No summary available.
መስከረም 21 ቀን 2006ዓ/ም ዳኞች፡- ተሻገር ገ/ሥላሴ አልማው ወል ዓላ መሐመድ ረታ ቶሎሳ ሙስጠፋ አህመድ አመልካቾች፡-
ጉዳዩ የቀረበው አመልካች ደቡብ ብሕር ብሕረሰቦችና ሕዝቦች የክልል ጠቅላይ ፍርድ ቤት ሰበር ሰሚ የሰጠው ውሳኔ መሰረታዊ የህግ ስህተት ያለበት ስለሆነ በሰበር ታይቶ ይታረምልኝ በማለት ያቀረበውን የሰበር አቤቱታ አጣርቶ ለመወሰን ነው። ጉዳዩ በመጀመሪያ የታየው በሸበደኖ ወረዳ ፍርድ ቤት ነው። ጉዳዩ የአፈፃፀም ክርክር የሚመለከት ነው።
የክርክሩ መነሻ ተጠሪዎች በስር ፍርድ ቤት በፍርድ ባለመብትነት ቀርበው የፍርድ ባለዕዳው የአባታችንን ውርስ ሀብት እንዲያካፍል በተሰጠው ፍርድ መሰረት እንዲፈፅም ይወሰንልን በማለት ያቀረቡት የአፈፃፀም ማመልከቻ ነው። አመልካች የፍርድ ባለዕዳ በመሆን ቀርቦ ተከራክሯል። የስር ፍርድ ቤት ተገቢ ነው የሚለውን አፈፃፀም ትዕዛዝ ሰጥቷል። አመልካቾች የስር ፍርድ ቤት በሰጠው የአፈፃፀም ትዕዛዝ ቅር በመሰኘት ይግባኝ ለሲዳማ ዞን ከፍተኛ ፍርድ ቤት አቅርበዋል። የዞኑ ከፍተኛ ፍርድ ቤት የግራ ቀኙን ክርክር ከሰማ በኋላ የስር ፍርድ ቤት የሰጠውን ውሳኔ አጽንቶታል። አመልካች በዚህ ውሳኔ ቅር በመሰኘት ለደቡብ ብሕር ብሕረሰቦችና ሕዝቦች ክልል ጠቅላይ ፍርድ ቤት ሰበር ችሎት የሰበር አቤቱታ አቅርቧል። የክልሉ ጠቅላይ ፍርድ ቤት ሰበር ችሎት ጉዳዩ የፍድራል ጉዳይ በመሆኑ በሰበር ለማየት ስልጣን የለኝም በማለት ውሣኔ ሰጥቷል።
አመልካች በ22/4/2005 ዓ.ም በተፃፈ የሰበር አቤቱታ አፈፃፀም ክስ ያቀረበበትን ፍርድ የተሰጠው ሸበደኖ ወረዳ ፍርድ ቤት ነው። ዋናው ፍርድ እስከ ክልሉ ጠቅላይ ፍርድ ቤት ሰበር ችሎት ድርስ ቀርቦ የፀና ነው። ይህንን ፍርድ ለማስፈፀም ክስ ስናቀርብ ጉዳዩ በፍደራል ጠቅላይ ፍርድ ቤት ሰበር ችሎት የሚታይ በመሆኑ ጉዳዩን ለማየት ስልጣን የለኝም በማለት የሰጠው ውሣኔ መሰረታዊ የሕግ ስህተት ያለበት ስለሆነ በሰበር ታይቶ እንዲታረምልኝ በማለት አመልክቷል። ተጠሪ በ1/8/2005 ዓ.ም ተጠሪዎች መልስ ለደቡብ ብሕር ብሕረሰቦችና ሕዝቦች ክልል ጠቅላይ ፍርድ ቤት ሰበር ችሎት የሰጠው ውሣኔ መሰረታዊ የሕግ ስህተት የለበትም በማለት ተከራከረዋል። አመልካቾች የመልስ መልስ አቅርበዋል።
ከሥር የክርክሩ አመጣጥና በሰበር የቀረበው ክርክር ከላይ የተገለፀው ሲሆን እኛም የደቡብ ብሕር ብሕረሰቦችና ሕዝቦች የክልል ጠቅላይ ፍርድ ቤት ሰበር ሰሚ ጉዳዩን ለማየት ስልጣን የለኝም በማለት የሰጠው ውሣኔ ተገቢ ነው ወይስ አይደለም የሚለውን ጭብጥ በመያዝ ጉዳዩን መርምረናል።
ጉዳዩን እንደመረመርነው አመልካች የአፈፃፀም ክስ ያቀረቡበት ፍርድ በሸበድኖ መጀመሪያ ፍርድ ቤት ውርሱ እንዲጣራ ተደርጎ የተወሰነና በሲዳማ ዞን ከፍተኛ ፍርድ ቤት ይግባኝ ታይቶ የፀና በመጨረሻም በክልሉ ጠቅላይ ፍርድ ቤት የሰበር ችሎት በሰበር መዝገብ የካቲት 11 ቀን 2003 ዓ.ም በሰጠው ውሣኔ የሸበድኖ መጀመሪያ ፍርድ ቤት ውሣኔና የሲዳማ ዞን ከፍተኛ ፍርድ ቤት ውሣኔ ሽሮ አመልካቾች የፍርድ ባለ መብት የሆኑበት ፍርድ ነው። በልላ አነጋገር አመልካቾች በሸበዲኖ የመጀመሪያ ፍርድ ቤት አፈፃፀም ክስ ያቀረቡት የሥር ፍርድ ቤትም አፈፃፀም ክሱን በመቀበልና በመመርመር 15/08/2004 ዓ.ም አፈፃፀም ትእዛዝ የሰጠው የክልሉ ጠቅላይ ፍርድ ቤት የሰበር ችሎት በሰበር መዝገብ የካቲት 11 ቀን 2003 ዓ.ም የሰጠውን ውሣኔ መሰረት በማድረግ ነው።
የፍርድ አፈፃፀም ማመልከቻ የሚቀርበው ፍርዱን ለፈረደው ፍርድ ቤት እንደሆነና ፍርድ የማስፈፀም ስልጣን ያለው ፍርድን የፈረደው ወይም ፍርዱን በሰጠው ፍርድ ቤት ፍርድ እንዲያስፈጽም ውክልና የተሰጠው ፍርድ ቤት እንደሆነ በፍ/ሥ/ሥ/ሕ/ግ/ቁ 378 ተደንግጓል። ከዚህ አንፃር ሲታይ በክልሉ ጠቅላይ ፍርድ ቤት የሰበር ችሎት በሰበር መዝገብ የካቲት 11 ቀን 2003 ዓ.ም የሰጠውን ውሣኔ የማስፈፀም ስልጣን ያላቸው የክልሉ ፍርድ ቤቶች እንጂ የፍድራል ፍርድ ቤቶች አይደሉም። የአፈፃፀም ስልጣን መሰረቱ ፍርዱ መስጠት ወይም ፍርዱን በሰጠው ፍርድ ቤት ፍርድ ለማስፀም የሚያስችል ውክልና ማግኘት መሰረት ያደረገ እንጂ የፍርድ ባለእዳውን ወይም የፍርድ ባለመብቱ የሚኖሩበትን ክልል /የከተማ አስተዳደር/ መሰረት ያደረገ አይደለም።
ከዚህ አንፃር ሲታይ የሥር ፍርድ ቤትም አፈፃፀም ክሱን በመቀበልና በመመርመር በ15/08/2004 ዓ.ም አፈፃፀም ትእዛዝ የሰጠውና በሲዳማ ዞን ከፍተኛ ፍርድ ቤት የአፈፃፀም ትእዛዙን በይግባኝ በማየት ያፀናው የፍ/ሥ/ሥ/ሕ/ግ/ቁ 378 ድንጋጌዎችን መሰረት በማድረግ ነው። ጉዳዩ ይህ ሆኖ እያለ የክልሉ ጠቅላይ ፍርድ ቤት የሰበር ችሎት ለአዋጅ ቁጥር 25/1988 አንቀጽ 5/2/ በተዛባ መንገድ በመተርጎም ጉዳዩን በሰበር ለማየት ስልጣን የለኝም በማለት የሰጠው ውሣኔ መሰረታዊ የሕግ ስህተት አለበት በማለት ወስነናል።
በደቡብ ብሕር፣ ብሕረሰቦችና ሕዝቦች የክልል ጠቅላይ ፍርድ ቤት ሰበር ሰሚ ችሎት በሰበር መዝገብ መስከረም 30 ቀን 2005 ዓ/ም የሰጠው ትዕዛዝ ተሽሯል።
በደቡብ ብሕር ብሕረሰቦችና ሕዝቦች የክልል ጠቅላይ ፍርድ ቤት ሰበር ሰሚ ችሎት የስር ፍርድ ቤትና የሲዳማ ዞን ከፍተኛ ፍርድ ቤት የሰጡትን የአፈፃፀም ትዕዛዝ በሰበር አይቶ የመወሰን ሥልጣን አለው በማለት ወስነናል።
የደቡብ ብሕር ብሕረሰቦችና ሕዝቦች የክልል ጠቅላይ ፍርድ ቤት ሰበር ሰሚ ችሎት የአምልካቾችን የሰበር አቤቱታ በመመርመር ውሳኔ እንዲሰጥበት ጉዳዩን በፍ/ሥ/ሥ/ሕ/ቁ 341(1) መሰረት መልሰን ልከንለታል።
በዚህ ችሎት ያወጡትን ወጭና ኪሳራ ግራ ቀኙ ለየራሳቸው ይቻሉ በማለት ወስነናል።
መዝገቡ ወደ መዝገብ ቤት ይመለስ
No topics extracted.