No summary available.
መስከረም 22 ቀን 2006 ዓ.ም.
ዳኞች፡- ተሻገር ገ/ሥላሴ አልማው ወል ዓላ መሐመድ ረታ ቶሎሳ ሙስጠፋ አህመድ አመልካች፡- የኢትዩጵያ ገቢዎችና ጉምሩክ ባለስልጣን ዐ/ሕግ መቅደስ ብሩ ቀረቡ ተጠሪ፡-
መዝገቡ ተመርምሮ ተከታዩ ፍርድ ተሰጥቷል።
**
ጉዳዩ የወንጀል ሲሆን ክርክሩ የተጀመረው በአዳማ ልዩ ዞን ከፍተኛ ፍርድ ቤት አመልካች ባአሁኑ ተጠሪዎች እና በሐናን በላይ ላይ በመሰረተው ክስ መነሻ ነው።
ተጠሪዎች የተከሰሱት በሁለት ምድብ በተከፈለ ክስ ሲሆን አንደኛው ክስ ባአሁኑ 1ኛ ተጠሪ ላይ የቀረበ ሁኖ ይዘቱም የተጨማሪ እሴት ታክስ አዋጅ ቁጥር 285/94 በአዋጅ ቁጥር 609/2001 አንቀጽ 50(ለ) እና የተጨማሪ እሴት ታክስ አዋጅ ቁጥር 285/1994 አንቀጽ 22(11) ስር የተመለከተውን በመተላላፍ የንግድ ፈቃድ ቁጥር 06/64213/01/00000040 መሰረት በሬስቶራንት ንግድ ላይ ተሰማርቶ ከሕዳር 16 ቀን 2004 ዓ/ም ጀምሮ የተጨማሪ እሴት ታክስ ከፋይ በመሆኑ 0032 በሆነ ተመዝግቦ እያለ የካቲት 11 ቀን 2004 ዓ/ም ከቀኑ በግምት 6፡05 ሰዓት በአዳማ ከተማ ቀበል 05 ክልል ውስጥ በሚገኘው የቤት ቁጥር 840 በሆነ የኬሮድ ባርና ሬስቶራንት ውስጥ ይታገስ አሸናፊ፣ግርማ ሚኮሬና ኮንስታብል ኢብራሂም አማን የተባሉ ሰዎች ሁለት ቅቅል ምግብና እና ሶስት ለስላሳ በአሁኗ ሁለተኛ ተጠሪና በስር ሶስተኛ ተከሳሽ በነበረ ሐናን በላይ በከል ብር 67.00 የሆነ ዋጋ ያለተጨማሪ እሴት ታክስ ደረሰኝ መሸጣቸውን ዘርዝሮ ተጠሪው የግል ባለንብረት በመሆናቸው የወንጀል ተጠያቂነት አለባቸው በማለት ክስ ማቅረቡን የሚያሳይ ሲሆን 2ኛው ክስ ባሁኗ 2ኛ ተጠሪ ላይ የቀረበ ሁኖ ዝርዝር ይዘቱም ተከሳሾቹ የተጨማሪ እሴት ታክስ አዋጅ ቁጥር 285/1994 አንቀጽ 55 እና በማሻሻያው አዋጅ ቁጥር 609/01 አንቀጽ 50(ለ) ስር የተመለከተውን በመተላለፍ በ1ኛው ክስ በተጠቀሰው ጊዜና ቦታ እንዲሁም ለአግልግሎቱ ተጠቃሚዎች የብር 67.00 ሽያጭ ደረሰኝ መቁረጥ ሲገባት ያለተጨማሪ እሴት ታክስ ደረሰኝ ሽያጩ እንዲፈፅም በማድረጓ 1ኛውን ተጠሪ የመርዳት ወንጀል ፈፅማለች የሚል ነው። 3ኛው ክስ በስር ሶስተኛ ተከሳሽ በነበረችው ሐናን በላይ ላይ የቀረበ ሁኖ በ1ኛው ክስ በተመለከተው ጊዜና ቦታ እንዲሁም ለአገልግሎት ተጠቃሚዎች ደረሰኝ ቆርጣ መስጠት ሲገባት ይህንኑ ባለመፈፀሟ አዋጅ ቁጥር 285/1994 አንቀጽ 55 እና ማሻሻያ አዋጅ ቁጥር 609/2001 አንቀጽ 50(ለ) ስር የተመለከተውን ተላልፋለች የሚል ይዘት ያለው ነው።
ተጠሪዎች የወንጀል አፈፃፀሙን ክደው ተከራክረው ዐ/ሕግ አሉኝ ያላቸውን ማስረጃዎችን በማቅረብ አስምቷል።ከዚህም በኋላ አመልካቾች እንዲከላከሉ ተደርጎ መከላከያ ማስረጃዎቻቸውን አሰምተዋል።ጉዳዩን በመጀመሪያ ደረጃ የተመለከተው ፍርድ ቤትም የአቃቤ ህግ ምስክሮች ከፍለው የነበረው ገንዘብ ደረሰኝ አልተሰጠንም በሚል ምክንያት መልሰው መውሳዳቸው ሽያጭ ያለመፈፀሙን እንደሚያሳይ፣ሽያጭ ተፈጽሟል ከተባለም 1ኛ ተጠሪ የቫት ደረሸኝ አሳትሞ ለተገልጋዮች እየቆረጠ የሚሰጥ መሆኑ መረጋጡን፣ተጠሪው የሽያጭ ማሽኑን በ25/05/04 ዓ/ም ገዝተው በ01/06/2004 ዓ/ም የተረከቡ መሆኑንና ወንጀሉ የተፈጸመበት ጊዜ በ11/06/2004 ዓ/ም አንፃር ሲታይ ስልጠና እስከሚያገኙ ድረስ ጊዜው አጭር መሆኑን፣ክሱ ለአቃቤ ሕግ ምስክሮች ደረሰኝ አልተሰጠም የሚል ሁኖ በማስረጃ የተረጋገጠው ግን ምስክሮቹ በእጅ የተፃፈ ደረሰኝ ተሰጥቷቸው በማሽን የተፃፈ ደረሰኝ ካልሆነ አልንቀበልም ማለታው መሆኑን፣ደረሰኞቹ በተጨማሪ ታክስ ምጣኔው ላይ ልዩነት የልላባቸው መሆኑንና በእጅ የሚፃፈው ደረሰኝም በተገቢው አካል ጥያቄ ቀርቦ 1ኛው ተጠሪ ያሳተሙትና ጥቅም ላይ ላውል የሚችል መሆኑን በምክንያትነት ይዞ ተጠሪዎች በመከላከያ ማስረጃዎቻቸው የአቃቤ ሕግን ማስረጃዎች ጥርጣሬ ውስጥ ከተዋል በማለት ተጠሪዎችን በነፃ አሰናብቷዋል።
በዚህ ውሣኔ አመልካች ቅር በመሰኘት ይግባኛቸውን ለአሮሚያ ክልል ጠቅላይ ፍርደ ቤት ይግባኝ ሰሚ ችሎት ይግባኙን ቢያቀርቡም ተቀባይነት አላገኘም።የአሁኑ የሰበር አቤቱታ የቀረበውም በስር ፍርድ ቤቶች የተሰጠው የተጠሪዎች ነፃ መለቀቅ ውሣኔ መሰረታዊ የሆነ የሕግ ስህተት የተፈፀመበት በመሆኑ ላታረም ይገባዋል በማለት ሲሆን የአመልካች መስሪያ ቤት አቃቤ ህግ ጥር 03 ቀን 2005 ዓ/ም የተፃፈ የሰበር ማመልከቻ ስላቀረቡ ነው።
የሰበር አቤቱታው ተመርምሮ ተጠሪዎች ሽያጩ አልተከናወነም በሚል ነፃ ተብለው የመወሰኑን አግባብነት ለመመርመር ሲባል ለሰበር ችሎቱ እንዲቀርብ ተደርጎ የግራ ቀኙ ክርክር በፅሑፍ ተደርጓል።
የጉዳዩ አመጣጥ አጠር ባለ መልኩ ከላይ የተገለፀው ሲሆን ይህ ችሎትም የግራ ቀኙን ክከርክር ለሰበር አቤቱታው መነሻ ከሆነው ውሣኔ እና አግባብነት ካላቸው ድንጋጌዎች ጋር በማገናዘብ በሚከተለው መልኩ መርምሮታል።፡ ከክርክሩ ሂደት መገንዘብ የተቻለው አመልካቾች ፈፅመዋል ተብለው የተከሰሱበትን የወንጀል ድርጊት ለማስረዳት ዐ/ሕግ ያቀረቧቸው ሁለት ምስክሮች ያረጋገጡት ፍሬ ነገር ኬሮድ ምግብ ቤት ከተጨማሪ እሴት ታክስ ደረሰኝ ውጪ ሽያጭ መፈፀሙ የሚያሳይ ሪፖርት ደርሷቸው መስሪያ ቤቱ ወደ ቦታው በክስ በተገለጸው ጊዜ የላካቸው መሆኑን፣ወደ ቦታው ደርሰውም ሶስት ምግብና ሶስት ለስላሳ በማዘዝ ከተጠቀሙ በኋላ ብር 100.00 ሂሳብ ከስር 3ኛ ተከሳሽ ለነበረችው አስተናጋጅ ሰጥተው እሷም ለአሁኗ 2ኛ ተጠሪ ከሰጠች በኋላ መልስ ብር 33.00 ያለደረሰኝ የመለሰችላቸው መሆኑን፣1ኛ ተጠሪም በጊዜው በቦታው ላይ እንዳልነበርና በኋላ ከመጣ በኋላ ምስክሮቹ ሲጠይቁትም ለጠየቀን እንሰጣለን ብሎ እንደመለሰላቸውና ከዚህ በኋላ ተከሳሾችን በቁጥጥር ስር ያዋሐቸው መሆኑን ነው።ተጠሪዎች ያቀረቧቸው መከላከያ ምስክሮች ደግሞ ድርጊቱ ተፈጸመ በተባለበት ምግብ ቤት በአስተናጋጅነት የሚሰጡ ሁነው በክሱ በተጠቀሰው ጊዜ ሶስት ሰዎች ወደ ምግብ ቤቱ መጥተው ምግብና ለስላሳ አዝዘው ከተጠቀሙ በኋላ የማሽን ደረሰኝ 3ኛ ተከሰሽ የሆነችውን አስተናጋጅ አምጪልኝ በማለት ሲጠይቋት ማሽኑ ስራ ስላልጀመረ በእጅ የሚሞላ ደረሰኝ አመጣላችኋለሁ ስትል በእጅ የሚፃፍ ደረሰኝ አንፈልግም፣የማሽን ነው እንጂ በማለት እምቢ ብለው ሄደው ከሶስት ደቂቃ በኋላ ተመልሰው በመምጣት ለአገልግሎቱ የከፈሉትን ብር 100.00 መልስ መውሰዳቸውን፣ቤቱ በእጅ የተጻፈ ደረሰኝ እንደሚጠቀምና ይህንኑ ደረሰኝ ምስክሮቹ ወስደው ቤቱን ያሸጉና ስራው የተከለከለ መሆኑን ሲሆን የሰነድ ማስረጃዎች ደግሞ የተጨማሪ እሴት ታክስ አስመልክቶ በአዲስ ዘመን ጋዜጣ በህዳር 30 ቀን 2004 ዓ/ም ማስታወቂያ መውጣቱን፣1ኛው ተጠሪ በ08/05/2004 እና 09/06/2004 ዓ/ም ለተፈፀሙ ሽያጮችም ደረሰኝ መቆረጣቸውን፣ተጠሪው ማሽኑን በ25/05/2004 ዓ/ም ገዝተው በ01/06/2004 ዓ/ም መረከባቸውን እንዲሁም 1ኛ ተጠሪ የተጨማሪ እሴት ታክስ ደረሰኝ ፍቃድ ከምስራቅ ሸዋ ዞን ገቢዎች ፅ/ቤት አግኝተው ደረሰኙን አሳትመው ወደ ስራው የገቡ መሆኑ በሰውና በሰነድ ማስረጃዎች መረጋገጡን የስር ፍርድ ቤት በውሳኔው ላይ በግልጽ አስፍሯል።
እንግዲህ ፍሬ ነገርን የማጣራትና ማስረጃን የመመዘን ስልጣን የስር ፍርድ ቤት ፍሬ ነገሩን አጣርቶና ማስረጃን መዝኖ የደረሰባቸው ድምዳሜዎች ከላይ የተጠቀሱት ሲሆን ተመሳሳይ ስልጣን ያለው የክልሉ ይግባኝ ሰሚ ፍርድ ቤትም የሥር ፍርድ ቤትን የማስረጃ ምዘና ድምዳሜ ሙሉ በሙሉ መቀበሉን የክርክሩ ሂደት ያስገነዝባል።በመሆኑም ይህ ችሎት በኢ.ፍ.ዲ.ሪ ሕገ መንግስት አንቀጽ 80(3(ሀ) እና አዋጅ ቁጥር 25/1988 አንቀጽ 10 ድንጋጌዎች ይዘትና መንፈስ አንፃር ፍሬ ነገርን ማጣራት ወይም ማስረጃን የመመዘን ስልጣን ስለልለው ስልጣን ባላቸው ፍርድ ቤቶች ስለመረጋገጣቸው የተጠቀሱትን ነጥቦች እንዳሉ የሚቀበላቸው ይሆናል።እዚህን ይዘን ወደ ሕጉ ስንመጣም ተጨማሪ እሴት ታክስ ጉዳይ የሚገዛው ራሱን በቻለ ሕግ ስለመሆኑ ከአዋጅ ቁጥር 285/1994 እና ከማሻሻያው አዋጅ ቁጥር 609/2001 ድንጋጌዎች የምንገነዘበው ጉዳይ ነው።እነዚህ ሕጎች የወንጀል ተጠያቂነት የሚያስከትሉ ተግባራትን ዘርዝረው ማስቀመጣቸውን ድንጋጌዎቹ ያሳያሉ።አዋጆቹን የማስፈፀም ስልጣንና ተግባርም የፍድራል መንግስት ስለመሆኑ የኢ.ፍ.ዲ.ሪ ሕገ መንግስት አንቀጽ 99 እና ይህንኑ ድንጋጌ መሰረት በማድረግ የፍድሬሽን ምክር ቤትና የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ሚያዚያ 03 ቀነ 1994 ዓ/ም ባደረጉት ሁለተኛ መደበኛ የጋራ ስብሰባ መወሰኑ የሚታወቅ ነው።በመሆኑም የአዋጆችን የአፈጻጸም የመቆጣጠር ስልጣንን መሰረት አድርጎ የተጠሪዎች ጠበቃ ያቀረቡት ክርክር የሕግ መሰረት የልለው ሁኖ ተገኝቷል።የተጨማሪ እሴት ሽያጭ ተከናወነ የሚባልበትን አግባብም በአዋጅ ቁጥር 285/1994 አንቀጽ 11(1)(2)፣ 22(1) እና (3) በአዋጅ ቁጥር 609/2001 እንደተሻሻለው በግልጽ ተመልክቷል።የአዋጁ አንቀጽ 11(1) በመርህ ደረጃ ሽያጭ ተከናወነ የሚባለው ለግብይቱ የተጨማሪ እሴት ታክስ ደረሰኝ ሲሰጥ ነው በሚል የሚያስቀምጥ ሲሆን በንዑስ ቁጥር ሁለት ድንጋጌ ስር ደግሞ እቃዎቹ ለተረካቢው ዝግጁ ሁነው መቀመጣቸው፣የእቃዎቹ ርክርብ ሽያጭ ወይም ማስተላለፍ መፈፀም ወይም የአገልግሎት መሰጠት፣እንዲሁም የእቃዎችን ርክክብ ማጓጓዝን የሚያካትት ሲሆን የእቃዎችን ማጓጓዝ ሲጀመር ሽያጭ ተከናወነ ብሎ ለመደምደም የሚቻል መሆኑን በልዩ ሁኔታነት ዘርዝሮ አስቀምጧል። ከእነዚህ ድንጋጌዎች በግልጽ መረዳት የሚቻለው ሽያጭ ተከናወነ ለማለት ለተከናወነው ግብይት ሂሳብ መክፈሉ ወይም አለመከፈሉ በቅድመ ሁኔታ የተቀመጠ ሳይሆን ሕጉ ትኩረት የሚያደረገው እቃዎቹ ለተረካቢው ዝግጁ ሁነው በተቀመጡ ጊዜ አገልግሎቶች በሚሰጡበት እና የመሳሳሉት ተግባራት መፈጸማቸው ላይ ነወ።በመሆኑም እነዚህ ተግባራት በሚፈጽሙበት ጊዜ የተጨማሪ እሴት ደረሰኝ ባይቆረጥም እንኳን ሽያጩ እንደተከናወነ ሕጉ እንደሚቆጥር የድንጋጌዎች ይዘትና መንፈስ ያሳያል።በመሆኑም የስር ፍርድ ቤት ለጉዳዩ ቀጥተኛ ተፈፃሚነት ያለው የሕግ ማእቀፍ ሽያጭ ተከናወነ የሚባልባቸውን ሁኔታዎችን ለይቶ አስቀምጦ እያለ በዚህ ረገድ ልዩ ሕግ የደነገገው ነገር እንደልለ በመቁጠር በፍትሐ ብሕር ሕጉ ስለሽያጭ የሚገዙትን ድንጋጌዎች ለጉዳዩ ተፈጻሚ ማድረጉ አግባብነት ያልነበረው ሁኖ አግኝተናል።
ቀጥሎ የተመለከትነው ተጠሪዎች ከወንጀል ተጠያቂነት ነፃ ናቸው ተብሎ የተሰጠው የውሳኔ ክፍል ውጤቱ መሰረታዊ የሆነ የሕግ ስህተት ያለበት መሆን ያለመሆኑ ነው። በመሰረቱ አንድ ወንጀል ተደረገ የሚባለው ወንጀሉን የሚያቋቋሙት ሕጋዊ፣ግዙፋዊ እና ሞራላዊ ፍሬ ነገሮች በአንድነት ተሟልተው ሲገኙ ብቻ መሆኑን በአዋጅ ቁጥር 414/1996 የወንጀል ሕጉ አንቀጽ 23(2) በግልፅ ደንግጓል።እንግዲህ አንድን ድርጊት ወንጀል ነው ብሎ ለመወሰን ሕጋዊ፣ግዙፋዊ እና ሞራላዊ ፍሬ ነገሮች ተጣምረው መገኘት የግድ ይላል።በተያዘው ጉዳይ የስር ፍርድ ቤት ተጠሪዎችን ነፃ በማድረግ ላወሰን የቻለው ሽያጩ አልተከናወነም በሚል ብቸኛ ምክንያት ሳይሆን የአቃቤ ሕግ ምስክሮች በእጅ የተፃፈ የቫት ደረሰኝ አንቀበልም ማለታቸው በተጠሪዎች የመከላከያ ማስረጃዎች መረጋገጡን ተቀብሎ 1ኛው ተጠሪ ለቫት ከተመዘገቡበት፣ማሽኑን ከገዙበትና ከተረከቡት ጊዜ አንፃር ሲታይ ድርጊቱ ተፈጸመ የተባለበት ጊዜ አጭርና ለማሽኑ አጠቃቀም ስልጠና የሚያስፈልግ መሆኑን ግንዛቤ ውስጥ አስገብቶ ጭምር ነው።ከዚህም መረዳት የሚቻለው ማሽኑ እያለ ሕጋዊነቱ በተረጋገጠው ደረሰሰኝ በእጅ ተፅፎ ለአቃቤ ሕግ ምስክሮች የሽያጭ ደረሰኙ ላሰጥ የነበረ መሆኑ ፍሬ ነገሩን የማጣራትና ማስረጃን የመመዘን ስልጣን ባላቸው የበታች ፍርድ ቤቶች መረጋገጡን ነው።እንዲህ ከሆነ ተጠሪዎች በወቅቱ ሽያጩን ያለቫት ደረሰኝ ለማከናወን ፍላጎትና ዝግጁነት የነበራቸውና የወንጀል ድርጊቱን ለመፈፀም የሓሳብ ክፍላቸው ተሟልቷል ለማለት የሚቻልበት አግባብ የለም።በእርግጥ ለቫት የተመዘገበና ማሸኑን የተረከበ የቫት ተመዝጋቢ ሽያጩን ማከናወን ያለበት በማሽኑ ደረሰኝ መሆኑ በሚንስትሮች ምክር ቤት በወጣው ደንብ ቁጥር 139/1999 የተደነገጉ ሲሆን ማሽኑ ጋር ተገቢውን ስልጠና መውሰድም ግድታ መሆኑ የሚታመን ቢሆንም ማሽኑ ገብቶ በአጭር ጊዜ ውስጥ ከማሽኑ አሰራር ጋር ባለመታዋወቅ በእጅ በተፃፈ ሕጋዊ ደረሰኝ ሽያጩን ያከናወነ ሰው በአቃቤ ሕግ በኩል በቀረበው ክስ አቀራረብ አይነት በወንጀል እንዲጠየቅ ማድረግ በኢ.ፍ.ዲ.ሪ የወንጀል ሕግ አንቀጽ 23 (2)፣58 (3) ስር የተመለከቱትን መርሆዎች የሚጥስ በመሆኑ ተቀባይነት ላሰጠው የሚችል አይደለም።በመዝገቡ ከተያዘውና በፍሬ ነገር ደረጃ ከተረጋገጠው የጉዳዩ ልዩ ባህርይ ስንነሳ ተጠሪዎች የወንጀል መስራት ሓሳብ ነበራቸው ለማለት የሚያስችል የፍሬ ነገር ምክንያት አላገኘንም።ሲጠቃለልም የበታች ፍርድ ቤቶች በፍሬ ነገር ያረጋገጧቸው ነጥቦች በዚህ ችሎት የሚለወጡበትን አግባብ ስላላገኘንና በዚህ ረገድ የቀረቡት የአመልካች የቅሬታ ነጥቦች የማስረጃ ምዘና እንጂ የመሰረታዊ ሕግ ስህተትን መመዘኛ የማያሟሉ ሁነው ስለአገኘናቸው የበታች ፍርድ ቤቶች ተጠሪዎችን በነፃ በማሰናበት የሰጡት የውሳኔ ክፍል የሚነቀፍ ባለመሆኑ መሰረታዊ የሆነ የሕግ ስህተት የለበትም በማለት ተከታዩን ወስነናል።
ው ሣ ኔ
በአዳማ ልዩ ዞን ከፍተኛ ፍርድ ቤት በመ/ መስከረም 10 ቀን 2005 ዓ/ም ተሰጥቶ በክልሉ ጠቅላይ ፍርድ ቤት ይግባኝ ሰሚ ችሎት በመ/ ህዳር 27 ቀን 2005 ዓ/ም የጸናው ውሳኔ በወ/መ/ሥ/ሥ/ሕ/ቁጥር 195(2(ሀ)) መሰረት ጸንቷል።
ተጠሪዎች በነፃ እንዲሰናበቱ በተሰጠው ውሳኔ መሰረታዊ የሆነ የሕግ ስህተት የለም ብለናል።
No topics extracted.