No summary available.
መስከረም 21 ቀን 2006 ዓ.ም.
ዳኞች፡- ተሻገር ገ/ሥላሴ አልማው ወል ዓላ መሐመድ ረታ ቶሎሳ ሙስጠፋ አህመድ አመልካች፡- የኢዮጵያ ገቢዎችና ጉምሩክ ባለስልጣን ዐ/ሕግ - ዐ/ሕግ ሜቴ አቶምሳ እና አሰፋ ሐፎስ ቀረቡ ተጠሪዎች፡-
አመልካች በዚህ መዝገብ የሰበር አቤቱታ ያቀረበው ተጠሪዎቹ በፍ/ከ/ፍ/ቤት በተናጠል በተለያየ መዝገብ ተከሰው የጥፋተኝነት እና የቅጣት ውሳኔ ከተሰጠባቸው የወንጀል ክሶች መካከል ሁለቱንም ተጠሪዎች በ1ኛ ክስ ከተመለከተው ወንጀል በነፃ በማሰናበት በፍ/ጠ/ፍ/ቤት ይ/ሰሚ ችሎት የሰጠው ውሳኔ መሰረታዊ የሕግ ስህተት የተፈጸመበት በመሆኑ ላታረም ይገባል በማለት ነው።የጉዳዩን አመጣጥ በተመለከተ አመልካች በተጠሪዎቹ ላይ በተለያዩ መዝገቦች ያቀረባቸውን የተለያዩ የወንጀል ክሶች የተመለከተው የፍ/ከ/ፍ/ቤት የግራ ቀኙን ማስረጃ ከሰማ በኃላ፤
በ1ኛ ተጠሪ ላይ በአምስት ክሶች የጥፋተኝነት እና በድምሩ የሃያ ዓመት ጽኑ እስራት ቅጣት ከብር 165,000 መቀጮ ጋር፤ በ2ኛ ተጠሪ ላይ በአምስት ክሶች የጥፋተኝነት እና በድምሩ የአስራ ሶስት ዓመት ጽኑ እስራት ቅጣት ከብር 100,000 መቀጮ ጋር፤ ውሳኔ መስጠቱን፣በውሳኔው ቅር በመሰኘት ሁለቱ ወገኖች ያቀረቡለትን ይግባኝ የመረመረው የፍ/ጠ/ፍ/ቤት ይግባኝ ሰሚ ችሎት በበኩሉ ተጠሪዎቹ ያቀረቡትን ይግባኝ በተመለከተ ከላይ እንደተጠቀሰው ሁለቱንም ተጠሪዎች ከ1ኛ የወንጀል ክስ በአብላጫ በነጻ በማሰናበት እና በልሎች የወንጀል ክሶች ተጠሪዎቹ ያቀረቡትን ቅሬታ በሙሉ ድምጽ ውድቅ በማድረግ ውሳኔ መስጠቱን፤አመልካች ያቀረበውን ይግባኝ በተመለከተም የተጠሪዎቹ የይግባኝ ቅሬታ ውድቅ በተደረገባቸው የወንጀል ክሶች በተጠሪዎቹ ላይ በከፍተኛ ፍ/ቤት ተጥሎ የነበረውን የቅጣት መጠን ከፍ በማድረግ በ1ኛ ተጠሪ ላይ በከፍተኛ ፍ/ቤት በአምስት የወንጀል ክሶች ተጥሎ በነበረው የሃያ አመት ጽኑ እስራት ምትክ በይግባኝ ደረጃ የጥፋተኝነት ውሳኔው በጸናባቸው አራት የወንጀል ክሶች የ25 ዓመት ጽኑ እስራት፤በ2ኛው ተጠሪ ላይ በከፍተኛ ፍ/ቤት በአምስት የወንጀል ክሶች ተጥሎ በነበረው የ13 ዓመት ጽኑ እስራት ምትክ በይግባኝ ደረጃ የጥፋተኝነት ውሳኔው በጸናባቸው አራት የወንጀል ክሶች የ20 ዓመት ጽኑ እስራት ቅጣት በመጣል ውሳኔ መስጠቱን፤በ2ኛ ተጠሪ ላይ በከፍተኛ ፍ/ቤት የተጣለው የመቀጮ መጠን በይግባኝ ሰሚው ፍ/ቤት ያልተለወጠ ሲሆን በ1ኛ ተጠሪ ላይ ተጥሎ የነበረው የብር 165,000 መቀጮ ወደ ብር 300,000 ከፍ መደረጉንና እና በንብረት ውርስ ረገድም አንዳንድ ማሻሻያዎች በይግባኝ ሰሚው ፍ/ቤት ውሳኔ መካተታቸውን የመዝገቡ ግልባጭ ያስረዳል።
የፍ/ጠ/ፍ/ቤት ይ/ሰሚ ችሎት ከላይ እንደተገለጸው በተጠሪዎቹ ላይ በ1ኛ ክስ በከፍተኛ ፍ/ቤት ተሰጥቶ የነበረውን የጥፋተኝነትና የቅጣት ውሳኔ በመሰረዝ ተጠሪዎቹ በእነዚህ የወንጀል ክሶች ረገድ በነጻ እንዲሰናበቱ የሰጠው ውሳኔ መሰረታዊ የህግ ስህተት የተፈጸመበት ነው በማለት አመልካች በሶስት መዝገቦች ያቀረበው አቤቱታ በሆነው መዝገብ ተጣምሮ ከታየ በኃላ ተጠሪዎቹ ብድርን እንደመደበኛ ስራቸው በማድረግ በተደጋጋሚ ጊዜ ቼኮችን፣የቦታ ካርታን፣የንግድ ፍቃድን እና የመኪና ላብሬን መያዣ በማድረግ ለተለያዩ ሰዎች በሚላዮኖች የሚቆጠር ገንዘብ በብድር ይሰጡ እንደነበር ከፍተኛ ፍ/ቤት በማስረጃ አረጋግጦ የጥፋተኝነት ውሳኔ በሰጠበት ሁኔታ ተጠሪዎቹ ብድር መስጠትን እንደመደበኛ ስራ በማድረግ ተደጋጋሚ ብድር መስጠታቸውም ሆነ ብድሩን የሰጡት በተደጋጋሚና በከፍተኛ መጠን መሆኑ ከወንጀል ህግ አንቀጽ 3 ድንጋጌ አነጋገር አንፃር የባንኮችንና የልሎች የገንዘብ ተቋማትን ስራ ያለ ፍቃድ ሰርተዋል ለማለት የማይቻል በመሆኑ ድርጊቱ በወንጀል ህግ አንቀጽ 61 መሰረት በአራጣ ወንጀል ክስ ስር ተጠቃሎ የሚታይ ነው በማለት በሁለቱ ተጠሪዎች ላይ በ1ኛ ክስ በከፍተኛ ፍ/ቤት ተሰጥቶ የነበረው የጥፋተኝነት እና የቅጣት ውሳኔ በይ/ሰሚው ፍ/ቤት የመሰረዙን አግባብነት ተጠሪዎቹ ባሉበት ለመመርመር ይቻል ዘንድ ጉዳዩ ለሰበር ክርክር እንዲቀርብ ተደርጎ ተጠሪዎቹ በተያዘላቸው ቀጠሮ መልስ ባለማቅረባቸው መብታቸው ከታለፈ በኃላ 1ኛ ተጠሪ በተያዘላቸው ቀጠሮ መልስ ያላቀረቡበትን ምክንያት ገልጸው በተፈቀደላቸው መሰረት በጠበቆቻቸው የተዘጋጀና የተፈረመ መልስ በማያያዝ የክርክሩ ተካፋይ ሆነዋል።የጉዳዩ አመጣጥ እና የክርክሩ ይዘት ባጭሩ ከላይ የተመለከተው ሲሆን እኛም የፍ/ጠ/ፍ/ቤት ይ/ሰሚ ችሎት የተጠሪዎቹን ይግባኝ በከፊል በመቀበል በፍ/ከ/ፍ/ቤት ከተሰጠው ውሳኔ ውስጥ በሁለቱ ተጠሪዎች ላይ በ1ኛ ክስ ተሰጥቶ የነበረውን የጥፋተኝነትና የቅጣት ውሳኔ ሰርዞ ተጠሪዎቹ ከእነዚህ ክሶች በነጻ እንዲሰናበቱ በድምጽ ብልጫ የሰጠው ውሳኔ መሰረታዊ የህግ ስህተት የተፈጸመበት መሆን አለመሆኑን መርምረናል።
በዚህም መሰረት በተጠሪዎቹ ላይ ቀርቦ የነበረው 1ኛ ክስ ተመሳሳይ ድንጋጌ የተጠቀሰበት ሆኖ ይዘቱ በጥቅል ሲታይ ተጠሪዎቹ በገንዘብና በባንክ አዋጅ ቁጥር 83/86 አንቀጽ 59(1)(ሸ) እና 2 (ሀ)ስር የተደነገገውን በመተላለፍ የብድር ስራ አገልግሎት ለመስጠት የሚያስችል ከብሕራዊ ባንክ የተሰጠ ፍቃድ ሳይኖራቸው ለተለያዩ ግለሰቦች እና ድርጅቶች በርካታ መጠን ያለው ገንዘብ በብድር በመስጠትና ለብድሮቹም ቼኮችንና የተለያዩ ሰነዶችን በመያዣነት በመቀበል ለባንኮችና ለመሰል ፋይናንስና አክሲዮን ማህበራት የተፈቀደውን የባንክ ስራ በህገወጥ መንገድ እንደንግድ ስራ በተደጋጋሚ የመስራት ወንጀል ፈጽመዋል የሚል ሲሆን ወንጀሉን ፈጽመዋል የተባሉትም 1ኛ ተጠሪ በአራት ወራት ጊዜ ውስጥ አምስት ጊዜ ለአንድ ድርጅት በድምሩ ብር 12,090,000 ፤2ኛ ተጠሪ በአስር ዓመታት ውስጥ በ25 የውል ሰነዶች ለ11 ተበዳሪዎች በድምሩ ብር 3,711,111 በብድር በመስጠት መሆኑን የክሶቹ ዝርዝር ያመለክታል።ሁለቱ ተጠሪዎች በየቀረበባቸው 1ኛ ክስ የተመለከተውን የገንዘብ መጠን፣በየክሶቹ በተመለከተው የጊዜ ወሰን፣የድግግሞሽ መጠን እና ሁኔታ በየክሶቹ ለተጠቀሱት ግለሰቦችና ድርጅቶች በብድር መስጠታቸውን ክሱ የቀረበለት ፍ/ከ/ፍ/ቤት በማስረጃ አጣርቶ ያረጋገጠ ሲሆን በክሶቹ የጥፋተኝነት ውሳኔ የሰጠባቸውም ተጠሪዎቹ ከሳሽ ወገን ያስረዳባቸውን ፍሬ ነገሮች በመከላከያቸው አላስተባበሉም በማለት ነው።በክሶቹ የተመለከተው ግዙፋዊ ፍሬ ነገር በተጠሪዎቹ መፈጸሙ በማስረጃ ተጣርቶ ተረጋግጦአል መባሉ በመሰረቱ በይ/ሰሚው ፍ/ቤት ውሳኔውን በሰጠው አብላጫ ድምጽም ቢሆን አልተነቀፈም።
የፍ/ጠ/ፍ/ቤት ይ/ሰሚ ችሎት ግዙፋዊ ፍሬነገሩ ተረጋግጦአል መባሉን ተቀብሎ ነገር ግን የጥፋተኝነት እና የቅጣት ውሳኔውን በአብላጫ ድምጽ ለመሰረዝ የሰጠው ዓይነተኛ ምክንያት በሁለቱ ተጠሪዎች ላይ በቀረበው 1ኛ ክስ ማንኛውም ሰው "…በማናቸውም ልላ አኳኃን የዚህን አዋጅ ወይም በዚህ አዋጅ መሰረት የወጡ ደንቦችን እና መመሪያዎችን የተላለፈ ወይም አፈጻጸማቸውን ያሰናከለ እንደሆነ ወንጀል የተሰራበት እንደሆነ ወንጀል የተሰራበት ሀብት መወረሱ እንደተጠበቀ ሆኖ በወንጀለኛ ህግ መሰረት ይቀጣል።" የሚል አነጋገር እና "ወንጀሉ የተፈጸመው ሥልጣንን መከታ በማድረግ ወይም በመንግስት ስራ አጋጣሚ ወይም ተገቢ ባልሆነ መንገድ ሀብትን ለማካበት ወይም በተደጋጋሚ ሲሆን ወንጀል የተሰራበት ሀብት መወረሱ እንደተጠበቀ ሆኖ ቅጣቱ ከአስራ አምስት ዓመት የማይበልጥ ጽኑ እስራት እና ከብር 20,000 የማይበልጥ የገንዘብ መቀጮ ይሆናል።" የሚል አነጋገር ያዘሉት የአዋጅ ቁጥር 83/86 አንቀጽ 59(1)(ሸ) እና (2)(ሀ) ድንጋጌዎች በተደጋጋሚ፣ለንግድ መጠን እና ለበርካታ ተበዳሪዎችም ቢሆን በግለሰብ ደረጃ ብድር የመስጠት ስራ የተከለከለ ወይም የሚያስቀጣ የወንጀል ተግባር መሆኑንና እና ብድር የመስጠት ስራ ላከናወን የሚችለው በባንክ ብቻ መሆኑን በግልጽ እንደማይደነግጉ፣ፍ/ቤቶች ሕግን ከመተርጎም የማይታገዱ መሆኑ እንደተጠበቀ ሆኖ ሕገወጥነቱ በሕግ ያልተደነገገን ድርጊት ወይም ግድፈት እንደ ወንጀል ላቆጥሩትና ቅጣት ላወስኑበት እንደማይችሉ፣በሕግ ላይ ከተደነገጉት ወንጀሎች ጋር ይመሳላል በማለት ወንጀልነቱ በግልጽ ያልተደነገገን ድርጊት ወይም ግድፈት እንደ ወንጀል ላቆጥሩት እንደማይችሉ በወንጀል ህግ በአንቀጽ 2 ስር የተደነገገ በመሆኑ ወንጀልነቱ በግልጽ ባልተደነገገ ድርጊት በተጠሪዎቹ ላይ የጥፋተኝነትና የቅጣት ውሳኔ መተላለፉ መሰረታዊ የሆነውን የህጋዊነት መርህ የሚጻረር ነው የሚል መሆኑን የውሳኔው አጠቃላይ ይዘት ያስገነዝባል።
እንደተባለው በከፍተኛ ፍ/ቤት ሁለቱ ተጠሪዎች በ1ኛ ክስ ጥፋተኛ ተብለውበት የነበረው የገንዘብና የባንክ አዋጅ ቁጥር 83/86 አንቀጽ 59(1)(ሸ) እና (2)(ሀ) ድንጋጌዎች ይዘቱ ቀደም ሲል የተገለጸውንና በተጠሪዎቹ መፈጸሙ የተረጋገጠውን ግዙፋዊ ፍሬነገር በወንጀልነት የሚፈርጁ ወይም የሚደነግጉ አለመሆኑን ከድንጋጌዎቹ ይዘት መገንዘብ የሚቻል በመሆኑ በዚህ ረገድ በይ/ሰሚው ፍ/ቤት አብላጫ ድምጽ የሰጠውን ሰፊ ትችት እና የደረሰበትን ድምዳሜ በበኩላችን ስህተት ያለበት ሆኖ አላገኘነውም። የወንጀል ሕግ በተወሰኑ ጉዳዮች በተለየ ሁኔታ ህጉ ደንግጎ ሲገኝ ግምት የሚወስድባቸው አጋጣሚዎች መኖራቸው እንደተጠበቀ ሆኖ በመሰረታዊነት ግን የአንድ ድርጊት ወይም ግድፈት ወንጀልነት በሕጉ በግልጽ ተደንግጎ መገኘት የሚገባው መሆኑ በቀድሞውም ሆነ በአዲሱ የወንጀል ሕግ አንቀጽ 2 በተመሳሳይ ሁኔታ ተደንግጎ የሚገኝ ሲሆን በወንጀል ጉዳይ የሚቀርብ ክስ ስለድርጊቱ እና ስላፈጻጸሙ የሚሰጠው መግለጫ ድርጊቱን ወንጀል ከሚያደርገው ሕግ አነጋገር ጋር በጣም የተቀራረበ መሆን እንደሚገባው በወ.መ.ሕ.ስ.ስ.ቁ. 112 የተመለከተው ድንጋጌም ይህንኑ የሚያጠናክር ነው። የድርጊቱ ወይም የግድፈቱ ወንጀልነት በሕጉ በግልጽ ያልተደነገገ በሆነ ጊዜ ወንጀልን ለማቋቋም ከሚያስፈልጉት ፍሬ ነገሮች መካከል አንዱ የሆነው ሕጋዊ ፍሬ ነገር የተጓደለ ስለሚሆን ከወ.ሕ.አ. 23(2) መሰረታዊ ድንጋጌ አንጻር ወንጀል ተፈጽሞአል ለማለት የሚቻልበት የሕግ አግባብ አይኖርም።
ሲጠቃለል የፍ/ጠ/ፍ/ቤት ይ/ሰሚ ችሎት የወንጀል ሕግን መሰረታዊ መርሆዎች መሰረት በማድረግ በተጠሪዎቹ በቀረበለት ይግባኝ መነሻ በፍ/ከ/ፍ/ቤት በሁለቱ ተጠሪዎች ላይ በ1ኛ ክስ ተሰጥቶ የነበረውን የጥፋተኝነትና የቅጣት ውሳኔ ሰርዞ በዚህ ረገድ ተጠሪዎችን በማሰናበት የሰጠው ውሳኔ መሰረታዊ የሕግ ስህተት የተፈጸመበት ነው ለማለት የሚያስችል ሕጋዊ ምክንያት ስላልተገኘ የሚከተለው ውሳኔ ተሰጥቶአል።
የፍ/ጠ/ፍ/ቤት ይግባኝ ሰሚ ችሎት 1ኛ ተጠሪን አስመልክቶ በመ.ቁ. 59831 በ03/08/2004 ዓ.ም.፣2ኛ ተጠሪን አስመልክቶ በመ.ቁ. 55859 በ01/08/2004 ዓ.ም. ከሰጠው ውሳኔ ውስጥ በተጠሪዎቹ ይግባኝ መነሻ በፍ/ከ/ፍ/ቤት በ1ኛ ተጠሪ ላይ በመ.ቁ. 82321 በ09/09/2002 ዓ.ም.፤በ2ኛ ተጠሪ ላይ ደግሞ በመ.ቁ. 82644 በ16/06/2002 ዓ.ም. በአንደኛ ክስ ተሰጥቶ የነበረውን የጥፋተኝነት እና የቅጣት ውሳኔ ሰርዞ በዚህ ረገድ ተጠሪዎቹን በማሰናበት በአብላጫ ድምጽ የሰጠው የውሳኔ ክፍል ፀንቶአል።
የዚህ ውሳኔ ግልባጭ ክርክሩ ከዚህ መዝገብ ጋር ተጣምሮ ከተወሰነው መ.ቁ. 81179 ጋር እንዲያያዝ ይደረግ።
ውሳኔ ያገኘ ስለሆነ መዝገቡ ተዘግቶአል።
No topics extracted.