No summary available.
የካቲት 12 ቀን 2006 ዓ.ም.
ዳኞች፡- አልማው ወል ዓላ መሐመድ ረታ ቶለሳ አዳነ ንጉሴ ሙስጠፋ አህመድ አመልካች፡- አቶ አህመድ አደም በሽር - ከጠበቃ ል/ኮ ስንታየሁ ደመቀ ጋር ቀረቡ ተጠሪ፡- የአማራ ብ/ክ/መንግስት ዐ/ሕግ - የቀረበ የለም መዝገቡ ተመርምሮ የሚከተለው ፍርድ ተሰጥቶአል።
በዚህ መዝገብ አመልካች የሰበር አቤቱታ ያቀረቡት ተጠሪ ያቀረበባቸውን በህክምናና በጤና አጠባበቅ ሙያ ሕገ ወጥ በሆነ መንገድ የመስራት የወንጀል ክስ አስመልክቶ በሶስቱም የክልሉ ፍ/ቤቶች የተሰጠባቸው የጥፋተኝነት ውሳኔ እና በሁለቱ የስር ፍ/ቤቶች ተሰጥቶ በክልሉ ጠ/ፍ/ቤት ሰበር ችሎት የተሻሻለው የቅጣት ውሳኔ መሰረታዊ የሕግ ስህተት የተፈጸመበት በመሆኑ ላታረም ይገባል በማለት ነው።
ተጠሪ በ03/07/2004 ዓ.ም. በተዘጋጀ የክስ ማመልከቻ በኮምቦልቻ ከተማ ወረዳ ፍ/ቤት 3ኛ ተከሳሽ በነበሩት የአሁኑ አመልካች ላይ ያቀረበው ክስ ይዘት ባጭሩ፡- አመልካች በኢ.ፍ.ዲ.ሪ የወንጀል ሕግ በአንቀጽ 535(3)(ሀ) እና (መ) ስር የተደነገገውን በመተላለፍ የህክምና መመርመሪያ መሳሪያዎችን በአግባቡ የመያዝ ሙያዊ ግድታ እያለባቸው በ21/11/2003 ዓ.ም. በኮምቦልቻ ከተማ በቀበል 03 ክልል የኮምቦልቻ ጤና አጠባበቅ ባለሙያዎች የግል ክላኒኮችን ክትትልና ቁጥጥር ለማድረግ በተገኙበት ጊዜ ተከሳሹ ሀያት በተባለ መካከለኛ ክላኒክ በህክምና ባለሙያነት እየሰሩ በነበረበት ጊዜ አንዱን የሽንት መመርመሪ መሳሪያ ለሶስት በመሰነጣጠቅ አብዝተው ሲሰሩ የተገኙ በመሆኑ በህክምና በጤና አጠባበቅ ሙያ ሕገወጥ በሆነ መንገድ የመስራት ወንጀል አድርጎአል የሚል ነው። አመልካች ተጠይቀው ወንጀሉን አላደረግሁም በማለታቸው ተጠሪ በክሱ መሰረት ያስረዱልኛል ያላቸውን ሶስት ምስክሮች አቅርቦ አሰምቶአል። የጽሁፍ ማስረጃም አቅርቦአል።ፍ/ቤቱም ተጠሪ በክሱ መሰረት ያስረዳ መሆኑን ገልጾ አመልካቹ መከላከያቸውን ማሰማት እንዲጀምሩ በወ.መ.ሕ.ስ.ስ.ሕ.ቁ 142 በሰጠው ትዕዛዝ መሰረት አመልካች መሳሪያዎቹ ለልምምድ የሚላኩ የህክምና ሙያ ተማሪዎች ሲጠቀሙባቸው የነበሩ እንጂ ለሕክምና ስራ የዋሉ አለመሆናቸውን ያስረዱልናል በማለት የሰው እና የጽሁፍ ማስረጃ አቅርበዋል።
ፍ/ቤቱም የግራ ቀኙን ማስረጃ ከክሱ ጋር አገናዝቦ ከመረመረ በኃላ አመልካቹ በተጠሪ ማስረጃ የተመሰከረበትን ፍሬ ነገር በማስረጃው አላስተባበለም በማለት በክሱ በተጠቀሰው ድንጋጌ ስር የጥፋተኘነት እና ቀጥሎም የግራ ቀኙን የቅጣት አስተያየት በመቀበል በአመልካቹ ላይ የአራት ዓመት ጽኑ እስራት እና የብር 16,000 መቀጮ ቅጣት ወስኖአል።አመልካች በውሳኔው ቅር ተሰኝተው ይግባኝ በማቅረባቸው የደቡብ ወሎ ዞን ከ/ፍ/ቤት የጥፋተኝነትም ሆነ የቅጣት ውሳኔውን በትዕዛዝ ሲያጸናው የሰበር ክርክሩን የተመለከተው የክልሉ ጠ/ፍ/ቤት ሰበር ችሎት በበኩሉ የጥፋተኝነት እና የጽኑ እስራት ቅጣቱን በማጽናት እና መቀጮውን ብቻ ወደ ብር 10,000 በማሻሻል ውሳኔ ሰጥቶአል።
አመልካች የሰበር አቤቱታ ያቀረቡት ከላይ በተመለከተው ሁኔታ በክልሉ ጠ/ፍ/ቤት ሰበር ችሎት የተሰጠው ውሳኔ መሰረታዊ የህግ ስህተት የተፈጸመበት በመሆኑ ላታረም ይገባል በማለት ሲሆን የሰበር አቤቱታው ተመርምሮ በዚህ ጉዳይ ሶስት ቦታ ተሰነጣጥቆአል የተባለው የሽንት መመርመሪያ መሳሪያ ድርጊቱ በራሱ ጥፋት መሆን አለመሆኑን ከወ.ሕ.አ. 535(ሀ)እና (መ) አንፃር፣ይህ ቢታለፍ የዐ/ሕግ ምስክሮች ወደ ክላኒ ኩ ሲሄዱ በተሰነጣጠቀ የሽንት መመርመሪያ መሳሪያ ባለሙያዎቹ ሲጠቀሙ አላየንም ባሉበት ሁኔታ አመልካች በስር ፍ/ቤቶች ጥፋተኛ ተብሎ የመቀጣቱን አግባብነት ተጠሪ ባለበት ለማጣራት ይቻል ዘንድ ጉዳዩ ለሰበር ክርክር እንዲቀርብ በመደረጉ ግራ ቀኙ የጽሁፍ ክርክር ተለዋውጠዋል። የጉዳዩ አመጣጥ እና የክርክሩ ይዘት ከላይ የተመከለተው ሲሆን እኛም በክርክሩ እልባት ማግኘት የሚገባው ነጥብ ተጠሪ በአመልካች ላይ ባቀረበው ክስ መሰረት የማስረዳት ግድታውን ተወጥቶአል ለማለት ይቻላል ወይስ አይቻልም? የሚል ነጥብ መሆኑን በመገንዘብ አቤቱታ የቀረበበት ውሳኔ መሰረታዊ የሕግ ስሕተት የተፈጸመበት መሆን አለመሆኑን ከዚሁ ጭብጥ አንፃር መርምረናል።
በዚህም መሰረት አመልካቹ ወንጀሉን አልፈጸምኩም በማለት ክደው የተከራከሩ ሲሆን በዐ/ሕግ በኩል የክስ ነጥቡን ለማስረዳት የቀረቡት የተጠሪ ምስክሮች ለቁጥጥር ተግባር በተሰማሩበት ጊዜ አመልካች በሚሰሩበት የመመርመሪያ ክፍል ውስጥ ከሚገኘው ጠረጴዛ ላይ 68 የተሰነጣጠቁ የሽንት መመርመሪያ መሳሪዎችን (ዲፕ ስቲክስ) ማግኘታቸውን ከመግለጽ ውጪ በእነዚህ መሳሪያዎች አመልካቹ ሲገለገሉበት ስለማየታቸው ወይም አመልካቹ ቀደም ብለው የተገለገሉባቸው ስለመሆኑ ወይም በክፍሉ ውስጥ ተቀምጠው የተገኙት በአመልካቹ በአገልግሎት ላይ ላውሉ ታስበው ስለመሆኑ በማረጋገጥ የሰጡት ምስክርነት አለመኖሩን የመዝገቡ ግልባጭ ያመለክታል።የጽሁፍ ማስረጃውም የሽንት መመርመሪያ መሳሪያዎችን ሰነጣጥቆ መጠቀም ተገቢ ስላለመሆኑ የሙያ አስተያየት የተሰጠባቸው ናቸው።የኮምቦልቻ ከተማ ወረዳ ፍ/ቤት ተከሳሽ የመከላከያ ማስረጃ እንዲያቀርቡ ትዕዛዝ የሰጠውና በኃላም አልተከላከሉም በማለት የጥፋተኝነት ውሳኔ ያስተላለፈባቸው ይዘቱ ከላይ በተገለጸው ማስረጃ ላይ ተመስርቶ ሲሆን በበኩላችን ይህ ማስረጃ ዐ/ሕግ በክሱ መሰረት አስረድቶአል ለማለት የሚያስችል መሆን አለመሆኑ በአግባቡ መጤን የሚገባው ሆኑ አግኝተናል።
No topics extracted.
በመሰረቱ አንድ ሰው ወንጀል አደረገ የሚባለው ሕገ ወጥነቱና አስቀጪነቱ በሕግ የተደነገገን ድርጊት ፈጽሞ በተገኘ ጊዜ መሆኑ እና አንድ ወንጀል ተደረገ የሚባለውም ወንጀሉን የሚቋቁሙት ሕጋዊ፣ግዙፋዊ እና ሞራላዊ ፍሬ ነገሮች በአንድነት ተሟልተው ሲገኙ ብቻ መሆኑ በወ.ሕ.አ. 23(1) እና (2) ስር ተደንግጎ የሚገኝ ሲሆን ማንም ሰው በዋና ወንጀል አድራጊነት ወንጀል እንዳደረገ ተቆጥሮ የሚቀጣው በቀጥታ ወይም በእጅ አዙር ወንጀሉን ያደረገ በሆነ ጊዜ ወይም ወንጀሉን እርሱ በቀጥታ ባያደርገውም እንኳን በመላ አሳቡና አድራጎቱ በወንጀሉ ድርጊትና በሚሰጠው ውጤት ሙሉ ተካፋይ በመሆን ድርጊቱን የራሱ ያደረገ በሆነ ጊዜ ስለመሆኑም በወ.ሕ.አ. 32(1) ስር ተደንግጎአል።በወንጀል ጉዳይ የሚቀርብ የክስ ማመልከቻ ተከሳሹ የተከሰሰበትን ወንጀል እንዲሁም የወንጀሉ መሰረታዊ ነገርና ሁኔታዎች የተገለጹበት ላሆን እንደሚገባ እና ስለ ወንጀሉና ስለሁኔታው የሚሰጠው ዝርዝር መግለጫ ተከሳሹ ፈጸመ የተባለውን ተግባር ወንጀል ከሚያደርገው ሕግ አነጋገር ጋር በጣም የተቀራረበ መሆን እንደሚገባው በወ.መ.ሕ.ስ.ስ.ቁ. 111 እና 112 ድንጋጌዎች ላይ የተደነገገውም ከሳሹን ወገን በወ.ሕ.አ. 23(2) ስር የተመለከቱት የወንጀል መማቋቋሚያ ፍሬ ነገሮች ተሟልተው መገኘታቸውን ለማስረዳት እንዲያስችለው መሆኑን ከድንጋጌዎቹ ይዘት መገንዘብ ይቻላል።በልላ አነጋገር ከሳሽ ወገን በክሱ መሰረት የማስረዳት ግድታ ተወጥቶአል ላባል የሚችለው ቀደም ሲል በተጠቀሱት የወ.መ.ሕ.ስ.ስ.ቁ. 111 እና 112 ድንጋጌዎች መሰረት አዘጋጅቶ ባቀረበው የክስ ማመለከቻ መሰረት ተከሳሹ ወንጀል መፈጸሙን ማስረዳት በቻለ ጊዜ ነው።ክሱ የቀረበለት ፍ/ቤትም ተከሳሹ መከላከያ ማስረጃ አቅርቦ ክሱን እንዲከላከል በወ.መ.ሕ.ስ.ስ.ቁ. 142 መሰረት ትዕዛዝ ላሰጥ የሚችለው ከሳሽ ወገን ያቀረበው ማስረጃ ተከሳሹን ጥፋተኛ የሚያደርገው መሆኑን ሲያረጋግጥ ስለመሆኑ በወ.መ.ሕ.ስ.ስ.ቁ. 141 ስር በግልጽ ተደንግጎ ይገኛል።
በተያዘው ጉዳይ በዐ/ሕግ በኩል በቀረበው ማስረጃ የተረጋገጡት መሰረታዊ ፍሬ ነገሮች አመልካች በሚሰሩበት የመመርመሪያ ክፍል ውስጥ ከሚገኘው ጠረጴዛ ላይ 68 የተሰነጣጠቁ የሽንት መመርመሪያ መሳሪዎችን(ዲፕ ስቲክስ) መገኘታቸው ብቻ ሲሆን አመልካቹ ተላልፈውታል ተብሎ የተጠቀሰባቸው ድንጋጌ የሚቀጣው ደግሞ ደህንነቱና ጥራቱ ባልተረጋገጠ፣በተከለከለ፣በተበላሸ፣በተጭበረበረ፣በተበከለ ወይም በማናቸውም ልላ ምክንያት በተጠቃሚው ላይ ጉዳት በሚያደርስ የሕክምና መገልገያ መሳሪያ መገልገልን ነው።በተያዘው ጉዳይ አመልካች ለህክምና ተግባር በእነዚህ መሳሪዎች ሲገለገሉ አልተገኙም፤ተቀምጠው የተገኙት ለሕክምና አገልግሎት ከዋሉ በኃላ ወይም ለማዋል በማሰብ ስለመሆኑም አልተረጋገጠም፤የሽንት መመርመሪያ መሳሪያዎቹ የተሰነጣጠቁት በምን ምክንያት እንደሆነም አልተገለጸም።በመሰረቱ በወ.መ.ሕ.ስ.ስ.ቁ. 141 ስር በግልጽ በተቀመጠው መስፈርት መሰረት ይዘቱ ከላይ የተገለጸው የዐ/ሕግ ማስረጃ ተከሳሹን ጥፋተኛ የሚያደርግ ነው ለማለት የሚያስችል አይደለም።ተጠሪ ለዚህ ችሎት ባቀረበው መልስም ይህንኑ በመገንዘብ በአመልካቹ ላይ ተሰጥቶ የነበረው ውሳኔ ቢሻር ተቃውሞ የልለው መሆን ገልጾአል።
ሲጠቃለል ጉዳዩን በመጀመሪያ ደረጃ የተመለከተው ፍ/ቤት በወ.መ.ሕ.ስ.ስ.ቁ. 141 መሰረት ተከሳሹን ማሰናበት ሲገባው የመከላከያ ማስረጃ እንዲያቀርብ ትዕዛዝ መስጠቱም ሆነ በመጨረሻም የዐ/ሕግን ማስረጃ አላስተባበለም በማለት በአመልካች ላይ የሰጠው እና በክልሉ የበላይ ፍ/ቤቶች ተቀባይነት ያገኘው የጥፋተኝነት የቅጣት ውሳኔ ከላይ የተመለከቱትን መሰረታዊ የሆኑ የወንጀል ሕግ እና የወንጀል ስነስርዓት ሕግ ድንጋጌዎችን የጣሰ እና መሰረታዊ የሕግ ስህተት የተፈጸመበት ሆኖ በመገኘቱ የሚከተለው ውሳኔ ተሰጥቶአል።
በትዕዛዝ የፀናው እና በክልሉ ጠ/ፍ/ቤት ሰበር ችሎት በመ.ቁ. 27041 በ19/10/2005 ዓ.ም. የተሻሻለው የቅጣት ውሳኔ በወ.መ.ሕ.ስ.ስ.ቁ. 195(2)(ለ)(2) መሰረት ተሽረዋአል።
ተጠሪ ባቀረበው የሰው እና የሰነድ ማስረጃ አመልካች ወንጀሉን ማድረጋቸውን ያላስረዳ እና በሕግ የተጣለበትን የማስረዳት ግድታ ያልተወጣ በመሆኑ አመልካች ከተከሰሱበት በህክምናና በጤና አጠባበቅ ሙያ ሕገ ወጥ በሆነ መንገድ የመስራት የወንጀል ክስ በነፃ ላሰናበቱ ይገባል በማለት ወስነናል።
በአመልካች ላይ ተጥሎ የነበረው የአራት ዓመት ጽኑ እስራት ቅጣት የተሻረ ቢሆንም አመልካች ቀደም ሲል በዚህ ችሎት ትዕዛዝ በራሳቸው ዋስትና በዋስ የተለቀቁ በመሆኑ ለማረሚያ ቤት የሚተላለፍ ትዕዛዝ አይኖርም።
አመልካች ተጥሎባቸው የነበረውን የመቀጮ ገንዘብ ለመንግስት ገቢ አድርገው ከሆነ ተመላሽ እንዲደረግላቸው ለሚመለከተው አካል ይፃፍ።
እንዲያውቁት የውሳኔው ግልባጭ ለስር ፍ/ቤቶች ይላክ።
ውሳኔ ያገኘ በመሆኑ መዝገቡ ተዘግቶአል።