No summary available.
የሰ/መ/ ግንቦት 19 ቀን 2005 ዓ.ም.
ዳኞች፡- አልማው ወል ዓላ መሐመድ ረታ ቶሎሳ አዳነ ንጉሴ ሙስጠፋ አህመድ አመልካች፡- የኢትዩጵያ ንግድ ባንክ - ነ/ፈጅ አልሣቤጥ ጌታቸው ቀረቡ ተጠሪ፡- የኢትዩጵያ መድን ድርጅት - ነ/ፈጅ ሀሮን ካሣዬ ቀረቡ መዝገቡን መርምረን የሚከተለውን ፍርድ ሰጥተናል።
ጉዳዩ ለመድን አረቦን ኃላፊ መሆን የሚገባው ወገንን የሚመለከት ነው።ክርክሩ የተጀመረው የአሁኑ ተጠሪ በአሁኑ አመልካች ላይ በምዕራብ ጎጃም ዞን ከፍተኛ ፍርድ ቤት በመሰረተው ክስ መነሻ ነው።የተጠሪ ክስ ይዘትም አመልካች ደንበኛ ለሆነው አቶ መኮንን ጸጋው የሰ.ቁጥር 3-40259 ኢት የሆነ የጭነት መኪና አጠቃላይ የመድን ዋስትና ሽፋን ተጠሪ እንዲሰጥላቸው በውል እድሳት ማሳወቂያ ሰነድ ማዘዙን፣የኢንሹራንስ ውሉም ለአንድ አመት የሚቆይ መሆኑና ተጠሪ ውሉን አድሶ አመታዊ አርቦን ብር 12,154.75(አስራ ሁለት ሺህ አንድ መቶ ሃምሳ አራት ብር ከሰባ አምስት ሳንቲም) እንዲከፍል ጠይቆ አመልካች ደንበኛው ወይም ባንኩ ይከፍላችኋል የሚል ምላሽ ሰጥቶ ከቆየና የመኪናው ባለንብረትም ውሉ እንዲታደስ ጥያቄ አላቀረብኩም በማለታቸው ለባለንብረቱም ሆነ ለባንኩ ማስጠንቀቂያ በመስጠት ውሉን እንዲሰረዝ ማድረጉን በመጥቀስ አመልካች ውሉ እንዲታደስ ትዕዛዝ ከሰጠበት ጊዜ ጀምሮ ውሉ እስከተሰረዘበት ጊዜ ላለው ብር 6,079.88 እንዲከፍል ይወሰንለት ዘንድ ዳኝነት መጠየቁን የሚያሳይ ነው።አመልካች ለክሱ በሰጠው መልስም ከተጠሪ ጋር በሕጉ አግባብ የገባው ግድታ የልለ መሆኑን ጠቅሶ ክሱ ውድቅ ላሆን ይገባል በማለት ተከራክሯል።የስር ፍርድ ቤትም የግራ ቀኙን ክርክር መርምሮ የመድን ውሉ እንዲታደሰ አመልካች ጥያቄ ማቅረቡ ተረጋግጧል በሚል ምክንያት አመልካችን ከውል የመነጨ ግድታ አለብህ በማለት ለክሱ ኃላፊ ያደረገው ሲሆን የኃላፊነቱን መጠን በተመለከተም ውሉ ከተቋቋመበት ጊዜ ጀምሮ እስከተቋረጠበት ጊዜ ድረስ ነው በማለት ጊዜውን ሶስት ወር አድርጎ በመለየት ለዚሁ ጊዜ ብር 3,453.30(ሶስት ሺህ አራት መቶ ሃምሳ ሶስት ብር ከሰላሳ ሳንቲም)ነው በማለት ወስኗል።በዚህ ውሳኔ አመልካች ቅር በመሰኘት ይግባኙን ለክልሉ ጠቅላይ ፍርድ ቤት ያቀረበ ሲሆን ይግባኙ በፍ/ብ/ሥ/ሥ/ሕ/ቁጥር 337 መሰረት ተሰርዞበታል።የአሁኑ የሰበር አቤቱታ የቀረበውም ይህንኑ ውሳኔ በመቃወም ለማስለወጥ ነው።የአመልካች የሰበር አቤቱታ መሰረታዊ ይዘትም አመልካች የመድን ውሉ ተጠቃሚ እንጂ ገቢ ስለመሆኑ ባልተረጋገጠበትና የእድሳት ጥያቄውን አመልካች አቅርቧል ተብሎ ለአረቦን ክፍያው አመልካች ኃላፊ መደረጉ የን/ሕ/ቁጥር 657 እና 675 እንዲሁም አስገዳጅነት ያለውን የሰበር ሰሚ ችሎት ውሳኔ ያላገናዘበ ነው በማለት መከራከሩን የሚያሳይ ነው።
አቤቱታው ተመርምሮም በሰበር ችሎቱ እንዲታይ የተደረገ ሲሆን ተጠሪም ቀርቦ ግራ ቀኙ በፅሑፍ እንዲከራከሩ ተደርጓል።
የክርክሩ አመጣጥ አጠር ባለመልኩ ከላይ የተገለፀው ሲሆን ይህ ችሎትም የግራ ቀኙን ክርክር ለሰበር አቤቱታው መነሻ ከሆነው ውሳኔ እና አግባብነት ካላቸው ድንጋጌዎች ጋር በማገናዘብ ጉዳዩን በሚከለተው መልኩ መርምሮታል።እንደመረመረውም የችሎቱን ምላሽ የሚያስፈልገው አቢይ ነጥብ አመልካች ለመድን አረቦን ክፍያው ኃላፊ ተብሎ በተሰጠው ውሳኔ መሰረታዊ የሆነ የሕግ ስህተት ተፈጽሟል ለማለት ይቻላል? ወይስ አይቻልም? የሚለው ነው።
የክርክሩ መሰረታዊ ይዘት ተጠሪ በከሳሽነት ቀርቦ በአመልካች ላይ ባቀረበው ክስ ንብረትነቱ የአቶ መኮንን ፀጋው የሆነ የጭነት ተሽከርካሪ አመልካች በመያዣነት ይዞ የመድን ሽፋን የተገባለት መሆኑን በመግለፅ ለመኪናው የመድን ሽፋን እድሳት ጥያቄ በአመልካች በኩል ቀርቦ እድሳቱ ከተደረገ በኋላ ለአንድ አመት የመድን ሽፋን መከፈል የነበረበት የአረቦን ክፍያ በድምሩ ብር 12,154.75 የሚፈለግባቸው ስለሆነ አመልካች እንዲከፍል ውሣኔ ይሰጥልኝ በማለት ያቀረበው ክስ ነው።አመልካች ግድታ የለብኝም በማለት ተከራክሯል።እኛም ጉዳዩን መርምረናል።
በመሰረቱ አንድ ሰው ግድታው የሚመነጨው ከውል ወይም ከሕግ ነው። አመልካች ከተጠሪ ጋር በንግድ ህግ ቁጥር 657 ወይም በንግድ ህግ ቁጥር 675 ድንጋጌዎች መሰረት ያደረገው የመድን ውል ያለ መሆኑ አንደኛ ተጠሪ በሥር ፍርድ ቤት በፍሬ ነገር ደረጃ ከተረጋገጠው እና በሰበር ካደረገው ክርክር ለመረዳት ይቻላል።
አመልካች መያዣው አስተማማኝ ዋስትና እንዲኖረው በማሰብ አቶ መኮንን ፀጋው የተባለ ደንበኛው በመያዣነት በተያዘው መኪና ላይ ለሚደርስ ጉዳት የመድን ውል እንዲገቡ ሲያደርግ በመድን ውሉ ፖላሲው ላይ በተበዳሪውና በአመልካች ስም መፃፉን፣በተለይም መጀመሪያ የተደረገው የመድን ሸፋን ጊዜ ሲያበቃ አመልካች በራሱ ጠያቂነት ለተጠሪ ባቀረበው የእድሳት ጥያቄ ተጠሪ ጥያቄውን ተቀብሎ ውሉን በማድስ ለአንድ አመት እንዲቆይ ከአደረገ በኋላ የመድን አረቦን ክፍያውን ጥያቄ አመልካች ራሱ ወይም ደንበኛውም ለመክፈል የሚችል መሆኑን ለተጠሪ ሲገልፅለት ከቆየ በኃላ የመኪናው ባለንብረትም ሆነ አመልካች ክፍያውን ላፈጽሙ ያልቻሉ መሆኑን በፍሬ ነገር ደረጃ የዞኑ ከፍተኛ ፍርድ ቤት ያረጋገጠው ጉዳይ ሲሆን ይህንኑ የዞኑን ከፍተኛ ፍርድ ቤት ድምዳሜ ደግሞ ፍሬ ነገርን የማጣራትና ማስረጃን የመመዘን ስልጣን ያለው የክልሉ ጠቅላይ ፍርድ ቤት ይግባኝ ሰሚ ችሎት ሙሉ በሙሉ ተቀብሎታል።ይህ ችሎት እነዚህን ፍሬ ነገሮች ማጣራት ወይም ማስረጃውን መመዘን የሚችልበት አግባብ የልለ መሆኑን ከኢ.ፍ.ዲ.ሪ ሕገ መንግስት አንቀፅ 80(3(ሀ)) እና አዋጅ ቁጥር 25/1988 አንቀጽ 10 ድንጋጌዎች ይዘትና መንፈስ የምንገነዘበው ጉዳይ ነው።አመልካች የእድሳት ጥያቄውን ራሱ ማቅረቡና የክፍያ ጥያቄ ሲቀርብለትም ባንኩ ወይም ደንበኛው የሆኑት አቶ መኮንን ፀጋው እንደሚከፍሉ ለተጠሪ ሲገልጽለት የቆየ መሆኑ በፍሬ ነገር ደረጃ ከተረጋገጠ አመልካች ከውል የመነጨ አረቦን የመክፈል ኃላፊነት የለበትም የሚባልበት አግባብ የለም።አመልካች የሰበር መዝገብ በመጥቀስ በጉዳዩ ላይ አስገዳጅ የሕግ ትርጉም ተሰጥቶበታል በማለት የሚያቀርበው ክርክርም ለዚህ ጉዳይ አግባብነት ያለው ሁኖ አልተገኘም።ምክንያቱም በሰ/መ/ መያዣ ያዥ የሆነው ባንክ ለመድን አረቦን ክፍያ ኃላፊነት የለበትም ተብሎ የተወሰነው የእድሳት ጥያቄው ባንኩ አቅርቦ ካለመሆኑም በላይ መድን ገቢውም ከስር ጀምሮ እስከ ሰበር በተደረገው ክርክር ኃላፊነቱ የራሱ መሆኑን ገልፆ ተከራክሮ ነው።በዚህ በተያዘው ጉዳይ ግን የመኪናው ባለንብረት የሆነው ግለሰብም የክርክሩ ተሳታፊ ያልሆነ ከመሆኑም በላይ ተጠሪ ወደ ክሱ ያመራውም ግለሰቡን ማስንጠቀቂያ ሰጥቶ ግለሰቡ የእድሳት ጥያቄውን ባለቀረቡበት ሁኔታ የሚጠየቁበት አግባብ የለም በማለት ከገለፁለት በኋላ በመሆኑ በመዝገቡ ያሉት የክርክሩ መሰረታዊ ፍሬ ነገሮች በሰ/መ/ ካሉት የክርክሩ መሰረታዊ ፍሬ ነገሮች ጋር የሚገናኙ አይደሉም። የክርከሩ መሰረታዊ ነጥቦች የተለያዩ ከሆነ ደግሞ በአንድ ጉዳይ ላይ የተሰጠ የሕግ ትርጉም በልላ ጉዳይ ላይ ተፈፃሚነት እንዲኖረው የሚደረግበት አግባብ የልለ መሆኑን ከአስገዳጅ የህግ ትርጉም ፅንሰ ሐሳብና ከአዋጅ ቁጥር 454/1997 አንቀፅ 2(1) ድንጋጌ ይዘትና መንፈስ የምንገነዘበው ጉዳይ ነው።በመሆኑም ጉዳዩ በሰ/መ/ ከተሰጠው አስገዳጅ የሕግ ትርጉም አንጻር ታይቶ ዳኝነት ላሰጥበት የሚችል ባለመሆኑ እና አመልካች ከውል የመነጨ ግድታ ያለበት በመሆኑ በጉዳዩ ላይ በተሰጠው ውሳኔ መሰረታዊ የሆነ የሕግ ስህተት ተፈጽሟል ለማለት የሚቻል ሁኖ አልተገኘም።በዚህም ምክንያት ተከታዩን ወስነናል።
ው ሣ ኔ
በጉዳዩ ላይ የተሰጠው ውሳኔ በፍ/ብ/ሥ/ሥ/ሕ/ቁጥር 348(1) መሰረት ጸንቷል።
አመልካች ከተጠሪ ጋር በገባው የመድን ውል መሰረት ውሉ እስከተሰረዘበት ጊዜ ድረስ ያልከፈለውን የአረቦን ክፍያና ተያያዥ ወጪውን ለተጠሪ እንዲከፍል መወሰኑ ተገቢ ነው ብለናል።
በዚህ ችሎት ለተደረገው ክርክር የወጣውን ወጪና ኪሳራ የየራሳቸውን ይቻሉ ብለናል።
No topics extracted.