No summary available.
ታህሳስ 30 ቀን 2ዐዐ6 ዓ.ም ዳኞች፡- አልማው ወል ዓላ መሐመድ ረታ ቶሎሳ አዳነ ንጉሴ ሙስጠፋ አህመድ አመልካች፡- ወ/ሮ ጂእቶ ያሲን ሺበሺ ቀረቡ ተጠሪ፡- አቶ ሐሰን መሐመድ - በልሉበት የሚታይ **
መዝገቡ ተመርምሮ ተከታዩ ፍርድ ተሰጥቷል።
**
ጉዳዩ የጋብቻ ክርክርን የሚመለከት ሲሆን ክርክሩ የተጀመረው በአፋር ብሕራዊ ክልላዊ መንግስት በፋንቲ ረሱ ከፍተኛ ሸሪዓ ፍርድ ቤት ነው፡፤ ፍርድ ቤቱ ለአሁኗ ለአመልካች በቁጥር ፋ/ሸ/577/05 በቀን 21/06/2005 በአድራሻቸው በፃፈው ውሳኔ የአሁኗ አመልካች ከአሁኑ ተጠሪ ጋር የተፋቱ ስለመሆኑ ማስረጃ አላቀረቡም፣ከአቶ አደም አንባዬ ጋር ተጋባሁ ስለሚሉት ጋብቻ ያቀረቡት ማስረጃ የማጭበርበሪያ ወረቀት መሆኑ ተረጋግጧል በሚል ምክንያት አመልካቿ የተጠሪው ሚስት እንጂ የአቶ አደም አንባዬ ሚስት አይደሉም ሲል መወሰኑን አረጋግጧል።በዚህ ውሳኔ የአሁኑ አመልካች ቅር በመሰኘት ይግባኛቸውን ለአፋር ብሕራዊ ክልላዊ መንግስት ጠቅላይ ሸሪዓ ፍርድ ቤት አቅርበው ፍርድ ቤቱ ግራ ቀኙን ከአከራከረ በኋላ ጉዳዩን መርምሮ የስር ፍርድ ቤትን ውሳኔ አጽንቶታል።የአሁኑ የሰበር አቤቱታ የቀረበውም ይህንኑ ውሳኔ በመቃወም ለማስለወጥ ነው። የአመልካች የሰበር አቤቱታም መሰረታዊ ይዘትም በያሎ ወረዳ ፍርድ ቤት ከተጠሪ ጋር በነበራቸው የጋብቻ ይፍረስልኝ ክርክር የወረዳው ፍርድ ቤት ግራ ቀኙን አከራክሮ በመ/ቁጥር 14/2003 በቀን 04/06/2003 በሰጠው ውሳኔ ጋብቻው መፍረሱን አረጋግጦ ባለበት ሁኔታ ጉዳዩ በሸሪዓ ፍርድ ቤት እንዲታይ መደረጉ ስነ ስርዓቱን የተከተለ አይደለም፣በአገሪቱ ሕገ መንግስት የተረጋገጠውን ጋብቻን በፈቃደኝነት የመመስረት መብትም የጣሰና የእኩልነት መብትን ያላስከበረ ነው በማለት መከራከራቸውን የሚያሳይ ነው።
አቤቱታቸው ተመርምሮም የግራ ቀኙ ጋብቻ በመደበኛ ፍርድ ቤት በክልሉ ከፈረሰ በኋላ የክልሉ የሸሪዓ ፍርድ ቤቶች ጉዳዩን ዳግም የማስተናገዳቸውን አግባብነት ከፍ/ብ/ሥ/ሥ/ሕ/ቁጥር 5 ድንጋጌ አንፃር ለመመርመር ሲባል ጉዳዩ ለሰበር ችሎት እንዲቀርብ የተደረገ ሲሆን ለተጠሪ በሕጉ አግባብ ጥሪ ተደርጎላቸው ባለመቅረባቸው በፅሑፍ መልስ የመስጠት መብታቸው ታልፏል።
የጉዳዩ አመጣጥ አጠር አጠር ባለመልኩ ከላይ የተገለፀው ሲሆን ይህ ችሎትም የግራ ቀኙን ክርክር ለሰበር አቤቱታው መነሻ ከሆነው ውሳኔ እና አግባብነት ካላቸው ድንጋጌዎች ጋር በማገናዘብ ጉዳዩን ለሰበር ችሎቱ ሲቀርብ ከተያዘው ጭብጥ አንጻር በሚከተለው መልኩ መርምሮታል።
ከክርክሩ ሂደት መገንዘብ የተቻለው አመልካችና ተጠሪ ጉዳዩን በያሎ ወረዳ ፍርድ ቤት በፍቺ ጉዳይ ተከራክረው በመካከላቸው ያለው ጋብቻ የፈረሰ መሆኑ በመ/ቁጥር 14/2003 በቀን 04/06/2003 ከተወሰነ በኃላ የጋብቻው ጉዳይ ተመልሶ በሸሪዓ ፍርድ ቤቶች የታዬና አመልካች ያለፍላጎታቸው ከተጠሪ ጋር በጋብቻ እንዲቀጥሉ ተብሎ የተወሰነ መሆኑን ነው።
በመሰረቱ በኢ.ፍ.ዲ.ሪ ህገ-መንግስት አንቀጽ 34(1) ስለ ተጋቢዎች በጋብቻ አፈፃፀም፣ በጋብቻ ዘመንና በፍቺ ጊዜ እኩል መብት ያላቸው ስለመሆኑ በግልጽ የተደነገገ ሲሆን በአንቀጽ 35(2) ድንጋጌም ሴቶች በሕገ መንግስቱ በተደነገገው መሰረት በጋብቻ ከወንዶች ጋር እኩል መብት ያላቸው መሆኑ በግልጽ ተቀምጧል። በልላ በኩል ሕገ መንግስቱ በሕግ በተለይ በሚዘረዝረው መሰረት በሐይማኖት፣ በባህል የሕግ ስርአቶች ላይ ተመስርተው ለሚፈጸሙ ጋብቻዎች እውቅና የሚሰጥ ሕግ ላወጣ እንደሚችል የኢ.ፍ.ዲ.ሪ ሕገ መንግስት በአንቀጽ 34(4) ከማስቀመጡም በላይ በዚሁ አንቀጽ በንዑስ ቁጥር አምስት ድንጋጌ ስር ሕገ መንግስቱ የግልና የቤተሰብ ሕግን በተመለከተ በተከራካሪዎች ፈቃድ በሀይማኖታቸው ወይም በባህሎቻቸው ሕጎች መሰረት መዳኘትን እንደማይከለክል፣ዝርዝሩም በሕግ እንደሚወሰን አስቀምጧል። በዚህም አግባብ የሸሪዓ ፍ/ቤቶች በአዋጅ ቁጥር 188/1992 የተቋቋሙ ሲሆን በቤተሰብ ጉዳይ ላይ ያላቸው የስረ ነገር የዳኝነት ስልጣን ተለይቶ ተቀምጦላቸዋል።
አሁን የተያዘው ጉዳይም በሕገ መንግስቱና በአዋጅ ቁጥር 188/1992 መሰረት ለሸሪዓ ፍ/ቤቶች በተሰጠው ስልጣን መሰረት እንዲታይ በተጠሪ በኩል የቀረበ ሲሆን አመልካች ጉዳዩ በአዋጅ ቁጥር 188/1992 መሰረት በተዘረጋው ስርዓት እንዲታይ ፈቃድ የሰጡ ስለመሆኑም የክርክሩ ሂደት የማያሳይ ቢሆንም አመልካች አጥብቀው የሚከራከሩት ከተጠሪ ጋር የነበራቸው ጋብቻ በመደበኛ ፍርድ ቤት ከፈረሰ በኋላ በሸሪዓ ፍርድ ቤቶች የሚታይበት ስነ ስርዓታዊ አግባብ የለም በሚል ምክንያት ነው። በመሆኑም በዚህ ችሎት ጉዳዩ ላታይ የሚችለው በአዋጅ ቁጥር 188/1992 አንቀጽ 5(4) እና 6(2) በተደነገገው መሰረት የሸሪዓ ፍ/ቤቶች ጉዳዩን ሲመሩ የፈፀሙት የስነ ሥርዓት ሕግ ግድፈት ካለ ብቻ ነው። ከዚህ ውጪ ሐይማኖትን መሰረት በማድረግ የሸሪዓ ፍ/ቤቶች የሚሰጡት ውሳኔ ተገቢ መሆን ያለመሆኑን ይህ ችሎት የመመርመር ስልጣን የለውም።ከዚህ አንጻር የሸሪዓ ፍርድ ቤት አመልካች ያለፍላጎታቸው ከተጠሪ ጋር በጋብቻ ላቀጥሉ ይገባል በማለት የደረሰው ድምዳሜ በዚህ ችሎት የሚታይበት አግባብ የልለ በመሆኑ አመልካች በሕገ መንግስቱ የተከበረላቸውን በፍላጎት ጋብቻ የመመስረት መብት መሰረት አድርገው የሚያቀርቡትን ክርክር አልፈነዋል።
አመልካች በተያዘው ጉዳይ ተፈፀመ የሚሉት የስነ ስርዓት ሕግ ግድፈት በመደበኛ ፍርድ ቤት የተሰጠ የፍቺ ውሳኔ እያለ ዳግም በሸሪዓ መታየቱ ተገቢነት የለውም የሚል ነው። በክልሉ የሸሪዓ ፍርድ ቤቶች የወል የዳኝነት ስልጣን በፍድራል በአዋጅ ቁጥር 188/1992 ከተዘረጋው የተለየ ስለመሆኑ በስር ፍርድ ቤት ክርክር ያልቀረበ ሲሆን በተጠቃሹ የፍድራሉ አዋጅ አንቀጽ 4 ስር የተመለከተ ሲሆን አዋጁ ፍርድ ቤቶቹ ስለሚሰሩባቸው ሕጎችም በአንቀጽ 6 ስር ደንግጓል።በዚህ አንቀፅ ስር ከተመለከቱት ሕጎች መካከል ስራ ላይ ያለውና በ1958 ዓ/ም የወጣው የፍትሐ ብሕር ሥነ ስርዓት ሕግ አንዱ ስለመሆኑ የተጠቃሹ አንቀፅ ንዑስ ቁጥር ሁለት ድንጋጌ በግልጽ ያሳያል።ከዚህ አንጻር ጉዳዩን ስንመለከተውም የፍትሐ ብሕር ክርክር አንድ ደረጃ ላይ ሲደርስ መቋጫ እንዲኖረው በማሰብ ከተደነገጉ በ1958 ዓ/ም በወጣው የስነ ስርዓቱ ድንጋጌዎች አንዱ የመጨረሻ ፍርድ ያገኙ ጉዳዮች /Res judicata/ የሚለው ሲሆን ይህ ጽንሰ ሀሣብ በፍ/ብ/ሥ/ሥ/ሕ/ቁ/ 5 ስር በግልጽ ተቀምጧል። በዚህ ድንጋጌ መሰረት የመጨረሻ ፍርድ ያገኙ ጉዳዮች ማለት በማናቸውም መልክ በሕግ በተቋቋመ ፍ/ቤት ቀርበው የመጨረሻ እልባት ያገኙ ጉዳዮችን የሚሸፍኑ መሆናቸውንና እንዲህ አይነት እልባት አግኝተዋል የሚባሉት ጉዳዮች ደግሞ በፍርድ፣ በብይን፣ በውሣኔ፣ በትእዛዝ፣ ወይም በጊዜያዊ አገልግልት ባለው ትእዛዝ የመጨረሻ ውጤት አግኝተው በልላ መልክ መንቀሣቀስ የማይችሉ የክርክር ነጥቦችን ሁሉ አጠቃልሎ የያዘ መሆኑንና መሰረታዊ አላማውም ክርክር አንድ ቦታ ላይ እንዲቆም ታስቦ በሕግ የተዘረጋ ስርዓት የሚያስገነዝበን ነው። በፍ/ብ/ሥ/ሥ/ሕ/ቁ 5 ስር በተመለከተው አኳኋን አንድ ጉዳይ አስቀድሞ በፍርድ ያለቀ ነው ለማለት መረጋገጥ ካላባቸው ሁኔታዎች ውስጥ ቀደም ሲል ቀጥተኛ የፍሬ ነገር ጭብጥ የነበሩ ጉዳዮች በድጋሚ በቀረበው ክስም ላይ በቀጥታ በፍሬ ነገር ጭብጥ ሆነው መቅረባቸው፣ቀደም ሲል የነበረውን ክርክር አሁን በክርክር ተሣታፊ በሆኑ ወገኖች ወይም ከእነሱ መብት በተላለፈላቸው ወይም ተላልፎላቸው በነበረ ወገኖች መሆኑንና እነዚህ ጉዳዮች ቀደም ሲል በተካሄደው ሙግት የመጨረሻ ፍርድ ያረፈባቸው መሆኑን ነው።
ሕጉ ቀጥተኛ የፍሬ ነገር ጭብጥ በመጨረሻ ፍርድ መቃወሚያነት ሲቀርብ ተቀባይነት የሚኖረው ይኸው ጉዳይ በድጋሚ በቀረበው ክርክር ላይ መቅረቡ ሲረጋገጥ ስለመሆኑም ያስገነዘስባል።ከሕጉ ይዘትና መንፈስ ቀጥተኛ የፍሬ ነገር ጭብጥ የሚለው ሐረግ ሲታይም በመጀመሪያው ክርክር ለይ ከአንደኛው ወገን ተጠይቆ በልላኛው ወገን የተካደ ወይም በቀጥታም ሆነ በተዘዋዋሪ የታመነና በዚሁ ላይ የፍርድ ውሣኔ ያረፈበት የክርክር ነጥብ መሆኑን ያስገነዝባል። በመሆኑም በድጋሚ በቀረበው ክስ በቀድሞው ክርክር ተሣታፊ በነበሩ ወገኖች ወይም ከእነሱ መብት በተላለፈላቸው ወገኖች የሚካሄድ መሆኑና በሁለተኛው ክስም የተያዘው ፍሬ ነገር ጭብጥ ከመጀመሪያው ጋር ሙሉ በሙሉ ተመሣሣይ ሆኖ የመጨረሻ ፍርድ ያረፈበት መሆኑ ከተረጋገጠ እንዲሁም ጉዳዩ የመጨረሻ ፍርድ አርፎበታል የሚል ተቃውሞ በተከራካሪ ወገን ከተነሣ ተቀባይነት ያለው ስለመሆኑ የፍ/ብ/ሥ/ሥ/ሕ/ቁ 5 (1) እና (2) ድንጋጌዎች ከፍ/ብ/ሥ/ሥ/ሕ/ቁጥር 244(2(ለ)) እና 245(2) ድንጋጌ ጋር ተጣምረው ሲታዩ የሚያስገነዝቡን ጉዳይ ነው። በአጠቃላይ የፍ/ብ/ሥ/ሥ/ሕ/ቁጥር 5 ድንጋጌ ሲታይ በቀዳሚው ክርክር የተያዘው ጭብጥና የፍሬ ነገር ክርክር ተመሳሳይ መሆኑ የተከራካሪ ወገኖች አንድነት ብቻ ሳይሆን በጉዳዩ ላይ ከላይ የተመለከቱት መመዘኛዎች በተሟሉበት ሁኔታ የመጨረሻ ፍርድ የተሰጠ መሆኑ ከተረጋገጠ በጉዳዩ ላይ አስቀድሞ የመጨረሻ ፍርድ የተሰጠበት በመሆኑ ድጋሚ ክስ የሚቀርብበት አግባብ የልለ መሆኑን ያስረዳል። ይህ ድንጋጌ ጉዳዮችን በአግባቡ ለመመራትና ተከራካሪ ወገኖች ለአላስፈላጊ ወጪና እንግልት እንዳይዳረጉ ለማድረግ የሚያስችል መሆኑም ይታመናል።
ወደ ተያዘው ጉዳይ ስንመለስም አመልካች በያሎ ወረዳ ፍርድ ቤት ከተጠሪ ጋር በነባራቸው የጋብቻ ይፍረስልኝ ጥያቄ ፍርድ ቤቱ በ1952ቱ የፍትሃ ብሕር ሕግ ስለቤተሰብ በተመለከቱት ድንጋጌዎች አግባብ ጉዳዩን በመመራት ጋብቻው መፍረሱን መወሰኑን በመ/ቁጥር 14/2003 በቀን 04/06/2003 የተሰጠው ውሳኔ ያሳያል።ተጠሪ ይህንኑ ውሳኔ የሚያውቁት መሆኑን የውሳኔው ግልባጭ ያሳያል። በዚህ አግባብ የፍቺ ውሳኔ ከተሰጠ በኃላ ተጠሪ ጉዳዩን ወደ ሸሪዓ ፍርድ ቤት በመውሰድ አሁን ለክርክሩ ምክንያት የሆነውን ውሳኔ አግኝተዋል።ይኸ የተጠሪ የክርክር ስልት በአገሪቱ ሰዎች በፈቃዳቸው በሀይማኖት ወይም በባህል ህግ መሰረት የመዳኘት መብት እንዳላቸው በህገ መንግስቱ አንቀፅ 34 ንዑስ አንቀፅ 5 የተረጋገጠውን መብት ተገቢ ባልሆነ መንገድ ተግባራዊ ለማድረግ የሞከሩ መሆናቸውን የሚያሣይ ነው። ተጠሪ በያሎ ወረዳ ፍርድ ቤት ቀርቦ ታይቶ እልባት ያገኘውን የፍቺ ጉዳይ ከውሳኔ በኋላ ለሸሪዓ ፍርድ ቤት ታይቶ እንዲወሰን ያቀረቡት ጥያቄ የህገ መንግስቱን አንቀፅ 34(5)፣የአዋጅ ቁጥር 188/1992 አንቀጽ 6(2) እና የፍ/ብ/ሥ/ሥ/ሕ/ቁጥር 5(1) የሚጥስ ነው።
ሲጠቃለልም ከላይ በተዘረዘሩት ምክንያቶች የፋንቲ ረሱ ከፍተኛ ሸሪዓ ፍርድ ቤትና የአፋር ክልል ጠቅላይ ሸሪዓ ፍርድ ቤት አመልካች የተጠሪ ሚስት ናቸው በማለት የሰጡት ውሳኔ መሰረታዊ የሆነ የስነ ስርዓት ሕግ ግድፈት ያለበት ሁኖ ስለአገኘነው ተከታዩን ወስነናል።
ው ሣ ኔ
በፋንቲ ረሱ ከፍተኛ ሸሪዓ ፍርድ ቤት በቁጥር ፋ/ሽ/577/05 በቀን 21/06/2005 ዓ/ም ተሰጥቶ በአፋር ክልል ጠቅላይ ሸሪዓ ፍርድ ቤት በመ//05 ሰኔ 28 ቀን 2005 ዓ/ም የጸናው ውሳኔ በፍ/ብ/ሥ/ሥ/ሕ/ቁጥር 348(1) መሰረት ተሽሯል።
በአመልካችና በተጠሪ መካከል ያለው ጋብቻ በያሎ ወረዳ መደበኛ ፍርድ ቤት የፈረሰና በፍ/ብ/ሥ/ሥ/ሕ/ቁጥር 5(1) አግባብ ፍርድ የተቋጨ በመሆኑ በአዋጅ ቁጥር 188/1992 አንቀጽ 6(2) መሰረት በሸሪዓ ፍርድ ቤቶች ዳግም የሚዳኝበት ስነ ስርዓት የለም ብለናል።
በዚህ ችሎት ለተደረገው ክርክር የወጣውን ወጪና ኪሳራ አመልካቸ የራሳቸውን ይቻሉ ብለናል።
No topics extracted.