No summary available.
መጋቢት 13 ቀን 2005 ዓ.ም.
ዳኞች፡- ተሻገር ገ/ስላሴ አልማው ወል ዓላ መሐመድ ረታ ቶሎሳ አዳነ ንጉሴ አመልካች፡- የሐረር (ደ/ሳ) ቅዱስ ሚካኤል ቤተክርስቲያን - አልቀረቡም ተጠሪዎች፡- ወ/ሮ ማንያህልሻል አበራ - አልቀረቡም መዝገቡን መርምረን የሚከተለውን ፍርድ ሰጥተናል።
ጉዳዩ የቀረበው በሐረር ክልል የከፍተኛ ፍ/ቤትና የክልሉ ጠቅላይ ፍ/ቤት የሰጡት ውሳኔ መሰረታዊ የሕግ ስህተት ያለበት ስለሆነ በሰበር ታይቶ ይታረምልኝ በማለት ያቀረበውን የሰበር አቤቱታ አጣርቶ ለመወሰን ነው። ጉዳዩ የመቃብር ቤት ግምት ይከፈለኝ በማለት የቀረበን ክስ የሚመለከት ነው። ጉዳዩ በመጀመሪያ የታየው በሐረሪ ሕዝብ ክልል የከፍተኛ ፍ/ቤት ነው። በከፍተኛው ፍ/ቤት ተጠሪ ከሳሽ አመልካች ተከሳሽ በመሆን ተከራክረዋል።
የክርክሩ መነሻ ተጠሪ በሐረር ከተማ በሚገኘው ቅዱስ ሚካኤል ቤተክርስትያን ግቢ ውስጥ የመቃብር ቤት ለመስራት እንዲፈቀድልኝ ጠይቄ የመቃብር ቤት እንድሰራ ስለተፈቀደልኝ ለእኔና ለዘመዶቼ የቀብር ስርዓት የሚፈፀምበት ቤት የመቃብር ቤት በብር 200,000 (ሁለት መቶ ሺህ ብር) ሰርቻለሁ። ሆኖም ቤተክርስቲያኗ ኃይማኖትሽን የለወጥሽ በመሆኑ በመቃብር ቤቱ ለመጠቀም አትችይም በማለት በግልፅ ደብዳቤ አሳውቆኛል።
ስለዚህ የኢትዮጵያ ተዋህዶ ኦርቶዶክስ ቤተክርስቲያን ኃይማኖት ተከታይ በነበርኩበት ጊዜ የሰራሁትን የመቃብር ቤት ያለምንም ካሳና ግምት ለመልቀቅ የውል ግድታ ያለገባሁ በመሆኑ የመቃብር ቤቱን ለመስራት ያወጣሁትን ብር 200,000 (ሁለት መቶ ሺህ ብር) እንድከፍል ይወሰንልኝ በማለት ያቀረበችው ክስ ነው። አመልካች በተከሳሽነት ቀርቦ የመጀመሪያ የክስ መቃወሚያ አቅርቧል መቃወሚያው በብይን ታልፏል። አመልካች ተጠሪ የመቃብር ቤት ሰርታለች። ተጠሪ በሰራችው የመቃብር ቤት የዘመዶቿ ስርዓተ ቀብር ተፈፀሞ የዘመዶቿ አጽም አርፎበት ይገኛል። ተጠሪ (ከሳሽ) ኃይማኖቷን የለወጠች በመሆኑ በመቃብር ቤቱ የመጠቀም መብት የላትም።
የመቃብር ቤት ግምት የመክፈል ያደረግነው ውል የልለ በመሆኑ ክሱ የእምነቱን መሰረታዊ ቀኖናና አሰራር የሚፃረር በመሆኑ የመቃብር ቤት ግምት የመክፈል ኃላፊነት የለብንም። ተጠሪ የሰራችው ቤት ግምትም ከብር 13,000 (አስራ ሶስት ሺህ ብር) የሚበልጥ አይደለም በማለት ተከራክሯል።
የከፍተኛው ፍ/ቤት የግራቀ ኙን ክርክርና ማስረጃ ከመረመረ በኋላ አመልካች ተጠሪ የሰራችውን የቤት ግምት የመክፈል ኃላፊነት አለበት በማለት በመቃብር ቤቱ በባለሙያ ተገምቶ እንዲቀርብ መጋቢት 26 ቀን 2003 ዓ/ም ውሳኔ ሰጥቷል። መቃብር ቤቱ በባለሙያ ብር 50,153.40 (ሃምሳ ሺህ አንድ መቶ ሃምሳ ሶስት ብር ከአርባ ሳንቲም) የተገመተ በመሆኑ አመልካች ይህንን የመቃብር ቤቱን ግምት ለተጠሪ እንዲከፍል በማለት መስከረም 28 ቀን 2005 ዓ/ም ውሳኔ ሰጥቷል። አመልካች በዚህ ውሳኔ ቅር በመሰኘት ይግባኝ ለክልሉ ጠቅላይ ፍ/ቤት አቅርቧል። የክልሉ ጠቅላይ ፍ/ቤት ይግባኙን በፍ/ሥ/ሥ/ሕግ ቁጥር 337 ሰርዞታል።
አመልካች ታህሳስ 25 ቀን 2005 ዓ/ም በተፃፈ የሰበር አቤቱታ ተጠሪ የኢትዮጵያ የኦርቶዶክስ እምነት ተከታይ በነበረችበት ወቅት ስሞት ስርዓተ ቀብሬ መፈፀሚያ ይሆናል በማለት መቃብር ቤት እንድትሰራ ፈቃድ ጠይቃ ተፈቅዶላታል። ተጠሪ በመቃብር ቤቱ ስርዓተ ቀብሯ ላፈፀም የሚችለው የእምነቱ ተከታይ ሆና ከዚህ ዓለም በሞት ስትለይ ነው። ተጠሪ ኃይማኖቷን ከቀየረች በቤተክርስቲያኑ የመቃብር ሥፍራ የልላ እምነት ተከታይ የሆነ ሰው የማይቀበር በመሆኑ በመቃብር ቤቱ ስርዓት ቀብሯ ላፈፀም አይችልም። አመልካች ይህንን ለተጠሪ ማሳወቁ ተገቢ ነው። ነገር ግን ፍ/ቤቱ ቦታው የመቃብር ቦታና የእምነቱ ጋር የተያያዘ መሆኑን ሳያገናዝብ ለጉዳዩ አግባብነት የልለውን የፍ/ሕ/ቁጥር 1179 በመጥቀስ የመቃብር ቤት ግምት ለተጠሪ እንዲከፍል የሰጠው ውሳኔ የሕግ መሰረት የልለውና መሰረታዊ የሕግ ስህተት ያለበት በመሆኑ በሰበር ታይቶ እንዲታረምልኝ በማለት አመልክቷል።
ተጠሪ የካቲት 4 ቀን 2005 ዓ/ም በተፃፈ መልስ የከፍተኛው ፍ/ቤት ተጠሪ ከሰራችው የመቃብር ቤት ውስጥ የቀብር ስርዓት ያልተፈፀመበት ቦታና ክፍል ግምት አመልካች እንዲከፍል ውሳኔ የሰጠው 26-1-2003 ዓ/ም ነው።
ይህ ውሳኔ አመልካች ይግባኝ ብሎ አላሻረም። ስለዚህ ቤቱ ከተገመተ በኋላ ያቀረበው ይግባኝ በአፈፃፀም እንደቀረበ ይግባኝ መታየት ያለበት ስለሆነ መዝገቡ ይዘጋልኝ። ተጠሪ የገነባቸውን የመቃብር ቤት እንዳትጠቀም አመልካች የከለከለ በመሆኑ፣ የቤቱን ግምት እንዲከፍል የተሰጠው ውሳኔ መሰረታዊ የሕግ ስህተት የለበትም በማለት መልስ ሰጥቷል። አመልካች የመልስ መልስ አቅርቧል።
ከስር የክርክሩ አመጣጥና ግራ ቀኙ ሰበሰር በጽሁፍና በቃል ባደረጉት ክርክር ከላይ የተገለፀው ሲሆን እኛም አመልካች ተጠሪ በቤተ ክርስቲያኑ ቅጥር ግቢ ውስጥ የሰራችውን የመቃብር ቤት ግምት እንዲከፍል የተሰጠው ውሳኔ ተገቢ ነው ወይም አይደለም የሚለውን ጭብጥ በመያዝ ጉዳዩን መርምረናል።
ከላይ የተያዘውን ጭብጥ ከመወሰናችን በፊት ተጠሪ አመልካችን የሰበር አቤቱታ በመቃወም ያቀረበውን ክርክር ህጋዊነት ተመልክተናል። አመልካች የሐረሪ ክልል ከፍተኛ ፍ/ቤት በመጀመሪያ አመልካች ተጠሪ የሰራተኛውን የመቃብር ቤት ግምት የመክፈል ኃላፊነት አለበት ብሎ መጋቢት 20 ቀን 2003 ዓ/ም የሰጠውን ውሳኔ የስር ፍ/ቤት በዚያው መዝገብ ንብረቱን አስገምቶ አመልካች ለተጠሪ የሚከፍለው የመቃብር ቤት ግምት ብር 50,153.40 (ሃምሳ ሺህ አንድ መቶ አምሳ ሶስት ብር ከሰርባ ሳንቲም ነው) በማለት መስከረም 28 ቀን 2005 ዓ/ም የሰጠውን ውሳኔ በማጠቃለል ይግባኝ ማቅረቡና ይግባኙ ውድቅ ሲሆንበት የሰበር አቤቱታ ማቅረቡ የፍ/ሥ/ሥ/ሕግ ቁጥር 320 ንዑስ አንቀጽ 2 እና የፍ/ሥ/ሥ/ሕግ ቁጥር 327 ንዑስ አንቀጽ 3 የመጀመሪያውን ፓራግራፍ መሰረት ያደረገ ነው። ተጠሪ ይግባኙ የአፈፃፀም ይግባኝ ነው በማለት ያቀረበ ቢሆንም የከፍተኛው ፍ/ቤት የአመልካች ለክሱ ኃላፊ መሆኑንና ለተጠሪ መክፈል የሚገባውን የገንዘብ መጠን የወሰነው የተጠሪንና የአመልካችን ክስ ባስተናገደበት የመዝገብ መሆኑን ተረድተናል። በልላ በኩል ተጠሪ ፍርዱን ለማስፈፀም ያስከፈተችው የአፈፃፀም መዝገብ መሆኑን ግራ ቀኙ ካደረጉት ክርክር ተረድተናል። ስለሆነም ተጠሪ የአመልካች የሰበር አቤቱታ ውድቅ እንዲደረግለት ያቀረበውን መቃወሚያ አልተቀበልነውም።
ዋናውን ጭብጥ በተመለከተ፣ ተጠሪ የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ቤተክርስቲያን ሃይማኖት ተከታይ በነበረችበት ወቅት የኃይማኖቱን መሰረታዊ ቀኖና ስርዓት መሰረት በማድረግ በምትሞትበት ጊዜ የእሷና የዘመዶቿ አስክሬን የሚያርፍበትና ሥርዓተ ቀብር የሚፈፀምበት የመቃብር ቤት በአመልካች ግቢ ውስጥ ለመስራት እንዲፈቀድላት ጠይቃ የመቃብር ቤት እንድትገነባ ልዩ ፈቃድ በመስጠት የተጠሪን “privilege” ጠብቆላታል። ተጠሪም በአመልካች በተሰጣት ልዩ ፈቃድ መሰረት መቃብር ቤቱን በአመልካች ግቢ ውስጥ በራሷ ወጭ የሰራች መሆኑ ግራ ቀኙ የሚተማመኑበት ፍሬ ጉዳይ ነው። እንደዚሁም ተጠሪ በሰራችው የመቃብር ቤት ውስጥ የኢትዮጰያ ተዋህዶ ኦርቶዶክስ ቤተክርስቲያን ኃይማኖት ተከታይ የሆኑ የተጠሪ ዘመዶች አስክሬን የተቀበረ መሆኑና አሁንም በመቃብር ቤቱ ውስጥ የተጠሪ ዘመዶች አፅም ያረፈበት መሆኑ የሚያከራክር አይደለም።
አመልካችና ተጠሪን የሚያከራክረው ጭብጥ በአሁኑ ወቅት የተለየ ኃይመኖት ተከታይ የሆነችው ተጠሪ በአመልካች በተሰጣት ልዩ ፈቃድ መሰረት በሰራችው የመቃብር ቤት ስትሞት የመቀበር መብት ይኖራታል ወይስ አይኖራትም? ተጠሪ በመቃብር ቤቱ የመቀበር መብት የላትም ከተባለ አመልካች የመቃብር ቤቱን ግምት ለተጠሪ የመክፈል ኃላፊነት አለበት ወይስ የለበትም የሚለው ነጥብ ነው።
ማንኛውም ሰው የማሰብ የሕላናና የኃይማኖት ነፃነት ያለው መሆኑንና ይህም መብት የመረጠውን ኃይማኖት ወይም እምነት የመያዝ የመቀበል ኃይማኖቱንና እምነቱን ለብቻ ወይም ከልሎቹ ጋር በመሆን በይፋ ወይም በግል የማምለክ፣ የመከተል የመተግበር፣ የማስተማር ወይም የመግለፅ መብትን እንደሚያካትት በሕገ መንግስቱ አንቀጽ 27 ንዑስ አንቀጽ 1 ተደንግጓል። እንደዚሁም ማንኛመው ሰው የሚፈልገውን እምነት ለመያዝ ያለውን ነፃነት በኃይል ወይም በልላ ሁኔታ በማስገደድ መገደብ ወይም መከልከል የማይቻል መሆኑ በሕገ መንግስቱ አንቀጽ 27 ንዑስ አንቀጽ 3 በግልፅ ተደንግጓል። ይህ በሕገ መንግስቱ የተረጋገጠው የእምነትና የኃይማኖት ነፃነት፣ ማናቸውም ሰው በሚያምንበት እምነትና በሚከተለው ኃይማኖት ቀኖና ስርዓት መሰረት በዚህ ዓለም በሚኖርበት ጊዜ ብቻ ሳይሆን ከዚህ ዓለም በሞት ከተለየ በኋላ መንፈሳዊ ፀጋ አገኝባቸዋለሁ የሚላቸውን የበጎ አድራጎት ተግባራቶችንና ልሎች ስራዎችን የማከናወን ነፃነትን ጭምር የሚመለከት ነው።
በዚህ መሰረት ተጠሪ የኢትዮጵያ ተዋህዶ ኦርቶዶክስ ቤተክርስቲያን ኃይማኖት ተከታይ በነበረችበት ወቅት በአመልካች ግቢ ውስጥ የመቃብር ቤት እንድትገነባ ልዩ ፈቃድ የተሰጣት እሷም የመቃብር ቤቱን በግል ወጭዋ የገነባችው አመልካች የሚያረምደውን ኃይማኖታዊ ቀኖና ሥርዓት በማመንና ተገዥ በመሆን እንደነበር ከግራ ቀኙ ክርክር ለመረዳት ይቻላል። አመልካች የመቃብር ቤቱን እንድሰራ ልዩ ፈቃድና ክብር የተሰጣት የኢትዮጵያ ተዋህዶ ኦርቶዶክስ ቤተክርስትያን ተከታይ አማኝ ስለነበረች ነው። አመልካች ትከተለው የነበረው የኢትዮጵያ ተዋህዶ ኦርቶዶክስ ቤተክርስቲያን ኃይማኖታዊ ቀኖና ሥርዓት የመለወጥና የመረጠችውን ኃይማኖት የመያዝና የማምለክ የመተግበር ነፃነት ያላት መሆኑ በሕገ መንግስቱ አንቀጽ 27 ንዑስ አንቀጽ 1ና ንዑስ አንቀጽ 3 እንደዚሁም በሕገ መንግስቱ አንቀጽ 13 ንዑስ አንቀጽ 2 እና አለም አቀፉ የሰብዓዊ መብቶች ሁለተናዊ መግለጫ አንቀጽ 18 እና ዓለም አቀፉ የሲቪልና የፖለቲካ መብቶች ቃል ኪዳን ስምምነት አንቀጽ 18(1) ድንጋጌዎች የተረጋገጠላት በመሆኑ ኃይማኖቷን በመለወጥና የምታምንበትን ኃይማኖት የመያዝ መብቷን ማረጋገጧ የሚገድብ አይደለም። አመልካችም ይህንን የተጠሪን መብትና ነፃነት የሚገድብ ደብዳቤ ያልፃፈና ልሎች የተጠሪን መብት የሚገድቡ ተግባሮችን ያልፈፀመ መሆኑን ተረድተናል።
ተጠሪ የአመልካችን ኃይማኖታዊ ቀኖና ሥርዓት መከተሐን አማኝ መሆኗን በማቆም የልላ ኃይማኖት ወይም እምነት ተከታይ መሆኗን በመካድ ያቀረበችው ክርክር የለም። ተጠሪ የአመልካችን የሚያራምደውን ኃይማኖትና መንፈሳዊ አስተምሮት በመተው የልላ ኃይማኖት ወይም እምነት ተከታይ መሆኗ ካልተካደ ተጠሪ የኢትዮጵያ ተዋህዶ ኦርቶዶክስ ቤተክርስቲያን ተከታይ አማኝ የነበረች በመሆኑ ምክንያት አመልካች ሰጥቷት የነበረው ክብር መብትና ጥቅም በነበረው ሁኔታ እንዲቀጥልላት ለመጠየቅ አትችልም። ተጠሪ የልላ እምነትና ኃይማኖት ተከታይ መሆን ስትጀምር ከአመልካች ጋር የነበራት ኃይማኖታዊና መንፈሳዊ ትስስርና ግንኙነት ሙሉ በሙሉ ይቋረጣል። አመልካች በቅጥር ግቢው ውስጥ በሚገኘው የመካነ መቃብር ቦታ ተጠሪ የመቃብር ቤት እንድትሰራ ልዩ ፈቃድ የሰጣት ተጠሪ ከአመልካች ጋር የነበራትን የኃይማኖትና የእምነት ትስስር መሰረት በማድረግ ነው። በአመልካች ቅጥር ግቢ ውስጥ ተጠሪ የመቃብር ቤት የገነባችው ከአመልካች ጋር በነበራት ጥብቅ የሆነ ኃይማኖታዊና መንፈሳዊ ግንኙነት ምክንያት እንጂ በአመልካችና በተጠሪ መካከል በገንዘብ የሚተመን የኢኮኖሚያዊ ውልና ስምምነትን መሰረት በማድረግ አይደለም። ስለዚህ አመልካች በቅጥር ግቢው የሚገኘው የመካነ መቃብር ቦታ ላይ ተጠሪ ቤት እንድትሰራ የሰጠው ልዩ ፈቃድና ተጠሪም በዚህ ፍቃድ መሰረት የሰራችው የመቃብር ቤት ከኃይማኖቱና ከእምነቱ ተለይቶ የሚታይ የሚፈፀምና የሚተገበር ተራ የሆነ የውል ወይም የንብረት ግኑኝነት ተደርጎ የሚወሰድ አይደለም። ስለሆነም አመልካች የኃይማኖቴና የእምነቴ ተከታይ ናት በሚል ምክንያት የሰጣትን ልዩ ፈቃድ መሰረት በማድረግ በአመልካች ቅጥር ግቢ ውስጥ በሰራችው የመቃብር ቤት ላይ ያላት መብትና ጥቅም፣ ተጠሪ ኃይማኖቷን ከለወጠችና የልላ እምነት ተከታይ ከሆነችበት ጊዜ ጀምሮ ሙሉ በሙሉ ይቋረጣል። ከዚህ አንፃር ሲመዘን አመልካች ትከተለው የነበረውን ኃይማኖትና እምነት በመለወጥ ልላ ኃይማኖት ተከታይ በመሆነሽ በአመልካች ግቢ ውስጥ በሰራሽው የመቃብር ቤት የመጠቀምና ስትሞችም በመቃብር ቤቱ የመቀብር መብት የለሽም በማለት ለተጠሪ የፃፈው ደብዳቤ የህገ-መንግሰቱን አንቀፅ 11 አንቀፅ 27 ከንዑስ አንቀጽ 1 እስከ ንዑስ አንቀጽ 3 የተደነገጉትን ድንጋጌዎች መሰረት ያደረገና ተገቢነት ያለው ሆኖ አግኝተነዋል።
ከላይ በተለፁት የህገ መንግስቱ ድንጋጌዎችና በልሎች ዓለም አቀፍ የስብዓዊ መብቶች ህግጋት ድንጋጌዎች የተረጋገጠለትን ሃይማኖቱን የመለወጥና የሚያምንበትን ኃይማኖት የመያዝ የማመለክና የመተግበር መብቱን ዕውን ያደርገ ሰው በፊት ሲከተለው የነበረውን ኃይማኖትና እምነት መሰረት በማድረግ ለሰራቸው ተግባራት እንዲፈርሱለት እንዲመለሱለት ወይም ለሰራቸው ተግባሮች ግምት እንዲከፈለው የመጠየቅ መብት ይኖረዋል ወይስ አይኖረውም? የሚለውን ነጥብ መታየት አለበት። የኃይማኖትና የእምነት ነፃነትና ኃይማኖትንና እምነትን የመለወጥ መብት አንድ ሰው በፊት ይከተለው የነበረውን ኃይማኖትና እምነት መሰረት በማድረግ ኃይማኖታዊና መንፈሳዊ ግድታውን ለመወጣትና መንፈሳዊ ፀጋና ቡራኬ ለመጎናፀፍ በማሰብ የሰጣቸው ስጦታዎች ወይም ወጫቸውን በመሸፈን የሰራቸው የኃይማኖትና የእምነት ማምለኪያና ኃይመኖሮታዊ ትምህርት ማስተማሪያ ቤቶች ወይም በእምነቱ መሰረት የቀብር ስርዓት መፈፀሚያ እንዲሆን በማሰብ የሰራው ቤት እንዲመለስለት ወይም እንዲፈርስ ወይም ግምታቸው እንዲከፈለው የመጠየቅ መብትን የሚያስከትል አይደለም። በመሆኑም ተጠሪ የአመልካች ኃይማኖታዊ አስተምሮትና እምነት ተከታይ በነበረችበት ወቅት ለእሷና ለዘመዶቿ ስርዓተ ቀብር ማስፈጸሚያ ይሆናል በሚል ዕምነት የሰራችውን የመቃብር ቤት ግምት አመልካች እንዲከፍላት ለመጠየቅ የሚያስችላት ህጋዊ መሰረት የለም። አመልካችም ተጠሪ የኃይማኖቱ ተከታይ በነበረችበት ጊዜ የኃይማኖቱን መሰረታዊ ቀኖና ስርዓት መሰረት በማድረግ ለስርዓተ ቀብሬ ማስፈፀሚያ ይሆናል በሚል ኃይማኖታዊና መንፈሳዊ እምነት ወጭውን ችላ በቅጥር ግቢው ውስጥ የሰራችውን የመቃብር ቤት ዋጋና ግምት የመክፈል ኃላፊነት የለበትም።
የሐረሪ ክልል ከፍተኛ ፍርድ ቤትና የክልሉ ጠቅላይ ፍርድ ቤት ለውሳኔቸው መሰረት በማድረግ የጠቀሱት የፍታብሄር ህግ ቁጥር 1179 ድንጋጌዎች ኃይማኖታዊና መንፈሳዊ እምነት መሰረት በአንድ ኃይማኖታዊ ተቋም ቅጥር ግቢ ውስጥ የተገነባ የመቃብር ቤት ላይ ተጠቃሽም ሆነ ተፈፃሚ የሚሆኑ አይደሉም።
ስለሆነም የበታች ፍርድ ቤቶች የፍታብሕር ህግ ቁጥር 1179 ድንጋጌዎች ይዘት ፣ ዓላማና ተፈፃሚነት ወስጥ፣ ከህገ መንግስቱ አንቀፅ 11 እና አንቀፅ 27 ድንጋጌዎች ጋር በማጣመር ሳይተረጉሙ፣ አመልካች ተጠሪ ለእኔና ለዘመዶቼ ስርዓተ ቀብር ማስፈፀሚያ ይሆናል በማለት የሰራችውን የመቃብር ቤት ግምት ለተጠሪ የመክፈል ኃላፊነት አለበት በማለት የሰጡት ውሳኔ መሰረታዊ የህግ ስህተት ያለበት ነው በማለት ወስነናል።
የሐረሪ ክልል የከፍተኛ ፍርድ ቤት በመዝገብ መጋቢት 20 ቀን 1983 ዓ.ም የሰጠው ውሳኔና መስከረም 28 ቀን 2005 ዓ.ም የሰጠው ውሳኔና የክልሉ ጠቅላይ ፍርድ ቤት በመዝገብ የሰጠው ውሳኔ ተሽሯል።
አመልካች ተጠሪ በቅጥር ግቢው ውስጥ የገነባችውን የመቃብር ቤት ግምት የመክፈል ኃላፊነት የለበትም በማለት ወስነናል።
በዚህ ፍርድ ቤት ያወጡትን ወጭና ኪሳራ ግራ ቀኙ ለየራሳቸው ይቻሉ።
መዝገቡ ወደ መዝገብ ቤት ይመለስ
No topics extracted.