No summary available.
ጥቅምት 21 ቀን 2006 ዓ.ም.
ዳኞች፡- ተገኔ ጌታነህ አልማው ወል ዓላ መሐመድ ረታ ቶሎሳ አዳነ ንጉሴ አመልካች፡- ቲኤንቲ ኮንስትራክሽንና የንግድ ስራዎች ድርጅት - የቀረበ የለም ተጠሪ፡- አቶ እያዩ ደጀኔ የቀረበ የለም **
መዝገቡ ተመርምሮ ተከታዩ ፍርድ ተሰጥቷል።
**
ጉዳዩ በአሰሪና ሰራተኛ መካከል የተመሰረተ የስራ ግንኙነትን መሰረት አድርጎ የተነሳውን ለተሰራ ስራ የሚከፈል ክፍያ ይከፈለኝ ጥያቄን ለማየት የስረ ነገር የዳኝነት ስልጣን ያለውን አካል የሚመለከት ነው።ክርክሩ የተጀመረው የአሁኑ ተጠሪ ባሁኑ አመልካች ላይ በድሬዳዋ አስተዳደር አስተዳደር ቀበል 02 ማህበራዊ ፍርድ ቤት ባቀረቡት ክስ መነሻ ነው።የተጠሪ የክስ ይዘትም፡- ተጠሪ በአሁኑ አመልካች ድርጅት ውስጥ በወር ብር 2000.00 ተቀጥረው ስራ መስራታቸውንና ለሰሩት ስራ ብር 2000.00 ያልተከፈላቸው መሆኑን ዘርዝረው ይህንኑ ገንዘብ አመልካች እንዲከፍላቸው ይወሰንላቸው ዘንድ ዳኝነት መጠየቃቸውን የሚያሳይ ነው።የአሁኑ አመልካች ለክሱ በሰጠው መልስም ጉዳዩ በቀበል ማህበራዊ ፍርድ ቤት ላታይ የማይችል መሆኑንና ክፍያው ለተጠሪ ያልተፈጸመው ተጠሪው በፈጸሙት ጥፋት መሆኑንና ተጠሪ ከአመልካች ድርጅት ብር 3000.00 ብድር ወስደው አንድ ሺህ ብር ብቻ ከፍለው ቀሪውን ባለመክፈላቸው መሆኑን ዘርዝሮ ክሱ ውድቅ ላሆን ይገባል በማለት ተከራክሯል።ጉዳዩ የቀረበለት የቀበል ማህበራዊ ፍርድ ቤትም ጉዳዩን በማየት አመልካችን ለክሱ ኃላፊ በማድረግ ከተለያዩ ወጪዎች ጋር በድምሩ ብር 2134.00 ለተጠሪ እንዲከፍል በማለት ወስኗል።በዚህ ውሳኔ የአሁኑ አመልካች ቅር በመሰኘት ይግባኙን ለድሬዳዋ ከተማ አስተዳደር የመጀመሪያ ደረጃ ፍርድ ቤት ይግባኙን ቢያቀርብም ግራ ቀኙ ከተራከሩ በኋላ የስር ፍርድ ቤት ውሳኔ ጸንቷል።የአሁኑ የሰበር አቤቱታ የቀረበውም ይህንኑ ውሳኔ በመቃወም ለማስለወጥ ነው።የአመልካች የሰበር አቤቱታ መሰረታዊ ይዘትም ጉዳዩ የአሰሪና ሰራተኛ ሲሆን በአዋጅ ቁጥር 377/1996 መሰረት በክልል መጀመሪያ ደረጃ ፍርድ ቤት የሚታይ ሁኖ እያለ በአዋጅ ቁጥር 416/1996 ከተሰጠው ስልጣን ውጪ የቀበል ማህበራዊ ፍርድ ቤት ጉዳዩን ማየቱ ያላግባብ ነው የሚል ነው።አቤቱታው ተመርምሮም በሰበር ችሎቱ እንዲታይ ተደርጎ ለተጠሪ ጥሪ ቢደረግላቸው ጥሪው በሕጉ አግባብ ደርሷቸው ባለመቅረባቸው በፅሑፍ መልስ የመስጠት መብታቸው ታልፏል።
የጉዳዩ አመጣጥ አጠር ባለመልኩ ከላይ የተመለከተው ሲሆን ይህ ችሎትም ጉዳዩን በሚከተለው መልኩ መርምሮታል።እንደመረመረውም የቀበል ማህበራዊ ፍርድ ቤት ጉዳዩን የማየት የሥረ ነገር ስልጣን አለው? ወይስ የለውም? የሚለው ነጥብ የችሎቱን ምላሽ የሚያስፈልገው ሁኖ አግኝቶታል።
ከክርክሩ ሂደት መገንዘብ የታቸው ተጠሪ ከአመልካች ጋር ቅጥር ላይ የተመሰረተ ግንኙነት መስርተው ስራ መስራታቸውንና ለሰሩት ስራ ደመወዝ ያልተከፈላቸው መሆኑን ጠቅሰው፤ የገንዘቡን መጠን ለይተው ገንዘቡ እንዲከፈላቸው ዳኝነት የመጠቃቸውን፣አመልካች ለክሱ በሰጠው መልስም የተጠሪ ክስ መሰረት ያደረገው ቅጥርን በመሆኑ በቀበል ማህበራዊ ፍርድ ቤት የስረ ነገር ስልጣን የማይወድቅ መሆኑን ገልፆ የተከራከረ መሆኑን ነው።
በመሰረቱ በድሬዳዋ ከተማ አሰተዳደር የሚገኙት ፍርድ ቤቶችና ልሎች የዳኝነት ስልጣን የተሰጣቸው አካላት ስልጣናቸው በአዋጅ ቁጥር 416/1996 ከአንቀጽ 31 እስከ 42 ድረስ በተዘረዘሩት ድንጋጌዎች መሰረት የተዘረጋ ሲሆን የአዋጁ አንቀጽ 41(1) ድንጋጌ በተለይ ሲታይም የአስተዳደሩ ቀበል ማህበራዊ ፍርድ ቤቶች ግምታቸው ከብር 2000.00 ያልበለጡ የገንዘብና የንብረት ክርክሮችን የማየት ስልጣን ያላቸው መሆኑን በግልጽ ደንግጓል።በልላ በኩል የአሰሪና ሰራተኛ ጉዳይን በተመለከተ ሕግ አውጪው በአዋጅ ቁጥር 377/1996 የተለየ ሕግ አውጥቶ አዋጁን መሰረት አድርገው የሚነሱ ክርክሮችን የመዳኘት ስልጣን ያላቸውን አካላት ለይቶ ማስቀመጡን የአዋጁ አንቀጽ 138 እና 142 ድንጋጌዎች ይዘት ያሳያል።ይህ ህግ የገንዘብ መጠንን ግንዛቤ ውስጥ ሳያስግባ በአዋጅ ቁጥር 377/1996 አግባብ የተቋቋመውን ግንኙነት መሰረት አድርጎ የሚነሳው የግል የስራ ክርክር በክልል የመጀመሪያ ደረጃ ፍርድ ቤት እንደሚታይ፣የወል የስራ ክርክር ከሆነ ደግሞ በአሰሪና ሰራተኛ ጉዳይ ወሳኝ ቦርድ የሚዳኝበትን አግባብ የዘረጋ ነው።በመሆኑም ሕጉ ለአሰሪና ሰራተኛ ግንኙነቶች ልዩ ሕግ እንደመሆኑ መጠን ለጉዳዩ ከልሎች ሕጎች ሁሉ የበላይ ተፈፃሚነት አለው።ከዚህ አንጻር ጉዳዩን ስንመለከተው ተጠሪ ከአመልካች ጋር የመሰረቱት ግንኙነት የአሰሪና ሰራተኛ መሆኑን በግልጽ ጠቅሰው ክስ በመሰረቱበት ሁኔታ የቀበል ማህበራዊ ፍርድ ቤት የገንዘቡ መጠን ብር 2000.00 መሆኑን ብቻ በመመልከት፣ጉዳዩን ከአዋጅ ቁጥር 377/196 አንጻር በመመልከት ስልጣኑ መሆኑን ሳያረጋግጥ ጉዳዩን ተቀብሎ ማየቱ ከአዋጅ ቁጥር 416/1996 አንቀጽ 41(1)፣ከአዋጅ ቁጥር 377/1996 ድንጋጌዎች እንዲሁም የፍ/ብ/ሥ/ሥ/ሕ/ቁጥር 9(1) እና 231(1(ለ)) ድንጋጌዎች ይዘትና መንፈስ ያላገናዘበ፣በጉዳዩ የተሰጠው ውሳኔ በሕጉ ከተዘረጋው ስርዓት ውጪ ስልጣን በልለው አካል የተሰጠ በመሆኑ ውሳኔው መሰረታዊ የሆነ የሕግ ስህተት ያለበት ሁኖ ስለአገኘነው ተከታዩን ወስነናል።
ው ሣ ኔ
በድሬዳዋ ከተማ አስተዳደር ቀበል 02 ማህበራዊ ፍርድ ቤት በመ/ቁጥር 0113/05 ጥር 14 ቀን 2005 ዓ/ም ተሰጥቶ በከተማው የመጀመሪያ ደረጃ ፍርድ ቤት በመ/ መጋቢት 27 ቀን 2007 ዓ/ም የጸናው ውሳኔ በፍ/ብ/ሥ/ሥ/ሕ/ቁጥር 348(1) መሰረት ተሸሯል።
የቀበል ማህበራዊ ፍርድ ቤት በአዋጅ ቁጥር 377/1996 መሰረት የተመሰረተውን ግንኙነት መሰረት አድርጎ የሚቀርበውን ክርክር የማየት የስረ ነገር ስልጣን የለውም ብለናል።
ተጠሪ ጥያቄአቸውን በአዋጅ ቁጥር 377/1996 መሰረት ስልጣን ላለው ፍርድ ቤት የማቅረብ መብታቸውን ይህ ውሳኔ አያግዳቸውም ብለናል።
በዚህ ችሎት ለተደረገው ክርክር የወጣውን ወጪና ኪሳራ የየራሳቸውን ይቻሉ ብለናል።
No topics extracted.