No summary available.
መስከረም 20 ቀን 2006 ዓ.ም ዳኞች፡- ተሻገር ገብረሥላሴ አልማው ወል ዓላ መሐመድ ረታ ቶሎሳ ሙስጠፋ አህመድ አመልካች፡- አቶ አብድልቀድር ሁሴን ቀረቡ ተጠሪ፡- የአዲስ ከተማ ክፍለ ከተማ አነስተኛ ግብር ከፋይ ቅርንጫፍ ጽ/ቤት ዐ/ሕግ ሜሮን ግርማ ቀረቡ ጉዳዩን መርምረን የሚከተለውን ፍርድ ሰጥተናል
ጉዳዩ የቀረበው አመልካቾች የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ግብር ይግባኝ ሰሚ ጉባኤ የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር የይግባኝ ፍርድ ቤት ሰበር ችሎት የሰጡት ውሳኔ መስራዊ የሀግ ሥህተት ያለበት በመሆኑ በሰበር ይታይልኝ በማለት የቀረቡትን የሰበር አቤቱታ አጣርቶ ለመወሰን ነው። ጉዳዩ በተጠሪ የተወሰነው የገቢ ግብርና የተጨማሪ እሴት ታክስ ግብርን የሚመለከት ነው።በግብር ይግባኝ ሰሚ ጉባኤው አመልካች ይግባኝ ባይ፣ተጠሪ መልስ ሰጭ በመሆን ተከራክረዋል።
መልስ ሰጭ ገቢዬንና የንግድ ሥራዬን በአግባቡ ሳያጠናና በቂ ማስረጃ ሳይኖረው ባለፈው ዓመት የከፈልኩትን ገቢ ግብር እጥፍ እንድከፍል ወስኖ ውሳኔ ማስታወቂያ ደርሶኛል። እንደዚሁም ይግባኝ ባይ የተጨማሪ እሴት ታክስ ተመዝጋቢ ሳልሆን የተጨማሪ እሴት ታክስ ውሳኔ ማስታወቂያ ደርሶኛል።
ስለዚህ ይግባኝ ባይ ከሕግ ውጭ የሰጠው ውሳኔ ተሸሮ ባለፈው ዓመት በከፈልኩት መሰረት በቁርጥ እንድከፍል ውሳኔ ይሰጥልኝ በማለት ይግባኝ ቅሬታውን አቅርቧል። መልስ ሰጭ በበኩሉ የይግባኝ ባይ የቀን ገቢ በኮሚቴ ተጠንቷል፡፤ ገማች ኮሚቴ ባጠናው የጥናት ውጤት መሰረት ገቢ ግብሩ ተስተካክሎ መወሰኑ በአግባቡ ነው። የይግባኝ ባይ የቀን ገቢ ከብር 1700 (አንድ ሺ ሰባት መቶ ) በላይ መሆኑ የተረጋገጠ ስለሆነ ለተጨማሪ እሴት ታክስ ከፋይነት መመዝገብ ይኖርበታል። በዚህ መሰረት ከሀምል ወር 2003 ዓ.ም ጀምሮ ለተጨማሪ እሴት ታክስ ከፋይነት የመመዝገብ ግድታ ያለበት በመሆኑ ከሚያዚያ ወር 2003 እሰከ ሰኔ 2003 ዓ.ም መክፈል ያለበትን የተጨማሪ እሴት ታክስ ግብር እንዲከፍል ውሳኔው ማስታወቂያ በነሀሴ ወር 2003ዓ.ም እንዲደርሰው የተደረገው በአግባቡ ነው በማለት ተከራክሯል።
የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ግብር ይግባኝ ሰሚ ጉባኤ ግራ ቀኙን ክርክርና ማስረጃ ከመረመረ በኋላ ይግባኝ ባይ መልስ ሰጭ በይግባኝ ባይ ላይ ገቢ ግብር ጨምሮ የወሰነው በገማች ኮሚቴ የይግባኝ ባይን የቀን ገቢ በማስጠናት በመሆኑ ተገቢ ነው። ለይግባኝ ባይ የተጨማሪ እሴት ታክስ የደረሰው የቀን ገቢው ብር 1700( አንድ ሺ ሰባት መቶ) በመሆኑ ነው። የግብር ይግባኝ ሰሚ ጉባኤው የሰጠው ውሳኔ ስህተት የለበትም። በዚህ ውሳኔ ቅር በመሰኘት አመልካች ለአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ይግባኝ ሰሚ ፍርድ ቤት ይግባኛ ሰሚ ችሎት ይግባኝ አቅርቧል ። ይግባኝ ሰሚው ችሎት የግራ ቀኙን ክርክር ከሰማ በኋላ የግብር ይግባኝ ሰሚ ጉባኤ ገቢ ግብር በተመለከተ የሰጠውን ውሳኔ አጽንቶ፣የተጨማሪ እሴት ታክስ ግብር በተመለከተ የሰጠውን ውሳኔ ሽሯል። በዚህ ውሳኔ ቅር በመሰኘት ተጠሪ ሰበር አቤቱታ አዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር የይግባኝ ፍርድ ቤት ይግባኝ ሰሚ ፍርድ ሰበር ችሎት አቅርቧል። የከተማው ሰበር ችሎት የግራ ቀኙን ክርክር ከሰማ በኋላ የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር የይግባኝ ፍርድ ቤት ይግባኝ ሰሚ ችሎት የሰጠውን ውሳኔ ሽሮ የግብር ይግባኝ ሰሚ ጉባኤ የሰጠውን ውሳኔ አጽንቶታል።
አመልካች 2/11/2004 ዓ.ም በተጻፈ የሰበር አቤቱታ አመልካች የቁርጥ ግብር ከፋይ ነኝ። ተጠሪ ገቢ ግብር አስተካክሎ መወሰን የሚችለው በየ አምስት ዓመቱ ነው። ተጠሪ በአመልካች ላይ በመሥከረም ወር 2002 ዓ.ም በሰጠው ግብር ውሳኔ ማስታወቂያ ቅር ተሰኝቸ ይግባኝ ለግብር ይግባኝ ሰሚ ጉባኤ አቅርቤ ተሻሽሎ ተወስኖልኛል። ተጠሪ የግብር ይግባኝ ሰሚ ጉባኤ ግብሩን አሻሽሎ ውሳኔ ከሰጠ ከሥምንት ወራት በኋላ በእጥፍ አሳድጎ የሰጠው ውሳኔ መሰረታዊ የህግ ስህተት ያለበት ነው። አመልካች የምሰራው የችርቻሮ ንግድ ስራ ሆኖ እያለ ጅምላ አከፋፋይ ነው በማለት የተሰጠው ውሳኔ ሕጉን መሰረት ያደረገ አይደለም። አመልካች ተጨማሪ አሴት ታክስ እንድመዘገብ የተወሰነ መሆኑን ሳያሳውቅ በህጉ መሰረት አሳውቀኝ የሶስት ወር ተጨማሪ አሴት ታክስ እድከፍል የሰጠው ውሳኔ መሰረታዊ የህግ ስህተት ያለበት ስለሆነ በሰበር ታይቶ እንዲታረምልኝ በማለት አመልክቷል። ተጠሪ በ04/06/2005 ዓ.ም በተጻፈ መልስ ግብር ይግባኝ ሰሚ ጉባኤው ስለ ገቢ ግብር ውሳኔና ተጠሪ አመልካች የሶስት ወር ተጨማሪ አሴት ታክስ እንድከፍል የሰጠው ውሳኔ ማስታወቂያ ተገቢ ነው በማለት የሰጠው ትርጉምና ውሳኔ የሕጉን መንፈስ የተከተለ ነው የሚል ይዘት ያለው መልስ አቅርቧል። አመልካች በ14/06/2005ዓ.ም የተጻፈ የመልስ መልስ አቅርቧል።
ከሥር ክርክሩ አመጣጥና በሰበር የቀረበው የጽሑፍ ክርክር ከላይ የገለፅነው ሲሆን እኛም የአዲስ አበባ ግብር ይግባኝ ሰሚ ጉባኤና የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር የይግባኝ ፍርድ ቤት የሰበር ችሎት የሰጡት ውሳኔ ተገቢ ነው? ወይስ አይደለም? የሚለውን ጭብጥ በመያዝ ጉዳዩን መርምረናል።
ጉዳዩን እንደመረመርነው ተጠሪ በአመልካች ላይ ገቢ ግብር ጨምሮ የወሰነው በመጋቢት ወር 2003 ዓ/ ም በገማች ኮሚቴ የአመልካችን የቀን ገቢ በማስጠናት መሆኑ እና የቀን ገቢው ብር 1700( አንድ ሺ ሰባት መቶ ብር) መሆኑ ፍሬ ጉዳይ የማጣራትና ማስረጃ የመመዘን ሥልጣን ባለው የግብር ይግባኝ ሰሚ ጉባኤ ተረጋግጧል።ከዚህ አንጻር ሲታይ አመልካች ያቀረበው አቤቱታ ፍሬ ነገርና ማስረጃ ምዘና የሚመለከት በመሆኑ አልተቀበልነውም።
የአመልካች የንግድ እንቅስቃሴ በዓመት ከብር 500,000 ( አምስት መቶ ሺ ብር) እንደሆነ ተረጋግጧል።
አመልካች ተጨማሪ እሴት ታክስ በአዋጅ ቁጥር 285/1994 መሰረት በፈቃዱ ለተጨማሪ እሴት ታክስ መመዝገብ ሲገባው እንዳልተመዘገበና አመልካች የቀን ገቢ ብር 1700 ( አንድ ሺ ሰባት መቶ ብር) እንደሆነ ተጠሪ በገማች ኮሚቴዎች በኩል ባደረገው ጥናት ተረጋግጧል ። ይህም አመልካች በአዋጅ ቁጥር 285/1994 አንቀጽ 3(1) ከነሀሴ 1 ቀን 2002 እሰከ ነሃሴ 30 ቀን 2002 ዓ/ም ለተጨማሪ እሴት ታክስ ማመልከቻ አቅርቦ መመዝገብ የነበረበት መሆኑን ያሳያል። አመልካች በአዋጅ ቁጥር 285/1994 አንቀጽ 3(1) ከነሀሴ 1 ቀን 2002 እሰከ ነሃሴ 30 ቀን 2002 ዓ.ም ለተጨማሪ እሴት ታክስ ማመልከቻ አቅርቦ መመዝገብ የነበረበት ሰው ካልተመዘገበ ፣ ለመመዝገብ ማመልከቻ ማቅረብ ከሚጀምርበት የሂሳብ ጊዜ አንስቶ ታክስ ከፋይ እንደሚሆን በአዋጅ ቁጥር 285/1994 አንቀጽ 3(3) ተደንግጓል። ከዚህ አንጻር ሲታይ አመልካች ለተጨማሪ እሴት ታክስ መመዝገብ ከነበረበት ጊዜ ጀምሮ ከሚቀጥለው የሂሳብ ጊዜ ማለትም መስከረም 2003 ዓ.ም ጀምሮ ታክስ የመክፈል ግድታ ያለበት ቢሆንም ተጠሪ ከመጋቢት ወር 2003 ዓ/ም በገማች ኮሚቴ የአመልካችን የቀን ገቢ በማስጠናት መሆኑ እና የቀን ገቢው ብር 1700( አንድ ሺ ሰባት መቶ ብር) መሆኑን ካረጋገጠ በኋላ ከሚያዚያ 2003 ዓ.ም እስከ ሰኔ 2003 ዓ.ም አመልካች ተጨማሪ እሴት ታክስ እንዲከፍል የተሰጠው ውሳኔ ተገቢ ሆኖ አግኝተነዋል። .
በመሆኑም ተጠሪ የሰጠው ውሳኔ አዋጅ ቁጥር 285/1994 አንቀጽ 3(1) ፣ አንቀጽ 3(3) እና አንቀጽ 16(1) /ለ/ መሰረት ያደረገ በመሆኑ የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ግብር ይግባኝ ሰሚ ጉባኤ የሰጠውን ውሳኔ ፣የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር የይግባኝ ሰሚ ፍርድ ቤት ይግባኝ ሰሚ ችሎትና ሰበር ችሎት ማጽናታቸው መሰረታዊ የህግ ስህተት የለበትም በማለት ወስነናል።
የአዲስአበባ ከተማ አስተዳደር ግብር ይግባኝ ሰሚ ጉባኤ፣የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር የይግባኝ ሰሚ ፍርድ ቤት የሰበር ችሎት የሰጡት ውሳኔ ጸንቷል።
በዚህ ፍርድ ቤት ያወጡትን ወጭና ኪሳራ ግራ ቀኙ ለየራሳቸው ይቻሉ።
መዝገቡ ወደ መዝገብ ቤት ይመለስ።
No topics extracted.