No summary available.
ታህሳስ 28 ቀን 2006 ዓ.ም.
ዳኞች:- አልማው ወል ዓላ መሐመድ ረታ ቶለሳ አዳነ ንጉሴ ሙስጠፋ አህመድ አመልካች፡- ሪዬስ ኢንጂነሪንግ አክሲዮን ማህበር ተጠሪ፡- የአክሱም ኮንስትራክሽን ባለቤት አቶ ጌታሁን ሁሴን **
መዝገቡ ተመርምሮ ተከታዩ ፍርድ ተሰጥቷል።
**
ጉዳዩ አንድ የፍርድ ባለእዳ የሆነ ንብረት ከአንድ በላይ በሆኑ የፍርድ ባለገንዘቦች ለፍርድ አፈፃፀም በእያንዳንዳቸው በተናጠል እንዲከበር ተደርጐ በሚገኝበት ጊዜ አፈፃፀሙ በንብረቱ ላይ ላቀጥል የሚችልበትን አግባብ የሚመለከት ሲሆን ክርክሩም የተጀመረው በፍድራሉ መጀመሪያ ደረጃ ፍ/ቤት የአሁኑ አመልካች በተጠሪ ላይ ባስከፈተው የአፈፃፀም መዝገብ መነሻነት ነው። የጉዳዩ አጀማመርም አመልካች በተጠሪ ላይ የገንዘብ ክፍያ አስፈርደው የፍርድ ባለመብት ሲሆኑ አፈፃፀሙም በፍድራሉ መጀመሪያ ደረጃ ፍ/ቤት የኮ/መ/ በሆነው ቀርቦ እና አመልካችም ይሄንኑ ፍርድ ለማስፈፀም ሲባል የተለያዩ የፍርዱን ባለእዳ ንብረቶችን ያስከበረ ቢሆንም ሆኖም ግን እነኝህ ንብረቶች በልላ የፍርድ ቤቱ መዛግብት ላይ በልሎች ፍርድ ባለገንዘቦችም የእግድ ትዕዛዝ የተሰጠባቸው በመሆኑ የአሁኑ አመልካች እግዱን አስነስተው ሲቀርቡ ወይም ልላ የፍርድ ባለእዳ ንብረት አፈላልገው ሲቀርቡ አፈፃፀሙ ላቀጥል ከሚችል በቀር በልላ ጉዳይ የእግድ ትዕዛዝ በተሰጠባቸው ንብረቶች ላይ የይሸጡ ትዕዛዝ መስጠት አይቻልም በማለት የፍርድ ባለመብቱን ጥያቄ ባለመቀበል የአፈፃፀም መዝገብ ጉዳዩን ሲመራ በነበረው የፍድራሉ መጀመሪያ ደረጃ ፍ/ቤት በትዕዛዝ እንዲዘጋ ተደርጓል።
የአሁኑ አመልካችም በትዕዛዙ ቅር በመሰኘት የይግባኝ አቤቱታውን ለፍድራሉ ከፍተኛ ፍ/ቤት ያቀረበ ቢሆንም ይግባኙ በፍ/ብ/ስ/ስ/ህ/ቁ 337 መሰረት ተቀባይነት አላገኘም አሁን የቀረበው የሰበር አቤቱታም ይሄንኑ በስር ፍ/ቤቶች የተሰጡትን ትዕዛዝ በመቃወም ለማስለወጥ ሲሆን መሰረታዊ ይዘቱም አመልካች ያስከበረውን ንብረት በልሎች መዛግብት ላይ ልሎች የፍርድ ባለመብቶችም የእግድ ትዕዛዝ አሰጥተውበት ከሆነም ፍ/ቤቱ እነዚህን ፍ/ባለመብቶች አስቀርቦ በመመርመር ከፍ/ብ/ሥ/ሥ/ህ/ቁ 403 ድንጋጌ ይዘት አኳያ በአፈፃፀም የተያዘውን ንብረት ለመከፋፈል የሚያበቃ ውሳኔ ካላቸው እንደየገንዘባችን መጠን ንብረቱ ተሸጦ እንድንከፋፈል መደረግ ሲገባ አፈፃፀሙ ላቀጥል አይችልም በማለት ፍርዱ ሳይፈፀም የአፈፃፀም መዝገቡን መዝጋቱ በአግባቡ ባለመሆኑ የሥር ፍ/ቤቶች ትዕዛዝ ተሽሮ አፈፃፀሙ ከፍ/ብ/ሥ/ሥ/ህ/ቁ 403 ድንጋጌ ይዘት አኳያ እንዲፈፀም ይታዘዝልን የሚል ነው።
አቤቱታውም ተመርምሮ ያስቀርባል በመባሉ ተጠሪም ቀርቦ ግራ ቀኙ በፅሁፍ እና በቃልም በችሎት እንዲሰሙ ተደርጓል።
የጉዳዩ አመጣጥና ይዘት ባጭር ባጭሩ ከላይ የተመለከተውን ሲመስል እኛም በበኩላችን አመልካች በልላ መዛግብት ላይ በልሎች ፍርድ ባለመብቶች በንብረቱ ላይ የተሰጠውን የእግድ ትዕዛዝ እንዲነሳ ካላደረገ አፈፃፀሙ ላቀጥል አይችልም ተብሎ የአፈፃፀም መዝገቡ በስር ፍ/ቤቶች መዘጋቱ በአግባቡ ነው? ወይስ አይደለም?
የሚለውን ነጥብ በጭብጥነት ይዘን ጉዳዩን በሚከተለው መልኩ መርምረናል።
መዝገቡን እንደመረመርነውም ተጠሪ በ1993 ዓ/ም ወደ ብር 1,172,503.06 (አብዛኛው ገንዘብ በ10.5% እና የተወሰነው ቀሪ ገንዘብ ደግሞ በ9% ከሚታሰብ ወለድ ጋር) ለአመልካች ይክፈል ተብሎ ፍርድ የተሰጠበት መሆኑን፣ አመልካችም ይሄንኑ ፍርድ ለማስፈፀም ሲባል የፍርድ ባለእዳ የሆኑ የተለያዩ ንብረቶችን የዕግድ ትዕዛዝ ሲያሰጥባቸው የቆየ ቢሆንም እዳው እስከአሁንም ሙሉ በሙሉ ተከፍሎ አለመጠናቀቁን፣ በመሆኑም የፍርድ ባለመብቱ በፍርድ ባለእዳ ባለቤት በወ/ሮ እፀገነት ታዬ ስም በካርታ ተመዝግቦ የሚገኘውንና የቤት ቁጥሩ 2089 የሆነውን መኖሪያ ቤት በአፈፃፀም ተሽጦ እዳው እንዲከፈለው ጥያቄ ያቀረበ መሆኑን፣ ሆኖም ግን ይህ ንብረት ልላ ባለገንዘብ በሆነው አንበሳ ኢንሹራንስም በተመሳሳይ ፍ/ቤት አፈፃፀም መ/ቁ 1251/92 በሆነው መከበሩንና እንዲሁም ይሄው መኖሪያ ቤት በዳሽን ባንክም በብድር ለተሰጠ እዳ በመያዣ ውል መያዙንም ከክርክሩ ሂደት ለመገንዘብ ተችሐል። ይህ ችሎትም በክርክሩ ሂደት የተረጋገጡትን ፍሬ ነገሮች መነሻ በማድረግ ጉዳዩን ከህጉ ጋር በማገናዘብ ተመልክቷል።
በመሰረቱ ፍርድ የተፈረደለት ሰው እንደፍርዱ እንዲፈፀምለት ፍርዱን ለሰጠው ፍ/ቤት የአፈፃፀም ማመልከቻ ማቅረብ እንደሚችል እና የአፈፃፀሙ ስነ-ስርዓትም የሚመራበት አግባብ በፍ/ብ/ሥ/ሥ/ህ/ቁ 378 እና የፍርድ አፈፃፀም ጉዳይን አስመልክቶ የተደነገጉ ተከታዮቹ ድንጋጌዎች መሰረት መሆኑን መገንዘብ ይቻላል። በዚሁ መሰረት በአንድ የፍርድ ባለእዳ ንብረት ላይ ፍርዱ እንዲፈፀምላቸው የሚጠይቁ የፍርድ ባለገንዘቦች ካሉም አፈፃፀሙ በፍ/ብ/ሥ/ሥ/ህ/ቁ 403 ድንጋጌ መሰረት ላስተናገድ እንደሚችል ህጉ ያመላክታል። ይሄውም በፍርድ ቤቱ ትዕዛዝ ተከብሮ የተያዘ ወይም በፍርድ ቤቱ ዘንድ ተቀማጭ የሆነ ሀብት ከመያዙ ወይም ከመቀመጡ በፊት ገንዘብ እንዲከፈላቸው በባለሀብቱ ላይ አስፈርደው እንደፍርዱ እንዲፈፀምላቸው የሚጠይቁ የፍርድ ባለገንዘቦች ሲቀርቡ ፍ/ቤቱ በፍርዱ መሰረት ያለመፈፀሙን ካረገገጠ በኋላ ተገቢውን ኪሳራ እና ወጪ ቀንሶ የተያዘውን ሀብት በውሳኔው መሰረት እንዲከፋፈሉ ይደረጋል በሚል በተጠቃሹ ድንጋጌ ስር በግልፅ ተደንግጐ ይገኛል።
No topics extracted.
ወደ ተያዘው ጉዳይ ስንመለስም አመልካች በተጠሪ ላይ የገንዘብ እዳ በ1993 ዓ.ም አስፈርደው እና ገንዘቡም ለክርክሩ መነሻ የሆነው መኖሪያ ቤት በአፈፃፀም ተሸጦ እንዲከፈለው እየጠየቀ ያለ ሲሆን ልላኛው የፍርድ ባለገንዘብ የሆነው አንበሳ ኢንሹራንስም ከዚህ የተለየ ነው በሚል ከግራ ቀኙ የቀረበ ክርክር የለም። ንብረቱም በፍ/ቤቱ ተከብሮ የተያዘ መሆኑ እስከተገለፀ እና እንዲሁም በድንጋጌው ስር የተመለከቱት ልሎች መስፈርቶችም እስከተሟሉ ድረስ አመልካችን ጨምሮ የሁሉም የፍርድ ባለመብቶች የአፈፃፀም ጥያቄ ከፍ/ብ/ሥ/ሥ/ሕ/ቁ 403 ድንጋጌ ይዘት አኳያ በንብረቱ ላይ ቀጥሎ ላስተናገድ ይገባል እንጂ አመልካች ልላ የፍ/ባለመብት በልላ የፍ/ቤቱ አፈፃፀም መዝገብ ላይ ያሰጠውን የእግድ ትዕዛዝ አስነስቶ ካልቀረበ በቀር አፈፃፀሙ ላቀጥል አይችልም መባሉ የስነ-ስርዓት ህጉን የተከተለ አካሄድ ሆኖ አላገኘንም። በልላ በኩል በንብረቱ ላይ የመያዣ ውልን መነሻ በማድረግ ከልሎች ፍርድ ባለገንዘቦቹ የተለየ ወይም የቀዳሚነት መብት አለን የሚሉ ወገኖችም ካሉ ጥያቄው ሲቀርብ እንደየአግባብነቱ ታይቶ ተገቢው ምላሽ የሚሰጥበት ይሆናል እንጂ አፈፃፀሙ በዚህ ምክንያት ከወዲሁ ላቀጥል አይችልም መባሉም ተገቢ አይደለም።
ስለሆነም አፈፃፀሙን ሲመራ የነበረው የፍድራሉ መጀመሪያ ደረጃ ፍ/ቤት አመልካችን ጨምሮ በተጠሪ ላይ የገንዘብ ክፍያ ፍርድ አሰጥተው እና ገንዘቡም እንዲከፈላቸው የአፈፃፀም ጥያቄ ያቀረቡ የፍርድ ባለገንዘቦችን አስቀርቦ ጥያቄያቸውን በመመርመር እና ጉዳዩንም ከፍ/ብ/ሥ/ሥ/ሕ/ቁ 403 ድንጋጌ ይዘት እና መንፈስ አኳያ አገናዝቦ በመመልከት አፈፃፀሙ ቀጥሎ እንደፍርዱ ላፈፀም በሚቻልበት አኳኋን አፈፃፀሙን መምራት ሲገባ ጉዳዮቹ በየተናጠል በመምራት እና በስተመጨረሻም ለዚህ ክርክር መነሻ የሆነው የአፈፃፀም ጉዳይ ላቀጥል አይችልም በማለት የአፈፃፀም መዝገቡን መዝጋቱ እና ይሄውም በይግባኝ ሰሚ ፍ/ቤት ታይቶ መታረም ሲገባ መፅናቱ ስለፍርድ አፈፃፀም የተመለከቱትን የፍ/ብሕር ስነ-ስርዓት ህግ ድንጋጌዎች ያላገናዘበ በመሆኑ መሰረታዊ የሆነ የህግ ስህተት የተፈፀመበት ሆኖ አግኝተናል። በመሆኑም ተከታዩን ውሳኔ ሰጥተናል።
የፍድራል መጀመሪያ ደረጃ ፍ/ቤት በኮ.መ. በ12/2/2006 ዓ/ም የሰጠው ትዕዛዝ እና የፍድራል ከፍተኛ ፍ/ቤት በኮ/መ/ በ7/6/2005 ዓ/ም የሰጠው ትዕዛዝ በፍ/ብ/ስ/ህ/ቁ 348(1) መሰረት ተሽሯል።
የፍድራሉ መጀመሪያ ደረጃ ፍ/ቤት ከዚህ በላይ በፍርዱ ክፍል እንደተጠቀሰው በኮ/መ/ እንዲቋረጥ የተደረገው የአፈፃፀም ጉዳይ እንዲቀጥል በማድረግ እና ጉዳዩንም ከፍ/ብ/ስ/ስ/ህ/ቁ 403 እና ልሎች አግባብነት ካላቸው ድንጋጌዎች አኳያ አገናዝቦ አፈፃፀሙ እንዲመራ በማድረግ በጉዳዩ ላይ ተገቢውን የአፈፃፀም ውሳኔ እንዲሰጥበት ዘንድ ጉዳዩን በፍ/ብ/ሥ/ሥ/ሕ/ቁ 343(1) መሰረት መልሰን ልከንለታል። ይፃፍ።
የሰበር ክርክሩን ወጪና ኪሳራ ግራ ቀኙ የየራሳቸውን ይቻሉ ብለናል።