No summary available.
የሰ/መ/ ህዳር 16 ቀን 2006 ዓ.ም ዳኞች፡- አልማው ወል ዓላ መሐመድ ረታ ቶሎሳ አዳነ ንጉሤ ሙስጠፋ አህመድ አመልካች፡- የንጋት ኮከብ ሸማቾች ኃ/የተ የግል ማህበር ጠበቃ አቶ እሸቱ ጓንጉል ቀረቡ ተጠሪዎች፡-
ለዚህ የሰበር ክርክር መነሻ የሆነው ጉዳይ በአሁን የሰበር አመልካች ከሳሽነት የተጀመረው በፍድራል የመጀመሪያ ደረጃ ፍርድ ቤት ሲሆን ከተራ ቁጥረ 1-5 ያሉት ያሁን ተጠሪዎችም በመ/ቁ/40407 ተከሳሾች ነበሩ።
መ/ቁ/40406 በሆነው ደግሞ የአሁን አመልካች ከሳሽ ፣ ከተራ ቁጥር 1 እስከ 10 ያሉ ተጠሪዎች ደግሞ ተከሳሾች ነበሩ። በሆነው መዝገብ ከሳሽ በቀን 27/09/2004 ዓ/ም ያቀረበው ክስ፡- ከሳሽ ማህበር በህብረት ሥራ ማህበር አዋጅ ቁጥር 147/1991 የተቋቋመ ሲሆን ተከሳሾችም የማህበሩን የእለት ተዕለት ሥራ እንዲሰሩ በማህበሩ ጠቅላላ ጉባኤ ተመርጠው ከ20/07/2003- 27/11/2003 በማህበሩ የሥራ አመራር ኮሚቴ አባልነትና በዕቃ ግዥ ሲሰሩ ከከሳሽ የመተዳደሪያ ደንብ ውጪ ህገ ወጥ አሰራር በመከተል በሥልጣናቸው ያለአግባብ በመገልገል የማህበሩን ገንዘብ ብር 369,202.75 መውሰዳቸው በኦዲት የተረጋገጠ በመሆኑ ይህንኑ ገንዘብ ከ9% ወለድ ጋር በአንድነት እና በነጠላ እንዲከፍሉ ይወሰንልኝ የሚል ነው።
ከሳሽ መ/ቁ/40406 በሆነው ደግሞ በመ/ቁ/ 40407 የተጠቀሱትን ተከሳሾች ጨምሮ በድምሩ በ10 ተከሳሾች ላይ ግንቦት 27/1004 ያቀረበው ክስ ተመሳሳይ ሆኖ ተከሳሾቹ ከ01/07/2001-19/07/2003 ዓ/ም የከሳሽ ማህበር የሥራ አመራር ኮሚቴ ፣ የዕቃ ግዥ እና ቁጥጥር ኮሚቴ ሆነው ሲሰሩ ሥልጣናቸውን ያለአግባብ በመገልገል የማህበሩን ብር 176,587.31 ማጉደላቸው በኦዲት ሪፖርት ስለተረጋገጠ ይህንኑ ገንዘብ ከ9% ወለድ ጋር እንዲከፍሉ ይወሰንልኝ የሚል ነው።
ተከሳሾችም ባቀረቡት የመጀመሪያ ደረጃ መቃወሚያ በህብረት ሥራ ማህበር አዋጅ ቁጥር 147/1991 በክፍል ዘጠኝ በአንቀጽ 46 መሰረት በቅድሚያ ጉዳዩ መታየት ያለበት በእርቅ መሆኑን፣ በእርቅ ማለቅ ካልቻለም ለሽምግልና ዳኝነት ጉባዔ ቀርቦ የሚወሰን ሆኖ ሳለ ከሳሽ በቀጥታ ለፍርድ ቤት ያቀረበውን ክስ ፍርድ ቤቱ ተቀብሎ አከራክሮ ለመወሰን ሥልጣን የለውም ሲሉ ተከራክረዋል።
ፍርድ ቤቱም የቀረበውን ክስና ተከሳሾች ያቀረቡትን የመጀመሪያ ደረጃ መቃወሚያ ከአዋጅ ቁጥር 147/1991 አንጽ 46 እና 49 ጋር አገናዝቦ በመመርመር፡- የግራ ቀኙ ተከራካሪዎች የማህበሩ አባል መሆናቸውን ያልተካካዱ ስለሆነና ጉዳዩም በቀጥታ በእርቅ ካልሆነም በሽምግልና ላታይ የሚገባ በመሆኑ ፍርድ ቤቱ ጉዳዩን ተቀብሎ አከራክሮ ለመወሰን የሥረ ነገር የዳኝነት ሥልጣን የለውም ሲል በፍ/ሥ/ሥ/ህ/ቁ/ 244(2)(ሀ) መሰረት ሁለቱንም የክስ መዝገቦች ዘግቷል።
ከሳሽም በሁለቱም መዝገቦች ይግባኝ የጠየቀ ቢሆንም ፍርድ ቤቱ ይግባኙን በፍ/ሥ/ሥ/ህ/ቁ/337 መሰረት በመዝጋት በማሰናበቱ የሰበር አቤቱታውን ለዚህ ችሎት አቅርቧል። አመልካች በሁለቱም መዝገቦች በዋናነት ያቀረበው የቅሬታ ነጥብ ሲጠቃለል፡- ተጠሪዎች የአመልካች ማህበር የመተዳሪያ እና የፋይናንስ ደንብ ተከትለው ባለመሥራታቸው ምክንያት በኦዲት ሪፖርት የተረጋጠውን የጉድለት ገንዘብ እንዲከፍሉ በአዋጅ ቁጥር 147/1991 አንቀጽ 39(1)(ሀ) መሰረት ጥረት ቢደረግም ፈቃደኞች ሆነው ባለመገኘታቸው በዚሁ አንቀጽ በንዑስ አንቀጽ 3 መሰረት ያጎደሉትን ገንዘብ ከነወለዱ እንዲከፍሉ በሚል የቀረቡትን ክሶች የሥር ፍርድ ቤቶች በአባላት መካከል እንደተነሳ አለመግባባት ቆጥረው በዕርቅ ወይም በሽምግልና ላፈታ የማይችለውን ጉዳይ ከአዋጁ አንቀጽ 46 እና 49 ዓላማና መንፈስ ውጪ በዕርቅ እና በሽምግልና ላታይ የሚገባ እንጂ ለፍርድ ቤት ቀጥታ የሚቀርብ ጉዳይ አይደለም በሚል ክሶቹን በብይን ውድቅ ያደረጉት ከዚህ በላይ የተቀመጡትን የአዋጁን ድንጋጌዎች ያላገናዘበና በኢ/ፍ/ዲ/ሪ/ህገ መንግስት አንቀጽ 37(2)(ሀ) -የህብረት ስራ ማህበራት ክስ መስርተው ፍትህ የማግኘት መብት አላቸው በሚል የተደነገገውን የሚቃረን ስለሆነ ተቀባይነት የለውም የሚል ነው።
ተጠሪዎች በተከሰሱበት የክስ መዝገብ በየበኩላቸው በሰጡት መልስ፡- አመልካች የህብረት ሥራ ማህበር ሲሆን ተጠሪዎች ደግሞ የቀድሞ የማህበሩ የሥራ አመራር ኮሚቴ አባላት ወይም በአዋጁ አገላለጽ ሹሞች በመሆናችን በመካከላችን የተፈጠረው አለመግባባት ላታይ የሚገባው ከፍርድ ቤት ይልቅ በአዋጁ አንቀጽ 46፣47 እና 49(3) መሰረት በእርቅ ወይም በሽምግልና ዳኝነት በመሆኑ የሥር ፍርድ ቤቶች የሰጡት ብይን የሚነቀፍበት ምክንያት የለውም ብለዋል።
አመልካችም ተጠሪዎች ላቀረቡት መልስ የመልስ መልስ በማቅረብ ተከራክሯል።
የጉዳዩ አመጣጥ ከዚህ በላይ የተመለከተው ሲሆን የሥር ፍርድ ቤቶች አመልካች በቀጥታ ያቀረቧቸውን ክሶች ለማየት የዳኝኘት ሥልጣን የለንም ሲሉ የክስ መዝገቦቹን የዘጉት በአግባቡ ነው? ወይስ አይደለም? የሚለውን ጭብጥ ይዘን ክርክሩን እንደሚከተለው መርምረናል።
የሥር ፍርድ ቤቶች ጉዳዩን ተቀብለው አከራክረው ለመወሰን የስረ ነገር የዳኝነት ሥልጣን እንደልላቸው በመግለጽ የክስ መዝገቦቹን የዘጉት የግራ ቀኙ ተከራካሪዎች የማህበሩ አባል መሆናቸውን ያልተካካዱ ስለሆነ ጉዳዩ በቀጥታ በእርቅ ካልሆነም በሽምግልና ላታይ ይገባል በሚል ነው። የህብረት ሥራ ማህበራት አዋጅ ቁጥር 147/1991 ማሻሻያ አዋጅ ቁጥር 402/1996 አንቀጽ 46 በአዋጅ ቁጥር 147/1991 አንቀጽ 49(1-4) የተመለከቱት ክርክሮች ለሽምግልና ዳኝነት ከመቅረባቸው በፊት ተከራካሪ ወገኖች በሚመርጡት 3ኛ ወገን በእርቅ መታየት ይችላል በሚል የተደነገገ ሲሆን በዕርቅ ያላለቁ እንደሆነ ደግሞ ለሽምግልና ዳኝነት እንደሚቀርቡ በአዋጅ ቁጥር 147/1991 አንቀጽ 47(1) ከተደነገገው መገንዘብ የሚቻል ነው። ይህ ችሎት በሰ/መ/ቁ/70351 በቀን 17/11/2004 ዓ/ም በዋለው ችሎት፡- ማህበሩ የሚጠይቀው ጉድለትን መሰረት ያደረገ ገንዘብ ከሆነ በአዋጅ ቁጥር 147/1991 አንቀጽ 47 እና 49 መሰረት በዕርቅ ወይም በሽምግልና መታየት አለበት ላባል የሚችል አለመሆኑን ፤ይልቁንም በአዋጁ አንቀጽ 26(2)፣39 (1)(ለ)(ሐ) እና በደንብ ቁጥር 106/1996አንቀጽ 14(ሀ)(ሐ)(መ) መሰረት የማህበሩ የሥራ ሀላፊዎች ያጎደሉትን ገንዘብ እንዲተኩ በቀጥታ ክስ ለፍርድ ቤት ማቅረብ እንደሚቻል በተመሳሳይ ጉዳይ አስገዳጅ የህግ ትርጉም ሰጥቷል።
በመሆኑም በተጠሪዎች ላይ አመልካች በሁለቱም መዝገቦች ክስ ያቀረበው የከሳሽ ማህበር የሥራ አመራር አካላት፣የቁጥጥር ከሚቴ እና ዕቃ ግዥ ሆነው በሚሰሩበት ጊዜ በእጃቸው የገባውን የማህበሩን ገንዘብ ለግል ጥቅማቸው በማዋል በማጉደላቸው ገንዘቡን ከነወለዱ እንዲከፍሉ እንዲወሰን በሚል እስከሆነ ድረስም ክስ የቀረበባቸውን ገንዘብ በተመለከተ ክርክር ተደርጎ በማስረጃዎች በሚረጋገጡ ፍሬ ነገሮች መሰረት ውሳኔ የሚሰጥበት ጉዳይ እንጂ አስቀድሞ በእርቅ ካልሆነም በሽምግልና ዳኝነት ከታዬ በኋላ በአዋጅ ቁጥር 147/1991 አንቀጽ 52 መሰረት በይግባኝ ሥርዓት ወደ መደበኛ ፍርድ ቤት ላመጣ የሚገባ ጉዳይ አይደለም። በመሆኑ ይህን ችሎት ከዚህ በላይ በተጠቀሰው የሰበር መዝገብ የአዋጅ ቁጥር 147/1991 አንቀጽ 47፣ 49፣26(2)፣39 (1)(ለ)(ሐ) እና ደንብ ቁጥር 106/1996 አንቀጽ 14(ሀ)(ሐ)(መ) መሰረት ተፈጻሚነትን በተመለከተ የሰጠውን አስገዳጅ የህግ ትርጉም ባላገናዘበ መልኩ የፍድራል መጀመሪያ ደረጃ ፍርድ ቤት በሁለቱም መዝገቦች በቀጥታ የቀረቡ ክሶችን አከራክሮ ለመወሰን ሥር ነገር የዳኝነት ሥልጣን የለኝም ሲል የክስ መዝገቦቹን በብይን የዘጋውና የፍድራል ከፍተኛ ፍርድ ቤትም ይህንኑ ብይን ተገቢ ነው ሲል ያጸናው መሰረታዊ ሆነ የህግ ስህተት የተፈጸመበት ሆኖ በማግኘታችን ተከታዩን ውሳኔ ሰጥተናል።
የፍድራል የመጀመሪያ ደረጃ ፍርድ ቤት በመ/ቁ/40406 በቀን 25/07/2005 ዓ/ም በዋለው ችሎት የሰጠውን ብይን ፣እንዲሁም በመ/ቁ/40407 በቀን 26/07/2005 ዓ/ም በዋለው ችሎት የሰጠውን ብይን በፍ/ሥ/ሥ/ህ/ቁ/348(1) መሰረት ሽረናል። እንዲሁም የፍድራል ከ/ፍርድ ቤት ጉዳዩን በይግባኝ ከተመለከተ በኋላ በመ/ቁ/135108 በቀን 15/9/2005 ዓ/ም በዋለው ችሎት የሰጠውን ትዕዛዝ እና በመ/ቁ/135110 በቀን 22/09/2005 ዓ/ም በዋለው ችሎት የሰጠውን ትዕዛዝ በፍ/ሥ/ሥ/ህ/ቁ/348(1) መሰረት ሽረናል።
አመልካች በተጠሪዎች ላይ ያቀረቧቸው ክሶች በአዋጅ ቁጥር 147/1991 አንቀጽ 49 ሥር የተደነገጉትን ሁኔታዎች የሚመለከቱ አይደለም። ስለሆነም ክሶቹ ለመደበኛ ፍርድ ቤት የሚቀርቡ በመሆናቸው የመጀመሪያ ደረጃ ፍርድ ቤት አከራክሮ ለመወሰን ስረ ነገር ሥልጣን አለው በማለት የተዘጉትን የክስ መዝገቦች በማንቀሳቀስ የግራ ቀኙን ወኖች በማከራከር፣ ማስረጃዎችን በማስማትና በመመዝን በጉዳዩ ላይ የበኩሉን ውሳኔ እንዲሰጥበት ክርክሩን በፍ/ሥ/ሥ/ህ/ቁ/343(1) መሰረት መልሰን ልከንለታል።ይጻፍ።
የዚህን ፍርድ ቤት ወጪና ኪሳራ የግራቀኙ ወገኖች የየራቸውን ይቻሉ።
የዚህ ፍርድ ግልባጭ ከሰ/መ/ቁ/ 90738 ጋር ተያይዞ ይቀመጥ።
መዝገቡ የተዘጋ ስለሆነ ወደመዝገብ ቤት ይመለስ።
No topics extracted.