No summary available.
መስከረም 21 ቀን 2006 ዓ/ም ዳኞች፡-
ጉዳዩ የቀረበው አመልካች በደቡብ ብሕር ብሕረሰሶችና ሕዝቦች ክልል ጠቅላይ ፍርድ ቤት የሰበር ችሎት የሰጠው ውሣኔ መሰረታዊ የሕግ ስህተት ያለበት ስለሆነ በሰበር ታይቶ ይታረምልኝ በማለት ያቀረቡትን የሰበር አቤቱታ አጣርቶ ለመወሰን ነው። ጉዳዩ በመጀመሪያ የታየው በጋሞ ጎፋ ዞን የሳውላ ከተማ የመጀመሪያ ደረጃ ፍርድ ቤት ነው። በሥር ፍርድ ቤት አመልካች ከሣሽ ተጠሪ ተከሣሽ በመሆን ተከራክረዋል። ጉዳዩ አመልካች ተጠሪ መንገድ ላይ በቆለለው አፈር ምክንያት በደረሰብኝ አደጋ የአካል ጉዳይ የደረሰብኝ ስለሆነ ካሣ ላከፈለኝ ይገባል በማለት የቀረበውን ክርክር የሚመለከት ነው።
2 የሥር ፍርድ ቤት ፍርድ ቤት የግራ ቀኙን ክርክር ከሰማ በኃላ የሞተር ሳይክሉ ከቁጥጥር ውጭ የወጣው የቴክኒክ ብቃት ስለልለውና አሽከርካሪው (ከሳሽ) ብቃት ስለልለው ላሆን ስለሚችል ተከሳሽ ለከሳሽ ካሳ የመክፈል ኃላፊነት የለበትም በማለት ውሳኔ ሰጥቷል። አመልካች በዚህ ውሳኔ ቅር በመሰኘት ለዞኑ ከፍተኛ ፍርድ ቤት ይግባኝ አቅርቧል። የዞኑ ከፍተኛ ፍርድ ቤት አመልካችን ይግባኝ ከመረመረና የግራ ቀኙን ክርክር ከሰማ በኃላ የሥር ፍርድ ቤት የሰጠውን ውሳኔ በመሻር የሥር ፍርድ ቤት የግራ ቀኙን ማስረጃ ከሰማ በኃላ ተከሳሽ በከሳሽ ላይ ለደረሰው ጉዳት ኃላፊ ነው ወይስ አይደለም? የሚለውን ጭብጥ እንዲወስን ጉዳዩን በፍ/ሥ/ሥ/ህግ ቁጥር 343(1) መሰረት ለሥር ፍርድ ቤት መልሶታል።የሥር ፍርድ ቤት ግራ ቀኙን ምስክሮች ቃል ከሰማ በኃላ በከሳሽ(አመልካች) ላይ ለደረሰው ጉዳት ተከሳሽ(ተጠሪ) በከፊል ኃላፊ ነው በማለት ተከሳሽ ለከሻስ (አስራ ሁለት ሺህ ሁለት መቶ ሰላሳ አምስት ብር) ካሳ እንዲከፍል ውሳኔ ሰጥቷል። ተጠሪ በዚህ ውሳኔ ቅር በመሰኘት ለዞኑ ከፍተኛ ፍርድ ቤት ይግባኝ አቅርቧል። የዞኑ ከፍተኛ ፍርድ ቤት የሥር ፍርድ ቤት የሰጠውን ውሳኔ አጽንቶታል። ተጠሪ ለክልሉ ጠቅላይ ፍርድ ቤት ሰበር ችሎት የሰበር አቤቱታ አቅርቧል። የክልሉ ጠቅላይ ፍርድ ቤት ሰበር ችሎት የሥር ፍርድ ቤትና የዞኑ ከፍተኛ ፍርድ ቤት የሰጡትን ውሳኔ በመሻር ተጠሪ በአመልካች ላይ ለደረሰው ጉዳት በኃላፊነት የሚጠየቅበት ምክንያት የለም በማለት ውሳኔ ሰጥቷል።
አመልካቾች መጋቢት 18 ቀን 2005 ዓ.ም በተፃፈ የሰበር አቤቱታ ተጠሪ ባልተፈቀደ የህዝብ ጎዳና አፈር መቆለሉና መንገዱ አፈር ተቆልሎበት ምልክት አለማስቀመጡ ፍሬ ጉዳይ የማጣራትና ማስረጃ የመመዘን ሥልጣን ባላቸው ፍርድ ቤቶች ተረጋግጧል። አመልካች ጉዳት የደረሰብን በተጠሪ ጥፋት መሆኑ በማስረጃ ተረጋግጦ እያለ የክልሉ ጠቅላይ ፍርድ ቤት የሰበር ችሎት አመልካች ለጉዳቱ ኃላፊ አይደለም በማለት መወሰኑ መሰረታዊ የህግ ስህተት ያለበት ስለሆነ በሰበር ታይቶ እንዲታረምልኝ በማለት አመልክተዋል። ተጠሪ ግንቦት 19 ቀን 2005 ዓ.ም በተፃፈ መልስ አመልካች በመንገዱ ላይ አፈር የቆለለበት መሆኑን አስቀድሞ ያውቃል። ከዚህ በተጨማሪ አመልካች ጉዳት የደረሰበት ከመሥመሩ ውጭ ሲያሽከረክር ነው። አመልካች በዚህ ሁኔታ ካሳ ላከፈለኝ ይገባል በማለት ያቀረበው ክርክር የህግ መሰረት የልለው ስለሆነ የክልል ጠቅላይ ፍርድ ቤት የሰበር ችሎት መሰረታዊ የህግ ስህተት የለበትም በማለት ተከራረዋል። አመልካች በ7/10/2005 ዓ.ም የመልስ መልስ አቅርበዋል።
No topics extracted.
ከሥር የክርክሩ አመጣጥና በሰበር የቀረበው ክርክር ከላይ የተገለጸው ሲሆን እኛም የክልሉ ጠቅላይ ፍርድ ቤት ተጠሪ በአመልካች ላይ ለደረሰው ጉዳት ኃላፊነት የለበትም በማለት የሰጠው ውሳኔ በአግባቡ ነው ወይስ አይደለም የሚለውን ጭብጥ በመያዝ ጉዳዩን መርምረነል።
ጉዳዩን እንደመረመርነው አመልካች ተጠሪ በፈጸመው ከፊል ጥፋት ምክንያት ጉዳት የደረሰበት መሆኑን የሚያስረዳ ማስረጃ በማቅረብ የማስረዳት ግድታውን የተወጣ መሆኑን የሥር ፍርድ ቤትም ሆነ በይግባኝ ሰሚው ፍርድ ቤት በውሳኔአቸው አረጋግጠዋል። የበታች ፍርድ ቤቶች ፍሬ ጉዳይ የማጣራትና ዕውነትን የማፈላለግ ሥልጣናቸውን በመጠቀም በአመልካች ላይ አደጋው የደረሰው ተጠሪ በህዝብ አውራ ጎዳና መንገድ ላይ አፈር በመቆለሉና መንገዱ አፈር የተቆለለበት መሆኑን የሚያሳይ ምልክት ባለማስቀመጡ አመልካች በምሽት መስመሩን ይዞ ሞተር ሳይክል በማሽከርከር ላይ እያለ ከተቆለለው አፈር ላይ በመውጣቱ ጉዳት የደረሰበት መሆኑ ፍሬ ጉዳይ ማጣራትና ማስረጃ መመዘን ሥልጣን ባላቸው ፍርድ ቤቶች ተረጋጧል።
ይህም አመልካች በተጠሪ ድርጊት የደረሰበትን ጉዳት ልክና የአካባቢ ሁኔታዎችን መሰረት በማረግ ተከሳሹ/ ተጠሪ/ ካሳ የመክፈል ኃላፊነት ያለበት መሆኑን በፍታብሕር ሕግ ቁጥር 2141 በተደነገገው መሰረት የማስረዳት ኃላፊነቱን የተወጣ መሆኑን ያሳያል ለጉዳቱ አመልካች በከፊል አስተዋጽኦ የበረከተ መሆኑ በበታች ፍርድ ቤቶች የተረጋገጠ ቢሆንም ተጠሪ የመንገዱን ቀርጽ አፈር ቆልሎ በመቀየሩና መንገዱ አፈር የተቆለለበት መሆኑን የሚያሳይ ምልክት ባለማድረጉ በፍታብሕር ህግ ቁጥር 2069 መሰረት ለአደጋው እና በአደጋው ምክንያት በአመልካች ላይ ለደረሰው ጉዳት በከፊል በኋላፊነት ተጠያቂ መሆኑን የሚያስቀረው አይደለም ስለሆነም የክልሉ ጠቅላይ ፍርድ ቤት ሰበር ችሎት ተጠሪ ለጉዳቱ ምንም አይነት ኃላፊነት የለበትም በማለት የሰጠው ውሳኔ መሰረታዊ የህግ ስህተት ያለበት ነው በማለት ወስነናል።
በደቡብ ብሕር ብሕረሰቦችና ሕዝቦች ክልል ጠቅላይ ፍርድ ቤት የሰበር ችሎት የሰጠው ውሳኔ ተሽሯል።
የጋሞጎፋ ዞን ከፍተኛ ፍርድ ቤትና የሳውላ ከተማ የመጀመሪያ ደረጃ ፍርድ ቤት የሰጡት ውሳኔ ጸንቷል
በዚህ ችሎት ያወጡትን ወጭና ኪሳራ ግራ ቀኙ ለየራሳቸው ይቻሉ በማለት ወስነናል መዝገቡ ወደ መዝገብ ቤት ይመለስ።