No summary available.
ታህሳስ 14 ቀን 2006 ዓ.ም.
ዳኞች:- አልማው ወል ዓላ መሐመድ ረታ ቶለሳ አዳነ ንጉሴ ሙስጠፋ አህመድ አመልካች፡- አቶ አብነት ዋቆ ብሩ - ጠበቆች መሃመድ አሚን እና ጫንያለው እሸቱ ቀረቡ ተጠሪ፡- የኦሮሚያ ክልል ዐቃቤ ህግ - የቀረበ የለም **
መዝገቡ ተመርምሮ ተከታዩ ፍርድ ተሰጥቷል።
**
ጉዳዩ ወንጀል ሲሆን ክርክሩ የተጀመረው የአሁኑ ተጠሪ ባሁኑ አመልካች ላይ በጂማ ዞን ከፍተኛ ፍርድ ቤት በመሰረተው ክስ መነሻ ነው። የክሱ ይዘትም፡- አመልካች በ1996 ዓ/ም በወጣው የወንጀል ሕግ አንቀጽ 543(2) ስር የተመለከተውን በተመላለፍ በሾፍርነቱ ሙያቸው የልላውን ሕይወትና ደህንነት የመጠበቅ ግድታ እያለባቸው ግንቦት 09 ቀን 2005 ዓ/ም ከጠዋቱ 12፡30 ሲሆን የሰልዳ ቁጥሩ 3-28157 ኦሮ የሆነውን ሚኒባስ መኪና እያሽከረከረ ከጅማ ከተማ ወደ አጋሮ ከተማ ሕዝብ ጭኖ በማሽከርከር ላይ እያሉ መንገዱን ለቅቆ ከእንጨት ጋር አጋጭቶ በመገልበጥ የተሸከርካሪው ረዳት የሆነው አብዲ ዋቆ የገደላቸው በመሆኑ በፈፀሙት በቸልተኝነት ሰው መግደል ወንጀል ተከሰዋል የሚል ነው። የአሁኑ አመልካችም የክስ ማመልከቻው ደርሷቸው ክሱን እንዲረዱት ከተደረገ በኋላ ስለእምነት ክህደት ቃል ሲጠየቁ ዳኛ በመሆናቸው ያለመከሰስ መብት ያላቸው መሆኑን ጠቅሰው በክሱ ላይ ተቃውሞ እንዳላቸው የገለፁ ሲሆን ፍርድ ቤቱም አቃቤ ሕጉ አመልካቹ ድርጊቱን እንደፈፀሙ ወዲያውኑ የተያዙ መሆናቸውን ገልፀው ያለመከሰስ መብታቸው ተቀባይነት የለውም በማለት የሰጡትን አስተያየት በመቀበል የክስ ተቃውሞውን ያለፈው ሲሆን የድርጊቱን አፈፃፀም በተመለከተ ግን የክህደት ቃላቸውን ሰጥተዋል።
አቃቤ ህግ በበኩሉ የሰውና የሰነድ ማስረጃዎችን አቅርቦ አሰምቷል። ከዚህም በኋላ አመልካች የወንጀል ድርጊቱን ስለመፈፀማቸውና ሟች በደረሰባቸው አደጋ ምክንያት ሕይወታቸው ያለፈ መሆኑን አቃቤ ህግ በማስረጃዎቹ ያስረዳባቸው መሆኑ በስር ፍርድ ቤት ታምኖበት ይህንኑ እንዲያስተባብሉ እድል ተሰጥቶ አመልካች አደጋው የደረሰው በድንገተኛ አደጋ አጋጣሚ መሆኑን የሚያሳይ ጭብጥ አስይዘው የመከላከያ ማስረጃ ያሰሙ ሲሆን የስር ፍርድ ቤትም ጉዳዩን መርምሮ አመልካች በመከላከያ ማስረጃዎቹ የዐቃቤ ህግ ማስረጃዎቹን ያላስተባበሉ መሆኑን በመጥቀስ አመልካችን በአቃቤ ህግ በኩል ተጠቅሶ በቀረበባቸው ድንጋጌ ስር ጥፋተኛ አድርጓቸዋል። ቅጣቱን በተመለከተም የግራ ቀኙ የቅጣት አስተያየት በመቀበልና በፍድራል ጠቅላይ ፍርድ ቤት የወጣውን የቅጣት አወሳሰን መመሪያ መሰረት በማድረግ በአንድ አመት ከስድስት ወር ቀላል እስራት እና በብር 3000.00 (ሶስት ሺህ ብር) እንዲቀጡ ሲል ወስኗል። በዚህ ውሳኔ አመልካች ባለመስማማት ይግባኛቸውን የሰበር አቤቱታቸውን እንደየቅደም ተከተላቸው ለክልሉ ጠቅላይ ፍርድ ቤት ይግባኝ ሰሚ እና ሰበር ሰሚ ችሎቶች ቢያቀርቡም ቅሬታቸው በወ/መ/ሕ/ሥ/ቁጥር 195(1) መሰረት ተሰርዞባቸዋል። የአሁኑ የሰበር አቤቱታ የቀረበውም ይህንኑ ውሳኔ በመቃወም ለማስለወጥ ነው።
አመልካች መስከረም 16 ቀን 2006 ዓ/ም በተፃፈ አራት ገጽ የሰበር አቤቱታ በበታች ፍርድ ቤቶች ውሳኔ ላይ መሰረታዊ የሆነ የሕግ ስህተት ተፈፅሟል የሚሉባቸውን ምክንያቶች ዘርዝረው አቅርበዋል። ይዘቱም ባጭሩ፡የአመልካች ያለመክሰስ መብት የታለፈው ያላግባብ መሆኑን፣ አመልካች ድርጊቱን የፈፀሙት በወንድማቸው ላይ ሆኖ ከአቅም በላይ በሆነ የአደጋ አጋጣሚ ሆኖ እያለ በስር ፍርድ ቤቶች መታለፉ ያላግባብ መሆኑን፣ የቅጣት ውሳኔም ተገቢነት የልለው መሆኑና የእስራት ቅጣቱ መገደብ ሲገባው መታለፉም ያለግባብ መሆኑን ዘርዝረው ውሳኔው መሰረታዊ የሕግ ስህተት ያለበት ነው በማለት መከራከራቸውን የሚያሳይ ነውው። አቤቱታው ተመርምሮም አመልካች ጥፋተኛ መባላቸው ከሰ/መ/ አንፃር ተገቢ መሆን ያለመሆኑን ለመመርመር ሲባል ለሰበር ሰሚ ችሎት እንዲቀርብ የተደረገ ሲሆን ለተጠሪም ጥሪ ተደርጎለት ቀርቦ ግራ ቀኙ በፅሁፍ እንዲከራከሩ ተደርጓል።
የጉዳዩ አመጣጥ አጠር አጠር ባለመልኩ ከላይ የተገለፀው ሲሆን ይህ ችሎትም የግራ ቀኙን ክርክር ለሰበር አቤቱታው መነሻ ከሆነው ውሳኔ እና አግባብነት ካላቸው ድንጋጌወች ጋር በማገናዘብ ጉዳዩ ለሰበር ሰሚ ችሎቱ ሲቀርብ ከተያዘው ጭብጥ አንፃር በሚከተለው መልኩ መርምሮታል።
በመሰረቱ አንድ ወንጀል ተደረገ የሚባለው ወንጀሉን የሚቋቋሙት ሕጋዊ፣ ግዙፋዊ እና ሞራላዊ ፍሬ ነገሮች በአንድነት ተሟልተው ሲገኙ ብቻ መሆኑን በአዋጅ ቁጥር 414/1996 የወንጀል ሕጉ አንቀጽ 23(2) በግልጽ ደንግጓል። እንግዲህ አንድን ድርጊት ወንጀል ነው ብሎ ለመወሰን ሕጋዊ፣ ግዙፋዊ እና ሞራላዊ ፍሬ ነገሮች ተጣምረው መገኘት የግድ ይላል። ሕጋዊ ፍሬ ነገሮች የሚባሉት ደግሞ ለጉዳዩ አግባብነት አለው ተብሎ የተጠቀውን ድንጋጌ ለማቋቋም ሙሉ በሙሉ መሟላት ያለባቸውን ነጥቦች ሲሆን ግዙፋዊና ሞራላዊ ፍሬ ነገሮች የሚባሉት ደግሞ እንደየቅደምተከተከላቸው ከድርጊት ማድረግ ወይም አለማድረግና ከሐሳብ ክፍል ጋር በሕጉ የተመለከቱትን ሁኔታዎች የሚመለከቱ ናቸው። በምክንያትነትና በውጤት መካከል ደግሞ በወንጀል ሕጉ አንቀጽ 24 በተመለከተው አግባብ ግንኙነት መኖሩ ላረጋገጥ ይገባል።
በተያዘው ጉዳይ ከላይ እንደተገለፀው አመልካች ሲያሽከረክሩት የነበረው ተሽከርካሪ ተገልብጦ ሟችን ግንቦት 09 ቀን 2005 ዓ/ም መግደላቸው የተካደ ጉዳይ አይደለም። አመልካች የሚከራከሩበት ነጥብ ሟች የሞቱት በድንገተኛ አደጋ ምክንያት ነው በሚል ነው። ይሁን እንጂ የሥር ፍርድ ቤት ለጉዳዩ ቀጥተኛ አግባብነት ያለውን የባለሙያ የምስክርነት አስተያየት፣ በአደጋው ቦታ የተነሳውን ፕላንና የግራ ቀኙን ምስክሮች ቃል መዝኖ አመልካች የተገቢውን ጥንቃቄ ሳያደርጉ ቀርተው አደጋው መድረሱን ማረጋገጡን ደምድሟል። እንዲህ ከሆነ ይህ ማስረጃ ለጉዳዩ ቀጥተኛ አግባብነት ያለው ከመሆኑም በላይ ታአማኒነቱ ሲታይ በወ/መ/ሕ/ሥ/ሥ/ሕ/ቁጥር 141 በተመለከተው የማስረጃ ምዘና አግባብ ጉዳዩን ለማስረዳት በቂና አሳማኝ መሆኑን ፍሬ ነገርን የማጣራትና ማስረጃን የመመዘን ስልጣን ባላቸው ፍርድ ቤቶች ያረጋገጡት በመሆኑ ይህ ችሎት በኢ.ፍ.ዲ.ሪፐብላክ ሕገ መንግስት አንቀጽ 80(3(ሀ)) እና አዋጅ ቁጥር 25/1988 አንቀጽ 10 ድንጋጌዎች ከተሰጠው ስልጣን አንፃር ይህን ማስረጃ ክብደት ላሰጠው አይገባውም ነበር ለማለት የሚችልበት አግባብ የለም። በመሆኑም አመልካች አደጋው በድንገተኛ አጋጣሚ የተከሰተ ነው በማለት የሚያቀርቡት የፍሬ ነገርና የማስረጃ ምዘና ክርክር በዚህ ችሎት ተቀባይነት የሚያገኝበት የሕግ መሰረት ያለው ሆኖ አልተገኘም።
በወንጀል ሕጉ አንቀጽ 57 በግልፅ እንደሰፈረው “ለድርጊቱ ኃላፊ ላሆን የሚገባው ሰው አስቦ ወይም በቸልተኝነት አንድ ወንጀል ካላደረገ በቀር በወንጀል ጥፋተኛ አይሆነም በአንፃሩ አንድ ሰው “የፈፀመው ድርጊት በሕግ የሚያሰቀጣ ቢሆንም ምንም ጥፋት ሳያደርግ ወይም ከአቅም በላይ በሆነ ኃይል ምክንያት ወይም በድንገተኛ አጋጣሚ ነገር የተፈፀመ ወይም የደረሰ ሆኖ ሲገኝ በወንጀል ሕግ ላፈረድበት አይገባውም በማለት የወንጀል ሕጉ አንቀጽ 57(2) ይደነግጋል። ከዚህ የሕጉ አጠቃላይ ይዘትና መንፈስ መገንዘብ የሚቻለው በአንድ ድርጊት ምክንያት አንድን ሰው በወንጀል ጥፋተኛ ነው ለማለት ከሳሽ የሆነው ዓቃቤ ህግ ድርጊቱ የተፈፀመው ሆነ ተብሎ ወይም በቸልተኝነት መሆኑን ማስረደፋት የሚጠበቅበት መሆኑን ነው። ድርጊቱ ሆነ ተብሎ ወይም በቸልተኝነት የተፈፀመ መሆኑ ማስረጃ ካልቀረበ ወይም ድርጊቱ ከአቅም በላይ ወይም በድንገተኛ አጋጣሚ የተፈፀመ መሆኑን የሚያስረዳ ማስረጃ በተከሳሽ በኩል ከቀረበ የተከሰሰውን ሰው በወንጀል ሕግ ጥፋተኛ ብሎ መፍረድ ከሕጉ መንፈስ ውጪ ነው። በወንጀል የተከሰሰ ሰው ቸልተኛ ነበር? ወይስ አልነበረም? የሚለው ጥያቄ በወንጀል ሕጉ በአንቀጽ 59 የሰፈረውን ድንጋጌ መሰረት በማድረግ የሚወሰን ነው። የዚሁ አንቀጽ ንዑስ አንቀጽ አንድ አሁን ለተያዘው ጉዳይ ቀጥተኛ አግባብነት ያለው በመሆኑም የሕጉን ይዘት እንዳለ ማስቀመጡ ጠቃሚ ነው። ይኸው፡- ማንም ሰው በቸልተኝነት የወንጀል ተግባር አደርጓል የሚባለው፡- (ሀ) ድርጊቱ በወንጀል ሕግ የሚያስቀጣ ውጤት ላያስከትል እንደሚችል እያወቀ አይደርስም የሚል ግምት ወይም ባለማመዛዘን ፣ ወይም (ለ) ድርጊቱ በወንጀል የሚያሰቀጣ ውጤት ላያስከትል እንደሚችል ማወቅ እለበት ወይም እየቻለ ባለመገመት ወይም ባለማሰብ ድርጊቱን የፈፀመ እንደሆነ ነው።” በዚህ ድንጋጌ መሰረት አንድ ሰው በቸልተኝነት ወንጀል ፈፅሟል የመባለው ውጤቱን እያወቀ ውጤቱ አይደርስም ከሚል መነሻ ድርጊቱን የፈፀመ እንደሆነ ወይም ደግሞ የወንጀል ውጤት የሚያስከትል መሆኑን ባያውቅም ውጤቱን ማወቅ ነበረበት ወይም ጥረት ቢያደርግ ውጤቱን ማወቅ ይችል ነበር ማለት ሲቻል ነው። በመሆኑም ቸልተኝነት አለ ለማለት ሕጉ የሚጠቀምበት ዋነኛ መስፈርት የተከሰሰው ሰው በድርጊቱና በውጤቱ መካከል ያለውን ግንኙነት አስመልክቶ ያለው ወይም ላኖረው የሚገባው ግንዛቤ ነው። ድርጊቱን የፈፀመው ሰው ነበረው ዕውቀትና ግንዛቤ ወይም ላኖረው የሚገባው ዕውቀትና ግንዛቤ የሚመዘነው የሰውዬው እድሜ፣ ያለው የኑሮ ልምድ፣ የትምህርት ደረጃው፣ ሥራውና የማህበራዊ ኑሮ ደረጃው ግምት ውስጥ በማስገባት እንደሆነም የሕጉ አንቀጽ 59(1) ይደነግጋል።
ወደተያዘው ጉዳይ ስንመለስም አመልካች በሙያቸው አሽከርካሪ ሆነው እያለና በአሽከርካሪነት ሙያው ደግሞ የልላውን ሕይወትና ደህንነት የመጠበቅ ግድታ እያለባቸው የሰልዳ ቁጥሩ 3-28157 ኦሮ የሆነውን ሚኒባስ መኪና እያሽከረከረ ከጅማ ከተማ ወደ አጋሮ ከተማ እያሽከረከሩ ተገቢውን ጥንቃቄ ከማድረግ ጉድለት መኪናው ተገልብጦ ሟች የሞቱ በመሆኑ አመልካች በወንጀል ሕጉ አንቀጽ 543(2) ስር የማይጠበቁበትን ምክንያት አላገኘንም።
ስለሆነም አመልካች የጥፋተኝነት ውሳኔውን አስመልክቶ የሚያቀርቡት ክርክር ከወንጀል ሕጉ አንቀጽ 23፣24፣57፣57 እና 543(2) ድንጋጌዎች ጣምራ ንባብ አንፃር ሲታይ ተቀባይነት የልለው ሆኖ አግኝተናል።
አመልካች ጥፋተኛ የተባሉት የወንጀል ህግ አንቀጽ 543(2) መሰረት ነው። በዚህ ድንጋጌ ጥፋተኛ የተባለ ሰው ላቀጣ የሚገባው ከአንድ ዓመት እስከ አምስት ዓመት ላደርስ በሚችል ቀላል እስራት እና ከሦስት ሺህ እስከ ስድስት ሺህ ብር ላደርስ በሚችል መቀጮ ነው፣ ቅጣት ደግሞ ላጣል የሚገባው በወንጀል ሕጉ አንቀጽ 88(2) ስር የተመለከቱትን ነጥቦች በማመዛዘን ነው። ከዚህ አንጻር ጉዳዩን ስንመለከተው የሥር ፍርድ ቤት አመልካች ላይ ቅጣት ሲጥል የግራ ቀኙን የቅጣት አስተያየት በመቀበል ከቅጣት አወሳሰን መመሪያ ጋር እና በወንጀል ሕጉ ከተመለከቱት የቅጣት አወሳሰን መርሆዎች ጋር በማገናዘብ ቅጣቱን መወሰኑን የገለፀ ቢሆንም ሟቹ የአመልካች ወንድም በመሆናቸው ምክንያት ቅጣቱን በወንጀል ሕጉ አንቀጽ 84(1) መሰረት ማክበዱ የሕግ መሰረት ያለውና የወንጀል ሕጉን መሰረታዊ አላማ የሚያሳካ ነው ለማለት የሚቻል ሆኖ አልተገኘም። በመሆኑም ይሄው ምክንያት ላያዝ የማይገባው ከሆነ አመልካችን ላያርማቸው፣ ልላውን ደግሞ ላያስጠነቅቅ የሚችለው የቅጣት መጠን አንድ አመት ቀላል እስራት ሆኖ አግኝተናል። ሲጠቃለልም ከላይ የተመለከቱት ሕጋዊ ምክንያቶች በጉዳዩ ላይ በበታች ፍርድ ቤቶች የተሰጠው የጥፋተኝነት ውሳኔ ተገቢ ቢሆንም የቅጣት ውሳኔ ክፍል ግን በከፊል መሰረታዊ የሆነ የሕግ ስህተት ያለበት ሆኖ ስለአገኘነው ተከታዩን ወስነናል።
በጅማ ዞን ከፍተኛ ፍርድ ቤት በመ/ ነሐሴ 03 ቀን 2005 ዓ/ም ተሰጥቶ በኦሮሚያ ክልል ጠቅላይ ፍርድ ቤት ይግባኝ ሰሚ ችሎት በመ/ ነሐሴ 12 ቀን 2005 ዓ/ም፣ በክልሉ ጠቅላይ ፍርድ ቤት ሰበር ሰሚ ችሎት በመ/ ነሐሴ 30 ቀን 2005 ዓ/ም በትዕዛዝ የፀናው የጥፋተኝነትና የቅጣት ውሳኔ በወ/መ/ሕ/ሥ/ሥ/ቁጥር 195(2)(ለ)(2)) መሰረት ተሻሽሐል።
አመልካች በ1996 ዓ/ም በወጣው የወንጀል ህግ አንቀጽ 543(2) ስር የተመለከተውን ድንጋጌ የተላለፉ ጥፋተኛ ናቸው መባላቸው በአግባቡ ሲሆን ቅጣቱ ግን ተገቢ ያልሆነ የቅጣት ማክበጃ ምክንያት ተይዞ እንዲከብድ የተደረገ በመሆኑ ምክንያቱን ውድቅ በማድረግ አመልካች ላቀጡ የሚገባው የቅጣት መጠን በአንድ አመት ቀላል እስራት ነው ብለናል፣ የገንዘብ መቀጮው ብር 3000.00 (ሶስት ሺህ ብር) እንዲቀጡ ተብሎ የተሰጠው የውሳኔ ክፍል መሰረታዊ የሆነ የህግ ስህተት የተፈፀመበት አይደለም ብለናል።
የሥር ፍርድ ቤት የእስራት ቅጣት ውሳኔ የተሻሻለ መሆኑን አውቆ ቅጣቱን ተከታትሎ እንዲያስፈፅም ለማረሚያ ቤቱ ይገለጽለት ብለናል።
No topics extracted.