No summary available.
የካቲት 11 ቀን 2006 ዓ.ም.
ዳኞች፡- አልማው ወል ዓላ መሐመድ ረታ ቶሎሳ አዳነ ንጉሴ ሙስጠፋ አህመድ አመልካች፡- ወ/ሮ ብጥር ታገለ - የቀረበ የለም ተጠሪ፡- ወ/ሮ አገር ተሰማ - የቀረበ የለም መዝገቡ ተመርምሮ የሚከተለው ፍርድ ተሰጥቶአል።
በዚህ መዝገብ አመልካች አቤቱታ ያቀረቡት የዳግም ዳኝነት ጥያቄ ማስረጃ መመዘንን የሚያስከትል በመሆኑ እና ሰበር ችሎቶች የማስረጃ ምዘና ተግባር የሚያስከትሉ ጥያቄዎችን የማስተናገድ ስልጣን የልላቸው ስለመሆኑ ቀደም ሲል ውሳኔ የተሰጠ በመሆኑ አመልካች ለሰበር ችሎቱ ያቀረቡት የዳግም ዳኝነት አቤቱታ ተቀባይነት የለውም ሲል የአማራ ብ/ክ/መ/ጠ/ፍ/ቤት ሰበር ችሎት የሰጠው ብይን መሰረታዊ የሕግ ስህተት የተፈጸመበት በመሆኑ ላታረም ይገባል በማለት ነው።
የጉዳዩን አመጣጥ በተመለከተ ከሟች ወ/ሮ አብንደጅ አምባው የተላለፈልኝን የእርሻ ይዞታ አላግባብ ይዘውብኛል በማለት የአሁኗ አመልካች የሰበር ክርክሩ ተካፋይ ባልሆኑት በእነ አቶ የሻምበል ተሰማ ላይ በሜጫ ወረዳ ፍ/ቤት ክስ መመስረታቸውን፣ ተከሳሾቹም ቀርበው መሬቱን ይዘው የሚገኙት ስለ አሁኗ ተጠሪ መሆኑን በመግለጻቸው ተጠሪ በጉዳዩ በጣ/ገብነት መከራከራቸውን፣ፍ/ቤቱም የግራ ቀኙን ምስክሮች ቃል እና በሟች የቤተሰብ አባልነት የተመዘገቡት ከሳሽ ስለመሆናቸው ከሚመለከተው አካል ተጣርቶ የተላከለትን ማስረጃ መሰረት በማድረግ እና ጣ/ገብ በማስረጃነት ያቀረቡት በቀበልው ማህበራዊ ፍ/ቤት በ15/09/1995 ዓ.ም. የተሰጠው ውሳኔ በጉዳዩ ተከራካሪ ወገን ባልነበሩት የአሁኗ ከሳሽ ላይ በማስረጃነት ላቀርብ የሚችል ባለመሆኑ ምክንያት ተቀባይነት የልለው መሆኑን በመግለጽ ክርክር ያስነሳውን የእርሻ ይዞታ ጣ/ገብ ለከሳሽ ለቀው እንዲያስረክቡ በ19/08/2002 ዓ.ም.
ውሳኔ መስጠቱን፣ይ/ሰሚው ፍ/ቤትም ጣ/ገቧ ያቀረቡለትን ይግባኝ በ26/08/2002 ዓ.ም. ዘግቶ ማሰናበቱን እና በጣ/ገብ ጠያቂነት ጉዳዩን በመጨረሻ የተመለከተው የክልሉ ጠ/ፍ/ቤት ሰበር ችሎት በበኩሉ የግራ ቀኙን ክርክር ከሰማ በኃላ ጣ/ገብ መሬቱን የያዙት ከሳሽ ተከራካሪ ወገን በነበሩበት በማህበራዊ ፍ/ቤት በ15/09/1995 ዓ.ም.
በተሰጠው ውሳኔ መሰረት መሆኑ ተረጋግጦ እያለ አስቀድሞ በፍርድ ባለቀ ጉዳይ ጣ/ገብ መሬቱን ለከሳሽ እንዲለቁ የተሰጠው ውሳኔ ተቀባይነት የለውም በማለት የስር ፍ/ቤቶችን ውሳኔ ሽሮ ጣ/ገብ መሬቱን ለከሳሽ ለመልቀቅ አይገደዱም በማለት በ15/02/2004 ዓ.ም. ውሳኔ መስጠቱን፣በዚህ ውሳኔ ላይ አመልካች አቅርበውት የነበረው የሰበር አቤቱታ በፍ/ጠ/ፍ/ቤት ሰበር አጣሪ ችሎት በመ.ቁ.75679 በ27/04/2004 ዓ.ም. መዘጋቱን፣ አመልካች ይህ በ15/02/2004 ዓ.ም. የተሰጠው ውሳኔ እንዲሰረዝላቸው በፍ.ስ.ስ.ህ.ቁ. 6 ድንጋጌ መሰረት የዳግም ዳኝነት ይታይልኝ አቤቱታ ለክልሉ ሰበር ችሎት ያቀረቡትም ሰበር ችሎቱ የስር ፍ/ቤቶችን ውሳኔ ለመሻር መሰረት አድርጎት የነበረው በ15/09/1995 ዓ.ም. በማህበራዊ ፍ/ቤት የተሰጠ ነው የተባለው ውሳኔ ሀሰተኛ መሆኑ በፎረንሲክ ምርመራ ተረጋጦአል መባሉን መሰረት በማድረግ መሆኑን እና ቀደም ሲል በመግቢያው እንደተገለጸው የክልሉ ሰበር ችሎት ይህንን የአመልካች ጥያቄ ባለመቀበል በ17/11/2005 ዓ.ም. በዋለው ችሎት አቤቱታ የቀረበበትን ብይን የሰጠው አቤቱታው ማስረጃ የመመዘን ተግባርን የሚያስከትል በመሆኑ በሰበር ላታይ አይችልም በማለት መሆኑን የመዝገቡ ግልባጭ ያመለክታል።
አመልካች ለዚህ ችሎት ያቀረቡት የሰበር አቤቱታ ተመርምሮ በዚህ ጉዳይ የክልሉ ሰበር ችሎት ክርክር የተነሳበት መሬት በ1995 ዓ.ም. ለተጠሪ የተወሰነ ነው በማለት ቀደም ሲል ለሰጠው ውሳኔ መሰረት አድርጎት ለነበረው የማህበራዊ ፍ/ቤት ውሳኔ መሰረት የሆነው ማስረጃ ሀሰተኛ መሆኑ በፎረንሲክ ምርመራ ስለተረጋገጠ ዳኝነቱ በድጋሚ ይታይልኝ በማለት አመልካች በፍ.ስ.ስ.ሕ.ቁ. 6 ድንጋጌ መሰረት ያቀረቡት ጥያቄ ማስረጃን በሰበር ችሎት የመመዘን ዕድል ይፈጥራል በማለት ጥያቄውን ውድቅ የማድረጉን አግባብነት ተጠሪ ባሉበት ለማጣራት ይቻል ዘንድ ጉዳዩ ለሰበር ክርክር እንዲቀርብ ተደርጎ ግራ ቀኙ የጽሁፍ ክርክር ተለዋውጠዋል።የጉዳዩ አመጣጥ እና የክርክሩ ይዘት ከላይ የተመለከተው ሲሆን እኛም አቤቱታ የቀረበበት ብይን መሰረታዊ የህግ ስህተት የተፈጸመበት መሆን አለመሆኑን መርምረናል።
በዚህም መሰረት ቀደም ሲል በግራ ቀኙ መካከል በነበረው የእርሻ መሬት የይዞታ ክርክር ሁለቱ የስር ፍ/ቤቶች ውሳኔ የሰጡት ለአሁኗ አመልካች ጥቅም ሲሆን የሁለቱን የስር ፍ/ቤቶች ውሳኔ እና ትዕዛዝ በመሻር ጉዳዩን ለአሁኗ ተጠሪ ጥቅም የወሰነው የክልሉ ሰበር ችሎት ነው።የክልሉ ሰበር ችሎት ለውሳኔው መሰረት ያደረገውም ከሳሽ ተካፋይ ባልሆኑበት ክርክር የተሰጠ ነው በማለት የስር ፍ/ቤቶች ውድቅ ያደረጉትን 15/09/1995 ዓ.ም.
No topics extracted.
በማህበራዊ ፍ/ቤት የተሰጠ ነው የተባለውን ውሳኔ ነው።በመሰረቱ ማንኛውም ውሳኔ የተሰጠበት ሰው በፍ.ስ.ስ.ሕ.ቁ. 6(1)(ሀ) እና (ለ) ስር የተመለከቱትን ሁኔታዎች ወይም ከእነዚህ አንዱን መሰረት በማድረግ የዳግም ዳኝነት አቤቱታውን ማቅረብ የሚችለው ፍርዱን ለፈረደው ወይም ትዕዛዙን ወይም ውሳኔውን ለሰጠው ፍ/ቤት ስለመሆኑ በፍ.ስ.ስ.ሕ.ቁ. 6(1) ስር በግልጽ ተመልክቶአል።አመልካቿን ተረቺ የሚያደርግ ውሳኔ የሰጠው የክልሉ ሰበር ችሎት እስከሆነ ድረስ የዳግም ዳኝነት ጥያቄው በቀጥታ ለሰበር ችሎቱ መቅረቡ ከድንጋጌው አነጋገር አንጻር ሲታይ ተገቢነት የለውም ላባል የሚችል አይደለም።የዳግም ዳኝነት ጥያቄን የሚያስተናግድ ፍ/ቤት ደግሞ ለጉዳዩ አግባብነት ያላቸውን ፍሬ ነገሮች የማጣራት እና የግራ ቀኙን ማስረጃ የመመዘን ተግባራትን ማከናወን የሚጠበቅበት መሆኑን ከድንጋጌው ይዘት ግልጽ መገንዘብ ይቻላል።በልላ በኩል በክልሎችም ሆነ በፍድራል ፍ/ቤቶች ውስጥ የሰበር ስርዓት የተዘረጋበት ዓይነተኛ ዓላማ አንድ ወጥ የሕግ አተረጓጎም ስርዓትን ለማስፈን ይቻል ዘንድ በመጨረሻ ውሳኔዎች ላይ የተፈጸመ መሰረታዊ የሕግ ስህተትን ማረም ስለመሆኑ በኢ.ፍ.ዲ.ሪ.ሕገ መንግስት በአንቀጽ 80(3)(ሀ) እና(ለ)፣በብ/ክ/መንግስታት ሕገ መንግስቶች እንዲሁም በፍድራልና በክልሎች ዝርዝር ሕጎች በግልጽ ተመልክቶአል።ይህም አግባብነት ባላቸው የስረነገር እና የስነ ስርዓት ሕጎች መሰረት ፍሬ ነገርን የማጣራት እና ማስረጃን የመመዘን ስልጣን የተሰጠው ለመጀመሪያ ደረጃ እና ለይ/ሰሚ ፍ/ቤቶች መሆኑን እና በዚህ ረገድ ለሰበር ችሎቶች የተሰጠ ስልጣን አለመኖሩን መገንዘብ የሚያስችል ነው። በመሆኑም በዚህ መዝገብ ለተያዘው የክርክር ጭብጥ ተገቢውን ውሳኔ መስጠት ይቻል ዘንድ የፍ.ስ.ስ.ሕ.ቁ. 6 ድንጋጌን ዓላማ እና ይዘት የሰበር ችሎቶችን የስልጣን ወሰን ከሚመለከቱ ድንጋጌዎች ጋር አገናዝቦ ማየቱ ተገቢ ነው።
እንደሚታወቀው የሰበር ክርክር የሚመራበት የተዘረጋ የተለየ ስነ ስርዓት ባለመኖሩ አጠቃላይ የስነ ስርዓት ሕጉ ድንጋጌዎች በሰበር ክርክር ጉዳይም እንደየአግባብነታቸው ተፈፃሚነት ይኖራቸዋል።በመሰረቱ የፍ.ስ.ስ.ሕ.ቁ. 6 ዓይነተኛ ዓላማ ተገቢ ሁኔታዎችና ፍሬ ነገሮች ተሟልተው መገኘታቸው ሲረጋገጥ በሀሰተኛ ማስረጃ፣ በመደለያና በመሰል ወንጀል ጠቀስ ድርጊቶች ምክንያት የተዛነፈውን ፍትሕ ወደነበረበት መመለስ ነው።ይህ ሂደት ከሰበር ችሎቶች የስልጣን ወሰን ውጪ የሆነው ፍሬ ነገርን የማጣራት እና ማስረጃን የመመዘን ተግባራት የሚከናወንበት በመሆኑ ምክንያት በሰበር ችሎት ላስተናገድ የሚችልበት የህግ አግባብ ባለመኖሩ የተጠቀሰውን የስነ ስርዓት ድንጋጌ ዓላማ ለማሳካት ይቻል ዘንድ የሚኖረው አማራጭ የዳግም ዳኝነት አቤቱታው ፍሬ ነገር የማጣራት እና ማስረጃ የመመዘን ተግባራትን የማከናወን ስልጣን ባላቸው የስር ፍ/ቤቶች እንዲስተናገድ ማድረግ ይሆናል። በዚህ ሁኔታ ጉዳዩ የሚመራለት የስር ፍ/ቤትም የዳግም ዳኝነት ጥያቄው የቀረበበትን ውሳኔ የሰጠው በፍ/ቤቶች የስልጣን ተዋረድ መሰረት የበላይ የሆነው ሰበር ችሎት የመሆኑን ጉዳይ ከግምት ሳያስገባ ፍሬ ነገር የማጣራት እና ማስረጃ የመመዘን ተግባራትን አከናውኖ ተገቢ ነው ያለውን ውሳኔ በመስጠት ረገድ በስነ ስርዓት ድንጋጌው መሰረት ሙሉ ስልጣን ይኖረዋል። የተከራካሪ ወገኖች የይግባኝ መብት እንዳይጣበብ ለማድረግ ያስችል ዘንድም ጉዳዩ ለወረዳው ፍ/ቤት እንዲመራ መደረጉ የተሻለ መሆኑን ተገንዝበናል።
ሲጠቃለል የክልሉ ሰበር ችሎት የዳግም ዳኝነት ጥያቄውን እራሱ ማስተናገድ እንደማይችል የያዘው አቋም ተገቢ ቢሆንም ጉዳዩ ፍሬ ነገር የማጣራት እና ማስረጃ የመመዘን ተግባራትን የማከናወን ስልጣን ባላቸው የስር ፍ/ቤቶች እንዲታይ መምራት ሲገባው የአመልካች የዳግም ዳኝነት አቤቱታ ተንጠልጥሎ እንዲቀር ማድረጉ ተገቢ ሆኖ ስላልተገኘ የሚከተለው ውሳኔ ተሰጥቶአል።
የአማራ ብ/ክ/መንግስት ጠ/ፍ/ቤት ሰበር ችሎት በመ.ቁ. 09404 በ17/11/2005 ዓ.ም. የሰጠው ብይን በፍ.ስ.ስ.ሕ.ቁ. 348(1) መሰረት ተሻሽሎአል።
ከላይ በተ.ቁ.1 ከተጠቀሰው ብይን ውስጥ የዳግም ዳኝነት አቤቱታ ፍሬ ነገርን የማጣራት እና ማስረጃን የመመዘን ተግባራት የሚከናወንበት በመሆኑ ምክንያት በሰበር ችሎት ላስተናገድ የሚችል አይደለም በሚል የተሰጠው የብይኑ ክፍል በፍ.ስ.ስ.ሕ.ቁ. 348(1) መሰረት ፀንቶአል።
ከላይ በተ.ቁ.1 ከተጠቀሰው ብይን ውስጥ አቤቱታው በሰበር ችሎት ላስተናገድ የሚችል ስላልሆነ ተቀባይነት የለውም በሚል የዳግም ዳኝነት አቤቱታው በእንጥልጥል እንዲቀር በማድረግ የተሰጠው የብይኑ ክፍል በፍ.ስ.ስ.ሕ.ቁ. 348(1) መሰረት ተሽሮአል።
በአመልካቿ የቀረበውን የዳግም ዳኝነት አቤቱታ ተቀብሎ በማስተናገድ በፍ.ስ.ስ.ሕ.ቁ. 6 ድንጋጌ መሰረት ተገቢውን ውሳኔ ይሰጥበት ዘንድ ጉዳዩ በፍ.ስ.ስ.ሕ.ቁ. 341(1) መሰረት ለሜጫ ወረዳ ፍ/ቤት እንዲላክ ወስነናል።
በዚህ ውሳኔ መሰረት መፈጸም ያስችለው ዘንድ የዚህ ውሳኔ ግልባጭ ለሜጫ ወረዳ ፍ/ቤት ይላክ።
እንዲያውቀው የዚህ ውሳኔ ግልባጭ ለክልሉ ሰበር ችሎትም ይላክ።
የሰበር ክርክሩ ያስከተለውን ወጪና ኪሳራ ግራ ቀኙ የየራሳቸውን ይቻሉ።
ውሳኔ ያገኘ ስለሆነ መዝገቡ ተዘግቶአል።