No summary available.
የካቲት 25 ቀን2005 ዓ.ም.
ዳኞች፡- ተሻገር ገ/ስላሴ አልማው ወል ረታ ተሎሳ አዳነ ንጉሴ ሙስጠፋ አህመድ አመልካች፡- ወ/ሮ ውድነሽ እሸቱ ቀረቡ ተጠሪ፡- አቶ ፍቅረማሪያም ወርቁ ቀረቡ መዝገቡ ተመርምሮ የሚከተለው ፍርድ ተሰጥቷአል።
ጉዳዩ የውርስ ክርክር ሲሆን የተጀመረውም የአሁኑ ተጠሪ በሻሸመኔ ወረዳ ፍ/ቤት ባቀረበው ክስ ነው። የክሱም ይዘት ባጭሩ ሁለቱም ወላጆች በሞት መለየታቸውን እና በውርስ ንብረቱን ሁለቱ ተከሳሾች ይዘው እንደሚገኙ የሚገልጽ ሆኖ ክርክሩ ከቀረበው ንብረት ውስጥ ድርሻው የሆነውን አንድ ስድስተኛ እንደያስከፍሉ ዳኝነት የተጠየቀበት ነው። 2ኛ ተከሳሽ የነበረው ሰው ከዚህ አለም በሞት ተለይቷል በመባሉ ከክርክሩ ውጭ የተደረገ ሲሆን 1ኛ ተከሳሽ የነበረችው የአሁኗ አመልካች በበኩሐ ከሳሽ የውርስ ሀብት ናቸው ሲል ከዘረዘሯቸው መካከል ወፍጮ እና ወፍጮው የሚገኝበትን ቤት ሟች እናታችን በህይወት እያሉ በስጦታ አስተላልፈውልኝ የቤቱ ባለቤትነቱም ሆነ የወፍጮው ንግድ ፍቃድ በስሜ ተዛውሮ የሚገኝ በመሆኑ የውርሱ አካል አይደለም ቀሪዎቹን ንብረቶች በተመለከተ ግን እኔም ወራሽ ስለሆንኩኝ እንዲከፋፈለን ቢደረግ ተቃውሞ የለኝም በማለት መልስ ሰጥታለች። ፍ/ቤቱም ከቤቱ ማህደር ጋር ተያይዘዎል የተባሉትን ሰነዶች ከኩየራ ከተማ አስተዳደር አስቀርቦ ከተመለከተ በኃላ ሰነዶች በፍ.ስ.ቁ.2443 እና 881 መሰረት ስጦታ መደረጉን ማስረዳት የማይችሉ በመሆኑ የተከሳሽ ክርክር ተቀባይነት የለውም በማለት ከውርስ ንብረቶቹ ውስጥ አንድ ስድስተኛው ለከሳሽ ይሰጥ ሲል ውሳኔ የሰጠ ሲሆን የምዕራብ አሩሲ ዞን ከፍተኛ ፍ/ቤት በበኩሉ የይግባኝ ክርክሩን ከሰማ በኃላ ሟች በሂወት እያሉ ለስር 1ኛ ተከሳሽ በስጦታ አስተላልፈው በስሟ የተዛወረው የወፍጮ ቋት እና ቤቱ የውርስ ንብረቱ አካል ነው የተባለው አላግባብ ነው ሲል በዚህ ረገድ የተሰጠውን ውሳኔ ሽሮአል።
የስር ከሳሽ በዚህ ውሳኔ ቅር በመሰኘት በተራው ባቀረበው ይግባኝ መነሻ የኦሮሚያ ጠ/ፍ/ቤት ክርክሩን ከሰማ በኃላ የወረዳው ፍ/ቤት ለውሳኔው የተሰጠውን ምክንያት በመደገፍና በማጠናከር የከፍተኛውን ሽሮ የወረዳ ፍ/ቤትን ውሳኔ ያፀና ሲሆን የጠቅላይ ፍ/ቤት ሰበር ችሎት በበኩሉ የግራ ቀኙን ክርክር ከሰማ በኃላ ውርሱን የሚቀበለው የሟቹ ወደታች የሚቆጠር ተወላጅ የሆነ ሰው መመለስ የለብህም ተብሎ ከሟቹ ያገኘው ችሎታ ስለሆነ በስተቀር አስቀድሞ በስጦታ ወይም በኑዛዜ ተሰጥቶት የነበረውን ንብረት መልሶ ከውርሱ ንብረት ጋር መቀላቀል እንዳለበት በፍ.ሕ.ቁ.1065 እና 1067 (1) እና (2) ተደንግጐ የሚገኝ መሆኑን በተጨማሪ ምክንያትነት በመጥቀስ የይግባኝ ሰሚ ችሎቱን ውሳኔ አፅድቋል።
አመልካች ለዚህ ችሎት አቤቱታ ያቀረበችው ከከፍተኛ ፍ/ቤት ውሳኔ በስተቀር ቀሪው የስር ፍ/ቤቶች ውሳኔ መሰረታዊ የሕግ ስህተት የተፈፀመበት በመሆኑ ላታረም ይገባል በማለት ሲሆን በ 20-10-04 አዘጋጅታ ያቀረበችው አቤቱታ ተመርምሮ ሟች በሕይወት በነበሩበት ጊዜ ቀድሞውኑ በኑዛዜ ያስተላለፉት ስመ ሀብቱን ያዛወሩት እና በሞቱበት ጊዜ የራሳቸው ያልነበረው ንብረት የሟች የውርስ ንብረት አካል ነው ተብሎ ለወራሾች ይከፋፈል የመባሉን አግባብነት ለመመርመር ጉዳዩ ለሰበር ክርክር እንዲቀርብ በመደረጉ ግራ ቀኙ የጽሑፍ ክርክር ተለዋውጣዋል።
የጉዳዩ አመጣጥ እና የክርክሩ ይዘት ከላይ የተመለከተው ሲሆን እኛም አቤቱታ የቀረበበት የስር ፍ/ቤቶች ውሳኔ መሰረታዊ የሕግ ስህተት የተፈፀመበት መሆን አለመሆኑን መርምረናል።
በዚህም መሰረት አመልካች ከስር ጀምሮ በአንድ በኩል የወፍጮውን ቋት እና ወፍጮው የተቋቋመበትን ቤት ሟች በሕይወት እያሉ በስጦታ ያስተላለፈልኝና በስሜ ተዛውሮ የሚገኝ በመሆኑ የውርስ አካል ተደርገው ላወስድ አይገባም በማለት ስትከራከር መቆየቷ እና በልላ በኩል ደግሞ በስጦታ ተላልፎልኛል ከምትለው ንብረት ውጪ ያለውን ውርስ እንደ አንድ የመጀመሪያ ደረጃ ወራሽ ለመካፈል ዝግጅ ወይም ፍቃደኛ መሆኗ እንዲሁም በስጦታ ተላልፎልኛል የምትለውን ንብረት ወደ ውርሱ መልሶ ከማግባት በሟች ነፃ ተደርጌአለሁ በሚል ያቀረባቸው ክርክርና ማስረጃ አለመኖሩ በስር የመጀመሪያ ደረጃ እና ይግባኝ ሰሚ ፍ/ቤቶች በተደረገው ክርክር በፍሬ ነገር ደረጃ ተረጋግጠዋል። የኦሮሚያ ጠ/ፍ/ቤት ሰበር ችሎት እነዚህን የተረጋገጡ ፍሬ ነገሮች እና በክርክር ለተረጋገጠው ፍሬ ነገር አግባብነት ያላቸውን ድንጋጌዎች በመለየት አመልካች በስጦታ የተላለፈላትን ንብረት መልሳ በውርሱ ውስጥ ማግባት እንዳለባት የሰጠው ውሳኔ በመሰረቱ የሚነቀፍ አይደለም። ይሁን እንጅ ሰበር ችሎቱ የዚህ አይነቱ ንብረት ወደ ውርሱ መልሶ እንዲገባ የሚደረግበትን ስርዓት ጭምር በውሳኔው ውስጥ በግልጽ ሳያሰፍር የቀረው በአግባቡ መሆኑ አለመሆኑ ላጤን የሚገባው ሆኖ ተገኝቶአል በዚሁም መሰረት የጋራ ወራሾች ስለሚመለሱት ንብረት እና መመለሱ ስለሚፈፀምበት ስርዓት ተደንግጐ የሚገኝው በፍ/ሕጉ አንቀጽ 5 በምዕራፍ 3 በክፍል 2 ቁጥር 1065 እስከ 1078 ድረስ ሲሆን ከሟች በስጦታ ወይም በኑዛዜ የተሰጠውን ንብረት ወደ ውርስ መለሶ የማግባት ግድታ ያለበት ወደታች የሚቆጠር የሟች ተወላጅ ከውርሱ መልሶ ማግባት ያለበት ንብረቱን ራሱን ሳይሆን የንብረቱን ዋጋ መሆኑ በፍ/ሕ/ቁ.1065 እና 1074 (1) በግልጽ ተደንግጋል የንብረቱ የዋጋ ግምት የሚታወቅበት ስርዓትም በቁጥር 1077 ድንጋጌ ተመልክቷል። የክልሉ ጠ/ፍ/ቤት ሰበር ችሎት ንብረቱን መልሶ ወደ ውርስ በማግባት ስርዓት መፈፀም የሚገባው ከላይ የተመለከቱትን ድንጋጌዎች ተከትሎ መሆኑን በውሳኔው ላይ በግልጽ ማስፈር ሲገባው አላስፈለጊ የሆነ ተጨማሪ ሙግት በሚጋብዝ አኳኃን አመልካች በስጦታ የወሰደችውን ንብረት መልሳ ከውርስ ጋር መቀላቀል አለባት በማለት በደፈናው የሰጠው ውሳኔ መሰረታዊ የሕግ ስህተት የተፈፀመበት በመሆኑ ላታረም የሚገባው ሆኖ ተገኝቷል በመሆኑም የሚከተለው ውሳኔ ተሰጥቷል።
No topics extracted.
የሻሸመኔ ወረዳ ችሎት በመ.ቁ.29205 በ19/09/2003 ዓ.ም የኦሮሚያ ጠቅላይ ፍ/ቤት ይግባኝ ሰሚ ችሎት በመ.ቁ.119303 በ24/04/2004ዓ.ም እና የጠቅላይ ፍ/ቤት ሰበር ችሎት በመ.ቁ.135371 በ04/10/2004 ዓ.ም የሰጠው ውሳኔ በፍ.ስ.ስ.ሕ.ቁ.348 (1) መሰረት ተሻሽሐል።
አመልካች ወደ ውርሱ መልሳ ማስገባት ያለባት ንብረቱን እራሱን ሳይሆን የዋጋ ግምቱን ነው በማለት ወስነናል።
የንብረቱ ግምት ጉዳዩ ከላይ በተጠቀሰው የፍ.ሕ.ቁ.1077 መሰረት በሻሸመኔ ወረዳ ፍ/ቤት በመ.ቁ.36929 በተያዘው የአፈፃፀም ክርክር ታይቶ የሚወሰን ይሆናል በማለት ወስነናል።
የሰበር ክርክር ያስከተለውን ወጪና ኪሳራ ግራ ቀኙ የየራሳቸውን ይቻሉ ።
የአፈፃፀም ዕግድ ተነስቷል።
የውሳኔው ቅጂ ለስር ፍ/ቤቶች ይላክ።
ውሳኔ ያገኙ ስለሆነ መዝገቡ ተዘግቷል።