No summary available.
መስከረም 23 ቀን 2006 ዓ.ም.
ዳኞች፡- ተገኔ ጌታነህ ተሻገር ገ/ሥላሴ አልማው ወል ረታ ቶሎሳ ሙስጠፋ አህመድ አመልካች፡- የገቢዎችና የጉምሩክ ባለስልጣን-የሐረር መቆጣጠሪያ ጣቢያ- ዐ/ሕግ ጌቱ ቀዎች ቀረቡ ተጠሪ፡- ሰይፈዲን አብዱልቃድር ጠበቃ ሻምበል ተሾመ ደምሴ ቀረቡ **
መዝገቡ ተመርምሮ ተከታዩ ፍርድ ተሰጥቷል።
**
ጉዳዩ የጉምሩክ ሕግንና አፈጻጸሙን መሰረት ባላደረገ መንገድ መኪናው ተይዞ ለቆየበት ጊዜ ይገኝ የነበረውን ገቢ ይከፈለኝ ጥያቄን የሚመለከት ነው።ክርክሩ የተጀመረው በሐረሪ ሕዝብ ክልላዊ መንግስት ከፍተኛ ፍርድ ቤት ሲሆን ከሳሽ የነበሩት የአሁኑ ተጠሪ ናቸው።የአሁኑ ተጠሪ ባሁኑ አመልካች ላይ የመሰረቱት ክስ ይዘቱ ባጭሩ፡ኮድ 3-00700 ሐረ ላንድ ክሩዘር የጭነት መኪና የሆነ ተሸከርካሪያቸውን በቆመበትና ምንም የኮንትሮባንድ ድርጊት ሳይፈፅም ጥቅምት 01 ቀን 2002 ዓ/ም አመልካች ከሕግ ውጪ መያዙንና ላለቅ ባለመቻሉ በፍርድ ቤት ክስ መስርተው መኪናው የተያዘው ከሕግ ውጪ መሆኑ ተረጋግጦላቸው መኪናው እንዲለቀቅ እስከፍድራል ጠቅላይ ፍርድ ቤት ሰበር ሰሚ ችሎት የተወሰነላቸውና መኪናውን መጋቢት 26 ቀን 2004 ዓ/ም በፍርድ ኃይል መረከባቸውን፣በዚህ ጊዜ ውስጥ ላያገኙ ይችሉ የነበረው የቀን ገቢ ብር 500.00 (አምስት መቶ ብር) ሁኖ በድምሩ የሁለት አመት ከስድስት ወራት ብር 450,000.00 (አራት መቶ ሃምሳ ሺህ ብር) ገቢ የቀረባቸው መሆኑን ገልጸው ይህንኑ የተቋረጠባቸውን ገቢ አመልካች ከተለያዩ ወጪና ኪሳራ ጋር ጭምር እንዲከፍል ይወሰንላቸው ዘንድ ዳኝነት መጠየቃቸውን የሚያሳይ ነው።
የአሁኑ አመልካች ለክሱ በሰጠው መከላከያ መልስም የመጀመሪያ ደረጃ መቃወሚያና የፍሬ ነገር ክርክሮችን አቅርቧል።በክርክሩም ጉዳዩ በፍርድ ቤት ላታይ የማይገባው መሆኑና መኪናው የጉምሩክ ስነ ሥርዓት ያልተፈፀመበት በመሆኑ በሕጉ በተሰጠው ስልጣን መሰረት ያከናወነው ተግባር መሆኑን፣የመኪናው ገቢም ቢሆን በተጠሪ የተገለጸው ሳይሆን ከክፍሉ ገቢዎች ባለስልጣን የተሰጠው ማስረጃ የሚያረጋግጠው ብር 3000.00 በአመት የሚያገኘው መሆኑንና በዚህ ሂሳብ ሲሰላም መኪናው ለቆመበት ጊዜ ከብር 10,500.00 (አስር ሺህ አምስት መቶ ብር) በላይ ላሆን የሚችልበት አግባብ የልለ መሆኑን ገልፆ ክሱ ውድቅ ላሆን ይገባል ሲል ተከራክሯል።የስር ፍርድ ቤትም የተጠሪን ምስክሮች ከሰማ በኋላ አመልካች አለኝ የሚለውና ከክፍሉ የገቢዎች ባለስልጣን የመኪናው አመታዊ የተጣራ ገቢ ብር 3000.00 ስለመሆኑ የሚገልጸውን ማስረጃ ውድቅ ከአደረገ በኋላ የተጠሪ ምስክሮች የሰጡትን ቃል መሰረት በማድረግ ገቢው በቀን ብር 500.00 መሆኑን ተቀብሎና መኪናው ስራ ላሰራባቸው የማይችላቸውን የእሁድ ቀናት ቀንሶ በጠቅላላው ብር 349,500.00 (ሶስት መቶ አርባ ዘጠኝ ሺህ አምስት መቶ ብር) ተጠሪ የተቋረጠባቸው መሆኑ ተረጋግጧል በማለት ይህንኑ ገንዘብ በታሪፉ መሰረት ከዳኝነት ገንዘብና ከ10% የጠበቃ አበል ጋር አመልካች እንዲከፍላቸው ሲል ወስኗል።በዚህ ውሳኔ አመልካች ባለመስማማት ይግባኙን ለሐረሪ ክልላዊ መንግስት ጠቅላይ ፍርድ ቤት ቢያቀርብም ይግባኙ በፍ/ብ/ሥ/ሥ/ሕ/ቁጥር 337 መሰረት ተሰርዞበታል።የአሁኑ የሰበር አቤቱታ የቀረበውም ይህንኑ ውሳኔ በመቃወም ለማስለወጥ ነው።
የአመልካች ነገረ ፈጅ ሚያዚያ 10 ቀን 2005 ዓ/ም በጻፉት አስር ገጽ የሰበር አቤቱታ በበታች ፍርድ ቤቶች ውሳኔ ላይ መሰረታዊ የሆነ የሕግ ስህተት ተፈጽሟል የሚሉበትን ምክንያት ዘርዝረው አቅርበዋል።ይዘቱም ባጭሩ፡የተጠሪ ክሱ የተመሰረተው በሕጉ አግባብ የውክልና ስልጣን ለተጠሪ ጠበቃ ሳይሰጥ መሆኑን፣አመልካች በሕጉ አግባብ በተሰጠው ሥልጣን መሰረት የፈፀመው ድርጊት ስለመሆኑ ገልፆ ከመከራከሩም በተጨማሪ መኪናው የሚያስገኘው አመታዊ ገቢን የሚያሳየው ማስረጃ ከሚመለከተው የገቢዎች ባለስልጣን ቀርቦ እያለ ማስረጃው ውድቅ መደረጉና የተጠሪ የሰው ምስክሮች ቃል ተቀባይነት አግኝቶ በቀን ብር 500.00 መሰረት ተደርጎ ካሳው መሰላቱ ከፍ/ብ/ሕ/ቁጥር 2090 እና 2011 ድንጋጌዎች ይዘትና መንፈስ ውጪ መሆኑን ዝርዝረው ውሳኔው እንዲሻር ዳኝነት መጠየቃቸውን የሚያሳይ ነው።አቤቱታው ተመርምሮም በሰበር ችሎቱ ላታይ ይገባዋል ተብሎ በመታዘዙ ለተጠሪ ጥሪ ተድርጎላቸው ቀርበው ግራ ቀኙ በጽሑፍ እንዲከራከሩ ተደርጓል።
የጉዳዩ አመጣጥ አጠር አጠር ባለመልኩ ከላይ የተገለፀው ሲሆን ይህ ችሎትም የግራ ቀኙን ክርክር ለሰበር አቤቱታው መነሻ ከሆነው ውሳኔ እና አግባብነት ካላቸው ድንጋጌዎች ጋር በማገናዘብ ጉዳዩ ለችሎቱ ሲቀርብ ከተያዘው ጭብጥ አንጻር በሚከተለው መልኩ መርምሮታል።እንደመረመረውም የዚህን ችሎት ምላሽ የሚያስፈልገው አብይ ነጥብ የአመልካች የሰነድ ማስረጃ ውድቅ ተደርጎ በተጠሪ የሰው ምስክሮች ብቻ ካሳው መወሰኑ ባግባቡ ነው? ወይስ አይደለም ? የሚለው ሁኖ አግኝቶታል።
No topics extracted.
ከክርክሩ ሂደት መገንዘብ የተቻለው ተጠሪ ለክርክሩ ምክንያት የሆነው ተሽከርካሪ ያላግባብ በአመልካች ተይዟል በሚል ክስ አቅርበው አመልካች ከሕግ አግባብ ውጪ የያዘው መሆኑ በፍርድ ተረጋግጦ መኪናው እንዲለቀቅላቸውና መኪናው ተይዞ ለቆመበት ጊዜ ገቢ እንዲከፈላቸው ተጠሪ ወደፊት ክስ አቅርበው የመጠየቅ መብታቸው እንዲጠበቅላቸው ዘንድ ዳኝነት ጠይቀው መኪናው እንዲለቀቅላቸው እና የጉዳት ኪሳራውን የመጠየቅ መብታቸው ተጠብቆ በበታች ፍርድ ቤቶች ውሳኔ ተሰጥቶ ውሳኔው እስከዚህ ሰበር ችሎት ደርሶ የጸና መሆኑን የሰ/መ/ የሚያረጋግጠው ጉዳይ መሆኑን፣አመልካች አሁን አጥብቆ የሚከራከረው የጉዳት ካሳ መጠን የተሰላበት አግባብ ከሕግ ውጪ የተጠሪ የሰው ምስክሮች ቃል ብቻ መሰረት ተደርጎና ከሚመለከተው አካል የቀረበው የአመልካች የሰነድ ማስረጃ ግን ውድቅ ተደርጎ ስለመሆኑ ዘርዝሮ መሆኑን ነው።
በመሆኑም የስር ፍርድ ቤቶች አመልካችን ለጉዳቱ ሀላፊ ነው ያሉት ቀድሞ በፍርድ ያለቀውን ጉዳይ መሰረት በማድረግ በመሆኑና አመልካችም የተጠሪን ክስ ነጣጥሎ በማቅረብ ላይ ግልጽ ቅሬታ ያላቀረበበት ጉዳይ ከመሆኑም በላይ ጉዳዩ ለዚህ ችሎት ሲቀርብም በጭብጥነት ያልተያዘ በመሆኑ የኃላፊነት ጭብጥ በዚህ ችሎት አሁን የሚታይበትን አግባብ አላገኘንም።በዚህ ችሎት መታየት ያለበት ነጥብ የጉዳት ካሳ መጠኑ የተወሰነበት መንገድ ተገቢ መሆን ያለመሆኑን የሚመለከት ስለሆነ ይህንኑ ጭብጥ ግንዛቤ ውስጥ አስገብተን ጉዳዩን እንደሚከተለው ተመለክተናል።በመሰረቱ ለደረሰው ጉዳት አላፊ መሆኑ በህግ የታወቀ ሰው የጉዳት ኪሳራ መክፈል ያለበት ሲሆን ጉዳት የደረሰበት ሰው የሚካሰውም ለጉዳቱ ተመዛዛኝ የሆነ ኪሳራ በመከፈል እንደሆነ በፍ/ህ/ቁ/ 2090(1) ተመልክቷል። የኪሳራው ልክም ሀላፊነቱን ያመጣው ጉዳይ በተበዳዩ ላይ ከደረሰው ጉዳት ጋር እኩል ሆኖ በመመዛዘን መሆን እንደሚገባ የፍ/ህ/ቁጥር 2091 ድንጋጌ በግልጽ ያሳያል።ጉዳዩ የቀረበለት ፍርድ ቤትም በሚቀርቡለት ማስረጃዎች የጉዳቱን መጠንና ላከፈል የሚገባውን ካሳ መጠን አመዛዝኖ በህጉ መሰረት መወሰን የሚገባው ስለሆነ ከፍ/ብ/ሕ/ቁጥር 2141፣2152 እና 2153 ድንጋጌዎች ይዘት የምንረዳው ሲሆን ጉዳቱ ያስከተለውን ኪሳራ በትክክል ለመወሰን ያልተቻለ እንደሆነም በፍ/ህ/ቁ/2102 በተመለከተው አግባብ በርትዕ ለመወሰን እንደሚቻል ሕጉ ያስቀምጣል። እንዲህ ሲደረግ ግን ለጉዳዩ የቀረቡት ማስረጃዎች ለጉዳዩ አግባብነት፣ጥንካሬና ክብደት ያላቸው መሆኑን በቅድሚያ ማረጋግጥን የግድ ይሐል።በመሆኑም ፍርድ ቤቱ ማስረጃዎቹ በሕጉ አግባብ ከቀረቡለት ደግሞ ማስረጃዎችን የማይቀበልበትን ሕጋዊ ምክንት በግልጽ ማስፈር ያለበት መሆኑን የሚሰጠው ምክንያትም ሕጋዊ መሰረት ያለው መሆን ያለበት ስለመሆኑ በፍ/ብ/ሥ/ሥ/ሕ/ቁጥር 138፣ 180 (1) እና ልሎች ስለማስረጃ አቀራረብና አቀባበል ከሚደነገጉት የስነ ስርዓት ሕጉ ድንጋጌዎች ይዘትና መንፈስ የምንገነዘበው ጉዳይ ነው።
በዚህ ጉዳይ የስር ፍርድ ቤት የጉዳት ካሳ ግምቱን የወሰነው በተጠሪ በኩል የቀረቡትን የሰው ምስክሮች ቃል ተቀብሎ በአንጻሩ ግን አመልካች በሕጉ አግባብ በመኪናው የአመታዊ ገቢ ግብር ተጠሪ እንደሚከፍሉበት ያሳያል የተባለውን የሰነድ ማስረጃ በማለፍ ነው። በአመልካች በኩል የቀረበዉ ይህ ማስረጃ በበታች ፍርድ ቤቶች ተቀባይነት ያጣበት ሕጋዊ ምክንያት ግን በግልጽ በውሳኔው ላይ አልሰፈረም።በአንድ የመንግስት ባለስልጣን የተረጋገጠ የሰነድ ማስረጃ ደግሞ የማስረጃነት ዋጋ ሳይሰጠው የሚታለፍበት አግባብ በሕጉ መሰረት ተቃውሞ ቀርቦበት ዋጋ የልለው መሆኑ ሲረጋገጥ ስለመሆኑ ከፍ/ብ/ሕ/ቁጥር 2010 እና 2011 እንዲሁም ከፍ/ብ/ሥ/ሥ/ሕ/ቁጥር 140 ድንጋጌዎች ይዘትና መንፈስ የምንረዳው ጉዳይ ነው።ጉዳዩ በመኪና ገቢ የግብር መጠን የሚጣልበትን አግባብ የሚያስረዳ ሙያዊ ምስክርነት ማስቀርብን የሚያስፈልግ መሆኑንም የክርክሩ ባህርይ ያስገነዝባል።እንዲህ በሆነ ጊዜ ደግሞ በፍ/ብ/ሥ/ሥ/ሕ/ቁጥር 136 ድንጋጌ አኳያ ከሚመለከተው አካል የሙያ ምስክር አስቀርቦ ከተጠሪ ምስከሮች ቃል፣አመልካች አለኝ ከሚለው የሰነድ ማስረጃ ይዘት ጋር ማመዛዘንና ዳኝነት መስጠትን የግድ የሚል ነው።
ስለሆነም የስር ፍርድ ቤት አመልካች ያቀረባቸውን የሰነድ ማስረጃዎችን ትክክለኛና ሕጋዊ ያለመሆናቸውን በተገቢው መንገድ ሳያረጋግጥ ለተጠሪ ምስክሮች ቃል ብቻ ክብደት ሰጥቶ የጉዳት ካሳ መጠኑን መወሰኑ የማስረጃ አቀባበል መርህንና የጉዳት ካሳ መጠን መወሰን ያለበት ከደረሰው ጉዳት ጋር እኩል ሁኖ ተመዛዝኖ ስለመሆኑ በፍ/ብ/ሕ/ቁጥር 2090 እና 2091 ድንጋጌዎች ስር የተመለከተውን መርህ የሚጥስ ሁኖ አግኝተናል።በልላ በኩል የተጠሪ መኪና ለበርካታ ወራት ያለስራ በአመልካች ሕገ ወጥ ተግባር መቆሙ የተረጋገጠ በመሆኑ ተጠሪ የተቋረጠባቸው ገቢ የለም ብሎ ለማለት የሚቻልበት አግባብም የለም።ስለሆነም ለካሳው መጠን አወሳሰን ይረዳ ዘንድ በተጨማሪነት ላጣሩ የሚገባቸው ፍሬ ነገሮች ያሉ ሁነው አግኝተናል።ከዚህ አንጻር ጉዳዩን ስንመለከተውም፡-
አመልካች የተጠሪን መኪና አመታዊ የተጣራና ግብር የሚከፈልበትን የገቢ መጠን ያሳያል በማለት ያቀረበው ሰነድ በፍ/ብ/ሕ/ቁጥር 2010 መሰረት ተቃውሞ የሚቀርብበትና በፍ/ብ/ሕ/ቁጥር 2011 አግባብ የማስረጃነት ዋጋ የማይሰጥበት ሕጋዊ ምክንያት አለ? ወይስ የለም?
የተጠሪ መኪና አመታዊ የተጣራ ገቢ ብር 3000.00 ተብሎ የተወሰነበት አግባብ ሕጋዊ መሰረት አለው?
ወይስ የለውም? ፤የሚመለከተው የክፍሉ የገቢዎች ባለስልጣን የተጠሪን አይነት መኪና ላይ ግብር የሚያስከፍልበት አሰራር ምንድው?
እነዚህ ፍሬ ነገሮች በሕጉ አግባብ ሳይጣሩና ሳይሟሉና የጉዳት ካሳ መጠኑ መወሰን የጉዳት ካሳ አወሳሰን መሰረታዊ ዓላማና የዳኝነት አሰጣጥ ስርዓትን የሚጥስ መሆኑን ተረድተናል።ሲጠቃለልም በጉዳዩ ላይ የተሰጠው ውሳኔ ከላይ በተመለከቱት ምክንያቶች ተቀባይነት የሚሰጠው ሁኖ ስላላገኘነው ውሳኔው በከፊል መሰረታዊ የሆነ የሕግ ስህተት ያለበት በመሆኑ ተከታዩን ወሰንናልወ።
በሐረሪ ሕዝብ ክልላዊ መንግስት ከፍተኛ ፍርድ ቤት በመ/ በቀን 22/04/2005 ዓ/ም ተሰጥቶ በክልሉ ጠቅላይ ፍርድ ቤት ይግባኝ ሰሚ ችሎት በመ/ቁ/ 02400 መጋቢት 05 ቀን 2005 ዓ/ም የፀናው ፍርድ በፍ/ሥ/ሥ/ህ/ቁ/ 348(1) መሰረት አሻሽለናል።
የሥር ፍርድ ቤቶች አመልካች በተጠሪው መኪና ላይ በፈፀመው ሕገ ወጥ ተግባር ለደረሰው ጉዳት ሀላፊ ነው በሚል የሰጡት የውሳኔ ክፍል የሚነቀፍበት ምክንያት የለውም ብለናል፤ጸንቷል።
የጉዳት ካሳ መጠኑን በተመለከተ የተሰጠው ውሳኔ ግን በተገቢው መንገድ ለጉዳዩ አግባብነት ባላቸው ማስረጃዎች ሳይጣራ የተሰጠ በመሆኑ ሙሉ በሙሉ ተሸራል።በመሆኑም የሐረሪ ክልል ከፍተኛ ፍርድ ቤት ክርክሩን በመ/ ቀጥሎ በፍርደ ሐተታው ላይ ከተራ ቁጥር 1 እስከ 3 የተጠቀሱትን ነጥቦችንና ለትክክለኛ ፍትህ አሰጣጥ አስፈላጊ ናቸው የሚላቸውን ልሎች ነጥቦችን ለጉዳዩ አግባብነት ያላቸውን ማስረጃዎች ከሚመለከተው የክፍሉ የገቢዎች ባለስልጣን እንዲቀርቡ በማድረግና የባለሙያ አስተያየት ሁሉ በመስማት በጉዳዩ ላይ ተገቢ ነው የሚለውን ውሳኔ እንዲሰጥበት በማለት ጉዳዩን በፍ/ብ/ሥ/ሥ/ሕ/ቁጥር 343(1) መሰረት መልሰን ልከንለታል።ይጻፍ።
በዚህ ችሎት ለተደረገወ ክርክር የወጣውን ወጪና ኪሳራ የየራሳቸውን ይቻሉ ብለናል።