No summary available.
መስከረም 22 ቀን 2006 ዓ.ም.
ዳኞች፡- ተገኔ ጌታነህ አልማው ወል ዓላ መሐመድ ረታ ቶሎሳ ሙስጠፋ አህመድ አመልካች፡- የኢትዩጵያ ገቢዎችና ጉምሩከ ባለስልጣን - ዐ/ህግ ቢኒያም አብርሃም ቀረቡ ተጠሪ፡- ግሎሪ ኢትዩጵያ አስጎብኝና የጉዞ ወኪል ኃ.የተ.የግል ማህበር - ጠበቃ ጫንያለው ከበደ ቀረቡ **
መዝገቡ ተመርምሮ ተከታዩ ፍርድ ተሰጥቷል።
**
ጉዳዩ ከአስጎብኚና የጉዞ ወኪል የንግድ ፈቃድ ስራ ጋር በተያያዘ ለአንድ ተሽከርካሪ የጉምሩክ ቀረጥ የሚከፈልበትን አግባብ የሚመለከት ነው።
የግራ ቀኙ ክርክር የተጀመረው በፍድራል መጀመሪያ ደረጃ ፍርድ ቤት ሲሆን የአሁኑ ተጠሪ ከሳሽ፣የአሁኑ አመልካች ደግሞ ተከሳሽ ሆነው ተከራክረዋል።
የአሁኑ ተጠሪ ለፍድራሉ መጀመሪያ ደረጃ ፍርድ ቤት ያቀረበው የክስ ማመልከቻ ይዘት በአጭሩ ድርጅታቸው በኢ.ፍ.ዲ.ሪፐብላክ የኢንቨስትመንት ባለስልጣን የማስጎብኝት አገልግሎት ፈቃድ የተሰጠው መሆኑን፣በዚሁ መሰረት መንግስት በዘርፋ ለተሰማሩ ባለሀብቶች የሰጠውን ከቀረጥ ነጻ መብት ተጠቅሞ በደንብ ቁጥር 146/2000 አግባብ በተሰጠው መብት መሰረት ከሚመለከታቸው መስሪያ ቤቶች አስፈላጊውን ሁኔታ ሁሉ አሟልቶ፣ተሸከርካሪዎችን ገዝቶ ከቀረጥ ነጻ እንዲገቡ የአሁኑን አመልካች በመጠየቅ ሐምል 15 ቀን 2002 ዓ/ም በተፃፈ ደብዳቤ መኪኖቹ ከማናቸውም ቀረጥና ታክስ ነጻ ሁነው እንዲገቡ በፈቀደው መሰረት ተሸከርካሪዎቹ አስፈላጊ የሆኑ ፎርማላቲዎችን አሟልተው ቀረጥ ሳይከፈልባቸው መግባታቸውን፣ ተጠሪ መኪኖቹን ወደ ስራ ከአሰማራ በኋላ ከሶስቱ መኪኖቹ አንዱ ከ10 ሰው በታች የሚጭን ስለሆነ ቀረጥና ታክስ መክፈል አለብህ በ ማለት አመልካች መጠየቁን፣ ተሽከርካሪዎቹን አስመልክቶ መሟላት የሚገባቸውን መስፈርቶች የመግለፅና የማሳወቅ ስልጣን የተሰጠው ለትራንስፖርት ባለስልጣን መሆኑ እየታወቀና ይኼው ባለስልጣን ማብራሪያ ተጠይቆ ሚኒባስ ማለት አሽከርካሪውን ሳይጨምር ከ7-14 ሰው የሚጭን መሆኑን ገልጾ ማብራሪያ መስጠቱንና በዚህ አግባብ አመልካችም ሲያስተናግድ ቆይቶ ምክንያቱ ምን እንደሆነ ባልታወቀ ሁኔታ ቀረጥና ታክስ ካልከፈልክ ማለቱ ያላግባብ መሆኑን ዘርዝሮ ሁከቱ ተወግዶ የአመልካች የቀረጥ ክፍያ ጥያቄ ውድቅ ሁኖ እንዲወሰን ዳኝነት መጠየቁን የሚያሳይ ነው።
የአሁን አመልካች ቀርቦም ፍርድ ቤቱ ጉዳዩን በቀጥታ ለማየት የሚችልበት አግባብ የልለ መሆኑን በመጀመሪያ ደረጃ መቃወሚያነት ያነሳ ሲሆን በፍሬ ነገር ደረጃ ደግሞ እርምጃው በሕጉ የተሰጠውን ስልጣን መሰረት አድርጎ የተከናወነ መሆኑን በመጥቅስና ለጉዳዩ አግባብነት አላቸው ያላቸውን የህግ ማዕቀፎችን ዘርዝሮ ክሱ ውድቅ ላሆን ይገባል በማለት ተከራክሯል። የስር ፍርድ ቤትም አመልካች ስልጣንን መሰረት አድርጎ ያነሳውን ክርክር በተመለከተ የተጠሪ ጥያቄ ከቀረጥ ነጻ መብት የተያያዘ እንጂ ከቀረጥና ከታክስ አከፋፈል ጋር የተያያዘ አይደለም በሚል ምክንያት ውድቅ አድርጎታል።ፍሬ ጉዳዩን በተመለከተም የግራ ቀኙን ክርክርና ማስረጃ በመመርመር የአመልካች ጥያቄ ሕጋዊ አይደለም በማለት ወስኗል።በዚህ ውሳኔ የአሁኑ አመልካች ቅር በመሰኘት ይግባኙን ለፍድራሉ ከፍተኛ ፍርድ ቤት ቢያቀርብም ተቀባይነት አላገኘም። የአሁኑ የሰበር አቤቱታ የቀረበውም ይህንኑ ውሳኔ በመቃወም ለማስለወጥ ነው። የአመልካች የሰበር አቤቱታ መሰረታዊ ይዘትም የስር ፍርድ ቤት ጉዳዩን በቀጥታ ማየቱ በሕጉ ከተዘረጋው ስርዓት ውጪ መሆኑንና በአከራካሪው መኪና ላይ የአመልካች የቀረጥና የታክስ ይከፈል ጥያቄ በሕጉ በተፈቀደው አግባብና ስልጣኑን መሰረት አድርጎ የተከናወነ ሁኖ እያለ ተጠሪ የሁከት ይወገድልኝ ክስ አቅርቦ ፍርድ ቤቱ ተገቢውን ጭብጥ ሳይመሰርትና አግባብነት ያላቸውን ሕጎች በአግባቡ ሳይመለከት የአመልካች ጥያቄ አግባብ አይደለም ብሎ መወሰኑ መሰረታዊ የሆነ የሕግ ስህተት ነው በማለት መከራከሩን የሚያሳይ ነው።
አቤቱታው ተመርምሮም በሰበር ችሎቱ እንዲታይ በመደረጉ የግራ ቀኙ ክርክር በፅሑፍ እንዲደረግ ተደርጓል።
የጉዳዩ አመጣጥ አጠር አጠር ባለመልኩ ከላይ የተገለጸው ሲሆን ይህ ችሎትም የግራ ቀኙን ክርክር ለሰበር አቤቱታው መነሻ ከሆነው ውሳኔ እና ለጉዳዩ ቀጥተኛ አግባብነት ካላቸው የህጉ ድንጋጌዎች ጋር በማገናዘብ ጉዳዩን በሚከተለው መልኩ መርምሮታል።እንደመረመረውም የስር ፍርድ ቤት ጉዳዩን በቀጥታ ክስ ማስናገዱ ተገቢ ነው?
ወይስ አይደለም? የሚለው ነጥብ በጭብጥነት ላታይ የሚገባው ሁኖ አግኝተናል።
ከክርክሩ መገንዘብ የተቻለው የአሁኑ ተጠሪ ባለው የኢንቨስትመንት ፈቃድ በኢንቨስትመንት ስራ ላይ በመሰማራት ለስራው የሚገለገልባቸውን ተሸከርካሪዎችን ከቀረጥና ከታክስ ነጻ ወደ አገር ውስጥ ለማስገባት ፈልጎ ይህንኑ በማመልከት ስለተፈቀደለት አስፈላጊ ዶክመንቶችን በማሟላት መኪኖችን ገዝቶ ከአስገባና ስራ ላይ ከአሰማራ በኋላ ከገቡት ተሸከርካሪዎች ውስጥ አንዱ ከአስር ሰው በታች የሚጭን በመሆኑ ቀረጥ ላከፍልበት ይገባል በማለት አመልካች መሰሪያ ቤት መጠየቁን ገልጾ ጥያቄው ሁከት በመሆኑ ላቆም ይገባል በማለት ዳኝነት መጠየቁን፣የአመልካች ዋና የመከራከሪያ ነጥብ ደግሞ ለተጠሪ የቀረበው አይነት ጥያቄ በአመልካች መቅረቡ በሕጉ የተፈቀደና በጥያቄው ቅሬታ ያለው ወገንም በአዋጅ ቁጥር 622/2001 አግባብ በአመልካች መስሪያ ቤት በተዘረጋው ስርዓት ቅሬታውን ማቅረብ፣በሚሰጠው ውሳኔ ቅሬታ ካደረበትም ጉዳዩ ለግብር ይግባኝ ሰሚ ጉባኤ ከሚቀርብና በስርዓቱ መሰረት ለፍድራል ከፍተኛ ፍርድ ቤትና ለበላይ ፍርድ ቤቶቸ ቅሬታው ታይቶ ከሚስተናገድ በስተቀር በቀጥታ ክስ ለመደበኛ ፍርድ ቤት የሚቀርብበት ጉዳይ አይደለም፣ከአስር በታች የሆነ ሰው የሚጭን መቀመጫ ያለው ተሽከርካሪ ደግሞ “ሚኒባስ” በሚለው ትርጉም አይካተትም በሚል መሆኑን ነው።
ከላይ ከተገለፀው የግራ ቀኙ ክርክር መረዳት የሚቻለው ተጠሪ የቀረጥና የታክሰ ነጻ መብት አለኝ በማለት ከመጥቀሱ ውጪ አከራካሪው ተሸከርካሪ ከቀረጥና ታክስ ነጻ ተብሎ በሕጉ አግባብ ላመደብ የሚችል መሆን ያለመሆኑ የክርክሩ መሰረታዊ ጭብጥና ግራ ቀኙን የሚያከርከር ጉዳይ መሆኑን ነው።እንዲህ ከሆነ ከእቃው አመዳዳብ፣የጉምሩክ ስነስርዓት፤ ከቀረጥና ታክስ አከፋፈል ጋር ተያይዞ ቅሬታ መነሳቱን የሚያመላክት በመሆኑ በአዋጅ ቁጥር 622/01 አንቀጽ 87 (1) ስር በግለጽ እንደተመለከተው በእቃዎች አሰያየም፣አመዳደብ ወይም በታሪፍ ልክ ላይ ተቃውሞ ካለ እንዲሁም በተጠቃሹ አንቀጽ ንዑስ አንቀጽ 3 (ሐ) ስር እንደተመለከተው ማንኛውም ከጉምሩክ ሥነ ሥርዓት ጋር በተያያዘ በሚሰጡ ውሳኔዎች ላይ ቅሬታ ያለው አካል አቤቱታውን ማቅረብ ያለበት ቀጥታ ለፍርድ ቤት ሳይሆን በተጠቃሹ አዋጅ በተዘረጋው የይግባኝ ሰርዓት መሆኑ ተመልክቷል።የይግባኝ አቀራረብ ስርዓቱም ጉዳዩ ከአመልካች መስሪያ ቤት የጉምሩክ ጉዳዮች አቤቱታ አጣሪ ኮሚቴ ቀርቦ ከታዬ በኋላ ቅሬታ ያለው ወገን በአንቀጽ ንዑስ ቁጥር 5 መሰረት ለግብር ይግባኝ ሰሚ መቅረብ እንደአለበት፣ ከዚያም በአንቀጹ ንኡስ ቁጥር 9 መሰረት ለፍድራሉ ከፍተኛ ፍርድ ቤት መቅረብ እንደአለበት፣በዚህ ውሳኔ ቅሬታ ያለው ወገንም በአንቀጹ ንኡስ ቁጥር 10 ድንጋጌ አግባብ በአዋጅ ቁጥር 286/1994 አንቀጽ 112 አና በኢ.ፍ.ዲ.ሪፐብላክ ሕግ መንግስት አንቀጽ 80(3(ሀ) እና አዋጅ ቀጥር 25/1988 አንቀጽ 10 ድንጋጌዎች አግባብ ለበላይ ፍርድ ቤት እንደየቅደምተከተሉ ይግባኙንና የሰበር አቤቱታውን ማቅረብ እንደሚችል የድንጋጌዎች አቀራራጽና ይዘት ያሳያል። ይሄ ከሆነ ደግሞ የአመልካች የቀረጥና የታክስ ክፍያ ጥያቄ አግባብነት የለውም የሚለው የተጠሪ ክርክር በእነዚሁ አዋጆች በተዘረጋው ስርዓት መሰረት ታይቶ እልባት ከሚያገኝ በስተቀር በቀጥታ ለመደበኛ ፍርድ ቤት የሚቀርብበት እና ፍርድ ቤቶች ጐዳዩን በቀጥታ አይተው ውሳኔ የሚሰጡበት አግባብ አይኖርም። የበታች ፍርድ ቤቶችም ጐዳዩ ሲቀርብላቸው ጉዳዩን በቀጥታ የማየት ስልጣን እንደልላቸው በመገንዘብ በፍ/ብ/ሥ/ሥ/ሕ/ቁጥር 9፣231(1(ለ)) እና 244(2(ሀ)) መሰረት መመለስ ሲገባቸው ክሱን በመቀበልና በማከራከር ውሳኔ መስጠታቸው የሕጉን አካሄድ የተከተለ ሁኖ አላገኘነውም።
ሲጠቃለልም የበታች ፍርድ ቤቶች ተጠሪ ባቀረቡት የቀረጥና የታክስ ክፍያ ጥያቄ ላይ ስልጣን ሳይኖራቸው የሰጡት ውሳኔ የሕግ መሰረት የልለው፣የክርክሩን አጠቃላይ ይዘት አግባብነት ካላቸው ድንጋጌዎች ጋር ያላገናዘበ በመሆኑ መሰረታዊ የሆነ የህግ ስህተት የተፈጸመበት ሁኖ ስለአገኘነው ተከታዩን ወስነናል።
በፍድራሉ መጀመሪያ ደረጃ ፍርድ ቤት በመ/ ነሐሴ 13 ቀን 2003 ዓ/ም ተሰጥቶ በ07/02/2004 ዓ/ም የተገለጸውና በፍድራሉ ከፍተኛ ፍርድ ቤት በመ/ ጥር 06 ቀን 2005 ዓ/ም የፀናው ውሳኔ በፍ/ብ/ሥ/ሥ/ህግ ቁጥር 348 (1) መሰረት ተሽሯል።
የመደበኛ ፍርድ ቤት ተጠሪ ያቀረበውን ጥያቄ በቀጥታ ክስ በመቀበልና በመመልከት ውሳኔ ለመስጠት የስረ ነገር ስልጣን የለውም ብለናል።
በዚህ ችሎት በተደረገው ክርክር በግራቀኙ ለደረሰው ወጪና ኪሳራ የየራሳቸውን ይቻሉ ብለናል።
No topics extracted.