No summary available.
መሥከረም 23 ቀን 2006 ዓ ም ዳኞች፡- ተገኔ ጌታነህ ተሸገር ገ/ ሥላሴ አልማው ወል ዓላ መሐመድ ሙሥጠፋ አህመድ አመልካች ተፈሪ ሚናሞ አልቀረቡም ተጠሪ የደቡብ ብሕር ብሕረሰቦችና ሕዝቦች ክልል ዐቃቤ ሕግ አልቀረቡም መዝገቡን መርምረን የሚከተለውን ፍርድ ሰጥተናል።
ጉዳዩ የቀረበው አመልካች የሶዶ ከተማ መጀመሪያ ፍርድ ቤት በመዝገብ ህዳር6ቀን 2005 ዓ.ም፣ የሰጠው ፍርድና የወላይታ ዞን ከፍተኛፍርድ ቤት በመዝገብ በ ጥር 9ቀን 2005ዓ.ም የሰጠው ውሳኔናየደቡብ ብሕር ብሕረሰቦችና ሕዝቦች ክልል ጠቅላይ ፍርድ ቤት የሰበር ችሎትመሰረታዊ የህግ ሥህተት ያለበት ስለሆነ በሰበር ታይቶ ይታረምልኝ በማለት ያቀረቡትን የሰበር አቤቱታ አጣርቶ ለመወሰን ነው።
ጉዳዩ የእምነት ማጉደል ወንጀል የሚመለከት ነው።በሥር ፍርድ ቤት አመካች ተከሳሽ ተጠሪ ከሳሽ በመሆን ተከራክረዋል።
አመልካች በተከሳሽነት ቀርቦ መጀመሪያ ደረጃ የክስ መቃወሚያ አቅርቦ ውድቅ ተደርጎበታል። አመልካች ወንጀል አልፈጸምኩም፣ ጥፋተኛ አይደለሁም በማለት ተከራክሯል።
ተጠሪ ክሱን ለማስረዳት ሥድስት የሰው ምስክሮች አቅርቧል። አንደኛና ሁለተኛ የተጠሪ ምስክሮች የግል ተበዳይና አመልካች ጓደኛሞች መሆናቸውን፣ አመልካች የጋምጎፋ ዞን ደንባ ጎፋ ወረዳ የገንዘብና ኢኮኖሚ ልማት ጽ/ቤት አላቂ ዕቃ ለማቅረብ በጨረታ አሸንፍአለሁ። ለሥራ ማስኪያጃና ለቅድመ ( ሃያ አንድ ሺ ብር) ስጠኝ በማለት በዕምነት ወስዶ አልመለሰም። ልሎቹ ምስክሮች የግል ተበዳይንና አመልካችን ሲያሸማግሉ አመልካች ገንዘቡን የወሰደ መሆኑን ለሽማግልዎቹ ያመነ መሆኑን የመሰከሩ መሆኑን ጉዳዩ ያሳያል። አመልካች በበኩሉ ከግል ተበዳይ በአደራ ወሰድኩት ገንዘብ ላለመኖሩ ያስረዱልኛል በማለት ሁለት የመከላከያ ምስክሮችን እንዳቀረበ ከሥር ፍርድ ቤት ውሳኔ ተገንዝበናል።
የሥር ፍርድ ቤትየግራ ቀኙን ክርክርና ማስረጃ ከሰማና ከመረመረ በኃላተከሳሽ ጨረታ አሸንፍአለሁ በማለት ከግል ተበዳይ ለሥራ ማስኪያጃና ለቅድመ ክፍያ ( ሃያ አንድ ሺ ብር) ያልመለሰ በመሆኑ በወንጀል ሕግ አንቀጽ 675 ንኡስ አንቀጽ 1 የተመለከተውን በመተላለፍ የዕምነት ማጉደል ወንጀል የፈጸመ ጥፋተኛ ነው በማለት አመልካች በ አንድ ዓመት ከ አምስት ወር እሥራት እንድቀጣ ውሳኔ ሰጥቷል።አመልካች በዚህ ውሳኔ ቅር በመሰኘት ይግባኝለ ወላይታ ዞን ከፍተኛ ፍርድ ቤት አቅርቧል።የዞኑ ከፍተኛ ፍርድ ቤት የአመልካችንናየተጠሪን ክርክር ከሰማ በኋላ የስር ፍርድ ቤት ውሳኔ የሰጠውን የጥፋኝነትና የቅጣት ውሳኔ በወንጀለኛ መቅጫ ሥነ ሥርዓት ሕግ ቁጥር195 ንዑስ አንቀጽ2(ለ)2 መሰረት አጽንቶታል። አመልካች ለክልሉ ጠቅላይ ፍርድ ቤት የሰበር አቤቱታ አቅርቦ የሰበር አቤቱታው ውድቅ ተደርጎበታል።
አመልካች ሚያዚያ 11ቀን200ዓ.ም በተጻፈ የሰበር አቤቱታየሥር ፍርድ ቤት፣ የወላይታ ዞን ከፍተኛ ፍርድ ቤትና የክልሉ ጠቅላይ ፍርድ ቤትየሰጡትውሳኔ መሰረታዊ የህግ ስህተት አለበት። የግል ተበዳይ የሰጠው ምስክርነት ለአመልካች ( ሃያ አንድ ሺ ብር) በብድር ሰጥቸው አልመለሰልኝም የሚል ነው።ይህ ፍታብሕራዊ ግኑኝነትን ሚመለከት እንጂ ወንጀል አይደለም። በተጠሪ ክስም ሆነ ማስረጃ እኔ እንደፈጸምኩት የተገለጸው ተግባር በወንጀል ሕግ አንቀጽ 675 ንኡስ አንቀጽ 1 የተደነነውን የእምነት ማጉደል ወንጀል የማቃቁምና በወንጀል ሕጉ በወንጀልነት ያልተደነገገነው። እንደዚሁም ተጠሪ ክስና ማስረጃ አመልካች በወንጀል ህጉ አንቀጽ23 መሰረት የህግ፣ የግዙፍ ተግባርና ሞራል ሁኔታ በተሟላበት ሁኔታ ወንጀል የፈጸምኩ አለመሆኑያላረጋገጠበት ሆኖ እያለ የጥፋተኝነት ውሳኔ መሰጠቱ መሰረታዊ የህግ ስህተት ያለበት ነው። በአጠቃላይ የሥር ፍርድ ቤት፣ይግባኝ ሰሚው ፍርድ ቤትና የክልሉ ጠቅላ ፍርድ ቤት የሰበር ችሎት አመልካችበወንጀል ሕግ አንቀጽ 675 ንኡስ አንቀጽ 1 የተመለከተውን በመተላለፍ የዕምነት ማጉደል ወንጀል የፈጸመ ጥፋተኛ ነው በማለት አመልካች በአንድ ዓመት ከአምስት ወር እሥራት እንድቀጣ የሰጡት ውሳኔ የወንጀል ህጉን አንቀጽ23 የሚተላለፍና መሰረታዊ የህግ ስህተት ያለበት ሥለሆነ በሰበር ታይቶ እንዲታረምልኝ በማለት አመልክተዋል። ተጠሪ መጥሪያ ደርሶትና መልስ የሚያቀርብበት ተለዋጭ ቀጠሮ ተሰጥቶት መልስ ባለማቅረቡ መልስ የመስጠት መብቱ ታልፏል።
ከሥር የክርክሩ አመጣጥና በሰበር የቀረበው ክርክር ከላይ የተገጸው ሲሆን እኛምየሥር ፍርድ ቤትና ይግባኝ ሰሚው ፍርድ ቤት አመልካችበወኝጀል ሕግ አንቀጽ 675 ንኡስ አንቀጽ 1 የተመለከተውን በመተላለፍ የዕምነት ማጉደል ወንጀል የፈጸመ ጥፋተኛ ነው በማለት አመልካች በአንድ ዓመት ከአምስትስት ወር እሥራት እንድቀጣ የሰጡት ውሳኔተገቢ ነው ወይስ አይደለም የሚለውን ጭብጥበመያዝ ጉዳዩን መርምረናል።ጉዳዩን እንደመረመርነው ከላይ የተያዘውን ጭብጥ ለ መወሰን በመጀመሪያ በበታች ፍርድ ቤቶች የተረጋገጡ መሰረታዊ ፍሬ ጉዳዮች አግባብነት ካላቸው የህግ ድንጋጌዎች ጋር መመርመሩ አስፈላጊ ነው።
ተጠሪ አመልካች የእምነት ማጉደል ወንጀል የፈጸመ ስለመሆኑ ለሥር ፍርድ ቤት ያቀረበው ማስረጃ በይዘቱ፣ የግል ተበዳይና አመልካች ጓደኛሞች እንደሆኑ፣ አመመልካች የጋምጎፋ ዞን ደንባ ጎፋ ወረዳ የገንዘብና ኢኮኖሚ ልማት ጽ/ቤት አላቂ ዕቃ ለማቅረብ በጨረታ አሸንፍአለሁ። ለሥራ ማስኪያጃና ለቅድመ ( ሃያ አንድ ሺ ብር) ስጠኝ በማለት የጠየቀው መሆኑንና ገንዘቡን የግል ተበዳዩ አመልካችንሰነዶችን በሚስቱ በኩል በማስፈረም በመያዥነት ይዞ ገንዘቡን ለአመልካች የሰጠው መሆኑን፣ አመልካች ገንዘቡን ለግል ተበዳይ ያልመለሰ መሆኑን እንዳስረዱ ከሥር ፍርድ ቤት ውሳኔ ለመገንዘብ ችለናል።ፍሬ ጉዳይ የማጣራትና ማስረጃ የመመዘን ሥልጣን ባላቸው ፍርድ ቤቶች የተረጋገጡትና ከላይ የተገለጹት ተግባራት የግል ተበዳይና በአመልካች መካከል የመሰረቱት ግኙኝነት አደራ ሰጭና የአደራ ተቀባይ ነው ወይስ አበዳሪና የተበዳሪ ግኑኝነት አመልካችና የተጠሪ ግኑኘነት አበዳሪና የተበዳሪ ግኑኙነት አላቸው ቢባልህጋዊ ውጤቱ ምንድን ነው የሚሉት ጥያቄዎች መታየት ያለባቸው ሆነው አግኝተናቸዋል።
ከላይ የተነሳውን ጥያቄ ለመመለስ የወንጀል ሕግ አንቀጽ 675 ድንጋጌ አቀራረጽ ፣ዝርዝር ይዘትናመሰረታዊ ዓላማ መመርመሩ አስፈላጊ ነው። በወንጀል ህጉ በንብረት ላይ የሚፈጸሙ ወንጀሎችን በሚዘረዝርበት ምእራፍ ሁለት በልዩ ሁኔታ በተንቀሳቃሽ ንብረቶች ላይ የሚፈጸሙ ወንጀሎችን በሚዘረዝረው ክፍል አንድ ሥር የተደነገገ የዕምነት ማጉደል ወንጀል መሰረታዊ ባህሪ፣ ይዘትና የሚስከትለውን ኃላፊነት የሚዘረዝር ድንጋጌ ነው።የወንጀል ሕግ አንቀጽ 675 ንዑስ አንቀጽ1 ድንጋጌ የአማረኛ ቅጅ ቃል በቃል ሲነበብ ማንም ሰው ተገቢ ብልጽግና ለማግኘት ወይምለልላ ሰው ለማስገኘት በማሰብ የልላ ሰው የሆነውንና ለአንድ ለተወሰነ ግልጋሎት ወይም በአደራ የተሰጠውን ዋጋ ያለውን ነገር ወይም ጥሬ ገንዘብ በሙሉ ወይም በከፊል ለራሱ ደረገ፣ ወይም ለልላ ሰው የደረገ፣የወሰደ፣ ያስወሰደ፣ የሰወረ ወይም ለራሱ ወይም ለልላ ሰው አገልግሎት ያዋለ ወይም ይህን መሳሰለውን ማናቸውንም አድራጎት የፈጸመ እንደሆነ እንደነገሩ ሁኔታ በቀላል እስራት ወይም ከአምስት ዓመት በማይበልጥ ጽኑ እስራት ይቀጣል በማለት ይደነግጋል።የወንጀል ሕግ አንቀጽ 675 ንዑስ አንቀጽ3 የተከሳሹ ወንጀል ሃሳብ ግምት ሚደነግግ ሲሆን ይዘቱም ተከሳሹ ሲጠየቅ በእምነት ወይም በአደራ የተሰጠውን ዕቃ ወይም ጥሬ ገንዘብ ለመመለስ ወይም ለመክፈል ወይም ዕቃው ያለበትን ሁኔታ ለማሳየት ወይም ለተገቢው አገልግሎት ያዋለው መሆኑን ማስረዳት ካልቻለ ለራሱ ወይም ለልላ ሰው ያልተገባ ጥቅም ማዋል ሀሳብ እንዳለው ይቆጠራል የሚል ይዘት ያለው ነው።
የእንግላዘኛውን ቅጅ ስንመለከት- Breach of Trust የሚል ርዕሥ ያለው አንቀጽ 675 Whoever, with intent to obtain for himself or to procure for a third person an unjustifiable enrichment, appropriates, or procures for another, takes or causes to be taken, misappropriates, uses to his own benefit or that of a third person, or disposes of for any similar act, in whole or in part, a thing or a sum of money which is the property of another and which has been delivered to him in trust or for a specific purpose, is punishable, according to the circumstances of the case, with simple imprisonment, or with rigorous imprisonment not exceeding five years. በማለት በንዑስ አንቀጽ1 የሚደነግግ ሲሆን ንዑስ አንቀጽ3 The intent to obtain for himself or to procure for third person an unjustifiable enrichment shall be presumed where the criminal is unable upon call, to produce or repay the thing or sum entrusted, or at the time when he should have returned it or accounted there for. በማለት ይደነግጋል።
አመልካች ከግል ተበዳይ ጨረታ ያሸነፍኩ ስለሆነ ለሥራ ማስኪጂያና ለቅድመ ክፍያ ( ሃያ አንድ ሺ ብር) የጠየቀና የግል ተበዳይም የአመልካችን ሰነዶች በመያዥነት ይዞ የሰጠው መሆኑን በተጠሪ ማስረጃ እንደተገለጸ ተረድተናል። አንድ ሰው ለልላወ የተበደረውን ነገር በአይነቱ ለመመለስ ተገዳጅ በማድረግ ገንዘብ ወይም በማገልገል የሚያልቅ ልላ ነገር ለተበዳሪው ለመስጠትና ኃብትነቱን ለማስተላለፍ የሚፈጽሙት ተግባር የማያልቅ ነገር ብድር እንደሆነ ከፍታብሕር ሕግ ቁጥር 2471 ከተሰጠው ትርጓሜ ድንጋጌ ለመረዳት ይቻላል። አንድን ነገር በብድር መሥጠትና አንድን ነገር በአደራ መስጠት የተለያየ ባህሪና ይዘት ላቸው ናቸው። አደራ አደራራ ተቀባዩ አደራ አስቀማጩ ሰጠውን ዕቃ ተቀብሎ በአደራ እንዲያስቀምጥለት የሚገባው ግደታና ተግባር መሆኑንከፍታብሕር ሕግ ቁጥር2779 ከተሰጠው ትርጓሜ ለመረዳት ይቻላል። በአደራ የተቀበሉትን ገንዘብ ለአደራ አስቀማጩ አለመመለስ የወንጀል ሕግ አንቀጽ 675 ንዑስ አንቀጽ1 በመተላለፍ በዕምነት ማጉደል ወንጀል ላያጠየቅ የማይችል የወንጀል ተግባር ነው።
በአንጻሩ ተበዳሪ በብድር የወሰደውን ገንዘብ በወቅቱ አለመክፈሉ አግባብነት ባላቸው ህግ ድንጋጌዎች በፍታብሕር ከሚጠየቅ በሰተቀርየወንጀል ሕግ አንቀጽ 675 ንዑስ አንቀጽ1 ተላልፏል ተብሎ በዕምነት ማጉደል ወንጀል ላጠየቅ የማይችል መሆኑንከወንጀል ሕግ አንቀጽ 675 ድንጋጌ ዝርዝር ይዘት ለመረዳት ይቻላል።.ማንም ሰው በዕምነት ማጉደል ወንጀል የሚጠየቀው ተገቢ ብልጽግና ለማግኘት ወይምለልላ ሰው ለማስገኘት በማሰብ የልላ ሰው የሆነውንና ለአንድ ለተወሰነ ግልጋሎት ወይም በአደራ የተሰጠውን ዋጋ ያለውን ነገር ወይም ጥሬ ገንዘብ በሙሉ ወይም በከፊል ለራሱ ያደረገ፣ ወይም ለልላ ሰው ያደረገ፣የወሰደ፣ ያስወሰደ፣ የሰወረ ወይም ለራሱ ወይም ለልላ ሰው አገልግሎት ያዋለ መሆኑ ሲረጋገጥ ነው ። የአመልካች አድራጎትየወንጀል ሕግ አንቀጽ 675 ንዑስ አንቀጽ3 በሚደነግገው ወንጀል ሃሳብ ግምት የማይሸፈን መሆኑን ከድንጋጌው ይዘት ለመረዳት ይቻላል።
ማንኛውም ሰው የወንጀል ክስ ሲቀርብበት የተከሰሰበት ድርጊት በተፈጸመበት ጊዜ ድርጊቱን መፈጸሙ ወይም አለመፈጸሙ ወንጀል መሆኑ በህግ ካልተደነገገ በስተቀር ላቀጣ እንደማይችል በህገ መበንግስቱ አንቀጽ22 ንዑስ አንቀጥ 1 ተደንግጓል። ከዚህ በተጨማሪ አንድ ሰው በወንጀል ጥፋተኛ ተብሎ የሚቀጣው የህግ ፣የግዙፍ ተግባርና የሞራል ሁኔታ መሟላቱ ሲረጋገጥ እንደሆነ በወንጀል ህጉ አንቀጽ23 ተደንግጓል።
በያዝነው ጉዳይ ከላይ ዘረዘርነው የግዙፍ ድርጊት የህግ የሃሳብ ሁኔታዎች አልተሟሉም። ይህ ሁኔታ መሟላቱን ሳያረጋግጡ የሥር ፍርድ ቤትና ይግባኝ ሰሚው ፍርድ ቤትና የክልሉ ጠቅላይ ፍርድ ቤት የሰበር ችሎት አመልካችበወንጀል ሕግ አንቀጽ 675 ንኡስ አንቀጽ 1 የተመለከተውን በመተላለፍ የዕምነት ማጉደል ወንጀል የፈጸመ ጥፋተኛ ነው በማለት አመልካች በአንድዓመት አምስት ወር እሥራት እንዲቀጣ የሰጡት ውሳኔ የወንጀል ሕግ አንቀጽ 675 ድንጋጌ አቀራረጽ ፣ዝርዝር ይዘትና መሰረታዊ ዓላማ ያላገናዘበና መሰርታዊ የህግ ስህተት ያለበት በማለት ወስነናል።
የሶዶ ከተማ መጀመሪያ ፍርድ ቤት ፣ የወላይታ ዞን ከፍተኛፍርድ ቤትናየደቡብ ብሕር ብሕረሰቦችና ሕዝቦች ክልል ጠቅላይ ፍርድ ቤት የሰበር ችሎት የሰጡት የጥፋተኝነትና የቅጣት ውሳኔ በወንጀለኛ መቅጫ ሥነሥርዓት ህግ ቁጥር195 ንዑስ አንቀጽ2(ለ)1 መሰረት ተሸሯል።
አመልካች ጨረታ አሸንፍለሁ በማለት ለሥራ ማስኬጃና ለቅድመ ክፍያ የሚሆን ብር21000( ሃያ አንድ ሺ ብር) ከግል ተበዳዩ በብድር የወሰደውን ገንዘብ ለግል ተበዳይ አለመክፈሉ ( አለመመለሱ) አመልካችን በወንጀል ሕግ አንቀጽ 675 ንኡስ አንቀጽ 1 ድንጋጌ መሰረት በዕምነት ማጉደል ወንጀል የሚያስጠይቀው ባለመሆኑ በነጻ ይሰናበታል በማለት ወስነናል።
አመልካች ከቀረበበት ወንጀል ክስ በነጻ ተሰናበተ በመሆኑ ከእስር እንዲለቀው ለክፍሉ ማረሚያ ቤት ይጻፍ።
መዝገቡ ወደ መዝገብ ቤት ይመለስ
No topics extracted.