No summary available.
መጋቢት 12 ቀን 2005 ዓ.ም.
ዳኞች፡- ተሻገር ገ/ስላሴ አልማው ወል ረታ ቶሎሣ አዳነ ንጉሴ ሙስጠፋ አህመድ አመልካቾች፡-
መዝገቡ ተመርምሮ ተከታዩ ፍርድ ተሰጥቷል።
**
ጉዳዩ በልላ ሰው ጥቅም የስራ አመራር ላይ የተፈፀመ ወንጀልን የሚመለከት ሲሆን ክርክሩ የተጀመረው የአሁኑ ተጠሪ በአመልካቾች ላይ በአ/ብ/ክ/መንግስት ደሴ ከተማ ወረዳ ፍ/ቤት ባቀረበው የወንጀል ክስ መነሻነት ነው።
የክሱ ይዘትም አመልካቾች የወንጀል ህግ አንቀጽ 32/1/ሀ/ 7ዐ2/3/ በመተላለፍ በደሴ ከተማ ቀበል ዐ9 ማዕከል መርከዘል ብርሃን የሚባል ለሙስላሙ ማህበረሰብ በበጐ አድራጐትነት ወይም በወቅፋ የተሰጠ ለትርፍ ያልተቋቋመ ህጋዊ ሰውነት ያለውን ድርጅት 1ኛ አመልካች ከሟች ወላጅ አባቱ በተሰጠው የኑዛዜ ውክልና መሰረት የድርጅቱን ስራ ላመራ ሲገባ ድርጅቱ ከተቋቋመ ዓላማ ውጪ በስሙ የንግድ ፈቃድ በማውጣት ወደ አትራፊ ንግድ ድርጅት ቀይሯል፣2ኛ አመልካችም ድርጅቱን ወደ ግል ድርጅት እንዲዞር በማሰብ አዲስ የሚቋቋም ተቋም በማስመሰል በሚያዝያ ወር 1992ዓ.ም ንግድ ፈቃድ በማውጣት የድርጅቱን ገቢና ሃብት ለግል ጥቅማቸው በማዋል በልላ ሰው የንብረት ጥቅም ስራ አመራር ላይ ጉዳት ማድረስ ወንጀል ፈጽመዋል በሚል ክስ የቀረበባቸው ሲሆን አመልካቾችም እንዲቀርቡ ከተደረገ በኋላ ወንጀሉን አለመፈፀማቸው ክደው የእምነት ክህደት ቃላቸውን በመስጠታቸው ዐ/ህግ እንደ ክሱ የሚያስረዱለትን የሰው እና የሰነድ ማስረጃዎችን አቅርቦ ከተሰሙና ከተመረመሩ በኋላ አመልካቾች ወንጀሉን መፈፀማቸው ተረጋግጦባቸዋል በማለት እንዲከላከሉ ትዕዛዝ ተሰጥቷል።
አመልካቾችም በትዕዛዙ መሰረት ወንጀሉን ለመከላከል የተለያዩ የሰነድ ማስረጃዎችን ያቀረቡ ቢሆንም በዐ/ህግ በኩል የቀረቡትን ማስረጃዎች ማስተባበል አልቻሉም በሚል የጥፋተኝነት ውሣኔ ከተሰጠባቸው በኋላ 1ኛ አመልካች በ6 ወር እና 2ኛ አመልካች ደግሞ በ1 ወር እስራት እንዲቀጡ ከተወሰነ በኋላ በወ/ህጉ አንቀጽ 192 መሰረት ቅጣቱ በ2 ዓመት የፈተና ጊዜ በመስጠት እንዲገደብላቸው ተደርጓል። በ1ኛ አመልካች የተሰጠው የድርጅቱ ንገድ ፈቃድም ከንግድ መዝገብ ተሰርዞ ድርጅቱ በቀድሞ ሁኔታ እንዲተዳደር በማለት ተጨማሪ ትዕዛዝ ተሰጥቷል።
አመልካቾችም በተሰጠው ውሣኔ ባለመስማማት የይግባኝ አቤቱታቸውን ለዞኑ ከፍ/ፍ/ቤትና ክልሉ ሰበር ችሎት ያቀረቡ ቢሆንም ሁለቱም ፍ/ቤቶች ተመሣሣይነት ባለው መልኩ የስር ፍ/ቤቱን ውሣኔ በማጽናት ወስኗል።
ሚያዝያ 3ዐ ቀን 2ዐዐ4ዓ.ም በተጻፈ ማመልከቻ አመልካቾች ያቀረቡት የሰበር አቤቱታ ይህንኑን ውሣኔ በመቃወም ሲሆን ይዘቱም ባጭሩ የቀረበብን ክስ በወ/ህጉ ቁ. 217/1/ሰ/ መሰረት በይርጋ ቀሪ ሆኖ እያለ ጥፋተኛ ተብለን መቀጣታችን መሰረታዊ የህግ ስህተት ያለበት መሆኑን ጉዳዩ ቀደም ሲል በሸሪዓ ፍ/ቤቶች ቀርቦ ውሣኔ ያገኘ መሆኑ እየታወቀ እንደገና በወንጀል ቀርቦና ታይቶ ጥፋተኛ መባላችን ስህተት መሆኑን ድርጅቱም በጐ አድራጐት ድርጅት ነው መባሉ ስህተት መሆኑን የድርጅቱ ንግድ ፈቃድ በእኔ 1ኛ አመልካች ቢወጣም የድርጅቱ ካርታና ኘላን በድርጅቱ ስም ያለ መሆኑንና የድርጅቱ ንግድ ፈቃድም በ1ኛ አመልካች እንዲወጣ የተደረገው አቅም ካላቸው ተማሪዎች መጠነኛ ክፍያዎችን በመቀበል ለተለያዩ ወጪዎችና ለአስተማሪዎች ደመወዝ እንዲውል መደረጉ ድርጅቱን ከተረጅነትና በዘላቂነት ከችግሩ ለማውጣት በማሰብ እንጂ የግል ጥቅምን ለማሟላት አይደለም።
ይልቁንም 1ኛ አመልካች ከግል ወደ 5ዐዐ,000 ብር በላይ ለድርጅቱ እርዳታ ማድረጌ ጥፋተኛ የተባልኩበትን ወንጀል ለመፈፀም ሀሳብ የልለኝ መሆኑ እየታወቀ ጥፋተኛ ሆነን መቀጣታችንና የድርጅቱ ንግድ ፈቃድም ተሰርዞ በቀድሞ ሁኔታ እንዲተዳደር በሚል የተሰጠው ውሣኔ መሰረታዊ የሆነ የህግ ስህተት ያለበት በመሆኑ ተሽሮ እንዲወሰንላቸው በመከራከር ጠይቀዋል።
አቤቱታውም ተመርምሮ ለሰበር ችሎቱ ያስቀርባል በመባሉ ተጠሪ እንዲቀርብ ተደርጎ የበኩሉን መልስ ሰጥቶበታል። አመልካቾችም የመ/መልሳቸውን ሰጥተውበታል።
የጉዳዩ አመጣጥም አጠር አጠር ባለ መልኩ ከላይ የተገለፀው ሲሆን ይህ ችሎትም የግራ ቀኙን ክርክር የሰበር አቤቱታ ከቀረበባቸው ውሣኔዎችና አግባብነት ካላቸው ድንጋጌዎች ጋር በማገናዘብ በውሣኔዎቹ ላይ መሰረታዊ የሆነ የህግ ስህተት የተፈፀመባቸው መሆን አለመሆኑን በሚከተለው መልኩ መርምረናል።
ከክርክሩ ሂደት መገንዘብ እንደተቻለው ለክርክሩ መነሻ የሆነውና በደሴ ከተማ ቀበል ዐ9 መርከዘል ብርሃን ተብሎ የሚጠራው ት/ቤት በመጀመሪያ በበጎ አድራጊዎች ሲቋቋም ለትርፍና የገንዘብ ጥቅም ለማግኘት የተቋቋመ ሣይሆን በበጎ አድራጎት ማህበር ዓይነት ወላጅ አልባ የሆኑ ህጻናትን በነጻ ማሰተማር አረብኛ ቋንቋንና ቅዱስ ቁራንን ማስተማርና እንዲሁም መስጊዶችን ለመስራት የተቋቋመ ስለመሆኑ በእነዚህ በጎ አድራጉ በሆኑ ሰዎች በተሰበሰበ ንብረት አማካኝነት ት/ቤቱ የመምስረቻ ጽሑፍ ተቀረፆለት በ1984ዓ.ም የተቋቋመ መሆኑና ከተቋቋመም በኋላ ለተወሰኑት ዓመታት ስራውን ያለምንም ክፍያ በነጻ ሲያከናውን የቆየ ስለመሆኑ በፍሬ ነገር ደረጃ በስር ፍ/ቤቶች የተረጋገጠ ነገር ነው። ይሁን እንጂ በኋላ ላይ 1ኛ አመልካች ድርጅቱን እንዲመራ ከሟች አባቱ በኑዛዜ በተሰጠው ኃላፊነትና 2ኛ አመልካችም ከ1ኛ አመልካች ባገኘው ውክልና መነሻነት የት/ቤቱን ስራ በመምራት ላይ እያሉ በ1992ዓ.ም የድርጅቱን ንግድ ፈቃድ በ1ኛ አመልካች እንዲወጣ በማድረግ በፊት ከተቋቋመለት ዓላማ ወጪ ወደ ንግድ ድርጅትነት ቀይረው እስከ አሁን በዚሁ አኳኋን እየሰሩ ይገኛሉ። ት/ቤቱ በፊት ያለ ክፍያ በነጻ ሲያከናውን የነበረው ስራ ቀርቶ አሁን ከሚያስተምራቸው ተማሪዎች ገንዘብ እየሰበሰቡ መሆናቸውን አመልካቾችም አይክዱም። የተከሰሱበት ድርጊትም ይሄው ነው። ይህ ድርጊት ደግሞ እስከ አሁንም ሣይቋረጥ የቀጠለ በመሆኑ በወ/ህጉ አንቀጽ 219/2/ ስር እንደተመለከተው በይርጋ ቀሪ ላሆን የሚችልበት አግባብ የለም። ስለሆነም የይርጋ ክርክርን በሚመለከት የቀረበው የሰበር አቤቱታ በዚህ ምክንያት ተቀባይነት አይኖረውም።
ጉዳዩ ከዚህ ቀደም በሸሪዓ ፍ/ቤቶች ታይቶ የመጨረሻ ውሣኔ አግኝቶ እያለ በድጋሜ በወንጀል ተከሰን ጥፋተኛ መባላችን አግባብ አይደለም በሚል የቀረበው ክርክርም ቢሆን በፍታብሕር ኃላፊነት ተከሰው በጉዳዩ ላይ ስልጣን ባለው አካል ውሣኔ መስጠቱ በወንጀል ህጉ በኩል ያለውን ኃላፊነት ላያስቀር የሚችል ባለመሆኑ በዚህ ረገድ የቀረበው አቤቱታ ከወ/ህጉ አንቀጽ 2/5/ እና እንዲሁም በወ/መ/ህ/ሥ/ሥ/ቁ 13ዐ/2/ለ/ አኳያ ሲታይ ተቀባይነት ያለው ሆኖ አላገኘንም። የተከሰሱበት ድርጊትም በህግ ወይም በውል አማካኝነት የተሰጣቸውን ኃላፊነት ያለአግባብ በመገልገል በልላ ሰው ጥቅም ላይ ጉዳት በሚያደረስ አኳኋን በጎ አድራጎት የነበረን ድርጅት ወደ ንግድ ድርጅትነት ቀይሯል በሚል ሲሆን ይህ ድርጊትም ስለመፈፀሙ በፍሬ ነገር ደረጃ በስር ፍ/ቤቶች የተረጋገጠ ጉዳይ ነው። ስልጣን ባላቸው ፍ/ቤቶች መፈፀሙ የተረጋገጠው ድርጊትም አመልካቾች የተከሰሱበትን የወንጀል ህጉን ድንጋጌ አንቀጽ 7ዐ2/3/ ስር የተመለከተውን ወንጀል የሚያቋቁም ነው። በመሆኑም አቤቱታ የቀረበባቸው ውሣኔዎች ላይ መሰረታዊ የሆነ የህግ ስህተት የተፈፀመባቸው ሆኖ ስላላገኘን ተከታዩን ውሣኔ ሰጥተናል።
ው ሣ ኔ
በዚህ ጉዳይ በደሴ ከተማ ወረዳ ፍ/ቤት ደቡብ ወሎ መስተደደር ዞን ከፍ/ፍ/ቤትና እንዳሁም በክልሉ ሰበር ችሎት የተሰጡት ውሣኔዎች በወ/መ/ህ/ስ/ስ/ቁ.195/2/ለ/2/ መሰረት ፀንቷል።
የአመልካቾች የሰበር አቤቱታ ተቀባይነት የለውም ብለናል።
No topics extracted.