No summary available.
መጋቢት 25 ቀን 2005 ዓ.ም ዳኞች፡- አልማው ወል ዓላ መሐመድ ረታ ቶሎሳ አዳነ ንጉሴ ሙስጠፋ አህመድ አመልካች፡- እነ ሰይፉ ደስታ - ቀረቡ ተጠሪ፡- የኦሮሚያ ክልል ዐቃቤ ህግ - አልቀረበም መዝገቡን መርምረን የሚከተለውን ፍርድ ሰጥተናል።
ጉዳዩ የቀረበው አመልካች የፍድራል ጠቅላይ ፍ/ቤት ሰበር ችሎት የሰጠው የቅጣትና የቅጣት አፈፃፀም ውሳኔ መሰረታዊ የሕግ ስህተት ያለበት ስለሆነ በሰበር ታይቶ ይታረምልኝ በማለት ስላመለከቱ ነው። ጉዳዩ በከባድ ቸልተኝነት የሰው መግደል ወንጀል የሚመለከት ነው። ጉዳዩ በመጀመሪያ የታየው በፊንፊኔ ዙሪያ ዞን ከፍተኛ ፍ/ቤት ነው። የዞኑ ከፍተኛ ፍ/ቤት ተጠሪ ከሳሽ አመልካች ተከሳሽ በመሆኑ ተከራክረዋል።
የክርክሩ መነሻ ተጠሪ አመልካች በኢ.ፍ.ዲ.ሪ የወንጀል ሕግ አንቀጽ 543 ንዑስ አንቀጽ 2 የተመለከተውን በመተላለፍ፣ የሰልዳ ቁጥሩ 3-41869 በማሽከርከር ላይ እያለ ተገቢውን ጥንቃቄ ባለማድረግ ጥር 27 ቀን 2003 ዓ.ም ከቀኑ ስምንት ሰዓት ተኩል ሲሆን ጫናጮ ከተማ ቀበል 01 ፍኔት ግዛው የተባለች ልጅ በመግጨት በከባድ ቸልተኝነት የሰው መግደል ወንጀል ፈፅሟል። አመልካች አደጋው ተከስቷል። ከአቅሜ በላይ በሆነ ሁኔታ ህፃኗን ገጭቻለሁ በማለት ተከራክሯል። ተጠሪ የሰው ምስክሮችና የትራፊክ ፕላን መግለጫ በማስረጃነት አቅርቧል።
ተጠሪ መከላከያ ምስክሮች አቅርቦ አሰምቷል። ፍ/ቤቱም የግራ ቀኙን ክርክርና ማስረጃ ከመረመረ በኋላ አመልካች በወንጀል ሕግ አንቀጽ 543(2) የተመለከተውን በመተላለፍ በከባድ ቸልተኝነት የሰው መግደል ወንጀል የፈፀመ ነው በማለት ውሳ ሰጥቷል።
የቅጣት ውሳኔውን በተመለከተ አመልካች በህፃኗ ወላጆች ብር 35,000 (ሰላሳ አምስት ሺ ብር) ካሳ የከፈለ መሆኑን፣ የዘወትር ፀባዩ መልካም የነበረ መሆኑንና በዐቃቤ ህግ በኩል የቀረበ የቅጣት ማክበጃ ምክንያት የልለ መሆኑን በመዘርዝር አመለካች በአንድ ዓመት ከስድስት ወር ቀላል እስራትና በብር 1500 (አንድ ሺ አምስት መቶ ብር) እንዲቀጣ ውሳኔ ሰጥቷል። አመልካች የዞኑ ከፍተኛ ፍ/ቤት በሰጠው ፍርድ ቅር በመሰኘት ይግባኝ ለክልሉ ጠቅላይ ፍ/ቤት ይግባኝ ሰሚ ችሎት አቅርቧል። ይግባኝ ሰሚው ችሎት የግራ ቀኙን ክርክር ከሰማ በኋላ የስር ፍ/ቤት የሰጠውን የጥፋተኝነት ውሳኔ አጽንቶታል። ይግባኝ ሰሚው ፍ/ቤት የቅጣት ውሳኔውን በማሻሻል አመልካች በስምንት ወር እስራትና በብር 700(ሰባት መቶ ብር) እንዲቀጣ ወስኗል። እንዲሁም ይግባኝ ሰሚው ችሎት የቅጣት ውሳኔው ሳይፈፀም አመልካች ለሁለት ዓመት የፈተና ጊዜ መስጠት ተገቢ ሆኖ ያገኘው መሆኑን በመግለፅ፣ የቅጣት ውሳኔው ለሁለት ዓመት ተገድቦ እንዲቆይ ውሳኔ ሰጥቷል።
ተጠሪ ይህ ውሳኔ መሰረታዊ የሕግ ስህተት አለበት በማለት የሰበር አቤቱታ ለክልሉ ጠቅላይ ፍ/ቤት የሰበር ችት አቅርቧል። የክልሉ ጠቅላይ ፍ/ቤት የሰበር ችሎት የግራ ቀኙን ክርክር ከሰማ በኋላ የክልሉ ጠቅላይ ፍ/ቤት ይግባኝ ሰሚ ችሎት የእስራትና የገንዘብ ቅጣቱን የወሰነው የፍድራል ጠቅላይ ፍ/ቤት ያወጣውን የቅጣት መመሪያ ቁጥር 1/2000 ሳይከተል ነው በማለት ይግባኝ ሰሚው ችሎት የሰጠውን የቅጣት ውሳኔ በመሻር የዞኑ ከፍተኛ ፍ/ቤት የሰጠውን የቅጣት ውኔሳ አፅንቶታል።
የእስራት ቅጣት አፈፃፀሙንም በተመለከተ ክልሉ ጠቅላይ ፍ/ቤት ይግባኝ ሰሚ ችሎት የእስራት ቅጣቱ አፈፃፀም ለሁለት ዓመት የሙከራ ጊዜ ታግዶ እንዲቆይ የሰጠውን ትዕዛዝ በመሻር አመልካች የተወሰነበትን የአንድ ዓመት ከስድስት ወር የእስራት ቅጣት ይፈፅም በማለት ትዕዛዝ ሰጥቷል።
አመልካች የክልሉ ጠቅላይ ፍ/ቤት ሰበር ችሎት ይግባኝ ሰሚው ችሎት የሰጠውን የቅጣት ውሳኜ የሻረው ያለበቂ ምክንያትና ሕጋዊ መሰረት ነው። ተጠሪ የቅጣት ውሳኜው አፈፃፀም መገደብ የለበትም በማለት የሰበር አቤቱታ ያቀረበው ቅጣቱ የእስራት ቅጣትና መቀጮ በጣምራ የያዘ መሆኑን ገልፆ ነው። የክልሉ ጠቅላይ ፍ/ቤት የሰበር ችሎት ቅጣቱ በሁለት ዓመት የሙከራ ጊዜ ያመይገደብበትን ምክንያት በውሳኔው ሳገልፅና ሳይዘረዝር ይግባኝ ሰሚው ችሎት የቅጣት ውሳኔው እንዲገደብ የሰጠውን ውሳኔ መሻሩ መሰረታዊ የሕግ ስህተት ያለበት ስለሆነ በሰበር ታይቶ እንዲታረምልኝ በማለት ታህሳስ 15 ቀን 2005 ዓ.ም የተፃፈ የሰበር አቤቱታ አቅርቧል።
ተጠሪ ጥር 2 ቀን 2005 ዓ.ም በተፃፈ መልስ ይግባኝ ሰሚው ችሎት የሰጠው የቅጣት ውሳኔ የወንጀል ህጉንና የቅጣት አወሳሰን መመሪያውን መሰረት ያደረገ አይደለም። ስለዚህ የክልሉ ጠቅላይ ፍ/ቤት የሰበር ችሎት ይግባኝ ሰሚው ችሎት የሰጠውን የቅጣት ውሳኔ በመሻር የዞኑ ከፍተኛ ፍ/ቤት የሰጠውን የቅጣት ውሳኔ ማፅናቱ ተገቢ ነው። አመልካች ምንም አይነት ሙያዊ ጥንቃቄ ባለማድረጉና በፍጥነት በማሽከርከር ህፃኗን ገጭቶ የሞት አደጋ አድርሷል። ይህ የአመልካች አድርጎት የቅጣት ውሳኔውን ለመገደብ የሚያስችል ባለመሆኑ ይግባኝ ሰሚው ችሎት የቅጣት ውሳኔው እንዲገደብ የሰጠውን ውሳኔ የክልሉ ጠቅላይ ፍ/ቤት የሰበር እሎት መሻሩ መሰረታዊ የሕግ ስህተት የለበትም በማለት ተከራክሯል። አመልካች ጥር 24 ቀን 2005 ዓ.ም የተፃፈ የመልስ መልስ አቅርቧል።
ከስር የክርክሩ አመጣጥና በሰበር ያደረጉት የፅሁፍ ክርክር ከላይ የተገለፀው ሲሆን እኛም የክልሉ ጠቅላይ ፍ/ቤት ሰበር ችሎት ይግባኝ ሰሚ ችሎቱ የእስራት ቅጣት አፈፃፀሙ በሁለት ዓመት የሙከራ ጊዜ ተገድቦ እንዲቆይ የሰጠውን ውሳኔ መሻሩ ሕጋዊ ነው ወይስ አይደለም? የሚለውን ጭብጥ በመያዝ ጉዳዩን መርምረናል።
ጉዳዩን እንደመረመርነው የዞኑ ከፍተኛ ፍ/ቤት የወንጀል ህጉን መሰረታዊ ድንጋጌዎችና የፍድራል ጠቅላይ ፍ/ቤት የቅጣት አወሳሰን መመሪያ አንቀጽ 16 መሰረት በማድረግ የአንድ ዓመት ከስድስት ወር እስራትና ብር 1500(አንድ ሺ አምስት መቶ ብር) መቀጮ ወስኗል። ይግባኝ ሰሚው ችሎት የስር ፍ/ቤት የሰጠውን የቅት ውሳኔ የሻረው የቅጣት አወሳሰን መመሪያውን በተዛባ መንገድ በመተርጎም መሆኑን ከውሳኜ ይዘት ተረድተናል። ስለሆነም የክልሉ ጠቅላይ ፍ/ቤት ሰበር ችሎት ይግባኝ ሰሚው ችሎት የሰጠውን የቅጣት ውሳኔ በመሻር፣ የዞኑ ከፍተኛ ፍ/ቤት የሰጠውን የቅጣት ውሳኔ ማፅናቱ ምንም አይነት የሕግ ስህተት የልለበት በመሆኑ በዚህ ሰበር ችሎት እንዲታይ በጭብጥነት የተያዘ አይደለም። ከዚህ አንፃር የክልሉ ጠቅላይ ፍ/ቤት የሰበር ችሎት አመልካች በአንድ ዓመት ከስድስት ወር የእስራት ቅጣትና በብር 1500 (አንድ ሺ አምስት መቶ ብር) መቀጮ እንዲቀጣ የሰጠው ውሳኔ የህግ ስህተት የልለበት ነው።
በዚህ ሰበር ችሎት አከራከሪ የሆነው ጭብጥ በአመልካች ላይ የተሰጠው የእስራት ቅጣት ውሳኔ አፈፃፀም ለሁለት አመት የሙከራ ጊዜ ላገደብ ይገባዋል ወይስ አይደለም የሚለው ነው። ይግባን ሰሚው ችሎት በአመልካች ላይ የተወሰነው የእስራት ቅጣት አፈፃፀም ለሁለት ዓመት የሙከራ ጊዜ እንዲገደብ ውሳኔ የሰጠው የቅጣት ውሳኔው መገደቡ በወንጀል ህጉ አንቀጽ 192 የተመለከተውን መሰረታዊ ዓላማ የሚያሳካ ነው በማለት እንደሆነ ከውሳኔው ተረድተናል።
የክልሉ ጠቅላይ ፍ/ቤትም የሰበር ችሎት ይግባኝ ሰሚው ችሎት የእስራት ቅጣቱ አፈፃፀም እንዲገደብ የሰጠውን ውሳኔ የሻረው አመልካች ከባድ በሆነ ቸልተኝነት የግል ተበዳይን በመግጨት የሞት አደጋ አስከትሎባታል በማለት ነው። ሆኖም የክልሉ ጠቅላይ ፍ/ቤት የሰበር ችሎት አመልካች የወንጀል ህጉን አንቀጽ 543 ንዑስ አንቀጽ 2 በመተላለፍ በከባድ ቸልተኝነት የሰው መግደል ወንጀል የፈፀመ ጥፋተኛ ሆኖ መገኘቱን በመመልከት ብቻ የቅጣት ውሳኔው አፈፃፀም ለመገደብ የተሰጠውን ውሳኔ ሽሮታል። ሆኖም በተከሳሽ ላይ የተወሰነ የቅጣት ውሳኔ ከመገደቡ ወይም የገደብ ውሳኔው ከመሻሩ በፊት የቅጣት ገደብ ስለሚከለከልበትና ስለሚሻርበት ሁኔታ በወንጀል ሕጉ አንቀጽ 194 የተደነገጉትን ድንጋጌዎች ይዘትና አላማ ማገናዘብ አስፈላጊ ነው።
በወንጀል ጥፋተኛ ሆኖ የተገኘ ተከሳሽ የቅጣት አፈፃፀም እንዲገደብ ፍ/ቤቶች ትዕዛዝ መስጠት የማይችሉባቸው ሁኔታዎች በወንጀል ሕጉ አንቀጽ 194 በዝርዝር ተመልክተዋል። የክልሉ ጠቅላይ ፍ/ቤት የሰበር ችሎት በወንጀል ህጉ አንቀጽ 194 ንዑስ አንቀጽ 1 እና ንዑስ አንቀጽ 2 ከተዘረዘሩት ምክንያቶች፣ አንደኛውን ሁኔታ አመልካች የሚያሟላ ስለመሆኑ በውሳኔው አልገለፀም። ይህም በአመልካች ላይ የተወሰነውን የቅጣት ውሳኔው አፈፃፀም እንዳይገደብ በወንጀል ሕጉ አንቀጽ 194 የተዘረዘሩት የመከላከያ ምክንያቶች በልሉበት ሁኔታ የክልሉ ጠቅላይ ፍ/ቤት አመልካች በወኝጀል ሕጉ አንቀጽ 543 ንዑስ አንቀጽ 2 ጥፋተኛ ሆኖ መገኘቱን በመመልከት ይግባኝ ሰሚው ችሎት የቅጣት ውሳኔው እንዲገደብ የሰጠውን ውሳኔ መሻሩ፣ የወንጀል ህጉ አንቀጽ 194 ድንጋጌዎች ይዘትና መሰረታዊ ዓላማ መሰረት ያላደረገ ነው።
ከላይ ከተገለፀው በተጨማሪ አመልካች የተወሰነበት የእስራት ቅጣት ከሚፈፀም ይልቅ የቅጣት ውሳኔው ታግዶለት አመሉ ቢፈተን በወንጀል ህጉ አንቀጽ 190 በተደነገገው መሰረት የአመልካችን ጠባይ ለማረምና ለማሻሻልና አመልካችን ወደመደበኛ ማህበራዊ ኑሮው ለመመለስ የሚያስችል መሆኑ ስለ አመልካች ባሀሪ ማህራዊና አቋም፣ የትምህርት ደረጃና የወንጀለኛነት ባህሪና ፀባይ ማጣራትና ማስረጃ የመመዘን ስልጣን ባለው በይግባኝ ሰሚው ችሎት የታመነበትና ውሳኔ የተሰጠበት ነው። የክልሉ ጠቅላይ ፍ/ቤት የሰበር ችሎት በኢ.ፍ.ዲ.ሪ ሕገ መንግስት አንቀጽ 80 ንዑስ አንቀጽ 3(ለ) ከተሰጠው የሰበር ሥልጣን በመውጣት ስለአመልካች ጠባይ አመልካች ከጥፋቱ ላታረምና ላሻሻል ስለሚችልበት ሁኔታ ያሉትን ፍሬ ጉዳዮች በማጣራትና ማስረጃ በመመዘን ይግባኝ ሰሚው ችሎት በወንጀል ሕግ አንቀጽ 190 እና 192 መሰረት ቅጣቱ እንዲገደብ የሰጠውን ወሳኔ መሻሩ የሕግ መሰረት ያለው ሆኖ አላገኘነውም። በዚህ ረገድ የክልሉ ጠቅላይ ፍ/ቤት ሰበር ችሎት የሰጠው ውሳኔና የሕግ ትርጉም ይህ ሰበር ችሎት በሰበር መዝገብ እና በልሎች መዝገቦች የሰጠውን አስገዳጅ የሕግ ትርጉም ያልተከተለና የአዋጅ ቁጥር 454/97 አንቀጽ 2(1) አስገዳጅ የሕግ ድንጋጌ የሚጥስ ሆኖ አግኝተነዋል።
ከላይ በዝርዝር በገለፅናቸው ምክንያቶች የክልሉ ጠቅላይ ፍ/ቤት የሰበር ችሎት ይግባኝ ሰሚው ችሎት በአመልካች ላይ የተወሰነው የእስራት ቅጣት በሁለት ዓመት ሙከራ ጊዜ እንዲገደብ የሰጠውን ውሳኔ መሻሩ መሰራታዊ የሕግ ስህተት ያለበት ነው በማለት ውሳኔ ሰጥተናል።
የክልሉ ጠቅላይ ፍ/ቤት የሰበር ችሎት በአመልካች ላይ የተወሰነው የቅጣት ውሳኔ ላገደብ አይገባም፣ አመልካች የእስራት ውሳኔውን ይፈፀም በማለት የሰጠው የውሳኔ ክፍል ብቻ ተሽሯል።
በክልሉ ጠቅላይ ፍ/ቤት የሰበር ችሎትና የዞኑ ከፍተኛ ፍ/ቤት በአመልካች ላይ የወሰኑት የአንድ ዓመት ከስድስት ወር የእስራት ቅጣት በሁለት ዓመት የሙከራ ጊዜ ተገድቦ እንዲቆይ በወንጀል ሕጉ አንቀጽ 190 እና አንቀጽ 192 መሰረት ወስነናል። በዚህ በኩል የእስራት ቅጣት ውሳኔው አፈፃፀም እንዲገደብ የክልሉ ጠቅላይ ፍ/ቤት ይግባኝ ሰሚ ችሎት የሰጠው ውሳኔ የወንጀል ህጉን አንቀጽ 190፣ አንቀጽ 192 እና አንቀጽ 194 መሰረት ያደረገ የሕግ ስህተት ያልተፈፀመበት በማለት ወስነናል።
በአመልካች ላይ የተወሰነው የእስራት ቅጣት አፈፃፀም ለሁለት ዓመት የሙከራ ጊዜ የተገደበ መሆኑን እንዲያውቁት ለኦሮሚያ ክልል ፖላስ ኮሚሽንና ፍትህ ቢሮ ይፃፍ።
መዝገቡ ወደ መዝገብ ቤት ይመለስ።
No topics extracted.