቸው ነጥቦች ናቸው። አመልካችም በርካታ ገንዘብ ከውጭ ምንጮች አዋጁ ቁጥር 621/2001 ከመፅናቱ በፊትም ሆነ ከጸና በሁዋላ መሰብሰቡን ሳይክድ አንዱ የክርክር ነጥብ አድርጎ የሚያቀርበው ጉዳይ አመልካች ድርጅት ገንዘቡን የሰበሰበው ለቢሮ አገልግሎት የሚውል ቤት ለመግዛት ነው በሚል ነው። ይሁን እንጂ አመልካች አዋጅ ቁጥር 621/2001 ከመውጣቱ በፊት በማህበርነት ተመዝግቦ ሲሰራ የነበረ ሲሆን አዋጅ ቁጥር 621/2001 ከወጣ በኋላ በአዋጁ በተዘረጋው ስርዓት መሰረት ዳግም የተመዘገበ በመሆኑ አዋጁ ከጸና በኋላ በአዋጁ ለኢትዮጵያ ማህበር የተፈቀዱትን ዓላማዎች መስራት ያለበት በአዋጁ መሰረት በመሆኑና ይህንኑ ዓላማ ለማስፈጸም ደግሞ ቀድሞ ከውጭ የገቢ ምንጭ ያገኘውን ገንዘብ ለመጠቀም የሚችልበት አግባብ የለም በማለት ቦርዱና ይግባኙን የተመለከተው ከፍተኛ ፍርድ ቤት ያረጋገጡት ጉዳይ በመሆኑ ገንዘቡ ለቤት ግዥ ዓላማ የሚውል ነበር በማለት የሚያቀርበው ክርክር የክርክሩን ሂደት እና ለዚህ ችሎት በኢ.ፍ.ዲ.ሪ ሕገ መንግስት አንቀፅ 80(3(ሀ)) እና አዋጅ ቁጥር 25/1988 አንቀፅ 10 መሰረት የተሰጠውን የመሰረታዊ ሕግ ስህተት ማረም ስልጣን ያላገናዘበ የፍሬ ነገር ክርክር ሁኖ ስለአገኘን የምንቀበለው ሁኖ አልተገኘም።
እንዲሁም አዋጁ በአንቀጽ 108 ስር አንድ የበጎ አድራጎት ድርጅት ወደ ልላ በጎ አድራጎት ድርጅት አይነት ላቀይር ከፈለገ የሚችል ስለመሆኑ የሚያሳይ ሲሆን አዋጁን ለማስፈፀም በወጣው ደንብ ቁጥር 168/2001 አንቀፅ 18(3) ድንጋጌ ስር ደግሞ አንድ የበጎ አድራጎት ድርጅት ከውጪ ምንጭ ያገኘውን ገንዘብ ይዞ በሕጉ አግባብ ኢትዮጵያዊ ለመባል የማይችል ስለመሆኑ የተመለከተ በመሆኑ አመልካች በአዋጁ መሰረት እንደገና መመዝገቡ ከውጭ በጎ አድራጎት ድርጅትነት ወደ ኢትዮጵያዊ የበጎ አድራጎት ድርጅት እንደተቀየረ አያስቆጥረውም በማለት የሚያቀርበው ክርክር በአዋጁ የበጎ አድራጎት ድርጅት ኢትዮጵያዊ ለመባል መሟላት ያለባቸውን ቅድመ ሁኔታዎችና ለኢትዮጵያዊ በጎ አድራጎት ድርጅት ወይም ማህበር በሕጉ የተፈቀዱለትን ዓላማዎች አይነት ሳይለይ የቀረበ ክርክር በመሆኑ ተቀባይነት ያለው አይደለም።
ልላው አመልካች አጥብቆ የሚከራከረው ነጥብ ደንብ ቁጥር 168/2001 አንቀጽ 18 ተፈጻሚነት የሚኖረው በአዋጁ መሰረት ድርጅቱ ወይም ማህበሩ ፈቃድ አግኝቶ ከተመዘገበ በኋላ ነው በሚል ነው። ይሁን እንጂ አመልካች አዋጁ ቁጥር 621/2001 ከመውጣቱ በፊት በሕጉ አግባብ ተመዝግቦ ሲሰራ የነበረ ሲሆን አዋጁ ከወጣ በኋላ ዳግሞ ተመዝግቦ በአዋጁ ለኢትዮጵያዊ ድርጅት ወይም ማህበር የተፈቀዱትን ዓላማዎችን ይዞ እንደሚንቀሳቀስ በፍሬ ነገር ደረጃ የተረጋገጠ በመሆኑ አዋጁ ከፀናበት ከየካቲት 06 ቀን 2001 ዓ/ም ጀምሮ ከውጭ ምንጭ ከ10% በጀት በላይ መሰብሰብ የሚችልበት አግባብ የልለ መሆኑን የአዋጁን አንቀጽ 2(2)(3)፣ 14(5) እና የደንብ ቁጥር 18(3) ድንጋጌዎችን አንድ ላይ በምናነብበት ጊዜ የምንረዳው ጉዳይ ነው። ስለሆነም በዚህ ረገድ የቀረበው የአመልካች ክርክርም የሕግ መሰረት ያለው ሁኖ ስላላገኘን የምንቀበለው ሁኖ አልተገኘም።
አመልካች ከታገደው ገንዘብ ውስጥ ብር 4,987,781.20 ያህሉ አዋጁ ከመፅናቱ በፊት የተሰበሰበ መሆኑን፣ ቀሪው ገንዘብም በችሮታ ጊዜ የተሰበሰበ በመሆኑ አዋጁንና ደንቡን ይቃረናል ላባል አይችልም፣ የምዝገባ ውጤቱም ከታህሳስ 07 ቀን 2002 በኋላ ነው በማለትም ክርክር አቅርቧል። ለዚሁ ክርክሩ መሰረት የሚያደርጋቸው የሕግ ድንጋጌዎቹም የአዋጁ አንቀፅ 111(1) የደንቡን አንቀጽ 10(2) ድንጋጌን ነው። የአዋጁ አንቀጽ 111 ርዕሱ "የመሸጋገሪያ ድንጋጌዎች" በሚል የተቀመጠ ሲሆን ከላይ እንደተጠቀሰው ንዑስ አንቀፅ አንድ አዋጁ ከመውጣቱ በፊት ቀድሞ በነበረው ሕግ የተገኘ መብትና ግድታ አዋጁን እስካልተቃረኑ ድረስ እንደሚቀጥል ሲያስቀምጥ፣ ንዑስ ቁጥር ሁለት ድንጋጌ ደግሞ ቀደም ሲል የተመዘገቡ ማንኛውም የበጎ አድራጎት ድርጅቶች እና ማህበራት አዋጁ ከጸናበት ከየካቲት 06 ቀን 2001 ዓ/ም ጀምሮ በአንድ አመት ጊዜ ውስጥ እንደገና መመዝገብ ያለባቸው ስለመሆኑ በአስገዳጅ መልኩ ደንግጓል። የደንብ ቁጥር 168/2001 አንቀጽ 10(2) ደግሞ የድጋሚ ምዝገባ ውጤት ተግባራዊ የሚሆነው ምዝገባው በተጠናቀቀበት ጊዜ ሳይሆን አዋጁ ከጸናበት ጊዜ ከአንድ አመት በኋላ ይሆናል ሲል አስቀምጧል። እንግዲህ እነዚህ ድንጋጌዎች አንድ ላይ ሲታዩ ቅራኔ ያላቸው ናቸው ለማለት የሚቻል ሳይሆን እርስ በእርሳቸው የተጣጣሙ ናቸው። እንዲህ ከሆነ ደግሞ በመሸጋገሪያ ጊዜው ውስጥ አንድ ኢትዮጵያዊ የሆነ የበጎ አድራጎት ድርጅት ወይም ማህበር ከውጭ ምንጭ በሕጉ ከተመለከተው የገንዘብ መጠን በላይ እንዲሰበሰብ የሚፈቀድበት አግባብ የለም። ምክንያቱም የመሸጋገሪያ ድንጋጌ አይነተኛ አላማ ቀደም ሲል በነበሩ ሕጎች የተገኙ መብቶች እና ግድታዎች አዲስ ሕግ ሲወጣ አከራካሪ እንዳይሆኑ ተገቢውን ጥንቃቄ በማድረግ ግልጽ ምላሽ ለመስጠት ነው ተብሎ የሚታሰብ ሲሆን ከላይ የተጠቀሱት ድንጋጌዎች አንድ ላይ ሲታዩም ቀደም ሲል ለተገኙት መብቶችና ግድታዎች ተፈፃሚነት ያጣው ሕግ ተፈጻሚ እንዲሆን ማድረግ ሳይሆን በአዲሱ ሕግ እንዲሸፈኑ መደረጉን የሚያስገነዝቡን ናቸው። እንዲሁም ቀደም ሲል የበጎ አድራጎት ድርጅቶችና ማህበራት ምዝገባ የሕግ ማዕቀፍ የልለውና ከአዋጅ ቁጥር 621/2001 ዓላማ ጋር አንድ ላይ የማይሄድና የማይጣጣም በመሆኑና እንደ አይነታቸውና ባሕርያቸው በተለያዩ ድንጋጌዎች ስለሚገዙ አዋጁ በወጣ በአንድ አመት ጊዜ ውስጥ እንደገና መመዝገብ አስፈላጊ መሆኑ መደንገጉ አዋጁ ከፀናበት ጊዜ ጀምሮ በአዋጁ የተከለከሉ ዓላማዎችን በቀድሞው ሕግ መሰረት ማከናወን መቀጠል የማይቻል ስለመሆኑ የሚያስረዳ ነው። አመልካች መጋቢት 16 ቀን 2001 ዓ/ም የፍትሕ ሚኒስቴር ፃፈ የሚለውን ደብዳቤ ይዘት ጠቅሶ ያቀረበውን ክርክር ስንመለከተውም የደብዳቤው ይዘት አዋጅ ቁጥር 621/2001 መፅደቁን አስታውሶ መንግስት በአዋጁ መሰረት የበጎ አድራጎት ድርጅቶችና ማህበራትን የሚመዘግብና የሚከታተል የበጎ አድራጎት ድርጅቶችና ማህበራት ኤጀንሲ ለማቋቋም በሂደት ላይ ያለ ስለመሆኑ ጠቅሶ ኤጀንሲው ተቋቁሞ በአዋጁ መሰረት የምዝገባና የድጋሚ ምዝገባ ሥርዓት እስከሚጀምሩ ድረስ ነባር የበጎ አድራጎት ድርጅቶችና ማህበራት ከዚህ በፊት ይሰሩ በነበሩበት ሁኔታ እየሰሩ መቀጠል እንደሚችሉ ለሚመለከታቸው የአስፈጻሚ አካላት ስርኩላሩ መተላለፉን የሚያሳይ ነው። ይህ ሰርኩላር ይዘቱ የሚያስገነዝበው የአዋጁን አፈጻጸም ተግባራዊ ለማድረግ ይቻል ዘንድ ኤጀንሲው እስከሚቋቋም ድረስ የሚመለከታቸው አካላት ላያከናውኑ የሚገባቸውን ተግባራት የሚያሳይና አዋጁን ለማስፈፀም ይቋቋማል የተባለ ኤጀንሲ ከተቋቋመ በኋላ ግን ሁሉም ነገር በአዋጁ መሰረት መሰራት ያለበት መሆኑን የሚያስረዳ በመሆኑ አመልካች በአዋጁ አንቀጽ 2(2) እና 111(2)፣ በደንቡ አንቀጽ 10(2) ድንጋጌዎች መሰረት በችሮታው ጊዜ የራሱን አደረጃጀት በማስተካከል ያልተጠናቀቁ ስራዎችን ለማጠናቀቅ እንዲችል ሕጉ በሰጠው ችሮታ ጊዜ መንቀሳቀስ የሚገባበት እንጂ ገቢውን ከአዋጁ ይዘትና መንፈስ ውጪ እንዲሰበስብ እድል የሚሰጠውና የአዋጁን አላማ ውጤት አልባ በሚያደርግ መልኩ ተፈጻሚ የሚሆን አይሆንም።
አመልካቹ ተጠሪ በአዋጁ አንቀፅ 90 ስር ሰፊ ስልጣን የተሰጠው መሆኑን በማመን የተጠሪ እርምጃ ሕገ ወጥ ነው በማለት የሚከራከረው ተጠሪ ገንዘቡን ማገድ የሚችለው አዋጁ ተፈጻሚ ከሚሆንበት ጊዜ በኋላ ጀምሮ ተገቢ ያልሆነ የስራ አመራር ተፈጽሞ ሲያገኝና ድርጅቱን ከአደጋ ለመጠበቅ አስፈላጊ ሁኖ ሲያገኘው ነው በሚል ምክንያት ነው።
ተጠሪ በሕግ ተቋቁሞ አዋጅ ቁጥር 621/2001 እንዲሁም አዋጁን ለማስፈጸም በሕጉ አግባብ ስልጣን የተሰጠው አካል ያወጣቸውን ደንቦች ለማስፈጸም የሚችል ስለመሆኑ በአዋጁ አንቀፅ 6 ስር ከተዘረዘሩት ስልጣንና ተግባራት ይዘት የምንገነዘበው ጉዳይ ሲሆን ዓላማዎቹን ለማሳካት አስፈላጊ የሆኑ ልሎች ተግባሮችን መፈጸም እንደሚችል በተጠቃሹ አንቀፅ ፊደል "ቸ" ስር ከተቀመጠው ድንጋጌ ይዘትና መንፈስ ማየት የምንችለው ጉዳይ ነው። በአዋጁ አንቀፅ 90 መሰረት ለኤጀንሲው የተሰጠውን ስልጣን ስንመለከተው በተጠቃሹ የአዋጁ ድንጋጌ የንብረት ጥበቃ ወይም እገዳ ተግባር የሚፈፀመው ተገቢ ያልሆነ የስራ አመራር በበጎ አድራጎት ድርጅት ወይም በማህበር መፈጸሙ ሲረጋገጥ ስለመሆኑ የድንጋጌው ይዘት ያሳያል። በተያዘው ጉዳይ ተጠሪ የአመልካችን ገንዘብ ያገደው በአዋጁ አንቀፅ 90 መሰረት ተገቢ ያልሆነ የስራ አመራር በአመልካች ተፈጽሟል በሚል አይደለም። ይልቁንም በሕጉ ተለይቶ የተሰጠው ዓላማ አመልካች ኢትዮጵያዊ የበጎ አድራጎት ድርጅት የሚያደርገው ሁኖ እያለ አዋጁ ከጸናበት ጊዜ በፊትም ሆነ በኋላ ከውጪ ምንጭ በርካታ ገንዘብ ሰብስቧል፣ አመልካች ዓላማው ኢትዮጵያዊ ድርጅት ሁኖ እስከተመዘገበ ድረስ ይህንኑ ከውጪ የተገኘውን ገንዘብ ለዓላማው ማስፈፀሚያነት ላያውለው አይችልም በሚል ነው። እንዲህ አይነት ተግባር ተፈጽሞ ሲገኝ መፍትሕው ምን እንደሆነ አዋጁን ለማስፈፅም የወጣው ደንብ ቁጥር 168/2001 አንቀጽ 18 ምላሽ ይሰጣል። ይህ የደንቡ ድንጋጌ በኢትዮጵያ ውስጥ በአዋጁ መሰረት ፈቃድ አግኝቶ የተመዘገበ የውጭ የበጎ አድራጎት ድርጅት ወይም የኢትዮጵያ ነዋሪዎች የበጎ አድራጎት ድርጅት ወይም ማህበር በበላይ አካሉ ውሳኔ ወደ ኢትዮጵያ በጎ አድራጎት ድርጅትነት ወይም ማህበርነት ላቀየርና የምስከር ወረቀት ላያገኝ እንደሚችል በንዑስ ቁጥር አንድ በግልፅ ያስቀመጠ ሲሆን ማንኛውም የውጭ የበጎ አድራጎት ድርጅት ወይም የኢትዮጵያ ነዋሪዎች የበጎ አድራጎት ድርጅት ወይም ማህበር ወደ ኢትዮጵያ የበጎ አድራጎት ድርጅትነት ወይም ማህበርነት ሲለወጥ በባለቤትነቱ ስር ያለን ከውጭ ምንጭ የተገኘን ሀብት ለተለወጠው የበጎ አድራጎት ድርጅት ወይም ማህበር ላያስተላልፍ እንደማይችል፣ በንዑስ ቁጥር አንድ ድንጋጌ መሰረት ወደ ኢትዮጵያ የበጎ አድራጎት ድርጅትነት ወይም ማህበርነት ለመለወጥ ያመለከተ የውጭ የበጎ አድራጎት ድርጅት ወይም የኢትዮጵያ ነዋሪዎች የበጎ አድራጎት ድርጅት ወይም ማህበር የነበረው ከውጭ ምንጭ የተገኘን ሀብት በድርጅቱ የበላይ አካል ወይም በኤጂንሲው ውሳኔ ተመሳሳይ ዓላማ ላለው የውጪ የበጎ አድራጎት ድርጅት ወይም የኢትዮጵያ ነዋሪዎች የበጎ አድራጎት ድርጅት ወይም ማህበር መተላለፍ እንደአለበት የአንቀፁ ንዑስ ቁጥር ሁለትና ሶስት እንደየቅደምተከተላቸው ኃይለ ቃልን በያዘ አቀራረፅ ያስቀመጡት ጉዳይ ነው። በመሆኑም አመልካችን አይነት የበጎ አድራጎት ድርጅት ህጉ ከመፅናቱ በፊትም ሆነ በኋላ ከሕግ ውጪ ከውጭ ምንጭ የሰበሰበውን ገንዘብ ተጠሪ በሕጉ በተሰጠው ስልጣን መሰረት ተመሳሳይ ዓላማ ላለው ድርጅት ወይም ማህበር ማስተላለፍ እንደአለበት የደንቡ አንቀጽ 18(3) በግልጽ ያሳያል። እንግዲህ በአመልካች የተፈፀመው ተግባር ላይ ተጠሪ በሕጉ ላያደርገው ይገባ የነበረው ገንዘቡን ከማገድ የበለጠ ውጤት ያለውን፤ ገንዘቡን ለልላ ተመሳሳይ ድርጅት ወይም ማህበር ማስተላለፍን የሚያሳይ ነው። እንዲህ ከሆነ ከህጉ ከተቀመጠው ያነሰ እርምጃ ተጠሪ መውሰዱ አመልካችን የጠቀመ ነው ከሚባል በስተቀር ለተጠሪ በሕግ ከተሰጠው ስልጣን አድማስ ውጪ ነው ላባል የሚችል አይደለም። የተጠሪ እርምጃ ሕገ ወጥ ላሆን የሚችለው በሕጉ ተለይቶ ከተሰጠው ስልጣንና ተግባር ውጪ ተፈጽሞ ሲገኝ እንጂ በውጤቱ በሕጉ የተሰጠው ስልጣንና ተግባር ከሚያስከትለው ያነሰና ፍትሓዊ ነው የሚለውን አስተዳደራዊ እርምጃ በመፈፀሙ ተግባሩ ከስልጣኑና ከተግባሩ አድማስ ውጪ ነው ለማለት የሚያስደፍርበት ሕጋዊ ምክንያትና አግባብ የለም። በሕግ ያልተከለከለን ተግባር መፈፀም ተቀባይነት የማያገኝበት አግባብም የለም። በመሆኑም አመልካች የተጠሪን ስልጣንና የተወሰደውን እርምጃ መሰረት አድርጎ ያቀረበው ክርክርም ከአዋጁ አንቀጽ 90 ድንጋጌዎች ይዘትና መንፈስ እንዲሁም በደንቡ አንቀጽ 18(3) ስር ከተመለከቱት እርምጃዎች ውጤት አኳያ ሲታይ ተቀባይነት ያለው ሁኖ አላገኘነውም።
እንዲሁም አመልካች የታገደውን ገንዘብ ለምን እንደሚያውለው የተለያዩ የሰነድ ማስረጃዎችን አቅርቤ ተቀባይነት አላገኙም፣ የተጠሪ መልስም እንዲደርስ አልተደረገም በማለት ያቀረባቸው የቅሬታ ነጥቦች በሰበር አቤቱታው ላይ ያነሳ ሲሆን በአመልካች በኩል ለቦርዱ ቀርቦ ያልታየለት ማስረጃ ስለመኖሩና የመከራከር መብቱም የተጣበበት ስለመሆኑ የክርክሩ ሂደት የማያሳይ ባለመሆኑ ይህ ችሎት በዚህ የክርክር ደረጃ የሚቀበላቸው የቅሬታ ነጥቦች ሁነው አልተገኙም። ይልቁንም አመልካች በቦርዱ የመከራከር እድል እንደተሰጠው ከቦርዱ ውሳኔ ማረጋገጡን፣ የአመልካች የቤት መግዛት እቅድም በቦርዱ መታየቱን፣ ሆኖም አመልካች ቀድም ሲል ከ1987 ዓ/ም ጀምሮ መቋቋሙና ከአስራ ስድስት አመታት በላይ በሚቆይበት ጊዜ ስራውን የሚያከናውንበትን ቤት ሳይገዛ በአዋጅ ቁጥር 621/2001 እና በደንብ ቁጥር 168/2001 በተሰጠው የችሮታ ጊዜ ቤቱን ለመግዛት እቅድ ማቀዱንና ለቤት መግዣ ገንዘብ ከለጋሾች ጋር አዲስ ስምምነት በማድረግ በችሮታ ጊዜ ውስጥ እንደቀድሞው ስራውን መቀጠሉን አመልካች ራሱ በፍድራል ከፍተኛ ፍርድ ቤት በነበረው ክርክር ያመነው ስለመሆኑ ፍርድ ቤቱ በውሳኔው ላይ በግልጽ ያሳፈረው ጉዳይ ስለሆነ የአመልካች ድርጅት የመከራከር መብት አልተጠበቀም፣ ገንዘቡን ለቤት ግዥ ለማዋል ይችል እንደነበር የሚያስረዱለት ማስረጃዎች አልታዩለትም በማለት የሚያቀርበው ክርከር ተቀባይነት የልለው ነው። ከሁሉም በላይ አመልካች ማህበር ረዥም አመታት ያህል ስራ ላይ የነበረና ገንዘቡን ቀድሞ ያገኘው ከሆነ የፈቃድ መታደስ መዘገየት ከቤት ግዥ እና አፈጻጸም ጋር ተያያዥነት የልለውና አሳማኝነት የልለው ምክንያት ስለመሆኑ ፍሬ ነገሩን በሚያጣራውና ማስረጃዎችን በሚመዝነው የፍድራል ከፍተኛ ፍርድ ቤት የተረጋገጠ ጉዳይ በመሆኑ ይህ ሰበር ሰሚ ችሎት በኢ.ፍ.ዲ.ሪፐብላክ ሕገ መንግስት አንቀጽ 80(3(ሀ)) እና አዋጅ ቁጥር 25/1988 አንቀጽ 10 መሰረት ከተሰጠው ስልጣን አንፃር በዚህ ረገድ የቀረቡትን የአመልካችን የቅሬታ ነጥቦች የፍሬ ነገርና የማስረጃ ምዝና ጉዳዮች በመሆናቸው የሚቀበላቸው ሁነው አልተገኙም።
ሲጠቃለልም የአመልካች ተግባር በአዋጅ ቁጥር 621/2001 አንቀፅ 2(2፣3፣እና 4)፣6፣ 14(5)፣90፣111 እና 112፣እንዲሁም በደንብ ቁጥር 168/2001 አንቀፅ 10(2)፣18(3) እና 36 ድንጋጌዎች ይዘትና መንፈስ አንፃር ሲታይ ገንዘቡ በተጠሪ እንዳይታገድ የሚያደርግበት ሕጋዊ ምክንያት ስለልለ ተጠሪ ገንዘቡን ማገዱም ሆነ አመልካች ከአገር ውስጥ የገቢ ምንጭ 90% ያህሉን መሰብሰቡ እየተረጋገጠ ከታገደው ገንዘብ ውስጥ 10% እንዲለቀቅለት መደረጉ ሕጋዊ ከሚባልና በውጤቱም ፍትሃዊ ነው ተብሎ ከሚደመደም በስተቀር መሰረታዊ የሆነ የሕግ ስህተት ያለበት ነው ለማለት አልተቻለም።በዚህም ምክንያት ተከታዩን ወስነናል።
ውሣኔ
በተጠሪ ቦርድ ተሰጥቶ በፍድራሉ ከፍተኛ ፍርድ ቤት በመ/ ጥቅምት 17 ቀን 2004 ዓ/ም የጸናው ውሳኔ በፍ/ብ/ሥ/ሥ/ሕ/ቁጥር 348(1) መሰረት በድምጽ ብልጫ ፀንቷል።
የተጠሪ እርምጃ ሕገ ወጥ ነው ላባል የሚችልበት አግባብ የለም ብለናል።
በዚህ ችሎት ለተደረገው ክርክር የወጣውን ወጪና ኪሳራ የየራሳቸውን ይቻሉ ብለናል።
ውሳኔው በ09/02/05 ዓ.ም ተነበበ።
No topics extracted.