No summary available.
መስከረም 21 ቀን 2006 ዓ.ም.
ዳኞች፡- ተገኔ ጌታነህ ተሻገር ገ/ሥላሴ አልማው ወል ዓላ መሐመድ ሙስጠፋ አህመድ አመልካች፡- በትግራይ ገቢዎች ልማት ባለስልጣን ዐ/ህግ - የቀረበ የለም ተጠሪ፡- አቶ በርሀ ረዳ ኪዳኑ - የቀረበ የለም **
መዝገቡ ተመርምሮ ተከታዩ ፍርድ ተሰጥቷል።
**
ጉዳዩ ከተጨማሪ እሴት ታክስ ሕጎች ጋር ተያይዞ የተነሳውን የወንጀል ክርክር የሚመለከት ሲሆን ክርክሩ የተጀመረው የአሁኑ አመልካች ባሁኑ ተጠሪ ላይ በዞኑ ከፍተኛው ፍ/ቤት ላይ በመሰረቱት ክስ መነሻ ነው። የክሱ ይዘትም ተጠሪ ከአክሱም ከተማ ገቢዎች ጽ/ቤት ሳይፈቀድላቸው የቅዱስ ገብርኤል ማተሚያ ቤት መሳሪያ መደብር ፈቃድ አውጥተው ሲሰሩ ሃያ አንድ ፓድ ደረሰኝ አትመዋል፣ በሁለት ኮፒ የሚታተም ደረሰኝ በአንድ ገፅ 100 ፓድ አትመው ደግሞ ተራፊ የልለው አድርገው አትመዋል በዚህ አድራጎታቸው መንግስት ላያገኘው ይገባ የነበረ ገቢ አሳጥተዋል፣ እንደዚሁም ማህተም ብቻ በማድረግ ብር 1,908.00 ያለ ቫት ክፍያ ተጠቅመዋል በማለት የተጨማሪ እሴት ታክስ ማሻሻያ አዋጅ 609/2001 አንቀጽ 19፣ አዋጅ ቁጥር 285/1994 አንቀጽ 22(1)(2)፣ 50(ሐ) ስር የተመለከቱትን ድንጋጌዎችን ተላልፈዋል በሚል የቀረበባቸው መሆኑን የሚያሳይ ሲሆን ተጠሪ ክደው ተከራክረው አቃቤ ህግ አሉኝ ያላቸውን የሰውና የሰነድ ማስረጃዎች አቅርቦ አሰምቷል። ተጠሪ እንዲከላከሉ ተደርጎም የመከላከያ ማስረጃዎች የተሰሙላቸው ሲሆን ፍርድ ቤቱም ጉዳዩን መርምሮ የተጠሪን መከላከያ ማስረጃዎች ቃል ውድቅ አድርጎ ተጠሪን በአቃቤ ህግ ተጠቅሶ በቀረበባቸው ድንጋጌዎች ስር ጥፋተኛ በማድረግ በስድስት ወር እስራትና በብር 15,000.00 (አስራ አምስት ሺ ብር) እንዲቀጡ ሲል ወስኗል። ይህ ውሳኔ በክልሉ ጠቅላይ ፍርድ ቤት ይግባኝ ሰሚ ችሎትም ሙሉ በሙሉ የፀና ሲሆን ጉዳዩ ለክልሉ ሰበር ሰሚ ችሎት ቀርቦ ግን ግራ ቀኙ ከተከራከሩ በኋላ ህትመቱን ሰራ የተባለው አካል በሕጉ ድርጅት የሚለውን መስፈርት የማያሟላና ተጠሪም የግል ባለሃብት እንጂ በድርጅት መሪነት የሚሸፈኑ አይደሉም የሚሉ ምክንያቶችን ይዞ የስር ፍ/ቤቶች የጥፋተኝነትና ቅጣት ውሳኔ በድምጽ ብልጫ ሽሮታል። የአሁኑ የሰበር አቤቱታ የቀረበውም ይህንኑ ውሳኔን በመቃወም ለማስለወጥ ነው። የአመልካች የሰበር አቤቱታ መሰረታዊ ይዘትም ተጠሪ የድርጅቱ ባለቤትና ስራ አስኪያጅ ሆነው እያለና ሕጉ ደግሞ ማንኛውንም ሰው ተጠያቂ እንደሚያደርግ ደንግጎ ባለበት ሁኔታ የክልሉ ሰበር ሰሚ ችሎት ባልቀረበለት የፍሬ ነገር ክርክርና ከሕጉ ይዘትና መንፈስ ውጪ ተጠሪ በወንጀል አይጠየቁም በማለት መወሰኑ ያለግባብ ነው የሚል ሲሆን አቤቱታው ተመርምሮም በሰበር ችሎቱ እንዲታይ በመደረጉ ተጠሪ ቀርበው ግራ ቀኙ በፅሁፍ እንዲከራከሩ ተደርጓል።
የጉዳዩ አመጣጥ አጠር አጠር ባለመልኩ ከላይ የተገለፀው ሲሆን ይህ ችሎትም የግራ ቀኙን ክርክር ለሰበር አቤቱታው መነሻ ከሆነው ውሳኔ እና አግባብነት ካላቸው ድንጋጌዎች ጋር በማገናዘብ ጉዳዩን በሚከተለው መልኩ መርምሮታል። እንደመረመረውም የዚህን ችሎት ምላሽ የሚያስፈልገው አቢይ ነጥብ ተጠሪ የወንጀል ተጠያቂነት የለባቸውም ተብሎ መወሰኑ ባግባቡ ነው? ወይስ አይደለም? የሚለው ሆኖ አግኝቶታል። ክስ የቀረበበት አካል ድርጅት መሆኑን ፍሬ ነገርን ለማጣራትና ማስረጃን የመመዘን ስልጣን ያላቸው የበታች ፍ/ቤቶች ያረጋገጡት ጉዳይ ሲሆን የክልሉ ሰበር ሰሚ ችሎት በክርክሩ ሂደት የተረጋገጡት ፍሬ ነገሮች የሚያሳዩት ክስ የቀረበው በድርጅት ያለመሆኑን፣ አመልካች የግል ባለሃብት መሆናቸውን ነው ወደሚለው ድምዳሜ የደረሰው በኢ.ፍ.ዲ.ሪ ሕግ መንግስት አንቀጽ 80(3(ለ)) እና በክልሉ ሕገ መንግስት አንቀጽ 64(2(ሐ)) እንዲሁም በክልሉ ፍ/ቤቶች ማቋቋሚያ አዋጅ ቁጥር 49/1994 አንቀጽ 16 እና 17 ስለ ሰበር ችሎት ዳኝነት ስልጣን ከሚደነግጉት ስርዓት ውጪ ነው። ተጠሪ የማተሚያ ቤቱ ንግድ ፈቃድ በራሳቸው መሆኑና ግብርም በስማቸው የሚገብሩ መሆኑን ፍሬ ነገሩን ለማጣራትና ማስረጃን የመመዘን ስልጣን በሕጉ የተሰጣቸው የዞኑ ከፍተኛ ፍ/ቤትና የክልሉ ይግባኝ ሰሚ ችሎት ያረጋገጧቸው ነጥቦች ናቸው።
ይህንኑ ይዘን ወደ ሕጉ ስንመጣም ተጠሪ በስራ አስኪያጅነት የሚመሩትና የግል ሃብታቸው በሆነው የንግድ ድርጅት በአመልካች በክሱ የተመለከቱትን ድርጊቶች ድርጅቱ ከሚመለከተው አካል ፈቃድ ሳያገኝ ተገቢ ያልሆኑ ፓዶችን ማሳተሙን፣ ብር 1908 ያለ ቫት ደረሰኝ መጠቀሙ በፍሬ ነገር ደረጃ የተረጋገጠ በመሆኑ በመርህ ደረጃ ተጠሪ በአዋጅ ቁጥር 285/94 አንቀጽ 2(11) እና 56(1) እንዲሁም በማሻሻያ አዋጅ ቁጥር 609/2001 አንቀጽ 19(50(ሐ)) ድንጋጌዎች መሰረት ጥፋተኛ የሚባሉ መሆኑ በህጉ ተደንግጓል።
ተጠሪ በአዋጅ ቁጥር 285/94 አንቀጽ 56 ንዑስ አንቀጽ 3 የተመለከቱትን ልዩ ሁኔታዎች በማስረዳት ከተጠያቂነት ነፃ ለመሆን ይጠቅመኛል በማለት ያቀረቡት ክርክር በልላ ቦታ የነበሩ መሆኑን ያሳያሉ ያሉት የመከላከያ ማስረጃ ነው። ሆኖም ተጠሪ በልላ ቦታ የነበሩ መሆኑ ከወንጀል ተጠያቂነት የሚያድናቸው አይደለም።
ከዚህ በተጨማሪ ተጠሪ በአዋጅ ቁጥር 285/94 አንቀጽ 56 ንዑስ አንቀጽ 3/ለ/ በተደነገገው መሰረት ማንኛውም በጎ አሳቢ ሰው ላያደርገው የሚችለውን ጥንቃቄ ያደረጉና ጥበብ በተሞላበት ሁኔታ ድርጅቱን በመምራት ኃላፊነታቸውን የተወጡ መሆኑን የሚያረጋግጥ ማስረጃ ያለማቅረባቸውን ፍሬ ነገርን ለማጣራትና ማስረጃን የመመዘን ስልጣን ያላቸው የዞኑ ከፍተኛ ፍርድ ቤትና የክልሉ ጠቅላይ ፍርድ ቤት ይግባኝ ሰሚ ችሎቶች ከሰጡት የውሣኔ ይዘት የምንገነዘበው ጉዳይ ነው። ስለሆነም ተጠሪ በአዋጅ ቁጥር 285/1994 አንቀጽ 3/1/ሀ/ መሰረት ለተጨማሪ እሴት ታክስ ከፋይነት ተመዝግበውና የድርጅቱ ባለሃብትና ስራአስኪያጅ ሁነው ያልተፈቀደ ደረሰኝ በማተምና ብር 1908 ያለ ቫት የተጠቀሙ መሆኑ ተረጋግጦ እያለ የክልሉ ሰበር ሰሚ ችሎት ተጠሪ ስራ አስኪያጅ ሳይሆኑ የግል ባለሃብት ስለሆኑ የወንጀል ተጠያቂነት የለባቸውም በማለት የዞኑ ከፍተኛ ፍርድ ቤትና የክልሉ ጠቅላይ ፍርድ ቤት የሰጠውን የጥፋተኝነትና የቅጣት ውሣኔ መሻሩ በአዋጅ ቁጥር 285/1994 አንቀጽ 2/11/፣3/1/ሀ/፣56 እንዲሁም ይህንኑ አዋጅ ለማሻሻል የወጣውን አዋጅ ቁጥር 609/2001 አንቀጽ 2፣19/50/ሐ/ ድንጋጌዎችን ይዘትና መንፈስ ባላገናዘበ ሁኔታ በመሆኑ ውሣኔው መሰረታዊ የህግ ስህተት ያለበት ሆኖ ሰላገኘነው ተከታዩን ወስነናል።
ው ሣ ኔ
የትግራይ ብሕራዊ ክልላዊ መንግስት ጠቅላይ ፍርድ ቤት ሰበር ሰሚ ችሎት በመ/ ታህሳስ 23 ቀን 2005 ዓ.ም የሰጠው ውሣኔ በወ/መ/ሥ/ሥ/ሕ/ቁጥር 195/2/ለ-1/ መሰረት ተሽሯል።
በዞኑ ከፍተኛ ፍርድ ቤት በመ/፣ በቀን 24/7/2004 ተሰጥቶ በክልሉ ጠቅላይ ፍርድ ቤት በመ/ ሚያዝያ 26 ቀን 2004 ዓ.ም የጸናው የጥፋተኝነት እና የቅጣት ውሣኔ በወ/መ/ሥ/ሥ/ሕ/ቁጥር 195/2/ለ-2/ መሰረት ጸንቷል።
ተጠሪ በጉዳዩ ላይ የታሰሩበት ጊዜ የሚታሰብላቸው ሆኖ በዞኑ ከፍተኛ ፍርድ ቤት የተወሰነባቸውን የስድስት ወር ቀላል እስራትና የብር 15,000.00 የአክሱም ማረሚያ ቤት ተከታትሎ እንዲያስፈፅም ታዟል። የዞኑ ፖላስም ተጠሪን ይዞ ለማረሚያ ቤቱ እንዲያስረክብ ታዟል። ይጻፍ።
No topics extracted.