No summary available.
ታህሣስ 15 ቀን 2006 ዓ.ም.
ዳኞች፡- አልማው ወል ዓላ መሐመድ ረታ ቶሎሣ አዳነ ንጉሴ ሙስጠፋ አሕመድ አመልካች፡-
ጉዳዩ ምንም የጥቅም ግንኙነት በልለበት ሁኔታ አቅመ አዳም ያልደረሰን ሕፃን በተሽከርካሪ ጭኖ በመጓዝ ሂደት ተሽከርካሪው ተገልብጦ ሕፃኑ ለሞት ሲዳረግ የመኪናውን ባለንብረትና አሽከርካሪው ስላለባቸው ፍትሐብሕር ኃላፊነት የሚመለከት ነው።
ክርክሩ በመጀመሪያ የተታየው በፍድራል መጀመሪያ ደረጃ ፍርድ ቤት ነው። በሥር ፍርድ ቤት አመልካቾች ተከሣሽ፣ ተጠሪ ደግሞ ከሣሸ በመሆን ተከራክረዋል። ተጠሪ 2ኛ አመልካች አሽከርካሪ በመሆን የ1ኛ አመልካች ንብረት የሆነውን የሰልዳ ቁጥር 4-14199 ኢት ፒካፕ የሆነ መኪና ሲያሽከረክር ግንቦት 08 ቀን 2002 ዓ.ም በአዲስ አበባ ከተማ የካ ክፍል ከተማ ቀበል 03/04 ብረት ድልድይ ከተባለ ቦታ ወደ ፈረንሣይ ኢንባሲ አቅጣጫ እያሽከረከረ በውጪ እቃ መጫኛ ላይ እድሜው 13 አመት የሆነ ደረጃ ማሞ የተባለ ህፃን ጭኖ በመጓዝ ላይ እያለ ሕፃኑ ወድቆ እንዲሞት ማድረጉ ሕፃኑን በሕይወት እያለ ጫማ በመጥረግ ለተጠሪ ገቢ ሲያገኙላቸው የነበረ መሆኑን በጉዳቱ ምክንያት ለህክምናም ሆነ ለቅብር ስነ ስርዓት ወጪ ያወጡ መሆኑን፣ ሕፃኑ በሕይወት ቢኖሩ ኑሮ እድሜው ሃምሳ ዓመት እስኪሞላው ለተጠሪ ያስገኝ የነበረው የቀን ገቢ ብር 8.00 እንደሚቀጥልና በመሞቱ ምክንያት ግን መቋረጡን ዘርዝረው ይህንኑ ገቢና በጉዳቱ ምክንያት ያወጡትን ወጪ በድምሩ ብር 119,870.00 (አንድ መቶ አስራ ዘጠኝ ሺህ ስምንት መቶ ሰባ ብር) እንዲከፍሉ እንዲወሰንላቸው ዳኝነት ጠይቀዋል። የአሁኑ አመልካችም ለክሱ ኃላፊነት የልለባቸው መሆኑንና የቀረበው የካሳ ክፍያም የሕግ መሰረት የልለው መሆኑን ጠቅሰው ተከራክረዋል። እንዲሁም የኢትዮጵያ መድን ድርጅትም በጉዳዩ ላይ ጣልቃ ገብቶ እንዲከራከር ተደርጓል።
የሥር ፍርድ ቤትም የግራ ቀኙን ክርክርና የተጠሪን ምስክሮች በመስማት ጉዳዩን መርምሮ አመልካቾችን ለክሱ ኃላፊ ያደረጋቸው ሲሆን ጣልቃ ገቡን ግን ከክሱ ነፃ እንዲሰናበት ወስኗል። የካሳውን መጠን በተመለከተም በርትዕ በድምሩ ብር 31,300.00 (ሰላሳ አንድ ሺህ ሶስት መቶ ብር) እንዲሆን ወስኗል። በዚህ ውሳኔ አመልካቾች ቅር በመሰኘት ይግባኛቸውን ለፍድራሉ ከፍተኛ ፍርድ ቤት አቅርበው ይግባኙ በፍ/ስ/ስ/ሕግ ቁጥር 337 ተሰርዞባቸዋል። የአሁኑ የሰበር አቤቱታ የቀረበውም ይህንኑ ውሳኔ በመቃወም ሲሆን ጉዳዩ ለሰበር ችሎት እንዲቀርብ በመደረጉ ተጠሪ ቀርበው ግራ ቀኙ በፅሁፍ እንዲከራከሩ ተደርጓል።
የጉዳዩ አመጣጥና በሰበር የቀረበው ክርክር ከላይ ባጭሩ የተገለፀው ሲሆን እኛም ጉዳዩን አመልካቾች ለጉዳቱ ኃላፊ ናቸው ተብሎ የተሰጠው ውሳኔ በአግባቡ ነው? ወይስ አይደለም? የሚለውን ጭብጥ በመያዝ ጉዳዩን መርምረናል።
በክርክሩ ውስጥ በፍሬ ነገር ደረጃ የተረጋገጡት ነጥቦች የተጠሪ ልጅ የሕዝብ ማመላለሻ ባልሆነው የ1ኛ አመልካች መኪና በ2ኛ አመልካች በእቃ መጫኛው ላይ ተሳፍሮ ሲሄድ ወድቆ ለሕልፈተ ሕይወት መዳረጉና 2ኛ አመልካች የ1ኛ አመልካች ተቀጣሪ ሰራተኛ መሆናቸው፣ ለጉዳቱ መድረስ ጥፋቱ የሹፍር መሆኑን የሚያሳዩ ናቸው።
ወደ ሕጉ ስንመጣ በመሰረቱ የፍ/ብ/ሕግ ቁ. 2089/1/ የሚገኘው ከውል ውጪ ስለሚደርስ አላፊነትና ያለአግባብ ስለመበልፀግ በሚለው በፍታብሕር ሕጉ በአንቀጽ 13 ስር ነው። ተጠሪ አመልካቾች የከሰሱትም ከውል ውጪ ደረሰ የሚለውን ኃላፊነት መሰረት በማድረግ ነው። በስር ፍ/ቤቶች በተደረገው ክርክር በፍሬ ነገር ረገድ እንደተረጋገጠው ህፃኑ የተባለው ጉዳት የደረሰበት በ1ኛ አመልካች መኪና በመገጨቱ ሳይሆን፣ በመኪናው ላይ በ2ኛ አመልካች እውቅና ተሳፍሮ ሲሄድ ከመኪናው በመውደቁ ምክንያት ነው። በእርግጥ መኪናው የ1ኛ አመልካች ንብረት ነው። ሆኖም መኪናው ገንዘብ በማስከፈል ሰዎችን የሚያጓጉዝ የንግድ መኪና ሳይሆን ለመንግስት ስራ ጥቅም ላይ የሚውል ነው። ይህ በመሆኑም ህፃኑ በመኪናው ላይ ስለመሳፈሩ 1ኛ አመልካች ያውቃል ወይም ማወቅ ይጠበቅበታል ተብሎ አይገመትም። መኪናው የተሰማራው ሰዎችን ለማጓጓዝ ባለመሆኑ 1ኛ አመልካች ሟቹን ህፃን በማሳፈር ያገኘው ጥቅም አለ ብሎ ለመደመደም የሚቻልበት ሕጋዊ ምክንያት የለም።
በፍሬ ነገር ረገድ እነዚህን ሁኔታዎች ከተረጋገጡ ቀጥሎ መታየት ያለበት አመልካቾች ለደረሰው ጉዳት ኃላፊ የሚሆኑበት የሕግ አግባብ አለ? ወይስ የለም? የሚለው ነው።
በፍ/ብ/ሕ/ቁጥር 2081/1/ እንደተደነገገው የመኪናው ባለቤት መኪናው በሶስተኛ ወገን ላይ ለሚያደርሰው ጉዳት ኃላፊ የሚሆንበት አግባብ አለ። ይህ እንግዲህ በአጠቃላይ የተቀመጠ የኃላፊነት መርህ ሲሆን፣ በቁ 2089 ደግሞ ልዩ ሁኔታ ማለትም የመኪናው ባለቤት ኃላፊ የማይሆንበት ሁኔታ ተደንግጎአል። ከድንጋጌው ርእስ መገንዘብ እንደሚቻለው ጉዳቱ የደረሰው ጥቅም በልለው ግንኙነት ጊዜ ሲሆን የመኪናው ወይም ጉደቱን ያደረሰው ንብረት ባለቤት ኃላፊነት አይኖርበትም። ከላይ እንዳመለከትነው ተጠሪ በአመልካች መኪና የተገለገለው ለአመልካች ጥቅም በማያስገኝ ሁኔታ ነው። ከሁሉ በላይ ደግሞ 1ኛ አመልካች በዚህ ረገድ ጥፋት ፈጽሞአል አልተባለም። ይልቁንም የ1ኛ አመልካች ሹፍር፤ 2ኛ አመልካች ጥፋት መፈፀሙ ተረጋግጧል ተብሎ 1ኛ አመልካች ኃላፊነቱን እንዲወስድ መደረጉን የበታች ፍ/ቤቶች ውሣኔ በግልጽ ያሳያል። ይሁን እንጂ የፍ/ብ/ሕ/ቁጥር 2089/2/ ድንጋጌ በድንጋጌው ንዑስ ቁጥር አንድ ስር የተቀመጠውን መርህ በልዩ ሁኔታ ያስቀመጠ ሲሆን ባለሃብቱ ወይም ጠባቂው ጥፋት ማድረጋቸው ከተረጋገጠ ኃላፊነት ያለባቸው መሆኑን ድንጋጌው ያሳያል። በዚህ ልዩ ሁኔታ አነጋገር መሰረት የመኪናውን ባለሃብት ወይም ጠባቂውን ጥቅም በልለው ግንኙነት መኖሩ ቢረጋገጥም ተጠያቂ ማድረግ የሚቻለው ባለሃብቱ ወይም ጠባቂው ጥፋት ካለባቸው ብቻ ነው። በድንጋጌው ስር ባለሃብት የሚለው ቃል ግልጽ ሲሆን ጠባቂ የሚለው ቃል ግን ግልጽነት የጎደለው መሆኑ የሚታመን ነው። በዚህ ረገድ በተጠሪ በኩል ለቃሉ እየቀረበ ያለው ክርክር ባይኖርም ተቀጣሪ ሹፍር ጠባቂ በሚለው ቃል የሚሸፈን ነው ወይስ አይደለም የሚለው የሕግ ጥያቄን ማየቱ ተገቢ ነው። ይሁን እንጂ የአማርኛው አቻ የእግላዘኛ ቃሉ ‘’holder’’ በሚል የተቀመጠ ሲሆን ይህ ቃል በሕግ መዝገበ ቃላት ከተሰጠው ትርጉም አንዱ a person who possesses or uses property በሚል የተቀመጠ መሆኑን ታዋቂው የብላክስ ሎው መዝገበ ቃላት ያሳያል። ከዚህም መገንዘብ የሚቻለው ጠባቂ የሚለው ቃል ለራሱ ጥቅም መኪናውን ይዞ የሚገኘውን ሰው መሆኑን ነው። ሹፍር በሰራው ምክንያት ላጠፋው ጥፋት ካልሆነ በስተቀር አሰሪው የመንግስት መስሪያ ቤት ወይም ባለሃብት ተጠያቂ የሚሆንበት አግባብ የልለ መሆኑን ተጠቃሹን ድንጋጌው ከፍ/ህ/ቁጥር 2126/2/፣2127፣2130 እና ከፍ/ሕ/ቁጥር 2131 ድንጋጌዎች ይዘት ጋር በማገናዘብ ስናነብ የምረዳው ጉዳይ ነው። የ1ኛ አመልካች ሹፍር የሆኑት 2ኛ አመልካች ስራውን ሲሰሩ የፈፀሙት ጥፋት የልለ ስለመሆኑ ወይም ጥፋቱ የ2ኛ አመልካች የግላቸው ስለመሆኑ 1ኛ አመልካች በፍ/ብ/ሕ/ቁጥር 2126/2/ እና 2127 ድንጋጌዎች አግባብ የማስረዳት ግድታውን አልተወጣም። ይልቁንም ከፍተኛ ጥንቃቄ ላደረግላቸው ከሚገባቸው የህብረተሰብ ክፍሎች መካከል የሆነውን የተጠሪ ልጅ ህፃን ደረጀ ማሞን በእቃ መጫኛው ላይ 2ኛ አመልካች በስራ ላይ እያሉ ጭነው ለህልፈት መዳረጋቸው በፍሬ ነገር ደረጃ ተረጋግጧል።
አንድ ባለሃብት ጥቅም በልለው ግንኙነት ለደረሰ ጉዳት ኃላፊነት የሚወስድበት ሕጋዊ አግባብ የልለ መሆኑን ይህ ችሎት በሰ/መ/ እና በልሎች በርካታ መዛግብት በአዋጅ ቁጥር 454/1997 አንቀጽ 2/1/ በየትኛውም እርከን የሚገኝ ፍ/ቤትን የሚያስገድድ የህግ ትርጉም የሰጠበት ጉዳይ ቢሆንም ይህ ጉዳይ ግን ከጉዳዩ ልዩ ባህርይ ላታይ የሚገባው ስለመሆኑ በክርክሩ ሂደት የተረጋገጡት ፍሬ ነገሮች የሚያስገነዝቡን ጉዳይ ሁኖ አግኝተናል።
በመሆኑም በሰ/መ/ የተሰጠው አስገዳጅ የሕግ ትርጉም በመሰረታዊ ፍሬ ነገሮች በዚህ መዝገብ ከተያዘው ጉዳይ ጋር የሚገኛኝ ሁኖ ስላልተገኘ ለውሳኔው መሰረት ለማድረግ የምንገደድበት ሁኖ አልተገኘም ምክያቱም ጉዳቱ የደረሰው ህፃን ላይ ከመሆኑም በላይ ከፍተኛ ጥንቃቄ ላደረግለት ለሚገባው ለዚህ ህፃን 2ኛ አመልካች በ1ኛ አመልካች ስራ ላይ እንዳሉ ባሉበትና ጥንቃቄ ሳያደርጉ በተሸከርካሪ እቃ መጫኛ ጭነው ሲጓዙ ለህልፈት የዳረጉት ስለመሆኑ በፍሬ ነገር ደረጃ የተረጋገጠ በመሆኑ በሰ/መ/ የተሰጠው አስገዳጅ የህግ ትርጉም በዚህ መዝገብ ከተያዘው ጉዳይ ጋር ሲነፃፀር ከተበዳዩም ሆነ በተበዳዩና በባለንብረቱ ከነበረው ግንኙነት ጋር የሚገናኝ አይደለምና ህፃናት በኢ.ፊ.ዲ/ሪ ሕገ መንግስት አንቀጽ 36/2/፣15 እና 25 ድንጋጌዎች እንዲሁም ኢትዮጵያ ተቀብላ ባፀደቀቻቸው አለም አቀፍ ስምምነቶም በሕፃናት መብቶች ስምምነት አንቀጽ 3፣ 6/1/ በአፍሪካ ህፃናት መብቶችና ደህንነት ቻርተር አንቀጽ 4/1/፣5/1/ ድንጋጌዎች በሕይወት የመኖርና የአካል ደህነት ጥበቃ የተደረገላቸው መሆኑ ግልጽ ስለሆነ የካሳ ክፍያ ጉዳይም እነዚህን ሕጎችን ሁሉ እግምት ውስጥ ማስገባት ያለበት ነው በእነዚህ ሁሉ ምክንያቶች አመልካቾች በተጠሪ ላይ ለደረሰው ጉዳት ኃላፊ የማይሆኑበት አግባብ የለም ሲጠቃለልም የሰር ፍ/ቤቶች በጉዳዩ ላይ የሰጡት ውሳኔ በውጤት ደረጃ ሲታይ መሰረታዊ የሕግ ስህተት ያለበት ነው ለማለት የሚቻል ሁኖ ስላላገኘነው ተከታዩን ወስነናል።
ሐምል 22 ቀን 2005 ዓ/ም ተሰጥቶ የነበረው እግድ ተነስቷል። ለሚመለከታቸው አካላት ይፃፍ።
No topics extracted.