No summary available.
ሚያዝያ 07 ቀን 2005 ዓ.ም ዳኞች፡- አልማው ወል ዓላ መሐመድ ረታ ቶሎሳ አዳነ ንጉሴ ሙስጠፋ አህመድ አመልካች፡- ጌታቸው ገላዬ ፈረደ - የቀረበ የለም ተጠሪ፡- የደቡብ ክልል ዐቃቤ ሕግ - የቀረበ የለም **
መዝገቡ ተመርምሮ ተከታዩ ፍርድ ተሰጥቷል።
**
ጉዳዩ ሰው የመግደል ወንጀል ሲሆን ክርክሩ የተጀመረው የአሁን ተጠሪ ባሁኑ አመልካች እና አቶ ሰይፈ ገ/ሚካኤል በተባሉት ግለሰብ ላይ በሐዋሳ ከፍተኛ ፍርድ ቤት በመሰረተው ክስ መነሻ ነው። የክሱ ይዘትም ተከሳሾቹ በዋና ወንጀል አድራጊነትና ተካፋይነት ሰኔ 02 ቀን 2004 ዓ/ም በሀዋሳ ከተማ ባህል አዳራሽ ክፍለ ከተማ በአደሬ ቀበል ፋሚላ ሆቴል ተብሎ በሚጠራው ቤት ሟች ቡቼ ወይም ብስራት ተፈሪ የተባለውን የአሁኑ አመልካች በያዘው ሽጉጥ ተኩሶ ግራ ብብቱን መትቶ እንደገደለውና የሥር ሁለተኛ ተከሳሽ የነበረው ግለሰብ ደግሞ የውሲኪ ጠርሙስ ይዞ ሟች እንዳይቀሳቀስ ያደረገውና ሟች የተመታበት ሽጉጥ ቀላህ በመሰወር የአሁኑን አመልካች የረዳ መሆኑን ዘርዝሮ ተከሳሾቹ ሆነ ብለው በፈፀሙት ከባድ የግድያ ወንጀል በ1996 ዓ.ም በወጣው የወንጀል ሕጉ አንቀፅ32(1(ሀ) እና 539(1ሀ) ስር የተመለከተውን ድንጋጌ ተላልፈዋል የሚል ነው። የአሁኑ አመልካችም እንደክሱ ድርጊቱን ያለመፈፀማቸውን ጠቅሰው ጥፋተኛ ያለመሆናቸውን ገልፀው ተከራክረዋል።
የአሁኑ ተጠሪም አሉኝ ያላቸውን ማስረጃዎችን አቅርቦ ያሰማ ሲሆን የአሁኑ አመልካችም ድርጊቱን ራሱ ለመከላከል ሲሉ የፈፀሙት መሆኑን የሚያሳይ ጭብጥ አስይዘው የመከላከያ ማሰረጃዎቻቸውን አሰምተዋል።
ጉዳዩን በመጀመሪያ ደረጃ የተመለከተው ፍርድ ቤትም የአመልካች ድርጊት በሕጋዊ መከላከል ስር የማይወድቅ መሆኑን ያሳያሉ ያላቸውን ምክንያቶችን ጠቅሶ አመልካች በዚህ ረገድ ያቀረቡትን ክረክር ውድቅ በማድረግ የወንጀል ተጠያቂነት አለባቸው ወደሚለው ድምዳሜ የደረሰ ሲሆን ድርጊቱ የሚሸፍነው ደግሞ በአቃቤ ክስ በተመለከተው ድንጋጌ ሳይሆን በወንጀል ሕጉ አንቀፅ 540 ስር ነው በማለት አመልካችን በተራ የሰው ግድያ ወንጀል ጥፋተኛ ያላቸው ሲሆን ቅጣቱን በተመለከተም የግራ ቀኙን የቅጣት አስተያየት በመቀበልና ከወንጀል ቅጣት አወሳሰን ጋር አዛምዶ መመልከቱን ገልፆ አመልካችን በ15 ዓመት ፅኑ እስራት እንዲቀጡ ሲል ወስኗል።
በዚህ ውሳኔ የአሁን አመልካች ባለመስማማት ይግባኙን ለክልሉ ጠቅላይ ፍርድ ቤት አቅርበው ግራ ቀኙ ከተከራከሩ በኃላ ፍርድ ቤት ጉዳዩን መርምሮ አመልካች በተራ የሰው ግድያ ወንጀል ጥፋተኛ መባላቸውን በተመለከተ ያፀናው ሲሆን ቅጣቱን በተመለከተ ግን አሻሽሎ ስምንት ዓመት ላሆን ይገባል ሲል ምክንያቱን ጠቅሶ ወስኗል። ጉዳዩ በሰበር አቤቱታ የቀረበለት የክልሉ ሰበር ሰሚ ችሎትም የክልሉ ጠቅላይ ፍርድ ቤት ይግባኝ ሰሚ ችሎት በሰጠው ውሳኔ ላይ መሰረታዊ የሆነ የህግ ስህተት የለም ሲል የአመልካችን አቤቱታ ሳይቀበል የቀረ ሲሆን የአሁኑ የሰበር አቤቱታ የቀረበውም በዚሁ ውሳኔ ላይ ነው። የአመልካች የሰበር አቤቱታው መሰረታዊ ይዘትም ድርጊቱን በሕጋዊ መከላከል ስር የሚሸፍን ሁኖ እያለ የበታች ፍርድ ቤቶች በዚህ ረገድ የቀረበውን ክርክር ውድቅ በማድረግ አመልካችን በወንጀል ተጠያቂ ማድረጋቸው ከህጉ ውጪ ነው የሚል ነው። አቤቱታው ተመርምሮ በሰበር ችሎቱ ላታይ የሚገባው መሆኑ ታምኖበት ለዚህ ችሎት እንዲቀርብ የተደረገ ሲሆን ለተጠሪም ጥሪ ተደርጎለት ተጠሪ ቀርቦ በሰጠው መልስ የአመልካች አድራጎት በሕጋዊ መከላከል ስር የማይሸፈን ስለመሆኑ በማስረጃ መረጋገጡን ጠቅሶ በጉዳዩ ላይ የተሰጠው ውሳኔ መሰረታዊ የሆነ የህግ ስህተት የለም ሲል ተከራክሯል። አመልካችም የሰበር አቤቱታቸውን በማጠናከር የመልስ መልሳቸውን ሰጥተዋል።
የጉዳዩ አመጣጥ አጠር አጠር ባለመልኩ ከላይ የተገለጸው ሲሆን ይህ ችሎትም የግራ ቀኙን ክርክር ለሰበር አቤቱታው መነሻ ከሆነው ውሳኔ እና አግባብነት ካላቸው ድንጋጌዎች ጋር በማገናዘብ ጉዳዩን በሚከተለው መልኩ መርምሮታል። እንደመረመረውም አመልካች በወንጀል ድርጊት ተጠያቂ መደረጋቸው ባግባቡ ነው? ወይስ አይደለም? የሚለው ነጥብ በጭብጥነት ላታይ የሚገባው ሁኖ አግኝቶታል።
ከክክሩ ሂደት መገንዘብ የተቻለው አመልካች ሟችን መግደላቸውን ሳይክዱ አጥብቀው የሚከራከሩት ድርጊት ሕጋዊ መከላከል ነው። በወንጀል ተጠያቂነትን አያስከትልም በማለት መሆኑን የበታች ፍርድ ቤቶች አመልካችን በወንጀል ተጠያቂነት አለባቸው በማለት ውሳኔ ላሰጡ የቻሉት አመልካች ከሟች ጋር ተጣልተው በሰዎች ከተገላገሉ በኃላ ሟች ወደ አመልካቹ በመሄድ ላይ እያለ አመልካቸ ልሎች አማራጮችን ሳይጠቀሙ የጦር መሳሪያ ያልያዘውን ሟች ወደ አመልካቹ ሳይጠጋ ተኩሰው መምታታቸው በሕጋዊ መከላከል ስር የሚሸፈን አይደለም በሚል ምክንያት መሆኑን ነው። አመልካቹ ሟች በሕይወቴ ላይ አደጋ ላያደርስ የሚችል ሳንጃ ይዞ በመምጣት ጥቃት ላሰነዝርብኝ ሲል ድርጊቱን መፈፀሜ ተረጋግጦ እያለ የበታች ፍርድ ቤቶች ይህንን ውድቅ ማድረጋቸው ያላግባብ ነው በማለት አድራጎታቸው በሕጋዊ መከላከል ስር እንዲወድቅ ከሚያደርጉ ምክንያቶች ውስጥ ባግባቡ ያልታዩላቸው መሆኑን በመግለጽ የሚከራከሩ መሆኑንም ተረድተናል። ሆኖም አመልካቹና ሟቹ ተጣልተው ቆይተው ሰዎች ከገላገሐቸው በኃላ ሟቹ ወደ አመልካች የሥራ ቦታ ተመልሶ በመሄድ ላይ እያለ በሽጉጥ ጥይት ተመትቶ ስለመሞቱ ከመረጋገጡ ውጪ አመልካች በዚህ ሰበር ደረጃ ሟቹ በህይወት አትኖራትም ብሎ ዝቶ ከሄደ በኃላ ሳንጃ ይዞ በመመለስ ልላ አማራጭ በልለበት ሁኔታ ጥቃት ላያደርስ ሲል ነው ድርጊተጁ የተፈፀመው በማለት የሚያነሷቸው ፍሬ ነገሮች ፍሬነገርን የማጣራትና ማስረጃን የመመዘን ስልጣን ያላቸው የበታች ፍርድ ቤቶች ያላረጋገጧቸው በመሆኑ ይህ ሰበር ሰሚ ችሎት በኢ.ፍ.ዲ.ሪፐብላክ ህገ መንግስት አንቀፅ 80(3(ሀ) እና አዋጅ ቁጥር 25/1988 አንቀጽ 10 ድንጋጌዎች መሰረት ከተሰጠው ስልጣን አንፃር በዚህ የሰበር ደረጃ ተቀባይነት የሚሰጣቸው ነጥቦች አይደለም። ይህ ችሎት መሰረታዊ የሆነ የህግ ስህተትን ከማረም ውጪ ፍሬ ነገርን የማጣራትና ማስረጃን የመመዘን ስልጣን በሕግ አልተሰጠውምና። በመሆኑም የበታች ፍርድ ቤቶች በፍሬ ነገር ደረጃ ያረጋገጧቸው ነጥቦች አመልካች በዚህ ሰበር ደረጃ ከሚያነሷቸው ጋር የማይጣጣሙ በመሆኑ በዚህ ረገድ የቀረቡትን የአመልካችን ቅሬታዎችን የምንቀበላቸው ሁነው አልተገኘም በበታች ፍርድ ቤበቶች የተረጋገጡትን ፍሬ ነገሮች እንዳለ ይዘን ጉዳዩ በህጋዊ መከላከል ስር የሚወድቅ መሆን ያለመሆኑን ተመልክተናል።
በመሰረቱ ህጋዊ መከላከል በወንጀል የሚያስቀጣው የራስን ወይም የልላውን ሰው መብት ህገ ወጥ ከሆነ ጥቃት ወይም በቅርብ ከሚደርስ ህገወጥ ጥቃት ለማዳን ጥቃቱ እንዳይደርስ ለማድረግ ልላ መንገድ ሳይኖር ከሁኔታው መጠን ባለማለፍ የተፈጸመ መሆኑ ሲረጋገጥ ስለመሆኑ ከኢ.ፍ.ዲ.ሪብላክ የወንጅል ሕግ አንቀጽ 78 ይዘትና መንፈስ የምረዳው ጉዳይ ነው። ሕጋዊ መከላከል የወንጀል ተጠያቂነትን የማያስከትለው ተመጣጣኝ የሆነ ዘድ ወይም መሳሪያ በመጠቀም በቅርብ መድረሱ የማይቀረውን ህገ ወጥ የሆነ ጥቃት ለመከላከል አስፈላጊ የሆነ ድርጊት መፈፀም ሲረጋገጥ ስለመሆኑ የኢ.ፍ.ዲ.ሪብላክ የወንጀል ህግ አንቀፅ 78 እነ 79 ድንጋጌዎች ጣምራ ንባብ በግልጽ ያሳያል። አመልካች በሕይወታቸው ጥቃት እንዳይደርስ ልላ አማረጭ ያልተጠቀሙ መሆኑን ሟቹ ከያዘው መሳሪያ ተመጣጣኝነት የልለውን መሳሪያ መጠቀማቸው በሚገባ የተረጋጠ ጉዳይ ነው። እንዲህ ከሆነ አመልካች ድርጊቱ የተፈፀመው በህጋዊ መከላከል ነው በማለት የሚያቀርቡት ክርክር የሕግ መሰረት ያለው ሁኖ አልተገኘም። በወንጀል ህጉ አንቀፅ 541 ስር በተመለከተው አኳኋን ሕጋዊ መከላከልን ከመጠን የማሳለፈው አድራጎት ነው እንዳይባልም ድርጊቱ የተፈፀመው አመልካቹና ሟቹ ጠብ አስነስተው በሰዎች ተገላግለው ከተለያዩ በኃላ በመሆኑ ቅጣትን የሚያቀሉ ምክንያቶች ሰውን የመግደል ወንጀል ተፈጽሟል ለማለት የሚቻል ሁኖ አልተገኘም። ስለሆነም በፍሬ ነገር ደረጃ ከተረጋገጡት ነጥቦች ስንነሳ የአመልካች አድራጎት መበህጋዊ መከላከል ስር የሚሸፈን ሁኖ ስላላገኘነው በዚህ ረገድ የቀረበውን የአመልካችን ቅሬታ አልተቀበልነውም።
ልላው አመልካች በቅጣት አወሳሰን ጊዜ የበታች ፍርድ ቤቶች የወንጀሉን ደረጃ ከባድ ነው በማለት መመደባቸው ተገቢ አይደለም በማለት የሚያቀርቡት ቅሬታም ጉዳዩን በመጀመሪያ ደረጃ የተመለከተው ፍርድ ቤት በዚህ ረገድ ውሳኔ ሲሰጥ የያዘው ድምዳሜ መሰረት ያደረገ እንጂ ይሕ የሥር ፍርድ ቤት ድምዳሜ በይግባኝ ሰሚው የክልሉ ጠቅላይ ፍርድ ቤት ተለውጦ ወንጀሉ መካከለኛ ደረጃ ተብሎ የተመደበ መሆኑን መሰረት ያላደረገ የክርክሩን ሂደት የማያሳይ በመሆኑ ተቀባይነት የልለው ሁኖ አግኝተናል። ሲጠቃለልም አመልካች በወንጀል ተጠያቂ ናቸው ተብሎ በተራ ቁጥር የሰው መግደል ወንጀል ጥፋተኛ ተብለው በስምንት ዓመት ጽኑ እስራት እንዲቀጡ በተሰጠው ውሳኔ ላይ መሰረታዊ የሆነ የህግ ስህተት ስላላገኘ ተከታዩን ወስነናል።
ታህሳስ 18 ቀን 2005 ዓ.ም የሰጠው ትዕዛዝ በወ/መ/ሥ/ሥ/ህ/ቁጥር 195(2(ለ-2)) መሰረት ሙሉ በሙሉ ፀንቷል።
የአመልካች ድርጊት በሕጋዊ መከላከል የሚሸፈን አይደለም ብለናል።
በክልሉ ጠቅላይ ፍርድ ቤት የተሰጠው ውሳኔ የፀና መሆኑን አውቆ ቅጣቱን ተከታትሎ እንዲየስፈጽም ለማ/ቤቱ ይገለፅለት ብለናል።
No topics extracted.