No summary available.
ሚያዝያ 7 ቀን 2005 ዓ.ም.
ዳኞች:- ተገኔ ጌታነህ አልማው ወል ዓላ መሐመድ ረታ ቶሎሳ አዳነ ንጉሤ አመልካቾች፡- አቶ ታሪኩ ጫኔ - የቀረበ የለም ተጠሪ፡- የፍድራል ስነ ምግባርና ፀረ ሙስና ኮሚሽን አቃቤ ሕግ - የቀረበ የለም **
መዝገቡ ተመርምሮ ተከታዩ ፍርድ ተሰጥቷል።
**
ጉዳዩ አንድ ሰው በፍ/ብሕር ጉዳይ ተከስሶ ኃላፊነት የለበትም ተብሎ የመጨረሻ ፍርድ ከተሰጠ በጉዳዩ ላይ በወንጀል የሚጠይቅበት ሕጋዊ አግባብ መኖር ያለመኖሩን የሚመለከት ነው። አመልካች ላይ ተጠሪ ክስ ያቀረበው በኢ.ፍ.ዲ.ሪ የወንጀል ሕግ አንቀጽ 32(1ሀ(ለ)) እና 413(ሀ) እና (ለ)) ስር የተመለከተውን በመተላለፍ ነሐሴ 20 ቀን 2001 ዓ/ም በኢትዮጵያ ጨረር መከላከያ ባለስልጣን የአካባቢና ምግብ ጨረር መጠን ክትትል ባለሙያ ሆነው በሚሰሩበት ጊዜ የማይገባ ቁሳዊ ጥቅም ለማግኘት እና በመንግስት ሀብት ላይ ጉዳት ለማድረስ በማሰብ ከመስሪያ ቤቱ ፈርመው የተረከቡትን የቀረጥና የማጋጋዣ ዋጋ ሳይጨምር ግምቱ ብር 76.867.34 የሆነን ዩኒቨርሳል ሰርቬየር ሜትር ሞድል አር፣ጂ፣ኤስ የሆነ የጨረር መጠን መከላከያ መሳሪያ (Universal servey meter) RGS- 200 እና የርቀት መቆጣጠሪያ ያለው በባትሪ የሚሰራ ባለ ብዙ ዘርፍ አገልግሎት ዲጂታል የራጂ ማሽነሪ፣ የጥፋት መቆጣጠሪያ ኪት (digital diagnostic quality control)(RAD-Check plus model p6 526 multifunction meter with remot control model Rmt 240 A and collimation test too) የተሰኙ መሳሪያዎችን አመልካቹ በአዳማ ከተማ የአዳማ ሆስፒታል የራጅ መሳሪያዎችን ፍተሻ እንዲያከናውን ታዞ በተጠቀሰው ቀን በስር ሁለተኛ ተከሳሽ ከነበረውና ከመስሪያ ቤቱ ሹፍር በሆነው በአቶ አረጋዊ ታደገ በሚሽከረከር መኪና በመጫን ወደ ናዝሬት ከወሰዱ በኋላ በተጠቀሰው ሆስፒታል ተገኝተው የምርመራ ስራቸውን ማከናወናቸውን ተከትሎ እንዚህን መሳሪያዎች ለመስሪያ ቤቱ ማስረከብ ሲገባቸው ያለአግባብ ለመበልጸግ ንብረቶችን ባለመመለሳቸውና በመሰወራቸው የመውሰድና የመሰወር የሙስና ወንጀል ፈፅመዋል በሚል ነው።
አመልካች ክደው ተከራክረው አቃቤ ሕግ አሉኝ ያላቸውን ማስረጃዎችን ያሰማ ሲሆን አመልካችም የመከላከያ ማስረጃዎቻቸውን አሰምተዋል። ጉዳዩን በመጀመሪያ ደረጃ የተመለከተው ፍ/ቤትም አመልካች የወንጀል ድርጊቱን መፈፀማቸውን ያለመከላከላቸው ተረጋግጧል በሚል ምክንያት በክሱ ተጠቅሶ በቀረበው ድንጋጌ ጥፋተኛ አድርጎ በስድስት ወር ጽኑ እስራትና በአንድ ሺህ ብር እንዲቀጡ ወስኖባቸዋል። አመልካች ይግባኛቸውን ለፍድራሉ ጠቅላይ ፍ/ቤት አቅርበውም ተቀባይነት አላገኘም። የአሁኑ የሰበር አቤቱታ የቀረበውም ይህንኑ ውሳኔ በመቃወም ለማስለወጥ ነው። የአመልካች የሰበር አቤቱታ መሰረታዊ ይዘትም አመልካች በንብረቱ ላይ የፍ/ብሕር ክስ ቀርቦባቸው ሃላፊነት የለባቸውም ተብሎ መጨረሻና አስገዳጅ የህግ ትርጉም ለመስጠት ስልጣን ባለው የፍድራል ጠቅላይ ፍ/ቤት ሰሚ ችሎት ውሳኔ በተሰጠበት ሁኔታ ጥብቅ የሆነ ማስረጃ ምዘና በሚጠይቀው የወንጀል ጉዳይ ላይ ጥፋተኛ መባላቸው በወንጀል ጉዳይ የማስረጃ ምዘና መርህን ያላገናዘበ መሆኑን ጠቅሰው መከራከራቸውን የሚያሳይ ነው። አቤቱታው ተመርምሮም በሰበር ችሎቱ ላታይ የሚገባው መሆኑ ታምኖበት ለተጠሪ ጥሪ ተደርጎለት ቀርቦ ግራ ቀኙ በጽሁፍ እንዲከራከሩ ተደርጓል።
የጉዳዩ አመጣጥ አጠር አጠር ባለመልኩ ከላይ የተገለፀው ሲሆን ይህ ችሎትም የግራ ቀኙን ክርክር ለሰበር አቤቱታው መነሻ ከሆነው ውሳኔ እና አግባብነት ካላቸው ድንጋጌዎች ጋር በማገናዘብ በሚከተለው መልኩ መርምሮታል። እንደመረመረውም ጉዳዩ ለሰበር ሰሚ ችሎት ላቀርብ የቻለው አመልካች በፍ/ብሄር ጉዳይ ተጠያቂነት የለባቸውም ተብሎ ተወስኖ እያለ በወንጀል ተጠያቂነት አለባቸው ተብሎ በእስር እንዲቀጡ መወሰኑ ተገቢ መሆን ያለመሆኑን ለመመርመር ሲባል ነው።
አመልካች በንብረቶቹ መሰወርና መውሰድ በፍትሐ ብሕር ተከሰው ተጠያቂነት የለባቸውም ተብሎ በሰ/መ/ የተወሰነ መሆኑን፣ በፍትሐ ብሕር ጉዳይ የተሰሙት ማስረጃዎች በወንጀል ጉዳዩም የተሰሙ መሆኑ ግራ ቀኙን ያላከራከሩ ነጥቦች ሲሆን አከራካሪው የሕግ ጥያቄ በፍትሐ ብሕር ጉዳይ ነፃ የተባለ ሰው በወንጀል ጥፋተኛ ተብሎ የሚጠይቅበት ሕጋዊ አግባብ አለ? ወይም የለም? የሚለው ነው። ተጠሪ የወንጀል ችሎት በፍትሓ ብሕር ችሎት ውሳኔ ላገደድ የሚችልበት ሕጋዊ አግባብ የለም በማለት የሚከራከር ሲሆን አመልካች በበኩላቸው በወንጀል ጉዳይ የማስረጃ ምዘና መርሁ በፍትሐ ብሕር ጉዳይ የማስረጃ ምዘና መርህ የጠበቀ በመሆኑ በፍትሓ ብሕር ጉዳይ ነፃ የተባለ ሰው በተመሳሳይ ጉዳይና ማስረጃ በወንጀል ተጠያቂ የሚሆንበት ሕጋዊ አካሄድ የለም በሚል የሚከራከሩ መሆኑን ተረድተናል።
በመሰረቱ በወንጀል ጉዳይ የተሰጠ ውሣኔ በዚያው ጉዳይ በፍትሐብሕር በማስረጃነት አግባብነት እና ብቃት የሚኖረው ስለመሆኑ የፍ/ብ/ሕ/ቁ 2149 ድንጋጌ ተቃራኒ ንባብ ያስገነዝበናል። በዚህ ድንጋጌ መሰረት በወንጀል የተሰጠ ውሣኔ በፍትሐብሕር ለቀረበው ክስ በማስረጃነት አግባብነት የሚኖረው በወንጀል ክሱ በወንጀል ፍ/ቤት ተከሣሹ ጥፋተኛ ተብሎ ከተወሰነ ስለመሆኑ እና ለዚህም የሚሰጠው ምክንያት የወንጀል ክስ ማስረጃ አመዛዘን መርህ ከፍትሐብሕር የበለጠ ጠንካራና የማያሻማ ማስረጃ የሚጠይቅ መሆኑ ነው። ወደዚህ ድምዳሜ ለመድረስም በወንጀሉ ጉዳይ የተሰሙት ማስረጃዎችም በፍትሐብሕሩ ጉዳይም የቀረቡና የተሰሙ ላሆኑ ይገባል። በወንጀሉና በፍትሐብሕር ጉዳይ የተሰሙት ማስረጃዎች የተለያዩ ከሆነ እና በወንጀል ጉዳይ ክስ የቀረበበት ነጥብም ከፍትሐብሕሩ ክስ ጋር ግንኙነት የልለው ከሆነ በወንጀል ክስ ተጠያቂ መሆን ሁል ጊዜ በፍትሐብሕሩ ክስ ኃላፊነትን የማያስከትል ስለመሆኑ የፍ/ብ/ሕ/ቁጥር 2149 ድንጋጌ ይዘት፣ መንፈስና አላማ ያስገነዝበናል። ይህ ስለመሆኑም ይህ ሰበር ሰሚ ችሎት በሰ/መ/ እና በልሎች በርካታ መዛግብት በአዋጅ ቁጥር 454/1997 አንቀጽ 2(1) መሰረት በየትኛውም እርከን የሚገኝ ፍ/ቤትን የሚያስገድድ የሕግ ትርጉም ሰጥቶበታል።
በመሆኑም የፍ/ብ/ሕ/ቁጥር 2149 ድንጋጌ አጠቃላይ ይዘትና መንፈስ የሚያስገነዝበን በወንጀል ጉዳይ የቀረበ ማስረጃ ክብደት ያለው መሆኑ ከተረጋገጠ ለፍትሐብሕሩ ክርክር ብቃት ያለው ማስረጃ መሆኑና በፍትሐብሕር ክብደት ላሰጠው አይገባም የተባለ ማስረጃ ለወንጀሉ ክስ ሲቀርብ ክብደት የሚሰጥበት አግባብ የልለ መሆኑን ነው።
ወደተያዘው ጉዳይ ስንመለስም አመልካች በጉዳዩ በፍትሐብሕር ክስ ቀርቦባቸው ኃላፊነትን የሚያስከትል ድርጊት አልፈጸሙም ንብረቶቹን በጥንቃቄ አስቀምጠው እያለ ከራሳቸው ቁጥጥር ውጭ በሆነና በልላ ሰው በተፈፀመ የስርቆት ተግባር ንብረቶቹ መጥፋታቸው ተረጋግጧል በማለት በሰ/መ/ በሆነው አስገዳጅና የመጨረሻ ፍርድ ተሰጥቶ ባለበት ሁኔታ አመልካች በጉዳዩ በሙስና ወንጀል ተከሰው በፍትሐብሕር የቀረቡት ተመሳሳይ ማስረጃዎች በቀረበበትና በተሰሙበት እንዲሁም ተመሳሳይ ፍሬ ነገር በተረጋገጠበት ሁኔታ ጥብቅ የሆነ የማስረጃ ምዘና በሚጠይቀው የወንጀል ጉዳይ አመልካች የወንጀል ድርጊት ፈፅመዋል፣ አድራጎቱም ተገቢ ያልሆነ ጥቅም ለማግኘትና በመንግስት ንብረት ላይ ጉዳት ለማድረስ በማሰብ የተፈፀመ ነው ተብሎ ድምዳሜ መያዙ መሰረታዊ የሆነ የወንጀል ማስረጃ ምዘና መርህን ባልተከተለ ሁኔታ የተሰጠ ውሳኔ በመሆኑ አግባብ ሆኖ አላገኘነውም። ሲጠቃለልም ለክርክሩ መነሻ የሆነው ድርጊት አመልካች በፍትሐብሕር ተከሰው ነጻ ከተባሉበት ድርጊት ጋር ሙሉ በሙሉ ተመሳሳይነት ያለው በመሆኑ በጉዳዩ ላይ የተሰጠው የጥፋተኝነት ውሳኔ የወ/መ/ህ/ሥ/ሥ/ሕ/ቁጥር 141 ድንጋጌ ይዘትና መንፈስ ከፍ/ብ/ሕ/ቁጥር 2149 ድንጋጌ ተቃራኒ ንባብ ጋር የሚጣረስና መሰረታዊ የሆነ የሕግ ስህተት ያለበት ሁኖ ስለአገኘነው ተከታዩን ወስነናል።
በፍደራሉ ከፍተኛ ፍርድ ቤት በመ/ ነሐሴ 20 እና 23 ቀን 2003 ዓ.ም ተሰጥቶ በፍደራሉ ጠቅላይ ፍርድ ቤት ይግባኝ ሰሚ ችሎት በመ/ ጥር 02 ቀን 2004 ዓ.ም የፀናው የጥፋተኝነትና የቅጣት ውሳኔ በወ/መ/ሕ/ሥ/ሥ/ቁጥር 195(2(ሐ) መሰረት ሙሉ በሙሉ ተሽሯል ።
አመልካች የወንጀል ድርጊት ስለመፈጸማቸው በወ/መ/ሕ/ሥሥ/ቁጥር 141 ድንጋጌ ይዘትና መንፈስ አልተረጋገጠባቸውም ብለናል።
መዝገቡ ተዘግቷል ወደ መዝገብ ቤት ይመለስ
No topics extracted.