No summary available.
የሰ/መ/ ሚያዚያ 24 ቀን 2005 ዓ.ም.
ዳኞች፡- ተሻገር ገ/ሥላሴ አልማው ወል ዓላ መሐመድ አዳነ ንጉሴ አዳነ ንጉሤ አመልካች፡- ወ/ሪት ማህልት ልዑለቃል ጠበቃ በፈቃዱ ተላላ ቀረቡ ተጠሪ፡- የለም መዝገቡን መርምረን የሚከተለውን ፍርድ ሰጥተናል።
ለዚህ የሰበር ክርክር መነሻ የሆነው ጉዳይ አመልካች ያቀረቡትን አቤቱታ ጉዳዩ በመጀመሪያ ደረጃ የቀረበለት የአዲስ አበባ ከተማ የመ/ደ/ፍርድ ቤት ውድቅ በማድረጉና በየደረጃው ያሉ የከተማው አስተዳደር የበላይ ፍርድ ቤቶችም የመ/ደ/ፍርድ ቤት የሰጠውን ውሳኔ በማጽናታቸው ነው።
አመልካች ሰኔ 04 ቀን 2004 ዓ/ም ያቀረቡት አቤቱታ ፍሬ ቃሉ ፡- ከአባቴ ከአቶ ፈለቀ ደንበልና ከእናቴ ከወ/ሮ ፋንቱ ገብረሕይወት ተወልጄ ማህልት ፈለቀ በሚል ስም በላፎንቴን መዋዕለ ሕጻናት ትምህርት ቤት እየተጠራሁ ትምህርቴን የጀመርኩ ቢሆንም መደበኛ ትምህርቴ ላሴ ገብረማርያም ትምህርት ቤት ሲቀጥል በት/ቤቱ መምህር በሆኑት አሳዳጊዬ በአቶ ልዑለቃል ገብረየሱስ ስም በመመዝገብ ተምሬ እስከ ዩኒቬርሲቲ ያጠናቀቅኩ ቢሆንም አሁን ግን በሥጋ ወላጆቼ ስም መጣራት ስለምፈልግ ማህልት ፈለቀ ደንበል ተብዬ እንዲጠራ ይወሰንልኝ የሚል ነው።
የመ/ደረጃ ፍርድ ቤትም፡- አመልካች አቤቱታቸውን ለማስረዳት ያቀረቡት የሰው ምስክሮች የሰጡትን ቃልና የጽሁፍ ማስረጃዎችን በመመርመርና በመመዘን በሰጠው ውሳኔ፡- አመልካች በፍ/ህ/ቁ/32(2) መሰረት ሥልጣን ከተሰጠው አካል የተሰጠ የቤተዘመድ ስም የሚገልጽ ማስረጃ ካለማቅረባቸውም ልላ የተሰሙት ምስክሮችም ‹‹ ልዑለቃል ገብረየሱስ ›› በሚል ስትጠራበት የነበረው የአሳዳጊ አጎቷ ስም መሆኑን እንጂ የቤተዘመድ ስም አለመሆኑን ስላስረዱና እንዲለወጥላቸው የፈለጉት ስም የቤተዘመድ ስም ስለመሆኑ ተገቢውን ማስረጃ በማቅረብ ስላላስረዱ አቤቱታው ተቀባይነት የለውም ሲል ውድቅ አድርጓል። ይህ ውሳኔም ከዚህ በላይ ከፍ ተብሎ እንደተገለጸው በበላይ ፍርድ ቤቶች በመጽናቱ ምክንያት ለዚህ ሰበር ችሎት የሰበር አቤቱታቸውን አቅርበዋል።
አመልካች በሰበር አቤቱታቸው በዋናነት የጠቀሱት የቅሬታ ነጥብም ሲጠቃለል፡- አንድ ሰው አንድ የቤተዘመድ ስምና አንድ ወይም ብዙ የግል ስሞችና የአባት ስም እንደሚኖረው በፍ/ህ/ቁ/32(1) የተደነገገ ሲሆን በቁጥር 33(1) ደግሞ የልጁ የቤተዘመድ ስም ማለት የአባቱ የቤተዘመድ ስም እንደሆነ ተመልክቷል። ስሙ እንዲለወጥለት በሚጠይቅ ሰው አቤቱታም የአቤቱታ አቅራቢውን የቤተዘመድ ስም ዳኞች ላለውጡ እንደሚችሉ ቁጥር 42 ተመልክቷል። በአሁን በአገራችን ባለው ተጨባጭ የስም አሰጣጥ ባህል መሰረትም የቤተዘመድ ስም የሚባል የለም። የቤተዘመድ ስም ሳይኖርው ሲቀር ደግሞ የቤተዘመድ ስም ነው ተብሎ የሚወሰደው የአባት ስም እንደሆነ በፍ/ህ/ቁ/ 33 (2) ተደንግጎ እያለና አመልካችም የቤተዘመድ ስሜ በወላጅ አባቴ ስም እንዲሆን እንዲወሰን በቂ የሰውና ጽሁፍ ማስረጃዎችን አቅርቤ ሳለሁ ፍርድ ቤቶች ውድቅ ያደረጉት ህጋዊ መሰረት ያለው አይደለም ብለዋል።
የጉዳዩ አመጣጥ ከዚህ በላይ የተመለከተው ሲሆን አመልካች በወላጅ አባቴ ስም እንድጠራ ይወሰንልኝ ሲሉ ያቀረቡትን አቤቱታ የሥር ፍርድ ቤቶች ውድቅ ያደረጉት በአግባቡ ነው? ወይስ አይደለም? የሚለውን ጭብጥ ይዘን ክርክሩን እንደሚከተለው መርምረናል።
በመርህ ደረጃ አንድ ሰው የቤተዘመድ ስም( family name)፣አንድ ወይም ከዚያ በላይ የግል ስሞች( first names) እና የአባት ስም( patronymic ) እንደሚኖረው በፍ/ህ/ቁ/32(1) የተደነገገ ሲሆን ለልጁ የአባት ስም የሚሆነው ደግሞ የአባቱ የግል ስም እንደሆነ በቁጥር 36 ተመልክቷል።
የልጁን መወለድ መግለጫ ላሰጥ የሚገባው ሰው ደግሞ ልጁ ከተወለደበት ቀን አንስቶ ባለው ተከታዩ ዘጠና ቀናት ውስጥ ለልጁ የተሰጠውን የግል ስም ልጁ በተወለደበት ቀበል(አጥቢያ) ለሚገኘው የክብር መዝገብ ጽህፈት ቤት መግለጫ የማቅረብ ግድታ ያለበት ስለመሆኑ በቁጥር 37 ከተደነገገው መገንዘብ የሚቻል ነው። የመወለድ ጽሑፍም ከሚያካትታቸው መስፈርቶች አንዱ በአንቀጽ 99(መ) ሥር የተመለከተው የቤተዘመድ ስም ነው። በልላ በኩል አንድ ሰው የቤተ ዘመድ ስም እንዲለወጥ የመጠየቅ መብት ያለው መሆኑ በቁጥር 42 የተመለከተ ሲሆን በዚህ ረገድ የሚቀርበውን ጥያቄ ዳኞች ተቀብለው ስሙ እንዲለወጥ መወሰን የሚችሉት ስሙን ለመለወጥ በቂ ምክንያት መኖሩን ሲያረጋግጡ ሲሆን የስሙ መለወጥም በልሎች ሶስተኛ ወገኖች ላይ አንድም ጉዳት እንዳያስከትል ጥንቃቄ ማድረግ የሚገባቸው ስለመሆኑም ህጉ ያመላክታል። እንግዲህ በክብር መዝገብ ላሰፈር የሚገባው የመወለድ ጽሑፍ ቃል የቤተዘመድ ስምንም የሚያካትት እስከሆነ ድረስ በጊዜው ልደትን፣ጋብቻና ሞት የሚመዘግበው የክብር መዝገብ ሹም ባለመኖሩ በፍ/ህጉ በቁጥር 3361(1) ስር ስለ ክብር መዝገቦች የተዘረዘሩት የፍ/ህግ ቁጥሮች በሥራ ላይ የሚውሉበት ቀን ተወስኖ በነጋሪት ጋዜጣ ላይ እስከሚወጣ ድረስ ተፈጻሚነት እንደማይኖራቸው የተደነገገ ሲሆን በንዑስ ቁጥር 2 ልደትን፣ጋብቻን እና ሞትን የሚገልጽ ማስረጃ በጊዜው በነበረው አጠራር የአገር ግዛት ሚኒስቴር የመረጣቸው ሰዎች ያዘጋጁትን የታወቁ ጽሁፎች በማቅረብ ማስረዳት የሚቻል ስለመሆኑ የተመለከተ ቢሆንም በይበልጥ ከዚህ ከሚያከራከረው ጉዳይ ጋር ተያይዞ የቤተዘመድ ስም የግል ስም እንዲሁም የአባት ስም( patronymic) በተደራጀ መልኩ የሚመዘግብ አካል የለም። በመሆኑም አመልካች በተወለዱበት በ1979 ልደትን በአግባቡ መዝግቦ ማስረጃ የሚሰጥ የክብር መዝገብ ሹም ወይም አካል በልለበት ሁኔታ አመልካች እንዲለወጥላቸው የጠየቁት ስም የቤተዘመዳቸው ስም ስለመሆኑ የሚያረጋግጥ ማስረጃ (ሰነድ) አለቀረቡም በሚል አቤቱታቸውን ፍርድ ቤቶቹ ውድቅ ያደረጉት ከዚህ በላይ የተጠቀሱትን ህጋዊ ምክንያች ያላገናዘበ ሆኖ አግኝተናል።
No topics extracted.
ወደ ፍሬ ጉዳዩ ስንመለስ አመልካች ላፎንቴን መዋዕለ ሕጻናት ትምህርት ቤት በ23/12/1991 ዓ/ም በተሰጣቸው የተማሪ ውጤት መግለጫ(ካርድ) ላይ ማህልት ፈለቀ በሚል ስማቸው መመዝገቡን ፣ላሴ ገብረማርያም 2ኛ ደረጃ ት/ቤት ሲማሩ ደግሞ ማህልት ልዑለቃል ገ/የሱስ በሚል ተመዝግበው መማራቸውን እንዲሁም በአዲስ አባባ ዩኒቨርሲቲ የንግድ ትምህርት ቤት ሲማሩም ማህልት ልዑለ ቃል ገብረየሱስ ተብለው እንደሚጠሩ በመ/ደ/ፍርድ ቤት ከቀረቡት የሰነድ ማስረጃዎች የተረጋጠ ሲሆን፤ ቀርበው ከተሰሙት የአመልካች አባት እና እናት ከሆኑት ምስክሮች ቃልም፡- አቶ ልዑለ ቃል ገብረየሱስ የአመልካች እናት ወንድም መሆናቸውን እና በት/ቤቱም መምህር ስለነበሩ አመልካችን ት/ቤቱ እንዲቀበላቸው በሚል የወላጅ አባታቸው ስም ተለውጦ በመምህር ልዑለ ቃል ገብረየሱስ ስም እንዲመዘገብ መደረጉን ካስረዱት የተረጋገጠ ፍሬ ነገር ነው።
እነዚህን ማስረጃዎችን የመመዘንና የመመርመር ሥልጣን ባለው የሥር የመ/ደ/ፍርድ ቤት የተረጋገጡትን ፍሬ ነገሮች ይዘን ጉዳዩን እንደመረመርነው አመልካች ቀደም ሲል ሲጠሩበት የነበረውን የአባታቸውን ስም በመለወጥ ማህልት ልዑለቃል ገ/የሱስ ስም የተጠሩት መደበኛ ትምህርታቸውን ለመማር በሚፈልጉበት ትምህርት ቤት ገብተው ለመማር አንዲያስችላቸው በሚል ምክንያት ሆኖ ሳለ ፍርድ ቤቶቹ በተረጋገጡት ፍሬ ነገሮች መሰረት ጉዳዩ ላይ ውሳኔ መስጠት ሲገባቸው ልዑለ ቃል ገብረ የሱስ የቤተዘመዳቸው ስም ስለመሆኑ ያቀረቡት ማስረጃ የለም ሲሉ ውድቅ ያደረጉት መሰረታዊ የሆነ የህግ ስህተት ያለበት ሆኖ በማግኘታችን ተከታዩን ውሳኔ ሰጥተናል።
የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር የመ/ደ/ፍርድ ቤት በመ/ቁ/2827/2004 በቀን 20/10/2004 ዓ/ም በዋለው ችሎት የሰጠውን ውሳኔ፣የከተማው ይግባኘ ሰሚ ፍርድ ቤት በመ/ቁ/18469 በቀን 23/12/2004 ዓ/ም በዋለው ችሎት የሰጠውን ትዕዛዝ እና የከተማው አስተዳደር ሰበር ሰሚ ችሎት በመ/ቁ/19021 በቀን 24/03/2005 ዓ/ም በዋለው ችሎት የሰጠውን ትዕዛዝ በፍ/ሥ/ሥ/ህ/ቁ/348(1) መሰረት ሽረናል።
አመልካች በወላጅ አባታቸው በአቶ ፈለቀ ደንበል ስም እንዲጠሩ በጠየቁት መሰረት ቀደም ሲል ሲጠሩበት የነበረው ስም ማህልት ልዑለቃል ገብረየሱስ ተቀይሮ ማህልት ፈለቀ ደንበል በሚል እንዲጠሩ ወስነናል።
መዝገቡን ዘግተን ወደ መዝገብ ቤት መልሰናል።