No summary available.
ታህሣስ 18 ቀን 2006 ዓ.ም.
ዳኞች፡- አልማው ወል ዓላ መሐመድ ረታ ቶሎሣ አዳነ ንጉሴ ሙስጠፋ አሕመድ አመልካች፡- አቶ አብዱራዛቅ ኢብራሒም ቀረቡ ተጠሪ፡- የኢ.ፍ.ዲ.ሪ ፍትህ ሚኒስቴር ዐ/ህግ ድንበሩ አንዳርጌ ቀረቡ መዝገቡን መርምረን የሚከተለውን ፍርድ ሰጥተናል።
ጉዳዩ የቀረበው አመልካች የፍትህ ሚኒስቴር ሚንስትር የሚኒስትሮች ምክር ቤት ያወጣውን የዐቃቤ ሕግ መተዳደሪያ ደንብ ቁጥር 44/1991 ድንጋጌዎች በሚጥስ ሁኔታ ዐቃቤ ሕግነት ተመድቤ ሣገልገል የነበረኩትን አመልካች ከሥራ እንድስናበት ውሣኔ ሰጥቷል። የሚኒስትሩ ውሣኔም በቁጥር 02/አሰአ.128/10/1 ግንቦት 8 ቀን 2005 ዓ.ም በተፃፈ ደብዳቤ ተገልፆልኛል። የፍትህ ሚስቴር የአቃቤ ሕግ መተዳደሪያ ደንብ ቁጥር 44/1991 ከሚደነግገው ውጭ ካለአግባብ ስልጣኑን በመጠቀም ከሁለት ወር በላይ ከሥራና ከደመወዝ አግዶ አቆይቶኛል። ከሁሉም በላይ አመልካች ቀርቦብኝ የነበረውን የዲሲፕላን ክስ በበቂ ሁኔታ ሚኒስቴር መስሪያ ቤቱ ያላስረዳ በመሆኑ የመከላከያ ማስረጃ ማቅረብ ሣያስፈልገኝ በነፃ የተሰናበትኩ መሆኑን በመግለጽ የአቃቤ ሕግ አስተዳደር ዋና ጉባኤው ውሣኔ ሰጥቶ ውሣኔው በቁጥር 24/ሰ-16/91/4 ሕዳር 21 ቀን 2005 ዓ.ም በተፃፈ ደብዳቤ ገልፆልኛል። ይህንን የአቃቤ ሕግ አስተዳደር ዋና ጉባኤ ሚኒስትሩ ሲሽር ለቀረበብኝ ይግባኝ መልስ እንድሰጥ እድል እልተሰጠኝም። እንደዚሁም የአቃቤ ሕግ አስተዳደር ዋና ጉባኤ ውሣኔ ከተሻረም ጉዳዩ ወደ ጉባኤው ተመልሶ የመከላከያ ማስረጃውን የማቅረብ መብቴ ላጠበቅ ሲገባው የእኔን የመከራከርና የመከላከል መብት ሣይጠበቅ የተሰጠው ውሣኔ ደንብ ቁጥር 44/1991 እና የውሣኔ አሰጣጥ ስርዓትን የሚጥስ መሰረታዊ የሕግ ስህተት የተፈፀመበት በመሆኑ ይኸ የሰበር ችሎት በሕገ መንግስቱ አንቀጽ 80 ንዑስ አንቀጽ 3/ሀ/ እና በአዋጅ ቁጥር 25/1988 አንቀጽ 10 በተሰጠው ስልጣን መሰረት በሰበር አይቶ እንዲያርምልኝ በማለት ነሐሴ 6 ቀን 2005 ዓ.ም የተፃፈ የሰበር አቤቱታ በማቅረቡ ነው።
አመልካች ከሰበር አቤቱታው ጋር በማያያዝ የአቃቤ ሕግ አስተዳደር ዋና ጉባኤ አመልካች የዲስፕላን ጥፋት የፈፀመ ስለመሆኑ በማስረጃ ስላልተረጋገጠ ከቀረበበት የዲስፕላን ክስ የመከላከል ማስረጃ ማቅረቡ ሣያስፈልገው በነፃ የተሰናበተ መሆኑን በመግለጽ በቁጥር 24/ሰ-16/91/4 ሕዳር 21 ቀን 2005 ዓ.ም የፃፈውን ደብዳቤና በፍትህ ሚኒስቴር ሚኒስትር ድኤታ ፊርማ አመልካች ከሥራ የተሰናበተ መሆኑን በመግለጽ በቁጥር 02/አሰደ-128/10/1 ግንቦት 8 ቀን 2005 ዓ.ም የተፃፈ ደብዳቤ በማያያዝ አቅርቧል።
አመልካች ላቀረበው የሰበር አቤቱታ ተጠሪ መልስ በጽሑፍ እንዲያቀርብ በተሰጠው ትእዛዝ መሰረት ተጠሪ መስከረም 30 ቀን 2006 ዓ.ም የተፃፈ መልስ አቅርቧል። ተጠሪ የፍትሕ ሚኒስቴር ሚኒስትር የአቃቤ ሕግ አስተዳደር ዋና ጉባኤ ውሣኔ የሻረው በአቃቤ ሕግ መተዳደሪያ ደንብ ቁጥር 44/1991 አንቀጽ 78 እና አንቀጽ 79 በተሰጠው ስልጣን መሰረት ጉዳዩን በይግባኝ ለማየት ባስተላለፈው ውሣኔ መሰረት ነው። ውሣኔው በደንቡ መሰረት የተሰጠ በመሆኑ መሰረታዊ የሕግ ስህተት የለበትም በማለት ተከራክሯል። አመልካች ጥቅምት 15 ቀን 2005 ዓ.ም የተፃፈ የመልስ መልስ አቅርቧል።
የጉዳዩ አመጣጥና ግራ ቀኙ ያቀረቡት ክርክር ከላይ የተገለፀው ሲሆን እኛም የኢ.ፊ.ድ.ሪ ፍትህ ሚኒስቴር ሚኒስትር የአቃቤ ሕግ አስዳደር ዋና ጉባኤ የሰጠውን ውሣኔ የሻረው አስገዳጅነት ያላቸውን የሕግ ሥርዓቶች በመከተልና የደንብ ቁጥር 44/9/ ድንጋጌዎችን መሰረት በማድረግ ነው ወይስ አይደለም? የሚለውን ጭብጥ በመያዝ ጉዳዩን መርምረናል።
ከላይ የተያዘውን ጭብጥ ለመወሰን በመጀመሪያ የአቃቤ ሕግ መተዳደሪያ ደንብ በመጣስ የዲስፕላን ክስ የቀረበበት ዐቃቤ ሕግ በደንቡ የተጠበቁለት መሰረታዊ መብቶችን መመርመር አስፈላጊ ነው የዲስፕላን ክስ የቀረቡለት አቃቤ ሕግ ላይ ያቀረበበትን የዲስፕላን ክስ ለማጣራትና አቃቤ ሕጉ በሕጉ መጣራት ማስረጃዎችን ለማሰባሰብ አስፈላጊውን የአፈፃፀም ሥነ ሥርዓት መጠቀም እንዳለበት በደንቡ አንቀጽ 82 ንዑስ አንቀጽ 1 መሰረታዊ መርህ ሆኖ ተደንግጓል። ጉባኤው ይህንን የማጣራት ግድታውውን በመወጣት ከተገቢ የውሣኔ ሃሣብ ላይ ለመድረስ በዲስፕላን የተከሰሰው አቃቤ ሕግና መሥሪያ ቤቱ እያንዳንዳቸው ጉዳያቸውን እንዲያስረዱ ማድረግ እንዳለበት በደንቡ አንቀጽ 82 ንዑስ አንቀጽ 2 ተደንግጓል። ይህ ድንጋጌ አቃቤ ሕጉ በመስሪያ ቤቱ የቀረበለትን ክስና ማስረጃ የማስተባበልና መከላከያ የሚሆኑት ነጥቦች የማቅረብና የመከላከያ ማስረጃ የመስማት መብት ያለው መሆኑ የሚደነግግ ነው።
ከላይ ከተገለፀው በተጨማሪ ክስ የቀረበበት አቃቤ ሕግ ለቀረበበት ክስ መልስና መከላከያ ለማቅረብ እንዲቻል የቀረቡትን ክስ በዝርዝር የሚገልጽ የክስ ጽሑፍ ክሱን ለማረጋገጥ የቀረበበትን ማስረጃ መልስ የሚሰጥበት ቀን ሰዓት ቦታ ከሚገልጽ መጥሪያ ጋር እንዲደርሰው ማድረግ እዳለበት በደንቡ አንቀጽ 83 ንዑስ አንቀጽ 1 ተደንግጓል። ይህም አቃቤ ሕጉ የቀረበበትን የዲሲፕላን ክስ ለመከላከል የሚችልበትንና ማስረጃ የሚሰማበትን ቀን የማወቅ መብት ያለው መሆኑን የሚያሣይ ነው። በተያዘው ጉዳይ የአቃቤ ሕግ አስተዳደር ዋና ጉባኤ ውሣኔ የሰጠው የአመልካች የመከላከያ ማስረጃን በመስማትና በመመዘን እንዳልሆነና፣ የአቃቤ ሕግ አስተዳደር ዋና ጉባኤ የተጠሪን ምስክሮቹ ከሰማ በኃላ ተጠሪ ያቀረበውን ክስ የሚያስረዳ ማስረጃ አላቀረበም። ስለዚህ የአቃቤ ሕጉን /የአመልካችን/ መከላካያ ማስረጃ መስማት አስፈላጊ አይደለም በማለት ተጠሪ የመከላከያ ማስረጃ ሣይሰማ የተጠሪን ክስ በደንቡ አንቀጽ 84 ንዑጽ አቀጽ /ሀ/ በሚደነግገው መሰረት ውድቅ በማድረግ አመልካች በተከሰሰበት የዲስፕላን ጥፋት አልፈፀመም በማለት በነፃ ያሰናበተው መሆኑ ሕዳር 21 ቀን 2005 ዓ.ም በፃፈውና በአቃቤ ሕግ አስተዳደር ዋና ጉባኤ ውሣኔ ይዘት በሚገልፀው ደብዳቤ ለመረዳት ይቻላል።
በአቃቤ ሕግ አስተዳደር ዋና ጉባኤ ውሣኔ ቅር በመሰኘት የሚኒስቴር መሥሪያ ቤቱ ክርክር ጉዳዮች ሚኒስትር ድኤታ ይግባኝ ለፍትሕ ሚኒስትሩ ያቀረቡ መሆኑ ከግራ ቀኙ ክርክር ተረድተናል። የክርክር ጉዳዮች ሚኒስትር ድኤታ በአቃቤ ሕግ አስተዳደር ዋና ጉባኤ በሰጠው ውሣኔ ቅር በመሰኘት ይግባኝ ለሚኒስትሩ ማቅረቡ የደንቡን አንቀጽ 85 ድንጋጌዎች መሰረት ያደረገ በመሆኑ ሕጋዊነቱ ክርክር የሚያስነሣ አይደለም።
አክራካሪው የሆነው ሚኒስትር ድኤታው በአቃቤ ሕግ አስተዳደር ዋና ጉብኤ ውሣኔ ቅር በመሰኘት የቀረበውን ይግባኝ ሚኒስትሩ ያስተናገደበት ሥርዓትና ሚኒስትሩ አቃቤ ሕግ የአስዳደር ጉባኤ ውሣኔን በመሻር አመልካች ከሥራ እንዲሰናበት የሰጠው ውሣኔ በደንቡ አመልካች በአንቀጽ 82 ንዑስ አንቀጽ 2 እና አንቀጽ 83 ንዑስ አንቀጽ 1 የተሰጠውን ክስን የመከላከልና የመከላከያ ማስረጃ የማሰማት መብት በጠበቀ ሁኔታ የተሰጠ ነው ወይስ አይደለም የሚለውን ጭብጥ ነው።
ሚኒስቴር ከአቃቤ ሕግ አስተዳደር ዋና ጉባኤ የቀረበውን ይግባኝ የማያስተናግድበት ዝርዝር ሥርዓት በደንቡ አንቀጽ 85 አልተደነገገም። ሆኖም ይህ ማለት በአቃቤ ሕግ አስተዳደር ዋና ጉባኤ በዲስፒላን የሚያስከስስ በቂ ማስረጀ በሚንስትር መሥሪያ ቤቱ አልቀረበበትም ተብሎ በደንቡ አንቀጽ 86 ንዑስ አንቀጽ /ሀ/ መሰረት የዲስፒላን ክሱ የተሰራበትን አቃቤ ሕግ ያቀረበው የይግባኝ ቅሬታ ዝርዝር ይዘት አውቆ መልስ እንዲሰጥበት ሣያደርግ ሚኒስትሩ ሚኒስቴር ድኤታው ያቀረበውን የይግባኝ ቅሬታ ብቻ በማየት ውሣኔ ይሰጣል ማለት እንዳልሆነ በደንቡ አንቀጽ 82 ንዑስ አንቀጽ 2 ከተደነገው የአቃቤ ሕጉ የቀረበበትን ክስና ማስረጃ የማወቅና የመከላከያ መልስን ማስረጃውን የማቅረብ መብት ለመረዳት ይቻላል። ሚኒስቴር አመልካች ተጠቃሚ የሆነበትን የአቃቤ ሕግ አስተዳደር ዋና ጉባኤ ውሣኔ በደንቡ አንቀጽ 85 መሰረት በይግባኝ አይቶ ውሣኔውን የሚያሻሽለው ወይም የሚሽረው በሆነ ጊዜ በደንቡ አንቀጽ 82 እና አንቀጽ 83 የተደነገጉት ሥርዓቶች በመከተል አቃቤ ሕጉ የቀረበበትን ይግባኝ ማመልከቱ በጽሑፍ እንደደረሰውና መልስ እንዲሰጥበት በማድረግ የአቀቤ ሕጉን የመከራከርና የመሰማት መብት የማክበር ኃላፊነት ይኖርበታል።
ስለዚህ ምክንያቱ በደንቡ አንቀጽ 85 በሚኒስትሩ የተሰጠው የይግባኝ ስልጣን አስተዳደራዊ ስልጣን ሣይሆን የዳኝነት ነክ ስልጣን መሆኑ ነው። የዳኝነት ወይም ከፊል የዳኝነት ስልጣን በተሰጠው አካል ፊት ክርክርና ክርክሩን የሚደግፉለትን ማስረጃ የማቅረብና ፍትሕ የማግኘት መብት በሕገ መንግስቱ አንቀጽ 37 እውቅናና ጥበቃ የተሰጠው መብት ነው የዳኝነት ነክ ስልጣን በሕግ የተሰጠው አካልም ለተከራካሪዎቹ በሕገ መንግስቱ አንቀጽ 25 የተደነገገው የእኩልነትና እኩል የሕግ ጥበቃና ዋስትና የማግኘት መብት በማክበር ተከራከሪዎቹ ክርክራቸውን እንዳያቀረቡ ማድረግና ለተከሪካሪዎች እኩል እድል የመስጠትና ጉዳዩን ገለልተኛ ሆኖ የመመርመር ውሣኔ የመስጠት ግድታ አለበት ከዚህ አንፃር በያዝነው ጉዳይ ሚኒስትሩ የአቃቤ ሕግ አስተዳደር ዋና ጉባኤ የሰጠውን ውሣኔ በመቃወም መስሪያ ቤት ያቀረበው የይግባኝ ቅሬታ ለአመልካች እንዲደርሰውና መልስ እንዲሰጥበት ሣያደግ አመልካች የዲስፕላን ጥፋት አልፈፀመም ተብሎ የተሰጠውን ውሣኔ መሻሩ ከላይ በዝርዝር የገለጽነውን አስገዳጅ የሆኑ ክርክር አሰራር ሥርዓትና ሕገ መንግስታዊ ድንጋጌዎች ያልተከተለና መሰረታዊ የሕግ ስህተት የተፈፀመበት ሆኖ አግኝተነዋል።
ሚኒስትሩ መሥሪያ ቤቱ በአንቀጽ 85 መሰረት የአቃቤ ሕግ አስተዳደር ዋና ጉባኤ የሰጠውን ውሣኔ በመቃወም ያቀረበው የይግባኝ ማመልከቻ አመልካች ደርሶት መልስ እንዲሰጥበት ሣያደረግ ውሣኔውን መሻሩ የመጀመሪያ ክርክር አሰራር ሒደት የፈፀመው ስህተት መሆኑ እንዳለ ሆኖ ሚኒሰትሩ የሰጠውን ውሣኔ የሕግ ስህተት የተፈፀመበት ሆኖ አግኝተነዋል። ምክንያቱም የአቃቤ ሕግ አስተዳደር ዋና ጉባኤ በሚኒስተር መ/ቤቱ በአመልካች ላይ የቀረበውን የዲሲፕላን ክስ ውድቅ ያደረገው የዲሲፕላን ክስ የቀረበው መስሪያ ቤት አመልካች የዲስፕላን ጥፋት የፈፀመ መሆኑን በማስረዳት ያቀረባቸው ምስክሮችና ማስረጃዎች ክሱን አላስረዱም የዲስፕሉን ክስ የቀረበው አካል ክሱን በበቂ ማስረጃ ያላስረዳ በመሆኑ ተከሣሹ /የአመልካቹ/ የመከላከያ ማስረጃ መስማት አስፈላጊ አይደለም በማለት አመልካች በደንቡ አንቀጽ 82 ንዑስ አንቀጽ 2 የተጠበቀለትን የመከላከያ ማስረጃ የማቅረብና የማሰማት መብት በማለፉ እንደሆነ የሰበር አቤቱታው ጋር ተያይዞ የቀረበው የአቃቤ ሕግ አስተዳደር ዋና ጉባኤ ውሣኔን በያዙት ከሚገለፀው ደብዳቤ ተረድተናል።
ሚኒስትሩ በደንቡ አንቀጽ 85 መሰረት ጉዳዩን በይግባኝ አይቶ በሚኒስቴር መሥሪያ ቤቱ የቀረበውን የተሰማው ማስረጃ የዲስፕላን ክሱ በዚህ ሁኔታ ለማስረዳት የሚችል ነው ከሚል መደምደሚያ ላይ ከደረሰ የአቃቤ ሕግ አስተዳደር ዋና ጉባኤ ውሣኔ መሻር ጉባኤው ጉዳዩን እንደገና በማየትና አመልካች በደንቡ አንቀጽ 82 ንዑስ አንቀጽ 2 እና አንቀጽ 83 ንዑስ አንቀጽ 3 በተሰጠው የመከላከያ ማስረጃ የማቅረብና የማሰማት መብት ተጠቅሞ የሚያቀረበው የመከላከያ ማስረጃ በማስማት ጉባኤው ውሣኔ እንዲሰጥ ማድረግ ይጠበቅበታል። ሚኒስትሩ ይህንን ሥርዓት ለመከተል ካልፈገለ አመልካች ለአቀቤ ሕግ አስተዳደር ዋና ጉባኤ በመከላከያ ማስረጃ አድርጎ የቆጠራቸው ምስክሮች እዲያቀረብና እንዲያሰማ በማድረግ ልሎች የመከለካያ ማስረጃውን ተቀብሎ በመመርመር አመልካች በደንቡ አንቀጽ 82 ንዑስ አንቀጽ 2 የተሰጠውን የመከላከያ ማስረጃ የማቀረብ መብት በማክበርና በማስከበር ውሣኔ የመስጠት ኃላፊት አለበት ሚኒስተሩ የአመልካች የመከላከያ ማስረጃ የማቅረብ መብት የሚከበርበት ሁኔታ ሣይፈጥር ወይም አመልካች የመከላከያ ማስረጃውን እንዲያቀርብ እድል ሣይሰጥ የአቀቤ ሕግ አስተዳደር ዋና ጉባኤ ውሣኔን በመሻር አመልካች ከሥራ እንዲሰናበት የሰጠው ውሣኔ የአቃቤ ሕግ መተዳደሪያ ደንብ ቁጥር 44/1991 አንቀጽ 82 ንዑስ አንቀጽ 2 አስገዳጅ ድንጋጌን የሚጥስ እና መሰረታዊ የሕግ ስህተት ያለበት ሆኖ አግኝተነዋል። ከላይ በዝርዝር በገለጽናቸው ምክንያቶች ሚኒስትሩ የአቃቤ ሕግ አስተዳደር ዋና ጉባኤ ውሣኔን በመሻር አመልካች ከሥራ እንዲሰናበት የሰጠው ውሣኔ አስገዳጅ የሆኑ የክርክር አመራር ሥርዓት ያልተከተለና የአቃቤ ሕግ መተዳደሪያ ደንብ አንቀጽ 82 ንዑስ አንቀጽ 2 አንቀጽ 83 ንዑስ አንቀጽ 1 እና አንቀጽ 85 ድንጋጌዎችን መሰረታዊ ይዘት መንፈስና አላማ ያልተከተለና መሰረታዊ የሕግ ስህተት ያለበት ነው በማለት በሕገ መንግስቱ አንቀጽ 80 ንዑስ አንቀጽ 3/ሀ/ አንቀጽ 37 እና አንቀጽ 79/1/ ድንጋጌዎችን መሰረት ማድረግ ወስነናል።
ው ሣ ኔ
ሚኒስትሩ የክርክር ጉዳዮች ድኤታ ባቀረበው ይግባኝ ባይ አመልካች መልስ እንዲሰጥ ሣያደግርና የአመልካችን የመከላከያ ማስረጃ የማቅረብ መብት ሣያከብርና እንዲከበር ሣያደርግ አመልካች ከሥራ እንዲሰናበት የሰጠው ውሣኔ ተሽሯል።
በዚህ ፍርድ ቤት የወጡትን ወጭ ግራ ቀኙ ለየራሣቸው ይቻሉ።
መዝገቡ ወደ መዝገብ ቤት ይመለስ።
No topics extracted.