No summary available.
መስከረም 24 ቀን 2006 ዓ.ም ዳኞች፡- ተገኔ ጌታነህ አልማው ወል ዓላ መሐመድ ረታ ቶሎሳ ሙስጠፋ አህመድ አመልካች፡- ሣባ ኢንጂንሪግ ኃ.የተ.የግል ማህበር ጠበቃ ምስጋናው ካሴ ቀረቡ ተጠሪ፡- የፕራይቬታይዜሽንና የመንግስት ልማት ድርጅቶች ተቆጣጣሪ ኤጂንሲ ነ/ፈጅ መስፍን በሻህ ቀረቡ **
መዝገቡ ተመርምሮ ተከታዩ ፍርድ ተሰጥቷል።
**
ይህ የሰበር አቤቱታ ላቀርብ የቻለው አመልካች በሽያጭ ውል መሰረት ለተጠሪ ላከፍል የሚገባውን ቀሪ የሽያጭ ገንዘብና የተጣራ ትርፍ ክፍያ እንዲከፍል ተጠሪ በፍድራል ከፍተኛ ፍ/ቤት በአመልካች ላይ ክስ መሥርቶ ፍ/ቤቱም ግራ ቀኙን አከራክሮ አመልካችን ለክሱ ኃላፊ በማድረግ ለክሱ መሰረት የሆነውን ገንዘብ ላከፍል ይገባል በማለት ውሣኔ በመስጠቱና የፍድራል ጠቅላይ ፍ/ቤት ይግባኝ ሰሚ ችሎትም ይሄው ውሣኔ ጉድለት የለበትም በማለቱ መሰረታዊ የሕግ ስህተት ተፈጽሟል በማለት አመልካች ቅሬታ በማቅረቡ ነው።
የጉዳዩ አመጣጥም ባጭሩ ሲታይ ተጠሪ በአመልካች ላይ በፍድራል ከፍ/ቤት ባቀረበው ክስ የቦል ቡልቡላ ጠጠር ማምረቻ አክሲዩን ማህበርን ለመሸጥ ባወጣው የጨረታ ማስታወቂያ መሰረት ከተወዳዳሪዎች መካከል አመልካች የአክሲዩን ማህበሩን ሙሉ ድርሻ ለመግዛት ባቀረበው ዋጋና ቢዝነስ ፕላን መሰረት አሸናፊ በመሆኑ ሀምል 08 ቀን 1999 ዓ/ም በተፈረመ የሸያጭ ውል በብር 17,020,570.00 ለመግዛት ስምምነት ማድረጉን፣የሽያጭ ውሉ አንቀጽ 4(2) መሻሻል በማስፈለጉ ጥር 12 ቀን 2002 ዓ/ም ማሻሻያ የተደረገለት መሆኑን፣በዚሁ መሰረትም አመልካች የሽያጩን ጠቅላላ ዋጋ 35% ብር 5,957,060.00 ከፍሎ ቀሪውን 65% የሽያጭ ዋጋ ደግሞ በየዓመቱ በእኩል ክፍያ ወለድን ጨምሮ አመልካች ለተጠሪ እየከፈለ ሐምል 08 ቀን 2004 ዓም ድረስ ለማጠናቀቅ ስምምነት መደረጉን፣ክሱ እስከቀረበበት ሰኔ 17 ቀን 2003 ዓ/ም እና እስከ ሚያዚያ 30 ቀን 2003 ዓ/ም ድረስ መክፈል የነበረበትና ያልተከፈለ የሽያጭ ቀሪ ገንዘብ ብር 5,129,494.00፣ወለድና ቅጣት ብር 735,637.00 በጠቅላላው ብር 5,865,131.00 እንደሚፈልግበት፣በሽያጭ ውሉ አንቀጽ 6(2) መሰረት ከሐምል 1 ቀን 1998 ዓ/ም ጀምሮ ርክክቡ እስከተጠናቀቀበት እለት ድረስ ያለውን የተጣራ ትርፍ አመልካች ለተጠሪ መክፈል ያለበት መሆኑ በግራ ቀኙ ስምምነት የተደረገበት መሆኑና አመልካች ያልከፈለው ብር 2,821,490.00 ሁኖ ይህም አክሲዩን ማህበር ላይ የተመሰከረላቸው የሂሳብ አዋቂዎችና ኦዲተሮች ያረጋገጡት የሂሳብ መጠን መሆኑን፣ተጠሪ ገንዘቡ እንዲከፈለው በተለያዩ ጊዜአት ለአመልካች ማስጠንቀቂያና ማሳሳቢያ ቢልክለትም አመልካች የተለያየና አጥጋቢ ያልሆነ ምክንያት እያቀረበ ለመክፈል ፈቃደኛ ያለመሆኑን ዘርዝሮ ከዋናው የሽያጭ ገንዘብ ቀሪ እና የተጣራ ትርፍ ክፍያ በጠቅላላው ብር 8,686,621.00 (ስምንት ሚላዩን ስድስት መቶ ሰማንያ ስድስት ሺ ስድስት መቶ ሃያ አንድ ብር) እና በውሉ ላይ የተመለከተውን ወለድ(7.5%) ገንዘቡን ከፍሎ እስከሚያጠናቅቅበት ጊዜ ድረስ ታስቦ አመልካች እንዲከፍል ይወሰንለት ዘንድ ዳኝነት መጠየቁን የሚያሳይ ነው።
የተጠሪ ክስና ማስረጃ ለአመልካች ደርሶ በሰጠው መልስ የሽያጭ ውሉ መኖሩና 35% መክፈሉን፣ እንዲሁም ቀሪው 65% የሽያጭ ገንዘብ ተከፍሎ የሚጠናቀቅበት ጊዜ ሐምል 08 ቀን 2004 ዓ/ም መሆኑን ሳይክድ ክሱ በውሉ የተመለከተው የጊዜ ገድብ ሳያልቅ የቀረበ በመሆኑ ተቀባይነት የለውም፣አመልካች ድርጅት የገባውን ውል ግድታ የሚያፈረስ አንዳችም ጥፋት ያለመፈጸሙን፣ለመክፍል እምቢተኛ ያለመሆኑን፣ማስጠንቀቂያ ተሰጥቶት አለመክፈሉም እንደ እምቢተኛ ያስቆጥረዋል የሚባል ከሆነም በተለያየ ጊዜ የተከሰተውን የተፈጥሮና ሰው ሰራሽ ችግሮች አስመልክቶ የተሰጡት የጽሁፍ መልሶችና ማስረጃዎች መቅረባቸውን፣የማሻሻያ ውሉም የመክፍያ ጊዜ ገደቡን ያልነካው መሆኑን፣የመጀመሪያ ውል ከተደረገ በኋላ በየዓመቱ እኩል ክፍያ የሚል ሐረግ ተጠሪ በማስገባት ውሉ እንዲሻሻል ያደረገው አመልካች ያጋጠመውን የኤልክትሪክ ኃይል መቋረጥና በፈረቃ ሥራ እንዲሰራ የመደረጉን ሁኔታ ያላገናዘበና በወቅቱ በተፈጠረው ሰው ሰራሽና የተፈጥሮ ችግሮች ምክንያት ጥያቄዎችን ለተጠሪ ሲያቀርብ ውሉ ተሻሻለ እንጂ ቀደም ሲል የነበረውን ውል በየዓመቱ በእኩል ክፍያ ትከፍላለህ የሚል ስምምነት ያለመደረጉን፣አመልካች በኤልክትሪክ ኃይል እጥረት ለሁለት አመታት ያህል ማምረቱን ማቆሙን፣ለ150 ሰራተኞች ደመወዝ ከብር 200,000.00 በላይ መከፍሉንና ይህንን ችግር ለተጠሪ ማሳወቁን፣በዚህም መሰረት ውይይት ተደርጎ የሽያጭ ዋጋና ወለዱ በረዥም ጊዜ ክፍያ ተከፍሎ እንዲያልቅ በውሉ ላይ የተቀመጠው ቅጣት ደግሞ እንደማይከፈልና እንደሚነሳ የድርጅቶቹን ሕልውናና የሰራተኞችን ቀጣይ ሕይወት ለመታደግ ሲባል ስምምነት ላይ የተደረሰና በኤጂንሲው ቦርድም እንዲጸድቀና ተቀባይነት እንዲያገኝ መደረጉን፣አመልካች ድርጅት ከሚፈልግበት እዳ ላይ በቅድሚያ ብር 5,957,060.00 እና በተለያዩ ሰነዶች የተከፈለ ብር 3,732,622.00 በአጠቃላይ ብር 9,689,682.00 ከነትርፍ ድርሻው የመክፍያውን የጊዜ ገደብ ሳይጠብቅ መከፈሉን፣ተጠሪ ከሚያዚያ 30 ቀን 2003 ዓ/ም በኋላ ያለውን እንዳልፈለገው ተቆጥሮ እዳው ከመክፈል ቀሪ ይሆናል ስለሚል ሕጉ ተጠሪ መስሪያ ቤት የጠየቀው ወደፊት የመክሰስ መብት በሕግ ተቀባይነት የልለው መሆኑን፣አመልካች የጠጠር ማምረቻ ቦታ ሚያዚያ 03 ቀን እና ሚያዚያ 26 ቀን 2003 ከቦል ክፍል ከተማ አስተዳደር የወረዳ 12 ዋና ስራ አስኪያጅ ፅ/ቤት በተፃፈ ደብዳቤ ቦታውን እንዲለቅ በመደረጉ ድርጅቱ ስራውን ማቆሙንና ይህም ከአቅም በላይ የሆነ ምክንያት መሆኑን ዘርዝሮ የተጠሪ ክስ ውድቅ ላሆን ይገባል በማለት ተከራክሯል።
የግራ ቀኙ ክርክር በዚህ መልኩ የቀረበለትም የፍድራል ከ/ፍ/ቤትም ጉዳዩን መርምሮ አመልካች በውሉ መሰረት ለክሱ ኃላፊነት ያለበት መሆኑን፣የኤልክትሪክ መቋረጥም ሆነ የቦታው ለሕዝብ ጥቅም ሲባል መወሰድ የውል ግድታውን ለመፈፀም የማያስችሉ ከአቅም በላይ የሆኑ ምክንያቶች ናቸው ላባሉ የማይችሉ መሆኑን በምክንያትነት ይዞ በዚህ ረገድ የቀረበውን የአመልካችን ክርክርም ውድቅ ያደረገው ሲሆን አመልካች በሽያጭ ውሉ መሰረት ላከፈለው የሚገባውን ቀሪ ገንዘብ እስከ ሚያዚያ 30 ቀን 2003 ዓ/ም ድረስ መክፈል የነበረበትን ብር 5,129,494.00፣በመጀመሪያው ውልና በተሻሻለው ውል መሰረት መክፈል የነበረበትን ገንዘብ ባለመክፈሉ በውሉ አንቀጽ 8(3) መሰረት ቅጣት ብር 735,637.00፣ በዋናው ውል አንቀጽ 6(2) መሰረት ከሐምል 1ቀን 1998 ዓ/ም ጀምሮ ርክክቡ እስከተጠናቀቀበት እለት ድረስ ያለውን የተጣራ ትርፍ ብር 2,821,490.00፣በውሉ አንቀጽ 4(4) መሰረት ደግሞ ላልተከፈለው ቀሪ የሽያጭ ገንዘብ ለተጣራ ትርፍ ክፍያ ወለድ ብር 7.5% ተከፍሎ እስኪጠናቀቅ ድረስ ያለውን አመልካች ለተጠሪ እንዲከፍል ሲል ወስኗል።በዚህ ውሳኔ የአሁኑ አመልካች ቅር በመሰኘት ይግባኙን ለፍድራሉ ጠቅላይ ፍርድ ቤት ይግባኝ ሰሚ ችሎት ያቀረበ ቢሆንም ይግባኙ በፍ/ብ/ሥ/ሥ/ሕ/ቁጥር 337 መሰረት ተሰርዞበታል።
የአሁኑ የሰበር አቤቱታ የቀረበውም ይህንኑ ውሳኔ በመቃወም ለማስለወጥ ነው።የአመልካች የሰበር አቤቱታ መሰረታዊ ይዘትም ተጠሪ በውሉ የተመለከተው የመክፈያ ጊዜ ሳይጠናቀቅና ውሉ የተሻሸለ መሆኑን የሚያሳይ ማስረጃ በፍርድ ቤቱ እገዛ እንዲቀርብ ተጠይቆ ማስረጃው ሳይቀርብ መቅረቱ እንዲሁም የውል ግድታውን አመልካች ከኤልክትሪክ ኃይል መቋረጥና ተጠሪ የሸጠው የጠጠር ማምረቻ ድርጅት ያለበትን ቦታ መንግስት ለኮንዶሚኒየም መስሪያ በመፈለጉ በአስቸኳይ ቦታው እንዲለቀቅ ተጠይቆ ቦታውን አመልካች በመልቀቅ ስራውን ያቆመ መሆኑ የውል ግድታውን ለመወጣት የማያስችሉ ምክንያቶች ሁነው እያለ የበታች ፍርድ ቤቶች ሁኔታዎቹ ስለመፈጠራቸው እንኳ በአግባቡ ሳይመረምሩ ማለፋቸው ያላግባብ ነው የሚል ነው።አቤቱታው ተመርምሮም በዚህ ሰበር ሰሚ ችሎት እንዲታይ በመደረጉ ለተጠሪ ጥሪ ተደርጎለት ቀርቦ ግራ ቀኙ በፅሑፍ እንዲከራከሩ ተደርጓል።
የጉዳዩ አመጣጥ አጠር አጠር ባለመልኩ ከላይ የተገለፀው ሲሆን ይህ ችሎትም የግራ ቀኙን ክርክር ለሰበር አቤቱታው መነሻ ከሆነው ውሳኔ እና አግባብነት ካላቸው ድንጋጌዎች ጋር በማገናዘብ ጉዳዩን በሚከተለው መልኩ መርምሮታል።እንደመረመረውም የዚህን ችሎት ምላሽ የሚያስፈልገው አቢይ ነጥብ በጉዳዩ ላይ በተሰጠው ውሳኔ መሰረታዊ የሆነ የሕግ ስህተት ተፈጽሟል ለማለት ይቻላል? ወይስ አይቻልም? የሚለው ሁኖ ተገኝቷል።ይህንኑ ጭብጥ ለመመለስ ይቻል ዘንድም በአመልካች የቀረቡትን መሰረታዊ የቅሬታ ነጥቦች አንድ ባንድ መመልከቱ ተገቢ በመሆኑ እንደሚከተለው መርምረናል።
አመልካች አጥብቆ ከሚከራከርባቸው መሰረታዊ ነጥቦች አንዱ ስለውሉ መሻሻል እንደሚያስረዳ ተገልፆ በፍርድ ቤት እገዛ እንዲቀርብ የተጠየቀው ማስረጃ በስር ፍርድ ቤት ሳይቀርብ ውሳኔ መሰጠቱ ያላግባብ ነው የሚል ይገኝበታል።አመልካች ይህ ማስረጃ ቃለ ጉባኤ ስለመሆኑ ጠቅሶ ማስረጃው ቢቀርብ የሚያስረዳው አመልካቹ ከወለድና ከቅጣት ነጻ መሆኑን ስለመሆኑ የገለፀ ሲሆን ተጠሪ በበኩሉ በተጠሪ እጅ የሚገኘው ቃለ ጉባኤ ለማስረጃነት መቅረቡን፣ወለድና ቅጣትንም ነፃ ለማድረግ ስምምነት የልለ መሆኑን ጠቅሶ መልሱን ሰጥቷል።
በመሰረቱ ከሳሽ ክሱን ሲያቀርብ አስፈላጊ ማስረጃዎችን በሙሉ አጠቃሎ ማቅረብ ላያቀርባቸው የማይችላቸውን ደግሞ በፍ/ሥ/ሥ/ሕ/ቁ 145 መሰረት በፍ/ቤቱ እገዛ እንዲቀርቡለት መጠየቅ የሚችል መሆኑን በፍትሐ ብሕር ስነ ስርዓት ሕጉ ስር የተደነገጉት የማስረጃ አቀራረብ ደንቦች ያሳያሉ።ይህ የማስረጃ አቀራረብ ስርዓት ለተከሳሽም የሚሰራ ስለመሆኑ ከፍ/ብ/ሥ/ሥ/ሕ/ቁጥር 234(1) ድንጋጌ ይዘት የምንረዳው ጉዳይ ነው።በመሆኑም ከሳሹ ወይም ተከሳሹ ላያቀርባቸው ሲችል ሆነ ብሎ ወይም በቸልተኛነት ያላቀረባቸውን ማስረጃዎች በክርክር ሂደት ሁሉ እያንጠባጠበ ላያቀርብ ወይም የማስረጃ ማሰባሰብ ስራውን ፍርድ ቤት እንዲያከናውን ላጠይቅ የሚችልበት የማስረጃ አቀራረብ ስርዓት የልለ ሲሆን ከሥነ ስርዓት ህጉ አላማ ጋርም አብሮ የማይሄድ ጉዳይ በመሆኑ ሕጉ የሚፈቅደው አካሄድ አይደለም።በፍርድ ቤት እገዛ ማስረጃ የሚቀርበው ተከራካሪ ወገን አጠቃልሎ ማቅረብ የማይችላቸው መሆኑ በቅድሚያ ሲረጋገጥ ነው። ከዚህም በተጨማሪ በፍርድ ቤት ማስረጃ እንዲቀርብ ጥያቄ ሲቀርብ ፍርድ ቤቱ ማስረጃው ለጉዳዩ ያለውን አግባብነትም በመመልከት ተገቢውን ትዕዛዝ መስጠት የሚችል መሆኑን ከማስረጃ አቀራረብ ደንቦች ይዘትና መንፈስ የምንረዳው ጉዳይ ነው።ከዚህ አንጻር ጉዳዩን ስንመለከተው አመልካች አልቀረበልኝም የሚለው ማስረጃ ስለመቅረቡ ተጠሪ የገለፀ ከመሆኑም በላይ አለ የተባለው ማስረጃ ደግሞ ቃለ ጉባኤ ሁኖ በወለድና በቅጣት ኃላፊነት ላይ በይዘቱ ከዋናው ውልና ጥቅምት 12 ቀን 2002 ዓ/ም ተደረገ ከተባለው የማሻሻያ ውል የተለየ መሆኑን አመልካች ጠቅሶ የሚከራከር በመሆኑ አመልካች የውሉ ቅጂ የራሱን ድርሻ ከተጠሪ ሳይወስድና ሳይኖረው የሚቀርበት ሕጋዊ ምክንያትና አግባብ ይኖራል ተብሎ ስለማይታሰብ ማስረጃውን ራሱ ማቅረብ ይገባው የነበረ ከመሆኑም በላይ ሰነዱ ቃለ ጉባኤ ብቻ ነው ከተባለ ደግሞ በፅሑፍ የተደረገውን ውል ማሻሻል የሚቻለው የመጀመሪያው ውል በተደረገበት የጽሑፍ አግባብ ስለመሆኑ የፍ/ብ/ሕ/ቁጥር 1722(1) ድንጋጌ የሚያስገነዘበን ጉዳይ በመሆኑ ማስረጃው ቢቀርብም በሕግ ፊት ዋጋ የሚሰጠው ነበር ለማለት የሚቻል ሁኖ አልተገኘም።ስለሆነም አመልካች ማስረጃውን ለማቅረብ የማይችል የነበረ ስለመሆኑ ባልተረጋገጠበትና ማስረጃውም በሕጉ አግባብ ውሉ መሻሻሉን የሚያሳይ ሳይሆን ቃለ ጉባኤ መሆኑን ጠቅሶ በሚከራከርበት አግባብ የማስረጃ ማቅረብ መብቱ ሳይጠበቅ ውሳኔ እንደተሰጠ አድርጎ የሚያቀርበው ቅሬታ ተቀባይነት የሚሰጠው ሁኖ አልተገኘም።
ልላው አመልካች አጥብቆ የሚከራከርበት ነጥብ በውሉ የተመለከተው የመክፈያ ጊዜ ከመድረሱ በፊት ክስ መቅረቡ ያላግባብ ነው በሚል ምክንያት ነው።በእርግጥ አንድ ተዋዋይ በውሉ የተመለከተውን ግድታ እንዲወጣ የሚጠየቀው በውሉ በተመለከተው የክፍያ የጊዜ ገደብ ግድታውን ሳይወጣ መቅረቱ ሲረጋገጥ መሆኑ ከፍ/ብ/ሕ/ቁጥር 1731(1)፣1740፣1756፣1846 እና ከልሎች ድንጋጌዎች ይዘትና መንፈስ የምንገነዘበው ጉዳይ ነው።
በተያዘው ጉዳይም የሽያጭ ገንዘቡን አመልካች ከፍሎ ለማጠናቀቅ በውሉ ተቆርጦ የተቀመጠው የጊዜ ገደብ ሐምል 08 ቀን 2004 ዓ/ም መሆኑ በፍሬ ነገር ደረጃ የተረጋገጠ ጉዳይ ነው። ይህ ጊዜ በሕጉ አግባብ ተሻሽሐል የሚል ክርክር አመልካች የልለው መሆኑን የክርክሩ ሂደት ያሳያል።እንግዲህ በውሉ የተመለከተው የገንዘቡ መክፍያ ጊዜ ሐምል 08 ቀን 2004 ዓ/ም ሁኖ እያለ ተጠሪ አመልካች ግድታውን አልተወጣም በሚል ክስ ያቀረበው ሰኔ 17 ቀን 2003 ዓ/ም፤በውሉ ከተመለከተው ጊዜ ቀድሞ ነው።ይህ ተገቢ ያልነበረ መሆኑን ይህ ችሎት የሚቀበለው ጉዳይ ነው።ይሁን እንጂ አሁን የሥር ፍርድ ቤት ውሳኔ እስከሰጠበት እስከ ሐምል 13 ቀን 2004 ዓ/ም ድረስም ሆነ ክርክሩ እስከዚህ ሰበር ሰሚ ችሎት ደርሶ ባለበት ሁኔታ በውሉ የተመለከተው የሽያጭ ገንዘቡን ከፍሎ የማጠናቀቂያ የጊዜ ገደብ አልፎ ከአንድ ዓመት በላይ ተጨማሪ ጊዜ ማለፉን የክርክሩ ሂደት የሚያስገነዝበን ፍሬ ነገር ነው።በመሆኑም በውሉ የተመለከተው የጊዜ ገደብ አልደረሰም የሚለው የአመልካች የክርክር ነጥብ በስር ፍርድ ቤት ውሳኔ ሲሰጥም ሆነ ባሁኑ ጊዜ ቀሪ የሆነ በመሆኑና በእነዚህ ጊዜያት ውስጥ ደግሞ አመልካች ግድታውን የተወጣ መሆኑን ወይም እየተወጣ የሚገኝ መሆኑ ገልፆ ያቀረበው ክርክር ስለልለ በፍ/ብ/ሥ/ሥ/ሕ/ቁጥር 280 አግባብ የገንዘቡ መክፍያ ጊዜ አልደረሰም የሚለው መከራከሪያ ነጥብ የክርክሩ ምክንያት ላሆን የሚችል ሁኖ አልተገኘም።ስለሆነም በዚህ ረገድ የቀረበው የአመልካች መከራከሪያ ነጥብም ተቀባይነት ላሰጠው የሚገባው ሁኖ አልተገኘም።
ልላው አመልካች የሚከራከርበት ነጥብ የኤልክትሪክ ኃይል መቋረጥና ከተጠሪ የገዛው የጠጠር ማምረቻው ድርጅት የነበረበት ቦታ ለኮንዶሚኒየም መስሪያ በመንግስት መወሰዱ ግድታውን ለመወጣት የማያስችሉ ከአቅም በላይ የሆኑ ምክንያቶች ናቸው ተብሎ የቀረበው ክርክር በስር ፍርድ ቤቶች የታለፈው ከአቅም በላይ የሆነ ምክንያት መፈጠር አለመፈጠሩ እንኳ በአግባቡ ሳይመረመርና ቦታውን አመልካች እንዲለቅ ያደረገው የቦል ክፍለ ከተማ መሬት ልማት ባንክና ከተማ ማደስ ፕሮጀክት ጽ/ቤት ወደ ክርክሩ ጣልቃ እንዲገባ ሳይደረግ ነው የሚል ነው።
እኛም ጉዳዩን እንደተመለከትነው የኤልክትሪክ ኃይል እጥረት የነበረ መሆኑና ድርጅቱ የነበረበት ቦታ ለኮንዶሚኒየም መስሪያ ተፈልጎ በአስቸኳይ እንዲለቀቅ ሚያዚያ 03 እና 16 ቀን 2003 ዓ/ም በሚመለከተው የመንግስት አካል ለአመልካች ደብዳቤ መፃፉ በፍሬ ነገር ደረጃ የተረጋገጠ ሲሆን የኤልክትሪክ ኃይል እጥረቱ ግን አመልካችን ድርጅቱን ከተጠሪ ከተረከበበት ጊዜ ጀምሮ ክስ እስከ ቀረበበት ጊዜ ድረስ ሙሉ በሙሉ እንዳይጠቀም ያደረገው ስለመሆኑ ተገልጾ በአመልካች ክርክር ያልቀረበበት ከመሆኑም በላይ የስር ፍርድ ቤት ችግሩ ከአቅም በላይ የሆነ ምክንያት ነው ለማለት የማያስችል ነው በማለት ውድቅ ያደረገው መሆኑን ተገንዝበናል።ስለዚህ የሥር ፍርድ ቤት በዚህ ረገድ የቀረበውን የአመልካችን ክርክር በአግባቡ ሳይመረመር አልፏል የሚለው የአመልካች ቅሬታ የስር ፍርድ ቤትን የውሳኔ ይዘት ያላገናዘበ በመሆኑ እውነት የልለው ነው።ስለሆነም በሕግ ጭብጥነት መታየት ያለበት የኤልክትሪክ ኃይል እጥረት ከአቅም በላይ የሆነ ምክንያት ነው ተብሎ ላወሰድ ይችላል? ወይስ አይችልም? የሚለው ነው።
በዚህ መሰረትም ከአቅም በላይ የሆነ ሁኔታ አለ ለማለት የሚቻለው መቼ እንደሆነ በፍ/ብ/ሕ/ቁ.1792 ላይ የተመለከተ ሲሆን ይህም ድንጋጌ ከአቅም በላይ የሆነ ላመልሱት የማይቻል ኃይል ደርሷል የሚባለው ባለአዳው ባላሰበው ነገር ድንገት ደራሽ ሆኖበት ግድታውን እንዳይፈጽም ፍፁም መሰናክል በሆነ አይነት የሚደግፈው ነገር ባጋጠመ ጊዜ እንደሆነ ተደንግጓል። በዚሁ አንቀጽ ንዑስ ቁጥር 2 ላይ ደግሞ በአእምሮ ግምት ባለአዳው ቀደም ብሎ ላያስብበት የሚችል መሆኑ የታወቀ አንድ ድንገተኛ ደራሽ ነገር ወይም ለውሉ አፈፃፀም ከባድ የሆነ ወጭ በባለአዳው የሚደርስበት ቢሆን ከአቅም በላይ የሆነ ኃይል ነው ተብሎ እንደማይገመት ተመልክቷል።
በመሆኑም በእነዚህ የሕጉ ድንጋጌዎች መሰረት ከአቅም በላይ የሆነ ሁኔታ ተከስቷል ላባል የሚችለው ባለእዳው በምንም መልኩ በቅድሚያ ላያስበው ወይም ላገምተው የማይችል ክስተት ሲፈጠር ነው። ነገር ግን ባለአዳው ሁኔታው ላፈጠር ወይም ላከሰት እንደሚችል ቀድሞ ላገመት ወይም ላያስብና ጥንቃቄ ላያደረግበት የሚችል ከሆነ ሁኔታው ድንገተኛ ደራሽ ነገር ቢሆን እንኳን ከአቅም በላይ የሆነ ነገር ተብሎ እንደማይገመት መገንዘብ ይቻላል።
ወደተያዘው ጉዳይ ስንመለስም የሥር ፍ/ቤቶች አመልካችን ለክሱ ኃላፊ ያደረጉት የክሱ ምክንያት የሆነውን እዳ ለመክፈል የኤልክትሪክ ኃይል እጥረት ከአቅም በላይ የሆነ ምክንያት ነው ተብሎ የሚወሰድ አይደለም በማለት ነው።በመሆኑም አመልካች የገዛው ድርጅት የጠጠር ማምረቻ እና ይህንኑ ስራ የሚሰራውም በኤልክትሪክ ኃይል መሆኑ ቀድሞ የሚታወቅ ሲሆን ለስራው ቀጣይነት የኤልክትሪክ ኃይል አስተማማኝ መሆኑን ለሥራ በሚሰማራበት ጊዜም ሆነ በወቅቱ በአገሪቱ ካለው ተጨባጭ ሁኔታ አጣርቶ የክፍያ ምንጩ የድርጅቱ ስራና በስራው የሚገኘው ገቢ ከመሆኑ ጋር አገናዝቦ የክፍያ ጊዜውን በተመለከተ ከተጠሪ ጋር ስምምነት ላያደርግበት ይችል የነበረ መሆኑ የሚታመን ከመሆኑም በላይ በዚህ ረገድ አስፈላጊውን ጥንቃቄ አድርጎ ግዢውን ከፈፀመ በኋላም ተገቢውን ጥንቃቄ ማድረግ የሚችልበት ጉዳይ ነው። ይህንን ሣያደርግ ቀርቶ ጉዳት ቢደርስ እንደሕጉ አነጋገርና መንፈስ ከአቅም በላይ የሆነ ሁኔታ ላባል አይችልም። ስለሆነም አመልካች ከላይ እንደተመለከተው በድርጅቱ ግዢ ወቅትም ሆነ ከግዢ በኋላ የኃይል ችግር እንዳይደርስበት አስቀድሞ ላገምተውና ላከላከለው ሲገባ ይህንን የመከላከልና የጥንቃቄ ዕርምጃ አስቀድሞ ሣይወስድ በመቅረቱ እዳውን ለመክፈል ያልቻለው ከአቅም በላይ በሆነ ምክንያት ነው ላባል የሚችል ሁኖ አልተገኘም።በተጨማሪም አመልካች ስራውን በፈረቃ ይሰራ የነበረ መሆኑን በክርክሩ ሂደት የገለፀ በመሆኑ ፍጹም በሆነ መሰናክል ውስጥ ነበር ለማለት የሚቻልበት አግባብ የለም።
ልላው ከአቅም በላይ ምክንያት ጋር አያይዞ አመልካች የሚያነሳው ነጥብ በግዥ ያገኘው ድርጅት ያለበት ቦታ ለኮንዶሚኒየም መስሪያ የመንግስት አካል ተረክቦታል የሚለው ነው።በእርግጥ ቦታው እንዲለቀቅ ሚያዚያ 03 እና 16 ቀን 2003 ዓ/ም የተጻፉ ደብዳቤዎች የሚያሳዩና ተጠሪም ያልካደው ፍሬ ጉዳይ ሲሆን አመልካች የጠጠር ማምረቻ ስራውን የሚሰራበት ምትክ ቦታ የተሰጠውና ስራውንም እየሰራ የሚገኝ መሆኑንና ተገቢውን ካሳም አመልካች እንዲያገኝ ተጠሪ የበኩሉን ስለማድረጉ ገልጾ በሰጠው መልስ ግን አመልካች የማስተባበያ ክርክር አላቀረበበትም።ይህም በፍ/ብ/ሥ/ሥ/ሕ/ቁጥር 235 እና 83 ድንጋጌዎች መሰረት የሚያሳየው አመልካች የገዛው ድርጅት እስከ ሚያዚያ 16 ቀን 2003 ዓ/ም በቦታው የነበረ መሆኑንና በምትክም ልላ ቦታ አመልካች ወስዶ ስራውን የቀጠለ መሆኑን አመልካች በግልጽ ያልካደው፣ይልቁንም እንዳመነ የሚቆጠር ፍሬ ነገር መሆኑን ነው።እንዲህ ከሆነ ይህ ምክንያት በፍ/ብ/ሕ/ቁጥር 1791,1792 እና 1793 (ሀ) እና (ለ) ድንጋጌዎች አግባብ ከአቅም በላይ የሆነ ምክንያት ነው ብሎ ለመወስድ የሚቻልበት አግባብ የልለ መሆኑን የሚያስገነዘበን ነው።ቦታው እንዲወሰድ ትዕዛዝ ያስተላለፈው አካልም የክርክሩ ተካፋይ በመሆን የሚያስጠብቀው መብት ወይም ጥቅም እንዲሁም እንዲወጣ የሚገደድበት ግድታ የልለ በመሆኑ የክርክሩ ተካፋይ ሳይሆን ውሳኔ ተሰጥቷል የሚለው የአመልካች ክርክር የፍ/ብ/ሥ/ሥ/ሕ/ቁጥር 39 እና 40 ድንጋጌዎችን ይዘትና መንፈስ ያላገናዘበ በመሆኑ ተቀባይነት የልለው ሁኖ አግኝተናል።
ሲጠቃለልም አመልካች በሕጉ አግባብ ማቅረብ የሚችለውን ማስረጃ ማቅረቡ ስለተረጋገጠና ያለፍርድ ቤት እገዛ ደግሞ ማስረጃውን ማቅረብ የማይችል መሆኑ ያልተረጋጠ በመሆኑ፣የእዳው መክፍያ ጊዜም በክርክሩ ሂደት የደረሰና አመልካችም ግድታውን ያልተወጣ መሆኑ የተረጋገጠ በመሆኑ እንዲሁም ግድታውን ለመፈፀም ከአቅም በላይ የሆኑ ምክንያቶች ተከስተዋል ለማለት የሚቻል ባለመሆኑ የበታች ፍርድ ቤቶች አመልካችን ለክሱ ኃላፊ በማድረግ የሰጡት ውሳኔ ውጤቱ ሲታይ መሰረታዊ የሆነ የሕግ ስህተት ያለበት ነው ለማለት ስላልተቻለ ተከታዩን ወስነናል።
ው ሣ ኔ
82501 በ17/03/2005 ዓ.ም በትዕዛዝ የፀናው ውሳኔ ውጤቱ ሲታይ መሰረታዊ የሆነ የሕግ ስህተት የልለበት በመሆኑ በፍ/ብ/ሕ/ሥ/ሥ/ቁ. 348/1/ መሰረት ጸንቷል።
በዚህ ችሎት መጋቢት 25 ቀን 2005 ዓ/ም የተሰጠው እግድ ተነስቷል።ይጻፍ።
No topics extracted.