No summary available.
መስከረም 20 ቀን 2006 ዓ.ም.
ዳኞች- ተሻገር ገብረሥላሴ አልማው ወል ዓላ መሐመድ ረታ ቶሎሳ ሙስጠፋ አህመድ አመልካች፡- አቶ ሻፊ አብዱራህማን አብዱ - ቀረቡ ተጠሪ፡-
ጉዳዩ የቀረበው አመልካች የኦሮሚያ ክልል ምዕራብ ሸዋ ዞን ከፍተኛ ፍርድ ቤት፣ የክልሉ ጠቅላይ ፍርድ ቤት ይግባኝ ሰሚ ችሎትና የሰበር ሰሚ ችሎት የሰጡት ውሳኔ መሰረታዊ የህግ ስህተት ያለበት ስለሆነ በሰበር ታይቶ ይታረምልኝ በማለት ያቀረቡትን የሰበር አቤቱታ አጣርቶ ለመወሰን ነው። ጉዳዩ በመጀመሪያ የታየው በኢሉ ገላን ወረዳ ፍ/ቤት ነው። ጉዳዩ የማይንቀሳቀስ ንብረት ለመፋለም የቀረበን ክርክር የሚመለከት ነው።
የክርክሩ መነሻ አመልካች በሥር ፍርድ ቤት በከሳሽነት ቀርበው በአጃጂ ከተማ ውስጥ ቁጥሩ 858 እና ቁጥሩ 859 የሆነ ቤት አለኝ። በእነዚህ ቤቶች ከዚህ በፊት የእህል ንግድ ሳከናውንባቸው ቆይቼ ኪሳራ ስለደረሰብኝ ቤቶቹን ዘግቼ ሥራ ፍለጋ ልላ ቦታ ሄጄ ቆይቻለሁ። በዚህ ወቅት የተዘጉትን ቤቶች ቀበልው በመክፈት ለልሎች ሰዎች ሲያከራየው ቆይቷል። እኔም ከሄድኩበት ተመልሼ ቤቴ እንዲለቀቅልኝ ስጠይቅ ከተማው አስተዳደር በጽሁፍ ውሳኔ ሰጥቷል። የቀበልው አስተዳደርም ለተከራዮቹ(ተጠሪዎች) በጽሁፍ አሳውቋል። ተከሳሾችም ቤቱን ለእኔ ኪራይ እየከፈሉ ለመኖር ጠይቀውኝ በወር ብር 5 (አምስት ብር) አከራይቻቸዋለሁ። እኔም የቤቱን ግብር ያለማቋረጥ እየከፈልኩ እገኛለሁ። ሆኖም በማላውቀው ሁኔታ ከ2002 ዓ/ም ጀምሮ የቀበልው አስተዳደር ቤት ኪራይ ከተከራዮች እየተቀበለ በመሆኑና ተከሳሾች ቤቱን እንዲለቁ ፈቃደኛ ባለመሆናቸው ቀበልው የቤት ኪራይ መቀበሉን እንዲያቆምና ተከሳሾች ቤቱን እንዲያስረክቡኝ ውሳኔ ይሰጥልኝ በማለት ያቀረበው የክስ ማመልከቻ ነው። አመልካች በሥር ፍርድ ቤት ተጅ ቀበል 01 በአንደኛ ተከሳሽነት ቀርቦ ቤቱ በደርግ ጊዜ የተወረሰ ነው። የከሳሽ ንብረት አይደለም በማለት ተከራክሯል። ተጠሪዎችም(ተከሳሾች) ቤቱ መንግስት ወርሶን ያከራየንና ለረዥም ጊዜ በእጃችን የቆየ ነው። ክሱ በይርጋ ይታገዳል፣ ጉዳዩን ለማየት ፍርድ ቤቱ ሥልጣን የለውም በማለት ተከራክረዋል።
የሥር ፍ/ቤት የግራ ቀኙን ክርክርና ማስረጃ ከሰማና ከመረመረ በኋላ የአምቦ ከተማ አስተዳደር ክስ የቀረበባቸውን ቁጥራቸው 858 እና 859 የሆኑ ቤቶች ቀበልው አላግባብ የያዘባቸው መሆኑን በማረጋገጥ ቤቱ እንዲለቀቅ ደብዳቤ ጽፏል። የቀበልው አስተዳደርም ተከራዮቹ ቤቱን ለከሳሽ እንዲለቁ በማለት በደብዳቤ አሳውቋል። ከዚህ በኋላ ተከሳሾች ቤቱን ከከሳሽ ፈቃድ ውጭ የሚይዙበት የህግ መሰረት የልለ በመሆኑ ቤቱን ለቅቀው ለከሳሽ እንዲያስረክቡ በማለት ውሳኔ ሰጥቷል። በዚህ ውሳኔ ተጠሪዎች ቅር በመሰኘት ይግባኝ ምዕራብ ሸዋ ዞን ከፍተኛ ፍርድ ቤት አቅርቧል። የዞኑ ከፍተኛ ፍ/ቤት የግራ ቀኙን ክርክር ከሰማ በኋላ ከሕግ ውጭ የተወረሱ ቤቶች መዳኘት ሥልጣን ያለው ፍርድ ቤት አይደለም።
የወረዳው ፍ/ቤት ጉዳዩን የማየት የዳኝነት ሥልጣን የለውም በማለት ወስኗል። ይህ ውሳኔ በክልሉ ጠቅላይ ፍ/ቤት ይግባኝ ሰሚ ችሎትና የሰበር ችሎት ጸንቷል።
ቤቶቹን ደርግ ሥልጣን ከያዘ በኋላ የእህል ንግድ ሳከናውንባቸው የነበሩ የግል ንብረቶች መሆናቸውንና የንግድ ኪሳራ ሲደርስብኝ ዘግቼ ወደልላ ቦታ በመሄድ ቀበልው ከፍቶ ሲያከራያቸው የነበሩ መሆናቸውን በአስተዳደሩ ክፍል ተረጋግጧል። ይህም በመሆኑ እኔ ያቀረብኩት የመፋለም ክስ በመሆኑ ጉዳዩን የማየት ሥልጣን ያለው ፍርድ ቤት ሆኖ እያለ፤ የዞኑ ከፍተኛ ፍ/ቤት፣ የኦሮሚያ ክልል ጠቅላይ ፍ/ቤት ይግባኝ ሰሚው ችሎትና የሰበር ችሎት ጉዳዩን ለማየት ፍርድ ቤቶች ሥልጣን የላቸውም በማለት የሰጡት ውሳኔ መሰረታዊ የህግ ስህተት ያለበት ስለሆነ በሰበር ታይቶ እንዲታረምልኝ በማለት አመልክተዋል። ተጠሪ በ11/06/2005ዓ.ም በተፃፈ መልስ ቤቱ በመንግስት የተወረሰ ሥለሆነ አመልካች አላግባብ ተወርሶብኛል የሚል ከሆነ ለፕራይቬታይዜሽን ኤጅነሲ ያቅርቡ በማለት የዞኑ ከፍተኛ ፍ/ቤት፣ የኦሮሚያ ክልል ጠቅላይ ፍ/ቤት ይግባኝ ሰሚው ችሎትና የሰበር ችሎት የሰጡት ውሳኔ መሰረታዊ የህግ ስህተት የለበትም በማለት ተከራክረዋል። አመልካች በ28/06/2005 ዓ.ም በተፃፈ የመልስ መልስ አቅርቧል።
No topics extracted.
ከሥር የክርክሩ አመጣጥና በሰበር የቀረበው ክርክር ከላይ የተገለፀው ሲሆን እኛም የኦሮሚያ ክልል የምዕራብ ሸዋ ዞን ከፍተኛ ፍ/ቤት የክልሉ ጠቅላይ ፍ/ቤት ይግባኝ ሰሚ ችሎትና የሰበር ሰሚ ችሎት ጉዳዩን ለማየት ፍ/ቤቶች ሥልጣን የላቸውም በማለት የሰጡት ውሳኔ ተገቢ መሆን ያለመሆኑን በጭብጥነት በመያዝ ጉዳዩን መርምረናል።
ከላይ የተያዘውን ጭብጥ ለመወሰን በመጀመሪያ አመልካች ለሥር ፍ/ቤት ያቀረቡትን የዳኝነት ጥያቄ መሰረታዊ ባህሪና ይዘት መመርመር አስፈላጊ ነው። አመልካች እንዲለቀቁለት የሚጠይቃቸው ቤቶች በአዋጅ ቁጥር 47/1967 መሰረት በትርፍነት ያልተወረሰና ከአዋጅ ቁጥር 47/1967 በኋላ በእሱ እጅ የነበሩና የእህል ንግድ ሲያከናውንባቸው የነበሩ መሆናቸውን በክሱ የገለጸ መሆኑን ከስር ፍ/ቤት ውሳኔ ተረድተናል። በልላ በኩል አመልካች ቤቶቹ ከአዋጅ ቁጥር 47/1967 ውጭ በባለስልጣን ቃል ትዕዛዝ ወይም በቀላጤ ያልተወረሱ መሆኑና አመልካች በሚነግድበት ወቅት ስለከሰረና ቤቶቹን ዘግቶ አካባቢውን ለቆ ለረዥም ጊዜ በመጥፋቱ የቀበልው አስተዳደር ቤቶቹን ከፍቶ ማስተዳደርና ለልሎች ሰዎች ማከራየት የጀመረ መሆኑን በክሳቸው ገልፀዋል።
ይህ አመልካች በዚህ ክርክር ተሳታፊ ያልሆነው ተጅ ቀበል 01 ቀበል ቤቶቹን የያዘውና ማስተዳደር የጀመረው በአዋጅ ቁጥር 47/1967 ተወርሰው ወይም ከአዋጅ ውጭ በባለስልጣን ቃል ትዕዛዝ ወይም በቀላጤ ሳይሆን የቤቶቹ ባለቤት በመጥፋቱና ቤቶቹ ተዘግተው ረዥም ጊዜ በመቆየታቸው በፍ/ብሕር ሕግ ቁጥር 2257 እና ተከታይ ድንጋጌዎች መሰረት የስራ አመራር ተግባር ለመፈፀም በወሰደው እርምጃ ነው የሚል ይዘት ያለው ነው። አመልካች በማስረጃነት ያቀረባቸውና አንቦ ከተማ አስተዳደርና ቀበልው አስተዳደር የጻፏቸው ደብዳቤዎች ይህንን የአመልካችን ክስ ባህሪና ይዘት የሚመለከቱ ናቸው።
በጥቅሉ ሲታይ አመልካች ክስ ያቀረበው በአዋጅ የተወረሰ ቤት ለማስመለስ ወይም ከአዋጅ ውጭ በባለስልጣን ቃል ትዕዛዝ ወይም በቀላጤ የተወሰደባቸውን ቤት ለማስመለስ አይደለም። አመልካች ክስ ያቀረበው በቤቶቹ ላይ ያለውን የባለሃብትነት መብት ለማስከበርና ለመፋለም ነው። ይህንን አይቶ የመወሰን ሥልጣን ያላቸው ፍ/ቤቶች እንጅ የፕራይቬታይዜሽን ኤጅንሲ ወይም ልላ አካል አይደለም።
የኦሮሚያ ክልል የምዕራብ ሸዋ ዞን ከፍተኛ ፍ/ቤት የክልሉ ጠቅላይ ፍ/ቤት ይግባኝ ሰሚ ችሎትና የሰበር ሰሚ ችሎት ጉዳዩን ለማየት ፍ/ቤቶች ሥልጣን የላቸውም በማለት የሰጡት ውሳኔ መሰረታዊ የህግ ስህተት አለበት በማለት ወስነናል።
የኦሮሚያ ክልል የምዕራብ ሸዋ ዞን ከፍተኛ ፍ/ቤት፣ የክልሉ ጠቅላይ ፍ/ቤት ይግባኝ ሰሚ ችሎትና የሰበር ሰሚ ችሎት ጉዳዩን ለማየት ፍ/ቤቶች ሥልጣን የላቸውም በማለት የሰጡት ውሳኔ ተሽሯል።
የምዕራብ ሸዋ ዞን ከፍተኛ ፍ/ቤት፣ ተጠሪዎች ያቀረቡትን ይግባኝና አመልካች የሰጠውን መልስ በመመርመር በዋናው ጉዳይ ላይ ውሳኔ እንዲሰጥበት ጉዳዩን በፍ/ስ/ስ/ሕግ ቁጥር 341(1) መሰረት ጉዳዩን መልሰን ልከንለታል።
በዚህ ችሎት ያወጡትን ወጭና ኪሳራ ግራ ቀኙ ለየራሳቸው ይቻሉ በማለት ወስነናል።
መዝገቡ ወደ መዝገብ ቤት ይመለስ