No summary available.
የካቲት 10 ቀን 2006 ዓ.ም.
ዳኞች:- አልማው ወል ዓላ መሐመድ ረታ ቶለሳ አዳነ ንጉሴ ሙስጠፋ አህመድ አመልካች፡- ወ/ት ሞሚና ሡልጣን ኮርዋላ - ቀረቡ ተጠሪ፡- የለም መዝገቡ ተመርምሮ የሚከተለው ፍርድ ተሰጥቶአል።
ጉዳዩ የአባት ስም ይስተካከልልኝ ጥያቄን የሚመለት ሲሆን የተጀመረውም አመልካች ከአሁን ቀደም በወላጅ አባታቸው ስም ሞሚና ሡልጣን ኮርዋላ ተብለው እና በአሳዳጊ አባታቸው ስም ሞሚና ወርቁ ይብሬ ተብለው በሁለት የአባት ስም ይጠሩ እንደነበረ እና አሁን ግን በትክክለኛው አባታቸው ስም መጠራት እንደፈለጉ በመግለጽ ሞሚና ወርቁ ይብሬ ተብለው መጠራታቸው ቀርቶ ሞሚና ሡልጣን ኮርዋላ ብቻ ተብለው እንዲጠሩ ይወሰንላቸው ዘንድ በመጠየቅ ለአ/አበባ ከተማ የመ/ደ/ፍ/ቤት ባቀረቡት የክስ አቤቱታ ነው።ፍ/ቤቱም አቤቱታውን እና የቀረበውን የሰነድ ማስረጃ ከመረመረ በኃላ አመልካች አሁንም ቢሆን ሞሚና ሡልጣን ኮርዋላ ተብለው የሚጠሩ መሆኑን ከሰነድ ማስረጃዎቹ መገንዘብ መቻሉን ገልጾ አመልካች እየተጠሩበት ባለው የአባት ስም እንድጠራ ይወሰንልኝ በማለት ያቀረቡት አቤቱታ የክስ ምክንያት የለውም በማለት መዝገቡን በፍ.ስ.ስ.ሕ.ቁ.
231(1)(ሀ) መሰረት በብይን ዘግቶአል።አመልካች ለዚህ ችሎት አቤቱታ ያቀረቡትም ለከተማው የበላይ ፍ/ቤቶች ያቀረቡት ይግባኝ እና የሰበር አቤቱታ ተቀባይነት በማጣቱ ሲሆን የሰበር አቤቱታው ተመርምሮ በዚህ ጉዳይ አመልካች በሁለት የአባት ስሞች እንደሚጠሩ በሰነድ ማስረጃ በተረጋገጠበት ሁኔታ ያቀረቡት የአባት ስም ይስተካከልልኝ ጥያቄ የክስ ምክንያት የለውም ተብሎ በስር ፍ/ቤቶች ውድቅ የመደረጉን አግባብነት ለመመርመር ጉዳዩ ለሰበር ችሎት እንዲቀርብ ተደርጎአል።
የጉዳዩ አመጣጥ እና የአመልካች ክርክር ይዘት ከላይ የተመለከተው ሲሆን እኛም የአመልካች የዳኝነት ጥያቄ የክስ ምክንያት የለውም ተብሎ በስር ፍ/ቤቶች የተሰጠው ውሳኔ መሰረታዊ የሕግ ስህተት የተፈጸመበት መሆን አለመሆኑን ለጉዳዩ አግባብነት ካላቸው የሕግ ድንጋጌዎች ጋር በማገናዘብ መርምረናል።
በዚህም መሰረት ፍ/ቤቶች የቀረበላቸውን የክስ አቤቱታ ተቀብለው ክርክሩን መስማት ከመጀመራቸው በፊት በክስ ማመልከቻው ላይ የተገለጸው ጉዳይ የሚያስከስስ መሆን አለመሆኑን ማርጋገጥ የሚገባቸው መሆኑ እና በክስ ማመልከቻው ላይ የተገለጸው ጉዳይ የማያስከስስ ሆኖ በተገኘ ጊዜ የክስ አቤቱታው ተቀባይነት እንደልለው ገልጸው መመለስ የሚገባቸው መሆኑ በፍ.ስ.ስ.ሕ.ቁ 231(1)(ሀ) ስር ተደንግጎ እንደሚገኝ የሚታወቅ ነው።ይሁን እንጂ በዚህ ድንጋጌ መሰረት ጉዳዩ የሚያስከስስ አይደለም ተብሎ ተቀባይነት ከማጣቱ በፊት በክስ ማመልከቻው ላይ የተገለጸው ጉዳይ በርግጥም የማያስከስስ መሆኑ በአግባቡ መረጋገጥ ይኖርበታል።ቀደም ሲል እንደተገለጸው የአመልካቿ የዳኝነት ጥያቄ ከአሁን ቀደም በወላጅ አባታቸው ስም ሞሚና ሡልጣን ኮርዋላ ተብለው እና በአሳዳጊ አባታቸው ስም ሞሚና ወርቁ ይብሬ ተብለው በሁለት የአባት ስም ይጠሩ እንደነበረ እና አሁን ግን በትክክለኛው አባታቸው ስም መጠራት እንደፈለጉ በመግለጽ ሞሚና ወርቁ ይብሬ ተብለው መጠራታቸው ቀርቶ ሞሚና ሡልጣን ኮርዋላ ብቻ ተብለው እንዲጠሩ እንዲወሰንላቸው ሲሆን ይጠሩበት በነበሩት ሁለቱም የአባት ስሞች የተዘጋጁ ወይም ከመንግስታዊ ተቋማት የተሰጡ ሰነዶችንም በማስረጃነት ማቅረባቸውን የመዝገቡ ግልባጭ ያመለክታል።
በመሰረቱ እያንዳንዱ ሰው አንድ የቤተዘመድ ስምና አንድ ወይም ብዙ የግል ስሞች እና የአባት ስም እንደሚኖረው፣እንዲሁም ለልጁ የአባት ስም የሚሆነው የአባቱ የግል ስም እንደሆነ በፍ.ሕ.ቁ.32(1) እና 36(1) ድንጋጌዎች ተመልክቶአል።አንድ ሰው በተለያዩ ምክንያቶች በአባቱ ብቻ ሳይሆን በአሳዳጊው ስም ጭምር ላጠራ የሚችልባቸው አጋጣሚዎች መኖራቸው የሚታወቅ ሲሆን እንዲህ ዓይነቱ ሰው ተገቢ ሆኖ ባገኘው ጊዜ በአሳዳጊው ስም ጭምር መጠራቱ ቀሪ ሆኖ ከላይ በተጠቀሰው የፍትሐብሕር ሕጉ ድንጋጌ መሰረት በአባቱ ስም ብቻ እንዲጠራ የመወሰን መብት ያለው በመሆኑ ይህንኑ መብቱን በፍርድ ለማረጋገጥ የሚያቀርበው የዳኝነት ጥያቄ የክስ ምክንያት የለውም የሚባልበት ሕጋዊ ምክንያት አይኖርም።አመልካች ክሱን ያቀረቡት በሚጠሩበት የአሳዳጊያቸው ስም የተሰጡ ሰነዶችን ወደሚጠሩበት አባታቸው ስም በሕግ አግባብ ለማስቀየር እና እነዚሁ ሰነዶች በሚሰጡት መብት ለመገልገል ጭምር መሆኑን ከክርክራቸው ይዘት መገንዘብ የሚቻል በመሆኑ ሞሚና ወርቁ ይብሬ ተብለው መጠራታቸው ቀርቶ ሞሚና ሡልጣን ኮርዋላ ብቻ ተብለው እንዲጠሩ ባቀረቡት የዳኝነት ጥያቄ መሰረት ላሰጥ የሚችለው ውሳኔ በአመልካቿ መብት ላይ የሚያስከትለው ሕጋዊ ውጤት አይኖርም ላባል የሚችል ሆኖ አላገኘነውም።
No topics extracted.
ሲጠቃለል ክሱ የቀረበለት የአ/አበባ ከተማ የመ/ደ/ፍ/ቤት የቀረበለትን የክስ ማመልከቻ እና ማስረጃ መርምሮ ተገቢውን ውሳኔ መስጠት የሚገባው ሆኖ እያለ በክስ ማመልከቻው ላይ የተገለጸው ጉዳይ የሚያስከስስ አይደለም በማለት ሲል የሰጠው እና በከተማው የበላይ ፍ/ቤቶች በትዕዛዝ የፀናው ብይን የክስ ማመልከቻውን እና የፍ.ስ.ስ.ሕ.ቁ 231(1)(ሀ) ድንጋጌን ይዘትና ዓላማ በአግባቡ ያላገናዘበ እና መሰረታዊ የህግ ስህተት የተፈጸመበት ሆኖ በመገኘቱ የሚከተለው ውሳኔ ተሰጥቶአል።
አመልካች ያቀረቡት የክስ ማመልከቻ የክስ ምክንያት የለውም ሲል መዝገቡን በፍ.ስ.ስ.ሕ.ቁ. 231(1)(ሀ) መሰረት በመዝጋት የአ/አበባ ከተማ የመ/ደ/ፍ/ቤት በመ.ቁ. 2908 በ07/12/2005 ዓ.ም. የሰጠው እና በከተማው ፍ/ቤቶች ይ/ሰሚ እና ሰበር ችሎቶች እንደቅደም ተከተሉ እና በመ.ቁ. 20742 በ27/12/2005 ዓ.ም.እና በመ.ቁ.21123 በ27/02/2006 ዓ.ም. በትዕዛዝ የፀናው ብይን በፍ.ስ.ስ.ሕ.ቁ. 348(1)መሰረት ተሽሮአል።
አመልካች ባቀረቡት የክስ ማመልከቻ ላይ የተገለጸው ጉዳይ የክስ ምክንያት ያለው መሆኑን ተገንዝቦ ጉዳዩን በማንቀሳቀስ የቀረበለትን የክስ ማመልከቻ እና ማስረጃ መርምሮ ተገቢውን ውሳኔ ይሰጥበት ዘንድ ጉዳዩ በፍ.ስ.ስ.ሕ.ቁ. 341(1)መሰረት ወደ አ/አበባ ከተማ የመ/ደ/ፍ/ቤት እንዲመለስ ወስነናል።
በዚሁ መሰረት ይፈጸም ዘንድ የውሳኔው ግልባጭ ለስር ፍ/ቤቶች ይላክ።
ውሳኔ ያገኘ ስለሆነ መዝገቡ ተዘግቶአል።