No summary available.
መስከረም 23 ቀን 2ዐዐ6 ዓ.ም.
ዳኞች፡- ተሻገር ገ/ሥላሴ አልማው ወል ዓላ መሐመድ ረታ ቶሎሣ ሙስጠፋ አህመድ አመልካች፡- የኮምቦልቻ ቆዳ ፋብሪካ አ/ማህበር ነ-ፈጅ አቶ አሰፋ ዓለሙ ቀረቡ ተጠሪ፡- አቶ ምስጋናው ጥሩነህ ጠበቃ አቶ ውቤ አለነ ቀረቡ መዝገቡ የተቀጠረው ለምርመራ ሲሆን፤ መርምረን ፍርድ ሰጥተናል።
የአሁን አመልካች በተጠሪ ላይ ክስ ለማቅረብ የሚያስችል ከሕግ ወይም ከውል የመነጨ መብት የለውም በሚል በሥር ፍ/ቤቶች የተሰጠውን ዳኝነት አግባብነት በክርክር ሂደት ከተረጋገጡት የፍሬ ነገር ጉዳዮችና ለጉዳዩ አግባብነት ካላቸው ድንጋጌዎች ጋር በማገናዘብ እንደሚከተለው ተመልክተናል።
እንደተመለከትነውም የአሁን ተጠሪ ለአመልካች ላከፍል ይገባል በሚል ለክሱ ምክንያት የሆነውን ገንዘብ ወሰደ የሚባለው ከኮምቦልቻ ቆዳ ፋብሪካ መሆኑንና በዚህ ገንዘብ ምክንያት ክስ በቀረበበት ጊዜ ደግሞ የኮምቦልቻ ቆዳ ፋብሪካ በሽያጭ ወደ አሁኑ አመልካች የተላለፉ ስለመሆኑ በፍሬ ነገር ደረጃ የተረጋገጠ ጉዳይ ከመሆኑም በላይ ግራ ቀኙን ያከራከረ ጉዳይ አይደለም።
አከራካሪ ነጥብ ሆኖ የተገኘው በመንግሥት እጅ የነበረ የልማት ድርጅት ከመሸጡ በፊት በሦስተኛ ወገኖች ላይ አለኝ የሚለውን ገንዘብ የልማት ድርጅቱ በሽያጭ ከተላለፈ በኋላ የመሰብሰብ መብት ያለው ማን ነው? የሚለው ነው።
ለዚሁ አከራካሪ ነጥብ አግባብነት ባለው የመንግሥት የልማት ድርጅቶችን ባለአደራ ቦርድን ለመቋቋምና ሥልጣንና ተግባሩን ለመወሰን በወጣው አዋጅ ቁጥር 2ዐ8/92 አንቀጽ 5 እና 6 ላይ “የመንግሥት የልማት ድርጅት ወደ ግል ይዞታነት፣ ወደ አክሲዮና ማህበር በሚለወጥበት ወይም ወደ ቀድሞ ባለሀብቱ በሚመለስበት ጊዜ ወደ አዲሱ ባለቤት የማይተላለፉ ተሰብሣቢ ሂሣቦችን ለመሰብሰብ፤ ዕዳዎችን ለመረከብና የፍርድ ቤት ጉዳዮችን ለመከታተል ሥልጣን የተሰጠው የመንግሥት የልማት ድርጅቶች ባለአደራ ቦርድ እንደሆነ ተደንግጓል።
በዚህም ጉዳይ የመንግሥት የልማት ድርጅት የነበረው የኮምቦልቻ ቆዳ ፋብሪካ በሽያጭ ወደ አሁን አመልካች በመተላለፉ ምክንያት የተሸጠው የኮምቦልቻ ቆዳ ፋብሪካ ከመሸጡ በፊት የነበረው ተሰብሣቢ ሂሣብና የነበረበት ዕዳ ወደ ገዥው የማይተላለፍ ሆኖ በተገኘ ጊዜ ከላይ በተጠቀሰው ሕግ መሰረት ተሰብሣቢ ሂሣቡንም ሆነ ዕዳውን በሚመለከት ለመሰብሰብም ለመረከብም ኃላፊነት እና ግድታ የተጣለበት ለመንግሥት የልማት ድርጅቶች ባለአደራ ቦርድ እንደሆነ መደንገጉ እየታወቀ የኮምቦልቻ ቆዳ ፋብሪካን በሽያጭ ወደ አሁን አመልካች እንዲተላለፍ በተደረገበት የሽያጭ ውል አንቀጽ 4.5 ላይ “ ገዥው የኮምቦልቻ ቆዳ ፋብሪካ አክሲዮን ማህበር የሸጠውን የኮምቦልቻ ቆዳ ፋብሪካን ቋሚ ንብረትንና ዕዳን ሁሉ የመረከብ ግድታ እንዳለበት ስለመደንገጉ ያከራከረ ጉዳይ አይደለም።
ይህም መሆኑ ከተረጋገጠ በአዋጅ ቁጥር 2ዐ8/92 አንቀጽ 5 እና 6 የተመለከቱት ድንጋጌዎች ተፈፃሚነት የተሸጠው የመንግሥት የልማት ድርጅት ከመሸጡ በፊት የሚሰበስባቸው ተሰብሣቢ ሂሣቦች እና ዕዳዎች በሽያጭ ውል መሰረት ወደ ገዥው የማይተላለፉ ሆኖ በተመለከተ ጊዜ ብቻ ነው። በዚህ በተያዘው የሽያጭ ውል ላይ የተሸጠው ድርጅት የነበረው ዕዳ ሁሉ ወደ ገዥው እንደሚተላለፍ በግልጽ እስከተመለከተ ድረስ ዕዳውን ተሸካሚ ከሆነ በሽያጭ ውል ከተመለከተው የድርጅቱ ቋሚ ንብረት ባሻገር ተሰብሣቢ የሂሣብ ሰነዶችንም የመሰብሰብ መብትና ሥልጣን ብቻ ተነጥሎ ለባለአደራ ቦርድ ተሰጥቷል ወደ ሚል መደምደሚያ ላያደርስ የሚቻል አይደለም። ይህ የሽያጭ ውል ከአዋጅ ዓብይ ዓላማ አንፃር ለሕግ ተፃራሪ ነው እስከልተባለ ድረስ የባለ አደራ ቦርድ ሥልጣንና ተግባር ወደ ገዥው ላተላለፉ በማይችሉ የተሸጠው ድርጅት ውጤትና ግድታ ላይ የተወሰነ ነው።
በመሆኑም የሥር ፍ/ቤቶች ለጉዳዩ አግባብነት ያለውን ሕግ ይዘቱን ግብር ዓላማውን ከሽያጭ ውሉ ይዘት ጋር በማገናዘብ ተመልክተው የሰጡት ትርጉም እንዳልሆነ ተገንዝበናል።
በመሆኑም የአሁን አመልካች ክስ የቀረበበት ጉዳይ ለጉዳዩ አግባብነት ካለው ሕግ እና ከሽያጭ ውሉ አንፃር ተገናዝቦ ከታዬ ክሱን በአሁኑ ተጠሪ ላይ ለማቅረብ ከሕግ ወይም ከውል የመነጨ መብት አለው ከሚባል በቀር የተለዬ ትርጉም የሚያሰጥ ሆኖ አላገኘነውም።
ከዚህም የትርጉም መስመር ባሻገር የተከራካሪ ወገኖችን መብትና ግድታ በትክክል እና ፍትሃዊ በሆነ አኳኋን ተመልክቶ ሕግን መሰረት ያደረገ ፍርድን መስጠት እንዲቻል ከተዘረጋው የክርክር አመራር ሥርዓት አንፃርም ይታይ ቢባል ለትክክለኛ ፍትህ አሰጣጥ እንዲመች የመንግሥት የልማት ድርጅቶች ባለአደራ ቦርድ በጉዳዩ ላይ ጣልቃ ገብቶ እንዲከራከር በፍ/ብ/ሥ/ሥ/ሕ/ቁ.4ዐ/2/ በተመለከተው መሰረት ማድረግም እየተቻለ ክርክሩ በደረሰበት ደረጃ ብቻ በመገደብ የአሁን አመልካች በጉዳዩ ላይ ክስ የማቅረብ መብት የለውም በሚል በሥር ፍ/ቤቶች የተሰጠው ዳኝነት መሰረታዊ የሕግ ስህተት የተፈፀመበት ሆኖ ስላገኘነው የሚከተለውን ውሣኔ ሰጥተናል።
No topics extracted.
ው ሣ ኔ 1/ የአሁን አመልካች በጉዳዩ ላይ ክስ ለማቅረብ የሚያስችል መብት የለውም በሚል ተወስኖ የበላይ የሆነው በአማራ ብ/ክ/መንግሥት ጠቅላይ ፍ/ቤት በይግባኝ ጉዳዩን ተመልክቶ በመ/ቁ. 468/ዐ1 ታህሣሥ 1ዐ ቀን 2ዐዐ5 ዓ.ም ይህንኑ ውሣኔ በማጽናት የሰጠው የመጨረሻ ፍርድ ተሽሯል።
2/በጉዳዩ የአሁኑን አመልካች በተጠሪ ላይ ክስ የማቅረብ መብት ያለው ስለመሆኑ በግራ ቀኙ መካከል የተነሣው ክርክር የሚያመለክት በመሆኑና አስፈላጊም ሆኖ በተገኘ ጊዜ ባለጥቅሙ ነው የተባለውንም የመንግሥት የልማት ድርጅቶች ባለአደራ ቦርድ በጉዳዩ ላይ ጣልቃ ገብቶ እንዲከራከር የሥነ ሥርዓት ሕጉ የሚፈቅድ በመሆኑ ይህንኑ ወገን የክርክር ተከፋይ በማድረግ ክርክሩ ቀጥሎ ይወሰን ዘንድ ጉዳዩን ወደ ክልሉ የዞን ከፍተኛ ፍ/ቤት እንዲመለስ በፍ/ብ/ሥ/ሥ/ሕ/ቁ. 341 መሰረት ወስነናል።
3/ በዚህ የሰበር ሰሚ ችሎት ግራ ቀኙ ክርክራቸውን በማሰማት ውሣኔ እስኪሰጠው ድረስ ላወጡት ወጭና ኪሣራ በየራሣቸው ይቻሉ።