No summary available.
ሐምል 18 ቀን 2005 ዓ.ም.
ዳኞች፡ አልማው ወል ዓላ መሐመድ ረታ ቶሎሳ አዳነ ንጉሴ ሙስጠፋ አህመድ አመልካች፡- አቶ ሙሉ አብርሃ ገ/ሕይወት ጠበቃ ብናልፈው ነጋ ቀረቡ ተጠሪ፡-
መዝገቡ ተመርምሮ ተከታዩ ፍርድ ተሰጥቷል።
**
ጉዳዩ የሁከት ይወገድልኝ ጥያቄን የሚመለከት ሲሆን ክርክሩ የተጀመረው የአሁኑ አመልካች ባሁኑ ተጠሪዎች ላይ በፍድራሉ መጀመሪያ ደረጃ ፍርድ ቤት በመሰረቱት ክስ መነሻ ነው።የክሱ ይዘትም አመልካች በአዲስ አበባ ከተማ በአዲስ ከተማ ክፍል ከተማ፣ወረዳ 8 ክልል ውስጥ የሚገኘውን ቁጥሩ 911 የሆነውን ንግድ ቤት ከ1ኛ ተጠሪ ላይ ተከራይተው ሕጋዊ የሆነ የንግድ ፈቃድ በማውጣት ሰራተኞችን በመቅጠር የንግድ ስራ ሲሰሩበት የቆዩ መሆኑን፣1ኛ ተጠሪ የአመልካች ሰራተኞች የሆኑት 2ኛ እና 3ኛ ተጠሪዎችን ተከራይ ነን በማለታቸው የኪራይ ውሉን በመመሪያ ቁጥር 4/2004 መሰረት ያቋረጠው መሆኑንና ተግባሩም ሁከት መሆኑን በመግለፅ የሁከት ተግባሩ እንዲወገድላቸው፣የኪራይ ውሉ ያላግባብ በመቋረጡ ምክንያት ያጡትን የቀን ገቢ ተጠሪዎች በአንድነትና በነጠላ እንዲከፍሉ ይወሰንላቸው ዘንድ ዳኝነት መጠየቃቸውን የሚያሳይ ነው።2ኛ እና 3ኛ ተጠሪዎች ለክሱ በሰጡት መልስም ክርክሩ መሰረት ያደረገው የመንግስት ቤትን መሆኑን በምክንያት ጠቅሰው ፍርድ ቤቱ ጉዳዩን ለማየት ስልጣን የለውም በማለት የመጀመሪያ ደረጃ መቃወሚያ ያቀረቡ ሲሆን በፍሬ ነገር ደረጃ ደግሞ አመልካች በወኪላቸው አቶ ዳዊት አብርሃም አማካኝነት ሚያዚያ 17 ቀን 2001 ዓ/ም ከተጠሪዎቹ ጋር የንግድ ቤት ኪራይ ውል በመፈፀም በወር ብር 2350፣በኋላም ብር 3000.00 ሲሰበስቡ መቆየታቸውን፣መንግስት ያወጣውን መመሪያም ተከትሎ አመልካች የንግድ ቤቱ እንዳይወሰድ ሆነ ብለው ተጠሪዎችን በማባበል እና በማስገደድ የሰራተኝነት ውል ማስፈረማቸውን፣ሆኖም የሰራተኝነት ውሉም ተቀባይነት የልለውና ተጠሪዎቹ ሰራተኛ ሳይሆኑ ተከራይ የነበሩ መሆኑን፣አመልካችም ቢሆኑ የስራ ገቢ ግብር በስማቸው ለመክፈላቸው ያቀረቡት ማስረጃ የልለ መሆኑን ዘርዝረው አመልካች የንግድ ቤቱን በከፍተኛ ዋጋ አከራይተው ሲገለገሉ በመመሪያው መሰረት የንግድ ቤቱን ለተጠሪዎቹ መተላለፉ የሁከት ተግባር ላባል አይችል በማለት ተከራክረዋል።የአሁኑ 1ኛ ተጠሪ ግን በሕጉ አግባብ ጥሪ ተደርጎለት ክሱ በሚሰማበት ቀነ ቀጠሮ ጭምር ሳይቀርብ በመቅረቱ ጉዳዩ በልለበት ታይቷል።የስር ፍርድ ቤትም የአመልካችንና የ2ኛ እና 3ኛ ተጠሪዎችን ክርክር ሲሰማ አመልካች ለተጠሪዎቹ ድርጅቱን እንጂ ቤቱን ያላከራዩ መሆኑን መግለፃቸውን አረጋግጦ ተጠሪዎቹ ስልጣንን መሰረት አድርገው ያነሱትን ተቃውሞ ወድቅ አድርጎ አመልካች ቤቱን ለተጠሪዎቹ ማስተላለፍ ያለማስተላለፋቸውን በጭብጥነት ይዞ የግራ ቀኙን ማስረጃዎችን ሰምቶ የአመልካች ሁለቱ ምስክሮች ተጠሪዎች ሰራተኛ መሆናቸው ላይ ተመሳሳይ ግንዛቤ የልላቸው መሆኑን የምስክርነት ቃላቸው እንደሚያሳይ፣የተጠሪዎች ሶስቱም ምስክሮች ደግሞ ተጠሪዎች ተከራይ እንጂ ሰራተኛ ያለመሆናቸውን መመስከራቸውን፣ተጠሪዎች በሰነድ ማስረጃነት ያቀረቡት ሰነድም ተጠሪዎች ቤቱን ተከራይተው ግምቱ ብር 6000.00 የሆነ ንብረት ያላቸው መሆኑን መግለፁ የተከራዩት ቤት እንጂ ድርጅቱን ያለመሆኑን እንደሚያሳይና ያለአከራይ እውቅና አመልካች ቤቱን ለ2ኛ እና 3ኛ ተጠሪዎች አስተላልፈው እንደአከራዩ መረጋገጡን በምክንያት ይዞ የተፈጠረ ሁከት የለም፣አመልካች የቀረባቸው የቀን ገቢም የለም፣ወጪና ኪሳራ በቁጥር ለ2ኛ እና 3ኛ ተጠሪዎች ብር 8000.00(ስምንት ሺህ ብር) ሲል ወስኗል።በዚህ ውሳኔ የአሁኑ አመልካች ቅር በመሰኘት ይግባኛቸውን ለፍድራሉ ከፍተኛ ፍርድ ቤት ቢያቀርቡም ተቀባይነት አላገኙም።የአሁኑ የሰበር አቤቱታ የቀረበውም ይህንኑ ውሳኔ በመቃወም ለማስለወጥ ነው።የአመልካች የሰበር አቤቱታ መሰረታዊ ይዘትም 2ኛ እና 3ኛ ተጠሪዎች የአመልካች ቅጥር ሰራተኞች መሆናቸው ተረጋግጦ እያለና ውሉን ተገደው የፈረሙ ስለመሆኑ ሳይረጋገጥ የአመልካች ምስክሮች ቃልና የቅጥር ውሉ ሰነድ ይዘት እንዲሁም አመልካች በቃል ክርክር ጊዜ ስለድርጅት ቤት ኪራይ የገለፁት አገላለፅ በተዛባ መልኩ ተመዝግቦና መንግስት ከአወጣው መመሪያ ይዘት ውጪ ቤቱን 1ኛ እና 2ኛ ተጠሪዎች እንዲነጥቁ የተደረገ መሆኑን ዘርዝረው ውሳኔ ላታረም ይገባል በማለት መከራከራቸውን የሚያሳይ ነው።አቤቱታቸው ተመርምሮም በሰበር ችሎቱ እንዲታይ የተደረገ ሲሆን 1ኛ ተጠሪ መጥሪያ ደርሶት ባለመቅረቡ በፅሑፍ መልስ የመስጠት መብቱ የታለፈ ሲሆን 2ኛ እና 3ኛ ተጠሪዎች ግን ቀርበው በፅሑፍ እንዲከራከሩ ተደርጓል።
የጉዳዩ አመጣጥ አጠር አጠር ባለመልኩ ከላይ የተገለፀው ሲሆን ይህ ችሎትም የግራ ቀኙን ክርክር ለሰበር አቤቱታው መነሻ ከሆነው ውሳኔ እና አግባብነት ካላቸው ድንጋጌዎች ጋር በማገናዘብ ጉዳዩን በሚከተለው መልኩ መርምሮታል።እንደመረመረውም በጉዳዩ ላይ በተሰጠው ውሳኔ መሰረታዊ የሆነ የሕግ ስህተት ተፈፅሟል ለማለት ይቻላል ወይስ አይቻልም የሚለው ነጥብ በጭብጥነት ላታይ የሚገባው ሁኖ ተገኝቷል።
ከክርክሩ ሂደት መገንዘብ የተቻለው አመልካች በተጠሪዎች ላይ ክስ ላመሰርቱ የቻሉት ከመንግስት ተከራይተው 2ኛ እና 3ኛ ተጠሪዎችን በሰራተኛነት ቀጥረው በማሰራት የሚጠቀሙበት ቤት 1ኛ ተጠሪ ከመመሪያ ቁጥር 4/2004 ውጪ ለ2ኛ እና 3ኛ ተጠሪዎች በኪራይ አሳልፎ ሰጥቶብኛል፣ይህም የሁከት ተግባር በመሆኑ ላወገድልኝ ይገበል በማለት ሲሆን 2ኛ እና 3ኛ ተጠሪዎች ለክሱ በሰጡት መልስም ቤቱን ከአመልካች ላያገኙ የቻሉት በሰራተኝነት ሳይሆን በኪራይ መሆኑን፣የሰራተኛነት ቅጥር ውል የተባለው ሰነድም መመሪያውን ተከትሎ የተደረገ ሽፋን እንጂ ትክክለኛ ያለመሆኑን ገልፀው ተግባራቸው ሁከት የሚሆንበት አግባብ የለም ሲሉ መከራከራቸውን ነው።የስር ፍርድ ቤት የግራ ቀኙን ክርክርና ማስረጃ የሰማ ሲሆን አመልካች ለተጠሪዎች ያከራየሁት የድርጅት ቤት ነው በማለት በቃል ክርክር ከመግለጻቸው በተጨማሪ አሉኝ የሐቸውን ምስክሮችን አቅርበውም ተጠሪዎች ሰራተኛ መሆን ያለመሆናቸው ላይ የምስክርነት ቃላቸውን እንዲሰጡ ያደረጉ መሆኑን ገልፆ ምስክሮች ተመሳሳይ በሆነ ሁኔታ ተጠሪዎቹ የአመልካች ቅጥር ሰራተኞች መሆናቸውን ያለመመስከራቸውን፣የተጠሪዎች ምስክሮች ግን ተጠሪዎቹ የአመልካች ሰራተኞች ሳይሆኑ የንግድ ቤቱን ተከራይተው የሚሰሩ መሆኑን በተመሳሳይ ሁኔታ መመስከራቸውን እንዲሁም የኪራይ ሰንዱ ተጠሪዎች ግምቱ ብር 6000.00 የሆነ ንብረት በቤቱ አስገብተው ያሉ ስለመሆኑ የሚገልጽ መሆኑ ተጠሪዎች የተከራዩት የንግድ ቤቱን እንጂ የድርጅት ቤቱን ያለመሆኑን እንደሚያሳይ ዘርዝሮ ቤቱ ለተጠሪዎች ተላልፎ የተሰጠው በመመሪያ ቁጥር 4/2004 በመሆኑ ተግባሩ የሁከት ተግባር ነው ላባል የሚችልበት ሕጋዊ አግባብ የለም በማለት ውሳኔ የሰጠ መሆኑን የክርክሩ ሂደት ያሳያል።እንግዲህ አመልካች በዚህ የሰበር ደረጃ ባቀረቡት ቅሬታ የስር ፍርድ ቤት ፍሬ ነገሩን በአግባቡ ያልመዘገበና ከአመልካች የክርክር ነጥብና ማስረጃዎቹ ከአረጋገጡት ውጪ መሆኑን ጠቅሰው እንደዚህ አይነት የዳኝነት አሰጣጥ የመሰረታዊ ሕግ ስህተት አይደለም ላባል የማይችልበት አግባብ የልለ መሆኑን አጥብቀው ገልጸዋል።ይሁን እንጂ የሥር ፍርድ ቤት በማስረጃ ስለመረጋገጣቸው የገለጻቸው ፍሬ ነገሮችን በውሳኔው ላይ በግልጽ ያስቀመጠ ሲሆን ይህንኑ የሥር ፍርድ ቤት የውሳኔ ግልባጭ ይግባኝ ሰሚው ፍርድ ቤትም ሙሉ በሙሉ የተቀበለው በመሆኑና ለዚህ ሰበር ሰሚ ችሎት ደግሞ ተያይዘው የሚቀርቡት የበታች ፍርድ ቤቶች የውሰኔ ግልባጭ ስለመሆኑ የአዋጅ ቁጥር 25/1988 አንቀፅ 21 እና 22 ስለሚያስገነዝቡ ይህ ችሎት ይህንኑ የበታች ፍርድ ቤቶች የውሳኔ ግልባጭ ይዘት አይቶ ተገቢውን ዳኝነት ከመስጠት በሰበር ደረጃ የቀረበው የአመልካች ቅሬታ የሚያግድው ሁኖ አልተኘም።በመሆኑም ለዚህ ችሎት በኢ.ፍ,.ዲ.ሪ ሕግ መንግስት አንቀጽ 80(3(ሀ))እና አዋጅ ቁጥር 25/1988 አንቀፅ 10 ድንጋጌዎች መሰረት የተሰጠው ስልጣን መሰረታዊ የሆነ የሕግ ስህተትን ማረም እንጂ ፍሬ ነገሩን የማጣራትና ማስረጃን የመመዘን ስልጣን ባለመሆኑ የበታች ፍርድ ቤቶች በዚህ ረገድ የያዙትን ድምዳሜ ለመለወጥ የሚቻልበት አግባብ የለም።ከዚህ አንፃር ጉዳዩን ስንመለከተው አመልካች ከመንግስት የተከራዩትን ቤት ከአከራዩ ፈቃድ ውጪ ለ2ኛ እና 3ኛ ተጠሪዎች አከራይተው ሲጠቀሙ የነበሩ መሆኑን፣ያከራዩትም የንግድ ድርጅቱን ሳይሆን የንግድ ቤቱን፣ተጠሪዎች የአመልካች ቅጥር ሰራተኞች ሳይሆኑ ተከራይ መሆናቸውን፣አመልካች አለ የሚሉት የኪራይ ውልም የመንግስት መመሪያን መውጣት ተከትሎ ለሽፋን የተደረገ መሆኑን ፍሬ ነገሩን ለማጣራትና ማስረጃን ለመመዘን በሕጉ ስልጣን በተሰጣቸው ፍርድ ቤቶች የተረጋገጠ በመሆኑ አመልካች ከመንግስት ተከራይተው የነበሩት ቤት ለ2ኛ እና 3ኛ ተጠሪዎች በ1ኛ ተጠሪ ተላልፎ የተሰጠውና 2ኛ እና 3ኛ ተጠሪዎች ይዘው ለአመልካች ላለቁ ፈቃደኛ ያለመሆናቸው የሁከት ተግባርን የሚያቋቁምበት የሕግ አግባብ የለም።በመሆኑም በጉዳዩ ላይ በተሰጠው ውሳኔ መሰረታዊ የሆነ የሕግ ስህተት ተፈፅሟል ለማለት የሚቻል ሁኖ ስላልተገኘ ተከታዩን ወስነናል።
ው ሣ ኔ
በፍድራል መጀመሪያ ደረጃ ፍርድ ቤት በመ/ ጥቅምት 01 ቀን 2005 ዓ/ም ተሰጥቶ በፍድራል ከፍተኛ ፍርድ ቤት በመ/ ጥር 02 ቀን 2005 ዓ/ም በትዕዛዝ የጸናው ውሳኔ በፍ/ብ/ሥ/ሥ/ሕ/ቁጥር 348(1) መሰረት ፀንቷል።
በአመልካች ላይ የተፈጠሩ ሁከት የለም ተብሎ መወሰኑ ባግባቡ ነው ብለናል።
በዚህ ችሎት ለተደረገው ክርክር የወጣውን ወጪና ኪሳራ የየራሳቸውን ይቻሉ ብለናል።
No topics extracted.