No summary available.
ሰኔ 20 ቀን 2005 ዓ.ም.
ዳኞች- ተሻገር ገ/ሥላሴ አልማው ወል ዓላ መሐመድ ረታ ቶሎሳ ሙስጠፋ አህመድ አመልካቾች፡-
ይህ የሰበር ጉዳይ በፍ/ብ/ሥ/ሥ/ሕ/ቁ 458 የተመለከተውን ድንጋጌ አተገባበር የሚመለከት ነው።
ጉዳዩም መነሻ የአሁን አመልካቾች በየመን አገር ፍ/ቤት በተሰጠ ፍርድ ባለመብት መሆናቸውን ገልፀው ይህንኑ በውጭ አገር ፍ/ቤት የተሰጠን ፍርድ የፍደራል ከፍተኛ ፍ/ቤት ያስፈጽምልን በማለት ያቀረቡት አቤቱታ ሲሆን የአሁን ተጠሪም የመን አገር በተሰጠው ፍርድ የክርክር ተካፋይ ስላልነበርኩ መብቴን የነካ ፍርድ ስለሆነ ፍርዱ ላፈፀም አይገባም በማለት ከዚህ በፊት በአመልካቾች ጥያቄ መሰረት ተሰጥቶ የነበረውን ፍርድ ተቃውሟል።
አመልካቾችም ክርክሩ በየመን አገር ሲደረግ ተጠሪው ኢትዮጵያ ውስጥ ስለነበረ ፍ/ቤቱ ወኪል አቁሞለት በወኪል የክርክር ተከፋይ የነበረ መሆኑንና ይህንንም ክርክር ተጠሪው ማቅረብ የሚችለው ፍርዱን ለሰጠው ለየመን አገር ፍ/ቤት እንጂ ለዚህ ፍ/ቤት አይደለም በማለት መልሳቸውን የሰጡበት ስለመሆኑ የስር የፍደራል ከፍተኛ ፍ/ቤት ከሰጠው ብይን ግልባጭ ተገንዝበናል።
ፍ/ቤቱም ይህንኑ የግራ ቀኙን ክርክር ጉዳይ ተመልክቶ በኮ/መ/ በቀን 17/9/2ዐዐ3ዓ.ም በዋለው ችሎት ከዚህ ቀደም አመልካቾች በየመን አገር የተሰጠው ፍርድ ይፈፀምልን በማለት ያቀረቡት አቤቱታ በፍ/ብ/ሥ/ሥ/ሕ/ቁ 456-461 የተመለከተውን ቅደመ ሁኔታ ያሟላ መሆኑ ታይቶና በፍርድ ባለዕዳነትም የተሰየሙት ወገኖች ያልተቃወሙት ስለሆነ ፍ/ቤቱ በዚሁ መዝገብ በቀን 25/2/02ዓ.ም በዋለው ችሎት በውሣኔው መሰረት እንዲፈፀም ትዕዛዝ ሰጥቷል። የአሁን ተጠሪ በስር ፍ/ቤቱ የፍርድ ተቃዋሚ ሆኖ በፍ/ብ/ሥ/ሥ/ሕ/ቁ 358 መሰረት ይፈጽም የተባለው ፍርድ ስህተት አለበት እኔ በክርክሩ ሳልሳተፍ የተሰጠ ፍርድም በመሆኑ መብቴን ተነክቷል በማለት የቀረበው ክርክር ላቀርብ የሚገባው ጉዳዩን አከራክሮ ፍርዱን በሰጠው በየመን አገር ፍ/ቤት እንጂ ፍርዱ በሚፈፀምበት ፍ/ቤት አይደለም። ችሎቱ እያየ ያለው የአፈጻጸምን ጉዳይ እንደመሆኑ በዚህ የአፈጻጸም ጉዳይ ላታይ የሚገባው የክርክር ዓይነት በፍ/ብ/ሥ/ሥ/ሕ/ቁ 418 መሰረት ፍርዱን ለማስፈፀም ሲባል በተያዘ ንብረት ላይ የሚቀርብ አቤቱታ የሆነ እንደሆነ ነው። የአሁን ተጠሪ የተቃውሞ ክርክር ያቀረበበት ጉዳይ በየመን ሀገር ፍ/ቤት ፍርድ ያረፈበት ንብረት የሚመለከት በመሆኑ በፍ/ብ/ሥ/ሥ/ሕ/ቁ 418 መሰረት የሚሸፈን አይደለም። በመሆኑም ተቃውሞው ተቀባይነት የለውም የሚለውን የፍርድ ትንታኔ ሰጥቶ ከዚህ በፊት እንደየመን አገር ፍ/ቤት ፍርድ ይፈፀም ሲል ሰጥቶት የነበረውን ትዕዛዝ አጽድቋል።
የአሁን ተጠሪ ለፍደራል ጠቅላይ ፍ/ቤት ባቀረበው የይግባኝ ቅሬታ ላይ እኔ በክርክሩ ሳልካፈልበት የተሰጠው ፍርድና ለማስፈፀም በፍ/ብ/ሥ/ሥ/ሕ/ቁ 458/ሀ/ መሰረት በሁለቱ አገሮች ፍርድን ለማስፈፀም ስምምነት ሣይኖር በየመን አገር የተሰጠው ፍርድ በኢት/ያ ፍ/ቤቶች እንዲፈፀም መበየኑ ተገቢ አይደለም ይሻርልኝ በማለት ባቀረበው ክርክር መነሻ ይግባኝ ሰሚው ፍ/ቤት በጉዳዩ ላይ ግራ ቀኙን ካከራከረ በኋላ በፍ/ብ/ይ/መ/ቁ 7ዐዐ47 ጥር 3ዐ ቀን 2ዐዐ4ዓ.ም በዋለው ችሎት ጉዳዩን መርምሮ፡በውጭ አገር የተሰጠን ፍርድ በኢት/ያ ለማስፈፀም የሚቻለው ከፍ/ብ/ሥ/ሥ/ሕ/ቁ 456-461 በተደነገገው መሰረት መሆን ይገባዋል። በተለይም በፍ/ብ/ሥ/ሥ/ቁ/ 458/ሀ/ በኢት/ያና ፍርዱን በፈረደው አገር መካከል ፍርዱን የማስፈፀም ስምምነት ላኖር ይገባል። ኢት/ያና የመን በፍርዱ ላይ ማህተም ማድረጋቸው የፍርድ ሰነድ ከየመን ወደ ኢት/ያ ሲገባ የሰነዱን ትክክለኛነት ለማረጋገጥ ሲባል የተከናወነ የማስተባበል ስራ እንጂ በአገሮች መካከል ፍርድን ለማስፈፀም ስምምነት መደረጉን አያመለክትም። ስለሆነም ይኸው የህጉ ማሟያ ሣይሟላ የተሰጠው ፍርድ ተሸሯል። በማለት ከወጭና ኪሣራ ጋር ወስኗል።
ይህ የሰበር ጉዳይ የቀረበው በዚሁ በፍደራል ጠቅላይ ፍ/ቤት ይግባኝ ሰሚው ችሎት በተሰጠው የመጨረሻ ፍርድ ላይ የአሁን አመልካቾች የሰበር አቤቱታቸውን በማቅረባቸው ነው።
በዚህ የሰበር ደረጃም ሁለቱም ወገኖች ያላቸውን ክርክር በጽሑፍ አቅርበው ክርክሩ ተጠናቋል።
No topics extracted.
የጉዳዩ አመጣጥ ከዚህ በላይ ባጭር ባጭሩ በይዘት ደረጃ የተመለከተው ሲሆን እኛም ጉዳዩን እንደሚከተለው ተመልክተናል።
በፍ/ብ/ሥ/ሥርአት ህጉ የተመለከተው የፍርድ አፈጻጸም ጉዳይ በሁለት ዓበይት ምዕራፎች የተመለከተ ሲሆን በምዕራፍ 1 ላይ የተመለከተው በኢት/ያ ግዛት ውስጥ የተሰጠን ፍርድ በማስፈፀም ረገድ ተፈጻሚነት ያላቸው ድንጋጌዎች ሲሆን በምዕራፍ 2 ከፍ/ብ/ሥ/ሥ/ሕ/ቁ 456 እስከ 461 የተጠቀሱት ድንጋጌዎች ደግሞ በውጭ ሀገር የተሰጠ ፍርድ ወይም ብይን የሚፈፀምበትን ሁኔታ የሚያመለክቱ ናቸው። ከዚህ ከህጉ አቀራረጽ መገንዘብ የሚቻለው ግራ ቀኙን እያከራከረ ያለው ጉዳይ በይዘቱ የፍርድ አፈጻጸምን የሚመለከት እንጂ ለአፈጻጸሙ ምክንያትና መነሻ ከሆነው ፍርድ ጋር በተያያዘ የሚነሣን ክርክር ለመጋበዝ ወይም ለማስተናገድ የሚያስችል አይደለም።
ሆኖም ምንም እንኳ ጉዳዩ በይዘቱ የአፈጻጸም ጉዳይ ቢሆንም ይፈፀም የተባለው ፍርድ በውጭ ሀገር የተሰጠ ፍርድ ከመሆኑ የተነሣ ይህንኑ ፍርድ በኢት/ያ ፍ/ቤቶች ዕውቅና ተሰጥቶት ለማስፈፀም የሚቻለው በፍ/ብ/ሕ/ሥ/ሥ/ሕ/ቁ 458 የተመለከቱትን ቅደመ ሁኔታዎች መሟላታቸው የተረጋገጠ እንደሆነ ብቻ መሆኑን በግልጽ ተመልክቷል።
እነዚህ በዚሁ ድንጋጌ የተመለከቱት ፍርዱን ለማስፈፀም የተመለከቱት ቅድመ ሁኔታዎች መሟላታቸውንና አለመሟላታቸውን አስመልክቶ ክርክር በቀረበ ጊዜም በፍ/ብ/ሥ/ሥ/ሥ/ሕ/ቁ 459 እና 460 በተደነገገው መሰረት ይህንኑ አስመልክቶ የሚቀርበውን ሙግት ሰምቶ ዳኝነት የሚሰጠው እራሱ የፍርዱን አፈጻጸም የያዘው ፍ/ቤት ነው።
በህጉ የተመለከተው ትክክለኛ የጉዳዩ አካሄድ ይህ ሆኖ እያለ የአፈጻጸም ጉዳዩ የቀረበለት ፍ/ቤት በግራ ቀኙ መካከል የተነሣውን የክርክር አግባብነት ከፍ/ብ/ሥ/ሥ/ሕ/ቁ 458 አንጻር በማየት ጉዳዩን ሰምቶ የመወሰን ስልጣኑ እና የዳኝነት ስራ ተግባሩ መሆኑ እየታወቀ የፍደራል ከፍተኛ ፍ/ቤት የአሁን ተጠሪ ያቀረበው ክርክር ፍርዱን በሰጠው በየመን አገር ፍ/ቤት ላቀርብ የሚገባው እንጂ በዚህ ፍርዱን ለማስፈፀም ሲባል የአፈጻጸም ጉዳዩ በቀረበለት ፍ/ቤት የሚታይ አይደለም በማለት የሰጠው ትርጉም ለጉዳዩ አግባብነት ያለውን እና ከላይ የተመለከቱትን ስነ ስርአታዊ ድንጋጌዎች ትክክለኛ አፈጻጸም የተከተለ አይደለም።
የአሁን ተጠሪም በመቃወሚያነት ካቀረባቸው ክርክሮች መካከል ይፈፀም በተባለው ፍርድ በተሰጠበት ጊዜ የመከራከር መብቴ አልተጠበቀም ይህንኑ ፍርድ በኢትዮጵያ አገር ፍ/ቤቶች ለማስፈፀም የሚቻል ስለመሆኑ በሁለቱ አገሮች መካከል ስለዚሁ ጉዳይ የተደረገ ስምምነት ስለመኖሩ አልተረጋገጠም የሚሉት ሁለቱ የመከራከሪያ ነጥቦች በፍ/ብ/ሥ/ሥ/ሕ/ቁ 458 /ሀ/ እና /ሐ/ የሚወድቁ ሲሆኑ ልሎች በተለይም በዚህ ሰበር ሰሚ ችሎት አስቀድሞ በኢትዮጵያ በሚገኙ የኃይማኖት ፍ/ቤቶች ታይቶ ፍርድ ባገኘ ጉዳይ በድጋሚ በየመን ሀገር ፍ/ቤት ላስተናገድ አይገባም የሚለው ክርክሩ በዚህ በተያዘው የአፈጻጸም ጉዳይ ቀርቦ ላስተናገድ የሚችልበት ስርአት አልተዘረጋም። በፍ/ብ/ሥ/ሥ/ሕ/ቁ 458 ስር የተመለከቱትን ነጥቦች በይዞታቸው ማየት እንደሚቻለው በአለም አቀፍ ህግ የሁለት አገሮችን ግንኙነት ከሚገዛው የአለም አቀፍ ህግ መርህና በኢትዮጵያ ተቀብላ ባፀደቀቻቸው የሲቪልና የፖለቲካ አለም አቀፍ ስምምነት በአንቀጽ14 ስር የተመለከተውን በህግ በተቋቋመ ፍ/ቤት ፊት የመዳኘት እና በክርክር በእኩል አይን የመታየት መብትን ለማስከበር ሲባል የተመለከቱትን መብቶች ተከብረውና ተጠብቀው የተሰጠ ፍርድ መሆኑ ታውቆ ማስፈፀም እንዲቻል በኢትዮጵያ ዝርዝር ህግ የተመለከቱ አንኳር ነጥቦች ናቸው እንጂ ማንኛውንም የክርክር ነጥቦች ባካተተ መንገድ የተቀረፀ ባለመሆኑ በግራ ቀኙ መካከል የተነሣው የክርክር ነጥብ በፍ/ብ/ሥ/ሥ/ሕ/ቁ 458 ስር ከተመለከቱት ሁኔታዎች ጋር የተገናኘ መሆኑ በቅድሚያ ላረጋገጥ የሚገባው በመሆኑ ነው።
ከዚህም አንጻር የአሁን ተጠሪ በቁጥር 458/ሀ/ የተመለከተውን ድንጋጌ ተንተርሶ ፍርዱን በኢትዮጵያ አገር ባሉ ፍ/ቤቶች ለማስፈፀም የሚያስችል በሁለቱ አገሮች ተመሣሣይ ስምምነት ስለመኖሩ አልተረጋገጠም በማለት ሲከራከር የአሁን አመልካቾች በበኩላቸው በየመን አገር የተሰጠው ፍርድ በኢትዮጵያ የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ተረጋግጦ በሁለቱም አገሮች በሚመለከታቸው ክፍሎች ተረጋግጦ የገባ መሆኑን የሚያመለክቱ ሰነዶችን ከማቅረባቸውም ባሻገር ሰለዚሁ ጉዳይ ተጨማሪ ማስረጃ ይቅረብልን በማለት እንደጠየቁ ከጉዳዩ አመጣጥ ተረድተናል። ይህ ጉዳይ በአገር ደረጃ የሚደረግ ስምምነት በመሆኑ ይህ አይነት ስምምነት ስለመኖሩና አለመኖሩ የማረጋገጥ ግድታ እንደማንኛውም በተከራካሪ እጅ እንደሚገኘ ማስረጃ ተቆጥሮ መቅረብ በሚገባው ጊዜና አኳኋን ካልቀረበ በቀር ተቀባይነት የለውም የሚል የጠበቀ የስነ ስርዓት መስፈርትን የሚከተል አይደለም ይልቁንም ይህ አይነቱ የተጨማሪ ማስረጃ ጥያቄ በቀረበ ጊዜ ይግባኝ ሰሚው ፍ/ቤት በፍ/ብ/ሥ/ሥ/ሕ/ቁ 345(1)ለ እንደተመለከተው የሚቀርበው ማሰረጃ ለጉዳዩ ትክክለኛ ፍርድ ለመስጠት የሚያስችል ከመሆኑ በላይ ይግባኝ ሰሚው ፍ/ቤት ተገቢ መስሎ ቢታየው በማናቸውም ምክንያት በተከራካሪው ወገን ጠያቂነትም ሆነ በእራሱ አነሣሽነት ይኸው አይነት ተጨማሪ ማስረጃ እንዲቀርብ ለመፍቀድ ለማዘዝ ስልጣን ያለው በመሆኑ በዚህ አግባብ ይኸው የሁለቱ አገሮች ስምምነት ያለ መሆኑንና አለመሆኑን ለሚመለከታቸው መንግስታዊ ክፍሎች በትዕዛዝ ማጣራት እየተገባው በአመልካቾች የቀረበው ማሰረጃ ስለማስረጃው ትክክለኛነት ከሚያረጋግጥ በቀር ስምምነት ስለመኖር ለማስረዳት ብቃት የለውም በሚለው ብቻ ተገድቦ የሰጠው ዳኝነት የማስረጃ አቀባበል ስርዓትን መሰረት ያደረገ ሆኖ አላገኘነውም። በዚህም ረገድ የአሁን ተጠሪ የተጨማሪ ማስረጃው ጥያቄ ስርዓቱን ጠብቆ በጊዜው የቀረበ ባለመሆኑ ተቀባይነት የለውም የሚለውም ክርክሩ በተመሣሣይ ምክንያት የህግ መሰረት ያለው አይደለም።
እንዲሁም የፍደራል ጠቅላይ ፍ/ቤት ጉዳዩን በይግባኝ ተመልክቶ በፍ/ብ/ሥ/ሥ/ሕ/ቁ 458/ሀ/ በተመለከተው ድንጋጌ አፈጻጸም ላይ ብቻ ተወስኖ የሰጠው ዳኝነት በመሆኑ ምክንያት የአሁን ተጠሪ በፍ/ብ/ሥ/ሥ/ሕ/ቁ 458/ሐ/ መሰረት ይፈፀም በተባለው ፍርድ አሰጣጥ ሂደት የክርክር ተካፋይ አልነበርኩም የመደመጥ መብቴ አልተከበረም በሚል ባነሳው ክርክር ሳቢያ አመልካቾችም በፍርዱ ሂደት ተጠሪው ኢት/ያ ውሰጥ የነበረ በመሆኑ በሀገሪቱ ህግ መሰረት ወኪል በፍ/ቤቱ ቆሞለት የታየ ጉዳይ ነው በማለት በመከራከራቸው የፍ/ብ/ሥ/ሥ/ሕ/ቁ 458/ሐ/ በዝምታ እንዳለፈው ከይግባኝ ሰሚው ፍ/ቤት ፍርድ ተረድተናል። ፍርድ ቤቱ ደርሶበት እንደነበረው መደምደሚያ ፍርዱን በዚህ አኳኋን መስጠት የሚቻል ሰለመሆኑ በፍ/ብ/ሥ/ሥ/ሕ/ቁ 247/4/ እና 182/3/ የተደነገገ ቢሆንም በፍርዱ መሰረት አድርጎ በያዘው የህግ ጭብጥ ላይ የሰጠው ዳኝነት በዚህ ሰበር ሰሚ ችሎት የህግ መሰረት ያለው ሆኖ ባለመገኘቱ የአሁን ተጠሪ በተደራቢነት አቅርቦት የነበረውን ነገር ግን በዝምታ ያለፈው ከፍ/ብ/ሥ/ሥ/ሕ/ቁ 458/ሐ/ ጋር በተያያዘ የተነሣውን የመደመጥ መብት የመከበርና ያለመከበር ሟሟያ ሁኔታንም በይግባኝ ሰሚነት ስልጣኑ እንደገና ተመልክቶ ዳኝነት ላሰጥበት የሚገባው ነጥብ ሆኖ ተገኝቷል።
በዚህ ሁሉ ምክንያት ይግባኝ ሰሚው ፍ/ቤት በጉዳዩ ላይ የሰጠው ውሣኔ መሰረታዊ የህግ ስህተት የተፈፀመበት ሆኖ ስላገኘነው የሚከተለውን ውሣኔ በአብላጫ ድምጽ ሰጥተናል።
ይግባኝ ሰሚው የፍደራል ጠቅላይ ፍ/ቤት በፍ/ይ/መ/ቁ 7ዐዐ47 ጥር 3ዐ ቀን 2ዐዐ4ዓ.ም የሰጠው ፍርድ ሙሉ በሙሉ ተሽሯል።
በፍርድ ሀተታው ላይ እንደተገለፀው በፍ/ብ/ሥ/ሥ/ሕ/ቁ 458/ሀ/ እና 458/ሐ/ በተመለከተ ግራ ቀኙ ባቀረቡት ክርክር ላይ ብቻ ተወስኖ እንዲሁም በቁጥር 458/ሀ/ን በሚመለከት በአሁን አመልካቾች በኩል የቀረበውን የተጨማሪ ማስረጃ አቀራረብ ጥያቄ ተቀብሎ በአመልካቾችም ሆነ በእራሱ አነሣሽነት ማስረጃውን በማየትና በማስቀረብ አስፈላጊውን ዳኝነት ይሰጥበት ዘንድ በፍ/ብ/ሥ/ሥ/ሕ/ቁ 343/1/ መሰረት መዝገቡን ለፍደራል ጠቅላይ ፍ/ቤት ይግባኝ ሰሚ ችሎት መልሰናል።
በዚህ ሰበር ሰሚ ችሎት የተደረገው ክርክር ላስከተለው ወጭና ኪሣራ ግራ ቀኙ የየራሣቸውን ይቻሉ።
መዝገቡን ዘግተናል። ወደ መዝገብ ቤት ይመለስ።
የመስማሚያ ሀሣብ እኔ ስሜ በሶስተኛው ተራ ቁጥር የተጠቀሰው ዳኛ አብላጫው ድምጽ የፍደራል ጠቅላይ ፍ/ቤት ይግባኝ ሰሚ ችሎት የሰጠውን ውሣኔ በመሻር ጉዳዩ እንደገና ተጣርቶ እንዲወሰን በደረሰበት መደምደሚያና በሰጠው ውሣኔ እስማማለሁ። ሆኖም ጉዳዩ መመለስ ያለበት ለፍደራል ጠቅላይ ፍ/ቤት ይግባኝ ሰሚ ችሎት ሣይሆን ለፍደራል ከፍተኛ ፍ/ቤት መሆን ይገባዋል የሚል ሀሣብ ያለኝ በመሆኑና ጉዳዩ ሲመለስ በጭብጥነት ላያዙ ስለሚገቡ ጉዳዬች ከአብላጫው ድምጽ የምለይባቸው ነጥቦች ያለ በመሆኑ ይህንን የመስማሚያ ሀሣብ ጽፍለሁ።
አመልካቾች በየመን አገር የተሰጠው ፍርድ እንዲፈፀምላቸው ያቀረቡትን አቤቱታ በመቀበል የፍደራል ከፍተኛ ፍ/ቤት ጥቅምት 25 ቀን 2ዐዐ2ዓ.ም ውሣኔ ሲሰጥ የአሁን ተጠሪ በፍ/ሥ/ሥ/ሕግ ቁጥር 459 ንዑስ አንቀጽ 1 መሰረት ቀርቦ አስተያየቱን አልሰጠም። ተጠሪ በእሱ በኩል የሚቀርቡ መከራከሪያዎች ሣይሰሙ የፍደራል ከፍተኛ ፍ/ቤት በየመን አገር የተሰጠው ፍርድ በኢትዩጵያ ውሰጥ ተፈጻሚ እንዲሆን በፍ/ሥ/ሥ/ሕ/ቁ/ 460/1/ መሰረት የሰጠው ውሣኔ ተሰርዞ የመን አገር የተሰጠው ፍርድ በኢትዩጵያ ውስጥ ተፈጻሚ ላሆን ይገባዋል ወይም አይገባውም? የሚለው ጭብጥ እሱ ባለበት ታይቶ እንዲወሰንለት ጥቅምት 1ዐ ቀን 2ዐዐ3ዓ.ም የፍርድ መቃወሚያ ማመልከቻ ያቀረበ መሆኑን የፍደራል ከፍተኛ ፍ/ቤት በመዝገብ ግንቦት 19 ቀን 2ዐዐ3ዓ.ም ከሰጠው ውሣኔ ለመረዳት ይቻላል።
የፍደራል ከፍተኛ ፍ/ቤት ተጠሪ በክርክሩ ተካፋይ ሣይሆን የአመልካቾችን አቤቱታ በመቀበል በየመን አገር የተሰጠው ፍርድ በኢትዩጵያ ውስጥ ተፈጻሚ እንዲሆን ጥቅምት 25 ቀን 2ዐዐ2ዓ.ም የሰጠው ውሣኔ በመሰረታዊ ይዘቱና ባህሪው በየመን አገር የተሰጠው ፍርድ በፍ/ሥ/ሥ/ሕ/ቁጥር 458 የተደነገጉትንና ልሎች አስፈላጊ መስፈርቶች የሚያሟላ በመሆኑ ፍርዱ በኢትዩጵያ ግዛት ክልል ባሉ ፍርድ ቤቶች ላፈፀም የሚችል መሆኑን ለማረጋገጥና በፍርድ ዕውቅና ለመስጠት የተሰጠ በፍ/ሥ/ሥ/ሕ/ቁጥር 46ዐ ንዑስ አንቀጽ 1 እና ንዑስ አንቀጸ 2 መሰረት የተሰጠ ውሣኔ ነው። ይህ ውሣኔ በፍ/ሥ/ሥ/ሕ/ቁጥር 358 መሰረት ለመቃወምና እንዲሰረዝ ለማድረግ የሚቻልበት ስርዓት ከፍተሐ ብሕር ስነ ስርዓት ሕግ ቁጥር 358 እስከ ፍታሐ ብሕር ስነ ስርዓት ሕግ ቁጥር 46ዐ ተዘርግቷል።
የፍደራል ከፍተኛ ፍ/ቤት ተጠሪ በፍ/ሥ/ሥ/ሕ/ቁጥር 358 መሰረት የተቃወመው በየመን አገር የተሰጠው ፍርድ በኢትዩጵያ ውስጥ ላፈፀም የሚችል ነው በማለት ፍርድ ቤቱ ጥቅምት 25 ቀን 2ዐዐ2 ዓ.ም በፍ/ሥ/ሥ/ሕ/ቁጥር 46ዐ የሰጠውን ውሣኔ መሆኑን ሣያገናዝብና በየመን አገር ፍ/ቤት የተሰጠው ፍርድ በኢትዩጵያ ውስጥ ላፈፀም የሚችል መሆኑን የሚረጋገጥና ዕውቅና የሚሰጥ ውሣኔ እንጂ የአፈጻጸም ትዕዛዝ እንዳልሆነ ሣይገነዘብ ተጠሪ መቃወሚያውን ማቅረብ ያለበት ፍርዱን ለሰጠው የየመን አገር ፍርድ ቤት እንጂ ለፍደራል ከፍተኛ ፍ/ቤት አይደለም። እንደዚሁም ክርክሩ የአፈጻጸም ክርክር በመሆኑ በፍ/ሥ/ሥ/ሕ/ቁጥር 418 ከተደነገገው ስርዓት ውጭ ተጠሪ ጥቅምት 25 ቀን 2ዐዐ2ዓ.ም የሰጠሁትን የአፈጻጸም ውሣኔ መቃወም አይችልም የሚል ይዘት ያለው ብይን ግንቦት 17 ቀን 2ዐዐ3 ዓ.ም ሰጥቷል።
ተጠሪ ለፍደራል ጠቅላይ ፍ/ቤት ይግባኝ ሰሚ ችሎት ይግባኝ ያቀረበው የፍደራል ከፍተኛ ፍ/ቤት ጥቅምት 25 ቀን 2ዐዐ2ዓ.ም የሰጠውን ውሣኔ በመሰረዝ እኔ ባለሁበት ጉዳይ ታይቶ እንዲወሰን ያቀረብኩት ጥያቄ ውድቅ ማድረጉን በመቃወም ነው። ይግባኝ ሰሚው ችሎት አመልካቾች እንዲፈፀምላቸው እየጠየቁ ያሉት በየመን አገር የተሰጠ ፍርድ በኢትዩጵያ ላፈፀም ይችላል ወይስ አይችልም? የሚለውን ጭብጥ በመያዝ በየመን አገር የተሰጠው ፍርድ በኢትዩጵያ ውስጥ ተፈጻሚ ላሆን አይችልም በማለት የፍ/ሥ/ሥ/ሕ/ቁጥር 358/ሀ/ መሰረት በማድረግ ውሣኔ ሰጥቷል። በእኔ እምነት የፍደራል ጠቅላይ ፍ/ቤት ይግባኝ ሰሚ ችሎት የፍደራል ከፍተኛ ፍ/ቤት ተጠሪ ፍ/ቤቱ ጥቅምት 25 ቀን 2ዐዐ2 ዓ.ም የሰጠውን ውሣኔ በመቃወም ያቀረበውን ክርክር በመቀበልና የአመልካቾችን ክርክርና ማሰረጃ በመቀበል በጉዳዩ ላይ ውሣኔ መስጠት አለበት ወይም የለበትም? የሚለውን ጭብጥ በመመስረት የስር ፍ/ቤት የተጠሪን የፍርድ መቃወሚያ ማመልከቻና የአመልካቾችን ክርክር በመስማትና በመመርመር ውሣኔ እንዲሰጥበት በፍ/ሥ/ሥ/ሕ/ቁጥር 341/1/ መሰረት ጉዳዩን መመለስ ነበረበት። ይግባኝ ሰሚው ችሎት የስር ፍ/ቤት ወደ ይዘቱ ገብቶ ያላየውንና ውሣኔ ያልሰጠበትን ጭብጥ ማለትም በየመን አገር የተሰጠ ፍርድ በኢትዩጵያ ላፈፀም ይችላል ወይስ አይችልም? የሚለውን ጭብጥ በመያዝ የሰጠው ውሣኔ አመልካቾች በየመን አገር የተሰጠው ፍርድ በኢትዩጵያ ውስጥ ላፈፀም ይገባል የሚሉበትን የተሟላ ክርክርና ማስረጃ የማቅረብ መብትና ተጠሪም በየመን አገር የተሰጠው ፍርድ በኢትዩጵያ ውስጥ ላፈፀም አይገባውም የሚልበትን የተሟላ ክርክርና ማስረጃ የማቅረብ መብት የሚያጣብብ ነው። እንደዚሁም በዚህ ጭብጥ ላይ በሚሰጠው ውሣኔ ተከራካሪዎቹ ላኖራቸው የነበረውን የይግባኝ መብት ያጣበበ ነው የሚል ሀሣብ አለኝ
ከዚህ አንጻር ከሰበር ችሎት ይግባኝ ሰሚው ችሎት የፍደራል ከፍተኛ ፍ/ቤት አመልካቾች በኢትዩጵያ ውስጥ እንዲፈፀምላቸው የጠየቁት የየመን ፍ/ቤቶች የሰጡት ፍርድ በኢትዩጵያ ውስጥ ላፈፀም የሚችል ነው ወይስ አይደለም? በሚለው ጭብጥ ላይ የግራቀኙን ክርክርና ማስረጃ በመስማት ውሣኔ እንዲሰጥበት በፍ/ሥ/ሥ/ሕ/ቁጥር 341/1/ መሰረት መመለስ ነበረበት። ይህንን አለማድረጉ መሰረታዊ የሕግ ስህተት ነው በማለት በሰበር በመሻር የፍደራል ከፍተኛ ፍ/ቤት በየመን አገር የተሰጠው ፍርድ በኢትዩጵያ ውስጥ ላፈፀም ይችላል ወይስ አይችልም? በሚለው ጭብጥ ላይ የአመልካቾችንና የተጠሪን የተሟላ ክርክርና ማሰረጃ ሰምቶ እንዲወሰን ላመለስለት ይገባል። አብላጫው ድምጽ ጉዳዩን ለይግባኝ ሰሚው ችሎት መመለሱ አመልካቾችና ተጠሪ በስር ፍ/ቤት የተሟላ ክርክርና ማስረጃ የማቅረብ መብታቸውን የሚያሣጣና የይግባኝ መብታቸውንም የሚያጣብብ ነው የሚል ሀሣብ ያለኝ በመሆኑ ጉዳዩ መመለስ የሚገባው ለይግባኝ ሰሚው ፍርድ ችሎት ሣይሆን ለፍደራል ከፍተኛ ፍ/ቤት መሆን ይገባዋል በማለት ይህንን የመስማሚያ ሀሣብ ጽፍለሁ።
ይህንን የመስማሚያ ሀሣብ ለመጻፍ ያነሣሣኝ ሁለተኛው ምክንያት አብላጫው ድምጽ ጉዳዩን ወደ ይግባኝ ሰሚው ችሎት የመለሰው አመልካቾች በኢትዩጵያ ውስጥ እንዲፈፀምላቸው ያቀረቡት በየመን አገር የተሰጠ ፍርድ በፍ/ሥ/ሥ/ሕ/ቁጥር 358/ሀ/ እና /ሐ/ ድንጋጌዎች የተቀመጡትን መስፈርቶች ያሟላ መሆኑን ወይም አለመሆኑን በማጣራት ውሣኔ እንዲሰጥበት በማዘዙ ነው። በእኔ በኩል ይግባኝ ሰሚው ችሎት በየመን አገር የተሰጠው ፍርድ በፍ/ሥ/ሥ/ሕ/ቁጥር 358 ከ/ሀ/ እስከ ከ/ሰ/ የተደነገጉትን ሁሉንም መስፈርቶች የሚያሟላ መሆኑን ወይም አለመሆኑን በማጣራትና በማረጋገጥ ውሣኔ ላሰጥበት ይገባል የሚል ሀሣብ አለኝ። በተለይም ተጠሪ አመልካቾች በየመን አገር በተሰጠ ፍርድ የፍርድ ባለመብት ሁነንበታል የሚሉት ጉዳይ በኢትዩጵያ የሸሪዓ ፍርድ ቤቶች ታይቶ የመጨረሻ ውሣኔ የተሰጠበትና በፍርድ ያለቀ ነው የሚል መቃወሚያና ክርክር እንዳቀረበ አብላጫው ድምጽ በውሣኔው ካሰፈረ በኋላ ይህን ጉዳይ በኢትዩጵያ ሸሪዓ ፍ/ቤት ውሣኔ ያገኘ ነው የሚለው መቃወሚያ ላስተናገድ የሚችልበት ስርዓት በፍ/ሥ/ሥ/ሕ/ቁጠር 458 እንዳልተዘረጋ ውሣኔው በገጽ 17 በመጨረሻው ፖራግራፍ በመግለጽ የሰጠው ምክንያትና የሕግ አተረጓጎም አልተቀበልኩትም።
ተጠሪ ጉዳዩ በኢትዩጵያ የሸሪያ ፍ/ቤት የመጨረሻ ውሣኔ ያገኘና በፍርድ ያለቀ ነው በማለት ያቀረበው መከራከሪያ በየመን አገር የተሰጠው ፍርድ ይፈፀምልን በማለት አመልካቾች ያቀረቡትን ጥያቄ ለመቃወምያ ላሆን የሚችል መሰረታዊ መከራከሪያ ነው የሚል ሀሣብ አለኝ። በአገራችን በፍርድ በተቋጨ ጉዳይ ልላ ክስ ማቅረብ እንደማይቻል በፍ/ሥ/ሥ/ሕ/ቁጥር 5/1/ ተደንግጓል። ይህም የአገሪቷ ፍ/ቤቶች በሕግ በተሰጣቸው የዳኝነት ስልጣን መሰረት በማድረግ አከራክረው የመጨረሻ ውሣኔ በሰጡት ጉዳይ የውጭ አገር ፍ/ቤቶት የሰጡት ውሣኔ አለና ይፈፀምልን የሚል ጥያቄ ቢቀርብ የኢትዩጵያ ፍ/ቤቶች ይህንን ጥያቄ የመቀበል የአገሪቱ ፍ/ቤቶች በፍርድ የሰጡት ጉዳይ ላይ የውጭ አገር ፍ/ቤት የሰጠውን ፍርድ ተፈጻሚ እንዲሆን የሚፈቅዱበት የሕግ መሰረት የለም። በእኔ እምነት ጥያቄው ከጅምሩ የአገሪቱን ፍርድ ቤቶች ብሄራዊ የዳኝነት ስልጣን የሚጋፋ ስለሆነ ውድቅ ላደረግ የሚገባው ነው የሚል ሀሣብ አለኝ፡ በያዝነው ጉዳይ ተጠሪ ጉዳዩ በሸሪዓ ፍ/ቤት የመጨረሻ ውሣኔ የተሰጠበት ነው የሚለውን ክርክር የቀረበ ቢሆንም ጉዳዩ በኢትዩጵያ የሸሪዓ ፍ/ቤት ውሣኔ ተሰጥቶበታል ወይስ አልተሰጠበትም? ጉዳዩ በሸሪዓ ፍ/ቤት ውሣኔ የተሰጠበት ከሆነ አመልካቾች በዚያው ጉዳይ በየመን አገር ፍ/ቤቶች የሰጡት ውሣኔ እንዲፈፀምላቸው ያቀረቡት ጥያቄ ህጋዊ መሰረት ያለው ነው ወይስ አይደለም? የሚሉት ጭብጦች በመያዝ ይግባኝ ሰሚው ችሎት በማጣራትና በማረጋገጥ ውሣኔ እንዲሰጥበት የሰበር ችሎት መመሪያ /ትዕዛዝ/ ላሰጥ ይገባዋል የሚል ሀሣብ አለኝ። ስለመሆኑም የሰበር ችሎት የፍደራል ጠቅላይ ፍ/ቤት በመዝገብ ቁጥር 7ዐዐ47 ጥር 3ዐ ቀን 2ዐዐ4ዓ.ም የሰጠው ውሣኔ እንዲሻርና ጉዳዩ ተጣርቶ እንዲወሰን በደረሰበት መደምደሚያ የምስማማ ቢሆንም ከላይ በዝርዝር በገለጽኳቸው ነጥቦች ከአብላጫው ድምጽ የምለይ በመሆኑ ይህንን የመስማሚያ ሀሣብ አስፍሬአለሁ፡ የማይነበብ የአንድ ዳኞች ፊርማ አለበት።