No summary available.
የሰ/መ/ የካቲት 13 ቀን 2005 ዓ.ም.
ዳኞች፡- ተሻገር ገ/ሥላሴ አልማው ወል ረታ ቶሎሣ አዳነ ንጉሴ ሙስጠፋ አህመድ አመልካቾች፡-
ጉዳዩ ኑዛዜን የማስፈረስ ክስ ወይም አቤቱታ ለፍ/ቤት ላቀርብ የሚገባበትን የጊዜ ገደብ የሚመለከት ነው።
የአሁኖቹ አመልካቾች ሟች አቶ አላ አህመድ ታህሳስ 4 ቀን 2ዐዐ1ዓ.ም አደረጉት የተባለውን ኑዛዜ ለአ/አበባ ከተማ የመ/ደ/ፍ/ቤት አቅርበው ውሣኔ በማሰጠት የኑዛዜ ወራሽነት ማስረጃ ከወሰዱ በኋላ የአሁኖቹ ተጠሪዎች የሟች የመጀመሪያ ደረጃ ወራሾች ሆነን እያለ በኑዛዜው የተደረገው ድልድል መብታችንን የሚነካ በመሆኑ ኑዛዜው ላሻር ይገባል በማለት በፍ/ስ/ስ/ሕ/ቁ 358 መሰረት መቃወሚያ በማቅረባቸው ፍ/ቤቱ የግራ ቀኙን ክርክር ከሰማ በኋላ የመ/አመልካቾቹ ኑዛዜው ሲነበብ ያልነበሩ እና ወኪልም ያልነበራቸዉ ቢሆንም ኑዛዜ መኖሩን ስለኑዛዜው ስልጣን በተሰጣቸው 3ኛ በመ/ተጠሪ እንዲያውቁ የተደረገ እና በክፍፍሉ ረገድም ሀሳባቸውን ሲሰጡ የነበሩ ስለመሆኑ የመ/ተጠሪዎች ካቀረቧቸው የሰነድ ማስረጃ መገንዘብ ስለተቻለ እና ስለድልድሉ ከ3ኛ የመ/ተጠሪ ከሰሙበት ጊዜ ጀምሮ አቤቱታቸውን በ15 ቀን ውስጥ ስላላቀረቡ አቤቱታቸው በፍ/ሕ/ቁ 973 እና 974 መሰረት በይርጋ ቀሪ ይሆናል በማለት በብይን አሰናብቶአቸዋል።
ይ/ሰሚው ፍ/ቤት በበኩሉ የግራ ቀኙን ክርክር ከሰማ በኋላ የስር የመ/ተጠሪዎች ውርስ አጣሪው በአግባቡ ተሰይሞ ስለውርስ ክፍፍልም ሆነ ድልድል ለስር የመ/አመልካቾች የገለፀላቸው ስለመሆኑ የሚያረጋግጥ ማስረጃ እንዳላቀረቡ ከስር የመ/አመልካቾቹ ጋር ሲጻጻፍበት ነበር የተባለውም ማስረጃ የመ/አመልካቾች ኑዛዜ ሰለመኖሩ ያውቁ ነበር የሚለውን ከሚያስረዳ በስተቀር አሁንም ስለውርስ ክፍፍልና ድልድል የሚገልፀው ነገር እንደልለ በዚህም ምክንያት አቤቱታው በፍ/ሕ/ቁ 973/1/ መሰረት በይርጋ ይታገዳል የተባለው በአግባቡ እንዳልሆነ በዝርዝር ገልጾ ብይኑን በመሻር የውርስ ክፍፍልን አስመልክቶ በኑዛዜው ላይ የቀረበውን ክርክር መርምሮ ውሣኔ ይሰጥበት ዘንድ ጉዳዩን ወደስር ፍ/ቤት የመለሰው ሲሆን የአሁኖቹ አመልካቾች አቤቱታቸውን ለዚህ ችሎት ያቀረቡት የአ/አበባ ከተማ ፍ/ቤቶች ሰበር ችሎት ያቀረቡለትን አቤቱታ ዘግቶ በማሰናበቱ ነው።
አመልካቾቹ በ17/12/04ዓ.ም አዘጋጅተው ያቀረቡት አቤቱታ ተመርምሮ ጉዳዩ ለሰበር ክርክር እንዲቀርብ በመደረጉ ግራ ቀኙ የጽሑፍ ክርክር የተለዋወጡ ሲሆን እኛም የይ/ሰሚው ችሎት ውሣኔ እና የሰበር ችሎቱ ትዕዛዝ መሰረታዊ የሕግ ስህተት የተፈፀመበት መሆን አለመሆኑን መርምረናል።
በዚህም መሰረት አንድ ኑዛዜ ፈራሽ ነው በሚል ስለሚቀርብ መግለጫ እና ክስ እንዲሁም መግለጫው እና ክሱ ላቀርብ ስለሚገባበት የጊዜ ገደብ በፍ/ሕ/ቁ 973 እና 974 ተደንግጐ ይገኛል። ቁጥር 973 ድንጋጌ ተፈጻሚነት የሚኖረው ኑዛዜው ሲነበብ በነበሩ ወይም በተወከሉ ሰዎች ጉዳይ ሲሆን ቁጥር 974 ድንጋጌ ደግሞ በኑዛዜው ስነስርዓት ባልነበሩ ወይም ባልተወከሉ ሰዎች ጉዳይ ነው። የፍ/ሕ/ቁ 973 እና 974 ድንጋጌዎች አቤቱታ አቅራቢው ኑዛዜው ሲነበብ የነበረ ወይም የተወከለ የመሆን አለመሆኑን መስፈርት መሰረት በማድረግ ይርጋው መቆጠር የሚጀምርበትን ጊዜ እና ፍጹም የሆነ የይርጋ ጊዜ /974 ንዑስ ቁጥር 2/ በተለየ ሁኔታ ከመደንገጋቸው በስተቀር ሁለቱም ድንጋጌዎች ኑዛዜው ፈራሸ ነው የሚል ክስ የሚቀርብበትን ስርዓት የሚደነግጉ በመሆናቸዉ በመሰረቱ ተያይዥነት አላቸው። በተያዘው ጉዳይ የአሁኖቹ ተጠሪዎች ኑዛዜው ሲነበብ ያልነበሩ ወይም ያልተወከሉ መሆኑ አላከራከረም። እንዲህ ከሆነ ደግሞ ይ/ሰሚው ፍ/ቤት ቢያንስ ሁለቱንም ድንጋጌዎች አጣምሮ መጥቀስ ሲገባው በውሣኔው ውስጥ ቁጥር 973 ድንጋጌን ብቻ ነጥሎ መጥቀሱ ተገቢ ሆኖ አልተገኘም። ከዚህ አንጻር ይግባኝ ሰሚው ፍ/ቤት ለጉዳዩ አግባብነት የልለውን ቁጥር 973 ድንጋጌ በመጥቀስ የሰጠው ውሣኔ የተሳሳተ ነው በማለት አመልካቾች ያቀረቡት ክርክር ከድንጋጌው አጠቃቀስ አንጻር ብቻ ተገቢነት ያለው ቢሆንም የይግባኝ ሰሚው ፍ/ቤት ውሣኔ ተመርምሮ መሰረታዊ የሕግ ስህተት የተፈፀመበት መሆን አለመሆኑ አቋም የሚወሰድበት ከድንጋጌው አጠቃቀስ አንጻር ብቻ ሳይሆን በሙሉ ይዘቱና መንፈስ ነው።
ዋናውን ፍሬ ጉዳይ በተመለከተ ተጠሪዎቹ ኑዛዜውን ያውቁ የነበረ መሆኑን ይ/ሰሚው ፍ/ቤት አረጋግጦ እያለ እና አጣሪውም በኑዛዜው ከተመለከተው ውጪ የሚያቋቁመው የተለየ የንብረት ድልድል በማይኖርበት ሁኔታ ተጠሪዎቹ ስለንብረት ድልድሉ እንዲያውቁ መደረጉን አመልካቾች አላስረዱም ሲል ይ/ሰሚው ፍ/ቤት የሰጠው ውሣኔ የተሳሳተ ነው በማለት አመልካቾች በሰበር አቤቱታቸው ተከራክረዋል። በመሰረቱ ኑዛዜ መኖሩን ማወቅ እና የኑዛዜውን ሙሉ ይዘት ማወቅ የተለያዩ ጉዳዮች ናቸው። ተጠሪዎቹ የኑዛዜውን ቅጂ እንዲያገኙ ተደርጐአል የሚል ክርክር አመልካቾቹ በስር ፍ/ቤቶችም ሆነ በሰበር ደረጃ አላቀረቡም። አመልካቾቹ ያቀረቡት ማስረጃ የኑዛዜውን መኖር እንጂ በኑዛዜው የተደረገውን የንብረት ድልድል ተጠሪዎች እንዲያውቁት መደረጉን የሚያስረዳ አይደለም በማለት ማስረጃን የመመዘን ስልጣን የተሰጠው ይ/ሰሚው ፍ/ቤት በማስረጃ ምዘና ረገድ የሰጠውን ውሣኔ አግባብነት መመርመር ደግሞ በዚህ ሰበር ችሎት የስልጣን ወሰን ውስጥ የሚካተት አይደለም።
No specific laws extracted.
No topics extracted.
በመጨረሻም ተጠሪዎቹ በኑዛዜው የተደረገውን የሀብት ድልድል ያወቁት በ13/03/04 ዓ.ም መሆኑን በሰበር መልሳቸው ያመኑ በመሆኑ እና የመቃወም አቤቱታቸውን ያቀረቡት ግን 15 ቀናት ካለፋ በኋላ በ03/05/04 ዓ.ም በመሆኑ ክሱ በይርጋ ውድቅ መደረግ ነበረበት በማለት አመልካቾች በመ/መልሳቸው ተከራክረዋል። በመሰረቱ በፍ/ሕ/ቁ 973/1/ የተመለከተው የ15 ቀን የጊዜ ገደብ የክስ ማቅረቢያ ጊዜ ሳይሆን የመግለጫ ማቅረቢያ ጊዜ ነው። በኑዛዜው የተሰየሙ አጣሪ ናቸው የተባሉት የአሁኗ 3ኛ አመልካች ስለንብረት ድልድሉ ለአሁኖቹ ተጠሪዎች ያሳወቁት ነገር አለመኖሩን ይ/ሰሚው ፍ/ቤት አረጋግጦአል። ተጠሪዎቹ የንብረት ድልድሉን እንዲያውቁ አልተደረገም ከተባለ ደግሞ መግለጫ የማቅረብ ግድታ አይኖርባቸውም። የዚህ ዓይነቱ ግድታ ከልለባቸው ደግሞ ጊዜው መቆጠር የሚጀምረው ተጠሪዎቹ በኑዛዜው የተደረገውን የንብረት ድልድል ማወቃቸውን ከገለጹበት ከ13/03/04ዓ.ም ጀምሮ በመሆኑ በ03/05/04 ዓ.ም ለመጀመሪያ ደረጃ ፍ/ቤት ያቀረቡት የመቃወም አቤቱታ በፍ/ሕ/ቁ 973/3/ በተመለከተው አነስተኛው የሶስት ወር የይርጋ ዘመን እንኳ የይርጋ ጊዜው ያለፈበት ሆኖ አልተገኘም።
ሲጠቃለል አቤቱታ የቀረበበት የስር ፍ/ቤቶች ውሣኔ መሰረታዊ የሕግ ስህተት ተፈጽሞበታል ማለት ስላልተቻለ የሚከተለው ውሣኔ ተሰጥቶአል።
የአ/አበባ ከተማ ይ/ሰሚ ፍ/ቤት በመ/ በ17/09/04 ከሰጠው ውሣኔ ውስጥ ይርጋን የሚመለከተው የውሣኔው ክፍል እና የአ/አበባ ከተማ ፍ/ቤቶች ሰበር ችሎት በመ/ በ06/11/04 የሰጠው ትዕዛዝ በፍ/ስ/ስ/ሕ/ቁ 348/1/ መሰረት ፀንተዋል።
የሰበር ክርክሩን ወጪና ኪሣራ ግራ ቀኙ የየራሳቸውን ይቻሉ።
በአ/አበባ ከተማ የመ/ደ/ፍ/ቤት በመ/ቁ 1944/03/ የተያዘው ክርክር ታግዶ እንዲቆይ በዚህ መዝገብ ተሰጥቶ የነበረው ትዕዛዝ ተነስቶአል።
የውሣኔው ቅጂ ለስር ፍ/ቤቶች ይላክ።
ውሣኔ ያገኘ ስለሆነ መዝገቡ ተዘግቶአል።