No summary available.
ሰኔ 04 ቀን 2005 ዓ.ም ዳኞች፡- አልማው ወል ዓላ መሐመድ ረታ ቶሎሣ አዳነ ንጉሴ መስጠፋ አህመድ አመልካች፡-
ጉዳዩ የቀረበው አመልካቾች የደቡብ ብሄር ብሐረሰቦችና ሕዝቦች ክልል የሀዋሳ ከተማ ከፍተኛ ፍርድ ቤትና የክልሉ ጠቅላይ ፍርድ ቤት የሰጡት የጥፋተኝነትና የቅጣት ውሣኔ መሰረታዊ የሕግ ስህተት የለበት ስለሆነ በሰበር ታይቶ እንዲታርምልን በማለት ያቀረቡትን የሰበር አቤቱታ አጣርቶ ለመወሰን ነው። ጉዳዩ ታክስ አለመክፈልን የሚመለከት ነው። በከፍተኛው ፍርድ ቤት ተጠሪ ከሳሽ አመልካቾች ተከሳሽ በመሆን ተከራክረዋል።
የክርክሩ መነሻ ተጠሪ ያቀረበው የወንጀል ክስ ማመልከቻ ነው።ተጠሪ በስር አንደኛ ተከሳሽ የሆነው አንደኛው አመልካች በወንጀል ህግ አንቀጽ 34/1/ እና በአዋጅ ቁጥር 255/94 አንቀጽ 26/1/ለ/2 አንቀጽ 56/1/2/ እና አንቀጽ 49 የተደነገገውን በመተላለፍ የታክስ ከፋይነት መለያ ቁጥርና የተጨማሪ እሴት ታክስ መለያ ቁጥር ተስጥቶት እያለ ከመጋቢት ወር 1999 ዓ.ም እስከ ሰኔ 2001 ዓ.ም በሚያከናውነው የንግድ እንቅስቃሴና ሽያጭ በየወሩ ተጨማሪ እሴት ታክስ በመሰበሰብ ለግብር አስገቢው መስሪያ ቤት ማሳወቅና መክፈል ሲገባው የንግድ ማህበሩ የማስታወቅ ግድታውን ብቻ በመወጣት የሚፈለግበትን ታክስ ባለመክፈሉ በሶስተኛ ወገን በተሰጠ ጥቆማ መነሻ በተደረገው ማጣራት መክፈል የሚገባው የተጨማሪ እሴት ታክስና አስተዳደራዊ መቀጫ ብር 9 ,065,777.59 /ዘጠኝ ሚላየን ስልሳ አምስት ሺ ሰባት መቶ ሰባ ሰባት ብር ከሃምሳ ዘጠኝ ሳንቲም/ ያልከፈለ በመሆኑ የወንጀል ክስ ቀርቦበታል የሚል ነው።
የአንደኛ ተከሳሽ ዋና ስራ አስኪያጅ የሆነው ሁለተኛው ተከሳሽ /ሁለተኛ ተጠሪ/ በአዋጅ ቁጥር 285/94 አንቀጽ 26/1/ለ/2/ አንቀጽ 56/1/2 እና አንቀጽ 49 የተደነገገውን በመተላለፍ አንደኛው ተከሳሽ/አንደኛ አመልካች/ የአክስዮን ባለድርሻና ባለንብረት እንዲዚሁም በመመስራቻ ጽሁፍ የተሾመ ስራ አስኪያጅ ሆኖ እያለ ከላይ መጠኑ የተገለፀውን ተጨማሪ እሴት ታክስ ሰብሰቦ ለግብር አስገቢው መስሪያ ቤት የመክፈል ግድታውንና ኃላፊነቱን ባለመወጣቱ የወንጀል ክስ ቀርቦበታል የሚል ይዘት የለው ነው።
አንደኛ ተከሳሽ በወንጀል ህግ አንቀጽ 34/1/ እና በአዋጅ ቁጥር 286/94 አንቀጽ 53 ንዐሱ አንቀጽ 1፣2 እና 3 አንቀጽ 102 እና አንቀጽ 96 የተደነገገውን በመተላለፍ ከዕቃ ገዥዎች በቅድሚ ክፍያ ተቀንሶና ተሰብስቦ ለግብር አስገቢው መስሪያ ቤት ማስገባት የነበረበትን ብር 374,818. 81 /ሶስት መቶ ሰባ አራት ሺህ ስምንት መቶ አስራ ስምንት ብር ከሰማኒያ አንድ ሳንቲም/ ያልከፈለ በመሆኑ የወንጀል ክስ ቀርቦበታል
ሁለተኛ ተከሳሽ ከላይ በተራ ቁጥር 3 የተደነገጉትን ድንጋጌዎች በመተላለፍ የአንደኛው ተከሳሽ ዋና ስራ አስኪያጅ ሆኖ ሲሰራ በቅድመ ክፍያ ቀንሶና ሰብስቦ መክፈል የሚገባውን መጡኑ በሶስተኛው ክስ የተገለጸውን ገንዘብ የልከፈለ በመሆኑ የወንጀል ክስ ቀርቦበታል የሚል ይዘት የላቸው አራት የወንጀል ክሶችን አቅርቧል። አመልካች በተከሳሽነት ቀርበው የወንጀሉን ድርጊት አልፈጸምንም ጥፋተኛ አይደለመንም በማለት ተከራክረዋል።
ተጠሪ ክሱን የሚያስረዱልን ምስክሮች አሉ በማለት ሶስት ምስከሮችን በማቅረብ አሰምቷል።
የመጀመሪያው ምስክር አንደኛ ተከሳሽ ተጨማሪ እሴት ታክስና የደመወዝ ግብር ገቢ በሕግ አግባብ እያሰበሰበና እየከፈለ አይደለም የሚል ጥቆማ ድርሰን። የደመወዝ ግብር ገቢ ለክልሉ ገቢዎች ባለስልጣን እንዲያውቀው አድርገን የተጨማሪ እሴት ታክሱን በኦዲት እንዲጣራ ተደርጎ በአንደኛው የክስ ማመልከቻ መጠኑ የተጠቀሰው የተጨማሪ እሴት ታክስ አንደኛው ተከሳሽ እንዳልከፈለ ተረጋግጧል ከዚያ በኋላ አንደኛ ተከሳሽ ለአቤቱታ አጣሪ ኮሚቴ አመልክተው ጥያቄው ውድቅ ተደርጎበታል። አንደኛ ተከሳሽ ሁለት ፐርሰንት ከተከፋይ ሂሳብ ተቀናሽ እያደረገ ለግብር አስገቢ መስሪያ ቤት ያልከፈለ መሆኑንና በሶስተኛው ክስ መጠኑ የተገለጸውን ገንዘብ እንዳልከፈለ በኦዲት ተረጋግጧል። ተጠሪ የግብር ገንዘቡን ለማስከፈል እንቅስቃሴ ቢያደርግም አንደኛ ተከሳሽ ከዳሽን ባንክ ለወሰደው ብድር ባንኩ መደባውን በመሸጡና በባንኩ እዳ የተረፈ ገንዘብ የልለ መሆኑ ስለተነገረን ልሎች ንብረቶችን በማፈላለግ ላይ እንገኛለን በማለት እንደመሰከሩ የስር ፍርድ ቤት በውሣኔው በግልጽ አስፍሮታል።
የድርጅቱን /አንደኛ/ ተከሣሽን ኦዲት ሰርቻለሁ። ኦዲት ስንሰራ እኛ ድርጅቱ በሣምንት አንድ ቀን ማለትም እሁድ ቀን ምርት እንደማያመርትና በወር አራት ቀናት እንደማያመርት በመቀነስ በወር ሃያ ስድሰት ቀናት እንደሚያመርት በመያዝ ሂሣቡን ሰርተናል። አንደኛ ተከሣሽ በወር ሃያ ስድስት ቀናት የማምረት አቅሙን ተጠቅሞ የሚያመርተውን በተጨማሪ እሴት ታክስ ማሣወቂያ ቅጽ አላሣወቀም የዊዝ ሆልድግ ታክሱም አለበት በማለት እንደመሰከረች ከስር ፍ/በት ውሣኔ ተረድተናል።
ሶስተኛው የተጠሪ ምስክር የአንደኛ ተከሣሽ ሒሣብ ኦዲት ሲደረግ አንደኛው ተከሣሽ የተሟላ መረጃ ይዞ አለመገኘቱንና የቀን ግምቱን መነሻ በማድረግ የግብሩን መጠን የሰሩ መሆኑን@ የድርጅቱን ትክክለኛ የሸያጭ መጠን ለማወቅ የተሟላ ሪከርድ የልለ መሆኑንና አስቸጋሪ እንደሆነ፣ የቀን ግምት በመውሰድ በወንጀል ክሱ የተገለፁት የተጨማሪ እሴት ታክስና የቅድመ ተከፋይ ተቀናሽ /ዊዝሆልድግ/ ታክስ የሚፈለግበት መሆኑን በመግለጽ ሪፖርት አቅርበናል የሚል ይዘት ያለው የምስክርነት ቃል እንደሰጠ ከስር ፍ/ቤት ውሣኔ ይዘት ተረድተናል።
አመልካቾች የመከላከያ ማስረጃ እንዲያቀርቡ የሰር ፍ/ቤት ብይን ሰጥቶ ሁለተኛው ተጠሪ የመከላከያ የምስክርነት ቃሉን የሰጠ ሲሆን፣ በቂ እውቀትና ክህሎት ያለው የሰለጠነ የሰው ኃይል ባለማግኘታችን የምርት ብልሽትና ብክነት ተከስቷል። ከመጋቢት 1999 እስከ 2001 መብራት ይቆራረጥ የነበረ በመሆኑ ድርጅቱ በአንድ ፈረቃ ብቻ ለማምረት ከመገደዱም በላይ ለቀናትና ለወራት ጭምር የምርት ስራ የቆመበት ሁኔታ ነበር። ለዙሁም ከኢትዮጱያ ኤልክትሪክ ኃይል ኮርፖሬሽን የተፃፈልን የጽሑፍ ማስረጃ አለ። በዚህ ጊዜ ውስጥ ከወር ሃያ ስድስት ቀናት በሶስት ፈረቃ እንደሚያመርት በመገመት የተሰራው የኦዲት ስራ እውነታውን የሚያሣይ አይደለም በማለት የምስክርነት ቃሉን የሰጠ ሲሆን ልሎች የአመልካቾች ሁለት ምስክሮችም ከመጋቢት ወር 1999 ዓ.ም ጀምሮ እሰከ 2ዐዐ1 ዓ.ም የመብራት መቋረጥ ምክንያት የምርት ስራ ተቋርጧል የሚሉበትን ሁኔታ በዝርዝር የመሰከሩ መሆኑን ከስር ፍርድ ቤት ውሣኔ ተረድተናል።
ጉዳዩን በመጀመሪያ ያየው የሃዋሣ ከተማ ከፍተኛ ፍርድ ቤት በተጠሪ በኩልና በአመልካቾች በኩል የቀረቡትን ማሰረጃዎች ከመረመረ በኋላ አንደኛ ተከሣሽ /አንደኛ አመልካች/ ተጠሪ ባቀረበው በአንደኛውና በሶስተኛው የወንጀል ክሶች ውሰጥ የጠቀሣቸውን የሕግ ድንጋጌዎች በመተላለፍ፣ በተጠሪ ክስ የተገለፁትን የወንጀል ድርጊቶች የፈጸመ ጥፋተኛ ነው በማለት የጥፋተኝነት ውሣኔ ሰጥቷል። ሁለተኛው ተከሣሽ/ሁለተኛ አመልካች/ ተጠሪ በሁለተኛውና በአራተኛው የወንጀል ክስ የጠቀሣቸውን የሕግ ድንጋጌዎች በመተላለፍ በክሱ የተገለፁትን የወንጀል ድርጊቶች የፈጸመ ጥፋተኛ ነው በማለት የጥፋተኝነት ውሣኔ ሰጥቷል። ቅጣቱን በተመለከተ አንደኛው አመልካች በብር አርባ ሺ ብር/ብር 4ዐ,ዐዐዐ/ መቀጮ እንዲከፍል ሁለተኛው አመልካች ከሐምል 12 ቀን 2ዐዐ4 ዓ.ም ጀምሮ በሚታሰብ አምሰት አመት ጽኑ እሰራት እንዲቀጣ በማለት ውሣኔ ሰጥቷል። አመልካቾች በዚሁ ውሣኔ ቅር በመሰኘት ይግባኝ ለክልሉ ጠቅላይ ፍርድ ቤት አቅርቧል። የክልሉ ጠቅላይ ፍርድ ቤት የአመልካቾችን ይግባኝ በወ/ሥ/ሥ/ሕ/ቁጥር 195/1/ መሰረት ሰርዞታል።
አመልካቾች ጥቅምት 9 ቀን 2ዐዐ5 ዓ.ም በተፃፈ የሰበር አቤቱታ ተጠሪ በወንጀል ክሱ የጠቀሣቸው የአዋጅ ቁጥር 285/94 እና የአዋጅ ቁጥር 286/94 ድንጋጌዎች የታክስ ስወራ ወንጀል የሚፈጸሙ ሰዎችን በወንጀል ኃላፊ እንዲሆንና እንዲቀጣ ለማድረግ ታስበው የታወጁ ናቸው። አመልካቾች በወቅቱ ለግብር ሰብሣቢው መስሪያ ቤት የማሣወቅ ግድታችንን የምንወጣ መሆኑን ተጠሪ ባቀረበው የወንጀል ክስና አቅርቦ ባሰማቸው ምሰክሮች ተረጋግጧል። የተጠሪ ኦዲተሮች በወቅቱ የነበረውን በኤልክትሪክ ሀይል እጥረት ምክንያት ምርት የሚቋረጥባቸውን ጊዜዎች ሣያገናዝቡ ድርጅቱ በሶስት ፈረቃ ሃያ ስድሰት ቀናት እንደሚያመርት የህላና ግምት በመያዝ የሰሩት ሒሣብና ያቀረቡት ሪፖርት በግምት ላይ የተመሰረተና የተመረተውን እርግጠኛ ምርትና የተደረገውን ግብይት መሰረት ያደረገ ባለመሆኑ@ በዚህ ማስረጃ መነሻ የወንጀል ክስ መቅረቡም ሆነ ጥፋተኛ ተብለን መቀጣታችን መሰረታዊ የሕግ ስህተት ያለበትም ስለሆነ በሰበር ታይቶ እንዲታረምልኝ በዊዝሆልዲንግ ታክስ ጥሰት ቢፈፀም እንኳን የወንጀል ተጠያቂነትና ቅጣት የሚያስከትል መሆኑ በአዋጅ ቁጥር 286/94 ያልተደነገገ በመሆኑ አመልካች ያቀረበው ሶስተኛውና አራተኛው የወንጀል ክስ የሕጋዊነት መርህን የሚጥስና መሰረታዊ የሕግ ስህተት ያለበት ስለሆነ የበታች ፍርድ ቤቶች የሰጡት የጥፋተኝነትና የቅጣት ውሣኔ በመሻር እንዲያሰናብተን በማለት አመልክተዋል።
ተጠሪ በበኩሉ የካቲት 26 ቀን 2005 ዓ.ም በተፃፈ መልስ አመልካቾች አዋጅ ቁጥር 285/94፣ በአዋጁ ቁጥር 286/94 እና በሚኒስትሮች ምክር ቤት ደንብ ቁጥር 78/94 የተጣለባቸው የተጨማሪ እሴት ታክስና የዊዝሆልዲንግ ታክስ የመክፈል ግድታቸውን ያልተወጡ መሆኑ በማስረጃ ተረጋግጧል።
አመልካቾች የማሣወቅ ግድታቸውን መወጣታቸው መክፈል የሚገባቸው ታክስ ባለመክፈላቸው የሚደርስባቸውን የወንጀል ተጠያቂነት የሚያስቀርላቸው አይደለም። ግብር አስገቢው መስሪያ ቤት ግብር በግምት እንዲወሰን የሚፈቅድለት የሕግ ድንጋጌዎች አሉ። ስለዚህ በግምት የተወሰነው የግብር ውሣኔ በወንጀል ጉዳይ እንደማስረጃ መቅረቡን በመቃወም አመልካቾች ያቀረቡት ክርክር የሕግ መሰረት የልለው ነው። በአጠቃላይ በበታች ፍርድ ቤቶች የተሰጠው የጥፋተኝነትና የቅጣት ውሣኔ መሰረታዊ የሕግ ስህተት የለበትም በማለት ተከራከሯል።
አመልካቾች መጋቢት 16 ቀን 2005 ዓ.ም የተፃፈ የመልስ መልስ አቅርበዋል።
ከሥር የክርክሩ አመጣጥና በዚህ ሰበር ችሎት ግራ ቀኙ ያቀረቡት የጽሑፍ ክርክር ከላይ የተገለፀው ሲሆን እኛም የበታች ፍርድ ቤቶች በአመልካቾች ላይ የሰጡትን የጥፋተኝነትና የቅጣት ውሣኔ አግባብነት ያላቸውን የሕግ ድንጋጌዎች መሰረት ያደረገ ነው ወይስ አይደለም የሚለውን ጭብጥ በመያዝ ጉዳዩን መርምረናል።
ከላይ የተያዘውን ጭብጥ ለመወሰን በመጀመሪያ ተጠሪ በአመልካች ላይ ያቀረበው የወንጀል ክስና ክሱን የወንጀል መሰረታዊ ይዘት ያለው መሆኑን መመርመር አስፈላጊ ነው። የአዋጅ ቁጥር 285/96 ድንጋጌዎች በመተላለፍ በሚፈፀው ወንጀሎች የወንጀለኛ መቅጫ ሕጉን በመተላለፍ የሚፈፀው በመሆኑ ክሱ የሚመሰረተው የሚታየውና በይግባኝ የሚቀርበው በወንጀለኛ መቅጫ ሥነ ሥርዓት ሕግ መሰረት እንደሆነ በአንቀጽ 48 የሚደነገግ ሲሆን የአዋጅ ቁጥር 286/94 አንቀጽ 94 ተመሣሣይ ይዘት ያለው እንደሆነ እንረዳለን ይህም በመሆኑ ተጠሪ በአመልካቾች ላይ ያቀረበው የወንጀል ክስ በወንጀለኛ መቅጫ ሥነ ሥርዓት ሕግ ቁጥር 111 እና በወንጀለኛ መቅጫ ሥነ ሥርዓት ሕግ ቁጥር 112 መሰረት የተዘጋጀን አመልካቾች በወንጀል ሕግ አንቀጽ 23 ንዑስ አንቀጽ 2 መሰረት የሕግ የሞራልና የግዙፍ ተግባር ሁኔታ በተሟላበት ሁኔታ አዋጅ ቁጥር 285/94 አንቀጽ 49፣ በአዋጅ ቁጥር 286/94 አንቀጽ 96 የተመለከተውን ድንጋጌ በመተላለፍ በተለይ የሕግ ጥሰት በመፈፀም ታክስ ያለመክፈል ወንጀል የፈፀመ መሆኑን የሚያሣይ የወንጀል ክስ ይዘትና ባህሪ ያለው ላሆን ይገባዋል።
የአዋጅ ቁጥር 285/94 አንቀጽ 49 እና የአዋጅ ቁጥር 286/94 አንቀጽ 96 ድንጋጌዎች ሕግን በመጣስ ተክስን አለመክፈል ወይም በእንግላዘኛው “Tax Evasion” የሚል ርእስ ያላቸው ሲሆን ይዘታቸው ተመሣሣይነት ያለው ነው። የድንጋጌዎቹ ይዘት ቃል በቃል ሲነበብ ሕግን በመጣስ የሰበሰበውን ግብር ያላሣወቀ ወይም የሚፈለግበትን ግብር ያልከፈለ ወይም መንግስትን ለማጭበርበር በማሰብ የማይገባውን ተመላሸ ታክስ የጠየቀ ማናቸውም ሰው ወንጀል አንደፈፀም ይቆጠራል በመሆኑም በዚህ አዋጅ ክፍል አሥራ አንድ መሰረት ከሚጣልበት መቀጮ በተጨማሪ ጥፋተኛ መሆኑ በፍርድ ሲረጋገጥ ከአምስት ዓመት በማያንስ እስራት ይቀጣል የሚል ይዘት ያለው ነው።
አመልካቾች ግብር የማሣወቅ ግድታቸውን የፈፀሙ መሆኑን ተጠሪ በአመልካቾች ላይ ባቀረባቸው የወንጀል ክሶች በግልጽ ያሰፈረው ጉዳይ ነው። ከዚህ በተጨማሪ የአንደኛ አመልካችን ሂሣብ ለማጣራት የተመደቡት የተጠሪ ምስክሮች አመልካቾችን በየወቅቱ በሂሣብ በግብር ማሣወቂያ ቅጽችን በመሙላት ለግብር አስገቢው መስሪያ ቤት ያሣውቁ እንደነበር ገልፀዋል። ከዚህ አንፃር ሲታይ አመልካቾች በአዋጅ ቁጥር 285/94 አንቀጽ 49 እና በአዋጅ ቁጥር 286/94 አንቀጽ 96 በተደነገገው መሰረት ግብር የማሣወቅ ግድታቸውን በመተላለፍ ታክስ ባለመክፈል የፈፀሙት ግዙፍ የወንጀል ተግባር የልለ መሆኑን ተጠሪ ባቀረበው የወንጀል ክስና ማስረጃ የተረጋገጠ ሆኖ አግኝተነዋል።
አመልካቾች በአዋጅ ቁጥር 285/96 አንቀጽ 49 እና በአዋጅ ቁጥር 286/94 አንቀጽ 96 በተደነገገው መሰረት መንግስትን ለማጭበርበር በማሰብ የማይገባቸውን የታክስ ተመላሽ በመጠየቅ ግዙፍ የወንጀል ተግባር የፈፀሙ መሆናቸውን ተጠሪ በአመልካቾች ላይ ያቀረባቸው የወንጀል ክሶች አይገልጽም። ተጠሪ በአመልካቾች ላይ ያቀረቧቸው ምስክሮችም አመልካቾች የማይገባቸውን የታክስ ተመላሽ በመጠየቅ መንግስትን የማጭበርበር ስራ ስለመስራታቸው የሰጡት የምሰክርነት ቃል የለም።
ተጠሪ አመልካቾች የአዋጅ ቁጥር 285/94 አንቀጽ 49 እና የአዋጅ ቁጥር 286/94 አንቀጽ 96 በመተላለፍ የወንጀል ድርጊት ፈጽመዋል በማለት ክስ ያቀረበው አመልካቾች ከመጋቢት ወር 1999ዓ.ም እስከ ሰኔ 3ዐ ቀን 2ዐዐ1ዓ.ም ድረስ በግምት የተወሰነባቸውን ብር 9,065,577.59 ተጨማሪ እሴት ታክስ ከነመቀጫውና ብር 374,818.81 ዊዝ ሆልዲንግ ታክስ በወቅቱ አልከፈሉም በማለት ነው። እዚህ ላይ መታየት ያለበት አመልካቾች አንደኛ አመልካች ያመረተውን የምርት መጠንና ያከናወኑትን ግብይት ከግብይቱ የሰበሰቡትን ገቢ በየወቅቱ ለግብር አስገቢው መስሪያ ቤት ያቀርቡ የነበረ መሆኑ በተጠሪ ክስና ማስረጃ የተገለፀና የተረጋገጠ በሆነበት ሁኔታና አመልካቾች በየወቅቱ ባቀረቡት የግብር ማሳወቂያ ቅጽ በመጀመሪያ አንደኛ ተከሣሽ ዕቃዎችን ሲያስገባ የከፈለው የተጨማሪ እሴት ታክስ እና አንደኛ ተከሣሽ የፋብሪካ የምርት ውጤቱን ሲሸጥ የሰበሰበው ተጨማሪ እሴት ታክስ ተቀናንሰው ባላንሱ ዜሮ መሆኑንና ለመንግስት የሚከፍሉት የግብር ገንዘብ የልለ መሆኑን በየወሩ መጨረሻ ሲያሳውቁ መኖራቸው በተረጋገጠበት ሁኔታ ኦዲተሮች ሂሣቡን ኦዲት ሲያደርጉ ፋብሪካው በሙሉ አቅሙ ማለትም በሶስት ፈረቃ በወር ሃያ ስድሰት ቀናት ላያመርት ይችላል የሚለውን የህላና ግምት በመያዝ የወሰኑት ግብር ባለመክፈላቸው በወንጀል የቀረበባቸው ክስ እና የተሰጠባቸው የጥፋተኝነትና የቅጣት ውሣኔ የአዋጅ ቁጥር 285/94 አንቀጽ 49 እና በአዋጅ ቁጥር 286/94 አንቀጽ 96 እና አንቀጽ 162 መስፈርት የማያሟላ መሆኑን ነው።
በአዋጅ ቁጥር 285/94 አንቀጽ 49 እና በአዋጅ ቁጥር 286/94 አንቀጽ 96 ግብር አለመክፈል የወንጀል ተግባር ተደርጎ የተደነገገው ግብር ከፋዬ ለግብር አስገቢው መስሪያ ቤት ባሳወቀና ባልከፈለው ግብርና ግብር አስገቢው መስሪያ ቤት ግብር ከፋዬ የያዛቸውን የሂሣብ ሰነዶችና ማስረጃዎች በተለያየ ምክንያት በመጣል በግምት በወሰነው ግብር መካከል ልዩነት ሲፈጠር ግብር ከፋዩን በወንጀል ለመጠየቅና ለመቅጣት በማሰብ አይደለም። ይልቁንም መክፈል የሚገባውን የግብር ገንዘብ ላለመክፈል በማሰብና ግብር አስገቢው መስሪያ ቤትም ንብረቶቸን በመያዝና በመሸጥ የግብር ገንዘቡን ገቢ እንዳያደርግ ለማድረግና ግብር ከመክፈል ኃላፊነቱ ለማምለጥ ንብረቶቹን የማሸሽና የመሰወር እና ልሎች ተመሣሣይነት ያላቸውን ህገወጥ ተግባራት በመፈፀም ግብር ያልከፈለ ግብር ከፋይን ተጠያቂ ለማድረግ እንደሆነ ይኸ ሰበር ችሎት በተመሣሣይ ጉዳይ በሰበር መዝገብ በቀን 11/1ዐ/ዐ2 ዓ.ም አስገዳጅ የሕግ ትርጉም ሰጥቶበታል።
ከዚህ አንጻር ሲታይ አመልካቾች በየወቅቱ ግብር የመስጠት ግድታቸውን ሲወጡ ቆይተዋል፡ አመልካቾች በየወቅቱ ባቀረቡት የሂሣብ ሪፖርት ለመንግስት የሚከፈል ገንዘብ የልለ መሆኑን ያሳወቁ መሆኑ ተረጋግጧል። ግብር አስገቢው መስሪያ ቤት በወንጀል ክሱ የተጠቀሰው የተጨማሪ እሴት ታክስ እና የዊዝ ሆልዲንግ ታክስ ገንዘብ ከአንደኛው አመልካች የሚፈለግ መሆኑን በመወሰን የግብር ውሣኔ ማስታወቂያ ከሰጣቸው በኋላ አመልካቾች በህጉ መሰረት አቤቱታ አቅርበዋል። ከዚህ በኋላ አመልካቾች በግብር አስገቢው መስሪያ ቤት የተወሰነውን ግብር ያልከፈሉት የአንደኛው አመልካች ንብረት በዳሽን ባንክ ዕዳ ምክንያት በመሸጡና የባንክ ዕዳ ተከፍሎ ቀሪ ገንዘብ ባለመኖሩ መሆኑን አንደኛው የተጠሪ ምስክር በስር ፍ/ቤት ባስመዘገበው የምሰክርነት ቃል እንደተገለፀ ተረድተናል።
ማናቸውም ሰው የፍታብሄር ዕዳ ለመክፈል ባለመቻሉ ምክንያት በወንጀል ጥፋተኛ ተብሎ እንደማይቀጣ በሲቪልና የፖለቲካ መብቶች ዓለም አቀፍ ስምምነት አንቀጽ 11 ተደንግጓል። ከዚህ አንፃር ሲታይ የአዋጅ ቁጥር 285/94 አንቀጽ 49 እና የአዋጅ ቁጥር 286/94 አንቀጽ 96 ድንጋጌዎችም ከህገ መንግስቱ አንቀጽ 13(2) እና ከላይ ከጠቀስነው ዓለም አቀፍ ድንጋጌ ጋር በማጣጣም ሁኔታ መተርጎምና ተፈፃሚ መሆን ያለባቸው መሆኑን ይህ ሰበር ችሎት በመዝገብ አስገዳጅ የህግ ትርጉም የሰጠበት ስለሆነ፣ አመልካቾች ግብር አስገቢው መስሪያ ቤት በግምት የወሰነውን የግብር ገንዘብ ለመክፈል ባለመቻላቸው ምክንያት በወንጀል ተጠያቂና ጥፋተኛ ላባሉ የሚችሉበት የህግ መሰረት የለም። በመሆኑም በህጉ የተደነገጉት መስፈርቶች ሳይሟሉና በወንጀል ህግ አንቀጽ 23 ንዑስ አንቀጽ 2 የተደነገገው የሃሳብና የግዙፍ ተግባር ሁኔታዎች ባልተሟሉበት ሁኔታ የሀዋሳ ከተማ ከፍተኛ ፍርድ ቤትና የክልሉ ጠቅላይ ፍ/ቤት አመልካችን ህግን በመተላለፍ ግብር ያለመክፈል ወንጀል ፈፅመዋል በማለት የሰጡት የጥፋተኝነትና የቅጣት ውሳኔ መሰረታዊ የሕግ ስህተት ያለበት ነው በማለት ወስነናል።
በደቡብ ብሕር ብሕረሰቦችና ሕዝቦች ክልል የሀዋሳ ከተማ ከፍተኛ ፍርድ ቤት በወንጀል መዝገብ የሰጠው ፍርድ እና የክልሉ ጠቅላይ ፍርድ ቤት በመዝገብ የሰጠው ትዕዛዝ በወ/መ/ሥ/ሥ/ሕግ ቁጥር 195 ንዑስ አንቀጽ 2(1) ሀ መሰረት ተሽሯል።
የበታች ፍርድ ቤቶች የሰጡት የጥፋተኝነትና የቅጣት ውሳኔ የተሻረ በመሆኑ አንደኛው አመልካች ብር 40,000 (አርባ ሺ ብር) መቀጮ ከመክፈል በነፃ ተሰናብቷል። አንደኛው አመልካች የመቀጮውን ከፍሎ ከሆነ ይመለስለት።
የበታች ፍርድ ቤቶች የሰጡት የጥፋተኝነትና የቅጣት ውሳኔ የተሻረ በመሆኑ ሁለተኛው አመልካች ከእስር እንዲለቀቅ በክፍሉ ማረሚያ ቤት መፍቻ ይፃፍ።
መዝገቡ ወደ መዝገብ ቤት ይመለስ።
No topics extracted.