No summary available.
መስከረም 22 ቀን 2006 ዓ.ም ዳኞች፡- ተሻገር ገ/ስላሴ አልማው ወል ዓላ መሐመድ ረታ ቶሎሣ ሙስጠፋ አህመድ አመልካች፡- አዋሽ ኢንሹራንስ ኩባንያ የቀረበ የለም ተጠሪዎች፡- 1ኛ. የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተክርስቲያን 2ኛ. የኢትዮጵያ መድን ድርጅት የቀረበ የለም መዝገቡ የተቀጠረው ለምርመራ ሲሆን፣ መርምረን የሚከተለውን ፍርድ ሰጥተናል።
ግራ ቀኙ በሥር ፍ/ቤቶች ባደረጉት ክርክር ከተረጋገጡት የፍሬ ነገር ጉዳዮች በመነሳት የአሁን 1ኛ ተጠሪ በመዳረግ ለቀረበው የጉዳት ካሣ ክስ ኃላፊነት አለበት ወይስ የለበትም? የሚለውን አከራካሪ ነጥብ እንደሚከተለው ተመልክተናል።
የአሁን አመልካች ለንብረት ጉዳት ካሣ መድን በመግባቱ ምክንያት የመድን ሽፋን የተሰጠው መኪና በሶስተኛ ወገን ተግባር ጉዳት ደርሶበታል በሚል በገባዉ የመድን ዋስትና ግድታ መሰረት በተጎዳው መኪና ባለቤት እግር ተተክቶ በመዳረግ ክስ የማቅረብ መብት ያለው መሆኑ ያከራከረ ጉዳይ አይደለም።
አከራካሪ ነጥብ ሆኖ የተገኘው በተጎጂው መኪና ባለቤት እግር ተተክቶ በመዳረግ የሚጠይቀውን የጉዳት ካሣ ገንዘብ መጠየቅ የሚችለው ከማን ነው? የሚለውን ነው።
በቀጥታም ሆነ በመዳረግ ሶስተኛ ወገን ተግባር ጥፋት ሳቢያ በደረሰ ጉዳት የጉዳት ገንዘብ ከማን ላይ መጠየቅ እንደሚቻል ጉዳዮን በቀጥታ በሚመለከተው አግባብነት ካለው የፍ/ብሕር ህግም ሆነ በአንድ ጉዳይ በተከሳሽነት መጨመር የሚገባቸው ወይም የሚችሉት ወገኖች እነማን እንደሆኑ በሚያመለክተው ስነ-ስርዓታዊ ህጐች በግልፅ ተመልክቷል። በእነዚህ መሰረታዊ ሆነ ሥነ-ስርዓታዊ ድንጋጌዎች መሰረት ከሳሽ የሆነው ወገን በክስ የሚጠይቀውን ገንዘብ አስተማማኝ በሆነ ሁኔታ ማግኘት እንዲችል እነማንን አጣምሮ መክሰስ እንደሚችል ከመደንገጉ በቀር በጉዳት ካሣ ክስ ምክንያት ላጠየቁ የሚችሉትን ወገኖች ሁሉ አጣምሮ መክሰስ እንዳለበት በህጉ ግድታ አልተጣለበትም። አጣምሮ መክሰስ የሚገባውን ሁሉ በቶሎ እና ክርክሩ በተነሣበት የዳኝነት አካል አጣምሮ ያለመክሰሱ ተግባር በማግኘትም ሆነ በማጣት ረገድ በእራሱ ላይ ጉዳት ከሚያስከትል በቀር በጉዳዩ ላይ የሚመለከታቸውን ሁሉ በአንድ ላይ በአንድ ፍ/ቤት አጣምሮ እንዲከስ በህግ የተጣለበት ግድታ የለም። በዚህም መሰረት የአሁን አመልካች የጉዳት አድራሹ መኪና ባለቤት ነው ባለው በአሁን 1ኛ ተከሳሽ ላይ ክስ አቅርቧል።
ይህ 1ኛ ተከሣሽም ጉዳት ያደረሰው መኪና ባለቤት ስለመሆኑ እንደ ህጉ አነጋገር የመኪናውን ባለቤትነት ማረጋገጫ ደብተር በማን ስም ተመዝግቦ እንደሚገኝ በማረጋገጥ የሥር ፍ/ቤቶች ያረጋገጡት ጉዳይ ነው። ይህም ከሆነ በፍ/ብ/ሕ/ቁ 1677፣1896 እና 2081ና በፍ/ብ/ስ/ስ/ሕ/ቁጥር 36/2/ መሰረት የአንድነትና የነጠላ ግድታ ካለባቸው ወገኖች መካከል የአሁን አመልካች በከሳሽነቱ የመኪናዉ ባለቤት ላይ ክስ የማቅረብ መብት ያለው በመሆኑና 1ኛ ተጠሪም በፍ/ብ/ሕ/ቁጥር 18 እና 2156 መሰረት ኃላፊነቱን በመጨረሻ በሚሸከመው ወገን ላይ በተራው ተተክቶ ክስ ከሚያቀርብ በቀር ልከሰስ አይገባም በማለት ለመከራከር ህጉ መብት አይሰጠውም።
ስለሆነም ይግባኝ ሰሚው ፍ/ቤት ጉዳዩን በይግባኝ ተመልክቶ ለዚህ ጉዳይ መነሻ በሆነው ክስ ላይ መጠቀስ ያለበት የመኪናው ባለቤት ማን ነው? የሚለው ሳይሆን ተሽከርካሪው ጉዳት በደረሰበት ጊዜ ለግል ጥቅሙ ሲገለገልበት የነበረው ማን ነው? የሚለው ነው። የአሁን 1ኛ ተጠሪ የመኪናው ባለቤት መሆኑ ቢረጋገጥም ከሳሽ ይህንኑ 1ኛ ተጠሪን ለመክሰስ ከህግ የመነጨ መብት የለውም የሚለውን ትርጉም በመከተል የሰጠው የመጨረሻ ፍርድ ከዚህ በላይ በፍርድ ሐተታው ከተገለፀው ህጋዊ ምክንያት አንፃር ሲታይ መሰረታዊ የሆነ የህግ ስህተት የተፈፀመበት ሆኖ ስላገኘነው የሚከተለውን ውሣኔ ሰጥተናል።
ው ሣ ኔ
ይግባኝ ሰሚው የፍድራሉ ከፍተኛ ፍ/ቤትም ሆነ የመጀመሪያ ደረጃ ፍ/ቤቱ እንደቅደም ተከተሉ በኮ/መ/ ጥር 15 ቀን 2005 ዓ.ም እና በኮ/መ/ ግንቦት 30 ቀን 2004 ዓ.ም የሰጡት ፍርዶች ሁሉ ተሽረዋል።
የአሁን 1ኛ ተጠሪ የሰ/ቁ 5-01-00002 አ.አ የሆነው ተሽከርካሪ ባለቤት በመሆኑ ምክንያት ብቻ ለቀረበበት የጉዳት ካሣ ገንዘብ ክስ ከህጉ የመነጨ የመካስ ኃላፊነት አለበት ብለናል። ስለሆነም የመካስ ኃላፊነት ያለበት መሆኑ ታውቆ በልላው የኃላፊነት ነክ ክርክሩ ረገድ ማለትም ጥፋት አለ የለም? ጉዳት ደርሷል አልደረሰም? የጉዳት ልክስ ምን ያህል ነው በሚል በፍሬ ነገር ክርክር ደረጃ የተነሣ ክርክር ካለ በስር ፍ/ቤት በአቤቱታ ፅሑፍ አቀራረብ የክርክር ደረጃ አንስቶ ከተከራከረበት ነጥብ አንፃር በማየት ጉዳዩ ታይቶ ይወሰን ዘንድ በፍ/ብ/ስ/ስ/ህ/ቁጥር 341 መሰረት ጉዳዩን ወደ መጀመሪያ ደረጃ ፍ/ቤት መልሰናል።
No topics extracted.
በዚህ ሰበር ደረጃ የተደረገው ክርክር ላስከተለው ወጭና ኪሣራ ግራ ቀኙ የየራሳቸውን ይቻሉ።