No summary available.
ታህሳስ 04 ቀን 2006 ዓ.ም.
ዳኞች፡- አልማው ወል ዓላ መሐመድ ረታ ቶሎሳ አዳነ ንጉሤ ሙስጠፋ አህመድ አመልካች፡- ግሎባል ኢንሹራንስ አልቀረበም ተጠሪዎች፡-
ለዚህ የሰበር ክርክር መነሻ የሆነው ጉዳይ በአሁን የሰበር ተጠሪዎች ከሳሽነት የተጀመረው በአዳማ ልዩ ዞን ከፍተኛ ፍርድ ቤት ሲሆን አመልካች ደግሞ ተከሳሽ ነበር። ክሱም የከሳሾች አውራሽ የጋራ ንብረት የሆነው የሰልዳ ቁጥሩ 3.19516 ኦ.ሮ ሚኒባስ መኪና በተከሳሽ ኩባንያ የኢንሹራንስ ሽፋን ያለው ሲሆን በ20/10/2004 ዓ.ም ከጠዋቱ 12፡10 ሲሆን ከአዳማ ወደ አዲስ አበባ እየተጓዘ ቢሾፍቱ ከተማ መግቢያ ላይ ትክክለኛ ምልክት ሳያሳይ መንገድ ዘግቶ የቆመውን መኪና በመግጨት ከፍተኛ የሆነ ጉዳት የደረሰበት ሲሆን ተከሳሽም መኪናውን አንስቶ የተጎዱ ተሽከርካርካሪዎች ወደሚጠገኑበት ቦታ ወስዶ መኪናውም ሙሉ በሙሉ ከጥቅም ውጪ መሆኑን ካረጋገጠ በኋላ የተሸርካሪውን ዋጋ ብር 350,000 ለመክፈል ዝግጁ መሆኑን ለከሳሾች ከገለጸ በኋላ መኪናው ላይ አደጋ የደረሰው ትርፍ ሰው በመጫኑ ምክንያት በመሆኑ ክፍያውን እንደማይፈጽም ስለገለጸልን የሚፈለግበትን ብር 350,000 ከ20/10/2004 ዓ.ም ጀምሮ ከሚታሰብ ህጋዊ ወለድ 9% ጋር እንዲከፍል ይወሰንበት የሚል ነው።
ተከሳሽም በሰጠው መልስ፡- ለመኪናው ኢንሹራንስ የተገባለትና ከአደጋ ቦታም እንዲነሳ የተደረገ ቢሆንም ስለአደጋው ፖላስ ሪፖርት እንዲያቀርብ ተጠይቆ በሰጠው ምላሽ በመኪናው ላይ አደጋ በደረሰበት ጊዜ 18 ሰዎችን ጭኖ የነበረ መሆኑን ገልጿል። በከሳሾችና እና በከሳሽ መካከል የተደረገው የውል ስምምነትም በኢንሹራንስ ፖላሲ ላይ የተመሰረተ ሲሆን አደጋው የደረሰበት መኪናም ሹፍሩን ሳይጨምር የመጫን አቅሙ 11 ሰው ሆኖ እያለ 7 ሰዎችን በትርፍ ጭኖ በጠቅላላው 18 ሰዎችን ጭኖ የደረሰ አደጋ መሆኑና አደጋውም የደረሰው ከአቅም በላይ በመጫኑ ምክንያት ፍሬን እንዳይታዘዝ በማድረጉና መሪውንም ወደሚፈለግበት መምራት ባለመቻሉ ነው።
ኢንሹራንስ ዋስትና የተገባለት ተሸርካርካሪ መጫን ከሚችለው አቅም በላይ ትርፍ በመጫን አደጋ በደርሰበት ጊዜ በኢንሹራንስ ፖላሲ አንቀጽ 6 በተመለከተው መሰረት አደጋ የደረሰበትን መኪና ዋጋ ተከሳሽ የመክፈል ግድታ ስለማይኖረው ክሱ ተቀባይነት የለውም ሲል ተከራክሯል።
የዞኑ ከፍተኛ ፍርድ ቤትም ከተከሳሽ ድርጅት እና ከኢትዮጵያ ኢንሹራንስ ድርጀት አንድ አንድ የሰርቬይ ባለሙያ በማስቀረብ ሙያዊ ምስክርነታቸውን በመስማት እንዲሁም ከትራፊክ ፖላስ ስለአደጋው የቀረበውን ሪፖርት ከባለሙያዎቹ የምስክርነት ቃል በማገናዘብ እና በመመርመር በሰጠው ውሳኔ፡- ከአቅም በላይ መጫን አደጋ አያስከትልም ማለት የማይቻል ቢሆንም ከትራፊክ ፖላስ የቀረበው የመኪና አደጋ ሪፖርት ለአደጋው መድረስ መንስኤ የሆነው በፍጥነት በማሽከርከርና በማንቀላፋት መሆኑን ከሚገልጽ ውጪ አደጋው መኪናው ከአቅም በላይ በመጫኑ ምክንያት መሆኑን የማያመለክት ስለሆነና ሪፖርቱም አደጋ በደረሰበት ጊዜ ያለውን ሁኔታ መሰረት አድርጎ የቀረበ በመሆኑ የሚታመን ነው፤በልላ በኩል ተከሳሽ አደጋ የደረሰው ከአቅም በላይ መኪናው በመጫኑ ነው ቢልም በከሳሾችና ተከሳሽ መካከል በ30/08/2012 የተፈረመው የኢንሹራንስ ውል ስምምነት ኢንሹራንስ የተገባለት መኪና ከአቅም በላይ ወይም ትርፍ ሰው ጭኖ ቢገኝ ካሳ አይከፈልም የሚል ባለመሆኑ የውል ስምምነቱ ለሚደርሰው የሞት አደጋ፣የአካል ጉዳት እንዲሁም በንብረት ላይ ለሚደርሰው ጉዳት ካሳ የሚከፈል መሆኑን ስለተስማሙና ይህም ስምምነት በፍ/ህ/ቁ/1731(1) መሰረት ህግ ሆኖ ስለሚያስገድድ ተከሳሽ ክስ የቀረበበትን ገንዘብ ከነወለዱ፣ለዳኝነት የተከፈለውን እንዲሁም ወጪና ኪሳራ ላከፍል ይገደዳል ብሐል።
ጉዳዩ በይግባኝ የቀረበለት የኦሮሚያ ጠ/ፍርድ ቤት ይግባኝ ሰሚ ችሎት አመልካች ያቀረበውን የይግባኝ በፍ/ሥ/ሥ/ህ/ቁ/337 መሰረት በመዝጋት በማሰናበቱ የሰበር አቤቱታውን ለዚህ ችሎት አቅርቧል።
አመልካች ባቀረበው የሰበር አቤቱታም የጠቀሳቸው የቅሬታ ነጥቦች ፡-ጉዳት የደረሰበት ሚኒባስ መኪና የኢንሹራንስ ሽፋን ዋስትና የተገባለት ቢሆንም በወቅቱ 18 ሰዎችን አሳፍሮ ሲጓጓዝ መንገድ ዳር ተበላሽቶ ከቆመ መኪና ጋር ተጋጭቶ 14 ሰዎች ሞተው 4 ሰዎች የተጎዱ መሆኑን የአድአ ወረዳ ፖላስ በደብዳቤ ከገለጸው የተረጋገጠ ሲሆን በኢንሹራንስ ውሉም ሆነ በመንገድ ትራንስፖርት ባለሥልጣን በተሰጠው የባለቤትነት ማረጋጫ ደብተር(ላብሬ)የመኪናው የመጫን አቅም 11 ሰው ብቻ መሆኑ በተገለጸበት ሁኔታ መኪናው 7 ሰዎችን በትርፍነት ጭኖ ጉዳቱ በመድረሱ በኢንሹራንስ ኩባንያ ፖላሲ ጠቅላላ ማግለያ በሚለው ክፍል ተራ ቁጥር 6 ‹‹ በኢንሹራንስ ውሉና ከሚመለከተው አካል በተሰጣቸው የባለቤትነት ማረጋጫ ደብተር ላይ ከተገለጸው ሰው ብዛትና መኪናው ካለው መቀመጫ ብዛት በላይ ጭኖ ለሚደርስ አደጋ ኢንሹራንስ ኩባንያው ማንኛውንም ክፍያ ለመክፈል ኃላፊነት አይኖርበትም ›› ስለሚል ይህንንም ግድታ ኢንሹራንስ ሰጭም ሆነ ኢንሹራንስ ገቢው በንግድ ህግ አንቀጽ 657(2-3) መሰረት በተጨማሪ የማግለያ ውል የግድታ ስምምነት የተፈራረምን ስለሆነ አመልካች የጉዳት ካሳውን ለመክፈል እንደማልገደድ በመጠቀስ ያቀረብኩትን ክርክር ፍርድ ቤቶቹ ሳይቀበሉት ያለፉት አግባብነት የለውም፤
አንድ መኪና ከአቅም በላይ ጭኖ ሲጓዝ እንደፈለጉት መሪም ሆነ ፍሬን መያዝ መቆጣጠር እንደማይቻል እና ከአቅም በላይ መጫን ለአደጋ ምክንያት እንደሚሆን የባለሙያ ምስክርነት በተሰጠበት ሁኔታ ፍርድ ቤቱ ከአቅም በላይ መጫን ለአደጋ ምክንያት አይሆንም፣እንዲሁም በኢንሹርነስ ፖላሲው ላይ ከሳሾች ግድታ ገብተው የፈረሙት ነገር ስለልለ የመኪናውን ግምት፤የጠበቃ አበል 10 ፐርሰንት ወጪ ኪሳራ ብር 500 ጨምሮ አመልካች ላከፍል ይገባል ሲሉ የወሰኑት ተቀባይነት የለውም የሚሉ ናቸው።
ተጠሪዎች በበኩላቸው በሰጡት መልስ፡-በአመልካችና በተጠሪዎች መካከል በተደረገው የኢንሹራንስ ዋስትና ውል የመድን ሽፋን የተሰጠው መኪና ትርፍ ሰው ከጫነ አመልካች ኃላፊነት አይኖረውም በሚል አልተስማማንም፣ በዚህ መልኩ ስለመዋዋላችን የሚገልጽ ማስረጃም አመልካች ለሥር ከፍተኛ ፍርድ ቤት አላቀረበም፤አመልካች የኢንሹራንስ ፖላሲ ነው በማለት ለሥር ፍርድ ቤት ያቀረበውም የፖላሲ ቁጥር የልለው ለማስታወቂያ ተብሎ የተዘጋጀውን ብሮሸር በመሆኑ ተጠሪዎችን የሚያስገድድ አይሆንም፤ እንዲሁም በተሽርከርካሪው ላይ አደጋ የደረሰው በፍጥነት በመንዳትና በአሽከርካሪው ማንቀላፋት ምክንያት መሆኑን በማረጋገጥ የትራፊክ ፖላስ ማስረጃ የሰጠበት ጉዳይ በመሆኑ አመልካች አደጋው የደረሰው ትርፍ ሰው በመጫኑ ምክንያት ነው ሲል ያቀረበው ክርክር ተቀባይነት የለውም ሲሉ ተከራክረዋል።
ተጠሪዎች ላቀረቡት መልስም አመልካች የመልስ መልስ በማቅረብ ተከራክሯል።
የጉዳዩ አመጣጥ ከዚህ በላይ የተመለከተው ሲሆን እኛም፡- ጉዳት ለደረሰበት መኪና ተጠሪዎች የጠየቁትን ገንዘብ አመልካች የመክፈል ኃላፊነት አለበት? ወይስ የለበትም? የሚለውን ጭብጥ ይዘን ክርክሩን እንደሚከተለው መርምረናል።
በአመልካችና በተጠሪዎች መካከል የንብረት ኢንሹራንስ ውል ስለመደረጉ በግራ ቀኙ የታመነ ጉዳይ ሲሆን አመልካችም የተጠሪዎች ንብረት ለሆነው ጉዳት ለደረሰበት ሚኒባስ መኪና የብር 350,000 የዋስትና ሽፋን ሰጥቷል። መኪናውም በደረሰበት አደጋ ጉዳት የደረሰበት መሆኑ የተረጋገጠ ጉዳይ ሲሆን የግራ ቀኙን ወገን እያከራከራቸው የሚገኘው ደግሞ ኢንሹራንስ ሰጪው ለደረሰው ጉዳት በሰጠው ዋስትና ሽፋን መሰረት ኃላፊ የመሆኑና ያለመሆኑ ጉዳይ ነው። አመልካች በመኪናው ላይ ለደረሰው ጉዳት የዋስትናውን ገንዘብ የመከፈል ግድታ የለብኝም ሲል በዋናነት የሚከራከረው መኪናው ላይ አደጋ ላደርስ የቻለው የመጫን አቅሙ 11 ሰዎች ሆኖ ሳለ በትርፍነት ሰባት ሰዎችን በመጫኑ ምክንያት ክብደት በመጨመሩ የመኪናው መሪና ፍሬን እንደልብ ባለመታዘዛቸው ነው። በኢንሹራንስ ፖላሲው ከተቀመጡት ጠቅላላ የማግለያዎች በአንቀጽ 6 የኢንሹራንስ ዋስትና ሽፋን የተሰጠው መኪና መጫን ከሚገባው የሰው ቁጥር በላይ በትርፍነት ጭኖ አደጋ የደረሰበት እንደሆነ አመልካች ኩባንያ የዋስትናውን ገንዘብ የመክፈል ሀላፊነት እንደልለበት ተመልክቷል በሚል ነው። ተጠሪዎች ግን በኢንሹራንስ ፖላሲው ተጠቅሷል በሚል አመልካች ቢከራከርም በማስረጃነት የኢንሹራንስ ፖላስ ነው በማለት ያቀረበው ለማስታወቂያ ሥራ ተብሎ የተዘጋጀ ብሮሸር እንጂ ትክክለኛ የኢንሹራንስ ፖላሲ አይደለም፣እንዲሁም አመልካች የጠቀሰው የማግለያ ምክንያትም አመልካችና ተጠሪዎች በገባነው የኢንሹራንስ ውል ያልተጠቀሰ በመሆኑ የሚያስገድደን አይደለም የሚል ክርክር አቅርበዋል።
የንብረት ኢንሹራንስ ውል ከተለያዩ የውል አይነቶች አንዱ ሲሆን ውሉም ህጋዊ የሆኑ ተግባራት በሚከናወኑበት ጊዜ ላደርስ የሚችለውን ጉዳት በዋስትናው ሽፋኑ መሰረት ለመካስ በማሰብ ላደረግ የሚገባ ነው።
በፍ/ህ/ቁ/1678 (ለ) እንደተመለከተው አንድ ውል በቂ የሆነ እርግጠኛነት ያለውና ህጋዊ የሆነ ጉዳይ ለማከናወን ላደረግ ይገባል። በአመልካችና በተጠሪዎች መካከል የተደረገው የንብረት ኢንሹራንስ ውልም በህጉ መሰረት የተደረገ ነው። ሆኖም ህጋዊ ውል የሚደረገው በህግ እንዲደረግ ያልተፈቀደውን ድርጊት ወይም የህግ ክልከላ የተደረገበትን ጉዳይ በማከናወን ያልተገባ ጥቅም ለማግኘት በማሰብ ወይም በሚኖረው ፍላጎት መነሻ ላሆን አይገባም። የተጠሪዎች መኪና ለህዝብ ትራንስፖርት አገልግሎት የሚውል መሆኑ የታመነ ጉዳይ ሲሆን ይህንኑ አገልግሎት በሚሰጥበት ጊዜም የትርንስፖርት አዋጅ፣ደንብና መመሪያዎችን መከተል ይኖርበታል። ነገር ግን አደጋው በደረሰበት ወቅትም መኪናው መጫን ከሚገባው 11 ሰዎች በላይ 7 ሰዎችን ጭኖ ሲጓዝ እንደነበር የተረጋገጠ ፍሬ ነገር ሲሆን ተጠሪዎቹም ቢሆኑ መኪናው ትርፍ ሰዎችን አልጫነም ሲሉ ያቀረቡት ክርክር የለም። መኪናው ከጫናቸው 18 ሰዎች ውስጥም በወቅቱ 14 ሰዎች መሞታቸው ከክርክሩ መገንዘብ ተችሐል።
መኪናው በህጉ ከተቀመጠው የሰው ቁጥር በላይ መጫኑ የትራንስፖርት ህጉን የሚጥስ ሲሆን ህጉ ተጥሶ ከተፈቀደው የሰው ቁጥር በላይ ሰዎችን ጭኖ ሲጓዝ ለደረሰው አደጋ አመልካች የዋስትናውን ሽፋን ገንዘብ የመክፈል ኃላፊነት ላኖረው አይችልም።
በአጠቃላይ በመኪናው ላይ ጉዳቱ የደረሰው ያለውን የትራንስፖርት ህግ በመጣስ ከወንበር በላይ በትርፍ 7 ሰዎችን ጭኖ ስለመሆኑ ለሥር ፍርድ ቤት የትራፈክ ፖላስ በማስረጃነት ከላከው ሪፖርት የተረጋገጠ ጉዳይ ነው። በመሆኑም በመንገድ ትራንስፖርት ህግ ከሚፈቅደው ውጪ ትርፍ ሰዎችን ጭኖ ሲጓዝ በመኪናው ላይ የደረሰው ጉዳት ሆኖ ባለበት የሥር ፍርድ ቤቶች አመልካች በኢንሹራንስ ውሉ መሰረት የዋስትና ሽፋን ገንዘብ ላከፍል ይገባል ሲሉ የወሰኑት መሰረታዊ የሆነ የህግ ስህተት የተፈጸመበት ሆኖ በመገኘቱ ተከታዩን ውሳኔ ሰጥተናል።
የአዳማ ልዩ ዞን ከፍተኛ ፍርድ ቤት በመ/ቁ/15121 በቀን 14/08/2005 ዓ.ም በዋለው ችሎት የሰጠውን ውሳኔና የኦሮሚያ ጠ/ፍርድ ቤት ይግባኝ ሰሚ ችሎት በመ/ቁ/161389 በቀን 15/08/2005 ዓ.ም በዋለው ችሎት የሰጠውን ትዕዛዝ በፍ/ሥ/ሥ/ህ/ቁ/348(1) መሰረት ሽረናል።
ተጠሪዎች የትራንስፖርት ህጉን ጥሰው ከወንበር በላይ ትርፍ ሰዎችን ጭነው መኪናው እየተጓዘ በመኪናቸው ላይ ለደረሰው ጉዳት አመልካች የዋስትናውን የሽፋን ገንዘብ የመክፈል ኃላፊነት አይኖርበትም ብለናል።
የዚህን ፍርድ ቤት ወጪና ኪሳራ የግራ ቀኙ ወገኖች የየራሳቸውን ይቻሉ።
መዝገቡ የተዘጋ ስለሆነ ወደ መዝገብ ቤት ይመለስ።
No topics extracted.