No summary available.
መስከረም 21 ቀን 2006 ዓ.ም.
ዳኞች፡- ተገኔ ጌታነህ ተሻገር ገ/ስላሴ አልማው ወል ረታ ቶሎሳ ሙስጠፋ አህመድ አመልካች፡- በኮልፍ ቀራኒዮ ክ/ከተማ የመሬት ልማት አስተዳደር ጽ/ቤት - ነ/ፈጅ አቶ ግርማ አበራ ቀረቡ ተጠሪዎች፡- 1ኛ ፀዳለ ካሣ 2ኛ/ ገነት ካሣ ሁለቱም ቀርበዋል 3ኛ/ ጌጤ ካሣ - ከጠበቃ አቶ ከፈለኝ ካሣ ቀረቡ መዝገቡ የተቀጠረው ለምርመራ ሲሆን፣ መርምረን የሚከተለውን ፍርድ ሰጥተናል።
ይህ የሰበር ጉዳይ በፍ/ብ/ሥ/ሥ/ሕ/ቁ 358 የተመለከተው ድንጋጌ በግራ ቀኙ መካከል ለተነሳው ክርክር ያለውን አፈፃፀም የሚመለከት ነው።
የጉዳዩ መነሻ የሆነው የአሁን ተጠሪዎች በመካከላቸው የተነሳው የውርስ ክርክር ጉዳይ በመጀመሪያ ደረጃ ፍ/ቤት እየታየ እያለ፤ ጉዳያቸውን በእርቅ/ በስምምነት የጨረሱ መሆኑን በመግለፅ በደረሱበት የእርቅ ስምምነት መሰረት ጉዳዩ እንዲቋጭ ጠይቀዋል። ፍ/ቤቱም ሰኔ 29 ቀን 1993 ዓ/ም በዋለው ችሎት ጉዳዩን በመ/ቁ 27/93 ተመልክቶ የእርቅ ስምምነቱን በማጽደቅ በስምምነቱ መሰረት ጉዳዩ የተቋጨ መሆኑን ሚገልጽ ዳኝነት ሰጥቷል።
በዚህ አኳኋን በተሰጠው ውሳኔ መሰረት እንዲፈጸምላቸው የአሁን ተጠሪዎች በአፈፃ/መ/ እንደጠየቁ የአሁን አመልካች በእርቅ ስምምነቱ እንዲከፋፈሉ የተስማሙበት ንብረት የይዞታ ማረጋገጫ የልለው መሆኑን ይህንኑ ዓይነት ንብረት በስምምነት እንድንከፋፈል ተስማምተናል በማለታቸው ምክንያት የእርሱን መብትና ጥቅም የነካ ውሳኔ ላሰጥ የቻለበትን ዝርዝር የፍሬ ነገር አግባብነት ካለው ህግ ጋር በማጣቀስ አቤቱታውን ዋናውን ውሳኔ ለሰጠው ፍ/ቤት አቅርቧል።
ፍ/ቤቱም ቀደም ሲል በውሳኔ የዘጋውን የመ/ቁ 27/93 የሆነውን መዝገብ ካንቀሳቀሰ እና የአሁን አመልካች ባቀረበው አቤቱታ መነሻ የግራ ቀኙን ክርክር ካዳመጠ በኋላ ቀደም ሲል ውሳኔ የሰጠው ግራ ቀኙ ያደረጉትን ስምምነት ተቀብሎ በማጽደቁ ምክንያት ነው። በዚህ መሰረት በተከራከሪ ወገኖች የእርቅ ስምምነት መሰረት የተሰጠው ውሳኔ በሶስተኛ ወገን ላይ ውጤት እንደማያስከትል በፍ/ብ/ሕ/ቁ 3311 ተደንግጓል። ስለሆነም ይህ በእርቅ ስምምነት መሰረት የተሰጠው ውሳኔ በአመልካች ላይ ውጤት ላያስከትል የሚችል ባለመሆኑ ጥያቄው ተቀባይነት የለውም የሚል ዳኝነት በመስጠቱና ይህም ዳኝነት በበላይ ፍ/ቤቱ በመፅደቁ የተነሳ ይህ የሰበር ጉዳይ ላቀርብ እንደቻለ ከጉዳዩ አመጣጥ ተገንዝበናል።
እኛም በዚህ አኳኋን በተሰጠው ዳኝነት ላይ ግራ ቀኙ በዚህ ሰበር ደረጃ ያቀረቡትን የጽሁፍ ክርክር ለጉዳዩ አግባብነት ካላቸው ድንጋጌዎች ጋር በማገናዘብ ተመልክተናል።
እንደተመለከትነውም በፍ/ብ/ሕ/ቁ 3311 ድንጋጌ ሁለት እና ከዚያ በላይ የሆኑ ወገኖች በሙግት ምክንያት ላሆን የሚችለውን ጉዳይ ወይም ደግሞ ያከራከራቸውን ጉዳይ በእርቅ በጨረሱ ጊዜ ይህ የእርቅ ስምምነት በሶስተኛ ወገን ላይ ውጤት አያስከትልም በሚል የተመለከተው የድንጋጌ ይዘት ግብና ዓላማ የእርቅ ስምምነቱ ግቡ ታራቂዎች በየግላቸው ያላቸውን መብትና ግድታ እንደሁኔታው በማስተካከል ለክርክር መንስኤ ላሆን የሚችለውን ወይም የሆነን ጉዳይ በስምምነት ማስቀረት እንደመሆኑ መጠን በዚህ የእርቅ ስምምነት ላይ ቀሪ የሆነን መብት እና ግድታን ወይም የተፈጠረን መብትና ግድታን ላመለከት የሚችለውና ተፈጻሚነቱ በእነዚያው በታራቂ ወገኖች ላይ ብቻ ተገድቦ የሚቀር፤ የልላ ሰውን መብትና ግድታ ሁሉ በማካተት የእነዚህ ሶስተኛ ወገኖች መብትና ግድታ አብሮ በእርቅ እንዳለቀ ላቆጠር እንደማይችል የእርቅ ስምምነቱ አንፃራዊ ውጤቱ በተስማሚ ወገኖች ላይ ብቻ የተገደበ መሆኑን የሚያመለክት እንደመሆኑ መጠን ይህ ክርክር የተነሳበት የእርቅ ስምምነት ጉዳይ የማንም ሦስተኛ ወገን መብትና ግድታን ሳይነካ በእራሱ ችሎ ላፈፅም የሚችል የመሆኑ ጉዳይ ላረጋገጥ ይገባል አሁን በተያዘው ጉዳይ ግን የእርቅ ስምምነት እንደ ታራቂዎች ሀሳብ በስምምነቱ ላይ የተገለፀው መብትና ግድታ ተፈፃሚነቱ በተስማሚዎች መብትና ግድታ ላይ ብቻ ተወስኖ ላቀር ያልቻለ መሆኑን የማያመለክት የፍሬ ነገርና የህግ ክርክር የአሁን አመልካች አቅርቧል። የአሁን አመልካች ይህንኑ ከመጥቀሱም በላይ እንደፍርዱ እንዲፈፀምላቸው በፍርድ ኃይል ዕገዛ የአሁን አመልካች ግድታውን እንዲፈጽም የአፈፃጸም ክስ ማቅረባቸውም ይህንኑ የሚያረጋግጥ ነው። በመሆኑም ጉዳዩ በፍ/ብ/ሕ/ቁ 3311 ከተመለከተው አንፃር ይታይ እንኳ ቢባል ተጠሪዎች የደረሱበት ስምምነት ወይም እርቅ ከእራሳቸው መብትና ግድታ አልፎ 3ኛ ወገን የአሁን አመልካችን መብትና ጥቅም የነካ ስለመሆኑ አመልካች ክርክር ያቀረበ መሆኑ እስከተረጋገጠ ድረስ የእርቅ ስምምነቱ የሚያስከትለው ህጋዊ ውጤት በታራቂዎች ላይ ብቻ ተወስኖ እንዳልቀረ እየታወቀ የሥር ፍ/ቤቱ ለድንጋጌው የሰጠው ትርጉም መሰረታዊ የሆነ የህግ ስህተት የተፈፀመበት ሆኖ ተገኝቷል።
No topics extracted.
የአሁን አመልካች ተጠሪዎች እርስ በእርሳቸው ያደረጉት የእርቅ ስምምነት እና በፍ/ቤት የፀደቀው ውሳኔ እና የስምምነቱ አካል ሳልሆን ክርክሬ ሳይሰማ መብትና ጥቅሜን ያስቀረ እኔን የጎዳ ውሳኔ ላሰጥ በመቻሉ መብትና ጥቅሜን በክርክር ማስከበር እንድችል የክርክር ተካፋይ ልሁን በማለት ያቀረበው ጥያቄ በፍ/ብ/ሥ/ሥ/ሕ/ቁ 358 አፈፃፀም ማሟያ የሚሆኑትን የፍሬ ነገር ጉዳዮች አግባብነት ካላቸው ህጎች ጋር በማጣቀስ የተደገፈ መሆኑ እስኪታወቅ እና ለዚህም ማስተባበያ እስካልቀረበበት ጊዜ ድረስ አመልካች በጉዳዩ ላይ የክርክር ተካፋይ ላሆን ሲገባ እንዲሁም የአሁን አመልካች በፍ/ብ/ሥ/ሥ/ሕ/ቁ 358 የተመለከተውን ድንጋጌ በመጥቀስ ያቀረበው አቤቱታ በፍ/ሕ/ቁ 3311 ከተመለከተው ድንጋጌ አፈፃፀም ጋር ተደጋጋፊ በመሆኑ የስር ፍ/ቤቶች ከእነዚህ ድንጋጌዎች ትክክለኛ አፈፃፀም እና ትርጉም በመራቅ የአሁን አመልካችን አቤቱታ ውድቅ በማድረግ የሰጡት ዳኝነት መሰረታዊ የሆነ የህግ ስህተት የተፈፀመበት ሆኖ በማግኘታችን የሚከተለውን ውሳኔ ሰጥተናል።
የፍድራል የመጀመሪያ ደረጃ ፍ/ቤት እና ይግባኝ ሰሚው ፍ/ቤት እንደቅደም ተከተሉ በጉዳዩ ላይ በመ/ቁ 27/93 ነሐሴ 29 ቀን 2004 ዓ/ም እና በኮ/መ/ ታህሳስ 02 ቀን 2005 ዓ/ም በትዕዛዝ አማካኝነት የሰጡት ዳኝነት ሁሉ ተሽሯል።
የፍድራል የመጀመሪያ ደረጃ ፍ/ቤት በመ/ቁ 27/93 ሰኔ 29 ቀን 2003 ዓ/ም በተጠሪዎች መካከል የቀረበውን የእርቅ ስምምነት ተቀብሎ ያፀደቀበት ውሳኔ የአመልካች መብትና ጥቅም የነካ ስለመሆኑ ላያመለክት የሚችል የክርክር መነሻ በአሁን አመልካች በኩል የቀረበ ስለሆነ በፍ/ብ/ሥ/ሥ/ሕ/ቁ 358 በተመለከተው ድንጋጌ መሰረት ፍ/ቤቱ በውሳኔ የዘጋውን መዝገብ በማንቀሳቀስ ጉዳዩን የአሁን አመልካች ባለበት እንደገና በማየት በጉዳዩ ላይ ተገቢውን ዳኝነት ይሰጥበት ዘንድ በፍ/ብ/ሥ/ሥ/ሕ/ቁ 341 መሰረት ወደ መጀመሪያ ደረጃ ፍ/ቤት ይመለስ ብለናል።
በዚህ የሰበር ሰሚ ችሎት የተደረገው ክርክር ላስከተለው ወጭና ኪሳራ ግራ ቀኙ የየራሳቸውን ይቻሉ።