No summary available.
የካቲት 11 ቀን 2005 ዓ.ም.
ዳኞች፡- ተሻገር ገ/ሥላሴ አልማው ወል ረቶ ቶሎሳ አዳነ ንጉሴ ሙስጠፋ አህመድ አመልካች፡- አቶ ተድላ ተገኝ ጉዳይ ተከታይ ቢያዝን አበራ ቀረቡ ተጠሪ፡- የአማራ ብሕራዊ ክልላዊ መንግስት ፍትህ ቢሮ ዐቃቤ ሕግ የረበ የለም **
መዝገቡ ተመርምሮ ተከታዩ ፍርድ ተሰጥቷል።
**
ጉዳዩ የወንጀል ሲሆን ክርክሩ የተጀመረው የአሁኑ ተጠሪ ባሁኑ አመልካች ላይ በምዕራብ ጎጃም ዞን ከፍተኛ ፍርድ ቤት በመሰረተው ክስ መነሻ ነው።ተጠሪ በአመልካች ላይ የመሰረተው ክስ በአምስት ምድብ የተከፈለ ሲሆን አንደኛው ክስ በ1949 ዓ/ም የወጣውን የወንጀል ሕጉ አንቀፅ 667(1) ስር የተመለከተውን በመተላለፍ ጥር 10 ቀን 1995 ዓ/ም ለአቶ አመሸ ጌታሁን በሰጡት የብር 40,000.00(አርባ ሺህ) ገንዘብ ብድር በወር 10% እንዲከፍል በመጠየቅና በመዋዋል ገንዘቡን በማበደር ተበዳይ ወለዱን ለወራት ሲከፍሉ ቆይተው በማቋረጡ በፍርድ ቤት ተከሰው በጠቅላላ ከእነወለዱ ብር 58,000.00(ሃምሳ ስምንት ሺኅ ብር) ቤቱን ሽጦ እንዲከፈል በማድረጋቸው የአራጣ የወንጀል ድርጊት ፈጸመል የሚል ሲሆን 2ኛው ክስም አመልካች ቀኑ በትክክል ባልታወቀበት በነሐሴ ውር በ1994 ዓ/ም ለግል ተበዳይ አቶ አሰፋ አበበ በወቅቱ የገጠመውን የገንዘብ ችግር ምክንያት በማድረግ ብር 20,000.00(ሃያ ሺኅ ብር) በማበደር በህግ ከተፈቀደው የወለድ መጠን በላይ በወር 10% ላከፍል በመዋዋልና በመያዣነት የገንዘብ መጠን የተፃፈበትን ቼክ በተበዳይ የተፈረመና በአመልካች ልጅ ስም የተፃፈ በመቀበል ብድሩን በመስጠት ተበዳይ ዋናውን ገንዘብ ከፍለው ወለዱን ብር 18,000.00 ሳይከፈሉ በመቅረታቸው በፍርድ ቤት ክስ በመመሰረት የመኖሪያ ቤታቸውን ያሸጡ መሆኑን በመጥቀስ ነባሩን የወንጀል ሕግ አንቀጽ 667(1) ተላልፈዋል የሚል ነው።3ኛ፣4ኛ እና 5ኛ ክሶችም በተለያዩ ግለሰቦች፣በተለያዩ ጊዜያአት ከተፈጸሙ የአራጣ ወንጀል ድርጊቶች ጋር የተያያዙ ሁነው በስር ፍርድ ቤት በተለያየ የክርክር ደረጃ አመልካች በነጻ እንዲሰናበቱ የተደረጉባቸው ስለመሆኑ የውሳኔው ግልባጭ ያሳያል።
አመልካችም ክሱን ከተረዱት በኋላ በሶስተኛው ክስ ላይ ተቃውሞ ከማቅረባቸው ውጪ በልሎች ክሶች ላይ ተቃውም የልላቸው መሆኑን በመግለጸቸው ምክንያት ስለየድርጊቱ አፈጻጸም የእምነት ክህደት ቃል ሲጠየቁ ክደው ተከራክሯል።አቃቤ ሕግ በበኩሉ የሰውና የሰነድ ማስጃዎች ያሉት መሆኑን ገልጾ ማስረጃዎችን አስምቷል።የአቃቤ ሕግ ማስረጃዎች ከተሰሙ በኋላም የአመልካች የመከላከል መብቱ ተጠብቆላቸው የመከላከያ ማስረጃዎች ተሰምተዋል።ፍርድ ቤቱም ጉዳዩን መርምሮ የአመልካች የመከላከያ ማስጃዎች የአቃቤ ሕግ ማስረጃዎችን ለማስተባበል የሚችሉ ሳይሆኑ የሚያጠናክሩ ሁነው መገኘታቸውን ገልጾ የመከላከያ ማስረጃዎችን ውድቅ በማድረግ አመልካችን በሁለት ክሶች ጥፋተኛ በማድረግ ቅጣቱን በተመለከተ ደግሞ ለሁለቱ ክሶች ለእያንዳንዳቸው በአንድ አመት ከስድስት ወር፣በድምሩ በሶስት አመት ፅኑ እስራትና በብር 4000.00(አራት ሺህ ብር) የገንዘብ መቀጮ እንዲቀጡ ሲል ወስኗል።አመልካች በዚህ ውሳኔ ባለመስማማት ይግባኙን ለአማራ ክልል ጠቅላይ ፍርድ ቤት ይግባኝ ሰሚ ችሎት እና ሰበር ሰሚ ችሎት ቢያቀርቡም ተቀባይነት አላገኙም።የአሁኑ የሰበር አቤቱታ የቀረበውም ይህንኑ ውሳኔ በመቃወም ለማስለወጥ ነው።የአመልካች የሰበር አቤቱታ መሰረታዊ ይዘትም የአቃቤ ሕግ ክስ ይዘት በወንጀል ሕጉ ስለአራጣ የተደነገገውን ድንጋጌ እንደማያቋቁም፣አቃቤ ሕግ በማስረጃዎቹ አቀራረብና የማስረዳት ግድታ በሕጉ የተመለከተውን መመዘኛ ያላሟላ መሆኑን ዘርዝረው የበታች ፍርድ ቤቶች የጥፋተኛነት ውሳኔ እንዲሻርላቸው ዳኝነት መጠየቃቸውን የሚያሳይ ነው።አቤቱታው ተመርምሮም አመልካች ላይ ከተጠቀሱት ክሶች ውስጥ በተራ ቁጥር ሁለት በተጠቀሰው የወንጀል ኃላፊነት አለባቸው ተብሎ የመወሰኑን አግባብነት ለመመርመር ሲባል ጉዳዩ ለሰበር ችሎቱ እንዲቀርብ የተደረገ ሲሆን ለተጠሪ ጥሪ ተደርጎለት ቀርቦ ግራ ቀኙ በጽሑፍ እንዲከራከሩ ተደርጓል።
የጉዳዩ አመጣጥ አጠር አጠር ባለመልኩ ከላይ የተገለፀው ሲሆን ይህ ችሎትም የግራ ቀኙን ክርክር ለሰበር አቤቱታው መነሻ ከሆነው ውሳኔ እና አግባብነት ካለቸው ድንጋጌዎች ጋር በማገናዘብ ጉዳዩን በሚከተለው መልኩ መርምሮታል።እንደመረመረውም በጉዳዩ ላይ በተሰጠው ውሳኔ መሰረታዊ የሆነ የሕግ ስህተት ተፈጽሟል ለማለት ይቻላል? ወይስ አይቻልም? የሚለው ነጥብ በጭብጥነት ላመረመር የሚገባው ሁኖ አግኝቶታል።
ተጠሪ በአመልካች ላይ የመሰረተው ክስ ብዛቱ አምስት ሲሆን ጥፋተኛ የተባሉት ግን በሁለት ክሶች ብቻ ሁኖ በእነዚህ ክሶችም አመልካች የግል ተበዳዮች የገንዘብ ችግር ያጋጠማቸው መሆኑን በማወቅና በተለያዩ ዘድዎች የግል ተበዳዮችን በማግኘት በተለያዩ ጊዜያአት፣ለተለያዩ ግለሰቦች የተለያየ መጠን ያለውን የገንዘብ ብድር ሰጥተው ከህግ ከተደነገገው ውጪ የወለድ ተመን ሲያስከፍሉ ቆይተዋል፣በዚህ አድራጎታቸውም የአራጣ ወንጀል ድርጊት ፈፅመዋል በሚል ነው።አመልካች የወንጀል ድርጊቶችን ክዶ የተከራከረ ሲሆን አቃቤ ሕግ በኩሉ አሉኝ ያላቸውን የሰውና የሰነድ ማሰረጃዎችን አቅርቦ ከአሰማ በኋላ የቀረቡት ማሰረጃዎች የወንጀል ድርጊቱ ስለመፈጸሙ በወ/መ/ሥ/ሥ/ሕ/ቁጥር 141 በተመለከተው ድንጋጌ መሰረት በበቂ ሁኔታ መመስከሩን ፍርድ ቤቱ በመገንዘብ አመልካች የአመልካችን የመከላከል መብት ያከበረላቸው ሲሆን አመልካች የመከላከያ ማስረጃዎቹን አቅርበዋል።በዚህ ችሎቱ እንዲታይ በጭብጥነት ለተያዘው የሁለተኛ ክስ አመልካች የወንጀል ድርጊቱን ለመከላከል ያቀረቡት በፍርድ ቤት የተሰጠውን የፍትሀ ብሕር ክስ ውሳኔዎችን ሲሆን ፍርድ ቤቱም እነኚህን የአመልካችን የመከላከያ ማሰረጃዎች ይዘት በመመዘን የአቃቤ ሕግ ማሰረጃዎችን የማስተባበል ብቃት የልላቸው መሆኑን ያሳያሉ ያላቸውን ምክንያቶችን ዘርዝሮ ውድቅ አድርጓቸዋል።በዚህ ረገድ አመልካች አጥብቀው የሚከራከሩትም በክሱ ለተጠቀሱት ግለሰብ መያዣ ይሆነው ዘንድ ቼኩ ተፅፎ የተሰጠው ለአመልካች ልጅ እንጂ ለአመልካች አይደለም፣የፍትሃ ብሄር ክሱ የሚያሳየውም አመልካችን ሳይሆን የአመልካችን ልጅ ነው በሚል ነው።ይሁን እንጂ ጉዳዩን በመጀመሪያ ደረጃ የተመለከተው ፍርድ ቤት የአመልካች ልጅ የተሰጣቸው ቼክ መነሻው ለግል ተበዳዩ አመልካች የሰጡት ብድር መሆኑንና ቀጥተኛ ግንኙነት ያለው መሆኑን፣ አመልካች ብድሩን ለግል ተበዳይ ማበደራቸውን፣የብድሩ ወርሃዊ የወለድ መጠንም ሕጋዊ ያለመሆኑን ከማረጋገጡም በተጨማሪ የአመልካች ልጅ በወንጀሉ አፈጻጸም ተሳታፊ ነበሩ ከሚያስኝ በስተቀር አመልካችን ከወንጀል ተጠያቂነት የማያድናቸው መሆኑን በፍርዱ ሐተታ ላይ በገለፀው ምክንያት መገንዘብ የምንችለው ጉዳይ ነው።ይህ የስር ፍርድ ቤት የፍሬ ነገር እና የማስረጃ ምዘና ድምዳሜ ፍሬ ነገሩን የማጣራትና ማስረጃን የመመዘን ስልጣን ባለው የክልሉ ጠቅላይ ፍርድ ቤት ይግባኝ ሰሚ ችሎትም ሙሉ በሙሉ ተቀባይነት አግኝቷል፡ጉዳዩ ለዚህ ችሎት ሲቀርብ የተያዘው ጭብጥ አመልካች ጥፋተኛ ተብሎ ከተቀመጡባቸው ድርጊቶች ሁለተኛው ክስ በልጃቸው ስም በመያዣነት በተሰጠው ቼክ እና የልጁ ተወካይ በመሆን የተበዳይን ቤት ማሸጡ ሆኖ ባለበት የስር ፍርድ ቤቶች በአራጣ ማበደር ወንጀል ጥፋተኛ ማለታቸው ተገቢ መሆን ያመሆኑን ለመመርመር ሲባል ነው።ይሁን እንጂ ከላይ እንደተገለጸው የቼኩ መነሻው የአመልካች ብድር መሆኑና ወለዱም ሕጋዊ ያልነበረ መሆኑ በአቃቤ ሕግ ማስረጃ ስለመረጋገጡ ፍሬ ነገሩን የማጣራትና ማስረጃን የመመዘን ስልጣን ያላቸው ፍርድ ቤቶች ያረጋገጡት ጉዳይ በመሆኑ አመልካችን ከወንጀል ተጠያቂነት ነፃ ለማድረግ የሚያስችል የህግ መሰረት የለም።ይልቁንም አመልካች በድርጊቱ በነባራቸው ተሳትፎ መጠን በወንጀል የሚጠየቁ መሆኑን ከክርክሩ ሂደት የምንገነዘበው ነጥብ ነው።በመሆኑም አመልካች ድርጊቶችን ስለመፈፀማቸው አቃቤ ሕግ በማሰረጃቹ አላስረዳም፣በመከላከያ ማስረጃዎችም ተደግፍአለሁ በማለት አመልካች የሚያቀርቡት የሰበር ቅሬታ የፍሬ ነገር እና የማስረጃ ምዘና ጉዳይ ሁኖ ስለአገኘነው ይህ ችሎት በኢ.ፍ.ዲ.ሪፐብላክ ሕግ መንግስት አንቀፅ 80(3(ሀ)) እና አዋጅ ቁጥር 25/1988 አንቀጽ 10 ከተሰጠው ስልጣን አንጻር የምንመለከታቸው ሁኖ ስላለአገኘን አልፈናል።
በፍሬ ነገር ደረጃ የተረጋገጡትን ነጥቦች ይዘን ወደ ሕጉ ጥያቄ ስንመጣ አመልካች ከሕግ ከተደነገገው ውጪ በወር 10% በማስከፈል ለግል ተበዳዮች ገንዘብ ማበደራቸው የተረጋገጠ በመሆኑ ከአበደሩት ገንዘብ እጥፍ የሆነ ገንዘብም ከግል ተበዳዮቹ የሰበሰቡና ንብረታቸውም እንዲሸጥ ያደረጉ በመሆኑ አድራጎታቸው የአራጣ ወንጀል የሚያቋቋም ሁኖ አግኝተናል።ቅጣትን በተመለከተ የቀረበ ቅሬታ ባለመኖሩ የምንመረምረው ሁኖ አልተገኘም።ሲጠቃለልም የበታች ፍርድ ቤቶች በአመልካች ላይ የሰጡት የጥፋተኝነት ውሳኔ ሲታይ መሰረታዊ የሆነ የህግ ስህተት የተፈፀመበት ነው ለማለት ስላልተቻለ ተከታዩን ወስነናል።
ው ሣ ኔ
በምዕራብ ጎጃም ዞን ከፍተኛ ፍርድ ቤት በመ/ መጋቢት 03 ቀን 2004 ዓ/ም ተሰጥቶ በአማራ ክልል ጠቅላይ ፍርድ ቤት ይግባኝ ሰሚ ችሎት በመ/ቁጥር 02-04311 ሚያዚያ 02 ቀን 2004 ዓ/ም በክልሉ ሰበር ሰሚ ችሎት በመ/ ሚያዚያ 24 ቀን 2004 ዓ/ም የጸናው የጥፋተኝነት ውሳኔ በወ/መ/ሥ/ሥ/ሕ/ቁጥር 195(2(ሐ) መሰረት ሙሉ በሙሉ ፀንቷል።
አመልካች በሁለት የአራጣ የወንጀል ድርጊቶች ጥፋተኛ ተብለው በሶስት አመት ፅኑ እስራትና በብር 4000.00(አራት ሺህ)የገንዘብ መቀጮ እንዲቀጡ ተብሎ በተሰጠው የበታች ፍርድ ቤቶች ውሳኔ ላይ መሰረታዊ የሆነ የሕግ ስህተት የለም ብለናል።
በበታች ፍርድ ቤቶች የተሰጠ የቅጣት ውሳኔ የፀና መሆኑን አውቆ ተከታትሎ እንዲያስፈፅም ለማረሚያ ቤቱ ይጻፍ ብለናል።
No topics extracted.