No summary available.
ሚያዝያ 24 ቀን 2005 ዓ.ም.
ዳኞች፡- አልማው ወል ዓላ መሐመድ ረታ ቶሎሳ አዳነ ንጉሴ ሙስጠፋ አህመድ አመልካች፡- አቶ አንተነህ ሲሳይ - ቀረቡ ተጠሪዎች፡- የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ፍትህ ቢሮ - ነገረ ፈጅ አሸናፊ ስዩም ቀረበ መዝገቡን መርምረን የሚከተለውን ፍርድ ሰጥተናል።
ጉዳዩ የቀረበው አመልካች የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ይግባኝ ሰሚ ችሎት ፍ/ቤት የሰበር ችሎት በመዝገብ ግንቦት 10 ቀን 2004 ዓ.ም የሰጠው ውሳኔ መሰረታዊ የሕግ ስህተት ያለበት ስለሆነ በሰበር ታይቶ እንዲታረምልኝ በማለት የቀረበውን የሰበር አቤቱታ አጣርቶ ለመወሰን ነው። ጉዳዩ የዲስፕላን ጥፋት የተፈፀመ መሆኑን ወይም አለመሆኑን የሚመለከት ነው። ጉዳዩ በመጀመሪያ በይግባኝ የታየው በአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር የመንግስት ሰራተኞች አስተዳደር ፍርድ ቤት ነው።
አመልካች ይህንን የስራ ግድታውን በመደበኛ የመንግስት የስራ ሰዓት ሰርቷል። ለግልግል ዳኛ አበል እንዲከፍል ትዕዛዝ ሲሰጡ ከልሎች የግልግል ዳኞች ጋር አብረው መወሰናቸው የመንግስት ሰራተኞችን ስነ ምግባር የጣሰ ነው። የግልግል ዳኛ በመሆናቸው የተከፈላቸውን አበል ለፍትህ ቢሮ ተመላሽ እንዲያደርጉ በቢሮው ኃላፊው ሲጠየቁ እንቢተኛ በመሆን ገንዘቡን ለግል ጥቅማቸው ማዋላቸው ከባድ የዲስፒላን ጥፋት ነው በማለት ከስራ ያሰናበተው መሆኑን በመግለፅ ለአስተዳደር ፍርድ ቤቱ ተከራክሯል። የአስተዳደር ፍርድ ቤቱ አመልካች የፈፀመው የዲስፒላን ጥፋት የልለ መሆኑን በመዘርዘር የዲሲፕላን ኮሚቴና የቢሮው ኃላፊ የሰጠውን ውሳኔ ሽሮታል። አመልካች ያልተከፈለው ደመወዝ ተከፍሎት ወደ ሥራው እንዲመለስ ውሳኔ ተሰጥቷል። ተጠሪ ይግባኝ ለአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ይግባኝ ሰሚ ፍርድ ቤት አቅርቧል። ይግባኝ ሰሚው ፍርድ ቤት የተጠሪን ይግባኝ በፍ/ስ/ስ/ሕ/ግ/ቁጥር 337 መሰረት ሰርዞታል።
ተጠሪ የሰበር አቤቱታ ለአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ይግባኝ ሰሚ ፍርድ ቤት የሰበር ችሎት የሰበር አቤቱታ አቅርቧል። የከተማው የሰበር ችሎት የግራ ቀኙን ክርክር ከሰማ በኋላ አመልካች የግልግል ዳኛ ሆኖ ለሰራበት አበል መቀበሉና አበሉን ለፍትህ ቢሮ እንዲመልስ ሲጠየቅ እንቢተኛ መሆኑ ከባድ የዲስፕላን ጥፋት ነው። አመልካች የበላይ ኃላፊውን ትዕዛዝ አላከበረም በማለት የመንግስት ሰራተኞች አስተዳደር ፍርድ ቤትና የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ይግባኝ ሰሚ ፍርድ ቤት የሰጠውን ውሳኔ በመሻር የዲስፒላን ኮሚቴ የሰጠውን ውሳኔ አጽንቶታል።
አመልካች ግንቦት 30 ቀን 2004 ዓ.ም በተፃፈ የሰበር አቤቱታ ተጠሪ የግልግል ዳኛ ሆኖ እንዲሰየም ደብዳቤ ፅፏል። የግልግል ጉባኤው በፍ/ስ/ስ/ሕ/ግ/ቁጥር 318(5) በተደነገገው መሰረት የአበል ክፍያ ወስኗል። የግልግል ዳኛ ሆኜ ተሰይሜ ለሰራሁበት የተከፈለኝን አበል ለቢሮው እንዳስገባ የካቲት 7 ቀን 2003 ዓ/ም በተፃፈ ደብዳቤ ትዕዛዝ ሰጠኝ አመልካች ገንዘቡን ለተጠሪ ገቢ የማደርግበት ከውል ወይም ከሕግ የመነጨ ግድታ የለብኝም። ስለዚህ አበል ለመመለስ ፈቃደኛ አይደለህም በማለት የዲስፒላን ጥፋት እንደፈፀምኩ የከተማው አስተዳደር የሰበር ችሎት የሰጠው ውሳኔ የሕግ መሰረት የልለው በመሆኑ በሰበር ታይቶ ይታረምልኝ በማለት አመልክቷል።
ተጠሪ መስከረም 28 ቀን 2005 ዓ.ም የተፃፈ መልስ አቅርቧል። ተጠሪ አመልካች የመንግስት ሰራተኛ ሆኖ እያለ አበል መቀበል፣ አበልም ከተቀበለ በኋላ ወክሎ የላከው መስሪያ ቤት ለማስረከብ ፈቃደኛ አይደለም ይህም ከባድ የዲስፒላን ጥፋት በመሆኑ የከተማው አስተዳደር የሰበር ችሎት የሰጠው ውሳኔ የሕግ ስህተት የለበትም በማለት መልስ ሰጥቷል። አመልካች ጥቅምት 19 ቀን 2005 ዓ/ም የተፃፈ የመልስ መልስ ሰጥቷል።
ከስር የክርክሩ አመጣጥና በሰበር ግራ ቀኙ ያቀረቡት የፅሁፍ ክርክር ከላይ የተገለፀው ሲሆን እኛም አመልካች ከባድ የዲስፒላን ጥፋት ፈፅሟል በማለት የተሰጠው ውሳኔ አግባብነት ያላቸውን የሕግ ድንጋጌዎች መሰረት ያደረገ ነው ወይስ አይደለም? የሚለውን ጭብጥ በመያዝ ጉዳዩን መርምረናል።
ጉዳዩን እንደመረመርነው ተጠሪ አመልካችን የመደብኩት፣ የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር የመሬት አስተዳደር የግንባታ ፈቃድ ባለስልጣን ከአያት አክሲዮን ማህበር ጋር በላዝ ውል አፈፃፀም ጋር ባለው አለመግባባት፣ አመልካች የሙያ ምክርና ድጋፍ ለመሬት አስተዳደር ባለስልጣኑ እንዲሰጥ ነው በማለት ይከራከራል። በልላ በኩል አመልካች ተጠሪ በፅሁፍ የገለፀልኝ የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር የመሬት አስተዳደር የግንባታ ፈቃድ ባለስልጣንና የአያት አክሲዮን ማህበር አለመግባባት በግልግል አይቶ ውሳኔ የሚሰጠው የግልግል ጉባኤ አባልና የግልግል ዳኛ ሆኜ እንድሰራ ነው በማለት ይከራከራል። አንድ ጉዳይ በፍርድ ቤት ወይም በግልግል ጉባኤ በሚታይበት ወቅት ለአንደኛው ወገን የሕግ ምክርና ድጋፍ እንዲያደርግ የተመደበ ባለሙያ ያለበት ሙያዊ ኃላፊነትና ላከተለው የሚገባው የስነ ምግባር ደንብ በሁለቱ ወገኖች መካከል የተነሳውን አለመግባባት በግለግል ዳኝነት አይቶ ውሳኔ እንድሰጥ ከተመደበ ባለሙያ ካለበት ኃላፊነትና ላከተለው ከሚገባው የስነ ምግባር ደንብ በእጅጉ የተለየ ነው። በመሆኑም ከላይ የተያዘውን ጭብጥ ለመወሰን ተጠሪ አመልካችን የመደበው ለመሬት አስተዳደር የግንባታ ፈቃድ ባለስልጣን የሕግ ድጋፍና ምክር አገልግሎት እንዲሰጥ ነው? ወይስ የግልግል ጉባኤ አባል ሆኖ የሁለቱን ተከራከሪ ወገኖች ክርክርና ማስረጃ ለመስማት ውሳኔ እንዲሰጥ የሚለው ነጥብ መለየት አለበት።
ተጠሪ ለመሬት አስተዳደርና ግንባታ ፈቃድ ባለስልጣን መጋቢት 15 ቀን 2002 ዓ.ም የፃፈው ደብዳቤና ተጠሪ ሚያዝያ 26 ቀን 2002 ዓ.ም ለአያት አክሲዮን ማህበር በፃፈው ደብዳቤ፣ አመልካች የሁለቱን ጉዳይ በግልግል እንዲያይ በግልግል ዳኝነት የተሰየመ መሆኑን የሚገልፅ ነው። አመልካች የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር፣ የመሬት አስተዳደርና የግንባታ ፈቃድ ባለስልጣንና ለአያት አክሲዮን ማህበር መካከል የላዝ ውል በተመለከተ የተፈጠረውን አለመግባባት በግልግል የሚያው የግልግል ጉባኤ አባል ሆኖ ኃላፊነቱን እንዲወጣ ተጠሪ በፅሁፍ መድቦታል። የግልግል ዳኛ ሆኖ የተሰየመ ባለሙያ (የግልግል ዳኛ) ሆኖ የተሰየመበትን ስራ በሚሰራበት ጊዜ ላከተለው የሚገባው የሙያ ስነ ምግባር ዳኛ የሚከተለውን ሥነ ምግባር እንደሆነና ከፍትሐብሕር ሥነ ሥርዓት ሕግ ቁጥር 351 ድንጋጌዎች ይዘት ለመረዳት ይቻላል።
አንድን ጉዳይ በግልግል አይቶ እንዲወሰን የተቋቋመው የግልግል ጉባኤ የግልግል ዳኛ በጉዳዩ ገለልተኛና ነፃ ሆኖ የግራ ቀኙን ክርክርና ማስረጃ በአግባቡ ሰምቶ የመወሰን ግድታ እንዳለበትና ይህ በተጓደለ ጊዜ የግልግል ጉባኤው ውሳኔ በይግባኝ ላታረም እንደሚችል የፍትሐብሕር ሥነ ሥርዓት ሕግ ቁጥር 351 ድንጋጌዎች ይደነገጋሉ።
በተለይም የአንቀጽ 351 ንዑስ አንቀጽ (2)(መ) የግልግል ወይም የሽምግልና ዳኝነት አባል የሆነ ሰው በስራው አፈፃፀም ላይ በዳኛ ላፈፀም የማይገባውን የአድሐዊነት እና የመጥፎ ባሕሪይ ፀባይ ማሳየት እንደልለበት የሚደነግግ ይዘት ያለው ነው። ስለዚህ አመልካች የግልግል ዳኛ ሆኖ ከተሰየመ በኋላ የግልግል ጉባኤ አባልነቱ ግራ ቀኙን ክርክርና ማስረጃ ነፃና ገለልተኛ ሆኖ የመስማት የመመዘንና በፍ/ሥ/ሥ/ሕ/ግ/ቁጥር 317 ድንጋጌዎች መሰረት ከማድረግ ክርክሩን የመምራትና የቀረበለትን ክርክርና ማስረጃ አግባብነት ካለው የሕግ ድንጋጌ ጋር በማገናዘብ የመሰለውን ውሳኔ የመስጠት ኃላፊነት አለበት።
የግልግል ጉባኤው ከሚወስናቸው ውሳኔዎችና ከገላጋይ ዳኞቹ ላከፈል የሚገባውን የአበል መጠን እንደሆነ በፍትሐብሕር ሥነ ሥርዓት ሕግ ቁጥር 318 ንዑስ አንቀጽ 5 በግልፅ ተመልክቷል።
አመልካች የግልግል ዳኛ ሆኖ ሲሰራ አንድ ዳኛ ማሟላት የሚገባውን የሙያ ስነ ምግባር ደንብ ማሟላት ግድታ ያለበት ሲሆን፣ የግልግል ዳኛ ሆኖ ተለይቶ የግራ ቀኙን ክርክር ማስረጃ መስማትና ውሳኔ መስጠት አመልካች ከተቀጠረበት መደበኛ ሥራ/ የህግ ምክርና ድጋፍ/ መስጠት በእጅጉ የተለየ ከባድ ኃላፊነት ነው። ከዚህ በላይ የግልግል ዳኛ ሆኖ የተሰየመ ሰው በግልግል ዳኝነቱ የተጣለበትን በአግባቡ ካልተወጣ ራሱን የቻለ የወንጀል ተጠያቂነት የሚኖርበት መሆኑ በወንጀል ህጉ አንቀጽ 399(1) ድንጋጌ ይዘትና ዓላማ ለመረዳት ይቻላል።
ከዚህ አንፃር ስንመለከተው አመልካች የግልግል ዳኛ ሆኖ የተሰየመበት ጉዳይ በውሳኔ እስኪጠናቀቅ ድረስ ጉዳዩን ተከራካሪ ወገኖችን በእኩልነት የማየት ነፃና ገለልተኛ ሆኖ የመስማት የመመርመርና ውሳኔ የመስጠት ኃላፊነቱን ያልተወጣ ስለመሆኑ ተጠሪ በክርክሩ አልገለፀም። ተጠሪ አመልካች የግልግል ዳኛ የሆነው የቢሮው ወኪል ሆኖ ነው በማለት ያቀረበው ክርክርም የህግ መሰረት የለውም። አመልካች በክርክሩ የግልግል ዳኛ እንዲሆን የተመረጠውና የተሰየመው በተጠሪ ፈቃድና ሥምምነት ነው። አመልካችና የግልግል ዳኛ ሆኖ ተሰይሞ ጉዳዩን በግልግል ዳኝነት ማየት ከጀመረ በኋላ ተጠሪን እያማከረና በግልግል ዳኝነት አባልነቱ የሚሰጠውን ብይንም ሆነ ውሳኔ በተጠሪ እያፀደቀና እያስፈቀደ ላሰራ አይችልም። አመልካች እንደማንኛውም ዳኛ ነፃና ገለልተኛ ሆኖ ጉዳዩን ማየትና የመወሰን ኃላፊነት አለበት።
ከዚህ አንፃር ካየነው አመልካች በግልግል ዳኝነት ተሰይሞ የሰጠውን ብይን (ተከራከሪዎች የግልግል ጉባኤ ወጭና አበል እንዲሸፍኑ) የግልግል ጉባኤው ሲወስን፣ አመልካች መስማማቱን እንደ ድስፒላን ጥፋት ማቅረቡ የፍ/ሥ/ሥ/ሕ/ግ/ቁጥር 351 ንዑስ አንቀጽ 2(መ) በአመልካች ላይ ከተጣለበት የዳኛ ሥነ ምግባር የመከተልና ገለልተኛ ሆኖ ብይንና ውሳኔ የመስጠት ግድታን የሚፃረር ነው። የአበል ክፍያን በተመለከተ የግልግል ጉባኤው እንደ አንድ ፍርድ ሰጭ ተቋም፣ ተከራከሪዎች ካልተስማማቸው በይግባኝ ላያስለውጡት የሚችሉበት ሥርዓት በተዘረጋበት ሁኔታ በፍ/ሥ/ሥ/ሕ/ግ/ቁጥር 318 ንዑስ አንቀጽ 2(5) የወሰነው እንጅ አመልካች በግሉ ከአያት አክስዮን ማህበር የተቀበለው ገንዘብ አይደለም። አበሉ ለአመልካች የተከፈለው አመልካች በተጠሪ ከተቀጠረበት የሕግ ምክርና ድጋፍ የመስጠት ስራ የተለየ ኃላፊነትና ሥልጣን ባለው የግልግል ጉባኤ የግልግል ዳኛ ሆኖ ለሰራው ስራና ለሰጠው ለአገልግሎት ነው።
ስለዚህ አመልካች ለአንድ ልዩ ጉዳይ የግልግል ዳኛ ሆኖ ለሰጠው አገልግሎት እንደማንኛውም የግልግል ጉባኤ አባል የተከፈለው የአበል ክፍያ የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ምክር ቤት የወጣውን አዋጅ ቁጥር 6/2000 አንቀጽ 31 የሚጥስ የሥነ ምግባር ጥፋት ተደርጎ ላያዝ የሚችል አይደለም።
ተጠሪ አመልካች ሰራተኛው በመሆኑና የግልግል ዳኛ ሆኖ አመልካች በጉዳዩ የተሰየመው በእሱ ፈቃድና ስምምነት መሆኑን መሰረት በማድረግ የአበል ክፍያውን አመልካች ገቢ ላያደርግ ይገባዋል በማለት የሚያቀርበው የሕግ መሰረት የለውም። ስለዚህ አመልካች በግልግል ዳኛ ሆኖ ለሰጠው ግልጋሎት እንደ ማንኛውም የግልግል ጉባኤ አባል የተከፈለውን አበል ለተጠሪ ገቢ አለማድረጉን ከባድ የስነ ምግባር ጥፋት ነው በማለት የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ይግባኝ ሰሚ ፍርድ ቤት የሰበር ችሎት በአብላጫ ድምፅ የሰጠው ውሳኔ መሰረታዊ የሕግ ስህተት ያለበት ነው በማለት ወስነናል።
የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር የመንግስት ሰራተኞች አስተዳደር ፍርድ ቤትና የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ይግባኝ ሰሚ ፍርድ ቤት የሰጡት ውሳኔ ፀንቷል።
የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ይግባኝ ሰሚ ፍርድ ቤት የሰበር ችሎት የሰጠው ውሳኔ ተሽሯል።
አመልካች የግልግል ዳኛ ሆኖ ሲሰራ የፈፀመው ከባድ የዲስፒላን ጥፋት የልለ በመሆኑ ተጠሪ የአመልካችን ውዝፍ ደመወዝ በሕጉ መሰረት ከፍሎ ወደ ስራ ላመልሰው ይገባል በማለት ወስነናል።
በዚህ ፍርድ ቤት ያወጡትን ወጭና ኪሳራ ግራ ቀኙ ለየራሳቸው ይቻሉ።
መዝገቡ ወደ መዝገብ ቤት ይመለስ።
No topics extracted.