No summary available.
የካቲት 10 ቀን 2006 ዓ.ም.
ዳኞች፡- ተገኔ ጌታነህ አልማው ወል ዓላ መሐመድ አዳነ ንጉሴ ሙስጠፋ አህመድ አመልካች፡- አቶ ኃይሉ ድሬሳ - ከጠበቃ ጅሬኛ ለሜሳ ቀረቡ ተጠሪ፡- ወ/ሮ ሱፍ አለሙ - ቀረቡ መዝገቡ ተመርምሮ የሚከተለው ፍርድ ተሰጥቶአል።
ጉዳዩ የፍቺ ውሳኔን ተከትሎ ከሳሽ በነበሩት የአሁኑ አመልካች የቀረበ የንብረት ክፍፍል ጥያቄን አስመልክቶ የተደረገ ክርክርን የሚመለከት ሆኖ ልሎች ንብረቶችን በተመለከተ ጉዳዩ ተጣርቶ በስር ፍ/ቤቶች በውሳኔ የተቋጨ ሲሆን አከራካሪ ሆኖ የቀጠለው እና በዚህ መዝገብ ለተያዘው ክርክርም ምክንያት የሆነው በኦሮሚያ ክልል በምዕራብ ሸዋ ዞን በአምቦ ከተማ በቀበል 01 ውስጥ በአሁኑ አመልካች ስም በባለቤትነት ማረጋገጫ ሰነድ ቁጥር AM/691/89 ተመዝግቦ የሚታወቀው ቤት ነው።ይህንኑ ቤት በተመለከተ ክሱን በመጀመሪያ ደረጃ የተመለከተው የአምቦ ወረዳ ፍ/ቤት የግራ ቀኙን ክርክር እና ማስረጃ ከሰማ በኋላ ቤቱ ከጋብቻ በፊት የተፈራ የአሁኑ አመልካች የግል ንብረት ነው በማለት ውሳኔ የሰጠ ሲሆን በአሁኗ ተጠሪ ጠያቂነት ይግባኙን የተመለከተው የምዕራብ ሸዋ ዞን ከ/ፍ/ቤት በበኩሉ የግራ ቀኙን ክርክር ከሰማ በኃላ ሰርቪስ ቤቶቹ ከጋብቻ በፊት፣ዋናው ቤት ግን ከጋብቻ በኃላ የተሰሩ መሆኑ ከቀረበው ክርክር እና ማስረጃ መገንዘብ እንደተቻለ ገልጾ የስር ፍ/ቤት ውሳኔን በማሻሻል ዋናው ቤት በጋብቻው ጊዜ የተፈራ በመሆኑ ግራ ቀኙ እኩል ላካፈሉት ይገባል በማለት ውሳኔ ሰጥቶአል። የአሁኗ ተጠሪ ሰርቪስ ቤቶቹ የአመልካች የግል ንብረት ናቸው በመባሉ በዚህ የከ/ፍ/ቤት ውሳኔም ቅር ተሰኝተው ይግባኝ በማቅረባቸው እና የአሁኑ አመልካች ደግሞ ዋናው ቤት የጋራ ነው በመባሉ ቅር ተሰኝተው መስቀልኛ ይግባኝ በማቅረባቸው የክልሉ ጠ/ፍ/ቤት ይ/ሰሚ ችሎት ጉዳዩ እንደገና በተጨማሪ ማስረጃ እንዲጣራ ካደረገ በኃላ በጋራ የተፈሩ መሆናቸው እንደተረጋገጠ ገልጾ የከ/ፍ/ቤት ውሳኔን በማሻሻል ዋናውንም ሆነ ሰርቪስ ቤቶቹን ግራ ቀኙ እኩል እንዲካፈሉ ውሳኔ ሰጥቶአል።
ዋናውን እና ሰርቪስ ቤቶቹን አስመልክቶ በአሁኑ አመልካች ጠያቂነት ጉዳዩ በመጨረሻ የቀረበለት የክልሉ ጠ/ፍ/ቤት ሰበር ችሎት የሰበር አቤቱታውን መርምሮ ሰርቪስ ቤቶቹን በጋራ ያፈሩት ነው በማለት ግራ ቀኙ እንዲካፈሉ የመወሰኑን አግባብነት ለማጣራት ጉዳዩ ለክልሉ ሰበር ችሎት እንዲቀርብ ሶስት ዳኞች የተሰየሙበት አጣሪ ችሎት በመ.ቁ. 158167 በ21/06/2005 ትዕዛዝ የሰጠ ሲሆን አመልካች አቤቱታቸውን ለዚህ ሰበር ችሎት ያቀረቡትም የክልሉ ሰበር ችሎት ሰርቪስ ቤቶቹን ብቻ ነጥሎ ጉዳዩ ለሰበር ክርክር እንዲቀርብ ትዕዛዝ መስጠቱ ዋናውን ቤት በተመለከተ ለክልሉ ሰበር ችሎት የቀረበው አቤቱታ ተቀባይነት እንዳጣ የሚያስቆጥር ነው በማለት ነው።ለዚህ ሰበር ችሎት የቀረበው አቤቱታ ተመርምሮ ጉዳዩ ለሰበር ክርክር እንዲቀርብ በመደረጉ ግራ ቀኙ የጽሁፍ ክርክር ተለዋውጠዋል።የጉዳዩ አመጣጥ እና የክርክሩ ይዘት ከላይ የተመለከተው ሲሆን እኛም ወደ ፍሬ ጉዳይ ክርክሩ ከመገባቱ በፊት በዚህ መዝገብ የቀረበው አቤቱታ ለሰበር ብቁ የመሆን አለመሆኑ ጉዳይ በቅድሚያ እልባት ማግኘት የሚገባው መሆኑን በመገንዘብ ጉዳዩን ከዚሁ ጭብጥ አንፃር መርምረናል።
በዚህም መሰረት በቀጥታ ወደ ተያዘው ጭብጥ ከመገባቱ በፊት በዚህ መዝገብ የሰበር አቤቱታው ተመርምሮ ለክርክር እንዲቀርብ የተያዘው ጭብጥ ከአመልካች የሰበር አቤቱታ ይዘት እና የዳኝነት ጥያቄ ጋር የሚጣጣም መሆን አለመሆኑ በቅድሚያ መታየት የሚገባው ሆኖ ተገኝቶአል።ቀደም ሲል እንደተገለጸው ሰርቪስ ቤቶቹን በተመለከተ ጉዳዩ ለሰበር ችሎት ያስቀርባል ተብሎ በክልሉ ጠ/ፍ/ቤት ሰበር ችሎት በሂደት ላይ የሚገኝ በመሆኑ አመልካች ለዚህ ችሎት አቤቱታ ያቀረቡት ዋናውን ቤት በተመለከተ ስለመሆኑ በ19/09/2005 ዓ.ም. አዘጋጅተው ካቀረቡት የሰበር አቤቱታ አጠቃላይ ይዘት መገንዘብ ይቻላል።የሰበር አቤቱታው ተመርምሮ ጉዳዩ ለሰበር ክርክር መቅረብ የሚገባው መሆን አለመሆኑን በተመለከተ ተገቢው ትዕዛዝ ላሰጥበት ይገባው የነበረው ዋናውን ቤት በተመለከተ ብቻ ሆኖ እያለ ሰርቪስ ቤቶቹ የጋራ ናቸው ተብሎ የመወሰኑን አግባብነት ለማጣራት በሚል በዚህ መዝገብ ለክርክር ተይዞ የቀረበው ጭብጥ የአመልካቹን የሰበር አቤቱታ ይዘት መሰረት ያደረገ አለመሆኑን ተገንዝበናል።
ከላይ የተጠቀሰውን ዋነኛ ጭብጥ በተመለከተ ቀደም ሲል እንደተገለጸው ግራ ቀኙን እያከራከረ ያለው በአምቦ ከተማ በቀበል 01 ውስጥ በአሁኑ አመልካች ስም በባለቤትነት ማረጋገጫ ቁጥር AM/691/89 ተመዝግቦ የሚታወቀው ቤት ነው።አመልካች ለዚህ ችሎት አቤቱታ ያቀረቡት ዋናው ቤት የጋራ ነው መባሉን በመቃወም ሲሆን በልላ በኩል የዚሁ ቤት ሰርቪስ ክፍሎች ጉዳይ በክልሉ ሰበር ችሎት በክርክር ላይ ይገኛል።ጉዳዩ አምስት ዳኞች ለሚሰየሙበት የክልሉ ሰበር ችሎት የተላለፈው ሰርቪስ ቤቶቹን በተመለከተ ቢሆንም በሰበር ችሎቱ የሚሰጠው የመጨረሻ ውሳኔ አልታወቀም።አምስት ዳኞች የሚሰየሙበት የክልሉ ሰበር ችሎት ተገቢ ሆኖ ሲያገኘው በአጣሪው ችሎት በተያዘው ጭብጥ ሳይገደብ በልሎች ነጥቦች ላይም ጭምር ጭብጥ በመመስረት ክርክሩ እንዲሰማ አድርጎ ተገቢ ነው የሚለውን ውሳኔ መስጠት የሚችል በመሆኑ ሰርቪስ ቤቶቹን አስመልክቶ የቀረበውን የአቤቱታ ነጥብ ለማጣራት ጉዳዩ ለክልሉ ሰበር ችሎት እንዲቀርብ ሶስት ዳኞች የተሰየሙበት አጣሪ ችሎት በመ.ቁ. 158167 በ21/06/2005 ዓ.ም. የተሰጠው ትዕዛዝ ጊዜያዊ አገልግሎት ያለው ነው ከሚባል በቀር የመጨረሻ ነው ላባል የሚችል አይደለም።ትዕዛዙ ጊዜያዊ አገልግሎት ያለው ነው ከተባለ ደግሞ አመልካች ዋናውን ቤት በተመለከተ አቤቱታቸውን ለዚህ ሰበር ችሎት ማቅረብ የሚገባቸው በፍ.ሥ.ሥ.ሕ.ቁ. 320(3) ድንጋጌ መሰረት በክልሉ ሰበር ችሎት የተያዘው ክርክር የመጨረሻ ውሳኔ ካገኘ በኃላ ነው።በመሆኑም ሰርቪስ ቤቶቹን የሚመለከተው የክርክሩ ክፍል በሂደት ላይ ባለበት እና የመጨረሻ ውሳኔ ባላገኘበት ሁኔታ ዋናውን ቤት አስመልክቶ አመልካች በዚህ መዝገብ ያቀረቡት የሰበር አቤቱታ በአሁኑ የክርክር ደረጃ ላስተናገድ የሚችል ሆኖ ባለመገኘቱ የሚከተለው ውሳኔ ተሰጥቶአል።
No topics extracted.
158167 በ21/06/2005 ዓ.ም. በተሰጠው ትዕዛዝ ላይ አመልካች በዚህ መዝገብ ያቀረቡት አቤቱታ ለሰበር ብቁ አይደለም በማለት ወስነናል።
አመልካች በክልሉ ሰበር ችሎት በመ.ቁ.158167 የተያዘው ክርክር የመጨረሻ ውሳኔ ካገኘ በኃላ ለዚህ የሰበር ክርክር ምክንያት የሆነውን ዋናውን ቤት አስመልክቶ ለዚህ ችሎት የሰበር አቤቱታ ከማቅረብ ይህ ውሳኔ የሚያግዳቸው አይሆንም በማለት ወስነናል።
ውሳኔ ያገኘ ስለሆነ መዝገቡ ተዘግቶአል።