No summary available.
የካቲት 12 ቀን 2005 ዓ.ም.
ዳኞች፡- ተሻገር ገ/ሥላሴ አልማው ወል ዓላ መሐመድ አዳነ ንጉሴ ሙስጠፋ አህመድ አመልካች፡- ጽናት የሆቴል ቱሪዝም ስራዎች ኃ.የተ.የግል ማህበር -ጠበቃ ኃ/ማሪያም ተመስገን ቀረቡ።
ተጠሪ፡-
አቶ ዳመነ ነጋ
አቶ አሰበ ፈቃዱ
አቶ ሱልጣን በደዊ - ጠበቃ በለጠ ጉራራ ቀረቡ።
አቶ አበራ አመንሲሳ
ወ/ት አለምፀሐይ ሰለሞን **
መዝገቡ ተመርምሮ ተከታዩ ፍርድ ተሰጥቷል።
**
ጉዳዩ የሁከት ይወገድልኝ ክስን መሰረት አድርጎ የቀረበውን በተከራይነት የተገኘ የንብረት ይዞታ ይልቀቅልኝ ጥያቄን የሚመለከት ነው። ክርክሩ የተጀመረው የአሁኑ አመልካች ባሀኑ ተጠሪዎች ላይ በፍድራሉ መጀመሪያ ደረጃ ፍርደ ቤት በመሰረተው ክስ መነሻ ነው።የአመልካች ክስ ይዘትም በአዲስ ከተማ ክፍለ ከተማ በወረዳ 5 ክልል ውስጥ የሚገኘውና ቁጥሩ 169 የሆነው ቤት ከሰላሳ ዘጠኝ ክፍሎች እና ከሁለት ሰርቪስ ቤቶች ጋር በ10/09/2003 ዓ/ም በተፈጸመ የኪራይ ውል ከመንግስት ቤቶች ተረክቦ ባለበት ሁኔታ ተጠሪዎች ምንም ሕጋዊ መብት ሳይኖራቸው እያንዳንዳቸው አንድ አንድ ክፍል በመያዝ ጨርቃ ጨርቅ በመያዝ እየነገዱ እንደሚገኙ ገልፆ በዚህ አድራጎታቸው ሁከት የተፈጠረበት ስለመሆኑ ጠቅሶ ሁከቱ እንዲወገድለትና ክፍሎቹ እንዲለቀቁለት ዳኝነት መጠየቁን የሚያሳይ ነው።ተጠሪዎች ለክሱ በሰጡት መከላከያ መልስም ጉዳዩን የመንግስት ቤቶች ኤጂንሲ በመመሪያው መሰረት እየተመለከተው መሆኑን ጠቅሰው ፍርድ ቤቱ ስልጣን የለውም፣አመልካችም በክፍሎቹ ላይ ክስ ለማቅረብ መብት ወይም ጥቅም የለውም ሲሉ ተከራክረዋል።ጉዳዩን በመጀመሪያ ደረጃ የተመለከተው ፍርድ ቤትም ግራ ቀኙኝ አከራክሮ አመልካች ከመንስት ቤቶች ኤጀንሲ ንብረቱን በወርሃዊ የኪራይ ገንዘብ ብር 40,000.00 ተከራይቶ ለተጠሪዎች ደግሞ ክርክር ያስነሱትን ክፍሎች እያንዳንዳቸውን በብር 15,000.00 ወርሃዊ የኪራይ ገንዘብ በማከራየት ጥቅም እያገኘበት መሆኑን የአመልካች ጠበቃ በክርክሩ ወቅት ማረጋገጣቸው፣ተጠሪዎች ወርሃዊ ኪራዩን ለመንግስት ቤቶች ኤጂንሲ እየከፈሉ እንደሚገኙ ገልጾና መመሪያው ሲወጣ ደግሞ አመልካች ተጠሪዎች ሁከት ፈጥረዋል ብሎ ክስ ማቅረቡ የመመሪያው አፈጻጸም እንዳይነካው በማሰብ ምክንያት ነው የሚሉትን ነጥቦችን በምክያትነት ይዞ ጉዳዩን ፍርድ ቤት ጣልቃ ገብቶ የሚዳኘው አይደለም በማለት እና የፍ/ብ/ሥ/ሥ/ሕ/ቁጥር 231 ድንጋጌን በዋቢነት ጠቅሶ ክሱን ውድቅ አድርጎታል።በዚህ ብይን አመልካች ቅር በመሰኘት ይግባኙን ለፍድራሉ ከፍተኛ ፍርድ ቤት ቢያቀርብም ይግባኙ በፍ/ብ/ሥ/ሥ/ሕ/ቁጥር 337 መሰረት ተሰርዞበታል።የአሁኑ የሰበር አቤቱታ የቀረበውም ይህንኑ ውሳኔ በመቃወም ለማስለወጥ ነው።የአመልካች የሰበር አቤቱታ መሰረታዊ ይዘትም ተጠሪዎች ክፍሎችን የያዙበትን አግባብ በተመለከተ የመንግስት ቤቶች ኤጀንሲ ባወጣው መመሪያ የማይሸፈን ስለመሆኑ በኤጂንሲው የተረጋገጠ ሁኖ እያለ የበታች ፍርድ ቤቶች የአመልካችን ማስረጃዎችን በአግባቡ ሳይሰሙና የጉዳዩን ክርክር በስርዓቱ መሰርት ሳይመሩ ውሳኔ መስጠታቸው ያላግባብ ነው የሚል ነው።አቤቱታው ተመርምሮም የአመልካች የሁከት ይወገድልኝ ክስ ውድቅ የመደረጉን አግባብነት ለመመርመር ሲባል ጉዳዩ ለሰበር ሰሚ ችሎት ያስቀርባል የተባለ ሲሆን ለተጠሪዎች ጥሪ ተደርጎላቸው ቀርበውም ክፍሎችን ከአመልካች የተከራይ አከራይ ሁኖ ተጠሪዎች ተከራይተው ይዘው ሲጠቀሙ እንደነበርና በመመሪያው መሰረትም የመንግስት ቤቶች ከተጠሪዎች ጋር የኪራይ ግንኙነት እንዲቀጥል በማድረግ ሲጠቀሙ መቆየታቸውን፣የመንግስት ቤቶች ኤጂንሲ ጉዳዩ በመመሪያው እንደማይሸፈን የገለፀበት ሁኔታ ተገቢነት የልለው መሆኑንና ባሁኑ ጊዜ ከመንግስት ቤቶች ኤጂንሰ ጋር በክርክር እንደሚገኙ ገልጸው የበታች ፍርድ ቤቶች ብይን መሰረታዊ የሆነ የሕግ ስህተት የለውም ሲሉ ተከራክረዋል።አመልካችም የሰበር አቤቱታውን በማጠናከር ተከራክሯል።
የጉዳዩ አመጣጥ አጠር አጠር ባለ መልኩ ከላይ የተገለፀው ሲሆን ይህ ችሎትም የግራ ቀኙን ክርክር ለሰበር አቤቱታው መነሻ ከሆነው ብይንና አግባብነት ካላቸው ድንጋጌዎች ጋር በማገናዘብ ጉዳዩን በሚከተለው መልኩ መርምሮታል።እንደመረመረውም የአመልካች የሁከት ይወገድልኝ ክስ ውድቅ ተደርጎ የተሰጠው ብይን ውጤቱ ሲታይ መሰረታዊ የሆነ የሕግ ስህተት ያለበት ነው ለማለት ይቻላል ወይስ አይቻልም የሚለው ነጥብ በጭብጥነት ላታይ የሚገባው ሁኖ ተገኝቷል።
ከክርክሩ ሂደት መገንዘብ የተቻለው አመልካች ተጠሪዎች ላይ የሁከት ይወገድልኝ ክስ የመሰረተው አመልካች ከመንግስት ቤቶች ኤጂንሲ የተከራየውን ቤት ተጠሪዎች ምንም መብት ሳይኖራቸው ይዘው ይገኛሉ በሚል ምክንያት መሆኑን፣ተጠሪዎች በበኩላች ክፍሎችን የያዙት ከአመልካች ጋር የኪራይ ውል አድርገው መሆኑን፣የመንግስት ቤቶች ኤጀንሲ መመሪያ ሲያወጣ ደግሞ ከአመልካች ጋር ያላቸው ግንኙነት ተቋርጦ የኪራይ ገንዘቡን ለቤቱ ባለቤት እየከፈሉ እንዲቀጥሉ መደረጉን በመግለፅ የተፈጠረ ሁከት የለም ሲሉ መከራከራቸውን ነው።የፍድራሉ መጀመሪያ ደረጃ ፍርድ ቤት ክርክሩን በሰማበት ወቅት የአመልካች ጠበቃ ለተጠሪዎች ክፍሎችን አመልካች አከራይቶ በወር ብር 15,000.00 ከእያንዳንዳቸው እንደሚሰብሰብና ከመንግስት ቤቶች ቤቱን ከተከራየበት ጠቅላላ ወርሃዊ ገንዘብ ብር 40,000.00(አርባ ሺኅ ብር) በላይ ብር 35,000.00(ሰላሳ አምስት ሺኅ) ማግኘቱንና ልሎች ክፍሎችን ይዞ በመጠቀም ላይ መሆኑን በፍሬ ነገር ደረጃ ያረጋገጠው ጉዳይ ሲሆነ ይህንኑ ፍሬ ነገር ይግባኝ ሰሚው ፍርድ ቤትም ተቀብሎታል።አመልካቾች ይህንኑ ፍሬ ነገር ፍርድ ቤቱ ገለልተኛ ሁኖ ጉዳዩን አልተመለከተም ከሚሉ በስተቀር በግል የሚክዱት ጉዳይ አለመሆኑን ከክርክሩ ሂደት መገንዘብ ተችሐል።እንግዲህ ፍሬ ነገርን የማጣራትና ማስረጃን የመመዘን ስልጣን ያላቸው ፍርድ ቤቶች ያረጋገጧቸው ነጥቦች ከላይ የተመለከቱት ከሆነ ይህ ችሎት እነዚህን ፍሬ ነገሮች የሚለውጥበት አግባብ የልለ መሆኑን ከኢ.ፍ.ዲ.ሪ ሕግ መነግስት አንቀፅ 80(3(ሀ))እና አዋጅ ቁጥር 25/1988 አንቀጽ 10 ድንጋጌዎች ይዘትና መንፈስ የምንገነዘበው ጉዳይ ነው።በመሆኑም እንዚህን ፍሬ ነገሮችን ይዘን በጉዳዩ ላይ የበታች ፍርድ ቤቶች ላሰጡ ይገባ የነበረውን ዳኝነት አይነት እና የበታች ፍርድ ቤቶችን ብይን ውጤት ተገቢነት ተመልክተናል።ይህንኑ ለይቶ ለመደምደምም በአመልካች የተጠየቀውን ዳኝነት አይነትና የዳኝነት አሰጣጥ ስርዓትን መመልከቱ ተገቢ ነው።
በመሰረቱ አመልካች በስር ፍርድ ቤት እንዲሰጠው የጠየቀው ዳኝነት በተጠሪዎች የተፈጠረው ሁከት እንዲወገድለት ነው።ተጠሪዎች ደግሞ ይዞታውን በሕግ አግባብ የያዙት ስለመሆኑ ጠቅሰው የአመልካችን ክስ ክደዋል።ስለሆነም የስር ፍርድ ቤት በጭብጥነት ላመለከተው ይገባ የነበረው መሰረታዊ ነጥብ ሁከት? አለ ወይስ የለም? የሚለው ነው። ይህ የጭብጥ አመራረት ከፍ/ብ/ሥ/ሥ/ሕ/ቁጥር 246 እስከ 248 ስር የተመለከቱትን ድንጋጌዎችን ያገናበዘ ሲሆን ዳኝነቱ መሰጠት ያለበት በከሳሽ በተጠየቀው መሰረት ስለመሆኑ በፍ/ብ/ሥ/ሥ/ሕ/ቁጥር 182(1) ድንጋጌ ከተቀምጠው መርህ ጋርም የተጣጣመ ይሆናል።ይህንኑ ጭብጥ ለመፍታት ደግሞ ስለሁከት የተደነገጉትን የፍትሐ ብሕር ሕጋችን ድንጋጌዎችን ይዘትና መንፍስ በክርክሩ ሂደት ከተረጋገጡት ፍሬ ነገሮች ጋር በማገናዘብ መመልከትን የግድ ይላል።
በመሰረቱ የአንድ ንብረት ባለይዞታ የሆነ ሰው ይዞታውን ለመንጠቅ ወይም በይዞታው ላይ ሁከት ለመፍጠር የሚፈፀምን ማንኛውንም ድርጊት እንዲቆም ወይም ንብረቱ እንዲመለስለት ህጉ ከጠበቀላቸው መንገዶች አንዱ አማራጭ የይዞታ ክስ ማቅረብ ስለመሆኑ የፍ/ሕ/ቁ. 1149/1/ ድንጋጌ ያሣያል። በዚሁ ድንጋጌ መሰረት የሁከት ይወገድልኝ ክስ መቅረብ የሚችለው አቤቱታ አቅራቢው ለክርክሩ መነሻ በሆነው ነገር በቀጥታ ወይም በጠባቂ ይዞታ ሲኖረው ነው። እንዲሁም የይዞታ ክስ የሚቀርበው ለክርክሩ መነሻ የሆነውን ንብረት በወቅቱ ለመያዝ ምንም ዓይነት መብት በልለው ሰው ላይ ስለመሆኑም የድንጋጌው መንፈስ ያስረዳል። የሁከት ይወገድልኝ አቤቱታ አቅራቢ በማስረጃ ማረጋገጥ ያለበት ንብረቱ በይዞታው ስር የነበረና የሁከት ድርጊት ፈፃሚው የኃይል ተግባር በመቀጠም ወይም በሚስጢር ንብረቱን የወሰደበት መሆኑን ነው። ሁከት መፍጠር የሚኖረው ባለይዞታ የሆነው ሰው በይዞታው ስር በሚገኘው ንብረት እንዳይገለገልበት ልላ ሰው ጣልቃ ገብቶበት መሰናክል ሲፈጥርበት ወይም ረብሻ ሲፈጥርበት ነው።
እንግዲህ የሁከት መፍጠር ድርጊት አጠቃላይ ትርጓሜና ይዘቱ ከላይ የተመለከተው ስለመሆኑ ከፍ/ህ/ቁ. 1140 እና 1149 ድንግጌዎች ይዘት የምንገነዘበው ጉዳይ ነው። በዚህም መሰረት የሁከት የወገድልኝ ክስ የሚያቀርበው ሰው ንብረቱ በእርሱ ግልጽ ቁጥጥር ስር መሆኑንና በዚህ ንብረት እንዳይገለገልበት ተከሣሹ ረብሻ የተነሣበት ወይም መሰናክል የተፈጠረበት ስለመሆኑ በማስረጃ የማስረዳት ሽክም አለበት። በልላ አገላለጽ የሁከት ይወገድልኝ ክስ አቅራቢ የተሻለ የይዞታ መብት ያለው ስለመሆኑ ማሣየት ይጠበቅበታል።
በተያዘው ጉዳይ ለክርክሩ መነሻ የሆኑትን ክፍሎች አመልካች ከመንግስት ቤቶች ኤጂንሲ ባገኙት የተከራይነት መብት በቁጥጥር ስር አድርጎ ላጠቀምበት ከተከራየ በኋላ ለተጠሪዎች ያከራየ መሆኑ ተረጋግጧል።የመንግስት ቤቶች ኤጂንሲም ጉዳዩን አጣርቶም የኪራይ ውሉን ተጠሪዎች ከመንግስት ቤቶች ጋር እንዲቀጥሉ ወስኖ የነበረ መሆኑና በኃላ ግን ጉዳዩ በፍርድ ቤት የተያዘ ነው በሚል ምክንያት ጉዳየ በመመሪያው እንደማይሸፈን እና ኪራዩም እንደገና ከአመልካች ጋር እንዲቀጥል በማለት ደብዳቤ መፀፉን፣ተጠሪዎች ደግሞ የመንግስት ቤቶችን እርምጃ ተቃውመው በፍርድ ቤት በልላ መዝገብ ክርክር ላይ እንደሚገኙ የክርክሩ ሂደት የሚያሳይ መሆኑን ነው።ከዚህ መገገንዘብ የሚቻለው የአከራካሪ ክፍሎች ሕጋዊ ተከራይ ማን ነው? ወደፊት ሕጋዊ ተከራይ ሁኖ መቀጠል ያለበት አመልካች ነው ወይስ ተጠሪዎች ናቸው? የሚሉት ነጥቦች ከሚታዩ በስተቀር አመልካች ተጠሪዎችን በራሱ ተነሳሽነት አከራይቶ ቆይቶ የሁከት ተግባር ፈጥረዋል ብሎ ክስ የሚያቀርብበት አግባብ የለም።ተጠሪዎች በኃይል ተግባር የአመልካችን ይዞታ እስካልያዙ ድረስ ክርከሩ የሁከት ይወገድልኝ ክስን መሰረት አድርጎ የሚታይበት አግባብ የለም።በልላ አነጋገር የሁከት ይወገድልኝ ክስ ለማቅረብ የሚቻለውና መብቱ የሚከበረው የተሻለ የይዞታ መብት በማሣየት ነው።እንዲሁም የሁከት ይወገድልኝ ክስ የሚያቀርብ ወገን የሚጠይቀው ዳኝንት የሁከት አድራጐት እንዲቆም በይዞታው ስር የነበረው ንብረት ላያስገኝለት የነበረውን ጥቅም በኪሣራ መልክ እንዲከፈለው ሲሆን በህጉ አግባብ የተፈፀመ የኪራይ ውል አለመኖሩን ተከትሎ የሚቀርበው ጥያቄ ግን ውጤቱ ከሁከት ይወገድልኝ ጥያቄ ጋር ተመሣሣይነት የለውም።በመሆኑም በሁከት ይወገድልኝ ክስ ሕጋዊ ተከራይ ማን ነው የሚለው ጥያቄ ተነስቶ ዳኝነት የሚሰጥበት ሁኔታ ስለመኖሩ መሰረታዊውም ሆነ የስነ ስርአት ህግ ድንጋጌዎችን አያመላክቱም።
በአጠቃላይ አመልካች ለክርክሩ መነሻ የሆኑት ክፍሎች ለተጠሪዎች አከራይቶ ቆይቶ ለተጠሪዎች የቤቱ ሕጋዊ ባለቤት የተከራይነት መብት ሲያስተላልፍ ሁከት ፈጥረዋል በማለት የሚያቀርበው ክርክር የፍ/ብ/ሕ/ቁጥር 1140 እና 1149 ድንጋዎችን ይዘትና መንፈስ ያላገናዘበ ነው።በመሆኑም የስር ፍርድ ቤቶች ጉዳዩን በዚህ አግባብ ማየትና ዳኝነት መስጠት እየተገባው ጉዳዩ በአዋጅ ቁጥር 555/2000 መሰረት በመንግስት ቤቶች ኤጂንሲ ታይቶ እልባት የሚሰጥበት እንጂ ፍርድ ቤት ጣልቃ የሚገባበት ነው በማለት የሰጠው የምክንያት ክፍል የተጠቃሹን አዋጅ ድንጋጌዎች ይዘትና መንፈስ ከፍርድ ቤት ስልጣን አድማስ ጋር ያላገናዘበ ቢሆንም ክሱን ውድቅ ማድረጉ ግን በውጤት ደረጃ ሲታይ መሰረታዊ የሆነ የሕግ ስህተት የተፈፀመበት ነው ለማለት የሚቻል ሁኖ አልተገኘም።በዚህም ምክንያት ተከታዩን ወስነናል።
ው ሣ ኔ
በፍድራሉ መጀመሪያ ደረጃ ፍርድ ቤት በመ/ መጋቢት 13 ቀን 2004 ዓ/ም ተሰጥቶ በፍድራሉ ከፍተኛ ፍርድ ቤት በመ/ ሚያዚያ 11 ቀን 2004 ዓ/ም በትእዛዝ የጸናው ብይን በተለወጠ ምክንያት ውጤቱ በፍ/ብ/ሥ/ሥ/ሕ/ቁ. 348/1/ መሰረት ጸንቷል።
አመልካች ለተጠሪዎች ክፍሎችን በኪራይ ከአከራየ ከአስተላለፈ በኋላ ተጠሪዎች ሁከት ፈጥረዋል ብሎ ክስ ማቅረቡ ስለ ሁከት ይወገድልኝ የተደነገጉትን ድንጋጌዎችን ይዘትና መንፈስ ያላገናዘበ በመሆኑ ተጠሪዎች በአመልካች ላይ የፈጠሩት ሁከት የለም ብለናል።
አመልካች በልላ አግባብ መብቱን ለማስከበር ይህ ውሳኔ አያግደውም ብለናል።
በዚህ ችሎት ለተደረገው ክርክር ወጪና ኪሣራ የየራሣቸውን ይቻሉ ብለናል።
No topics extracted.