No summary available.
ህዳር 06 ቀን 2006 ዓ.ም.
ዳኞች፡- አልማው ወል ዓላ መሐመድ ረታ ቶሎሳ አዳነ ንጉሴ ሙስጠፋ አህመድ አመልካች፡- ዓባይ ኢንሹራንስ አ.ማ ተጠሪዎች፡- አቶ አለማየሁ አሰፋ **
መዝገቡ ተመርምሮ ተከታዩ ፍርድ ተሰጥቷል።
**
ጉዳዩ በፍድራል መንግስት የተመዘገበ የልማት ድርጅት በክልል ወረዳ ፍርድ ቤት በተጀመረ ክስ የጣልቃ ገብ ተከራካሪ ሲሆን ጉዳዩን የወረዳው ፍርድ ቤት ለማየት የሚችል መሆን ያለመሆኑን የሚመለከት ነው።ክርክሩ የተጀመረው የአሁኑ ተጠሪ በአቶ ኃይለጊዩርጊስ አበጀ ላይ በውጫል ወረዳ ፍርድ ቤት በመሰረቱት ክስ መነሻ ነው።አመልካች በስር ፍርድ ቤት ጣልቃ ገብ ሁኖ ተከራክሯል።የተጠሪ ክስ ይዘትም፡- ንብረትነቱ የስር ተከሳሽ የአቶ ኃይለጊዩርጊስ አበጀ የሆነ የሰልዳ ቁጥር 3-22157 ተሸከርካሪ መኪናቸውን ነሐሴ 11 ቀን 2003 ዓ/ም በመግጨት ጉዳት አድርሶባቸው ለጥገናው ብር 13,970.00 (አስራ ሶስት ሺህ ዘጠኝ መቶ ሰባት ብር) ማውጣታቸውንና በጉዳቱ ምክንያት ደግሞ ብር 15,000.00 ገቢ የተቋረጠባቸው መሆኑን በመጥቀስ በድምሩ ብር 28,970.00 (ሃያ ስምንት ሺኅ ዘጠኝ መቶ ሰባ ብር) እንዲከፍሉ ይወሰንላቸው ዘንድ ዳኝነት መጠየቃቸውን የሚያሳይ ነው።የአሁኑ አመልካች በስር ፍርድ ቤት በተሰጠው ትዕዛዝ መነሻ ወደ ክርክሩ ጣልቃ ገብቶ እንዲከራከር የተደረገ ሲሆን ለክሱ በሰጠው መልስም ግጭቱን አደረሰ የተባለው የደንበኛው መኪና ለጉዳቱ ኃላፊ ስለመሆኑ በትራፊክ ማስረጃ ያለመረጋገጡን፣ለተቋረጠ ጥቅም ደግሞ ለደንበኛው የሰጠው ሽፋን የልለና በመድን ውሉ የተገለለ ጉዳይ በመሆኑ ኃላፊነት እንደልለው ገልጾ ተከራክሯል።የስር ፍርድ ቤትም በጉዳዩ ላይ ተገቢ ነው ያለውን ውሳኔ ከሰጠ በኋላ የዞኑ ከፍተኛ ፍርድ ቤት ጉዳዩን ተመለክቶ የሥር ፍርድ ቤትን ውሳኔ በመሻሩና የክልሉ ጠቅላይ ፍርድ ቤት ደግሞ የዞኑ ከፍተኛ ፍርድ ቤትን ውሳኔ በመሻር ኃላፊነቱ ተጣርቶ እንዲወሰን ለወረዳው ፍርድ ቤት ጉዳዩን መልሶለት ጉዳዩ የተመለሰለት የወረዳው ፍርድ ቤትም ጉዳዩን አጣርቶ ኃላፊነቱን የአመልካች ደንበኛ ነው በማለት የደመደመ ሲሆን የካሳ መጠኑን በተመለከተም ብር 26,230.43 (ሃያ ስድሰት ሺኅ ሁለት መቶ ሰላሳ ብር ከአርባ ሶሰት ሳንቲም) መሆኑን ገልጾ ይኼው ገንዘብ ለተጠሪ እንዲከፈል፣አመልካች የውል ግድታው ከዚህ በታች ከሆነ ተከሳሽ ይክፈሉ በማለት ወስኗል።በዚህ ውሳኔ የአሁኑ አመልካች ቅር በመሰኘት ይግባኙን ለሰሜን ሸዋ ዞን ከፍተኛ ፍርድ ቤት ቢያቀርብም ተቀባይነት አላገኘም።የአሁኑ የሰበር አቤቱታ የቀረበውም ይህንኑ ውሳኔ በመቃወም ለማስለወጥ ነው።የአመልካች የሰበር አቤቱታ መሰረታዊ ይዘትም ጉዳዩ በወረዳው ፍርድ ቤት የታዬው ያልስልጣኑ መሆኑንና የተቋረጠ ገቢ አመልካቸ የሚከፍልበት የሕግ አግባብም የልለ መሆኑን ጠቅሶ መከራከሩን የሚያሳይ ነው።የሰበር አቤቱታው ተመርምሮም በዚህ ሰበር ሰሚ ችሎት እንዲታይ የተደረገ ሲሆን ለተጠሪ ጥሪ ተደርጎላቸው ቀርበው ግራ ቀኙ በፅሑፍ እንዲከራከሩ ተደርጓል።
የጉዳዩ አመጣጥ አጠር ባለመልኩ ከላይ የተገለፀው ሲሆን ችሎቱም የግራ ቀኙን ክርክር ለሰበር አቤቱታው መነሻ ከሆነው ውሳኔ እና አግባብነት ካላቸው ድንጋጌዎች ጋር በማገናዘብ ጉዳዩን በሚከተለው መልኩ መርምሮታል።እንደመረመራም የዚህን ችሎት ምላሽ የሚያስፈልገው አቢይ ነጥብ ሁኖ የተገኘው ጉዳዩን በመጀመሪያ ደረጃ ተቀብሎ ውሳኔ የሰጠው የውጫል ወረዳ ፍ/ቤት ጉዳዩን የማየት የስረ ነገር ስልጣን ነበረው?
ወይስ አልነበረውም? የሚለው ሁኖ አግኝቶታል።
በዚህም መሰረት ከሳሽ ክሱን ያቀረበው በመኪናቸው ላይ ለደረሰበት ጉዳት ያወጡት ወጪ እንዲተካላቸውና የተቋረጠ ጥቅም እንዲከፈላቸው ሲሆን የክርክሩ የገንዘብ መጠንም በድምሩ ብር 28,970 (ሃያ ስንምት ሺህ ዘጠኝ መቶ ሰባ ብር) ነው።በኦሮሚያ ብ/ክ/መ/ፍርድ ቤቶችን ለማቋቋም የወጣውን አዋጅ እንደገና ለማሻሻል በወጣው አዋጅ ቁጥር 141/200 በአንቀጽ 28(1)(ለ)) እና በፍ.ስ.ስ.ሕ.ቁ. 226(1) መሰረት የከሳሽ የዳኝነት ጥያቄ የሚወድቀው በወረዳው ፍ/ቤት የስረ ነገር የዳኝነት ስልጣን ስር መሆኑ ግልፅ ነው።አመልካች ጣልቃ ገብ ሁኖ የተከራከረ ሲሆን ጣልቃ ገብነት በፍትሓ ብሕር ስነ ስርዓት ሕጉ አግባብ የተፈቀደ አንዱ የክርከሩ ተሳታፊነት የሚገለፅበትና የራሱን የቻለ መሰረታዊ አላማ ያለው፣በስነ ስርዓት ሕጉ የተዘረጋ ስርዓት ነው።በ1958ቱ የፍትሃ ብሄር ስነ ስርዓት ሕግ ወደ ክርክሩ ላገባ የሚችልበት ስርዓት የተለያየ ቢሆንም ይህ ስርዓት አገሪቱ ከምትከተለው የፍድራል ስርዓትና በዚሁ ስርዓት ከተዘረጋው የፍርድ ቤቶች አደራጃጀት ጋር ተጣጥሞ በመታየት ስራ ላይ ላወል የሚገባው መሆኑ ይታመናል።በመሆኑም አንድን ጉዳይ የፍድራል ወይም የክልል ብሎ ለመየት ይቻል ዘንድ በአዋጅ ቁጥር 25/1988 የተቀመጠው መስፈርት ታይቶ የጉዳዩን የመዳኘት የስረ ነገር ስልጣንም ከዚሁ አንጻር መለየት ያለበት ጉዳይ ነው።ከዚህ አንጻር ጉዳዩን ስንመለከተው በአዋጅ ቄጥር 25/1988 አንቀጽ 5 ስር አንድን ጉዳይ የፍድራል ጉዳይ ለማለት የሚያችሉ ምክንያቶች ተገልጸዋል።የአሁኑ አመልካች በፍድራል መንግስት የተቋቋመና የተመዘገበ የልማት ድርጅት ሲሆን በፍድራል መንግስቱ አካላት የተመዘገቡ ወይም የተቋቋሙ የንግድ ድርጅቶችና ማህበሮችን በሚመለከት የሚነሱ ክርክሮችን የማየት የስረ ነገር ስልጣን የተሰጠው ለፍድራል ፍ/ቤቶች መሆኑ እና እስከ ብር 500,000 ግምት ያለው የገንዘብ ክርክር የማየት ስልጣን ደግሞ በፍድል የመጀመሪያ ደረጃ ፍርድ ቤት ስልጣን ስር የሚወድቅ መሆኑ በአዋጅ ቁጥር 25/88 በአንቀጽ 5(6) እና በአንቀጽ 14 ስር ከተመለከቱት ድንጋጌዎች ይዘትና መንፈስ የምንረዳው ጉዳይ ነው።በኢ.ፍ.ዲ.ሪ.ሕገ መንግስት በአንቀጽ 80 (4) እና በአሮሚያ ብሕራዊ ክልላዊ መንግስት መንግስት በአንቀጽ 64(4) በተመለከተው የስልጣን ውክልና መሰረት በፍድራል መጀመሪያ ደረጃ ፍርድ ቤት የስረ ነገር ስልጣን ስር የሚወድቁ በክልሉ የሚነሱ ጉዳዮችን የማየት ስልጣን የተሰጠው ለክልሉ ዞን ከፍተኛ ፍርድ ቤት ነው።ስለሆነም የወረዳው ፍርድ ቤት ጉዳዩን የማየት የስረ ነገር ስልጣን በሕገ መንግስቱ አልተሰጠውም።የሥረ ነገረ የስልጣን ጥያቄ በማናቸውም የክርክር ደረጃ የሚነሳና ፍርድ ቤቱም በራሱ አነሳሽነት ጭምር ማየት የሚችለው ጉዳይ ነው።በመሆኑም የውጫል የወረዳው ፍ/ቤት የአሁኑ አመልካች ወደ ክርክሩ መግባቱ ጉዳዩን ከስረ ነገር ስልጣኑ ውጪ የሚያደርገው መሆኑን ተገንዝቦ ክሱ ጣልቃ ገቡን ባካተተ ሁኔታ ስልጣን ላለው ፍ/ቤት ይቀርብ ዘንድ ጉዳዩን ዘግቶ ማሰናበት ሲገባው ክርክሩን ቀጥሎ በማየት ውሳኔ መስጠቱና ይግባኝ ሰሚው ፍ/ቤትም በዚህ ረገድ የተፈጸመውን ስህተት ሳያርም መቅረቱ በፍ/ብ/ሥ/ሥ/ሕ/ቁጥር 9 እና 231(1(ለ)) ድንጋጌዎች የተመለከቱትን ድንጋጌዎች ያላገናዘበ እና ይህ ሰበር ሰሚ ችሎት በመ/ በቀረበው ተመሳሳይ የሕግ ጥያቄ ከሰጠው አሰገዳጅ የሕግ ትርጉም ጋር የማይጣጣም ሁኖ ስለአገኘነው የበታች ፍ/ቤቶች ውሳኔ መሰረታዊ የሕግ ስህተት የተፈጸመበት መሆኑን የሚያመለክት ነው። በመሆኑም የሚከተለው ውሳኔ ተሰጥቶአል።
በውጫል ወረዳ ፍ/ቤት በመ.ቁ. 05563 በ23/04/2005 ዓ.ም. ተሰጥቶ በኦሮሚያ ብሕራዊ ክልላዊ መንግስት፣ሰሜን ሸዋ ዞን ከ/ፍ/ቤት በመ.ቁ. 36566 በ17/08/2005 ዓ.ም. በትዕዛዝ የፀናው ውሳኔ በፍ/ብ/ሥ/ሥ/ሕ/ቁጥር 348(1) መሰረት ተሽሯል።
የአሁኑ አመልካች በጣልቃ ገብነት ተከራካሪ የሆነበትን ጉዳይ ተቀብሎ ማየት በአዋጅ ቁጥር 25/88 በአንቀጽ 5(6) መሰረት በፍድራል ፍርድ ቤቶች የስረ ነገር ስልጣን ስር የሚወድቅ ነው በማለት ወስነናል።
የስር ከሳሽ ለውጫል ወረዳው ፍ/ቤት አቅርቦት የነበረውን ክስ የአሁኑን አመልካች ጭምር በተከሳሽነት በማካተት ስልጣኑ ለሆነው ለሰሜን ሸዋ ዞን ከ/ፍ/ቤት የማቅረብ መብቱ በዚህ ውሳኔ ቀሪ አልሆነም ብለናል።
በዚህ ችሎት ለተደረገው ክርክር የወጣውን ወጪና ኪሳራ የየራሳቸውን ይቻሉ ብለናል።
No topics extracted.